ከዓረና ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

 የዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉአላዊነት ፓርቲ ማእከላይ ኮሚቴ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን የካቲት 16 እና 17 ቀን 2005 ዓ/ም በመቀሌ ከተማ በስኬት አጠናቋል። ማእከላይ ኮሚቴው ባካሄደው በዚሁ ስብሰባ ባለፈው ዓመት ያከናወናቸውን ድርጅታዊ እንቅስቃሴዎችንና አጠቃላይ ሀገራዊና ክልላዊ ሁኔታዎችን በጥልቀት በመመልከት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ዓረና የምርጫ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን በሀገራችን በሚካሄዱት ሀገራዊ፣ ክልላዊና የአከባቢ ምርጫዎች ለመሳተፍ ምንግዜም ዝግጁ ቢሆንም የውድድር ሜዳው ባልተስተካከለበትና የፖለቲካ ምህዳሩ እጅግ ጠባብ በሆነበት ሁኔታ ፍትሐዊ ምርጫ ይኖራል ብሎ አያምንም። ለዚህ ሲባልም ከምርጫ 2002 ዓ/ም ጀምሮ ምርጫውን ነፃና ፍትሐዊ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙርያ ከገዢው ፓርቲ ጋር ለመደራደር ዝግጁነቱን ገልፀዋል። ይህ ዓረና አባል በሆነበት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ኣማካኝነት ለኢህአዴግ የቀረበው የድርድር ሰነድ ምርጫውን ነፃና ፍትሓዊ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ጉዳዮችን አካቷል። ከነዚህ ጉዳዮች መካከል 1) በሕገ መንግስቱ የሰፈሩት የመሰብሰብ፣ ሰልፍ የመውጣት፣ የመቃወም፣ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ 2) በተቃዋሚዎች ላይ የሚደርሱ የእስር፣ የወከባ፣ የድብደባ፣ ከስራ የማባረር ወዘተ ድርጊቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ 3) ነፃ ሚድያዎች ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት መረጃ እንዲያቀርቡና የመንግስት ሚድያዎች ለተቃዋሚዎች ክፍት ሁነው ፍትሓዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ 4) መንግስት ለተቃዋሚዎች የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርግ የሚሉ ይገኙባቸዋል።

መድረክ እነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች ቢያቀርብም ገዢው ፓርቲ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ምንም መልስ ላለመስጠት መርጧል። እንዲያውም ከጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ሕልፈተ ህይወት በኋላ በተቃዋሚዎች በአጠቃላይ በተለይ ደግሞ በዓረና ላይ በከፈተው የጥቃት ዘመቻ የፖለቲካ ምህዳሩ ጭራሽ እንዲዘጋ ለማድረግ ሞክሯል። ከነሐሴ 2004 ዓ/ም ጀምሮ የታሰሩ፣ ዛቻና ጥቃት የደረሰባቸውና ንብረታቸውን ያጡ የዓረና አባላት በርካታ ናቸው። ከሁሉም በላይ “ዓረናዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ተደስቷል” በማለት ህዝቡ ጥቃት እንዲያደርስባቸውና እንዲያገላቸው ለማድረግ የተደረገው ቅስቀሳ አስከፊ ነበር። የክልሉና የየዞኑ አመራሮችና ከፍተኛ ካድሬዎች ዓረናን “ጋሬጣ” በማለት ከመላው ትግራይ ጠራርገው ለማጥፋት ይፋዊ ውሳኔዎችን አስተላልፈዋል። ህዝቡና ተራው የህወሓት ኣባል ባይቀበላቸውም በፀጥታ ኃይሎች አማካኝነት ዓረናን አጥቅቷል። በገዢው ፓርቲ የሚመሩት ሚድያዎችም ከፍተኛ የማጥላላት ፕሮፖጋንዳ ኣካሂዷል። በዚህ ሁኔታ በምርጫ መሳተፍ ቀርቶ ህልውና ለማረጋገጥም ስለማይቻል ዓረና ከሌሎች 33 ፓርቲዎች ጋር በመሆን ለምርጫ ቦርድ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤትና ለተወካዮች ምክርቤት ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ የሚሆንበት ሁኔታ በተመለከተ ለመነጋገር አቤቱታ አቅርቧል። ሆኖም በጎ ምላሽ አላገኘም።

 

ዓረና ባለፈው ዓመት በተለያዩ ዜዴዎች በህዝብ ላይ እየደረሱ ባሉት ችግሮችና በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ዙርያ ያለውን አቋምና ተቃውሞ አሰምቷል። ከነዚህ መካከልም ገዢው ፓርቲ ለዓመታት በዜጎቻችን እጅ የነበሩትን ነባር የከተማ ቦታዎች በመንጠቅ በስመ ሊዝ በእጁ ለማስገባት ያወጣውን አዋጅ አንዱ ነው። ይህ የገዢው ፓርቲ ድርጊት ሕገ መንግስቱን ከመፃረሩም በተጨማሪ ዜጎችን የመንግስት ጭሰኛ ለማድረግና ለመቆጣጠር ያለመ መሆኑም አጋልጧል። አዋጁ ምልአተ ህዝቡ ቢቃወመውም አሁንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ ዓረና በጥብቅ ይቃወማል። አዋጁ በቤቶች ሽያጭና ግንባታ ያሳደረው ተፅእኖ የግንባታ ኢንዱስትሪው ጭራሽ እንዲሽመደመድ በማድረግ ስራ አጥነትን እንዳባባሰም ዓረና ይገነዘባል።

 

ዓረና በነጋዴው ሕብረተሰብ የተጫነውን ከባድ ግብርና ቀረጥ አስመልክቶም ያለውን ስጋት ገልፀዋል። ግብር መክፈል ዜግነታዊ ግዳጅ መሆኑን ቢያምንም የግብር ከፋዩን አቅም ያላገናዘበና ቅጥ ያጣ ግብርና ቀረጥ ኢኮኖሚውን እንደሚያቀጭጨው ነው የሚገነዘበው። አቅምን ያላገናዘበ ከባድ ግብርና ቀረጥ ዞሮ ዞሮ የሚሸከመው ህዝቡ ቢሆንም በተዘዋዋሪ ነጋዴውንም ከጨዋታ ውጭ ሊያደርግ ይችላል። በክልላችን የተገነዘብነውም ይኸው ነው። በርካታ ነጋዴ ድርጅታቸውን እንዲዘጉና አንድንዶቹም ክልሉን ለቀው እየሄዱ መሆናቸውን ዓረና ተገንዝበቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ስለ የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያዊው ቅጂ ሙዚቃ ከቴዲ አፍሮ የተሰጠ መግለጫ፡ "ጉዞው ይቀጥላል!"

 

የነጋዴዎችና የባለሃብቶች ፍልሰት ምንጭ በክልሉ የሚታየው ከባድ የግብር ጫና ብቻ አይደለም። በክልሉ ከላይ እስከታች የሰፈነው ብልሹ አስተዳደርም ሌላው ምክንያት ነው። በችሎታቸውና በእውቀታቸው ሳይሆን ለገዢው ፓርቲ ባላቸው ተአማኒነት የሚሸሙትና የሚመደቡት የመንግስት ሰራተኞች ህዝቡን እጅግ አስመርሯል። ጥራትና ቅልጥፍና ያለው አገልግሎት መስጠት ያልቻሉት እነዚህ የፓርቲ ታዛዦች ህዝቡን በማገልገል ፈንታ ህዝቡን የመቆጣጠር ሚና ያላቸው ናቸው። እንድያውም ሲቪል ሰራተኛው በሙሉ የድርጅት አባል እንዲሆን መመርያ ወጥቶ ለከፋ ብልሹነት ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። እጅግ ግዙፍ ነገር ግን ብቃት የሌለው ቢሮክራሲ ከክልል እስከ ቀበሌ ተዋቅሮ ህዝቡን የሚጨቁንበትና የሚያሸማቅቅበት ሁኔታ ፈጥረዋል። በአሁኑ ግዜ የእያንዳንዱ ቢሮ ሐላፊ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ወይም ከፍተኛ ካድሬ መሆኑ ትኩረቱ ህዝቡን ለመቆጣጠር እንጂ ለማገልገል እንዳልሆነ በግልፅ ያመለክታል። ታድያ በርካታ ነጋዴዎችና ባለሃብቶች ይህን ጫና ሊቋቋሙት ስላልቻሉ በመፍለስ ላይ ናቸው።

 

