” ሺ ቢታለብ ያው በገሌ …፡፡“ – በመኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

  “ ሺ ቢታልብ ያው በገሌ ነው፡፡“ አለች ድመት ይባላል፡፡ “ድመት አለች“ ተባለ እንጂ ፣ ምን ቢደክም ፣ምን ቢለፋ፣ወትት ከምትሰጠው ላም ጋር ስቃዩን ቢያይም ፣ወተቷን አልቦ ሲያበቃ፣ለቀን ሙሉ ድካሙ ፣የማይመጣጠን ምንዳ እንጂ፣ተጨማሪ አንድ ማንኪያ ወተት እንኳን ስለማይሰጡት፣የህንን ኢ- ፍትሃዊ ድርጊት በማስተዋል ነው፤ አላቢው፣ “ ሺ ቢታለብ ያው በገሌ ነው የሚሰጠኝ ፡፡ “ ያለው፡፡ በጥቅሉ ለሥራው ተመጣጣኝ ክፍያ አይከፈለውም እና በአሠሪው ብዝበዛ ተማሯልም ልንል እንችላለን፡፡
      በእርግጥ ድመት ይህንን ጥየቄ ብታቀርብ ፣ከቶም ሳትሰራ ፣ሳትጥርና ሳተግር፣በምርት ሂደቱ አንዳችም አስተዋጾኦ ሳታደርግ፣ጥጃ አሳድጋ ፣ለጊደርና ለላም አብቅታ ፣አስጠቅታ በማስረገዝ ፣ጥጃ ሣታሥገኝ ፣የላሟን ወተት “ በድስት “ ወይም “ በባሊ “ ይሰጠኝ ብላ የመጠየቅ መብት ከቶም የላትም፡፡
    ተረቱን እንደ ድመት ክሥ ካየነው፣የድመቲቱ ክሥ ኘና ወቀሣ  ተገቢ አይደለም፡፡ የምንልበት አምክንዮ አናጣም።
   ” ድመቲቱ በአንድ ዘመናዊ እና የዐይጥ ዘር ፣ ዝር በማይልበት ፣ወተት ግን በበዛበት ፣ የጠገበ ሐብታም ቤት ከሆነ የተቀመጠችው፣ በዲታው፣የበዛ ቆንቋናነት ልትገረም፣ልትራገም፤ በስስታምነቱ፣ልትፈርጀው ና በስግብግብነቱ ልታማው አትችልም፡፡ “ብለን መፍረድ እንችላለን።
     ይሁን እንጂ፣ ይህቺ ላም በሀገር ብትመሰል፣ወተቷ የሀገር ሀብት ነው ና ሺ ቢታለብ ያው በገሌ ነው፡፡የሚለው አባባል፣ቁጭትን እና ተገቢ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል ያለመኖሩን የሚያሳይ ነውና ! ሀገርን ለሚመራ መንግስት ተረቱ በዋዛ የሚታይ አይሆንም፡፡
       ኢ-ዲሞክረሲያዊና አምባገነናዊ መንግስት ባለበት ሀገር ውስጥ፣የወተቱ ወይም  ” የሀብቱ ምንጭ “የሆነቸው ” ሀገር “፣ ግለሰቦች ፣ በቡድን ተደረጀተው፣በነፍጥ ፣ በዘብጥያ ና በአከሮባጅ ወዘተ፡፡እያስፈራሩ፣ዜጎች ጸጥ፣ለጥ ብለው እንዲገዙ በማደርግ ፣ ያለአንዳች ሃይ ባይ ወተቱን የሚጨልጡ  ፤ በጥሬውም ወተቷን ወደውጪ በመቸብቸብ ራሰቸውን እና ኪሳቸውን የሚያሳብጡ ከሆኑ ፤ በዚች ሀገር  ” የሺ ቢታለብ ያው በገሌ ነው ።” ተረት ቢተረት ተረቱም አውነተኛ ሽብርን ቢወልድ ከቶም አይገርምም፡፡
