May 11, 2019
6 mins read

ሀገሬ ናፈቀኝ / ከግርማ ቢረጋ

ሃገሬ ናፈቀኝ ወንዟ ሸንተረሯ

ናፈቀኝ ሃገሬ ነፃነቷ ክብሯ

ትዝታ ኑሮዋ ባህል ቁም ነገሯ ።

 

ያሳለፍኩት ሁሉ እየመጣ በእውኔ

እንቅልፌንም ነሳኝ ተሰማኝ ኩነኔ ።

 

መንደሬ ሰፈሬ አስፋልት ኮረኮንጁ

ቂማውና ጨብሲው > ጠላውና ጠጁ ።

 

ከረንቦላው ኳሱ ድራፍት ካቲካላው

ብትለው ብትጠጣው ሆድን የማይሞላው።

 

ጣፋጭ ትዝታዋ ሃገሬ ናፈቀኝ

እራቀኝ ሄደብኝ ከቶውን ላይገኝ ።

 

ከቤላ ፈረንሳይ ስድስት ኪሎ ሄጄ

ጭንቀት ሳይኖርብኝ ሽቅብ ታች ወርጄ።

 

 

የኖርኩበት ዘመን ላይገኝ መልሶ

ሊታለፍ የማይችል ፍፁም ተደባብሶ ።

 

 

ሃገሬ ናፈቀኝ ሰላምሽ ትዝታሽ

ቀድሞ የነበረው ወዘና ቁመናሽ ።

 

ከቶ ይናፍቀኛል እንዴት ልሁን ታዲያ

አልፈልግም ልትሆኝ ብቻ መቀበሪያ ።

 

 

ስደት የተባለ ወረርሽኝ ውጦኝ

ከሰፈር ቀበሌ ከጓደኛ አርቆኝ ።

 

ሃገሬ ናፈቀኝ ሆድ ባሰኝ ዘንድሮ

የማይወጣ ነገር ልቤ ውስጥ ተቀብሮ ።

 

ጭራሽ አይረሳም ፈረንሣይም ቤላ

ፍቅር የሞላበት ያደግኩበት ሁላ ።

 

ዜሮ አምስት ውቅያኖስ ቀጭ ቀጭ ሃሰን ሱቅ

በቡዜ ቀብራራው የነበረንን ሳቅ

እንዴትስ ይረሳል ለምንስ አይናፍቅ ።

 

ጃልሜዳ ወጥቼ ቅሜ ተጫውቼ

ጨፋናው ቴዲዬን ሃረሩን አግኝቼ

በቁኮ እና ለጌ ሻለቃን አውርቼ ።

 

የሽፌ ጨዋታ ጌቾ ትህትናው

የፈረንጅ አፉ የቋንቋ ችሎታው

ወልድዬ ወላሞ ነብስህን ይማረው ።

 

ሳቅና ጨዋታው ተካፍሎ መብላቱ

ትዝ አለኝ ሃገሬ ትዝ አለኝ የጥንቱ

ሃገሬ ናፍቆቱ ሃገሬ ስስቱ

ርቆ የሄደን  ሰው ወይ  ማሰቃየቱ ።

 

ጃልሜዳ አራት ኪሎ ቶታል ስድስት ኪሎው

የነ አይሰጬ ፈድሉ ሺሰማ ትዝታው

የጊቢው ተማሪ መጥተው ተኮልኩለው ።

 

ጠረባ ትረባው በአረንጓዴ ምላስ

ያ ጊዜ ተገኝቶ ምነው ባይበላስ ።

 

ለመርሳት ብሞክር ዜሮ አምስትን ከልቤ

ጃልሜዳ ጉልትን ላወጣው ከቀልቤ

አልሆንልህ አለኝ መጣ በምናቤ ።

 

ነበረኝ ብዙ ሙድ መገናኝ ገርጂ

ብዙ የሚናፍቀኝ የኖርኩበት ደጅ ።

 