ዓረናን ካሳሰቡት ጉዳዮች መካከል የሙሁራን ፍልሰትም ተጠቃሽ ነው። ባለፈው ዓመት በርካታ ሙሁራን በክልሉ ያለው ከባድ ዓፈና ለመሸሽ ሲሉ ክልሉን እየለቀቁ ሂደዋል። ከሚፈልሱት ሙሁራን መካከል እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ያለው የመምህራን ፍልሰት ነው። በክልሉ ከተሰማሩት 27 ሺህ መምህራን ባለፈው ዓመት ብቻ ከ3% በላይ ስራቸውን ለቀዋል። ብዙዎችም ስራቸውን እየጣሉ ወደ ዓረብ ሃገሮች ተሰዷል። ለምሳሌ የአንድ ትምህርት ቤት ዲሬክተርና መማህራን በሙሉ በአንድ ግዜ በመጥፋት ወደ አረብ ሃገር እንደ ተሰደዱ ታውቀዋል። ይህ ክስተት እጅግ መሰረታዊ ችግር እንዳለ የሚያመላከት ነው። ይኸውም ምሁራን ቁሳዊና መንፈሳዊ እርካታ ያለማግኘታቸውን ነው። ኑሯቸውም እጅግ የወረደ ሲሆን የአካዳሚ ይሁን የሙያ ነፃነት ማጣታቸውም ኣሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ የሚያመለክት ነው። ይህ ሁኔታ በቋፍ ላይ ያለው የትምህርት ጥራት ችግር ይበልጥ እያባባሰው እንደሆነ መረጃዎች እያመላከቱ ነው።

ከፍ ሲል የተገለፀው የነጋዴዎችና የምሁራን ፍልሰት በህዝቡ ኑሮ ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ዓረና በሚገባ ተገንዝበዋል። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች መጓደላቸውን የክልሉ አጠቃላይ አቅም ዝቅ የሚያደርግ ሲሆን በተለይ የስራ አጡ ቁጥር ከፍ እንዲልም ያደርገዋል። ነጋዴው ሲያስተዳድራቸው የነበሩ ወገኖች ወደ ስራ አጥነት እንዲቀላቀሉ ሲያደርግ አዲስ ስራ ፈላጊዎችም ስራ እንዳያገኙ በር ይዘጋል። በመሆኑም በርካታ በአከባቢያቸው እየሰሩ መኖር የሚችሉ ወጣቶች ሃገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ያደርጋል። የዓረና ማእከላዊ ኮሚቴ በአሁኑ ጊዜ በክልሉ የሚታየው የወጣቶች ፍልሰትም ኣሳስቦታል። በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ሴቶችና ወንዶች እግር በመራቸው ወሰን እየጣሱ ወደ ዓረብና ሌሎች አገሮች በመፍለስ ላይ ናቸው። ለመሰደድ በሚያደርጉት ሙከራም ቀላል የማይባል ሃብትና ህይወት እየወደመ ይገኛል። የአውሬና የዓሳ እንዲሁም የዘራፊዎች ሰለባ የሚሆኑ ወጣቶች በየጊዜው እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው። ሁኔታው በዚህ ድርጊት ለተሰማሩ ማፍያዎች የተመቻቸ ሆኖዋል።

 

በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ያለው የስራ አጦች ብዛት እጅግ ከፍተኛ ነው። ከ5 ሺ በላይ ከዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ወጣቶች በስራ አጥነት እየተሰቃዩ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ሁለተኛና የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ስራ አጥ የሆኑት ደግሞ በአስር ሺዎች ይቆጠራሉ። መንግስት ስራ ላይ ናቸው የሚላቸው ቢሆኑም በማይመጥናቸውና ህብረተሰቡን በሚያከስር ተግባር የተሰማሩ መሆኑን ግልፅ ነው። የዩኒቨርሲቲ ትምህርት አጠናቀው በኮብል ስቶን ማንጠፍ ስራ ላይ የተሰማሩት ወጣቶች ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ኪሳራ ነው። ያልተማረው ስራ አጥ ሊሰራ በሚችለው መስክ የተማረውን ማሰማራት ከግልም ይሁን ከህብረተሰብ ጥቅም አንፃር ሲታይ ኪሳራ ነው። መንግስት ባላሃብቶችንና ምሁራን በነፃነት እንዲሰሩ በማድረግ አዳዲስ ስራዎች ከመክፈት ይልቅ ምሁራንን በድንጋይ ፈለጣ ማሰማራቱ የላቀውንና ከባዱን የልማት ስራ ለመስራት ብቃት እንዳጣ የሚያመለክት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጄ/ል ክንፈ ወንድም የሆኑት አቶ ኢሳያስ ዳኘው ለቀረበባቸው ክስ መቃወሚያቸውን አሰሙ

