[email protected]
በ ሙሉጌታ ገዛኸኝ
ለዛሬው ማኅበራዊ ትችት መነሻየ መሰልጠን በምን ይገለፅ? የጠፋው ሰለጠነ ሰው ወይስ ቴክኖሎጂው? ጥቂት እያነሳን ብንጥል ምን ይለናል?
የሀገራችን ባሕልና ታሪክ ሲዳሰስ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት ከሆኑት እጅግ ጥቂት አገሮች አንዷ መሆኗን ያስረዳል፡፡ የተፈጥሮ ፀጋ የተላበሰችው ኢትዮጵያ በርካታ መስህቦችም አሏት፡፡ በተለይም የሰው ዘር መገኛ፣ የቡና መገኛ፣ የአባይ ወንዝ፣ የግእዝ ቋንቋ መሰረት መነሻ በመሆኗ ቀደምት አፍሪካዊ የግብጽ እና ኑብያ ስልጣኔም ጉልኅ አስተዋፅዖ አበርክታለች። ነፃነቷ ተጠብቆ የኖረችው ሀገራችን ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ወዲህ ውጫዊና ውስጣዊ ውስብስብ ምክንያቶች እንዲሁም በመካከለኛው ዘመን የእርስ በርስ ጦርነት የተነሳ ስልጣኔዋ ቀስ በቀስ እያሽቆለቆለ በውጤቱም በሽታ፣ ችጋር፣ ቸነፈር የመሳሰሉ ሰቆቃዎች መጋለጥ እጣ ፋንታዋ ሆነ፡፡ በአስከፊ ጦርነቶች ምክንያትም ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አዛውንቶች ሰለባ ሆነዋል፡፡ ይብዛም ይነስ ጦርነት ስደትን ያስከትላል፣ በዘመናት የተገነቡ የስልጣኔ አሻራ ከተሞችንም ዶጋመድ አድርጎ የሀገር ሀብትን ድምጥማጡ እያጠፋ እንዲባክን ያደርጋል፡፡
እስከዛሬም ድረስ በዓለም ረሀብና ድርቅ ልዩ ተጠቃሽነት ስሟ መነሳቱም አልቀረም፡፡ በዚህ ላይ የእውቀት እጦት ድንቁርና ታክሎበት ጭራሽ ኋላቀርነትን አስከተለ፡፡ ከነበረችበት የስልጣኔ ጣራ ቁልቁለት መንደርደሩን ተያያዘችው፡፡ የአገዛዞቹ ድክመት በራሱ ምክንያት ሆኖ የሕብረተሰባዊ አስተሳሰብ መላሸቅና ስንፍና የሥራ ባህል ልግመት እንዲሁም በእውቀት ያለመዳበር ዓይነተኛ መንስኤ ነው፡፡ የሰለጠኑ አገሮች የሚጠቀሙበትን የአሰራር እቅድ ዲሲፕሊንና ስልት ቀምሮ ተግባራዊ ያለመሆኑ ብሎም በርካሽ ዋጋ የሚቀርብ ዘመናዊ ማሽን ወደ አገር ውስጥ ያለማስገባትም ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ለምእተ ዓመታት ከተጠናወተን ማነቆ አሁንም በቅጡ ተላቀናል ለማለት ባስደፍርም ከተስፋ መቁረጥ ይልቅ በሥራ ጥረትና እድገት መቀየር እንደሚቻል የሚታዩ ቁጭቶች በዜጎች ዘንድ ከጊዜ ወደ ጊዜ መታየታቸውም አይቀረም፡፡
