ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
ግንቦት 5 ፣ 2019
መግቢያ
እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ ወደ ኋላ በቀሩ አገሮች ውስጥ በሃይማኖትና በብሄረሰብ ስም ተሳቦ በየጊዜው የሚነሳው መጋጨትና እንዲያም ሲል መገዳደል ዋናው ምክንያት ሌላ ነገር ሳይሆን በእነዚህ አገሮች ውስጥ መካሄድና መደረግ ያለበት መንፈሳዊ ተሃድሶ ከቁም ነገር ውስጥ ስለማይገባና ስላልተካሄደም ነው። በተለይም የፖለቲካ ስልጣንን የጨበጡና ሀብትን አካብተው የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖሩና፣ ወይም ደግሞ ስልጣን ላይ ለመውጣት የሚታገሉና በውጭ ኃይሎች የሚደገፉ አንዳንድ የነፃ አውጭ ድርጅት ነን ባዮች ጥቃቅን ልዩነቶችን እየፈለጉና ከሌላው በልጠው ለመገኘት ሲሉ የማያስፈልግና ሳይንሳዊ መሰረቶች የሌላቸውን ቃላቶችን በመወርወር አንደኛው የህብረተሰብ ክፍል በሌላው ላይ እንዲነሳ በማድረግ በቀላሉ ሊገታ የማይችል ግጭት ወይም የወንድማማቾች መተላለቅ እንዲፈጠር ለማድረግ ይበቃሉ።
በተለይም የህብረተሰብን ታሪክና ውጣ ውረድነትን በተጣመመ መልክ በመተርጎምና፣ የሚኖሩበትን ህብረተሰብ ከሌሎች አደጉ ከሚባሉት አገሮች ጋር ሳያነፃፅሩ፣ ጭቆናና በደል ደርሶብናል፣ ወይም የአንድ ጎሳ የበላይነት የሰፈነበት ነው በማለት ከሀቁ የራቀ ነገር በማውራት ልዩነቱ እንዲሰፋ፣ መጠራጠር እንዲኖርና የመጨረሻ መጨረሻ በቀላሉ እልባት የማያገኝ ጦርነት እንዲቀሰቀስ የማይጭሩት እሳት የለም። ጭቆና የሚባለው ነገር በእኛ አገር ብቻ ያለ ነገር አድርገው በማቅረብና በማናፈስ መሰረታዊ ከሆኑ ጥያቄዎች በመሸሸ አንድ ምስኪን ህዝብ በቀላሉ ሊወጣ የማይችለው ማጥ ውስጥ እንዲገባ ሁኔታውን ያመቻቻሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ የሰው አስተሳሰብ፣ በተለይም ደግሞ የወጣቱ ጭንቅላት በማያስፈልግ አስተሳሰብ በመጠመድ ተግባሩ ወደ ጠብ ጫሪነት እንዲያመራ ይደረጋል። ለዕውነተኛ ነፃነት መሰረት ከሆነውና በራስ ላይ ዕምነት ከሚያሳድረው ሳይንሳዊ ዕውቀት እንዲሸሽ በማድረግ ደሃና ኋላ ቀርቶ እንዲኖር ያደርጋሉ።
ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አንዳንድ አገዛዞች በደንብ ሳያገናዝቡ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች፣ እንዲሁም ካለአግባብ ሀብት ማካበት ለድህነትና በራሳቸው ለሃይማኖትና ለብሄረሰብ ግጭት ምክንያት ይሆናሉ። ምክንያቱም ከውጭ የሚመጡ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ዕውነተኛና የተስተካከለ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ዕድገት ስለማያመጡ ሆድ የባሰው ወጣት መሸሸጊያ የሚያደርገው የብሄረሰብንና የሃይማኖትን ጥያቄዎች በማንገብ ነው። የአገራችን ታሪክ እንደሚያረጋግጠው መንግስታቶቻችን በውጭ ኃይሎች እየተመከሩ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ የስራ-አጥነትን ወይም ፈትነትን የሚቀንሱ ሳይሆኑ በራሳቸው ለችግሩ ተጨማሪ ምክንያት በመሆንና በአንድ አገር ውስጥ የተዛባ ሁኔታ በመፍጠር ህብረተሰብአዊ ቅራኔ እንዲከሰትና እንዲሰፋ ለማድረግ በቅተዋል። በዚህ መልክ ካለብዙ ግንዛቤና ንቃተ-ህሊና መዳበር ጉድለት የተነሳ የሚወሰዱ እርምጃዎች አንዱን ብሄረሰብ የሚጠቅሙ፣ ሌላውን ደግሞ የሚጎዱ ተደርገው በመተርጎም የራሳቸውን አጀንዳ ዕውን ለማድረግ ለሚፈልጉ ጥቂት ኃይሎች ወይም ኤሊት ነን ለሚሉት አመቺ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል።
ዛሬ በአገራችን ምድር በብሄረሰብና አልፎ አልፎ በሃይማኖት ስም ተሳቦ በወንድማማቾች መሀከል የሚከሰተው አለመግባባትና ደም መፋሰስ በውጭ ኃይሎችና፣ የዚህም ሆነ የዚያኛው ብሄረሰብ ኤሊቶችና እኛ ነን መሪህ በሚሉ የተጠነሰሰና የተስፋፋ ነው። የጭቆናና የመበደል ጉዳዮች የሚነሱትና እንደልዩነት የሚራገቡት በእርግጥም በድህነት ዓለም ውስጥ ከሚኖረው ምስኪን ህዝባችን ሳይሆን፣ ጥያቄዎች የሚነሱት የተንደላቀቀ ኑሮ ከሚኖረውና ራሱ ሳይገባው ከውጭ የሚመጡ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ በማድረግ የራሱን ህዝብ ወደ ድህነት ዓለም ውስጥ ከሚገፈትረው ይኽኛውን ወይም ያኛውን ብሄረሰብ እወክላለሁ ከሚለው ኢሊት ነው። እንደዚህ ዐይነቱ ኤሊት በእርግጥም የሚታገለው እወክለዋለሁ ለሚለው ብሄረሰብ ሳይሆን የውጭ ኃይሎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው። የውጭ ኃይሎች ደግሞ እንደዚህ ዐይነቱን ግራ የተጋባና ያልተገለጸለትን ኤሊት በጥቅም በመግዛት ልዩነቱ እንዲሰፋና የድህነቱም ዘመን እንዲራዘም ያደርጋሉ። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያለች የረጅም ጊዜ ታሪክ፣ የተሟላ ቋንቋና ልዩ ልዩ የሚያማምሩ ባህሎችና እጅግ የሚያምር መልከዓ-ምድር ያላት አገር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ማደጓን ስለማይፈልጉ አለ የሚባለውን የብሄረሰብ ልዩነት ተገን በማድረግ ህዝባችን ተንሳፎና ግራ ተጋብቶ እንዲኖር የማይፈጥሩት ተንኮል የለም። መሳሪያ የሚሆናቸውም ከዚህ ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጣና ግራ የገባው ኤሊት ነኝ የሚለው ኃይል ነው። ከጥቅሙ በስተቀር አርቆ ማሰብ የማይችልና በውጭ ኃይሎች ቡራኬ የሚኖረውና የሚጠመዘዘው ዋናው ተግባሩም ሳይንስን፣ ፍልስፍናና ልዩ ልዩ የዕውቀት ዘርፎችን በማዳበር የዕድገት ኃይል ከመሆን ይልቅ ጥቁር ወንድሙንና እህቱን ሰላም መንሳት ነው። ኃይላቸውን ሰብሰብ አድርገው በአንድነት አገራቸውን እንዳይገነቡና በዓለም ህዝብ ፊት ተከብረው እንዳይኖሩ ማድረግ ነው።
ከዚህ አደገኛና አገራችንን ወደ ዲንጋይ ዘመን ሊለውጣት ከሚችለው ሁኔታ በመነሳት፣ ለምን በእንደዚህ ዐይነቱ ኤሊት በተለይ፣ በአጠቃላይ ደግሞ በጠቅላላው ኤሊት ነኝ በሚለው ዘንድ የሃሳብ መዘበራረቅ በመፈጠር አንድን አገር የጦርነት አውድማ አድርጎ የታሪክ ቅርስን ለማጥፋት የሚደረገውን አደገኛ አካሄድ ለማሳየት እሞክራለሁ። ክዚህ በመነሳት ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ ባልሆነ አስተሳሰብ ያልታነፀ ጭንቅላት ለምን ለጦርነትና ለአገር ውድመት ምክንያት እንደሆነ በንፅፅራዊ አገላለጽ ለማረጋገጥ እሞክራለሁ። ለዚህ ዐይነቱ ንፅፅር ሊጠቅመን የሚችለው የአውሮፓው የህብረ-ብሄር አወቃቀርና የካፒታሊዝም በአሸናፊነት መውጣትና ዛሬ የዓለምን ህዝብ የመኖርና ያለመኖር ዕድል መወሰንን እንደመነሻ በመውሰድ ነው። ስለሆነም ከአገራችን ይልቅ በአውሮፓ ምድር የበለጠ ደም መፋሰስና ጭቆና እንደነበርና የአውሮፖው ህዝብ ከብዙ መቶ ዓመታት ጦርነትና መፈናቀል በኋላ ራሱን በራሱ በማግኘት አነሰም በዛም ውስጠ-ኃይሉ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚና ማህበረሰብ እንደገነባ መገንዘብ ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ኃይልና የማያቋርጥ ጦርትነት ሳይሆን የመጨረሻ መጨረሻ ዋናው የዕድገት አንቀሳቃሽ ኃይል፣ የሃሳብ ጥራትና በሃሳብ ዙሪያ የተደረገ ምርምርና ክርክር ለህብረተሰብ ዕድገት ወሳኝ ሚናን እንደተጫውቱ መገንዘብ ይቻላል። ክዚህ ስንነሳ እንዴት የአውሮፓው ህብረተሰብ የፍልስፍና፣ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የማቲማቲክስ፣ የሊትሬቸርና የድራማ፣ እንዲሁም ከጭንቅላት ውስጥ የሚፈልቁ የልዩ ልዩ ዕውቀቶች ባለቤት በመሆን የበላይነትን ሊቀዳጅ እንደቻለ በተቻለ መጠን ማየት ይቻላል። በዚህም መሰረት ተንኮል፣ አጉል ጥላቻ፣ መናናቅ፣ ስራን አለማክበር፣ በዲስፕሊን አለመስራትና ኃላፊነት አለመሰማት እንዳሉ ተወግደው የእውሮፓው ማህበረሰብ በካፒታሊዝም የሚገለጽ ዕድገት ባለቤት ለመሆን እንደበቃና ዓለምን እንደሚያሽከረክራት መረዳት ይቻላል።
ከጭንቅላት መዘበራረቅ ወደ ከፍተኛ ንቃተ-ህሊና የመሽጋገር ሂደት ጉዳይ !
የመጀመሪያዎቹ የተፈጥሮ ፈላሳፋዎች የሚባሉት የግሪክ ጠቢባን ከሶስት ሺህ ዓመት በፊት ምርምራቸውን ሲጀምሩ አትኩሮአቸው የተፈጥሮን ምስጢርና፣ በአጠቃላይ ሲታይ ተፈጥሮ ከምን ከምን ነገሮች እንደተሰራችና፣ ምንስ ነገር እንደያዛት ማወቅ ነበር። ስለሆነም እያንዳንዱ ፈላስፋ በመሰለውና ባመነበት መንገድ ተፈጥሮ የተሰራው ከውሃና ከእሳት ነው ሲል፣ ሌላው ደግሞ ውሃ፣ እሳት፣ አፈርና አየር ናቸው በማለት የተፈጥሮን ምንነትና አሰራሩን ለማወቅ ጥረት ያደርጉ ነበር። ለዚህ መነሳቸው የሆነው ቀደም ብሎ ከነበረው ከአፈ-ታሪክ(Mythology) በመላቀቅ ሎጂካዊ አስተሳሰብን ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ነው የተፈጥሮን ምስጢርና ቀስ በቀስም የሰውን ልጅ አስተሳሰብ ለመረዳት የቻሉት።፡
በተለይም አራቱ ንጥረ-ነገሮች ተቀባይነትን ካገኙ በኋላ፣ የኋላ ኋላ ብቅ ያሉት እንደ ሶክራተስ፣ ፕላቶና አርስቲቶለስ የመሳሰሉት ፈላስፋዎች ደግሞ ከጊዜው አወዛጋቢና የጦርነት ሁኔታ በመነሳት ምርምር ማድረግ የጀመሩት ለምን ሰላምን የሚነሱ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ? ስግብግብነትና ስልጣን(Greed and Power) ማካበትና በሌላው ላይ የራስን ፍላጎት መጫን ምክንያቶቻቸው ምንድናቸው? በማለት የሞራል፣ የስነ-ምግባርን፣ የእኩልነትንና(Justice) የዕውቀትን ጉዳዮች በማንሳት ነበር ለእነዚህ አስቸጋሪ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሙከራ ያደርጉ የነበረው። በጊዜው ስግብግብነትና ስልጣን፣ እንዲሁም ደግሞ ከሌላው በልጦ ለመገኘት ሲባል፣ ወይም ደግሞ ሌላን አካባቢ በኃይል ለመያዝ አሰቃቂና ተከታታይ ጦርነት ይካሄድ ስለነበር የዚህ ዐይነቱን የስልጣኔና የሰላም ጠንቅ የሆነውን ዋና ምክንያት መጠየቅና መፍትሄ መፈለግ የግሪክ ፈላስፋዎች ዋናው ተግባርና ታሪካዊ ግዴታ ነበር ማለት ይቻላል። ከዚህም በመነሳት የምርምራቸው አትኩሮ ጭንቅላትንና የንቃተ-ህሊናን ጉዳይና፣ ከዚህ ጋር የተያያዘውን አርቆ የማሰብና ያለማሰብ ጉዳይ፣ የሎጂክንና የኢንተሌክትን ጉዳይ፣ በረቀቀ መልክ ማሰብን፣ ወደ ውስጥ መመልከትንና በነገሮች መሀከል ያለውን መተሳሰርና፣ ዕውቀት የሚባለው ነገር ከጭንቅላት ብቻ የሚፈልቅ መሆኑን ማሳየት ነበር። በመሆኑም ከዚህ ጋር የተያያዙትን መሰረተ-ሃሳቦች እንደመንግስት ጉዳይ፣ የዲሞክራሲና የእኩልነትን ጥያቄ፣ በአጠቃላይ ሲታይ የሰውን ልጅ የኑሮ ትርጉም በመረዳት እንዴት የተረጋጋና እኩልነት የሰፈነበት ማህበረሰብ መመስረት ይቻላል? በማለት ጥያቄዎችን በመጠየቅ መልስ ለማግኘት ጥረት ያደርጉ ነበር። ስለሆነም በምድር ላይ እንደሚታዩት የማቴርያላዊና የባህላዊ ዕድገት ደረጃዎች የሰው ልጅ ጭንቅላት በረቀቀና ሎጂካዊ በሆነ መልክ ያስባል፤ አዳዲስ ነገሮችን ይፈጥራል፤ በዚያው መጠንም የኑሮውን ሁኔታ በማሻሻል ከእንስሳ የተሻለ መሆኑን ያሳያል፤ ወይም ደግሞ አስተሳሰቡ ውስንና በነገሮች መሀከል መተሳሰር እንዳለ የማይገነዘብ ይሆናል። ስለሆነም ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ ነገር፣ ለጦርነትም ሆነ ለሰላም መኖር ዋናው ወሳኝ ነገር የአዕምሮአችን መዳበርና አለመዳበር ነው። ፕላቶ ሪፑብሊክ በሚለው በተለይም ስለፍትሃዊ አገዛዝ አስፈላጊነት በጻፈው መጽሀፍ ውስጥ መነሻው የሰውን ጭንቅላት ማዕከላዊ ቦታ በመስጠት ነው። በፕላቶን ምርምር መሰረት የሰው ልጅ ጭንቅላት በሶስት ክፍሎች የተከፋፈለ ሲሆን፣ እነሱም አርቆ-ማሰብ(Reason)፣ መንፈስና(Spirit) ፍላጎት(Apetit) ሲሆኑ፣ የሁለቱ አዛዥ ወይም ተቆጣጣሪ አርቆ ማሰብ ነው። በመሆኑም እንደ አርቆ-የማሰብ ወይም ንቃተ-ህሊና ደረጃ የመንፈስና የፍላጎትም ሁኔታ ይወሰናል ማለት ነው። ይህም ማለት የአንድ ሰው የማሰብ ኃይል ካደገ ወይም በሁሉም አቅጣጫ የሚመለከት ከሆነ መንፈስንና ፍላጎቱን ሊቆጣጠር ይችላል። ይሁንና የማሰብ ኃይል በራሱ ደግሞ በትክክለኛ ወይም በማያሳስት ዕውቀት የሚወሰን ነው። አንድ ፍልስፍናዊ መሰረት የሌለውና የሰውን አዕምሮ ለመቆጣጠር(Manipulate) በተዘጋጀ ትምህርት የሰለጠነ ሰው ዕውነትን ከውሽት የመለየት ኃይሉ ደካማ ስለሚሆን የማሰብ ኃይሉም ውስን ይሆናል። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱ ሰው የፍላጎቱ ተገዢ ስለሚሆን በስግብግብ መነፈሰ በመመራት ለሰላምና ለዕድገት ጠንቅ በመሆን አንድ ህዝብ እፎይ ብሎ እንዳይኖር ያደርጋል።