     ታሪክ ደጋግሞ እንደመሰከረው፣ “በገዛ ዳቦዬ ልብልቡን አጣሁት፡፡“ ባይ ከበዛ ወይም“ ሺ እየታለበ በማንኪያ የሚሰጠው ከበዛ “ በግልፅ አነጋገር “ህዝብ የበይ ተመልካች“ ከሆነ፣በሩን ዘግቶ ከመሰሎቹ ጋር የሀገርን ሀብት እየተቀራመተ ያለውን ገዢ ኃይል ከመንበሩ መገፍተሩ አይቀሬ እንደሆነ ከታሪክ እንረዳለን፡፡  ለምሳሌም የቀዳማዊ ኃይለሥላሤን የኢትዮጵያን ንጉሰ ነገሥት እና ግብታዊዉን የኢትዮጵያን አብዮት ለምሳሌ መጥቀስ ለዚ ጊዜ ትልቅ ማስፈራርቾ እና የማስጠንቀቅያ ደውል ይመስለኛል፡፡
    ይህ አብዮታዊ ክስተት፣የገበሬውን፣የላባ
አደሩን፣የነጋዴውን፣የወታደሩን ወዘተ ጥያቄ ይዞ፣ ቀስ፣በቀስ ፣ከነውጥና ከጥገናዊ ለውጥ ወደስር ነቀል አብዮታዊ እንቅስቃሴ በመሸጋገር፣በወታደራዊው ኮሚቴ(በደርግ) አማካኝነት ፣ንጉሱን ከዙፋናቸው በማውረድ፣ያለፍርድ የቀኃሥን ቁንጮ ባለስልጣናት ሲረሽን ፣ዳር ቆሞ የሚታዘበው ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ “ሺ ቢታለብ ያው በገሌ ነበር…“ በሚል አንድምታ ነብር ከቀኃሥ ጎን ያልተሰለፈው፡፡…
     በነገራችን ላይ ፣ ዛሬም  የህዝብ ፣ ጥያቄ የሊሂቃኑ የርእዮተዓለም ፣ የዘር ፣ የጎሣ ፣ ወይም ይሄ ፖርቲ የኔን ቋንቋ ሥለሚናገር ፣ቢገለኝም እርሱ ይግደለኝ የሚል አልነበረም።
  ልብ በሉ ፣ ለመኖር የሚያሥፈልጉ ፣ መሠረታዊ ጥያቄዎቹ ያልተመለሰለት ህዝብ ፣ ሥለአይዲኦሎጂ ፣ ሥለቋንቋ ፣ሥለማንነት ፣ሥለዘርና ጎሣ አይጨነቅም። ይሁን እንጂ በህዝብ ሥም የሚነግዱና ጠቀም ያለ ትርፍ ያገኙ ይኽ የሀብት ምንጭ የሆነ ሥርአት እንዳይኮታኮት  ይጨነቃሉ።
   ሥለሆነም ዛሬ እንዳሥተዋልነው ፣ እድሜ “ለሤራ    ፖለቲካ በብዙሃን ሥም የግል ትርፍ አምጪ ነውና    ፣በ27  ዓመት ውሥጥ ካገኙት ደጎሥ ያለ  ጥቅም አንጻር አዋጭነቱን  የተገነዘቡ ፣ ይህንን ጥቅማቸውን ለማሥቀጠል ፣ በሚረዳቸው ፣በህገ መንግሥቱ ውሥጥ በሰፈሩ ከፋፋይ ፣ ህጎች በመታገዝ ፣ ዳቦ እንዳታገኝ ፣መጠለያ እንደይኖርህ እና እንደትታረዝ ያደረገህ ህገመንግሥቱ ባልፈቀደለት ክልል ያለው የእገሌ ብሔር ነው።ወዘተ በማለት ፣ ወንድማማች የሆነው ህዝብ እርሥ በእርሱ እንዲጋጭ  የሚያደርጉት የግል ጥቅማቸውን፣ምቾትና ድሏታቸውን ለማሥቀጠል እንዱሆነ የዋሁ ፣የሴራ ፖለቲካ ያልገባው ህዝብ አያሥተውለውም።
 የሤራ ፖለቲካው ተጠቃሚ የሆኑ ሊሂቃን ፣ ያኔ በሽግግር መንግሥቱና በምክር ቤትም   በነ ሻለቃ አድማሴ ፣ተው፣እረፉ።ይህ መንገድ አያዋጣም።ተብለው ነበር።
       እናም ፣   ህዝብ  ተጠቃሚ የልሆነበት ሥርዓት  ፣የሥርዓቱ መንኮታኮት ፣ ህዝብን ፈፀሞ ሊያስከፋው ከቶም አይችልም፡፡  (ትላንት የሱዳኑ መሪ ከነበሩት  ከአልበሽር ውድቀት ያሥተዋልነውም ይህንን እውነት ነው።) እነኳን ተጨቋኙን በቅርብ ከሥርዓቱ ጋር በመኖር ፣በቅንነት አገልግሎ ምንም ጠብ ያለለለትን የሥረዓቱን አገልጋይ ወይም ፖሊሲ አስፈፃሚ ፣ የሥርዓቱ መንኮታኮት ፈፅሞ አያሥከፋውም፡፡ይህንን ጉዳይ በተረት ላጠናክረው ፡-
      “በደሮ ጊዜ ፣ብቻውን በመብላት እጅግ የፈረጠመ ጡንቻ ያፈራ ፣በኃያልኛ ጉልበቱም፣ እጅግ ጥብቅ የሆነ ፣ በረት እየደረመስ ፣የገበሬዎችን ከብቶች፣ ዘርፎ የሚበላ  ከራሱ ሆድ ውጪ ቤተሰቡ እንኳ ትዝ የማይለው  ጅብ ነበር፡፡የህ ስግብግብ ጅብ ፣” መንጆለላና መዝሩጥ ” የተባሉ ልጆች ነበሩት፡፡እነዚህ ልጆች በእናታቸው እቅፍ ሳሉ፣እናትየው የአባታቸውን ስግብግብነት እየተረከችና ለአቅመ አደን ሲደርሱ ፣በተቻለ መጠን ለብቻቸው በማደን ፣ህይወታቸውን ለማቆየት መጣር አለባቸው እንጂ፣ከቶም በአባታቸው እነዳይተማመኑ ትመክራቸው ነበር፡፡በምክሯም መሰረት፣ጥንቸልና ሚዳቋ እያደኑ፣ራሰቸውን ያኖሩ ነበር፡፡
“ከዕለታት አንድ ቀን ያ ስግብግብ አባታቸው ፣ከእርሱ ጋር ወደ አደን እንዲሄዱ ጎተጎታቸውና  አብረው ወደ አደን ተሰማሩ።በምክክራቹውም  ከአንዱ ገበሬ በረት አህያ ወይም ጥጃ በኃይል ጎትቶ በማውጠት በጋራ ለመብላት ተስማሙ።
   “በእቅዳቸው መሰረትም ፣   ልጆቹ መሬቱን በመጫር መግቢያውን ሲመቻቹለት፣አባትየው በጉልበቱ ብርታት በረቱን ደርምሶ አንዱን ጥጃ እየሥጮኸ እየጎተተ ወደሜዳ አወጥቶ ሲያበቃ፣ልጆችን  እንዳይካፈሉት  በመዳፉ እየመታ ና በጥርሱ እያሥፈራራ  ከበረረ በኋላ፣ አንጀቱን ዘርግፎ ሙዳ፣ሙዳ ሥጋ ብቻውን ይውጥ ጀመር፡፡
    “አንደኛው ልጁ መንጆለላም ቁልጭልጭ እያለ ሲያየው፣የጥጃውን አንድ ጆሮ ወረወረለት፡፡ወዲያው የመንደሩ ሰዎች መጥረቢያ፣ጦርና ዱላቸውን ይዘው ከየቤታቸው ሲወጡ፣ መዙርጥ አየና ለመንጆለላ በጆረው የሰዎቹን አድፍጦ ወደአባታቸው መጠጋት ሹክ አለው ና      ተያይዘው በማፈግፈግ፣ በጥሻ ውስጥ ተዱብቀው  የአባታቸውን መጨረሻ መመልከት ጀመሩ፡፡
“የስግብግቡ ና የሆዳሙ ጅብ ተግባር ያናደዳቸው የመንደሩ ሰዎች ለካስ ተማክረው ኖሮ ፣ጅቡ እንዳያመልጣቸው ከበባቸውን አጥበው ቀረቡትና ፣ኮሽታ ሰምቶ ገና ቀና እንዳለ ፣ ጦር የያዙት ወርውረው ሆዱ  ና አንገቱ ላይ ወጉት ፣እየተደፋንደፈ ለማምለጥ ሲሞክር የተሳለ መጥርቤያ የያዘ አንድ ፈርጠም ያለ ጎረምሳ ጋር ደረሰና ጭንቅላቱን ሲለው በአፍጢሙ ተደፍቶ፣
‘ልጄ መዝሩጥ!‘ ብሎ እንዲያድነው ሲጣራ