ጉለሌ ጋሽ መጋል ወርቁ ሸክላ ሄጄ

ጳውሎስን አልፌ ኳስ ሜዳ ወርጄ ።

 

ኢዲዩን ጎብኝቼ ስሄድ ዳትሰን ሰፈር

የክትፎውን ጣባ ዮሃንስ ስንሰብር ።

 

 

በቅዳሜ  ጠዋት ሾሌ ነጭ ጠላ በዞረ ጢንቢራ

ጨጓራው ተበልቶ ደልቶን ስናጓራ

ሃገሬ ናፈቀኝ የአራት ኪሎ ቢራ ።

 

ሰብለ ቤት ጨልጬ ሶሎ ቤት ስሸና

ይገቤ አልማዝ ቤት የጆሊ ባር ቡና ።

 

ካሳንቺስ ክትፏችን ከተማ ቤት ቢራ

የመጨረሻዬን ቺርስ ያልኩበት ተራ ።

 

ከወዳጆቼ ጋር የመለየት ለቅሶ

በአረቄና ቢራ ፍፁም ተለውሶ ።

 

ከቶ አይረሳኝም ነብስ ይማር መንግስቱ

ተጫዋች አሳቢ አንተ የኔ ከንቱ ።

 

ተቃቅፈን ተላቅሰን የሸኛችሁኝ ግዜ

ተክሎብኝ የቀረው ሃሳብ ከትካዜ።

 

ሼህ ዑመር ባህሩ ብሬ እና ውዶቹ

ከቶ እንዴት አድርጌ ከልቤ ላውጣችሁ ።

 

አርቆ የሸኘኝ  ላይመልሰኝ ግዜ

ሃገሬ ናፈቀኝ ተጫነኝ ትካዜ።

 

የኤጀርሳ ጎሮ የጎድን ጥብስ ሽታ

የታምራትን ቤት ኡኡታ ጫጫታ ።

 

ትዝ አለኝ ሃገሬ ናፈቀኝ መንደሬ

ስጎነጭ ስጨልጥ ከናፋቂው ወሬ ።

 

ፍፁም አይረሳም የአራት ኪሎ መንገድ

ከሥራ በኋላ ያለው  መንጎራደድ ።

 

በሞት ያጣዋቸው ወዳጅ ዘመዶቼ

ከቶ ላልረሳችሁ በልቼ ጠጥቼ

ከነጫጮቹ ምድር ጠፋሁኝ ሰስቼ ።

 

ጥዬው እንዳልመጣ እሩጬ ፈርጥጬ

የያዘው ይዞኛል ዝቅ  አርጎኝ ከአገጬ ።

 

አይመስለኝም ነበር ልቆይ እንዲህ እርቄ

በሃገር በህዝቤ ሁሌ ተጨንቄ ።

 

ልብ አቅም ሲደክም ሲወርህ እርጅና

ይናፍቃል ቀዬ የሰፈር ጓደኛ ።

 

 

ግና ለምን በኔ ስደት ጨከነሳ

ወይስ እኔ ፈራው አበዛው ወቀሳ ።

 

ሃገሬ ናፈቀኝ ወንዟ ሸንተረሯ

ናፈቀኝ ሃገሬ ነፃነቷ ክብሯ

ትዝታ ኑሮዋ ባህል ቁም ነገሯ ።

 

ሜይ 2019

ግርማ ቢረጋ / ስቶክሆልም

 

Previous Story

የ 2012 ዓ/ም ምርጫ ፣ የሚባል ነገር ካለ፣ ከወዲሁ ፣የበለፀጉትን ሀገሮች በቅንነት ፣ምርጫው እንከን አልባ እንዲሆን አግዙን ማለት ይበጃል

95234
Next Story

ውይይት ጠበቃ ተክለሚካኤል አበበ ከ ዶር ቃልኪዳን ነጋሽ ጋር በወቅታዊ ኢትዮጵያ ሁኔታ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop