ሎሬቱ ሰምቶ ይሆን? – መስፍን ማሞ ተሰማ

መስፍን ማሞ ተሰማ
ሠላም ለናንተ ይሁን!

ስለ ቴዎድሮስ ሹርባ ሎሬቱ ሰምቶ ይሆን? ከሰማ ንገሩን፤ ካልሰማም የምትችሉ ንገሩት፤ እኛ ግን ይህንን እንላለን። እነሆ ከ1868 እስከ 2019 (እአአ) በለንደን እንግሊዝ የኖረው የቴዎድሮስ ሹሩባ ሳይሆን የመይሳው መንፈስ ከመይሳው እናት ጋር አንድም ሁለትም እልፍም ሆነው ነው፤ ኢትዮጵያና ካሳ። በሹሩባው የገዘፈው ቴዎድሮስ ብቻ ሳይሆን ሽጉጡን የጠጣላት እናቱ ኢትዮጵያም እንጂ!

ዓለም ከዓለም ጥግጋት እየተጠራራ አንጡራውንም እያፈሰሰ (ለእንግሊዝ የእርም ገንዘብ) እንደ ትንግርት ሲመለከተውና ሲደመምበት የኖረው የቴዎድሮስ ሹሩባን ሳይሆን በሹሩባው ቀጫጭን ፀጉሮች ላይ የተፃፈውን የ3ሺህ ዘመን የእናቱን ገድልና ታሪክ ጭምር እንጂ!

እነሆ ለ150 ዓመት የአውሮፓን ሥነ ልቡና ያስጨነቀው – የቴዎድሮስ ሹሩባ መንፈስ – የዘመን ጉዞና ታሪክን ይዞ ከለንደን አዲስ አበባ (የእናቱ እምብርት) ተመልሷል። እናቱ ኢትዮጵያ ግን እንዴት ነበረች? እንዴትስ ናት?

መይሳው ቴዎድሮስ ያኔ መቅደላ አናት የኢትዮጵያን ውርደት <በጠላት እጅ ወድቄ ከማይ> ብሎ ጥይቱን ሊጠጣ ሲዘጋጅ እንዲህ ብሎ ለእናቱ ነገረ። <ይልቅስ ተረት ልንገርሽ የተላከ ከእንግሊዝ ዘንድ፤ እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ እጅ ተይዞ ሊወሰድ፤ ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ? አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ? ሆኖም ጎስቌላ አልምሰልሽ የሚያዝንልኝ አልፈልግም፤ ጠላትሽን በክንድሽ እንጂ በእንባሽ ወዝ ባላሸንፍም፤ የልቤን ፍቅር በስተቀር የማወርስሽ ውል የለኝ፤ የኮሶ ሻጭ ልጅ ድሃ ነኝ> ብሎ ነግሯት ነበር ቃታውን ስቦ መቅደላ አናት የወደቀው።

እና ያኔ፤ ከዛም በሁዋላ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ሲያንዣብብ የኖረው የመይሳው መንፈስ በዘመን ዥረት ተንሳፎ ከሰውም ሰው ኢትዮጵያዊ ዋርካ መርጦ በሎሬት ፀጋዬ ውስጠ ውስጥ አድሮ በሎሬቱ ሥነ ቃል ነፍስ ዘራ፤ ተናገረ፤ እንዲህም አለ፤

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ ላቶ መስፍን አርጋ! - Dr. Ing. Teferedegn Haile

ታዲያ እንግዲህ አንቺ ኢትዮጵያ፣ እኛስ ልጆችሽ ምንድነን

አመንኩሽ ማለት የማንችል፣ ፍቅራችን የሚያስነውረን

ዕዳችን የሚያስፎክረን

ግፋችን የሚያስከብረን

ቅንነት የሚያሳፍረን፣ ቂማችን የሚያስደስተን

ኧረ ምንድነን? ምንድነን?

አሜኬላ እሚያብብብን

ፍግ እሚለመልምብን

ከአረም ጋር ያፈራን ጊንጦች፣ ከእንክርዳድ ያልተለየን ዘር

ግርዱ ከምርቱ ተማጥቆ፣ ከቶ ያልተበራየን መከር

ምንድነን? ምንድነን እኮ?

አየሽ አንቺ ኢትዮጵያ ፤ አየሽ አንቺ እናት ዓለም

ቃል የእምነት እዳ ነው እንጂ፣ ያባት የናት እኮ አይደለም፤ ነበር ያለው መይሳው በሎሬቱ ነፍስ አድሮ የተናገረው። እና ዛሬስ? መይሳው ከ150 ዓመት በፊት ራሱን የሰዋላት ኢትዮጵያ ዛሬ የት ደርሳለች? <ቅንነት የሚያሳፍረን፤ ቂማችን የሚያስደስተን> ብሎ በሎሬቱ ቃለ ልሳን የተናገረላት ኢትዮጵያ ዛሬ የት ናት? የቂመኞች ጥግ የት ደርሷል? በስሟ የማሉ፤ በስሟ የተካቡ የመሪዎቿ ክህደት እስከምን ዘልቌል? ቃል የዕምነት እዳ እንጂ ያባት የናት እኮ አይደለም – ሲል ህያው ቅኔ የተቀኘላት ስንቶች ለቃላቸው አድረዋል? ስንቶችስ በቃላቸው ፀንተዋል? በቃላቸው ተገኝተዋል? ወይስ ስንቶች ቃላቸውን አጥፈው ቃላቸውን በልተው በናት አባት ቌንቌቸው ምህላቸውን አፍርሰዋል ቃላቸውን ውጠዋል? በሌሬቱ ሥነ ቃል አዋዝተን እነሆ በደረስንበት ዘመን አዲስ አበባ ላይ በሰፈነው የመይሳው መንፈስ እንጠይቃለን። እንሞግታለን። ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!

መጋቢት 2011 (ማርች 2019)

ሲድኒ አውስትራሊያ

https://youtu.be/RlSU_psoNUY

2 Comments

 1. ዕውነት እንደ መዩ ሎሬት ምን ይሰማው ይሆን?በምልክቷ(ቁንድሉ)ቴዎድሮስ ካሳሁንንም ስለሥራውprophetic meaning እናመሰግነዋለን፤እንድ እሱ ያሉትን በጣም አከብራለሁ።

  ትንቢተ-መዩ፤ተፈፀመ።

  ቁንድሉ ቀንዲል ሆኖ፤
  ለኢትዮጵያ ሊያበራ፤
  ለአንድነት ዜጎቹን
  በሙት-ድምፅ ተጣራ።
  ቁንድሉ ሳይረሳ፤
  ለቀንዲል ተነሳ።
  በተቈነደለው አካሉ ያልተረሳ፤
  መይሳው ለቀንዲል መዩ ሆኖ ተነሳ።
  ኢትዮጵያውያን
  ኑና ታምር እዩ፤
  ዛሬ አገር ይገባል
  ያ ትንቢተ-መዩ።
  ለመቶ ሃምሳ ዓመታት
  እየሜሰ!!!ሜሳ
  የኢትዮጵያው አንበሳ
  ከእንግሊዝ ተነስቶ
  ሸገር ላይ አገሳ!!!
  ያኔም ባጭር ታጥቆ፤
  ኢትዮጵያን ጠብቆ፤
  ዘረኝነትን የምር በዝምድና አንቆ፤
  ሲገድል የነበረ መሬት አደባልቆ።
  መዩ ያ መይሳው፤
  የኢትዮጵያ አንበሳው።
  እሳት ጎርሶ ወድቆ ሳይቀና፤
  ፀጥ አለ ክንዱ ላይ ተንተራሰውና።
  ዘመነ መሳፍንት ከእንግዲህ በል ዝለል፤
  “አጁሃንም ደርብ “ጛኣ-ጛኣህን ተቀበል።
  ሃያ አንድ መድፉን ለዚያ ግፍ ውለታህ፤
  ይሁዳ ወስደሃል አጋንንትም ይፍታህ።
  እንግሊዙ ግና የኛን ልቦና አውቆ፤
  ፈርጥጦ ቶሎ-ወጣ ዘርፎ ተደብቆ።
  “እኛ የምንሻው እስረኞቻችንን፤
  እሱ እጁን አልሰጠም እንሂድ አገራችን።”
  እየተባባሉ ኢትዮጵያዊው ሳይሰማ፤
  በባንዳዎች ሴራ ነብሱን መዩተቀማ።
  “የተባልነውም ሳትገድሉት እጁን ያዙ ነበር፤
  ጦራችን አልቻለም እንሂድ በቶሎ
  ኋላ እንዳንቸገር።”
  ብለውም ነጎዱ ያኔ የተረፉት፤
  ብርሌ እንኳ ሳይቀር
  በዝሆን የጫኑት ሞልቶ የዘረፉት።
  መዩ መይሳው፤
  የኢትዮጵያ አንበሳው።
  እሳቱን ጎርሶ ሱሪውንም ታጥቆ፤
  በጣዕረ-መንፈሱ በውስጡ ደብቆ፤
  የተቈነደለውን ሲሸልቱት አውቆ፤
  ለእማማ አልቅሶ ተኛ ሞቱን ንቆ።
  ፀጥ አለ በክንዱ ጀግናው ተንተርሶ፤
  እንደማያውቅ ህኖ እሳት ባፉ ጎርሶ።
  ከሃዲዎቹንም አያቸው በብሌን፤
  እዩልኝ እያለ ለትውልድ በደሌን።
  ተዋቡና እና አለማየሁ በክብር ሲጋዙ፤
  ባፅሙ ተጋድሞ ያይ ነበረ ብዙ።
  ነጭ ነኝ ባዮቹን በቁም ከርችሟቸው፤
  አልለቅም እንዳለው አለ ልቀቋቸው።
  ከራሴ ከሃዲዎች አይብስም የእነርሱ፤
  ብለው ለቀቛቸው በቀል ሳይመልሱ።
  ኢትዮጵያንም ብሎ በክንዱ ተማምኖ፤
  የእሳት ጉርሻ ዋጠ
  በእራሱ ጨክኖ።
  የተቆነደለው ያ መይሳው ካሳ፤
  ገድለናል እንዳይሉ
  በቀንዲል ተነሳ።
  መይሳው በመዩ
  ቀንዲል እያሳመ፤
  የመይሳው ትንቢት
  መዩ ተፈፀመ።

 2. ተዋቡ የሚሌው ጥሩየ ወይም ጥሩወርቅ ተብሎ ቢስተካክል? እቴጌ ተዋበች ይህንን ጉድ ሳያዩ ስለአረፉ።

Comments are closed.

Share