ከዚህ በመነሳትና የመንፈስን ወይም የአዕምሮን ጉዳይ ማዕከላዊ ቦታ በመስጠት በሰው ልጅና በኮስሞስ፣ እንዲሁም በተፈጥሮ መሀከል ያለውን ግኑኝነት በመመርመር፣ የሰው ልጅም ካለምክንያት እንዳልተፈጠረና ተልዕኮውን በመረዳት የግዴታ የተፈጥሮን ምስጢር ማወቅ እንዳለበት፣ ዕውቀት የሚባለው ነገር ከሰው ጭንቅላት ውስጥ ብቻ መፍለቅ እንደሚችል አመለከቱ። በዚህም መሰረት እንደተፈጥሮ ሳይንስ፣ ማቲማቲክስ፣ አርኪቴክቸርና መዚቃ… ወዘተ. የመሳሰሉትን በማዳበር የሰው ልጅ ካሰበበት ሰላማዊ ኑሮ መኖር እንደሚችል አመለከቱ። በዚህ መሰረት በመጥፎ ነገር ያልተወጠረው የመጀመሪያዎቹና የተከታታዩ ፈላስፋዎች ጭንቅላት ተፈጥሮን በመቃኘት ለሰው ልጅ መመሪያ የሚሆነውን ሁለንታዊ ዕውቀት ማፍለቅ ቻለ። የሰው ልጅም ከጨለማ ኑሮ በመውጣትና ራሱን በማግኘት በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ነገሮችን በማውጣትና ቅርጽ በመስጠት ከእንስሳ ባህርዩ ሊላቀቅ እንደሚችል አመለከቱ ። ይህ ዐይነቱ የሰውን ጭንቅላት ማዕከላዊ ቦታ ሰጥቶ ምርምር ማድረግና በጊዜው ይካሄድ የነበረው ፈጠራ የመጀመሪያው የዕድገት ወይም የዘመናዊነት ደረጃ በመባል ይታወቃል። በዚህ መልክ ማቀድ፣(Planning) ማደራጀትና (Organization) ያለሙትን ተግባራዊ ማድረግ (Action) የጭንቅላትን የንቃተ-ህሊና መዳበር የሚያሳዩ ሲሆኑ፣ ማንኛውም ነገር በስሜትና በግብታዊነት የሚሰራ ሳይሆን፣ አንድ ሰው አንድ ውጤት ላይ ለመድረስ ከፈለገ የግዴታ የተወሰነ የአሰራር ስልትን ማዳበርና ጥልቅ ምርምር ማድረግ እንዳለበት የሳይንስ መመሪያ ሊሆን በቃ። ይሁንና ግን ይህ የግሪኮቹ የመጀመሪያው የስልጣኔ መነሻ በሮማውያን ወረራ ምክንያት የተነሳ በዚያው መልክ እንዳይቀጥልና ወደ ሌሎች አገሮች እንዳይስፋፋ ይታገዳል። ስለሆነም ከግሪክ ስልጣኔ መጥፋት በኋላ የአውሮፓው ህዝብ እስከ 13ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲወድቅ ይደረጋል።
የአውሮፓ ህዝብ እስከዚህ ጊዜ ድረስ በጭፍን የካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎችና የፊዩዳል አገዛዞች በጦርነት፣ በረሃብና በበሽታ በሚሰቃይበት ዘመን እነ ዳንቴ መነሻቸው የነበረው ጭንቅላትን ማዕከላዊ ቦታ በመስጠትና ጭንቅላት በትክክለኛ ዕውቀት ከተቀረጸ ተዓምር መስራት እንደሚችል በመገነዘብ ነው። ዳንቴም የአምላኮች ኮሜዲ በሚለው ግሩም መጽሀፉ ውስጥ ለማሳየት እንደሞክረው የሰው ልጅ ጭንቅላት በተሳሳተ ርዕዮተ-ዓለምና በተዘበራረቀ ሁኔታዎች እንደሚታወርና የሚያደርገውን ሁሉ ማገናዘብ እንደማይችልና፣ ከጨለማው ወደ ብርሃኑ ዓለም ለመውጣትና እራሱን ለማግኘት ትክክለኛውን መንገድ መከተል እንዳለበት ያስተምረናል። በዚህም መሰረት ዳንቴ የመጀመሪያውን ተሃድሶ(Renaissance) መሰረት ሲጥል፣ ተከታታዩ ትውልድ እሱ በጣለው መሰረት ላይ በመመርኮዝ በስዕል፣ በአርኪቴክቸር፣ በኦፔራ፣ በዕደ-ጥብበና ሰብአዊነትን ያላበሰ ትምህርት በማስፋፋት ለእነጋሊሌዮ፣ ቡርኖ ጋርዲያኖ፣ ፔትራርካና አያሌ ሳይንቲስቶችና ሰዓሊዎች የስልጣኔውን በር ለመከፈት ችሏል። ይህ ተከታታይነት ያለው በሁሉም አቅጣጫ የሚገለጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በመዳበር፣ በመስፋፋትና በጭንቅላት ውስጥ በመቀረጽ የማሰብ ኃይል በዚህ ዙሪያ ብቻ የሚሽከረከርና ችግርም ሲፈጠር ለመፍታት የሚቻለው በማሰብ ኃይልና አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠር ብቻ እንደሆነ ተቀባይነትን ያገኝ በጭንቅላት ውስጥ የተቀረጸ(progrtammed) ዘዴ ሆነ። በኢጣሊያን አገር በተለይም የፕላቶንን ፍልስፋናና ዕውቀት በሚያራምዱ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ከተጀመረ በኋላ ብርሃኑን በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች በማንፀባረቅ በየአገሩ ብቅ ያለው አዳዲስ ምሁራዊ ትውልድ የየአገሩን ኋላ-ቀርነትና የሰውን የአስተሳሰብ መወላገድ ወይንም የራሱን ምንነት አለመገንዘብ በሬናሳንስ መነፅርና በግሪኮች የፍልስፍና ዕውቀት እንዲመለከት ተገደደ። በዚህም መሰረት ለጦርነትና በጨለማ ኑሮ ለመኖር ዋናው ምክንያት መንፈስ በማያስፈልጉ ነገሮች በመወጠሩና የተፈጥሮን ምንነት ለመረዳት የሚያስቸለው ዕውቀት በጭንቅላቱ ውስጥ መቀረጽ ባለመቻሉ ነው። በመሆኑም የአውሮፓ ህዝብ የድንቁርናው መስዋዕት ለመሆን የበቃውና የገዢዎችን ጦርነትና ድህነትን ፈልፋይ አገዛዝ አሜን ብሎ የተቀበለው ከእግዚአብሄር የመጣ ትዕዛዝ አድርጎ በማመን ነበር።
ከዚህ በመነሳት አዳዲስ ብቅ ያሉና የተገለጸላቸው ሊቃውንት ጥያቄዎችን በመጠይቅና ካለው ባህላዊ አኗኗርና የአገዛዝ ስልት ጋር በመጋፈጥ በሰው ጭንቅላት ውስጥ ብርሃን እንዲታይ ለማድረግ ቻሉ። ስለሆነም የአውሮፓው ህዝብ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ለመሆን ከሬናሳንስ በኋላ የግዴታ በሪፍሮሜሽንና በኢንላይተንሜንት የመንፈስ ተሃድሶና ጭንቅላትን የማጽዳት ሂደት ውስጥ ማለፍ ነበረበት። ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ አዕምሮ ባህላዊ ከሚባሉና አዕምሮን ከሚቆልፉና ለድህነትና ለጦርነት ዋና ምክንያት ከሆኑ ነገሮች በመላቀቅና እራሱን በማግኘት በተፈጥሮ ላይ የበላይነትን የሚቀዳጅበት መንገድ ተከፈተለት።
በተለይም በ16ኛው ክፍለ-ዘመን በማርቲን ሉተር አማካይነት በሃማኖት ላይ የጥገና ለውጥ እንቅስቃሴ ሲካሄድ ዋናው ዓላማው መጽሀፍ ቅዱስንና ጳጳሶች የሚሉትን ዝም ብሎ መቀበል ሳይሆን፣ ህሊናን ወይም አዕምሮን ዋናው የመመራመሪያና የመመዘኛ መሳሪያ በማድረግ ነው። የማርቲን ሉተሩ የሪፎርሜሽን እንቅስቃሴ ለአዲስ አስተሳሰብ በሩን ሲከፍት፣ መከራከርና መጠየቅ፣ እንዲሁም በአንድ ነገር ላይ ተውስኖ አለመቆየትና፣ ጥቂቶች የሚናገሩትን ዝም ብሎ አለመቀበል የዕውቀት መመራመሪያ ዘዴ በመሆን ምሁራዊ ዕምርታን አመጣ። ከማርቲን ሉተር ንጽህ በንጹህ የሃይማኖት አስተሳሰብ ራሳቸውን ያላቀቁ ኃይሎች ደግሞ የማህበራዊ ጥያቄን በማንሳት ለካፒታሊዝም ዕድገትና ብሎም ሰርቶ መበልጸግን መመሪያ በማድረግ የኢኮኖሚ ጥያቄም መልክ መያዝ ቻለ።
ይህ በተለይም በካቶሊክ ሃይማኖት ጥብቅ የሆነ ዐምነት ላይ የተጀመረው ዘመቻና መዳበር የቻለው አዲስ አስተሳሰብ ለጀርመኑ አይዲያሊስቶች ተብለው በመጠራት በሚታወቁት የጀርመን ፈላስፎች መንገዱን ከፈተ። ፍልስፋና ይበልጥ በመስፋፋት ዕውቀት ብቻ ሳይሆን፣ ስነ-ምግባርና ግብረ-ገብነት፣ እንዲሁም ከዕውቀት ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ ነገሮች በመፈጠርና በመዳበር የሰው ልጅ በተሻለ መንገድ ማሰብ እንደሚችልና፣ በተለይም ሄግል ሁለንታዊ በሚለው አስተሳሰቡ በጠቅላላው ዕውቀት የሚባለውን ነገር፣ ከፖለቲካ እስክ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ተፈጥሮን እስከመረዳትና በተፈጥሮና በሰው ልጅ መሀከል ስለሚኖረው ግኑኝነትና፣ ሌሎች የዕውቀት ዘርፎችን ሁሉ በማጠቃለል የሰው ልጅ ሁለንታዊ ዕውቀትን ሊቀስም እንደሚችልና መጣርም እንዳለበት ማሳየት ቻለ። ይሁንና ግን በካንት ዕምነት የሰው ልጅ ከተወሰነ ነገር በላይ እርቆ ሊሄድ እንደማይችልና ሁሉንም ነገር አጠቃሎ የማየትና የመገንዘብ ኃይል ሊኖረው እንደማይችል አመለከተ። በዚህም መሰረት በተለይም የእግዚአብሄር መኖር ክሰው የማሰብ ኃይል ውጭ ስለሆነ ስለሱ መኖርና አለመኖር በፍጹም ማረጋገጥ እንደማይቻል በማሳየት በዕምነትና በሳይንስ መሀከል ሊኖር የሚገባውን ወሰን አሳየ። ይህ ማለት ግን ካንት እግዚአብሄር የለም ብሎ አላስተማረም፤ ያለመኖሩንም አልተቀበለም። ለማለት የፈለገው በቀጥታ ለማረጋገጥና ለማየት በማንችለው ነገር ላይ መነታረክ የለብንም ማለቱ ነው።
ይህ ዐይነቱ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች መዳበር የቻለውና እየተፍታታ የመጣው ዕውቀት የግዴታ ለሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ብቻ ሳይሆን ለግለሰብአዊ ነፃነትም በር ከፈተ። ፖለቲካዊ ነፃነትም ለአንድ አገር ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት የተገነዘቡ በተለይም የእንግሊዝ ሊቃውንት ጊዜው የብርሃን ዘመን ነው በማለት በመንግስትና በህዝብ መሀከል ሊኖር የሚገባውን መተሳሰብንና መፈላለግን በማመልከት፣ ዲስፖታዊ አገዛዞች በሰፈኑበት ቦታ በሁሉም መልክ ሊገለጽ የሚችል ህብረተሰብአዊ ዕድገት ሊመጣ እንደማይችል አመለከቱ። በዚህም መሰረት ዘ ሩል ኦፍ ሎው(The Rule of Law) የሚለውን የማህበረሰብ መመሪያ በማዳበር እራሱም መንግስት የህግ ተገዢም መሆን እንዳለበት አመኑ። በዚህም መሰረት እያንዳንዱ ዜጋ ከህግ በፊት እኩል ሲሆን፣ መብቱንና ግዴታውን ማወቅ እንዳለበት አሳሰቡ። በዚህ ዐይነቱ ህብረተሰብአዊ ስምምነት(Social Contract) ብቻ አንድ ማሀበረሰብ እንደማህበረሰብ መኖር የሚችል ሲሆን፣ በዚያው መሰረትም በፈጠራ ስራና በሙያው ማንነቱን ሊገልጽ ይችላል። ይሁንና ግን በእንግሊዝ አገር የፈለቀው የሊበራሊዝም ቲዎሪ በሚታዩ ነገሮች ላይ(Phenomenal) የሚያተኩር ሲሆን፣ ፕላቶ እንደሚለው ከዚያ ባሻገር የሚኖረውን ነገር እንድናይ የሚያግዘን ዕውቀት አይደለም። በዚህም መሰረት በተለያዩ ነገሮች መሀከል ሊኖር የሚችለውን ግኑኝነት፣ መተሳሰርና ተለዋዋጭ መሆንን አያመለከትም። ይህንን በምሳሌ ማየት ይቻላል። በዛሬው ዓለም በብዙ የካፒታሊስት አገሮች ሊበራሊዝምና የገበያ ኢኮኖሚ ሰፍነዋል ብለው አንዳንዶች ለማሳመን ቢሞክሩምና የህዝብ ተጠሪዎችም በህዝብ ቢመረጡም ፣ በሌላ ወገን ግን መንግስታትና የህዝብ ተወካዮች ነን የሚሉት በሎቢይስቶች ቁጥጥር ስር ያሉ ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ሊበራሊዝም በ18ኛው ክልፍለ-ዘመን የፈለቀና የዳበረ አስተሳሰብ ሲሆን በተለይም የግል ሀብት በጥቂት ሰዎች ቁጥጥር ስር በመምጣት በተለይም በህዝብ የተመረጥን ነን የሚሉ የካፒታሊስት አገሮች አገዛዞች በኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ የሚጠቅሙበትና ሌላውን የሚጎዱበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። በተለይም በንጹህ መልክ የገበያ ኢኮኖሚ ይካሄድ ይመስል በመተርጎምና ሁሉም ነገር ለገበያው ኃይሎች መለቀቅ አለበት በማለት የገበያን ኢኮኖሚ ወደ ርዕዮተ-ዓለምነት(Ideology) ለውጠውታል። በሶስተኛ ደረጃ፣ የዛሬው ካፒታሊዝም በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ-ዘመን እንዳለው ዐይነት ሳይሆን የተወሳሰበ የመጣና ጥቂት ኦሊጎሎፖሊስቶች ከአገራቸው በማለፍ የብዙ አገሮችን ህዝቦች ህይወት የሚቆጣጠሩበትና፣ በተለይም የአፍሪካን መንግስታት ሽባ ያደረጉበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ስለሆነም አብዛኛዎቹ የዘመኑ ፈላስፋዎችና የተገለጸላቸው ምሁራን የዓለም ህዝብ አዲስና ተጨማሪ የኢንላይተንሜንት ወይም የመንፈስ ተሃድሶ እንደሚያስፈልገው ያሳስባሉ። ከዚህ ስንነሳ በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ-ዘመን በእንግሊዝ ሊበራሎች የፈለቀው አስተሳሰብ ውስንነት ሲኖረው፣ የእነሶክራተስ፣ ፕላቶ፣ ላይብኒዝ፣ ካንትና ሄግል እንዲሁም ኋላ የተነሱት የጀርመን ፈላስፋዎች አሁንም ቢሆን እጅግ ጠቃሚነትና ዘለዓለማዊነትም ያለው መመሪያ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ጉዳይ በተለይም ኳንተም ፍዚክስ(Quantum Physics) ከሚባለው ቲዎሪ ጋር በመገናኘት አንድ ማህበረሰብ ሁለንታዊ በሆነ መልክ መታየት እንዳለበትና፣ ችግሮችም ሁለ-ገብ በሆነ የችግር መፍቻ መሳሪያ መንገድ ነው ሊፈቱት የሚችለው። እንደነ ፕላቶን ፍልስፍናም ኳንተም ፊዚክስ ዋናው መነሻው ጭንቅላት ሲሆን፣ በሰው ልጅና በጠቅላላው በተፈጥሮ መሀከል የግዴታ መደጋገፍና ግኑኝነት መኖር እንዳለበት ያሳስባል። በሌላ አነጋገር ተፈጥሮ ወደ ተራ ተበዝባዥነት መለወጥ ያለበት ጉዳይ ሳይሆን የግዴታ እንክባክቤ የሚያስፈልገውና ለተከታታዩ ትውልድም ሊተላለፍ እንዲችል ሆኖ መዘጋጀት እንዳለበት በጥብቅ ያሳስባል።
ያም ሆነ ይህ፣ ይህ ዐይነቱ በተወሰኑ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ውስጥ የዳበረው ምሁራዊ እንቅስቃሴ የተከታታዩንም ደቀ-መዝሙር ጭንቅላት በማነፅና የማሰብ አድማሱን በማስፋት ለህብረተሰብ ግንባታ የሚያገለግል ልዩ ልዩ ዕውቀቶችን እንዲያፈልቅ አግዞታል ማለት ይቻላል። አንደኛው ምሁር ያዳበረውን ዕውቀት ሌላው ዝም ብሎ በጭፍን የሚከተል ሳይሆን ትክክል መሆኑና አለመሆኑን ከፍልስፍናና ከተጨባጭ ሁኔታዎች አንፃር በመመርመርና የጎደለውን በሟሟላት ለተስተካከለ የህብረተሰብ ዕድገት አቅጣጫዎችን ማሳየት የአውሮፓ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች ዋና ተግባርና ባህል ነበር። በሌላ ወገን ደግሞ እንደኢኮኖሚክስ የመሳሰሉት ዕውቀቶች የርዕዮተ-ዓለም ባህርይ በመውሰድ እንደየሁኔታው በሀብትና በፖለቲካ አይሎ የወጣውን የህብረተሰብ ክፍል ጥቅም እንዲያንፀባርቁ ሆነው ሊዘጋጁ የቻለበት ሁኔታም መፈጠር ችሏል። በተለይም ካፒታሊዝም እንደስርዓተ-ማህበር በአሸናፊነት ሲወጣ ካለሱ ሌላ አማራጭ መንገድ የለም ወይም አለ በሚሉ ምሁራን ዘንድ ክርክር በመፍጠር ይህ ዐይነቱ ምሁራዊ ውዝግብ ዓለም አቀፋዊ ባህርይም ሊወስድ ችሏል። ያም ሆነ ይህ ካፒታሊዝም ውስጥ ባለው ውስጣዊ ኃይል መሰረት ሌሎች የማህበረሰብ ቲዎሪዎች ፣ ማለትም እንደሶይስሎጂ፣ የስነ-ልቦና ሳይንስ፣ የከተማ ግንባታና የአርክቴክቸር ሳይንስና ሌሎችም በመዳበርና በመስፋፋት በአጠቃላይ ሲታይ የምሁራን አስተሳሰብ ወይም ጭንቅላት ጥያቄን በመጠየቅና ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ ችግሮችን በመፍታት ብቻ ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ በቃ። በሌላ አነጋገር ማንኛውም በምሁሮች ዘንድ የሚደረግ ክርክር በአፈ-ታሪክ ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን የግዴታ ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ ባህርይ በመውሰድ ንትርከ-አልባ ባህል ሊዳብር ቻለ። በዚህ መልክ በጥቂት የአውሮፓ አገሮች የዳበረው ዕውቀት ውስን በሆነ መልክ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመስፋፋት ለትምህርትቤቶችና ለዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት መመሪያ ለመሆን በቅቷል። እንደዚህ ዐይነቱ በብዙ መልኮች የሚገለጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ፈጠራ በሌሎች አህጉሮችና አገሮች በፍጹም አይታወቅም። ከሁለት ሺህና ከሶስት ሺህ ዐመታት በፊት፣ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በስምንተኛው ክፍለ-ዘመን በባግዳድ ሳይንስና ማቲማቲክስ እስከተወሰነ ደረጃ ቢስፋፉም፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ከ15ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ብቻ ነው በከፍተኛ ደረጃ ዕውቀት ሊስፋፋና የካፒታሊዝምም ዕድገት ሊፋጠን የቻለው። በአውሮፓ ምድር ውስጥ ጭቆናን አስመልክቶ ጦርነቶች ቢካሄዱም የመጨረሻ መጨረሻ ህብረተሰብአዊ ችግሮች ሊፈቱ የቻሉት በተፈጥሮ ሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ዕውቀቶች አማካይነት ብቻ ነው። ባጭሩ የመጨረሻ መጨረሻ ካፒታሊዝም በአሽናፊነት ሊወጣ የቻለው በመጮህና ጥቂት መፈክሮችን በማስተጋባትና ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨት ሳይሆን ተከታታይነት ባለው ዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው።
ይህ የሚያስገነዝበን ምንድነው? ይህ ዐይነቱ የመንፈስ ተሃድሶ ሂደትና ውጣ ውረድነት የሚያስተምረን ማንኛውም ህብረተሰብአዊ ችግር ሊፈታ የሚችለው በዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው። በዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው ህብረተሰብአዊ ፕሮጀክቶችን ማቀድ፣ ማደራጀትና ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው። በሌላ ወገን ደግሞ ትክክለኛ ዕውቀት በደንብ ስር ባልሰደደበትና ምሁራዊ ክርክር እንደባህል ባልዳበረበት አገር ተምሬአለሁ የሚለው ጥቂቱ ምሁር ሁልጊዜ የሚያደላው በአቋራጭ ስልጣን ላይ ቁጥጥ ማለትንና የአንድን አገር ህዝብ ህልም ማጨለምና ሰቆቃውን ማብዛት ነው። በዚህ መልክ በአንዳንድ ምሁራን ጭንቅላት ውስጥ እንደመጥፎ ሶፍትዌር የተተክለው የተዛባ አስተሳሰብ ወደ ውስጥና ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ማየት ስለማይችል በዓለም አቀፍ ደረጃ ህብረተሰብአዊ ውዝግቦችና ድህነት እንዲስፋፉና የየአገሩ ህዝቦችም ዘለዓለማቸውን የተዝረከረከ ኑሮ እንዲኖሩ ለማድረግ የሚጥሩ ኃይሎች ጉያ ስር በመውደቅና ትዕዛዝ በመቀበል ሳይንሳዊ ይዘት የሌላቸውን ፖሊሲዎች ተግባራዊ በማድረግ አንድ አገርና ህብረተሰብ ታሪክ መስሪያ መድረኮች መሆናቸው ቀርቶ ብልግናና አመጽ የሚስፋፉባቸው ለመሆን እንደበቁ የምናየው ሀቅ ነው።
ከዚህ ስንነሳ ሰፋ ያለ ዕውቀት በዳበረባቸው አገሮች ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች ሲፈጠሩና በዚያው መሰረትም ህብረተስብአዊ መተሳሰር በካፒታሊዝም ሎጂክ ሲገለጽ፣ እንደኛ ባለው አገር ደግሞ ህብረተሰቡን ሊያይዙ የሚችሉ አሰራሮችና ኢኮኖሚያዊ አደረጃጀቶች ከጥንታዊ ባህርያቸው ባለመላቀቅ ህዝቡ ወደባሰ ድህነት የሚገፈተርበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል። በተለይም ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር የማይችል ህብረተሰብ የውጭ ኃይሎች መስዋዕት በመሆን ለዝንተ-ዓለም ፍዳውን እንዲያይ ይደረጋል። በአጠቃላይ ሲታይ ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ማህበራዊ ችግሮችን መፍቻ ዕውቀቶች በተወሰነና ቀስ በቀስ የማሰብ ኃይሉ መዳበር በቻለ ማህበረሰብ ሊፈጠሩና ምጥቀትን የሚያገኙ ቢሆንም፣ የምዕራቡ ዓለም ወይም የነጭ ዘር የቴክኖሎጂን ዕድገት ከማህበራዊ ይዘቱ (Social Context) በማውጣት ሳይንስንና ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅና በተወሳሰበ መልክ ማዳበር የሚችለው የነጭ ዘር ብቻ ነው በማለት እንደኛ ባለው ወደ ኋላ በቀረው ምሁር ላይ የዝቅተኝነት ስሜት እንዲያድርበት ለማድረግ በቅቷል። በሌላ ወገን ግን ማንኛውም ህብረተሰብ የተወሰነ የህብረተሰብ ዕድገትን በመጓዝ ነው እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው። በሌላ አነጋገር ማንኛውም ህብረተሰብ ከቴክኖሎጂዎች ጋር አልተፈጠረም ወይንም ለተወሰነ የሰው ልጅ ብቻ ቴክኖሎጂዎች ተዘጋጅተው አልጠበቁትም። በተጨማሪም በጣም ጥቂት የሆነው የሰው ልጅ ከማሰብና ከመፍጠር ጋር ሲወለድ፣ ሌላው ደግሞ እንዳያስብና እንዳይፈጥር ሆኖ ጭንቅላቱ ተጣሞ አልተወለደም። የብዙ አገሮችን የህብረተሰብ ዕድገት ታሪክ ገረፍ ገረፍ አድርጎ ለተመለከተ ሁሉም አገሮችና ህዝቦች በአነሳሳቸው ተመሳሳይ ባህርይዎች አላቸው። በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመንም በብዙ አገሮች የአሰራር ስልቶች ተመሳሳይ ባህርይ ነበራቸው። ይህ ማለት ዛሬ የምናየው ዕድገት ብዙ ውጣ-ወረድንና ህብረተሰብአዊ ውዝግብ ከተፈጠረ በኋላ የተገኘ ነው።
ያም ተባለ ይህ ዛሬ የምናያቸውና የምንጠቀምባቸው ተክኖሎጂዎች በሙሉ፣ የሰው ልጅም ወደ ህዋ የሚጓዝበት መሳሪያ፣ ለጥፋት የሚሰራውም የጦር መሳሪያዎች… ወዘተ. እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከሰማይ ዱብ ያሉ ሳይሆኑ ጭንቅላትን በከፍተኛ ደረጃ በማስጨነቅ የተገኙ ውጤቶችና እየተሻሻሉ የመጡ ናቸው። ከተማዎችና መንደሮች፣ ድልድዮችና ካናሎች፣ እንዲሁም፣ ልዩ ልዩ ነገሮች የሚሰሩት በሰው የማሰብ ኃይልና በዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው። በአንፃሩ ደግሞ የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ጠባብ ከሆነ የሌሎች ኃይሎች መጫወቻ እንደሚሆንና፣ የተፈጥሮ ሀብት እንኳ ቢኖረውም የዝንተ-ዓለሙን በድህነት እየማቀቀ እንደሚኖር የራሳችን አገር ተጨባጩ ሁኔታ ያረጋግጣልናል። በተለይም በሰው ልጅ ጭንቅላት ውስጥ አንድ መጥፎ ነገር ከተተከለ ከዚህ ዐይነቱ ህብረተሰብን ከሚያናጋ ባህርይ ለማላቀቅ በጣም እንደሚያስቸግር የአገራችን ሁኔታ ያረጋግጣል። የአንድ ልጅ ጭንቅላት ከጨቅላነቱ ጀምሮ ልክ እንደ አበባ ወይም ፍሬ እንደሚሰጥ አትክልት በየጊዜው ልዩ እንክብካቤ ካልተደረገለትና ሳይታወቅ ጭንቅላቱ በመጥፎ አስተሳሰብ ከተቀረጸ ተግባሩ ሁሉ ሌላውን የሚጎዳና ማህበራዊ ሰላምን የሚያናጋ ይሆናል። እንደዚህ ዐይነቱ ባህርይም በተራ የአካዴሚክስ ዕውቀት በማስትሬትና በዶክትሬት ዲግሪ በፍጹም ሊለውጥ ወይም ሊወገድ አይችልም። በተለይም በአገራችንና በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያለውን የተወሳሰበ ችግር ስንመለከት የችግሮቹና የመዘበራረቁ ዋና ምክንያት ያልተማረው ምስኪን ህዝብ ሳይሆን እራሱ ተምሬአለሁ የሚለውና ዶክትሬት ዲግሪን የጨበጠው ነው ለድህነትና ለጦርነት፣ እንዲሁም ለተዘበራረቀ ኑሮ ዋናው ምክንያት።
ከዚህ ሁኔታ በመነሳት ነው አርባ ዐመት ያህል እልክ ውስጥ አስገብቶን የሚያጫራርሰንን አሰቸጋሪና የተጣመመ ጭንቅላት መረዳት የምንችለው። የአገራችን ዋናው ችግር ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ መጣሁ የሚለው ጥቂቱ ኤሊት ንቃተ-ህሊናውን ለማዳበር በሚያስችሉት የንቃተ-ህሊና ሄደቶች ውስጥ ማለፍ ባለመቻሉ ብቻ ነው። ይህንን ጉዳይ ካንትም ሆነ ሄግል በጽሁፎቻቸው ውስጥ ማረጋገጥ ችለዋል። የግሪክ ፈላስፎችም ይህንን ነው የሚያሳስቡን። ማለትም የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ሊዳብር የሚችለው፣ በአንድ በኩል በራሱ ጥረት ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የማቴሪያል ሁኔታዎችና የአኗኗር ስልቶች ሲሻሻሉ ወይም ሲለወጡ የሰው ልጅም የሰለጠነ ባህርይ ማዳበር ይችላል። በመሆኑም በሚያስፈልገው ጊዜ ከትክክለኛ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ጋር መተዋወቅ የማሰብ አድማስን ያሰፋል። ከጠብ ጫሪነትና ከአገር አፍራሽነት ያድናል። በሌላ ወገን ደግሞ የተበላሸ ወይም ለዕድገት የማያመችና የማደግና የመስፋፋት ባህርይ የሌለው ቴክኖሎጂዎችን አገራቸው ውስጥ የሚያስገቡና እነሱን የሚጠቀሙ አገሮች የሰለጠነ ማህበረሰብ የመገንባትና ከአንደኛው የዕድገት ደረጃ ወደ ተሻለው የመሸጋገር አቅማቸው በጣም ዝቅተኛ ይሆናል። ይህንን ወደ አገራችን ሁኔታ ስንተረጉመው ዛሬ የሚያፋልጠን ጉዳይና እንዳንግባባ ምክንያት የሆነን የገዢ መደቦቻቸን በአስፈላጊውና በትክክለኛው ወቅት ከትክክለኛ ዕውቀት፣ እንዲያም ሲል ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር እንድንተዋወቅና ጠንካራ ህብረተሰብ እንድነገነባ ጥረት ስላላደረጉ፣ ወይም ደግሞ ስላልተገለጸላቸው ነው። ከዚህ ውጭ ማሰብ ስህተት ብቻ ሳይሆን የማንወጣው ማጥ ውስጥ በመግባት የተከታታዩንም ትውልድ በቀላሉ ሊፈታው የማይችለው ችግር ውስጥ እንዲወድቅ እናደረገዋለን ማለት ነው።
የኃይል ሚና በህብረ-ብሄርና በህብረተሰብ ግንባታ ሂደት ውስጥ !
በአውሮፓ ምድር ውስጥ ፍልስፍና፣ ሳይንስ፣ ሊትሬቸርና ድራማ፣ እንዲሁም የተፈጥሮ ሳይንስ ዳብረውና፣ አገሮችም በአዲስ መልክ ቢቀረጹምና የሰው ልጅም እንዲኖርባቸው ለማድረግ ውብ ውብ የአርክቴክችር ስራዎች ቢሰሩም ህብረ-ብሄር(Nation-State) ካለደም መፋሰስ የተመሰረተበት አንድም የአውሮፓ አገር የለም ማለት ይቻላል። ዕድገትንና ስልጣኔን የሚፈልጉ ኃይሎች የመኖራቸውን ኃይል፣ ስልጣኔን አጥበቀው የሚጠሉና የነበራቸውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ ላለማጣት የሚፈልጉ ኃይሎች እንዳሉና አጥብቀውም እንደሚታገሉ የአውሮፓው የህብረተሰብ ታሪክ ያረጋግጣል። በዓለም ታሪክ ውስጥ ጦርነት የተስፋፋበትና ጭቆና ስር የሰደደበት እንደ አውሮፓው ማህበረሰብ አልነበረም ማለት ይቻላል። አብዛኛዎቹ ትላልቅ ጦርነቶች፣ ከመቶ ዓመት እስከ ሰላሳ ዓመቱ ጦርነትና፣ በጀርመን ምድር ሰባት ዓመት ድረስ የፈጀው ጦርነት፣ በእንግሊዝ አገር በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች መሀከል የተካሄደው 20 ዓመት ያህል የፈጀ ጦርነት ሁሉ የሚያረጋግጡት ህብረ-ብሄርን መመስረትና ሳይንስንና ቴክኖሎጂን ዕውን ለማድረግ የቱን ያህል አስቸጋሪ እንደነበር ነው። በኋላም የተለኮሱትና ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች ዕልቂት ተጠያቂ የሆኑት የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነቶች የሚያረጋግጡት የሰውን ልጅ ሙሉ በሙሉ አርቆ እንዲያስብና ከአመጽ እንዲቆጠብ ለማድረግ የቱን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ነው። በተለይም ኢኮኖሚያዊ ኃይል ከፖለቲካና ከሚሊታሪያዊ ኃይል ጋር በሚቆላለፉበት ጊዜ አገዛዞች ከአገራቸው አልፈው በሌሎች አገሮች ላይ ጦርነት በማወጅ የአንድን አገር ዕድገት ለብዙ ዓመታት ወደ ኋላ ለመጎተት እንደሚችሉም ማየት ይቻላል። በተለይም ካፒታሊዝም ወደ ኢምፔሪያሊዝምነት ከተሸጋገረና በክስተታዊ ዕውቀት(Empricism) ላይ የተመሰረተው የእንግሊዙ አስተሳሰብ በአሽናፊነት ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ለኢምፔሪያሊዝም ያደሩና በጥቅም የተገዙ ምሁራን በተለይም የነፃ ንግድንና የስራ-ክፍፍል የሚለውን ዶክትሪን በማስፋፋት ነው የአፍሪካን የጥሬ-ሀብት ለመቆጣጠር የቻሉትና ጦርነትም ያወጁቡን። ከሰላሳ ዓመት ጀምሮ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ በየአገሮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት ተግባራዊ የሚሆኑት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ሁሉ የሚያረጋግጡት የሶስተኛው ዓለም አገሮች ለዝንተ-ዓለም በድህነት ዓለም እየማቀቁ እንዲኖሩ የታቀደ አንደኛው ስትራቴጂ ነው። ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ ተቀባይነት ካላገኘ ደግሞ የካፒታሊስት አገሮች የተለያዩ ምክንያቶችን በመፈለግና ጦርነት በመክፈት የሶስት ሺህ ዓመትና ከዚያም በላይ ታሪክ ያላቸውን አገሮች ድምጥማጣቸውን እንደሚያጠፉ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። የኢራክንና የሶሪያን ሁኔታ መመልከቱ ብቻ ይበቃል።
ለማንኛውም ሁሉም የአውሮፓ አገሮች ተመሳሳይ የሆነ የዕድገት መሰረት አልነበራቸውም። በየአገሩ ሰፍኖ የነበረው ስርዓትና ህብረተሰብአዊ አወቃቀር የዕድገታቸውንም አቅጣጫ ሊወስነው ችሏል። የወግ አጥባቂነት፣ በተለይም ደግሞ የካቶሊክ ሃይማኖት ከባላባታዊ ስርዓት ጋር በተቆላለፈባቸው አገሮች ውስጥ የምርት ኃይሎች እንዳያድጉና፣ እንዲያም ሲል ህብረ-ብሄርን ለመገንባት አስቸጋሪ እንደነበር የህብረተሰብ ታሪካቸው ያረጋግጣል። በዚህም ምክንያት የተነሳ አምራች ኃይሎች ታፍነው በመቅረታቸውና ከባህላዊ የአመራረት ስልት ለመላቀቅ ባልቻሉባቸው እንደስፔይንና ፖርቱጋል የመሳሰሉት አገሮች ውስጥ የውስጥ ገበያና በማኑፋክቸር ላይ የተመሰረተ ካፒታሊስታዊ የአሰራርና የአደረጃጀት ስልት ሊዳበር አልቻለም። በከተማና በገጠርም መሀከል የነበረው የስራ-ክፍፍል ግልጽ ስላልነበር ካፒታልና የስራ ኃይል በቀላሉ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመንቀሳቀስ ስላልቻሉ በማኑፋክቸር ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያ መገንባት በፍጹም አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የተነሳ በአንዳንድ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ረሃብና በሽታ የተለመዱ እንድነበር የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።
በሌላ ወገን ደግሞ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት በተስፋፋባቸው አገሮች ውስጥ ዕውቀት መስፋፋቱ ብቻ ሳይሆን የካፒታሊዝም ዕድገት ፈጣን ነበር። ሰው ማሰብ ሲጀምርና ከስራውና ከንግድ ትርፍ ማግኘት ሲጀምር አትኩሮውን ወደ ስራ ላይ አደረገ። ይህ ዐይነቱ ግለሰብአዊ ሩጫና ቀስ በቀስም ማርክስ ቬበር እንዳለው ካፒታሊስታዊ መንፈስና(The Spirit of Capitalism) የስራ ስነ-ምግባር እየተለመዱ በመምጣት የጠቅላላው ህዝብ መንፈስ በካፒታሊዝም ሎጂክ ዙሪያ እንዲሽከረከር ሊያደርገው በቅቷል። በዚህ መልክና ቀስ በቀስ ደግሞ ከተማዎች በስርዓት ሲገነቡ የህዝቡ አስተሳሰብ ሰብሰብ ሲል የአገራዊና የብሄራዊ ስሜቱ መዳበር ቻለ። ይህ ማለት ግን እነዚህ ሁሉ በቀላሉ የተገኙ ዕድገቶችና ድሎች ናቸው ማለት አይደለም። ካፒታሊዝም ስር እየሰደደና እየተስፋፋ ሲመጣ ግልጽ የስራ ክፍፍል መዳበሩ ብቻ ሳይሆን፣ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛ በከፍተኛ ደረጃ ይበዘበዝ ነበር። ከዚህም ባሻገር በጊዜው እንደዛሬው ንቃተ-ህሊና የዳበረ ስላልነበር የአካባቢ ውድመት ከፍተኛና በአንዳንድ ከተማዎችም ውስጥ ደግሞ በተለይም የሰራተኛው አኗኗር እጅግ አሰቃቂ ነበር። የሰፊው ህዝብና፣ በተለይም ደግሞ የስራ መስክ ለመፈለግ ከገጠር ወደ ከተማዎች የተሰደደው ተጠባባቂ ሰራተኛ(Reserve Armey) አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ይኖር እንደነበር በሰፊው ተመዝግቧል፤ በስዕል መልክም ሊገለጽ ችሏል። የካርል ማርክስ ጉዳኛና ደጓሚው ፍሪድሪሽ ኤንግልስም ይህንን አሰቃቂ የወዝ አደሩን አኗኗር በሚገባ ገልጾታል። ይህም የሚያመለክተው የዛሬው የእኛ የተንደላቀቀ ኑሮና እዚህና እዚያ ካለምንም ችግር በአውሮፕላን መጓዝ የብዙ ዓመታት የስራና የፈጠራ ውጤትና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በደማቸው የከፈሉት ነው ማለት ይቻላል። የገበያ ኢኮኖሚ ሊያድግና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ሊወስድ የቻለው ትምህርትቤት እንደተማርነውና በሸመደድነው ዐይነት ሳይሆን በብዙ ውጣ ውረድና ትግል የተነሳ ነው ካፒታሊዝም ሊያድግና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ሊወስድ የቻለው።
እስቲ ደግሞ የጀርመንን የህብረ-ብሄር አገነባብ ታሪክ ባጭሩም ቢሆን እንመልከት። ይኸኛውን መጥቀሱ ዛሬ ላለንበት አስቸጋሪ ሁኔታ ምናልባት እንደትምህርት ሊሆነን ይችላል ብዬ አምናለሁ። የጀርመንን ታሪክ ብቻ ስንወስድ፣ ጀርመን ከሰላሳኛው ዓመት ጦርነት ከተላቀቀች በግምት ከመቶ ሃምሳ ዓመት በኋላ በአንድ ባንዲራ ስር የተጠቃለለች አገር ለመመስረት በታላቁ ፍሪድሪሽ የፕረሽያ ንጉስና በሳክሶን ገዢዎች መሀከል ሰባት ዓመት ያህል የፈጀ እልክ አሰጨራሽ ጦርነት ተካሂዷል። ጀርመን በተለያዩ መሳፍንታት የምትገዛና በዚህም ምክንያት ለውጭ ወራሪዎች የተጋለጠች አገር ስለነበረች፣ ዴንማርክና ስዊድን፣ፈረንሳይና አውስትሪያ ከአንዴም ከሁለቴም በላይ በመውረር ኃይሏን አዳክመው ነበር። ይህንን የተረዱት ታላቁ ፍሪድሪሽ የሳክሶንን መሳፍንቶች በሚገባ ከቀጧቸው በኋላ በፈረንሳይ ላይ የመጨረሻውን ጦርነት በማካሄድ ጀርመን በ1871 ዓ.ም ወደ ህብረ-ብሄር ለመሸጋገር በቃች። ይህንን መሰረት ለማስያዝ የግዴታ ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢንዱስትሪ አብዮት ማካሄድና ህብረተሰቡ እንዲሰባሰብና ብሄራዊ ባህርይ እንዲኖረው የማይታለፍ ጉዳይ ነበር። ለዚህ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያዳርስና ጭንቅላትን ክፍትና ብሩህ የሚያደርግ ትምህርት በቪሊሄልም ሁምቦልዶት በመነደፍ ተግባራዊ ተደርጓል። በዚህ መሰረትና በተቀነባበረ ምሁራዊና መንግስታዊ ኃይል ጀርመን በአንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ እንግሊዝን በኢንዱስትሪና በቴክኖሎጂ ቀድማ መሄድ ቻለች። ቀደም ብለው እንግሊዝና ፈረንሳይ ኢንዱስትሪ አብዮትን ለማካሄድና ወደ አጠቃላይ ዕድገትና ወደ ህብረ-ብሄር ለመሸጋገርና ጠንካራ አገር ለመመስረት የቻሉት አንዱ ሌላኛውን በመለማመጥ ሳይሆን ኋላ-ቀር የሆኑ የውስጥ ኃይሎችን በዕውቀትና በሚሊታሪ ኃይል በመቅጣት ብቻ ነው። ከዚህ ስንነሳ ወደ ህብረ-ብሄር ለመሸጋገር ያለው ጉዞ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ጥበብን የሚጠይቅና አልፎ አልፎም ኃይል ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት ታሪክ ያረጋግጣል። በተለይም ዕውቀትንና ዕውነተኛ ስልጣኔን የማይፈልጉ፣ በዚህም በዚያም አሳበው ጦርነትን የሚጭሩና ክወጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር አንድን አገር ለመበጣጠስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በመለማመጥና በአማላጅ ከእልክ አስጨራሽ ባህርያቸውና ተግባራቸው እንዲቆጠቡ በማድረግ አይደለም ወደ ሁለ-ገብ ዕድገት መሸጋገር የሚቻለው። እነዚህ ኃይሎች የሚፈልጉትን ስለማይረዱና ሰው መሆናቸውንም ስለማይገነዘቡ የመጨረሻ መጨረሻ ከእኩይ ተግባራቸው ሊያስቆማቸው የሚችለው የተቀነባበረ ኃይል ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ በፖለቲካ ስልጣን ላይ የተገለጸለትና በራሱ የሚተማመን፣ እንዲሁም አገር ወዳድ ኃይል ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ ሲታይ ለአውሮፓው የህብረ-ብሄር ምስረታና ዕድገት አመቺው ሁኔታ በአንድ በኩል ዕውቀት በቀላሉ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መንሸራሽሩ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች መሀክል የሚደረገው የሰው ዝውውርና በጋብቻ መተሳሰር ለፈጠራ ስራና ለውስጣዊ ኃይል ማደግ አመቺ በመሆን ዕድገትን ማፋጠን ችሏል ማለት ይቻላል። በተለይም ግለሰብ ሳይንቲስቶችና ፈላስፋዎች፣ እንዲሁም የልዩ ልዩ ዕውቀት ፈጣሪዎች በራሳቸው ተነሳሺነትና ውስጣዊ ፍላጎት በመመራት ለአውሮፓው የማህበረሰብ ዕድገት ከፍተኛውን አስተዋፅዖ ሊያበረክቱ ችለዋል። ጠለቅና ሰፋ ያለ ዕውቀት ባላቸውና ዕውቀታቸውን ባጣመሩ ኃይሎች አማካይነት ነው የአውሮፓው ካፒታሊዝም ሊያድግ የቻለው። በዚህም መሰረት የዕውቀት መዳበርና መንሸራሽር፣ እንዲሁም ደግሞ ልዩ ዐይነት የፖለቲካ ሁኔታ መፈጠር ለአንዳንድ አገሮች ፈጣን ዕድገት ሊሰጣቸው ችሏል። እንግሊዝ የኢንዱስትሪ አብዮትን ልታካሄድ የቻለችው ከሆላንድ ተባረውና ከኢጣሊያን ፈልሰው በመጡ የይሁዲ ምሁሮች አማካይነት ነው። በተጨማሪም ከህንድ የዘረፈችው ቴክኖሎጂ ለዕድገቷ አስተዋፅዖ ሲያበረክት፣ በተለይም በኢኮኖሚ ላይ የተደረገው ጥልቅ ጥናትና ክርክር፣ እንዲሁም ለማኑፋክቸር ማዕከላዊ ቦታ መስጠትና፣ የልብስ አስራርን ከፍሎሬንስ መኮረጅ የኢንዱስትሪ አብዮትንና የቴክኖሎጅ ምጥቀትን አዳብሯል ማለት ይቻላል። በዚህ ላይ በፍጹም ሞናርኪዎች የተወሰደው ወደ ውስጥ ያተኮረ የአገር ግንባታ ለተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ህብረ-ብሄሮቻቸውን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት አስችሏቸዋል። እንደዚሁም የጀርመን ህዝብ ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ከመጡ ስላቮች፣ ከማዕከለኛው ምስራቅና ከይሁዲዎች ጋር የተቀላቀለ ነው። በተለይም ይሁዲዎች ለጀርመን ፍልስፍና፣ ሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከት ችለዋል ማለት ይቻላል። በተጨማሪም በታላቁ ፍሪድሪሽ የግዛት ዘመን ከሆላንድና ከፈረንሳይ የዕደ-ጥበብ ባለሙያተኞችን አምጥቶ ማስፈርና ህዝቡን እንዲያሰለጥኑ ማድረግ የተለመደ ነበር። በተለይም በሃይማኖት ምክንያት ክትትል ይደረግባቸው የነበሩ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች፣ ሁገኖትስ የሚባሉት ጀርመን አገር ጥገኝነትን በማግኘት ለጀርመን ዕድገት የማይናቅ አስተዋፅዖ ለማበርከት ችለዋል። በአጭሩ የተለያዩ ነገሮች አንድ ላይ በመጣመርና በመዋሃድ፣ በተለይም ደግሞ ዕውቀትን ማዕከላዊ ቦታ በመስጠት ነው በየአገሩ ጠንካራ ማህበረሰብ ሊፈጠር የቻለው። አንድም አገር ቢሆን በአንድ ብሄረሰብና ራሱን ከሌላው በማግለልና፣ እኔ ከሌላው የተለየሁ ነኝ በማለት ያደገ አገር የለም። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ አለማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ አፈ-ታሪክ የሆነ ወይም ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው አባባልና አስተሳሰብ ነው። ተፈጥሮም ሆነ ማንኛውም ማህበረሰብ የልዩ ልዩ ነገሮች ቅንብሮች ናቸው። ማንኛውም ነገር በአንድ ነገር ላይ ብቻ በመመስረት ሊያድግ በፍጹም አይችልም። እንደዚሁም የሰው ልጅ ለማደግ ከሌላው ጋር መገናኘቱ ብቻ ሳይሆን፣ እንደሰው ልጅና እንደማህበረሰብ ለመኖር ከምግብ ባሻገር ቴክኖሎጂና ሳይንስ እንዲሁም ለመንፈስ ዕደሳ የሚያስፈልጉ ስዕል፣ ሙዚቃና ልዩ ልዩ ባህላዊ ነገሮች ያስፈልጉታል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ከአንድ ብሄረሰብ በተውጣጣ ኃይል የሚዳብሩ ሳይሆኑ፣ ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጡና የተሻለ ተሰጥዕዎ ባላቸው ግለሰቦች አማክይነት ነው። ለዚህ ዐይነት ልዩ ችሎታ ደግሞ የተወሰነ ማህበረሰባዊ አወቃቀር ወይም አመቺ ሁኔታ መፈጠር አለበት። ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ለባህል ዕድገትና ለፈጠራ ስራ እንደ አመቺ ጉዳዮች ሆነው ሊወሰዱ ይችላሉ።
ያም ሆነ ይህ ሰፋ ባለና በተወሳሰበ የኢኮኖሚ ግንባታ አማካይነት፣ በከተማዎች ዕድገትና በመገናኛና በመመላለሻ መንገዶች አማካይነት ብቻ ነው አንድ ሰውም ሆነ ህዝብ ነፃነቱን ሊቀዳጅ የሚችለው። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲዘዋወርና እዚያ አዲስ ኑሮን ሲጀምር በተሻለ መልክ የመፍጠር ችሎታውን በማዳበር የአንድ ክልል ሰው ብቻ ሳይሆን የአንድ አገር ዜጋም መሆኑን ይሰማዋል። በዚህም መሰረት በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽና ሰፋ ያለ መሰረት ያለው ኢኮኖሚ ሁሉንም በማስተሳሰር እያንዳንዱም ማንነቱን ሊገልጽ የሚችለው በስራው፣ በዕውቀቱና በሚፈጥረው ነገር ብቻ ይሆናል ማለት ነው። የሰውም ማንነት የሚገለጸው ባልፈጠረው መሬትና፣ ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ የመጣሁ ነኝ በማለትና ወይም ዘር በመቁጠር ሳይሆን፣ በዕውቀት አማካይነትና አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠርና ለአንድ ህብረተሰብ በሚያበረክተው አስተዋፅዖ ብቻ ነው። በአጭሩ የሰው ልጅ ማንነት መግለጫው ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ መፈጠሩና ያልፈጠረውን መሬትና ውሃ፣ እንዲሁም አየር የእኔ ነው በማለት ሳይሆን፣ በሳይንስና በቴክኖሎጅ፣ እንዲሁም በሌሎች የፈጠራ ስራዎች አማካይነት ብቻ እንደሆነ የአውሮፓው የህብረተሰብ ታሪክ ያረጋግጥልናል። ክዚህ ሁኔታ በመነሳት በአገራችን ምድር በብሄረሰብና በማንነት ዙሪያ የሚካሄደውን ኢ-ሳይንሳዊ ጩኸት ጠጋ ብለን እንመልከት። በመጀመሪያ ግን ከተወሰነ አካባቢ በመነሳት በአገራችን ምድር ትልቅ አገር የመመስረቱን ጉዳይ እንመልከት። ይህ ዐይነቱ ሂደት ተፈጥሮአዊ ቢሆንም፣ ያልተጠናቀቀው የህብረ-ብሄር ግንባታ ወይም የተጨናገፈው ዕድገታችን ለተለያዩ አገር አፍራሽ ለሆኑ የውስጥ ኃይሎች አመቺ ሁኔታን እንደፈጠረ መመልከት ይቻላል። በተለይም በዘመነ ግሎባላይዜሽን ፈተናው ከባድና አገራችንም የመፈረካከስ ዕድሏ በቀላሉ መመልከት እንደማያስፈልግ ለማሳየት እወዳለሁ። ዋናው ፈተናችንና በቀላሉ ልንወጣው የማንችለው የውስጥ ኃይሎች መልካቸውን አሳምረው በተለይም ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር በሚቆላለፉበትና የእነሱን ትዕዛዝ ተግባራዊ በሚያደርጉበት አገር ውስጥ ህበረተሰብአዊ ውዝግቡና እዚህና እዚያ የሚፈነዳው ጦርነት አንድ ጠንካራና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ሊገለጽ የሚችል አገር ለመገንባት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል።
መጠናቀቅ ያልቻለው የህብረ-ብሄር ግንባታና ያስከተለው መዘዝ !
በሁላችንም ዘንድ ያለው ስምምነት ከአክሱም በፊት የነበረው ስልጣኔና በኋላም ብቅ ያለው ንጉሳዊ አገዛዝና የፊዩዳሊዝም መሰረት መጣል፣ እንዲሁም የክርስትና ሃይማኖት ወደ አገራችን መግባትና መስፋፋት ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወተ ነው። በተለይም በአክሱም አገዛዝ ዘመን መልክ እየያዘ የመጣው የግዕዝ ፊደል-የግዕዝ ፊደል ቀደም ብሎ የተገኘ ወይም የተቀረጸ ቢሆንም- በአራተኛው ክፍለ-ዘመን የክርስትና ሃይማኖት ወደ አገራችን ከገባ በኋላ ነው ተነባቢዎች(Vowls) በመመጨመር ዕምርታን ሊሰጡት የቻሉት። የኋላ ኋላም በያሬድ መቃኘት የተጀመረው የቤተክርስቲያን መዝሙርና የኖት አጻጻፍ፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ የሙዚቃ መሳሪያዎች መፈጠርና መዳበር የሚያረጋግጡት የስልጣኔን ወይም የዕድገትን ደረጃን ነው። ይህም የሚያመለክተው ማንኛውም ነገር ከትንሽ በመነሳት እየተስፋፋ እንደሚሄድና ሌሎች አካባቢዎችን እንደሚያዳርስ ነው። ይሁንና የአክሱም ስልጣኔ በአማካኙ በእርሻና በሩቅ ንግድ ላይ የተመረኮዘ ስለነበር ስልጣኔው ውስጣዊ ኃይል በማግኘት የተለያዩ ጎሳዎችን ሊያጠቃልልና ወደ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ሊሸጋገር አልቻለም። የመጨረሻ መጨረሻም በቤጃዎች ጦርነትና በዮዲት ወረራ የተነሳ ስልጣኔው እንዳለ ይወድማል። በተጨማሪም የሚመካበት የሩቅ ንግድ ይዘጋበታል። የተወሰነው ኃይል ወደ ደቡቡ ክፍል በማፈግፈግ በ12ኛውና የኋላ ኋላ ደግሞ በ13ኛው ክፍለ-ዘመን በመንሰራራት የዛግዌና የሰለሞናዊያን ነገስታት የክርስትናን ሃይማኖትና የግዕዝን ፌደል እንዲያብብ ሊያደርጉት በቅተዋል። ይሁንና የግዕዝ ፊደል ለአማርኛ እንዲያገለግል በመደረጉ ለቋንቋው የበለጠ ማበብ ዕምርታን ሰጥቶታል ማለት ይቻላል።
በሰለሞናይት ዲይናስቲ ዘመን ነው ፊዩዳሊዝም የሚባለው ስርዓት የህብረተሰብ የአኗኗር ስልት በመሆን ሊዳብር የቻለው። ይህ ስርዓት እንደ ባህላዊ ሆኖ በመወሰዱና የገበሬውም ኑሮ ተደጋጋሚ በመሆኑና በከፍተኛ ደረጃ በመበዝበዙ ክውስጥ ቴክኖሎጂያዊ ለውጥ በፍጹም ሊመጣ አልቻለም። በተለይም የነጋዴውና የአንጥረኛው የህብረተሰብ ክፍል ከገበሬው ጋር የነበራቸው ግኑኝነት በጣም የላላ ስለነበርና፣ በዚህም አማካይነት በጋብቻና በተለያዩ ዐይነቶች የሚገለጽ ህብረተሰብአዊ መተሳሰር ስላልነበር በገንዘብ አማካይነት ሊገለጽ የሚችል ኢኮኖሚ መዳበር አልቻለም። አንጥረኛው በየጊዜው የምርት መሳሪያዎችን እየፈጠረና እያሻሻለ ማቅረብ አልቻለም። በዚህም ምክንያት የአገር ውስጥ ንግድ ሊያድግና ገበያም የልዩ ልዩ ዕቃዎች መገበያያ በመሆን ህዝቡን ሊያስተሳስረው አልቻለም። ከአገር ውስጥ ይልቅ የሩቅ ንድግ የሚባለው ነበር የቤተክርስቲያንና የባላባቱን የፍጆታ ፍላጎት ያሟላ የነበረው። ከውጭ የሚመጣውም ዕቃ ደግሞ በንጹህ መልኩ ለፍጆታ ብቻ የሚያገለግል ስለነበር ለቴክኖሎጂ ምጥቀት ያለው አስተዋዖ አልቦ ነበር ማለት ይቻላል። በዚህም የተነሳ የፊይዳሉ መደብ የሚመካው በመሬቱና ከገበሬው በሚያገኘው ግብር ብቻ ስለነበር የፍጆታ አጠቃቀሙን ሊያሻሽልና ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋፅዖ ሊያበረክት አልቻለም። ስለሆነም የውስጥ-ሃይላቸው(Dynamic social forces) ከፍ ያለ የህብረተሰብ ክፍሎች ብቅ ሊሉና ከተማዎችንና መንደሮችን ሊመሰረቱና ህብረተሰቡን ሊያያዙ አልቻሉም። በማህበረሰቡ ውስጥም ምንም ዐይነት ምሁራዊ እንቅስቃሴ የሚታይ ስላልነበርና፣ አገራችንም ከውጭው ስልጣኔ የተቋረጠች በመሆኗ ዕውቀት ከውጭ በመግባት አስተሳሰብን በማደስ ቴክኖሎጂያዊ ለውጥ እንዲያመጣ አላስቻለውም። በዚህ ላይ በየቦታው የሚያስተዳድሩት ፊዩዳሎች ዋናው ተግባራቸው ጦርነት ማካሄድ ብቻ ስለነበር በራሳቸው ተነሳሽነት ከተማዎችንና መንደርቶችን በመመስረት የዕደ-ጥበብ እንቅስቃሴ እንዲዳብር የሚያደርጉት ጥረት አልነበረም። ይህ ማለት ግን አንዳንድ ሙከራዎች ወይም ፈጠራዎች አልነበሩም ማለት አይቻልም። ዛሬ የምንመገባቸው እንጀራና የተለያዩ የወጥ ዐይነቶች፣ እንዲሁም የምንጠጣው ጠላና ካቲካላ በፊዩዳሉ ስርዓት ውስጥ መጠመቅ እንደተጀመረና ከዚያ በመስፋፋት ቀሰ በቀስ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ግዛት ማዳረስ እንደቻሉ መገንዘብ ይቻላል። የጠጅን አመጣጥ ታሪክ ስንከታተልና አፈ-ታሪኩም እንደሚነግረን ንግስት ሳባ ኢየሩሳሌም ተምራ እንደመጣችና በግዛቷ ውስጥም እንዲስፋፋ እንደገፋፋች ይነገራል። ይህንን የተረት ተረት ነው ብለን እንኳ ብንተው በፊዩዳሏ ኢትዮጵያ እንደዳበረና እንደተሰፋፋ ይታወቃል። ፈትልና የልብስ ስራዎችን ስንመለከት የተለመደ እንደነበር ይታወቃል። ይሁንና ባለው የቴክኖሎጂ ገደብና የመፍጠር ችሎታ አለመዳበር እነዚህ የመጀመሪያዎቹ ጅማሮች ማደግና በፋብሪካ መልክ እየተጠመቁና እየተሰሩ ሊስፋፉ አልቻሉም። በአንፃሩ ካፒታሊዝም ከማደጉ በፊት እንደነዚህ ዐይነቶች የዕደ-ጥበብ ስራዎችና የካቲካላና የጠላ ጠመቃ በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመንም በአውሮፓ ምድር ውስጥም የተስፋፋ ነበሩ። ለማንኛውም በአገራችን ምድር የተስፋፋው የምግብ አስራር፣ የጠላና የካቲካላ አጠማመቅ፣ እንዲሁም አንዳንድ የዕደ-ጥበብ ሙያዎች በፊዩዳሉ ስርዓት ውስጥ የፈለቁና የዳበሩ፣ ስርዓቱ ወደ ሌላ አካባቢዎች ሲስፋፋ እነዚህ ባህላዊ ነገሮች የበለጠ በመሻሻል ዕምርታን በማግኘት አብዛኛው ብሄረሰቦች ሊመገቧቸውና ሊጠቅሙባቸው በቅተዋል። በዚህ መልክ የተለያዩ ባህሎች አንድ ላይ በመዋሃድ በዲያሌክቲካዊ ሂደት ከዝቀተኛ ወደ ተሻለ ደረጃ መድረስ ችለዋል ማለት ይቻላል። ይህም የሚያረጋግጠው ባህል የሚባለው ነገር በአንድ አካባቢ ቢዳብርም የተሻለ ዕምርታን ሊያገኝ የሚችለው ከሌሎች ባህሎች ጋር ሲቀላቀል ወይም ሲዋሃድ ብቻ ነው። አንድም ማህበረሰብ ውስጣዊ ኃይል ሊያገኝ የሚችለው በዚህ ዐይነት ሂደትና ውህደት ብቻ ነው።
በተለይም ዛሬ አዲስ አበባ በመባል የሚታወቀውና በአፄ ምኒልክ የተቆረቆረው ከተማ ቀደም ብሎ በሸዋ ነገስታት እንደተመሰረተና በአካባቢው ብዙ ቤክርስቲያናትም እንደነበሩ ይታወቃል። አንዳንድ የሸዋ ነገስታት የዕደ-ጥበብ አዋቂዎችን በመሰብሰብ ስራቸውን እንዲያሻሽሉ ይገፋፉ እንደነበር የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። በዚህ ጊዜ ነው ግራኝ መሀመድ የሚባለው ጦርነት በማወጅ እስከተሸነፈበትና እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ስልጣኔውን እንዳለ ያወደመውና ብዙ ቤተክርስቲያናትን ያቃጠለው። የፊዩዳሉ አገዛዝ መደምሰስና የስልጣኔው መፈራረስ ኦሮሞ ለሚባለው ብሄረሰብ መንገድ በመክፈት የተቀሩት ስልጣኔዎች ሊወድሙ ችለዋል። ዛሬ ኦሮሞ በመባል የሚታወቀው ጎሳ በ16ኛው ክፍለ-ዘመን ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ሲስፋፋ ስልጣኔን ይዞ የመጣ አለነበረም። የዕደ-ጥበብ ልምድና ሙያ፣ እንዲሁም ከንግድ ልውውጥና ከከተማ ግንባታ ጋር የሚገናኝ ባህል ያልነበረው ስለነበር በሳይንሱና በፍልስፍና አገላለጽ እንደማህበረሰብ የሚኖር አልነበረም። የስራ-ክፍፍልም ስለማያውቅ እንደአገርና እንደህብረ-ብሄር የሚቆጠር ባህርይ አልነበረውም። ከዚህ ስነነሳና የዓለም ታሪክም ሆነ በተለይም የአውሮፓው የህብረተሰብ አገነባብ ታሪክ እንደሚያረጋግጠው አንድ ህዝብ እንደማህበረሰብና እንደህብረተሰብ ለመጠራት ብዙ ነገሮችን ማሟላት አለበት። እነዚህም የሰለጠነ ቢሮክራሲያዊ ኃይልና ሰፋ ያለ ተቋማትና ሌሎች በቴክኖሎጂ የሚገለጹ የአደረጃጀትና የአመራረት ስልቶች አንደን ህዝብ እንደማህበረሰብና እንደህብረተሰብ ሊያስጠሩት ይችላሉ። በተጨማሪም በሊትሬቸር፣ በሙዚቃና በሙዚቃ መሳሪያዎች አሰራርና አጠቃቀም የዳበረና ተሰባስቦ የሚገኝ ህዝብ ማህበራዊና ህብረተሰብአዊ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። ክዚህች አጭር ሀተታ ስንነሳ ጥቂቱና አክራሪው የኦሮሞ ኤሊት የሚያወራው ያልነበረን ነገርና በኢምፔሪካል ደረጃም ሊረጋገጥ የማይችልን ነገር ነው። በሊላ ወገን ግን እንደዚህ ተብሎ ሲጻፍ አንደኛውን ከፍ፣ ሌላውን ደግሞ ዝቅ አድርጎ ለማየት አይደለም። ያም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ አንዳንድ ጎሳዎች በማደግና የስራ-ክፍፍልን በማዳበር ቀስ በቀስ ወደማህበረሰብ ለመለውጥ ሲችሉ ፣ ሌሎች ደግሞ በተለያየ ምክንያት የተነሳ አይ ባለው ቦታ ረግተው ይቀራሉ፣ ወይም ደግሞ ሻል ያለ የቴክኖሎጂ ዕድገት ባለው ማህበረሰብ ይዋጣሉ። ያም ተባለ ይህ ስልጣኔ የኋላ ኋላ ዕምርታን ሊየገኝ የሚችለው የተለያዩ ህዝቦች ወይም ጎሳዎች ሲቀላቀሉና የየራሳቸውን ልምድ ሲያዋህዱ ወይም ሲያገናኙ ብቻ ነው።
ለማንኛውም ኢትዮጵያ ከአደዋ ጦርነትና በኋላ ነው በአፄ ምኒሊክ አማካይነት ወደ ህብረ-ብሄር ልትሸጋገር የቻለችው። እንደባቡር ሃዲድ የመሳሰሉት፣ የገንዘብ ዕተማና የማዕከላዊ ባንክ መቋቋም፣ ፖስታቤት መክፈትና ቴምብር ማተም፣ ትምህርት ቤት መክፈትና ሌሎችም ለዘመናዊነትና ለህብረ-ብሄር ምስረታና ግንባታ የሚያገለግሉ ነገሮች በሙሉ በአፄ ምኒልክና በአገዛዛቸው ነው የተቋቋሙት። ውስን በሆነ መልክም የውሃ ቧንቧ የተተከለው በአፄ ምኒልክ አገዛዝ ዘመን ነው። ከዚህ ሃቅ ስንነሳ አፄ ምኒልክ ከአፄ ቴዎድሮስ ቀጥሎ የተገለፃለቸው ንጉስ(Enlightend Monarchy) ናቸው ማለት ይቻላል። ይህ አጠራር በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ-ዘመን በአውሮፓ ውስጥ የተለመደ አነጋገር ነበር። ለማለት የተፈለገውም ኋላ-ቀር ከሆነ ስርዓት መላቀቅና ብርሃንን ማየት ማለት ሲሆን፣ በዚህ አማካይነት ነው የኋላ ኋላ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ግለሰበአዊ ነፃነት ሊገኝና የፈጠራ ስራም ሊዳብር የቻለው። ወደ ኢትዮጵያችን ስንመጣ በጊዜው የአፄ ምኒልክ ማሀበራዊ መሰረት ወይም የተገለጸለት ኃይል (Social forces) በጣም ውስን ስለነበር በመጀመሪያው ወቅት የተደረገውን የዘመናዊነት እንቅስቃሴ በአገር ደረጃ ማስፋፋት አልተቻለም። በየክፍለ-ሀገሩም ዘመናዊ ቢሮክራሲ ማቋቋምና ከተማዎችን መገንባት በፍጹም አልተቻለም። ስለሆነም በጊዜው በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ የተፈጠረው ህብረተሰብአዊ ቅራኔ፣ ማለትም ውስን ዘመናዊነትና የፊዩዳሉ አገዛዝ እዚያው በዚያው ጎን ለጎን መኖር የአፄ ምኒልክ የፈጠሩት ችግር ሳይሆን በጊዜው የነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ የፈጠረው ነገር ማለት ይቻላል። ከዚህም ባሻገር የኢምፔሪያሊዝም ማደግና መስፋፋት፣ እንዲሁም የሶስተኛው ዓለም አገሮችን የጥሬ-ሀብት ለመቀራመት መራወጥ ለጠንካራ ኢኮኖሚ ግንባታና ለህብረ-ብሄር ምስረታ በጣም አስቸጋሪ ነበር። በተጨማሪም ዕውቀት የሚባለው ነገር ከውጭ እንዳለ የሚገባ ስለነበር ትክክለኛውን ከተሳሳተው ለመለየት የሚችል ኃይል ስላልነበር ኢምፔሪያሊዝም እንደኛ ያለውን ህዝብ በቀላሉ ሊያታልል የሚችልበት ሁኔታ ነበር። በሌላ አነጋገር በጊዜው እንደጃፓኑ የሜጂ አገዛዝ ዐይነትና የተሻለ ማህበራዊ መሰረት ያለው በአገራችን ምድር ቢኖር ኖሮ የኢትዮጵያ ዕድገት ምናልባት የተሻለና የተስተካከለ ሊሆን ይችል ነበር። ለማንኛውም አፄ ምኒልክ የነበሩበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ስንመለከትና ከስራቸው የተሰለፈውን ኃይል በምንመረምርበት ጊዜ እሳቸውን እንደጭራቅ አድርጎ ማየቱ በጊዜው የነበረውን አስቸጋሪ የህብረተሰብ አውቃቀር በሚገባ አለማጤን ብቻ ሳይሆን፣ የራስንም ታሪክ በሚገባ መገንዘብ አለመቻል ነው። እንዲያውም የአፄ ምኒልክ አገዛዝ መስፋፋትና አገራችንም በአንድ አገዛዝ ስር መጠቃለሏ በዝቅተኛ የአኗኗር ስልት ይኖሩ የነበሩ ጎሳዎችን ከክልላቸው ወጥተው እንዲንቀሳቀሱና ብርሃንን እንዲያዩ አስችሏቸዋል ማለት ይቻላል። ስለዚህም አፄ ምኒልክን መወንጀሉ አልአግባብና በታሪክም ዘንድ ተጠያቂ የሚያደርግ ነው። በተለይም የትግሬና የኦሮሞ ኤሊቶች እጅግ ኋላ-ቀር በሆነ አመለካከት የሚያስተጋቡት ኢ-ታሪካዊና ኢ-ሳይንሳዊ አነጋገርና አፃፃፍ አንድ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ለሁሉም ህዝብ የሚጠቅም ማህበረሰብ እንዳንገነባ እንቅፋት እየሆነን መጥቷል ብል ማጋነን አይሆንም። አንዳንዶች በቅናትና በዝቅተኛ ስሜት እየተነሱ የሚያካሄዱት ዘመቻ ለሳይንሳዊ ክርክር በሩን እየዘጋ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ ላለን ችግር መፍትሄም እንዳንፈላልግ መንገዱን ሁሉ ዘግቷል።
ለማንኛውም ይህንን ትተን ወደ ኋላ ላይ ስንመጣ ለዛሬው መመሰቃቀላችንና ብሄራዊ ባህርይ አለመያዝ አዲስና አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጠራል። አፄ ኃይለስላሴ ከሁለተኛው የኢትዮጵያና የኢጣሊያን ጦርነት በኋላ ስልጣናቸውን እንደገና ሲጨብጡ አንዳንድ የግንባታ እርምጃዎችን ቢወስዱም፣ የተከሏቸው ኢንዱስትሪዎች በሙሉ የማደግና የመስፋፋት ባህርይ አልነበራቸውም ። በዚህም ምክንያት የተነሳ በአገር አቀፍ ደረጃ ሰፋ ያለና የተወሳሰበ የውስጥ ገበያ(Home market) ሊዳብርና ሊያድግ አልቻለም።
ይህ ሁኔታ በጊዜው ብቅ ማለት የጀመረውን የህብረተሰብ ኃይል ወደ ነጋዴነት ብቻ እንዲያዘነብል ገፋፋው። በዚህ ላይ በየቦታው የቀለጠፈና ዘመናዊ ቢሮክራሲና ሌሎች ለአገር ግንባታ የሚያገለግሉና ህዝቡን ሊያቅፉ የሚችሉ ተቋማት ባለመገንባታቸው በየክፍለ-ሀገሩ ያለው የሰው ጉልበትና የጥሬ ሀብቶችን በማንቀሳቅሰ ሰፋ ያለ ህዝቡን የሚጠቅም ግንባታ ማካሄድ አልተቻለም። የየክፍለ-ሀገራቱም ገዢዎች የተማሩ ስላልነበሩ በራሳቸው ተነሳሽነት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በማውጣትና ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎችን እንዲቋቋሙ በማድረግ ለሰፊው ህዝብ፣ በተለይም ደግሞ ለወጣቱ የስራ መስክ መክፈት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የተነሳ በየቦታው በባህል ረገድ ኋላ-ቀር ሁኔታ የሚታይበትና ሰፊው ህዝብም አጋዥ ያልነበረውና፣ በራሱ ኃይል ብቻ ጥሮ ግሮ የሚኖር ነበር። ከአውሮፓ የህብረተሰብ አገነባብ ታሪክ የምንማረው ነገር ካፒታሊዝም እራሱን እስኪችል ድረስ አብዛኛዎች ነገሮች፣ ማለትም የከተማ ግንባታ፣ የኢንፍራስትራክቸር መስፋፋት፣ የኢንዱስትሪዎች መቋቋምና ድጎማ ማግኘት፣ ልዩ ልዩ ተቋማትና ትምህርትቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ይስፋፉና ይገነቡ የነበረው በመንግስት አማካይነት ነው። በዚህም ረገድ ነው ቀስ በቀስ የገበያ ኢኮኖሚ የሚባለው ነገር ሊያብብ የቻለው። ወደ አገራችን ስንመጣ አገዛዙ የሚመራበትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ አለማወቁ ብቻ ሳይሆን፣ በምሁራን ደረጃም ለአገር በሚጠቅም ቲዎሪና ፖሊሲ ነክ ነገር ላይ ምንም ዐይነት ክርክር ስለማይደረግ በአገዛዙ ላይ ጫና ማድረግ አይቻልም ነበር። በመሆኑም ቀስ በቀስ በመንግስት ላይ ግፊት ሊያደርግና የፖሊሲ መሻሻል እንዲኖር ትምህርት የሚሰጥ ምሁራዊ እንቅስቃሴ አልነበረም። የምዕራብ አውሮፓን የካፒታሊዝም ዕድገትና የማህበራዊ ሁኔታዎችን መሻሻል ስንመለከት ግን ሁሉም ነገር ይፈልቁ የነበረው በምሁራን አማካይነት ነበር። በተለያዩ ቲዎሪዎችና ፖሊሲዎች ዘንድም የጦፈ ክርክር ስለሚደረግ መንግስታት በጭፍን አንዱን ፖሊሲ ብቻ ተግባራዊ የሚያደርጉበት ሁኔታ አልነበረም። ወደ አገራችን ስንመጣ ግን በነበረው ምሁራዊ ክፍተትና ውስን የሆነ ፖሊሲ ምክንያት የተነሳ አገዛዙ ሰፋ ብሎ እንዲያስብና አብዛኛውን ህዝብ የሚጠቅም ብሄራዊ ፖሊሲ እንዲነድፍና ተግባራዊ እንዲሆን አላስቻለውም። በዚህም ምክንያት የተነሳ በአገራችን ውስጥ ያልተስተካከለ ዕድገት መስፋፋቱ ብቻ ሳይሆን ያለንን የጥሬ-ሀብትና የሰው ኃይል በሚገባ መጠቀም አልተቻለም።
በሌላ ወገን ግን ይህ ዐይነቱ የዕድገት ክፍተት እያለ ከ1940ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ መታየትና ማደግ የጀመረው በተለያዩ መልኮች የሚገለጸው ባህል ብሄራዊ ስሜታችንን እንዳዳበረውና የኢትዮጵያዊነትን ስሜት እንዳደመቀው ለማንኛችንም ግልጽ ነው። ጣሊያን ድል ከተመታና ከተባረረ በኋላ ነው በተለይም የተለያዩ ሙዚቃዎች ሊዳብሩና ህዝቡን ሊያስተሳስሩት የቻሉት። የእነ ጥላሁን ገሰሰ፣ መሃሙድ አህመድና እንደብዙነሽ በቀለ… ወዘተ. የመሳሰሉት ዘፋኞች የዘመናዊነት ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። የአገር ባህል ሙዚቃም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው መዳበርና አገርን ማዳረስ የቻለው። በስነ-ጽሁፍ ደረጃም አያሌ ባይባልም ትችታዊ አመለካከት ያላቸው መጽሀፎች በመታተምና በመራባት ለንቃተ-ህሊና መዳበር የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ማድረግ ችለዋል። የቲያትር ስራዎችም በመዳበርና በመታየት እስከተወሰነ ደራጃ ድረስ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ጭንቅላት ማደስ ችለዋል። እነዚህና ሌሎች ባህላዊ ነክ ፈጠራዎች፣ እንደምግብ የመሳሰሉት በመስፋፋትና አብዛኛው ህዝብ እንዲመገበው ማድረግ ቀስ በቀስ ብሄራዊ ስነ-ምግባር እንዲዳብርና በመንፈስ እንድንያያዝ ሊያደርጉን በቅተዋል። ይሁንና ግን በኢኮኖሚው የውስጠ-ኃይል ደካማነት የተነሳ በአገሪቱ ውስጥ አጠቃላይ የሆነ የባህል ዕምርታ ሊታይ አልቻለም። እዚያው በዚያው ይህንን ዐይነቱን ብሄራዊ ባህል የሚቀናቀኑ ነገሮች በመፈጠራቸው ሰፋ ያለ ማህበራዊ ቅራኔም ይታይ እንደነበር ግልጽ ነው።
ባጭሩ በጊዜው የታየው ኋላ-ቀርነት ከ90% በላይ የሚቆጠረውን ህዝብ የሚመለከት ነበር። አገዛዙ ከአማራ ብሄረሰብ የተውጣጣ ስለነበር ለአንድ ብሄረሰብ ያደላል የሚለው ተራ ቅዠት እንጂ ተጨባጩን ሁኔታ የሚያንፀባርቅ አልነበረም። እንዲያውም ኋላ-ቀር የሚባለው ክፍል አብዛኛው የአማራው ግዛት ነበር። በዚህም ምክንያት ነው በወሎና በሰሜኑ አንዳንድ ቦታዎች በተደጋጋሚ ረሃብ ይከሰት የነበረው። በችግር ይሰቃይ የነበረው ጎንደሬው፣ ጎጃሜውም ሆነ የወሎ ሰው ስራ ለመፈለግ ወደ ደቡቡ ክፍለ-ሀገራት ነበር የሚያቀናው። ይህ ዐይነቱ የጊዜውን ሁኔታ ያላገናዘበና፣ በተለይም ደግሞ ካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲስፋፋ የሚያመጣውን ያልተስተካከለ ዕድገት ሳያጤኑ የትግሬና ዛሬ ኦሮሚያ ተብሎ የሚጠራው በዕድገት ወደ ኋላ የቀረና ጭቆና የሰፈነበት ነበር ብሎ ማራገብ ከዕውነተኛው ሁኔታ የራቀ ነበር። አፄ ኃይለስላሴና አገዛዛቸው ለአማራው ዲሞክራት ሆነው ለሌላው ደግሞ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ሊያራምዱ የሚችሉ አልነበሩም፤ ባህርያቸውም አይፈቅድም ነበር። በሌላ አነጋገር የዲሞክራሲና የነፃነት እጦትና፣ ጭቆናና ኋላ-ቀርነት ጠቅላላውን ህዝብና ሁሉንም ክፍለ-ሀገሮች የሚመለከት ነበር። ስለሆነም ነው የየካቲቱ አብዮት የፈነዳውና የመሬት ለአራሹም እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ተግባራዊ ሊሆን የበቃው። በጊዜው አስራስምንት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው በኧጠቃላይ ሲታይ አገሪቱን በማዳረስ ከፍተኛ የሆነ ብሄራዊ ባህርይ ያለው ስራ የተሰራውና፣ ህዝብን ማደራጀትና መብቱንም አውቆ አዲስ የአሰራርና የአደረጃጀት ስልት እንዲማር ከፍተኛ ትግል የተደረገው። በጊዜው ህዝቡም በጎሳው ሳይሆን እንደ አንድ ህዝብ በመነሳት ነው አዲሲቱ ኢትዮጵያን ለመገንባት ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለው። ይሁንና ግን ይህንን የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች አንድ ላይ በመጣመር በህዝባችንና በአብዮቱ ላይ ዘመቻ ከፈቱባቸው። ጉግ ማንጉግን ከኢትዮጵያ ውስጥ ማስወገድ ያስፈልጋል በሚለው ቅስቀሳ የተወናበደው መሳፍንት፣ የሚሊታሪና የሲቪል ብሮክራት፣ እንዲሁም የነፃ አውጭ ድርጅቶች ነን የሚሉና፣ እራሱም የማርክሲዝምን ሌኒንዝም አርማ አንግቤያለሁ የሚለው በአንድነት በመነሳትና ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ድጋፍ በማግኘት አጠቃላይ ጦርነት አወጁ። በዚህ የተወናበደውና ከስር በሲአይኤ ይገዘገዝ የነበረው የወታደራዊ አገዛዝ እራሱም ጦርነት በማወጅ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አለቁ። ይህ የእርስ በእርስ መተላለቅ ለወያኔና ለሻቢያ የፖለቲካ ክፍተት ፈጠረላቸው። ስልጣን እንዲጨብጡና ለኢትዮጵያ ህዝብና ለአገራችን የመቶ ዓመት የቤት ስራ መስጠት ቻሉ። በዚህ ድርጊታቸው የብልጣ ብልጥ ስራ የሰሩ መሰሏቸው ነበር። ያልገባቸው ነገር ቢኖር ለራሳቸውም ነው ጉድጓድ የቆፈሩትና ዛሬ ህዝባቸውን ወደ ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተቱት። አንዳንድ የኦሮሞ ኤሊትም ይህንን ዐይነቱን ድርጊት እየደገመና ድንቁርናውን እያስመሰከረ ነው። እነዚህ ሁሉ ያልገባቸው ነገር ቢኖር የሚያካሄዱት ኢ-ሳይንሳዊ ቅስቀሳና የናሽናሊዝምን ስሜት ማራገብ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው ጥቁር ህዝብ ላይም ነው ጦርነት ያወጁት። ተግባራቸውም ቆሜለታለሁ የሚሉትን ህዝቦቻቸውን የሚጠቅም ሳይሆን የአረብ አገሮችንና የኢምፔሪያሊስት ኃይሎችን ነው። በዚህ ድርጊታቸውም የስልጣኔና የዕድገት ህልማችን እንዳለ ይወድማል። ጠቅላላው ህዝባችን ወደ ዲንጋይ ዘመን እንዲወረወር ይደረጋል። በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነት ቢከሰት አገራችንና ህዝባችን ብቻ ሳይሆኑ የሚጠቁት የአካባቢው አገሮችም በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳሉ። አገራችንም የግብጽ፣ የሱዳን፣ የአረብ አገሮችና የስለላ ድርጅቶች መጫወቻ ትሆናለች። ታሪኳና ባህሏ ይወድማሉ። ይህንን ዐይነቱን አሉታዊ ውጤት ነው ወያኔዎችና ዛሬ ጊዜው የእኔ ነው ብሎ እዚህና እዚያ የሚራወጠው አንዳንድ የኦሮሞ ኤሊት ግልጽ ሊሆንለት ያልቻለው።
በዚህ ዐይነቱ የታሪክ ወንጀል ሳይንሳዊና ፍልፍናዊ ባህርይ ሳይኖረው ዝም ብለው የኢትዮጵያዊነትን ስሜት የሚያራግቡ ኃይሎችም ተጠያቂዎች ናቸው። አብዮቱ ሊከሽፍ የቻለውና አገራችንም እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ ልትደርስ የበቃችው ለአሜሪካ ባደሩና ለሱ በሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ኃይሎች ነው። እነዚህ ናቸው ከውስጥ ሆነው አገዛዙን በመገዝገዝ አገራችንን ራቁቷን ያስቀሯት። እነዚህ የድሮ የሰራዊቱ አባላትና አሁንም ለአሜሪካ የሚሰሩ አንዳንድ ግልሰቦች ወጣቱንና ሰፊውን ህዝብ በማወናበድ በሌላ መልክ ደግሞ ፀረ-ኢትዮጵያ ድርጊታቸውን እያጡጣፉት ይገኛሉ። እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ አሜሪካዊነትን የሚያስቀድሙ በአርባዎቹና በሃምሳዎቹ ዐመታት ዕድሜ የሚገኙ የፖለቲካ መድረኩን በማጣበብ ኢ-ሳይንሳዊና ፍልስፍና አልባ ቅስቀሳ በማድረግ ህዝብን ግራ እያጋቡ ነው። ባጭሩ በፍልስፋና ላይ የተመረኮዘና ሳይንሳዊ መሰረት ያለው ትግል ስለማይካሄድ ሁሉም በተወሰኑ መፈክሮች ላይ በመሰባሰብ በተለይም ወጣቱን እያሳሳተው ነው። ይህንን ዐይነቱን ውዥንብርና ለስልጣን ላይ ለመውጣት የሚደረግ እሽቅድምድሞሽን መልክስ ለማሲያዝና ጥራት ያለው ትግል ለማካሄድ በጣም አስቸጋሪ ነው። ማንም የሚሰማም ያለ አይመስለኝም። ሁሉም የመረጠው ዝም ብሎ መደናገርን እንጂ ጥራት ያለውንና ተከታታይ ትግልን ማካሄድ አይደለም። ጥያቄው ከእንደዚህ ዐይነቱ የተዘበራረቀና የተወናበደ ሁኔታ እንዴት መውጣት ይቻላል? የሚለው ነው። ከሁሉም በላይ ከላይ የዘረዘርኩትን በብሄረሰብ አኳያ የሚካሄደውን፣ ከሳይንስና ከፍልስፍና ውጭ የሚደረገውን ትግልና ቅስቀሳ እንዴት መግታት ይቻላል? የሚለው ነው አስቸጋሪው ጉዳይ። በእኔ ዕምነት የተገለፀለት ኃይል እስከሌለ ድረስ የአገራችን ጉዳይ እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል። ስለዚህ ይህንን ሁኔታ ሊያስቀለብስ የሚያስችል ስትራቴጅ መቀየስ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።
የብሄረሰብ ወይም የጎሳ፣ የማንነት ጥያቄና የዋና ከተማ ጉዳይ !