 

ሌላው ዓረና የተመለከተው ጉዳይ በገጠር ያለውን ሁኔታ ነው። “ገበሬው ሚልዮነር እየሆነ ነው! ከፍተኛ ሃብት እያፈራ ነው” በማለት ነጋ ጠባ በመንግስትና በድርጅት መገናኛ ብዙሃን ቢለፈፍም ሀቁ ከዚህ የተለየ እንደሆነ ዓረና ይገነዘባል። አሁንም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎች በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ የእርዳታ ጠባቂ እንደሆኑና በተለይ በደቡብና በምስራቅ የክልሉ አካባቢዎች ያሉ ገበሬዎች የረሃብ ሰለባ እንደሆኑ ግልፅ ነው። ከዚህ ሌላ በዘመቻ መልክ የሚካሄደው የመስኖና የግደባ ስራ እንደሚባለው 50% ማሳዎችን ሊሸፍን ቀርቶ የዚህን ግማሽ እንኳ ያላካተተ ሲሆን በአስገዳጅ የሚካሄደው የማዳበርያ ግዢ ገበሬውን እያንገሸገሸው እንደሚገኝ ይስተዋላል። ገበሬው ለማዳበርያ ግዢ ሲል የሚበደረው ገንዘብ መክፈል እያቃተው ንብረቱንና ከብቱን በርካሽ ዋጋ ለመሸጥ እየተገደደ እንደሆነም ግልፅ ነው። በስመ የልማት ሰራዊት ገበሬውን በባርነት ጠፍሮ የያዘው አካሄድ በነፃነት እንዳያስብና እንዳያለማ ስላደረገው አሁንም ገጠሩ ችግርና ድህነት የተጫነው ሁኗል። ከዚህ የተነሳም በርካታ የገጠር ወጣቶች ለስራ አጥነትና ለስደት ተዳርገዋል።

 

በገዥው ፓርቲ ሞት የተፈረደበት ሌላው ዘርፍ ትምህርት ነው። የመማር ማስተማር ሂደቱ በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ተፅዕኖ ስር ስለሆነ የትምህርት ጥራቱ በየግዜው እያሽቆለቆለ በመሄድ ይገኛል። በየዓመቱ ጥራትን ለማረጋገጥ ይረዳሉ የተባሉ ፓኬጆች ተግባራዊ እየሆኑ ነው ቢባልም የመማር ማስተማር ሂደቱ በፕሮፖጋንዳ ስብሰባዎች ስለተጠመደና አመራሩም በካድሬዎች ቁጥጥር ስር ስለሆነ ጭራሽ መሻሻል ሊታይ አልቻለም። እንዲያውም ከ ከክፍል ሞኒተር እስከ ትምህርት ሚኒስተር በፖለቲካ ሽሞኞች መያዝ አለበት የሚለው የገዢው ፓርቲ አስተሳሰብ ሙያተኞችን የሚገድል ሆኗል። ይህ ካሄድ እስካልተለወጠና ለሙያና ብቃት ቅድምያ እስካልተሰጠ ድረስ ደግሞ የትምሀርት ጥራት ፈፅሞ ሊሻሻል እንደማችል ግልፅ ነው።