‘ብቻህን እንደበላህ እስቲ ብቻህን ሮጠህ አምልጥ!‘ ሲለው፣ተስፈ ቆረጠና
‘ልጄ መንጆለላ!‘ብሎ ተጣራ፡፡መንጆለላም፡-
‘መች ሰጠኸኝ ከአንድ ጆሮ ሌላ!‘ ሲል መለሰለት፡፡ የዚን ግዜ እምም!እምም!እምምምም!…ብሎ በቁጭት በመጮኽ ሞተ፡፡“ ይባላል፡፡
   ተረቱ የሚያስረዳን የራሴ ነው፣የሚሉት ሰው፣ እንኳን ፣ ከዘረፋው ተካፋይ ካልሆነ፣ዘራፊው ሲወድቅ ፣ለመርዳት  ይቅርና  ዞር ብሎ ለማየት  እንደማይሞክር ነው፡፡
  ማንም ከህዝብ ተርታ የተሰለፈ ፣በሌብነት ተግባር ያልተባበረ፣ የጥቅም ተጋሪ ያልሆነ  ና ከላሚትዋ ወተት ቢያነስ በጣሳ ያልደረሰው፣ ያንን በሱ ስም ሲነግድ የነበረውን አልጠግብ ባይ፣ሥግብግብ፣አስመሳይ፣አዛኝ ቅቤ አንጓች፣ጨቋኝ ገዢ ሲወድቅ ለማንሣት አይዳዳም።
      ህዝብ ጨቋኞችን ከስልጣናቸው አውርዶ ሲያበቃ ፣ቀን ወደማይሰጠው እንጀራው ላይ ይሰማራል፡፡በዛ ደም መጣጭ ምትክ የተተካው ፣የህዝብን  ህጋዊ የሀብት ክፍፍል ጥያቄ ፣ እንደሚፈታ ና  የህዝብ አካል የሆነው እርሱም  (ግለሰብ) ወተቱን በሚገባው መጠን  እንደሚያገኝ ተስፋ በማደርግ፡፡
     ይህ በቀን ሦሥቴ ለመብላት ያልታደለው ና ይህንን የዘመናት ፍላጎቱን በየዘመኑ የሥልጣን አናት ላይ በውዴታው ና ያለውዴታው ፊጥ እንዲል የደገፈው መንግሥት እንዳላላደረገለት ተገንዝቧል።
    በስሙ ሲምልና ሲገዘት የነበረ ፣አፈ ጮሌ ሁሉ ፣የአገዛዙን እርካብ ከተቆናጠጠ በኋላ ፣ በራሱ ሥግብግብነትና በውጪ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች አሻጥር የልቡን ፍላጎት እውን ሊያደርግለት እንዳልቻለም ይረዳል፡፡
       በየዘመኑ በህዝዊ አመፅ እና፣እንቢ አልገዛም ባይነት ፤ ከስልጣን የፈነገላቸው ከምንዱባንነት ስላላላቀቁት መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ከስልጣናቸው ዳር እስከዳር በተቀጣጠለ አመጽ እና አብዮት ሲፈነገሉ፣ “ሺ ቢታለብ ያው በገሌ ነበር እሰይ ፣እንኳንም ተፈነገሉ! “ በማለት ከለውጥ ኃይሎች ጋር በየዘመኑ ህዝብ በነቂስ በመውጣት የተሰለፈውም ያልፍልኛል ብሎ እንደ ሆነ መዝንጋት የለበትም፡፡
    በህዝባዊ አመፅና እንቢተኝነት፣ ለስልጣን የበቃው የዛሬው የለውጥ ኃይል የሀገርን ወተት ፣ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን በእኩል እንዲዳረስ ማደረግ ካልቻለ፣ነገ፣ተነገ ወዲያ፣ እጣ ፈንታው እንደቀደምቶቹ መሪዎች ይሆናል፡፡ከቀደሙት የሀገር መሪዎች ስህተት የማይማር ፣ያንኑ ስህተት ሊደግም ይችላልና!
ትላንት የነበሩት መሪዎች የመላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ በቅጡ አልተረዱም፡፡ተገቢውንም መልስ አልሰጡም፡፡ “የኢትየጵያ ህዝብ ጥያቄ ፣የዘር ብልጫነት ወይም የቆዳ ማወደድ ጥያቄ ነው፡፡“ ብለው የሚምኑ የፖለቲካ ሊሂቃን እና የፓርቲ መሪዎች ዛሬም አሉ፡፡በእኔ እምነት፣ህዝቡና የፖለቲካ ልሂቃኑ የሚጠይቁት ጥያቄ የሰማይና የምድር ልዩነት አለው፡፡
    እኔ እንደገባኝ ፖለቲከኞቹ ፣በህዝብ ሥም የሚያወሩት የዘር ወሬ ፣ህዝቡን አይመለከተውም፡፡ይህንን የዘር ፖለቲካ ከወንዶች ይልቅ፣ ሰውን ለመውለድ ፀጋው የተሰጣቸው የዓለም ሴቶች በሙሉ የቃወሙታል፡፡
     በተወሰኑ የአፍሪካ ሀገሮች በተለይም በእኛዋ ሀገር ያሉ ሴት እህቶቻችን በዘር ፖለቲካ በእጅጉ ተጎድተዋል፡፡ብዙ ግፍ ተፈፅሞባቸዋል፡፡ይህ ሥቃያቸው የሚያበራው ፣የፖለቲካ ፓርቲ የመሰረቱ ፖለቲከኞችና ሊሂቃኖቻቸው፣በባሊ ወተት ለመጠጣት ሲሉ በእነሱ ስም መነገዳቸውን ሲያቆሙና ቢያንስ ልጆቻቸው በርሃብ ሳይሞቱ በጊዜ ደርሰውላቸው በብርጭቆ ወተት እንዲያገኙ የሚስችል የፖለቲካ መደላድል በዚች ሀገር እንዲፈጠር ሲያደርጉ ነው፡፡
     የኢትዮጵያን ህዝብ  ” ከሺ ቢታለብ ያው በገሌ …” ተረት እሥካላቀቁት ፣ ወይም ፍትህአዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ፣ ከህገመንግሥቱ ጀምሮ ለውጦችና በተጠያቂነት ላይ ያተኮሩ መንግሥታዊ  ተቋማትን እስካልገነቡ ጊዜ  ድረስ ፣ የለውጥ ኃይሎቹ ማሸለብ እንኳ የለባቸውም።
ህይወት ና ሰው
ህይወት እንደ ጅረት ትፈሳለች
“ሰው ራሱ ጅረት ነው”፣እያለች
አንዱ ሲሄድ፣አንደኛው ይመጣል
መሄድ፣መጓዝ መች ያቆማል??
በማለት፣ዘላለማዊ ፍሰቷን
እየመሰከረች።
መጣመር ፣መዋለድ
ማደግና ማርጀት
ጥንትም ነበረ፣
ዛሬም አልተቀየረም…
እያለች።
ሳታቋርጥ፣ሳትታክት፣ትጓዛለች
አንዱን ወስዳ፣ሌላውን እየተካች።
ግና…
በህይወት፣ጅረት
በወንዞ ፍሰት…
የምንመለከተው…
የምናስተውለው…
ጥቂት አለላችሁ
በየ ዕድራችሁ
ተራ ሞች ያልሆነ
በምናብ የገነነ።
አርቆ አሳቢ
በዕውቀት ተጠባቢ…
ነገን አመላካች
ለእውነት ተሞጋች።
……………………………
ደሞ፣ አለላችሁ…
የሚያደባባችሁ
ሊሰለቅጣችሁ።
ሲኦልን ፈጥሮላችሁ
ገነት ናት የሚላችሁ።
ሞት ደግሶላችሁ
” እኔ ልሙት ! ” የሚላችሁ።
መ/ሻ/ወ/ጊ 2011 ዓ/ም
ተጨማሪ ያንብቡ:  ቄስ፣ ወታደርና ነጋዴ፤ መስቀል፣ ጠመንጃና ብር - ሶስቱ ምስጢራዊ የወረራና የብዝበዛ መሣሪያዎች
Share