በመሰረቱ ብሄረሰብ ወይም ደግሞ ጎሳ ሳይንሳዊ መሰረት የለውም። ጽንሶ ሃሳቦቹ ሊገለጹ የሚችሉ አንድ በጣም ውስን የሆነ ተገልሎና በስራ-ክፍፍል ያልተደራጀ ከሆነና በጣም በጠባብ አካባቢ የሚኖር የሰው ስብስብ ከሆነ ምናልባት ጎሳ ወይም ብሄረሰብ ብሎ መጥራ ይቻል ይሆናል። በሶሻል ሳይንስ እንደዚህ ዐይነቱ በባህል፣ በስራ-ክፍፍልና በሌሎች እንደስዕል በመሳሰሉት… ወዘተ. የማይገለጽ የሰው ልጅ ያልተነጣጠለ(Undifferentiated) ተብሎ ይጠራል። እንደዚህ ዐይነቱ የሰው ልጅ ደግሞ በአሁኑ የግሎባል ካፒታሊዝም ዘመን በተወሰኑ፣ እንደ ካሜሩን በመሳሰሉ ጫካዎች ውስጥ የሚኖሩ ፒግሚዎች ተብለው በመጠራት የሚታወቁና በፓፕዋ ኖይጊዩኒዋ(Papua Neuguinea) ውስጥ ከዘመኑ ስልጣኔ ተነጥለው ለሚኖሩ መጠሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችል ይሆናል። ወደ አገራችን ስንመጣ ግን ይህ ዐይነቱን ተነጥሎና በጋብቻ ሳይተሳሰሩና ሳይዋለዱ የሚኖሩ ፈልጎ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው። ይህም ማለት በአገራችን የታሪክ ሂደትና በህብረተሰብ ግንባታ ውስጥ መሰበጣጠሮች፣ መዘዋወሮችና፣ ከአንደኛው ጎሳ መጣ የሚባለው፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በግለሰብም ሆነ በጥቅል የተወለደበትንና ያደገበትን አካባቢ ጥሎ የሄደው ሌላ ቦታ ሄዶ አዲስ ኑሮ ሲመሰርት በስራ ወይም በንግድ አማካይነት ግኑኝነት ይፈጥራል፤ ይጋባል፤ ይዋለዳልም፤ ይራባልም። በዚህ ምክንያት የተነሳና በአንድ አገር ውስጥ ቀስ በቀስ እያለ በሚዳብረው የስራ-ክፍፍልና ንግድ፣ እንዲህም የከተማ ግንባታና የንግድ እንቅስቃሴ አማካይነት የተነሳ አዲስ ህብረተሰብአዊ ግኑኝነት(Social relationship) ይፈጠራል ማለት ነው። አንደኛው አንጥረኛ፣ ሌላው ነጋዴ፣ የተወሰነው ደግሞ የፋብሪካ ሰራተኛ፣ እንደዚሁም ደግሞ ሌላው የቢሮ ሰራተኛና ቢሮክራት በመሆንና፣ እንዲሁም በሌላ ሙያ በመስልጠን ከድሮው ባህላዊ ከሚባለው አስተሳሰብ እየተላቀቀ በመምጣት አዲስ ዐይነት የፍጆታ አጠቃቀምና አነጋገርም ይለምዳል ማለት ነው፤ ስነ-ልቦናውም ይቀየራል ማለት ነው። በዚህ መሰረት በአንድ አገር ውስጥ በገቢ ወይም በመደብ(Income or Social Classes) የሚገለጽ የህብረተሰብ ክፍል በመፈጠር ድሮ በጎሳ መልክ ይታይ የነበረው ግለሰብም ሆነ በጥቅል የሚጠራው እየሟሟ ይሄዳል። የለም በብሄረሰብ ብቻ የሚገለጽ ሰው ነው ያለው የሚባል ከሆነ ደግሞ እንደዚህ ዐይነቱ ግለሰብም ሆነ በጥቅል የሚጠራ ውስጣዊ-ኃይል የለውም ማለት ነው። የማሰብ፣ የመፍጠር፣ መሳሪያዎችን የመስራትና በንግድ አማካይነት የሚገለጽ ተግባርም ሊያዳባር አይችልም ማለት ነው።
ወደ ተጨባጩ የአገራችን ሁኔታ ስንመጣ ከትግሬ በስተቀር ሌሎች ዛሬም መጠሪያችን ይኸኛው ወይም ያኛው ብሄረሰብ ነው ብሎ እራሳቸውን የሚገልጹ ከሌላው ሳይጋቡ አልኖሩም ማለት ይችላል። በተለይም ከ15ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የክርስትና ሃይማኖት ወደ ደቡቡ ክፍል ሲስፋፋ ደብተራዎችና ቄሶች ለአስተማሪነት በመሄድና እዚያው በመኖር ከሌላው ጋር ተጋብተዋል፣ ተዋልደዋልም። እንደዚህም ግራኝ መሀመድ ባደረሰው እልቂት የተነሳ ከፍተኛ ክፍተት ስለተፈጠረ ኦሮሞዎች ከአንድ ቦታ በመነሳት ተስፋፍተዋል። በአንዳንድ ቦታዎች የነበሩ ስልጣኔዎችንና ነገስታትን በመደምሰስ ብዙ ቦታዎችን በቁጥጥራቸው አውለዋል። ከተቀረውም ሰው ጋር በመጋባት ተዋልደዋል። ይህም ማለት ዛሬ የኦሮሞ ኤሊት ነኝ ብሎ ችግር የሚፈጥረው በሙሉ ከዚህ ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ ጋር ሳይጋባና ሳይዋለድ በንጹህ መልኩ የሚገኝ አይደለም። ዛሬ የፖለቲካውን ሜዳ የሚቆጣጠሩትና ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉት ሁሉ በአባታቸው ወይም በእናታቸው ከአማራ ወይም ከሌላው ብሄረሰብ የሚወለዱ ናቸው። ይሁንና ግን ድርቅ በማለትና የጭቆናንና የመበደልን አርማ በማንገብ የኦሮሞ ብሄረሰብ ተሸማቆ እንዲኖር ተደርጓል፤ ተጨቁኗል፤ በቋንቋውም እንዳይናገር ተከልክሎ ነበር ይሉናል። በዚህም መልክ የተረት ተረት በማውራት የፖለቲካ ቲያትር በመስራት ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ለሰው ልጅ ዕድገት ከሚጠቀሙ ከባህላዊ ነገሮች እንድንረቅና ለህብረተሰብ ዕድገት በማይጠቅሙ ነገሮች ላይ ብቻ እንዳንረባረብ እያስገደዱን ነው። ዋና ዓላማቸው ጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ በእንደዚህ ዐይነቱ ሳይንሳዊ መሰረት በሌለው ነገር ላይ በመጠመድ ደንቁሮ እንዲኖር ለማድረግ ያሰቡ ይመስላል። ተልእኮአቸውም የአንድ የውጭ ኃይልን ዓላማ ለማሳካት ይመስላል። አገርን መበታተንና ጥሬ-ሀብትን ማዘረፍ። ተጨቁነናል የሚሉ ከሆነ ደግሞ እንዴት ማማር እንደቻሉና ወደ አውሮፓና ወደ አሜሪካ በመምጣት የተንደላቀቀ ኑሮ እንደሚኖሩ ሊያስረዱን በፍጹም አይችሉም።
ለማንኛውም ካለን ማረጋገጫ ቀደም ብለው የነበሩና አሁንም በህይወት የሚኖሩ አንዳንድ የኦሮሞ ብሄረሰብ አቀንቃኞች ሃዘል ብላት ከሚባል ለጀርመን የስለላ ድርጅት ይሰራ ከነበረና የኢትዮጵያ ጠላት ጋር የጠበቀ ግኑኝነት እንደነበራቸውና በእሱም እንደሚበወዙ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ሰውየው ከሞተም በኋላ ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚሰሩና ከአንድ ከሰሜን ጀርመን፣ ኸርማንስቡርግ ከሚባል ከተማ ካለ የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን ማንኛውንም ዕርዳታ እንደሚያገኙ የታወቀ ጉዳይ ነው። ቄሶቹም በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ ይመላለሳሉ። በተለይም ባለፉት 27 ዐመታት ወያኔ ያመቸቻለቸውን ሁኔታ በመጠቀም የኦሮሞን ናሺናሊዝም ሊያግሉት ወይም ሊያሞቁት ችለዋል። ባጭሩ ታሪኩ እንደዚህ ሲሆን፣ የእነዚህ ኤሊቶች ዓላማ ቆመንለታል ለሚሉት ብሄረሰባቸው ስልጣኔን ማምጣት ሳይሆን የአበባና የቡና ተካይ፣ እንዲሁም ለጀርመንና ለተቀረው የአውሮፓ ገበያ ልዩ ልዩ ፍራፍሬዎችን ተካይና ባርያ አድርጎ ለማስቀረት ነው ዋናው ዓላማቸው። ዓላማቸው ከዚህ ውጭ አይደለም ፤ ሊሆንም አይችልም።
ወደ ማንነት ጥያቄም ስንመጣ በጣም አስቸጋሪና ግልጽ ያልሆነ ጉዳይ አለ። ማንነት በምንድነው የምገለጸው? ዘለዓለማዊ ወይስ ጊዜያዊ ነው? በቋንቋ፣ በባህል፣ በስነ-ልቦና፣ በምግብ፣ በአለባበስ ወይስ በሌላ ነገር የሚገለጽ? ይህንን ጉዳይ በቀላሉ ለማስረዳት ያስቸግራል። የማንነትን ወይም የአይደንቲቲን(Identity) ጥያቄ የሚያነሱ በተለይም የፋሺዥም ወይም የቀኝ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ናቸው። እነዚህ ዐይነቶች በጀርመን፣ በፈረንሳይና እንዲሁም በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች እያደጉ የመጡና በተለይም ጥቁርን የሚጠሉ ናቸው። ዘራችን ንጹህ ስለሆነና የማሰብ ኃይላችንም ከሌላው የተሻለ ነው ብለው ስለሚያምኑ ከሌላው ጋር በመጋባት ዘራችን መበላሸት የለበትም በማለት ቅስቀሳ ያደርጋሉ፤ በአንዳንድ ቦታዎች ሰው ይደበድባሉ ወይም ይገድላሉ። ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር የማንነትን ጥያቄ የሚያነሱ በመሰረቱ ከእነዚህ ናዚዎች የሚለዩበት ነገር የለም። በሌላ ወገን ደግሞ የማንነትን ጥያቄ የሚያነሱ ከሆነ እነሱ ያልፈጠሯቸውን ነገሮች በሙሉ መጠቀም፣ መብላትና መጠጣት የለባቸውም። ይህን የሚያደርጉ ከሆነ ደግሞ ማንነታቸውን እረስተዋል ማለት ነው። ብዙም ሳያስቡ፣ ሳያወጡና ሳያወርዱ የሚናገሯቸው ነገሮች በሙሉ ችግር ከመፍጠር በስተቀር ለመፍትሄ የሚያገለግሉ አይደሉም። ስለዚህ በሳይንስ ከማይደገፍ አስተሳሰብ መላቀቅ አለባቸው። በመሰረቱ የፖለቲካ ዓላማ አለኝ የሚል ግለሰብም ሆነ ድርጅት ከሳይንስ፣ ከቲዎሪና ከፍልስፍና ውጭ ማሰብ የለበትም። ይህንን በግለሰብ ደረጃ ሊያደርግ ወይም ከጓደኛው ጋር በመሆን ሊያወራ ይችላል። በሌላ ወገን ግን እንደመቀስቀሻና ማስተማሪያ መሳሪያ እጠቀማለሁ የሚል ክሆነ መቀጣትና መከልከል ያለበት ነው። ስለሆነም ማንኛውም በብሄረሰብ የተደራጀ የፖለቲካ ዓላማ አለኝ የሚል የግዴታ መከልከል አለበት። በመሰረቱ በብሄር ደረጃ የተደራጀ ዲሞክራት ሊሆን በፍጹም አይችልም። ሳይንስን ሊያዳብር አይችልም፤ የማህበራዊ ጥያቄዎችንም ሊያነሳና እንደመታገያ ሊያደርግ አይችልም። በአጭሩ በብሄረሰብ የተደራጀ ኃይል የስልጣኔ ጠንቅ ነው። የአንድ አገር ህዝብ እንዳይሰባሰብና በጋራ ታሪክ እንዳይሰራ የሚያግድ ነው። የተፈጥሮንና የህበረተሰብን ህግ የሚፃረር ነው።
ወደ ዋና ከተማ ስንመጣ፣ በመሰረቱ ይህ ነገር ማወዛገብ የለበትም፤ ጉዳዩም ለውይይት መቅረብ ያለበት አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ በአንድ ብሄረሰብ ውስጥ መንደር ካልሆነ በስተቀር ብዙ ነገሮችን ሊያሟላ የሚችል ከተማ ሊመሰረት አይችልም። በሁለተኛ ደረጃ፣ የከተማ ዕድገት እንደ ህብረተሰብም ታሪካዊ ሄደት አለው። በመሆኑም ከተማዎች ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ሰዎች የሚገነቡትና ልዩ ዕምርታን(Melting points) የሚሰጡት የታሪክ ውጤት ነው። የከተማዎችን ዕድገት ስንመለከት በተደራጁ ገዢዎች የሚመሰረቱና በሂደት እያደጉ የሚመጡና የአንድ ብሄረሰብ መለያ ሆነው ሊቀሩ የሚችሉ አይደሉም። ከተማን ከተማ የሚያሰኘው ከተለያየ ቦታ የሚመጡ ሰዎች መጥተው ሲከትሙና የራሳቸውን የባህል ማህተም ሲያደርጉበት ነው። በዚህም የተነሳ እንደየሁኔታውና እንደ አገዛዞች የማሰብ ኃይል የተነሳ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ኃይሎች የራሳቸውን የውስጥ ኃይል በማዳበር ከተማዎችን የፈጠራና የልዩ ልዩ ባህል መገናኛዎች ያደርጋሉ ። ከዚህ ስንነሳ አዲስ አበባን የአንድ ብሄረሰብ መኖሪያ ለማድረግ የሚሞከረው ሙክራ ወይንም በዲሞግራፊ የህዝቡን ቁጥር ለመቀየር የሚደረገው ሽር ጉድና አሻጥር የአጭር ጉዞ አመለካከት ነው። አንድን ህዝብና የከተማን ዕድገትን ማቀጨጭ ነው። የሚገርመው ጉዳይ የውጭ ኩባንያዎች ወደ አዲስ አበባ በመምጣትና መሬት በመከራየት አፓርትሜንታዎች በመስራት ቅርምት ውስጥ ገብተዋል። በሌላ ወገን ደግሞ ኗሪው ህዝብ እንዲገፋ በመደረግ ላይ ነው። በአገራችን ምድር ዘረኝነት እየተካሄደ ነው ማለት ይቻላል።
መደምደሚያ !
ከላይ ከሞላ ጎደል ለማሳየት እንደሞከርኩት አንድን አገርና ህብረተሰብ ለመመስረት ብዙ ውጣ ውረዶችን መጓዝ እንደሚያስፈልግ ነው። በተለይም ደግሞ በህብረተሰብና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ንቃተ-ህሊና ወይንም እራስን በእራስ ማግኘት ከፍተኛውን ሚና ይጫወታሉ። ከጭንቅላታችን ውጭ የምናደርገው ነገር የለም። የሰው ልጅ ዕድገት ከታቻ ወደ ላይ ቀስ በቀስ የሚጓዝ ሲሆን አብዛኛውን ግዜ በደመ-ነፍስ የሚደረግ ሂደት ነው። የሰው ልጅ እንደ ጦጣ ዛፍ ላይ ከመንጠልጠል አልፍፎ አዳኝ ሆኖና አራሽ እስኪሆንና በስራ-ክፍፍልም እስኪያልፍ ድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል። ከፍልስፍና ጋር የኋላ ኋላ ደግሞ ከተፈጥሮ ሳይንስና ከሌሎች ዕውቀቶች ጋር የተለማመዱና ጥልቅ ምርምር ማድረግ የጀመሩ ጭንቅላታቸውን ሰብሰብ አድርገው አንድን ማህበረሰብ ሲመሰርቱ፣ እንደኛ ያለው አገር ደግሞ እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ ታሪክ ቢኖረው በውስጣዊ ድክመት የተነሳ ከዝቅተኛው ወደ ከፍተኛው ደረጃ መሸጋገር አልቻለም። የፖለቲካ ስልትን በማዳበርና ከውጭ የሚመጣውን በብዙ መልክ የሚገለጸውን አሳሳች ዘዴ መክቶ ለመመልስ ባለመቻል ከውስጥ በተታላይ ኃይሎች በመፈልፈል ለብሄራዊ ነፃነትና እንዲያም ሲል ለኢኮኖሚ ዕድገት ጠንቅ መሆን ተቻለ። የዚህ ዐይነቱ ክፍተት ለጥራዝ ነጠቅ ኤሊቶች አመቺ ሁኔታ ፈጠረላቸው።
በህብረተሰብ ግንባታ ውስጥ እንደተረጋገጠው ለጠንካራ ኢኮኖሚ፣ በተለይም ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ አትኩሮ የማይሰጥ አገዛዝና ምሁር የመጨረሻ መጨረሻ አገሩን ያስበላል። ይህ አንደኛው ሲህን፣ በመሰበጣጠርና በመበታተን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን አይቻልም። የአንድ ህዝብም በተለያየ መልክ የሚገለጽ ችግር በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው ሊፈታ የሚችለው። ሳይንስና ቴክኖሎጂ ደግሞ በአገር ደረጃ ነው የሚዳብሩት እንጂ በክልል ደረጃ አይደደለም። ምክንያቱም ማንኛውም ብሄረሰብ በክልል ደረጃ የሚወሰንና አትድረሱብኝ የሚል ከሆነ የማደግና የመበልጸግ ኃይሉ እጅግ ዝቅተኛ ይሆናል ማለት ነው። ወደ ዲንጋዩ ዘመን እንመለስ ካልተባለ በስተቀር አጣቃላይ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው በአገር አቀፍ ደረጃ ብቻ ነው። የሃሳብ መንሸራሸር ሲኖር፣ የሰው ኃይልና ካፒታል እንዲሁም ዕቃዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሽከርከር ሲችሉ ብቻ ነው አንድ ክልልም ሆነ አንድ አገር ሊያድግ የሚችለው። ስለሆነም እያንዳንዱ ጭንቅላቱ ውስጥ ከተከለው አጉል ጥላቻና ተንኮል፣ እንደዚሁም ቂም በቀል እስካልተላቀቀ ድረስ በማንኛውም ክልልም ሆነ በአገር ደረጃ በፍጹም ዕድገት ሊኖር አይችልም። ከዚህ ስንነሳ ምርጫችን ሁለት ነው። አይ ስልጣኔን፣ አሊያም የዲንጋይ ወይም ደግሞ የኋላ-ቀርነቱን ዘመን መምረጥ። መልካም ግንዛቤ !!