March 20, 2019
50 mins read

ዝክረ አድዋ እና እኛ  (ጠገናው ጎሹ)

እንደ መግቢያ

ይህ ትውልድ የእራሱን እጣ ፈንታ በእራሱ እንደሚወስን ትውልድ የታሪክን ትምህርታዊነት (አስተማሪነት) በአግባቡ  እያስተዋለና እየተረዳ ለተሻለ የዛሬና የነገ እሱነቱ ትርጉም ያለው የጋራ ጥረት ባለማድረጉ የዓለም የጭራዎች  ጭራና ምፅዋእት ለማኝ ሆኖ  ከዘለቀበት ክፉ አዙሪት ለመውጣት አልተቻለውም ።  ይኸውና አሁንም ደጋግሞ ከወደቀበት በስሜት ትኩሳት የመነዳት ፖለቲካ ስህተት ተምሮ  በሰከነ አስተሳሰብ፣ በማይናወጥ መርህ እና ራእዩን እውን ለማድረግ በሚያስችል አደረጃጀት ላይ የተመሠረተ  የጋራ ትግል ማድረግ ገና አልተሳካለትም ።

ለዚህ ነው   በግዙፍና መሪር  መስዋእትነት የታየችውን የለውጥ ተስፋ ብርሃን መልሰን ካላጠፋናትና ካልተጠፋፋን የሚሉ  ፅንፍ የረገጡ የጎሳ/የብሄረብ /የዘር  አጥንት  ቆጠራ (DNA)  ፖለቲከኞች ወይም አክቲቪስቶች ያዙኝና ልቀቁኝ ባሉ ቁጥር አገር የሚሸበረው።  በስሜትና በቁጭት ትኩሳት ፖለቲካ  የሚዘወር ወጣት (ትውልድ) የራሳቸውን እጅግ እኩይ የሆነ የግልና የቡድን ፍላጎት ያሳካልናል ብለው እስከ አመኑ ድረስ የአገር ምስቅልቅልና የህዝብ ሰቆቃ ጉዳያቸው ያልሆነ የጎሳ/የዘውግ/የመንደር/ ፖለቲካ ማንነት ፖለተቲከኞችና አክቲቪስቶች  የጥፋት አጀንዳ ተሸካሚ አጋሰሳቸውና የዓላማቸው  ማስፈፀሚያ መሣሪያ ቢያደርጉት ያሳዝን እንደሆነ እንጅ አያስይገርምም።

የዚህ ትውልድ በስሜትና በቁጭት ትኩሳት ፖለቲካ የመነዳት አባዜ አስከፊ ውጤቱ ፅንፍ በረገጡ የጎሳ/የዘውግ አጥንት ቆጠራ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶችብቻ የሚወሰን አልሆነም ። የለውጥ አራማጅ ከመባል አልፎ “የዘመናችን ሙሴዎች” ተብለው የተሞካሹት ፖለቲከኞችም በቀጥታም ይሆን በተዘዋዋሪ የዚሁ አስቀያሚ ብቻ ሳይሆን አደገኛ  የፖለቲካ ልክፍት ተለካፊዎች የመሆናቸው ነገርም አሳዛኝ ዜና ይሆን እንደሆነ እንጅ አስገራሚ ግን አይደለም ።  “ሙሴነታቸው”ይህ ትውልድ በተለይ ደግሞ ተማርኩና ተመራመርኩ የሚለው ክፍል ልክ ከሌለው የስሜታዊነት ፖለቲካ  ትኩሳትና መፍትሄ አልባ ከሆነ የዘመናት ቁጭት ተነስቶ የሰጣቸው “ሰማያዊ የማእረግ ሹመት”  በመሆኑ አንድ ዓመት ሳይሞላቸው እውነተኛ ምንነታቸውና ማንነታቸው የአደባባይ ሚስጥር ቢሆን ጨርሶ የሚገርም አይደለም ። የሃዘን ስሜቱ ግን ብርቱ ነው ።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ነው  ያ ታላቅ ፣ ክቡርና ባለውለታ ትውልድ  ታሪካዊ ገድል  ያስመዘገበበት የአድዋ ድል አንድ መቶ ሃያ ሶስት ዓመት የሆነው ።

በአገራችን የታሪክ ሂደት በውጭ ወራሪ ወይም ቅኝ ገዥ ሃይል ሥር ወድቆ በገንዛ አገር ከሰብአዊ ፍጡር በታች ላለመውደቅ እጅግ ግዙፍና መሪር መስዋእትነት ተከፍሏል። በመላው ዓለም ነፃነት አልባ ለነበረው ህዝብ አነፀባራቂ አርአያ የሆነው ፣ የአገራችን በሉአላዊ አገርነት የመቀጠልን ታሪክ ያረጋገጠው፣በወቅቱ (በዚያን ጊዜ) የነበረውን ዓለም አቀፍ ግኑኝነት ከቀየሩት ኩነቶች አንዱ የሆነው  እና በዋጋ የማይተመን (pricelss) እሴትነቱ ( value) ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋጋረ አያሌ ዘመናት ያስቆጠረው  የአድዋው ተጋድሎ ድል ነው ።   የአድዋ ድል የአያሌ ዘመናት ሉአላዊት አገርን በማይቋረጥ የትውልድ ቅብብሎሽ ሰንሰለት ያስተሳሰረ ተመን የማይገኝለት (pricelss) የአርበኝነት ተጋድሎ ውጤት ነው ።አዎ!  ከየትኛውም አቅጣጫና የህብረተሰብ ክፍል ተጠራርቶ በዘመተ ፣ ደሙ ተቀላቅሎ በፈሰሰ እና አጥንቱ ተነባብሮ በተከሰከሰ ትውልድ የተከናወነ እፁብ ድንቅ ድል ነው ።  የአድዋ ድል !

ከምርና ከቅንነት ለመማር ፈቃደኛና ዝግጁ ለሆነ ትውልድ የአድዋ የአርበኝነት ታጋድሎ ድል ተፅፎ ከሚነበበው በላይ በእያንዳንዱ መልካም ዜጋ አእምሮ ውስጥ እራሱን የቻለ ቤተ መዘክር  አለው ። የአንዲት አገር ልጆች ልብ ለልብ ተናበውና እጅ ለእጅ ተያይዘው በመዝመት አድዋ ላይ ከወራሪ ፋሽስቶች ጋር ሲተናነቁና በደምና አጥንት ወደር የሌለው ገድል ሲሠሩ የሚያሳይ ወርቃማ  የአእምሮ ቤተ መዘክር ! አዎ! የአድዋ ተጋድሎ ድል በውስጡ የያዛቸው ዝክረ ምእራፎች በዘር/በጎሳ ፣ በሃይማኖት ፣ በቋንቋ፣ በመልክአ ምድር ፣ በፃታ፣ በባለፀጋነት ወይም በድሃነት ፣ በታሪክ ሂደት በሚፈፀሙ የውስጥ ቁርሾዎች ልዩነቶች  ምክንያት አገርን (የዘለዓለም ቤትን) አሳልፎ መስጠትን በተፀየፉ የአንድ አገር ልጆች ደምና አጥንት የተፃፉና የታተሙ ናቸው  ። ልብ የሚል ልብ ኖሮት ልብ ለሚል ትውልድ።

አለመታደል ሆኖብን ሳይሆን በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጨረሻው አሥር ዓመት ሥልጣን ላይ በመውጣት ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የዘለቁትና ይኸውና አሁንም ተገደው እንዲከፍቱ የተደረገውን የለውጥ ተስፋ በር መልሰው ለመከርቸም (ለመዝጋት) የሴራ ቅሌት ውስጥ በሚዳክሩት ፖለቲከኞቻችን ምክንያት ይህን ግዙፍና ጥልቅ የታሪክ እሴታችንን በሚገባው መጠን ልንዘክረው አልቻልንም ። “በደማቅ ትእይንትና በመሪዎች ድንቅ ዲስኩር ተከብሮ የለም ወይ?” ብሎ ከቅንነት የሚጠይቅ ወገን እንደሚኖር እገምታለሁ ። አዎ! ለብዙ ዓመታት በእጅጉ ተዳክሞ የነበረውን የአገር ፍቅር ስሜት በአንፃራዊነት የሚያነቃቁ ዲስኩሮች ተደስኩረዋል ፥ ትዕይንቶችም ታይተዋል  ፥ በወጣቶችም የመታስቢያ ጉዞ ተደርጓል ።  ይህ በጣም እሰየው ያሰኛል ። ጥያቄው ግን ከዚህ የበለጠ ስፋትና ጥልቀት ያለውና ተመጣጣኝ አረዳድና ምላሽ የሚጠይቅ ነው ።

ለመሆኑ ከየት ወደ የት እየሄድን ነው?     

በእጅጉ የሚያሳስብና የሚያስጨንቅ ጥያቄ ነው ። ለስሜት በሚጥሙ ንግግሮች፣ ቅን አመለካከትና አድናቆት ያለውን ተመልካች ቀልብ በሚስቡ ትእይንቶች ፣ እና እሰየው በሚያሰኝ  የመታሰቢያ ጉዞ  የዘከርነውን  የአድዋ ድል መሬት ላይ እየሆንና እያድረግን ካለው እውነታ ጋር እንዴት አብሮ ይሄዳል  ? የሚለው ጥያቄ አሳሳቢነቱንና አስጨናቂነቱን ከምር ካልተረዳነው የዛሬውን ሃላፊነታችን በአግባቡ ተወጥተን ነገን በላቀ እኛነት ለመቀበል በእጅጉ እንቸገራለን ።

በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እርስ በርሳችን መሬት ላይ እየሆንና እያደረግን ያለነው እውነታ እና በአድዋና በሌሎችም የአርበኝነት ተጋድሎ ውሎዎች የተመዘገበው የታሪክ  እውነታ ከዲስኩር ባለፈ አልተገናኘልንም (አላገናኘነውም) ። የአገር ነፃነት ተጋድሎው ታሪክ  የሁላችንም ነው ብሎ ከበሬታ ካለመስጠት አልፎ “የታሪኩ ዋና ተዋናይ የነበሩትን መሪዎች ስም አትጥሩብኝ” የሚል እና በአገር አርማነቱ አብሮ በዘመዝመት የጠላት ከባድ  የጦር መሣሪያ ወላፈን እንደ እሳት ሲገርፈው የነበረውንና የድል ብስራትን  በድል አምባ ላይ ያበሰረውን ሰንደቅ ዓላማ “ድራሹን ካላጠፋችሁልኝ” በማለት ያዙኝና ልቀቁኝ የሚል የፅንፈኛ “ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች” ሰለባ የሆነው የዚህ ትውልድ ክፍል (አባል) ቁጥር ቀላል አይደለም ። በዚህ እንኳን ሰብአዊ ፍጡር ሌሎች እንስሳት እየሰለጠኑ አስገራሚ አገልግሎት በሚሰጡበት ዘመን  በሰለጠነና ገንቢ በሆነ  የአስተሳሰብና የተግባር ሰብእና  በእኩልነት ፣ በሰላምና በጋራ ብልፅግና የምታኖር ዴሞክራሲያዊት አገር ከመመሥረት ይልቅ እንዲህ አይነት የእብደት ወይም የድንቁርና ፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ እራስን ማግኘት በእጅጉ አሳፋሪና አሳዛኝ ነው ።

በመሬት ላይ እየሆነ ያለው ነገር እኮ ከችግርነት አልፎ አጠቃላይ ማለትም ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ሞራላዊ ፣  መንፈሳዊና ብሎም አገራዊ  ቀውስ ሆኗል ። ከየት ወደ የት እየሄድን እንደሆነ በግልፅ ይናገራሉ (ያሳያሉ) የምላቸውን ነጥቦች ጥያቂያዊ በሆነ አቀራረብ  እንደሚከተለው ላቅርባቸው ፦

  • በገንዛ ወገን ላይ ዘውግ ፣ ቋንቋና መንደር ለይቶ ሰቆቃና ግድያ ከመፈፀም ፣ ከማፈናቀልና  በርሃብ ከመቅጣት በላይ ምን አስከፊ  ቀውስ አለ
  • በዘመናት የታሪክ ሂደትና ማህበረሰብአዊ መስተጋብር የተገነባውን እንደ አንድ አገር ህዝብ አብሮ የመኖር ገመድ (fabric) ለመበጣጠስ ከመሞከር የከፋ የአስተሳሰብና የአካሄድ ውድቀትስ የት አለ?
  • “ያንተ/ች እና የእኔ ታሪክ የሚጠፋፋ እንጅ የሚስማማ አይደለም” በሚል ያዙኝና ልቀቁኝ ከማለት  የባሰ ምን አይነት እብደት ይኖራል ?
  • አስከፊውን የሩብ ምእተ ዓመት የጎሳ/የዘውግ ሥርዓት ለማስወገድ በተደረገ የጋራ መስዋእትነት ትግል “ደምህ/ሽ ደሜ ነው!” በሚል እጅግ ጥልቅ የአብሮነት ቃል ኪዳን ለመተሳሰር ከየአቅጣጫው የተስተጋባውን ወርቃማ የአብረን እንዳን ጥሪ አምክኖ “ወገንን በገንዛ አገሩ ክልሌንና መንደሬን ለቀህ/ሽ ካልወጣህ/ሽ ደምህን/ሽን  ነው የማፈሰው” በሚል እጅግ ዘግናኝ የማንነት ፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ከመዘፈቅ የባሰ የትውልድ ውድቀትስ የት አለ?  
  • ለዘመናት አብሮ የኖረን ወገን በጎሳ/በቋንቋ/በዘር ለይቶ ህይወቱን በማመሰቃቀል የወላጆቻቸውን ሰቆቃ እያዩና እየሰሙ የደም እንባ ለሚያነቡ ህፃናት የሚራራ ልብ የሌላቸው ባለሥልጣናትና  ካድሬዎች የፖለቲካ መዘውሩን በሚዘውሩበት አገር ስለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ከየት ወደ የትነት እንዴት መነጋገር ይቻላል ? በምድርም ሆነ በሰማይስ ከዚህ የከፋ ምን አይነት ወንጀል ወይም ኅጢአት  ሊገኝ  ይችላል  ?  
  • “የለውጥ ሃዋርያት” ያልናቸው ፖለቲከኞች (መሪዎች) ህዝብን ከፅንፈኛ የጎሳ/የመንደር ፖለቲካ እብዶች መታደግ ካለመቻል አልፈው የጨዋታው አካል መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር የሆነበት ሁኔታ ከየት ወደ የት እየሄድን እንደሆነ ካልነገረን ሌላ ምን አይነት ማስረጃ ሊነግረን ይችላል ?
  • በከፍተኛ አመራር ደረጃ አባል የሆኑበትና የህዋሃትን አገዛዝ የመተካት የፖለቲካ ሴራ ውስጥ የተዘፈቀው የፖለቲካ ድርጅት (ኦዴፓ) ካድሬዎችና ከንቲባ ተብየዎች ንፁሃን ዜጎችን በገንዛ አገራቸው ያለምንም ሰብአዊ ርህራሄ ከነችግራቸው የኖሩባቸውን ቤቶቻቸውን በቡልዶዘር ከአፈር ጋር ቀላቅለው ከበርካታ ህፃናት ልጆቻቸውና አረጋዊ ቤተሰቦቻቸው ጋር እንደማነኛውም የማይጠቅም ቁሳቁስ ሜዳ ላይ ሲወረውሯቸው “ዳግማዊ ሙሴ” እያልን  ያሞካሸናቸው ጠቅላይ ሚኔስትር አላወቅሁም ወይም የከተማ ከንቲባ አይደለሁም  ማለታቸውን ከድርጊቱ በላይ ልብ የሚያደማ ነው ማለት ይበዛ ይሆን?
  • አስመራ (ኤርትራ) ድረስ ከፍተኛ ልኡካኖቻቸውን ( የኦሮሚያ መስተዳር ፕሬዝደንት አቶ ለማንና የወቅቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁን) ልከው ለህዝብ ግልፅ ባልሆነ (ባልተደረገ) ስምምነት የአቶ ዳውድ ኢብሳው ኦነግ የአገር ቤት ጦረኞቹ መሣሪያቸውን እንደ ደቀኑ ወደ አገር ቤት እንዲመለስ ያደረጉና ሲመለስም በደማቅ አቀባበል የተቀበሉ ፖለቲከኞች (መሪዎች) አሁን እራሳቸውን ግልፅ ማድረጋቸው ከቶ የሚገርም አይደለም ። የሴራ ፖለቲካው ጨዋታ በዚህ አላበቃም። ለመሆኑ ታላቅ ማህበራዊና ሞራላዊ እሴት በሆነው የሽምግልና ባህል   ፀንቶ የቆመ ስንቱን ነው? የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ ሽምግልናን እንደ አስፈላጊ የመፍትሄ አፈላላጊ አካል  መጠቀም ትክክልና ተገቢ መሆኑን ማጣጣል ወይም መካድ እጅግ ከባድ ስህተት ነው።

በሽምግልና ስም አሉታዊ የሆነ ፖለቲካ ጨዋታን ለመጫወትና በህግ ተጠያቂነትን ለመሸሽ የሚደረግን ሙከራ አካፋን አካፋ በሚል የዜግነትና የሞራል ወኔ አለመሞገትም ከባድ ስህተትና  ውድቀት ነው።

ለሁሉም ተቀዋሚ ድርጅቶች  በተላለፈው ጥሪ መሠረት አገር ቤት ከገባ  በኋላ ከነፍስ ግድያ እስከ ባንክ ዘረፋ ወንጀል የፈፀመን አካል  ሙሉ በሙሉ በሚያሰኝ አኳኋን  ከመንግሥት ሃላፊነትና ተጠያቂነት  አውጥቶ እንደቀላል ጉዳይ ለሽምግልና እና እንደ  ጃዋር መሃመድ ለመሰሉ ፅንፈኛ ጎሰኞች/መንደርተኞች መስጠት ፈፅሞ የጤናማ ፖለቲካ ጨዋታ ሊሆን አይችልም ። ፍለጠውና ቁረጠው እንባባል አይደለም እያልኩ ያለሁት ።እያልኩ ያለሁት የፖለቲካ ጨዋታው ሃቀኝነት፥ የህግ የበላይነት፣ ሃላፊነት፣ ተጠያቂነትና ገንቢነት ባለው አካሄድ እና በጋራ ወደ ፊት ሊያራምድ የሚያስችል መንገድን በሚያመቻች አኳኋን ይሁን ነው።  ይህን አስመልክቶ ግልፅ ቀጥተኛና ገንቢ የሆነ አመለካከትና አቋም ለመያዝ  ያልደፈረው (ያልፈለገው) “የለውጥ ሃዋርያው” ቡድን (Team Lemma) ጉዳይ  ከየት ወደየት እየሄድን እንደሆነ ካልነገረን ሌላ ምን የሚነግረን ነገር የኖራል?

  • ህግ አውጭው፣ ህግ አስፈፃሚው ፣ ህግ ተርጓሚው እና ተያያዥ ተቋማት በእውነተኛ የለውጥ አራማጅነት ሳይሆን ከመጣው ጋር ጭራውን በሚቆላ አደገኛ አድር ባይ እና የወያኔን የአናሳ ቁጥር (minority) የጎሳ/የብሄረሰብ ፖለቲካ በኦህዴድ/ኦዴፓ የብዙ ቁጥር (majority) የጎሳ /የብሄረሰብ ፖለቲካ  የመተካት የፖለቲካ ሴራ በሚያሴሩ ፅንፈኛ  ፖለቲከኞች በተጠረነፉበት ሁኔታ ውስጥ ዴሞክራሲያዊት የጋራ አገርን እውን ስለማድረግ መተማመን እንዴት ይቻላል ?

 

በአጠቃላይ በእንዲህ አይነት እኩይ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ እንኳን ዴሞክራሲን እውን የሚያድረግ ታሪክ ለመሥራት  የአገር ህልውናን ማስቀጠልስ እንዴት ይቻላል ? ከፊት ለፊታችን ቆሞ የሚሞግተንና ሳይመሽ ተገቢውን መልስ እንድንሰጥ የቀረበልን ፈተና ይኸው ነው ።

 

ከገዥው ቡድን (ከመንግሥት) ፖለቲከኞች ውጭ ያሉት አካላትስ ?

 

  • ገዥው ቡድን (መንግሥት) ከአሳሳቢ ችግርነት አልፎ በመጠንም ሆነ በአይነት እጅግ አደገኛ ወደ ሆነ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል እየሄደ ላለው ወቅታዊው የአገራችን  ሁኔታ የመጀመሪያው ተጠያቂ አካል መሆኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም ።

እጅግ አብዛኛዎቹን ፋይዳ እንዳላቸው የፖለቲካ አካላት መቁጠሩ የሚያኮራ ሳይሆን በእጅጉ የሚያሳፍር ቢሆንም ከገዥው ቡድን (ከመንግሥት) ቀጥሎ በተጠያቂነት አደባባይ ላይ መቆም ያለባቸው ተቀዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ተብየወች  ናቸው ።

 

ያለምንም ማጋነን ነገር ዓለሙ የተበላሸው  አገራችን ለዘመናት ከገባችበት ከባድና  እጅግ ሥር ከሰደደው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ድህነቷ  ላይ በጎሳ አባልነት፣ በቅርብ ወዳጅነትና በቤተሰብ አባልነት ከአንድ መቶ በላይ  የፖለቲካ ፖርቲዎች ነን ብለው እንደ አሸን የተራቡ እለት ነው ።  በመሠረቱ ይህ የወባ ትንኝን ለመከላከል ወይም ለማጥፋት መልሶ ትንኟን እንደማራባት አይነት ክፉ የፖለቲካ አዙሪት ነው ።

በቅንነትና በሚዛናዊነት ለሚያስብ ዜጋ ይህ በጣም የወረደና አሳፋሪነቱ  በእጅጉ ህሊናን እረፍት የሚነሳ የፖለቲካ ጨዋታ አሁንም (እንዲያውም በከፋ አኳኋን) መቀጠሉን መረዳት የሚሳነው አይመስለኝም ።

አገር ባለችበት እጅግ አሳሳቢ (አደገኛ) ሁኔታ ላይ በጥልቀትና ትርጉም ባለው አኳኋን መክረው በህዝብ ሰቆቃ ላይ የፖለቲካ ጨዋታ ለሚጫወቱትና ይህን አደገኛ ጨዋታ ማስቆም ላልቻለው (ላልፈለገው) ገዥ ቡድን (መንግሥት) በቀጥታና በግልፅ ቋንቋ መልክታቸውን ማስተላለፍ ወኔ ያጡት  የመቶ በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች ፖለቲከኞች  “ድንቅ የሆነ የፖለቲካ ድርሳነ ሥነ ምግባር” መፈራረማቸውን  እንኳን ደስ ያለን ከሚል ዜና ጋር ነግረውናል ። እራን አቂሎ ህዝብንም የማቄል የፖለቲካ ጨዋታ የሚያበቃበት ጊዜና ሁኔታ በእጅጉ ይናፍቃል ። መሬት ያለው መሪር ፈተና በዚህ ድርሳነ ሥነ ምግባር እንደተገለፀው ቀላል (ቀና) ቢሆን እንዴት ሁሉም ነገራችን ሸጋ በሆነ ነበር ። እራሳችን እናታል ካላልን በስተቀር በእዚህ አብዛኛዎቹ ፖርቲዎች (ድርጅቶች) ብሎ ለመጥራት በሚያሳፍሩ አካላት ተደርሶ ተፈረመ የተባለው ድርሳነ ሥነ ምግባር አገር ላለችበት እጅግ ከባድና አንገብጋቢ ሁኔታ ብዙም የሚፈይደው ፋይዳ የለም ። የዚህ ምክንያቱ ግልፅና ግልፅ ነው ። አሳማኝ ምክንያትና በጎ ውጤት ያለው ፖለቲካ ለማራመድ ከሚሞክሩትና በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር  አብዛኛዎቹ በየሚስጥር ኪሳቸው  የየራሳቸውን ዘውዶች ይዘው ከመዞር ክፉ ልክፍት ለመላቀቅ ከራሳቸው ጋር ትግል ያላደረጉ ናቸው ።

 

አገር አቀፍ ወይም ህብረ ብሄር ወይም የዜግነት ወይም የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ እናራምዳለን የሚል ተመሳሳይ የፖለቲካ ቋንቋ የሚደሰኩሩ ፖለቲከኞች እገሌ ከሚባለው/ሉት ጋር እዚም እዚህም “ልንጠጋጋ ነው” የሚል ልፍስፍስ የፖለቲካ ጨዋታ ከመጫወት ይልቅ  ሲሆን ወደ አንድ ካልሆነም ወደ ሁለት የፖለቲካ ሃይልነት ተሸጋግረው ትርጉም ያለው የፖለቲካ  ሥራ መሥራት  ለምን እንደማይሆንላቸው ለመረዳት ልዩ እውቀት አይጠይቅም ። ምክንያቱም እጅግ በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር  እጅግ አብዛኛዎቹ ተመሳሳይ ዲስኩር እየደሰኮሩ  በየሚስጥር ኪሳቸው ውስጥ የአለቆች አለቃ መሆን አለብኝ በሚል ቅዠት የየራሳቸውን  ዘውዶች  ይዘው ስለሚዞሩ ነው ።  በዚህ አይነት ክፉ የፖለቲካ አባዜ እስካሁን መልኩን እየቀያየረ ህዝብን ማለቂያ ወደ ሌለው ትርምስ ከመግፋት ያልተቆጠበውንና ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በጎሰኝነት/በቋንቋ/በጎጠኝነት እና ከዚሁ በሚገኝ ግለሰባዊና ቡድናዊ ጥቅም ላይ የተመሠረተን ሥርዓት አስወግዶ መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ማድረግ እንዴት ይቻላል ?

 

በሌላ በኩል በየጎሳቸው/በየቋንቋቸው/በየጎጣቸው የተሰባሰቡ በርካታ ስብስቦችም ለየጎሳቸው/ለየብሄረሰባቸው መቆማቸውን የሚገልፁበት የፖለቲካ ቋንቋ መሠረታዊ ልዩነት የለውም ። ታዲያ እንደአሸን እየተራቡ እንወክለዋለን የሚሉትን ማህበረሰብ ግራ ከማጋባትና ከኢትዮጵያዊነቱ ጋር እንዲጣላ ከማድረግ በመጠጋጋት ብቻ ሳይሆን ሲሆን ወደ አንድ ካልሆነም ወደ ሁለት  የፖለቲካ አካልነት በመሸጋገር በእኩልነትና በጋራ ብልፅግና የሚኖርባትን አገር እውን ለማድረግ  ያለመቻላቸው ምክንያት በጎሳ/በጎጥ  ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ከመሆናቸው በስተቀር መሠረታዊ ችግራቸው ከላይ ከጠቀስኳቸው ጋር ተመሳሳይነት አለው ።  የየራስን ዘውድ በየሚስጥር ኪስ ይዞ የመዞር ፖለቲካ ደዌ (በሽታ) ።

የወቅቱ የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ እንቅስቃሴን ተከትሎ “የለውጥ አራማጅ መሪዎች” “በሰላምና በነፃነት” የመንቀሳስ ጥሪ ባደረጉት መሠረት ሁሉም የተቀዋሚ ድርጅቶች ጥሪውን መቀበላቸውንና የፍለጋው አካል ለመሆን የመወሰናቸውን ተገቢነት ቢያንስ በመርህ ደረጃ የሚቃወም ለውጥ ፈላጊ ወገን የሚኖር አይመስለኝም ። አነጋጋሪና አጠያያቂ የሚሆነው   ጥሪውን ከተቀበሉ በኋላ ወደ ትብብርና ከተቻለም ወደ አንድነት የፖለቲካ ሃይልነት እየተሸጋገሩ የነፃነትና የፍትህ ፍለጋው ሂደት ጠንካራና  አወንታዊ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ከመሆን ይልቅ በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ  ከተወሰኑ በተለይ ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና መሰሎቻቸው ጋር ከመደበኛ (formal) የግንኙነት መስመር እየወጡ ኢ-መደበኛ (informal) ወደ ሆነው “እመነኝ አምንሃለሁ” አይነት የፖለቲካ መተሻሸት ውስጥ ሲገቡ  ነው ። ይህን አልታዘብኩም የሚል የህዝብ መከራና ውርደት የሚያሳስበው ቅንና አስተዋይ ወገን የሚኖር አይመስለኝም ።