የሕዝብ ቁጥር ማሻቀብ ብቻም ሳይሆን የከተሞች መስፋፋት ብሎም ከየከተሜነት የህይወት ዘይቤ ጋር በጎም ከፉም ቁርኝት በሰፊው እየተለመደ መጥቷል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሥራ አጥነት፣ የከተሞች መቆርቆዝ፣ የገነገነ ድሃነት፣ ያልተመጣጠነ ፍልሰት ወዘተረፈ ዋነኛ መገለጫዎች እየሆኑ መምታታቸው በርካታ ዝርዝር የጥናት ውጤቶች ይጠቁማሉ፡፡
በከተሞች ጠቃሚ የመሰረተ ልማት እና ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎች መስፋፋት ብቻ ሳይሆን ትኩረት የሚሻው ጉዳይ ለሕብረተሰቡ የአኗኗር ዘይቤ ወሳኝ የሆኑ በጎ ገፅታዎች ማለትም ምቹ የመኖሪያ ሥፍራዎች፣ ውብና ፅዱ መናፈሻ አካባቢን መፍጠር አሁንም ተስኖናል፡፡ ከተሞቸው ያለቅጥ መቆሸሽ፣ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ቱቦዎች በክረምት ወቅት እየገነፈሉ መንገዶችን ማጥለቅለቅ፣ ባልተገባ ቦታ ከማጠራቀሚያ ገንዳ ውጪ ቆሻሻን ማስወገድና ማከማቸት ለዝንብና ትንኞች መከላከያ ክዳን አልባ በመሆኑ ለሕብረተሰብ ጤና ጠንቅ መንስኤነቱ አያጠራጥርም፡፡ በተለይም ታዳጊ ሕጻናት የሚጫዎቱበት ከብለት የፀዳ ቦታ በየሰፈሮቻቸው እንዲያገኙ ማመቻቸት በጨቅላ አዕምሮአቸው መልካም ነገሮች እንዲቀርፁ ለአገራቸውም የላቀ ፍቅር እንዲኖራቸው በትምህርት አንፆ ለማሳደግ ያግዛል፡፡ ለወደፊቱም ይህንን ኣርኣያነት እንዲከተሉ ፅኑ ፍላጎት ያሳድርባቸዋል፡፡
የሚገነቡ ሕንጻዎች የአየር አማቂ መስታወት የተንቆጠቆጡና ለአረንጓዴ ሥፍራ ታሳቢ ያለማድረ፣ በቂ የመኪና ማቆሚያ የሌላቸውና በግንባታ ወቅትም አስፈላጊውን የግንባታ ደህንነት አሸዋና ጠጠር በእግረኛ መንገድ ላይ መቆለል፣ አዳዲስ መንገዶች ሲቀየሱና ሲከፈቱ ያለ ዝርዝር ጥናትና እቅድ በርካታ ቤቶችን ማፍረስ፣ የከተሞች አየር በፋብሪካዎችና ከባድ ካሚዮኖች ጪስ መበከል፣ ሀገር በቀል ዛፍ ችግኞችን በስፋት ያለመተካት፣ የከተሞቹን ወንዞች ተፋሰስና ተዳፋት የመንገድ አውታሮችና ድልድዮች ትኩረት ማጣትና በተለየ እቅድ ያለመልማታቸው፣ በመሰረተ ልማት አቅርቦት ረገድ አንዱ በሌላው ላይ ጣል ገብነት ለሚፈጠረው የመቀናጀት ችግር ተጠያቂ መጥፋት፣ ለመሬት አጠቃቀም ጥናት ንድፍ የሚያግዝ ዘመናዊ የአየር ፎቶግራፍ ተደራጅቶ በሥነ ስርዓት ያለመደራጀቱ፣ በከተማ ፕላን የሚሰለጥኑ ባለሙያዎች ከፍተኛ ልምምድ እንዲያደርጉ ብሎም አዳዲስ ሀሳብ እንዲያመነጪ የሚያስችል አሰለጣጠን ዘይቤ ውሱንነት የመሣሰሉ ጠቅለል ያሉ ችግሮች ሳይጠቀሱ መቼም አይታለፍም፡፡
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በ1964 ዓ.ም ያሳተመው አንድ ፅሑፍ ሰንመለከት እንዲህ ይላል፦ «ሥልጣኔ በኑሮ ረገድ ጥንት ያልተሻሻለውን ነገር በቀላል ዘዴ እያሻሻሉ ምቾት የሚገኝበት ብልኀት…ሲሆን በመልካም ትምህርት እያሳደገ ወደ ከፍተና የኑሮ ዘዴ መምሪያ ነው፡፡ ድንቁርና ደግሞ የአንድ አገር ህዝብ ኑሮውንና ሀብቱን ደረጃ እንዳይሻሻል በጨለማዊ ሰንሰለት እየጎተተ ወደኋላ ወጥሮ የሚስብ ነው፡፡ ማናቸውም ሥራ ጠንከር ብለው ካልደከሙበት ጥቅም አይሰጥም፡፡ ይልቁንም ዝቅተኛ ሥራን አንዳንድ ሰዎች በስንፍና ምክንያት መስራት አቅቷቸው በችጋር አለንጋ በገዛ ራሳቸው ይገረፋሉ፡፡» ለውጥ የሚመጣው ማንንም አላስቸግርም ብሎ ጠንክሮ እየሰራ ራስን በመቻል እንጅ ሥራን ንቆ ከወዲያ ወዲህ በመንገላወድ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ለጊዜው ከፍ ያለ ሥራን አትቶ ዝቅ ያለ ሥራ ቢያገኝ ለጊዜው ያንኑ ይዞ የተሻለውን ሥራ ለማግኘት መጣጣር ይገባዋል፡፡ ሁናቴው እንደፈቀደ ከዝቅተኛው ሥራ ተነስቶ ሳይንቅ ወደ ተሻለው የሥራ ደረጃ ቢያዘግም ይበጀው እንደሁ እንጅ ፈፅሞ ግብረ ጠል መሆን አያሻውምና ከድንቁርና አዙሪትም በቀላሉ መላቀቅ ያስችላል፡፡
ሥልጣኔ በሰፈነባቸው ያደጉ ሀገራት እኮ የሕዝቡ ዋና ሀብት መሰረቱ ጤናው በሚገባ መጠበቁ ነው፡፡ አምራች ዜጋ ሆኖ ካላስፈላጊ ወጪም ይድናል፡፡ ሥልጣኔ ለከተሜው እውቀት ማደግ ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ለገጠሩ ሕዝብም የእርሻ ዘዴውን እንዲያሻሽል አጋዠ መሳሪያ ነው፡፡
የከተማን ውበትና የሕብረተሰብ ጤና አኗኗር እንዲሻሻል ቆሻሻን እንዳፈተተ ከነጥራጊው መጣል ሳይሆን በአግባቡ በመያዝና በማስወገድ ከመጥፎ ሽታና ጥቃቅን በካይ ነፍሳት መታደግ ያስችላል፡፡ በየሰፈሩ አንዳንድ ሰዎች የቆሻሻ መጣያ በአግባቡ ተጠቅመው ሲያስወግዱ አንዳንዱ ደግሞ በየደጃፉ ጥራጊውን በመጣል ለነዋሪው ጠንቅ ሆኖ ይታያል፡፡ ከዚህ የተነሳ የሕዝብ ጤና መበከሉ ብቻ ሳይሆን የከተማውም ፅዳትና ውበት መበላሸቱ አይቀርም፡፡ እንግዲህ መሰልጠን ማለት ካለማወቅ ወደ ማወቅ መሸጋገር ሲሆን ዋና መገለጫውም ትሁትነትና እና ለሕግ መከበር መታመን ነው፡፡ ለከተማ ውበት መጠበቅና መፅዳት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ግድ ይላል፡፡ የውጤታማነቱ ፍሬ ደግሞ ሀገር ተረካቢ ትውልድ በምቹና ፅዱ አካባቢ መኖር ባህል ሆኖ መለመድ ቀጣይነቱ አያጠያይቅም፡፡ ቸር ይግጠመን!!!