ዓረና በሀገራች አዳዲስ የፖለቲካ ክስተቶች እየተስተዋሉ መሆኑም ተገንዘቧል። በተለይ ገዢው ፓርቲ ሁሉንም እንቅስቃሴና ተቋም ለመቆጣጠር ካለው ፍላጎት የተነሳ በሃይማኖት ተቋማት የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት አደገኛ አቅጣጫን እየተከተለ ይገኛል። ከሌላው ሃይማኖት ጋር ተግባብቶ የመኖር ባህል ያላቸውን የሱፊ እስልምና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውን “አልሓባሽ” በተባለው እምነት ለመተካት ያደረገው ጣልቃ ገብነት ያስከተለው ችግርና መጅሊሱን (ኣመራሩን) በራሱ ደጋፊዎች ለመቆጣጠር ያደረገው ሙከራ ያለመረጋጋትን እየፈጠረ ይገኛል። ጉዳዩን በሕገ-መንግስቱ ዓንቀፅ 14 የሰፈረውን “መንግስት በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ መግባት የለበትም” የሚለውን ድንጋጌ መሰረት በማድረግ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ይባስ ብሎ “ጥያቄ አቅራቢዎች ሽብርተኛ ናቸው” በማለት ችግሩን ኣባብሶታል።  ከ1/3 በላይ ሙስሊሞች ባሉባት ሃገር ሁሉን ነገር መቆጣጠር ይኖርብናል በሚል አጉል አካሄድ የሚፈጠረው ችግር ለገዢዎች ብቻ ሳይሆን ለህዝቡም የሚበጅ ስላልሆነ ጣልቃ ገብነቱ መቆም እንዳለበት ዓረና ያለውን አቋም ይገልፃል።

 

ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ የተስተዋለው ሌላው ክስተት ደግሞ የኢትዮጵያ ጥቅም ያላገናዘበውንና ሉአላዊነታችን አደጋ ላይ የሚጥለውን የሰላም ድርድር ለማድረግ ለሻዕብያ የሚደረገው ጥሪ ነው። በተለይ በአቶ በረከት ስምዖንና በጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የተደረጉት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ድርድር ለማድረግ ዝግጁ ነን የሚሉ አገላለፆች የኢትዮጵያን ጥቅም ያገናዘቡ እንዳልሆኑ ዓረና ተገንዝቦታል። “የሄጉ ፍርድ ቤት ሕገ ወጥ ውሳኔን ተቀብለን ባድመን ለሻዕብያ አሳልፈን እንሰጣለን፣ የባህር በር ጥያቄ ጊዜው ያለፈበት የጦርነት ናፋቂዎቸ ጥያቄ ነው፣ አዲሱ ትውልድ የባህር ጥያቄ ቀርቶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንደነበረችም አያውቅም” በማለት አቶ በረከት ከኤርትራውያን ጋር ያደረጉት ውይይት ዓረናን እጅግ እንዳስቆጣውና በጥብቅ እንደሚያወግዘውም በዚህ አጋጣሚ ይገልፃል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በዳያስፖራ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት ግብረ ኃይል መግለጫ ሰጠ

 

የዓረና ማእከላዊ ኮሚቴ ከፍ ብለው የተገለፁትን ጉዳዮች በጥልቀት የተመለከተ ሲሆን እነዚህን መሰረት በማድረግም የተለያዩ ውሳኔዎችንና ጥሪዎችን አስተላልፈዋል። በዚህ መሰረትም፤

 

1ኛ) ገዢው ፓርቲ በዓረና አባላት ላይ እያደረሰ ያለውን ወከባ፤ እስርና ጥቃት እያወገዘ አባሎቻችን ይህን ከባድ ጫና ተቋቁመው ያደረጉትን አመርቂ እንቅስቃሴ ያደንቃል። በተለይ ባለፉት ስድስት ወራት “ዓረና አመኬላ ነው፣ ጋሬጣ ነው” በማለት በሰላማዊ ትግላችን ላይ የከፈተው ዘመቻ ሕገ-መንግስቱን ያልተከተለና በህዝቡ ላይ አምባገነናዊ አገዛዙን ለመጫን ያደረገው ስለሆነ በጥብቅ ያወግዘዋል። የዓረና አባላት በማህበራዊ ህይወት እንዳይሳተፉ፣ በነፃነት ሀሳባቸው እንዳይገልፁ፣ የዕለት ተዕለት ኑራቸውን እንዳይመሩ በገዢው ፓርቲ የሚደረገውን ጫና እንዲቆምም እናሳስባለን።

 

2ኛ) በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ የሚገኙ የዓረና ድጋፍ ኮሚቴ አባላት ዓላማችንን ለማስተዋወቅና እንቅስቃሴያችንን ለመደገፍ ያደረጉትን ብርቱ ጥረት እያደነቅን ለወደፊትም የጀመሩትን እንቅስቃሴ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

 

3ኛ) ምሁራን የሙያና የኣካዳሚ ነፃነት ተነፍገው በገዢው ፓርቲ አስተሳሰብ ብቻ እንዲነዱ የሚደረገው ሙከራ፣ ነጋዴዎች በግብር ጫናና በብልሹ አስተዳደር ተማርረው ከስራ ውጭ እንዲሆኑ የሚደረገው አካሄድ፤ ገበሬው በአስገዳጅነት እንዲደራጅ፣ ብድርና ማዳበርያ እንዲወስድ የሚደረገው ጫና፣ በክልሉ መልካም አስተዳደር፣ ዘላቂና አስተማማኝ ልማት እንዳይኖር የሚያደርግ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ነፃነታቸውን የሚያረጋግጡበት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ጥርያችንን እናቀርባለን። ገዢው ፓርቲ በተሰዉት ታጋዮች ስም እየተማፀነ፣ ”በመለስ ራዕይ” መፈክር እያሰማ፣ ተቃዋሚዎችን በጠላትነት እየፈረጀ የዓፈናና የምዝበራ አገዛዙን ለማስቀጠል የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተገንዝባችሁ መብቶቻችሁን ለማስከበር ተንቀሳቀሱ። በዚህ አጋጣሚ የምናደርገውን እንቅስቃሴ በሞራል፣ በሀሳብ፣ በገንዘብና በቁሳቁስ ትግላችንን የደገፋችሁ ሁሉ ምስጋናችንን ይድረሳችሁ እንላለን። በቀጣዩም ድጋፋችሁን በተጠናከረ መንገድ እንድትቀጥሉ በድጋሚ ጥሪ እናቀርባለን።

 

4ኛ)  ዓረና ከተመሰረተ ማግስት ጀምሮ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ጥምረት በመመስረት ሲንቀሳቀስ ቆይተዋል። ይህ “መድረክ” በሚል የሚታወቀው ጥምረት በአሁኑ ግዜ ወደ ግንባርነት ተሸጋግሮ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል። ዓረና በሀገራችን ጠንካራ ተቃዋሚ ኖሮ ህዝቡ አማራጭ የሚያገኝበት ሁኔታ እንዲመቻች አሁንም ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ወስኖዋል። መድረክ ጠንካራና የህዝበ ተአማኒነት ያለው አማራጭ ሆኖ እንዲወጣም የበኩሉን ድርሻ ማበርከት እንዳለበት ተስማምተዋል። መድረክ በአደረጃጀት፣ በአሰራርና በዓላማ ይበልጥ መቀራረብና ፈጥሮ ህዘቡ የሚፈልገውን ነፃነት፣ መልካም አስተዳደር፣ ዘላቂ ልማት እንዲረጋገጥ ጠንክሮ እንዲታገል ለማድረግ እንዲሰራም ተስማምተዋል። መድረክ የገዢውን ፓርቲ ጫና ተቋቁሞ ህዝቡ ዘንድ በመዝለቅ የማስተማርና የማደራጀት ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ወስኗል።

 

5ኛ) ዓረና በሕገ ደንቡ መሰረት ፖሊሲዎችንና እስትራተጂዎችን ለማፅደቅ፣ ፕሮግራሙንና ሕገ-ደንቡን ለማሻሻል፣ አመራሩን ለመምረጥ የሚችለው የድርጅቱን የበላይ አካል በሆነው ጉባኤ ነው። እስካሁን ድረስ ሁለት ጉባኤዎችን ያካሄደ ሲሆነ ከወራት በኋላም 3ኛ ጉባኤውን ለማካሄድ ዝግጅቱን ጀምረዋል። በዚህ መሰረትም በአሁኑ የማእከላይ ኮሚቴ ስብሰባው 9 አባላት ያቀፈ የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ አቋቁሟል። ይህ ከማእከላዊ ኮሚቴ፣ ከቁጥጥር ኮሚሽንና ከድርጅቱ አባላት በእኩል ቁጥር የተቋቋመው ኮሚቴ ድርጅቱን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ዝግጅት እንዲያደርግ የሚጠበቅ ሲሆን በዚህ አጋጣሚ ስራው የተቃና እንዲሆንለት የዓረና ማእከላዊ ኮሚቴ ይመኛል።

1 Comment

Comments are closed.

Share