  • መንግሥትና ቤተ እምነቶች (የሃይማኖት ተቋማት) በእያንዳንዳቸው መደበኛ ሃላፊነትና ሥልጣን ውስጥ ጣልቃ አይገቡም የሚለውን መሠረታዊ ህግና መርህ በገሃዱ ዓለም የሰው ልጅ ባህሪ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ለማዋል የተቻለበትን  የታሪክ ምሥክርነት  በበኩሌ አላነበብኩም ። የግንኙነታቸውን  ከልክ ያለፈና አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትን ለመቆጣጠር እንደተቻለና እንደሚቻልም ከታሪክ ብቻ ሳይሆን ከአሁኑ የገሃዱ ዓለም ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻል ግን እረዳለሁ ።

 

በእውነት ስለእውነት ከተነጋገርን የእኛ የሁለቱ ተቋማት ግንኙነት ታሪክ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ህዝብን እጅግ በሚያሳስትና ግራ በሚያጋባ ሁኔታ እየተደበላለቀ ሲያስቸግር የኖረና አሁንም እያስቸገረ ያለ ጉዳይ ነው ።

 

ለዚህ እውነትነት ባለፈው ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የሆነውን በአንክሮ መመርመርና መረዳት  እጅግ ትልቅ የተሞክሮ ጠቀሜታ ይኖረዋል ።ከባዱ ጥያቄ ግን በዚህ የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ እንቅስቃሴ ወቅትስ በዚህ ረገድ ያለብንን ብርቱ ፈተና ለመወጣት በሚያስችል ሁኔታ ላይ እንገኛለን ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው። እንደኔ ግንዛቤና አረዳድ እንመስላለን እንጅ በሚያስችል ሁኔታ ላይ አይደለንም ። የሩብ መቶ ክፍለ ዘመኑን የመከራና የምስቅልቅል ሥርዓት መዳከምን ተከትሎ በእራስ የሃይማኖታዊ አርበኝነት ተነሳሽነትና አነሳሽነት ባይሆንም በፖለቲከኞች የአስታራቂነት ጣልቃ ገብነት እርቀ ስላም (ከልብ መሆኑን ተስፋ እናድርግና) በመውረዱ ደስ ያላለው (የማይለው) ቅን ህሊና ያለው ኢትዮጵያዊ የሚኖር አይመስለኝም።

የሃይማኖት መሪዎዎችና ባለ ሌላ ማእረግ አገልጋዮች “የለውጥ አራማጅ መሪዎችን” የተቀበሉበት ሁኔታና ይህንኑ ለህዝብ ለመስበክ (ለመንገር) የሄዱበት በእጅጉ  የተለጠጠ (ለበቂ ግንዛቤ በቂ ጊዜ ያልሰጠ) አቀራረብ እና  አሁን ደግሞ በጎሳ/ በብሄረሰብ  ማንነት ላይ ተመሥርቶ  በሚካሄድ መቆራቆስና መፈናቀል ምክንያት ሚሊዮኖች ንፁሃን ዜጎችን መሸከም ለሚያስችግር ሰቆቃ ሰለባዎች በማድረግ ከዓለም አንደኞች ስንሆን “ዳግማዊ ሙሴዎች” ብለው የሰበኩላቸውን ፖለቲከኞች አንድ ጊዜ ሳይሆን ደጋግመው ግልፅ ፣ቀጥተኛና ገንቢ ተግሳፅና ምክር ለመሰንዘር ሲሳናቸው በማየት በሁለቱ ተቋሞቻችን መካከል ያለው ግንኙነት መልኩን ቀየረ እንጅ እንደተሳከረ ነው ቢባል  ማጋነን ሊሆን አይችልም። አካፋን አካፋ በማለት ችግሩን ጨርሶ ማስወገድ የሚቻል ባይሆንም (ይቻላል ተብሎም አይጠበቅምና) በቅጡ እንዲሆን የማሳሰብ ጉዳይ ነው የሚሆነው ።

 

በኖረበት ዘመን በሰው ልጆች መካከል ይታይ የነበረውን የፍትህና የሰብአዊ ፍጡርነት መብት ጉድለት ለተማሪዎቹና ለህዝብ ባስተማረ መርዝ ግተው የገደሉትን ሶክራቲስን (469 -399 ክርስቶስ ልደት በፊት)) ልብ ይሏል ። ምንም እንኳ ወደ ዚህ ዓለም የመጡበት መንገድ እና ዝርዝር የአስተምህሮቶቻቸው አካሄዶች የተለያዩ ቢሆንም ሶክራቲስና ክርስቶስ ዞሮ ዞሮ በአንድ ዋና ጉዳይ በቀጥታ ይገናኛሉ። ሁለቱም ባስተማሩት እጅግ ታላቅ የእውነትና የፍትህ አስተምህሮ ትውልደ ትውልድ ይድንበት ዘንድሞት ፅዋን በፀጋ ተቀብለዋል ።

በዚህ ዘመን የተቸገርነው እንዲህ አይነት የዘመን አቆጣጠር የማይገድበውና ለትውልደ ትውልድ ነፃነት ፣ፍትህ፣ መብት ፣ፍቅር፣ ሰላም፣ ደህንነትና ብልፅግና መስዕዋት መሆን ቀርቶ የአስተምህሮቱን ዓላማና ይዘት ለገሃዱ እና ለሰማያዊው ዓለም በሚበጅ አኳኋን የሚያዘጋጅና የሚያቀርብ  የሃይማኖታዊ እምነት አርበኛ በቀላሉ ለማግኘት ባለመቻላችን ነው ።

ለውጥ የሚመጣውና የሚረጋገጠው የሰው ልጅ  በተሰጠው ልዩ የአእምሮና የአካል ብቃት ተጠቅሞ የገሃዱን ዓለም እውነታ ለመጋፍጥ የሚያደርገውን የጋራ ጥረት ፈጣሪ እንዲባርከው በመጠየቅ (ተገቢውን ፀሎት በማድረስ) እንጅ ፖለቲከኞቸን ቀብቶ መንበር ላይ እንዲያስቀምጥ እግዚኦ በማለት ጨርሶ አይደለም ።  የፖለቲካውን ነፋስ እየተከተሉ የሚነፍሱ የሃይማኖት አባትና ቀሳውስት ተብየዎች  የማገናዘቢያ ጊዜ እንኳን ሳይወስዱ ፖለቲከኞችን በየቅዳሴው (ፈጣሪን የማመሰገኛ ሥርዓት) ሳይቀር “ከሰማየ ሰማያት ተቀብተው (anointed by divine power) የተላኩልን የለውጥ ሃዋርያት” በሚል እራሳቸው በፈጠሩት የክርስትና ስም እየጠሩ የዋሁኑ አማኝ “እርሱ ያመጣውን እርሱ እስኪመልሰው” በሚል ፈጣሪው የሰጠውን ሰው የመሆን ሃላፊነት መልሶ ወደ ፈጣሪው እየወረወረ መከራና ውርደቱን ተሸክሞ እግዚኦ! እንዲል የማድረጋቸው ልማድ አካሄዳችን የተሳሳተ እንጅ የሰመረ መሆኑን ፈፅሞ አያሳይም ።

 

ማጠቃለያ

ታሪካዊ ገድሎቻችንን የምንዘክርበትን  ምክንያት ለየዘመኑ  የትውልድ  መስተጋብራዊ ትስስርና  የእድገት ግስጋሴ  ቅብብሎሽ ካለው ፋይዳ  አንፃር ካልተረዳነውና  በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ታሪክን መማሪያ ሳይሆን  መጠላለፊያ  እያደረግን በሁለንተናችን የዓለም ጭራዎችና የምፅዕዋት ፍርፋሪ ለማኞች ሆነን ነው የምንቀጥለው ።

ታሪካዊ እሴቶቻችንና ቅርሶቻችን ከዛሬውና ከነገው የትውልድ ቅብብሎሽ ስኬታማነት ወይም ውድቀት ውጭ ነጥለን የምንዘክራቸው የተለምዶ  መታሰቢያዎች አይደሉም። ሊሆኑም አይገባም ። ያ የእውነተኛ አርበኝነት ትውልድ ሠርቶት ያለፈውን አንፀባራቂ የድል ታሪክ ለዛሬው ስኬታችንና ለነገው የበለጠ ግሥጋሲያችን ካለው ድንቅ እሴትነት ( precious value ) አንፃር ካላየነውና የራሳችንን ትውልዳዊ የታሪክ ተልእኮ ለመወጣት ብርቱ ትግል ካላደረግን በስተቀር አሁንም ከአሁን በፊት  መላልሰን የወደቅነውን  ውድቀት በከፋ ሁኔታ የማንደግምበት ምክንያት አይኖርም ። እናም ታሪካዊ የአርበኝነት ተጋድሎ ድሎቻችንን ስንዘክር  ከተለምዷዊ ንግግሮች (ዲስኩሮች)  እና ትእይንቶች ባሻገር ዘልቆ የሚሄድ ፣ የዛሬውን ማንነታችንና ምንነታችን በድፍረት የሚሞግትና ላለንበት ዘመን የሚመጥን የመፍትሄ ሃሳብ ማመንጨት የሚያስችል  ፈቃደኝነትና ዝግጁነት ሊኖረን የግድ ነው ።

ከእኛ አልፎ ዓለም የመሰከረላቸውን ታላላቅ የታሪክ አሻራዎቻችንን መታሰቢያዎች በኩራትና በድምቀት የማክበሩ (የመዘከሩ) አስፈላጊነት ከቶ ሊያጠያይቅን አይገባም  ።  ከምር መጠያየቅ ያለብን ይህ ትውልድ የቀደመው ትውልድ  በከፈለው ግዙፍና መሪር  መስዋትነት አቆይቶ ያስረከበውን አገር በነፃነትና በክብር የሚኖርባት ምድር ማድረግ ለምንና እንዴት ተሳነው ? በሚለውን ጥያቄ ዙሪያ  ነው ይህን ጥያቄ ግን ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ  የእውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ፍለጋ እንቅስቃሴ ውስጥ ነን በምንልበት በዚህ ወቅትም  ትርጉም በሚሰጥ አኳኋን ለመመለስ እየቻልን አይደለንም።የዚህ ልክ የሌለው ውድቀታችን ህመም እረፍት የማይነሳው ቅን የአገሬ ሰው ከቶ  የሚኖር አይመስለኝም ። የህመሙን ዋነኛ መንስኤ በቅጡ ተረድቶና ለይቶ ለመከላከልና ብሎም ለማስወገድ ግን ቅንነትና እግዚኦታ ብቻቸውን አንዳችም ፋይዳ አይፈይዱም ። ወሳኙ ፋይዳ ያለው በአግባቡ ከታቀደና ከተደራጀ የተግባር ማንነት ወይም ተፈላጊውን የጋራ እጣ ፈንታ (እውነተኛ ዴሞክራሲ)  በጋራ የመወሰን ተግባራዊነት ውስጥ ነው ።

 

እራሱ እየኖረበት ያለውን መሪር እውነት በቅጡ እያጤነ የእራሱን እጣ ፈንታ የመወሰን ዝግጁነትና አቅም ያነሰው ትውልድ በሴራ ፖለቲካ የተካኑ የጎሳ/የዘር/ የመንደር ፖለቲከኞች  ሰለባ ቢሆን የሚገርም አይሆንም ። የእየራሱን ደማቅ የታሪክ  አሻራ እያሳረፈ ማለፍ ሲገባው  ባለበት  የሚረግጥ ብቻ ሳይሆን ወደ ኋላ እየሄደ በታሪክ ኩነቶች ላይ  የሚነታረክ ትውልድ ከእውነተኛ ዴሞክራሲ ምንነትና እንዴትነት ጋር ሊተዋወቅ አይቻለውም ።

ብዙው የዓለም ህዝብ በሚያስገርም መጠንና ፍጥነት ወደፊት ሲገሰግስ እኛ ግን ባለመታደል ሳይሆን እኛው በእኛው ተጠላልፈን እየወደቅን ከመጣንበት አዙሪት አልወጣንም ። ይኸውና በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እና ዓመት ሊሞላው ጥቂት ጊዜ በቀረው የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ እንቅስቃሴያችን ወቅትም ይህን ክፉ የፖለቲካ አባዜ እንኳን ሰብረን ለመውጣት ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመቋቋም አልተቻለንም ። ለዚህ ነው ታሪካዊ የአገር ነፃነት ተጋድሎዎቻችን በዘልማድ ዘከርናቸው (አከበርናቸው) እንላለን እንጅ ከምር አልተማርንባቸውም ማለት እውነት የሚሆነው ።

የትናንቱን በጎ ሥራ ለዛሬውና ለነገው በጎ ጥረት ማጎልበቻ እና ጎጅውን ደግሞ ላለመድገም መማሪያ ለማድረግ ከምር ፍቃደኛና ዝግጁ የሆነ ትውልድ ብቻ ነው ከዘመን ጋር አብሮ የሚዘምንና በምንነቱና በማንነቱ የሚኮራ ። ታሪኩን በአግባቡ የማይረዳ እና ከዛሬውና ከነገው ምንነቱ ፣ማንነቱ፣ እንዴትነቱ እና ከየት ወደ የትነቱ ጋር እያስተያየ ወደፊት የማይገስግሥ  ትውልድ ሥር አልባ (root;ess) ነው ። የተክልን  ሥር ምንነትና ጠቀሜታ ማብራራት የሚያስፈልግ  አይመስለኝም ። ሥሩ ቢጎዳ ወይም ቢቆረጥ ውጤቱ ምን እንደሚመስል ጤናማ አእምሮ ላለው የሰው ልጅ ሁሉ ግልፅና ቀላል ስለሆነ የተለየ  ማብራሪያን ወይም ትንታኔን አይጠይቅም  ።

 

እንደ እኔ አረዳድ ታላቁን የ123ኛ የአድዋ ድል መታሰቢያ ያከበርነው ከላይ በጠቅሉ ከጠቀስኩት እጅግ ድብልቅልቅ ስሜት ጋር ነው ።

ይህ ትውልድ አለመታደል ሆኖበት ሳይሆን በእራሱ ልክ የሌለው ደካማነት ያጋጠመውን ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊ ፣ ሞራላዊና ድርጅታዊ  ቀውስ ባጋጠመው ቁጥር ነገረ ሥራው ሁሉ የፖለቲከኞችንና የፖለቲካ ኩነቶችን  ቴምፕሬቸር መውጣትና መውረድ እየተከተለ ሰሜቱን ማስተንፈስ እንደ ትልቅ የፖለቲካ ሥራ የቆጠረው ይመስላል ።

የለውጥ አራማጅ የምንላቸውን ፖለቲከኞች በውዴታ ግዴታ ወደ መሪነት ያመጣቸው  የኢትዮጵያ ህዝብ የዘመናት የመከራና የውርደት ቀንበርን ተሸክሞ ለመቀጠል ከማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱና በቃኝ ብሎ በመነሳቱ የመሆኑ እውነትነት የለውጥ ፍለጋ ፖለቲካ እወቀት ሀሁ ነው ።

ከህገ መንግሥት ተብየው ጀምሮ ኢህአዴግ የተከላቸው አበይት የጥርነፋ መሣሪያዎች (instruments) ባልተነኩበት የፖለቲካ ድባብ ውስጥ ሆኖ እዚያና እዚህ የሚስተዋሉ የጥገና ሽርፍራፊዎችን “እፁብ ድንቅ” ሊያሰኝ በሚችል የቋንቋና የአንደበት “ውበት” እያገዘፍንና እያሽሞነሞን ከቶ ልቀጥል አይገባም ።  እራሳችንን ከመሸንገል (ከማታለል) ክፉ ልማድ ለመላቀቅ ማድረግ ያለብንን የአርበኝነት (የአገር ወዳድነት፣ ለነፃነትና ለፍትህ ተጋዳይነት ፣ የአብሮነት ብልፅግና እና  የሰላም ሰማእትነት ፣ወዘተ) ተልእኮ ገና  ሀሁ ብለን ጀመርነው እንጅ አቅጣጫውን ከመዳረሻው እንኳ በቅጡ አላቆራኘነውም።

አሁንም ከስህተታችን ተምረን  በአግባቡ  ወደ የምንፈልገው የጋራ ግብ (መዳረሻ) የሚወስደንን ትክክለኛ አቅጣጫ በሚከተልእና  እርምጃቻችንን በሚያቀላጥፍ አኳኋን ከተጠቀምንበት እንደ አንድ አገር ህዝብ የተጋረጠብንን አደጋ አክሽፈን የምንፈልገውን ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ማድረግ ይቻለናል ። ለነገሩ እንደ ዜጋ ተከብረንና ተከባብረን የምኖርባትን አገር ህልውና ለማስጠበቅም ሌላ የተሻለ አማራጭ የለንም ።

መልካሙን ሁሉ ተመኘሁ !!!

haile larebo
Previous Story

የሊቅ ዐቢይ አስቸጋሪ ምርጫ።የግል አስተያየት – ከ(ፕ/ር ኀይሌ ላሬቦ)

pg7 logo 1
Next Story

ግንቦት ሰባት ከልምድህ…ግርማ በላይ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop