March 4, 2019
30 mins read

ሽግግር ስንል ምን ማለታችን ነው? – ገለታው ዘለቀ

ለመሆኑ ሽግግር ስንል ምን ማለታችን ነው? ብለን ከጠየቅን የሚከተሉት አራት መሰረታዊ ነገሮች ወደ አእምሯችን ይመጣሉ

  1. አሻገሪ ኣካል
  2. ተሻጋሪ ነገሮች
  3. የሽግግር ዘዴ (methodology)
  4. የጊዜ ሰሌዳ (Time frame)

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አራት ጉዳዮች ሽግግር የምንለውን ሃሳብ በጥራት እያገላበጥን እንድናየው ይረዱናል። በመሆኑም በነዚህ ጉዳዮች ላይ ጥቂት እንወያይ።

  1. አሻገሪ ኣካል

ኢትዮጵያ ሽግግር ላይ ናት ካልን በአንደኛ ደረጃ የምንመለከተው ነገር ማን ነው ኣሻጋሪው ሃይል? ማን ነው ይህንን ሃላፊነት የወሰደው? ወይም ሽግግሩን የሚመራው ቀዳሚ ሃይል ማን ነው? ከፍተኛ ኣስተዋጾ የሚጠበቅባቸው ኣካላት እነማን ናቸው? የሚለውን እንድናስብ ያደርገናል። ብዙ የዓለም ሃገሮች ወደ ሽግግር ሲገቡ የተለመደው ነገር የሽግግር መንግስት መመስረት ነው። በኛ ሃገር ግን ለየት ያለ ነገር የሚታይ ሲሆን መንግስት ራሱን ሪፎርም እያደረገ የሽግግር ስራውን ለመስራት ቃል በመግባቱና በተቃዋሚው ዘንድም የይሁንታ ምልክት በመታየቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መሪው ዶክተር ኣብይ የሚመሩት የለውጥ ሃይል ሆኗል። ይህ ሃይል ሽግግር ላይ ኣተኩሮ የሽግግር ስራ እንዲሰራ ይመከራል። ታዲያ ይህ ሃይል የሽግግሩን ስራ ይምራ እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ሽግግሩን በተለያዩ መንገዶች ሊመሩ የሚገባቸው ሃይሎች የሚከተሉት ናቸው።

  • ራሱ የለውጡ ሃይሉ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል
  • ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይላት
  • የተለያዩ ኮሚሽኖች ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የእርቅ ኮሚሽኑ፣ የማንነት ኣስተዳደርና ወሰን ኮሚሽኑና የመንግስት ተቋማት
  • የሲቪክ፣ የሃይማኖትና የባህል ተቋማት
  • የትምህርትና የምርምር ተቋማት በዋና ዋና ተዋናይነት የሚጠቀሱ ናቸው። ለውጡ ግቡን እንዲመታ እነዚህ ሃይላት መቀናጀትና በትብብር መስራት ኣለባቸው።
  1. ተሻጋሪ ነገሮች

በጣም መሰረታዊው ነገር ይሄ ነው። ሽግግር ማለት ለውጥ ማለት ነው። ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ሽግግር ካለ የሚለወጡ ነገሮች ኣሉን ማለት ነው። ሽግግሩን የሚመራው አካልም ሃገሪቱን እያሸጋገርኩ ነው ሲል የለውጡን ኣቅጣጫዎች ኣንድ ሁለት ብሎ በግልጽ ማስቀመጥ ኣለበት። የለውጥ ፍኖተ ካርታ የሚባለው ነገር ይሄ ነው። የሚለወጡትን ነገሮች ወይም እንዲለወጡ የፈለግናቸው ነገሮች ምን ምን ናቸው? የሚለውን ኣብጠርጥሮ ማሳየት ግልጽ ፍኖተ ካርታ ተብሎ ይጠራል። በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ በሽግግሩ ወቅት ልትሰራቸው የሚገቡ ሰባት የለውጥ ኣቅጣጫዎች ያሉ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ ተሻገረች የምንለው እነዚህ ሰባት ነገሮች ሲለወጡ ነው። እነዚህ ሰባት ተሻጋሪ ነገሮቻችን የሚከተሉት ናቸው።

  • የፌደራል ስርዓቱ
  • መድብለ ፓርቲ
  • የቋንቋ ማኔጅመንት
  • መሬት ላራሹ (የመሬት ላራሹ ጥያቄ)
  • የማንነት አያያዝ (የብሄር ጥያቄ)
  • ሃቀኛ ምርጫ
  • የአዲሱ ቤታችን ፕላንና የህገ-መንግስት መሻሻል

እነዚህ ሰባት የለውጥ ኣቅጣጫዎች በሽግግሩ ጊዜ ሊሰሩ የሚገባቸው ናቸው።

የአንባቢን ጊዜ ስልሻማ እነዚህን ሰባት የለውጥ አቅጣጫዎች በጥቂቱ ላብራራ።

  • የፌደራል ስርዓቱ

ኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓቷን በዚህ በሽግግሩ ወቅት መላ ልትል ይገባታል። ከሚለወጡ ነገሮቻችን መካከል ቀዳሚ ስፍራ ያለው ይህ ጉዳይም ነው። የፌደራል ስርዓታችን በሁለት ጽንፎች የተወጠረ ሲሆን በዜግነት ፖለቲካና በብሄር ፖለቲከኞች የገመድ ጉትቻ ሊቀጥል ኣይችልም። ስለሆነም የብሄር ጥያቄ የተባለውን የባህል ኢእክሉነት ሊያሻሽል የሚችል ለባህል አንድ ጥላ ፈጥሮ የፌደራል ስርዓቱን ማሻሻል ይቻላል። የብሄር ባህላዊ የፌደራል ስቴቶችና የዜግነት የፖለቲካና የኢኮኖሚ የፌደራል ስቴቶች ፈጥሮ መሃከለኛ የፌደራል ስርዓት መገንባት ኣንዱ የለውጥ ኣቅጣጫ ቢሆን ጥሩ ነው። በለውጥ ጊዜ ኣንዱ ሊለወጥ የሚገባው ጉዳይ ይህ የፌደራል ስርዓታችን ጉዳይ ነውና የለውጡ ሃይል በዚህ ላይ ኣቋም ሊይዝ ይገባዋል።

  • መድብለ ፓርቲ

ሌላው በሽግግሩ ወቅት ሊሻገር የሚገባው ጉዳይ ደግሞ የፓርቲ ስርዓታችን ነው። ኢትዮጵያ ወደ መድብለ ፓርቲ ስርዓት ኣልገባችም። አሁን ያለው የፖለቲካ መስመሯ ከመድብለ ፓርቲ ስርዓት ጋር  በሚከተሉት መንገዶች ሲፈተሽ ችግር ኣለበት።

ሀ. ከስብስቦች መካከል ተገቢውን ስብስብ መምረጥ

ማህበረሰብ አብሮ ሲኖር ብዙ ስብስቦች ኣሉት። የብሄር ስብስብ፣ የሃይማኖት ስብስብ፣ ሃገራዊ ስብስብ፣ የመልክዓምድር ስብስብስ፣ የጎሳ ስብስብ ወዘተ. ብዙ ስብስቦች አሉ። አንድ ሃገር ፖለቲካዊ ኣስተዳደር ሲመሰርት እነዚህ ስብስቦች ሁሉ የፖለቲካ መደራጃ እንዲሆኑ ኣይፈቅድም። አንዱን ስብስብ መምረጥ የግድ ነው። ስብስቦችን ሁሉ የፖለቲካ መደራጃ ማድረግ ከፈለግን ምርጫ ሊያምረን ኣይችልም። ከሁሉ በላይ ህግና ስርዓት የሌለው ትርምስ እንፈጥራለን። የፖለቲካ መጫወቻውን ሜዳ ቅጡን ባጣ ስርዓት እንሞላዋለን።

የዓለም ህዝቦች ከስብስቦች ሁሉ ሃገራዊ ስብሰብን ለፖለቲካ መደራጃነት ይመርጣሉ። ጥቂት ሃገራት በሃይማኖት ስበስብ ላይ የፖለቲካ መደራጀትን ይፈቅዱ ይሆናል። እጅግ ኣያሌው የዓለም ህዝብ ግን ሃገራዊ ስብስቡን መርጧል። ይህ ስብሰብ አግላይ ስላልሆነ ሁሉን ዜጋ ኣቃፊ ስለሆነ ተመርጧል። በኢትዮጵያ ሁኔታ አንዱ ችግር መልክዓምድራዊ ስብስብ፣ የብሄር ስብስብስ፣ ብሄራዊ ወይም ሃገራዊ ስብስብስ ሁሉ የፖለቲካ መደራጃ ይሆናሉ። ይህ ነገር ኣንዱ መለወጥ ያለበት ነገር ነው። ኢትዮጵያ ለፖለቲካ ቤት መስሪያዋ ሃገራዊ ስብስብን መርጣ ሌሎቹን ልታስቆም ይገባል።  ዴሞክራሲ ማለት ስብስብን ሁሉ ፖለቲሳይዝ ማድረግ ኣይደለም። ስብስብን ሁሉ ፖለቲሳይዝ ማድረግ ጸረ ዴሞክራሲ አካሄድ መሆኑን ማጤን ተገቢ ነው።

ለ.  መንግስት ለመመስረት

የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ማለት ፓርቲዎች ለስልጣን ተወዳድረው ኣሸናፊው መንግስትን የሚመሰርትበት ስርዓት ማለት ነው (A multi-party system is a system in which multiple political parties across the political spectrum run for national election, and all have the capacity to gain control of government offices, separately or in coalition) የኢትዮጵያን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁኔታ ስናይ በተለይ በተናጠል መንግስት መመስረት የሚችሉ ዓይደሉም። በብሄር ላይ የተመሰረቱ ስለሆኑ እዚያው ብሄራቸው ኣካባቢ የሚቀሩ እንጂ መንግስት መመስረት ኣይችሉም። ባለፉት አመታት የኢህአደግ እህት ፓርቲዎች የሚባሉትን ስናይ እነዚህ ፓርቲዎች ሁል ጊዜ ኣካባቢያዊ እንደሆኑ የቀሩ ናቸው። ባለፉት ዓመታት ኣንድም የጋምቤላ፣ የሃረሪ፣ የኣፋር፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ተወላጅ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር እንዳይሆን እድል ተነፍጎ ቆይተናል።ይህ የሆነበት ምክንያት እነዚህ ፓርቲዎች መንግስት መመስረት ስለማይችሉና የኢሃዴግ ኣባል ስላልሆኑ ይህ ኣስገራሚ ነገር ተፈጥሮ ቆይቷል። ከኢሃደግ ኣባል ፓርቲዎች መሃል ኣንዱ ፓርቲ ኢሃደግ ባይመቸውና ቢወጣ ተወዳድሮ መንግስት መመስረት ኣይችልም። ኣካባቢያዊ ሆኖ በዚያው በሰፈሩ ይቀራል። ይህ ከመድብለ ፓርቲ ስርዓት ጋር ኣይሄድም። ስለዚህ ኣንዱ መለወጥ ያለበት ነገር ፓርቲዎች ተወዳድረው  በቅንጅትም ሆነ በተናጠል መንግስት መመስረት የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ሲሆን ይሄውም ፓርቲዎች በብሄራዊ ስብስብ ጥላ ስር እንዲደራጁ ማድረግ ነው።

ሐ. መጠፋፋት ኣለበት

በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ በምርጫ ጊዜ መሸናነፍ ኣለ እንጂ ኣሸናፊው መንግስት ሲመሰርት ተሸናፊውን በህግ ኣያጠፋውም። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኣሰላለፍ ውስጥ መጠፋፋት ኣለ። ለምሳሌ ያህል በአሁኑ ሰዓት ምርጫ ተካሂዶ የዜግነት ፖለቲካ የሚያራምደው ፓርቲ ኣሸነፈ እንበል። ይህ ፓርቲ ሲያሸንፍ የሚመጣው ለውጥ ስር ነቀል ነው። የብሄር ፌደራል ስርዓቱን ሲለውጥ የብሄር ፖለቲካም ይቀየራል። በህግ ይለወጣል። በዚህ ጊዜ ይህ የአንድነት ሃይሉ በምርጫ ሲያሸንፍ ሌሎቹን ዘውግ ተኮር የሆኑትን ያጠፋል ማለት ነው። ዘውግ ተኮር የሆኑት ስልጣን ሲይዙ የአንድነት ሃይሉን ሊያጠፉ ይችላሉ። ወይም ብዙ ሰው ላለማስከፋት ሲሉ እንዳይሞቱ እንዳይሽሩ እያደረጉ እንዲኖሩ ያደርጓቸዋል። ይህ  ከመድብለ ፓርቲ ሰርዓት ጋር ኣይሄድም። ስለዚህ አንዱ የሽግግር ለውጥ መሆን ያለበት ይሄ ነው። በአጠቃላይ ከምርጫው በፊት ሃገራችን ልትለውጠው የሚገባው ነገር ይሄ ነው። ከስብስቦች ማሃል ሃገራዊ ስብስብን መርጦ በዚያ ላይ ተደራጅቶ መንግስት ለመመስረት መሮጥ ያስፈልጋል። ይህ ሳይሆን ምርጫ መግባት ሃገሪቱን ወደ ዴሞክራሲ ኣያሻግራትም።

  • የቋንቋ ማኔጅመንት

ሶስተኛው በሽግግር ጊዜ ሊለውጥ የሚገባውና ልናሻግረው የሚገባው ነገር የቋንቋ ማኔጅመንታችን ጉዳይ ነው።

ብዙህ የሆነች ኢትዮጵያን ለማስተዳደር የቋንቋ ጉዳይ ዋና ጥያቄ ነው። ቡድኖች በራሳቸው ቋንቋ ተጠቅመው መገልገል ችለው በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ጎን የሚያግባባቸው ቋንቋ ላይ ማሰብ ተገቢ ነው። በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ የቋንቋ ኣሰራሯን መመርመር ኣለባት። ቋንቋዎችን ሁሉ በታችኛው የስልጣን ርከን አካባቢ ኦፊሲያል ኣድርጎ ሌላ የማህበር ቋንቋ እንዲኖር ተስማምቶ መሻገር ያስፈልጋል።

  • የመሬት ላራሹ ጥያቄ

ይህን ጥያቄ በዚህ የሽግግር የጽሞና ጊዜ እንደገና ማብላላት(articulate ማድረግ ) እና ተገቢ ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው። መሬት ላራሹ እስካሁን በሙሉ ሃይሉ ያልተመለሰ ጥያቄ ነው። የአሁኑ ትውልድ ይህንን ጥያቄ የበለጠ ሊያፍታታው ሊያሰፋውና የኢኮኖሚ የሃብት ዝውውር ጥያቄ ኣድርጎ ሊመለከተው መልስም ሊሰጠው ይገባል። መሬት ላራሹ ዛሬ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄን ያካትታልና ይህንን ጥያቄ መመለስ መሬትን ለሚያርሰው ገበሬ፣ ለከተሜው ነዋሪ የባለቤትነት ሰርተፍኬቱን መስጠት ያስፈልጋል። ይህንን ካላደረግን ኣልተሻገርንም።

  • የብሄር ጥያቄ

የማንነት ጥያቄን የሚመለስ ሲስተም መዘርጋት የሽግግር የቤት ስራ ነው። የፌደራል ስርዓቱ ሲስተካከል የአርበኞች ቤት በማቋቋም የማንነት ጥያቄን መመለስ ይቻላል። ከዚህ ቤት በተጨማሪ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ብሄር ተኮር ጥያቄዎችን ለመመለስ የካሳ ኣሰራርን፣ ሁሉን የሚክስ ሲስተም መቅረጽን ይጠይቃል። የሽግግሩ መንግስት እነዚህን ጉዳዮች መጀመር ያለበት ሲሆን እኩልነትን ለማምጣት ግን ከምርጫ በሁዋላ የሚመጡ መንግስታት የሚሰሩበት ጉዳይ ይሆናል።

  • ምርጫ

አንዱ የምናሻግረው ነገር ምርጫችንን ነው። እስካሁን በምርጫ ቀልደናል። ደርግ የኢትዮጵያን ህዝብ ምርጫ እንዳማረው ኣይቶ ጥቁርና ኣረንጓዴ  ቀለም ያላቸውን ካርዶች ኣትሞ ከጨለማና ከልማት ኣንዱን ምረጥ ብሎ ቀልዷል። ህወሃት ኢሃዴግ የምርጫ ቦርዱን በጁ ይዞ፣ የፖለቲካ መስመሩን ለምርጫ እንዳይመች ኣድርጎ በምርጫ ሲቀልድ ኖሯል። አሁን ወደ ሃቀኛ ምርጫ መሻገር ከቻልን ነው ሃገራችን ተሻገረች የምንለው። የዚህ የሽግግር መንግስት የመጨረሻው የሽግግር ምእራፍ መዝጊያው ምርጫ  ነው። ምርጫ ኣድርገን ኣሸናፊው ፓርቲ ስልጣን ሲይዝ ኣዲስ ህይወት ነው የምንጀምረው። የሽግግሩ የመጨረሻ ጫፍ የምርጫው ቀን ሲሆን መንግስት እስከዚያ የሚለወጡ ነገሮችን ለውጦ በዚያ ቀን ይህን የሽግግር ምእራፍ ይዘጋል። ዋናው ጉዳይ ግን ለምርጫ ተፈላጊው ሰው ኣማራጩ ሃይል ነው። የሚመረጡት ፓርቲዎች ጥራት ወሳኝ ነው። ጥሩ ምርጫ ቦርድ ኖሮን ኣማራጭ ከሌለን ኣንሻገርም። ስለዚህ ነው ከፍ ሲል ወደ መድብለ ፓርቲ ስርዓት መሻገር ኣለብን የምለው።

  • የአዲሱ ቤታችን ፕላን፣ የህገ-መንግስት መሻሻልና የሲስተም ጉዳይ

በሽግግሩ ጊዜ ኣንዱ የምናስተካክለው ነገር  የኢትዮጵያን የመንግስት ስርዓት መወሰን፣ ለምሳሌ ፓርላመንታሪ ይሁን፣ ፕራዚደንሺያል ይሁን፣ ከተቋማት መካከል የትኞቹ የዴሞክራሲ መርሆዋቻችንን ይጥሳሉ የሚለውን አጥንቶ መለወጥ ያስፈልጋል። ጥርት ያለ የመንግስት ሲስተም ከምርጫ በፊት  ያስፈልጋል። ተቋሞቻችንን ስንፈትሽ ለምሳሌ የፌደሬሽን ምክር ቤት ሲቋቋም ጀምሮ አመሰራረቱንና የስራ ሃላፊነቱን ከዴሞክራሲ መርሆዎች ኣንጻር መገምገም ተገቢ ነው። የፌደሬሽን ምክር ቤት የህግ ትርጉም ስራ መስራቱ ከዴሞክራሲ መርሆ ጋር ይሄዳል ወይ? የሚለውን ማጥናትና ማስተካከል ተገቢ ነው። ይህ የሽግግር ጊዜ እንዲህ ዓይነት ተቋማቂ ጉዳዮችን በሰከነ መንፈስ የምናይበት ጊዜ ነው።

እነዚህ ለውጦች ሁሉ የህገ ማእቀፍ ይሻሉና አንዱ የሽግግሩ ስራ ህገ መንግስቱን ማሻሻልና ዘመናዊ ማድረግ ነው። ህገ-መንግስቱ ከስያሜው ጀምሮ ችግር ኣለበት። ብዙ እምቅ ችግሮችን ይዟል። ከዴሞክራሲ መርሆዎች ጋር የማይሄዱ “የልዩ ጥቅም” ጽንሰ ሃሳብ ይዞ ቁጭ ያለ ነው። ኢትዮጵያ ይህ ኣይመጥናትምና ህገ መንግስቱን ማሻሻል ኣንዱ የሽግግራችን ኣካል ነው። ህገ መንግስት ሳይሻሻል ተሻግረናል ማለት ኣንችልም።

  1. የሽግግር ዘዴ (methodology)

ከፍ ሲል ኣሻጋሪው ሃይል ማን ነው? እንዲሻገሩ የምንፈልጋቸው ነገሮች ምን ምን ናቸው? ብለን ተወያይተናል። ሶስተኛው ታሳቢ ነገር ደግሞ ዜዴ ነው። እንዴት ነው የምንሻገረው? የሚለው ነገር ማለት ነው። ሶስት ኣማራጮች ኣሉ

  • በምርጫ
  • በህግ (የሽግግር መንግስቱ ህግ እያወጣ ሁኔታዎችን መለወጥ)
  • በብሄራዊ መግባባት

የመጀመሪያው ኣሳብ ጥሩ ኣይደለም። በሽግግር ወቅት ሊሰሩ የሚገባቸውን ሳንሰራ እንዲሁ እንዳለን ምርጫ እንግባና ኣሸናፊ ሲመጣ ያ ፓርቲ መንግስት መስርቶ የሚቀይረውን ይቀይር የሚለው ኣሳብ ብዙ እምቅ ችግሮች ኣሉበት። በአሁኑ ሰዓት ኣንደኛ መድብለ ፓርቲ ስርዓት የለም፣ ሁለተኛ ባሉት የፖለቲካ ሃይላት መካከል ያለው ልዩነት በምርጫ የሚፈታ ኣይደለም። ምን ኣልባትም ምርጫው ብጥብጥ ሊያመጣ ይችላል። በአንድ የእግር ኳስ ሜዳ ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ኣስር ኳስ ይዘው፣ የተለያዩ ማልያ ለብሰው፣ እንደፈለጉ ኣይራገጡም። መስመር ያስፈልጋል። በአንድ በኩል ያሉት ኣንድ ቀለም፣ በሌላ በኩል ያሉት ኣንድ ቀለም ዳኛው ሌላ  ቀለም ያለው ማልያ ለብሰው ኣንድ ኳስ ይዘው ይዋጣላቸዋል። ፖለቲካም እንደዚህ ነው። ዳኛውና ተጨዋቾቹ በሚገባ መለየት ኣለባቸው። ስለዚህ ምርጫ ተስፋ የሚሆነን የመድብለ ፓርቲው ስርዓት ሲለወጥ ነውና በሽግ ግሩ ወቅት ይህ ነገር መስተካከል ኣለበት። የዚህ መንግስት ዋና ስራ ለምርጫ ሃገሪቱን ማዘጋጀት ነው ሲባል እነዚህን የሽግግር ስራዎችን ሁሉ መስራትን ያካትታል።

ሁለተኛው የመሸጋገሪያ ዘዴ ደግሞ የሽግግር መንግስቱን የሚመራው የለውጥ ሃይል ባለው ፓርላማ በኩል ህግ እያወጣ እነዚህን ለውጦች መምራት ነው። ይሄ ኣካሄድም ኣደገኛ ነገሮች ኣሉት። ግጭቶችን ቀስቅሶ ለውጡን ሊጎዳብን ይችላል። የለውጥ ጊዜ ብዙ እምቅ ችግሮች ስላሉት ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

ሶስተኛው ዘዴ በብሄራዊ መግባባት ዘዴ ሽግግሩን መምራት ነው። ይሄ በጣም ተመራጭ ነው። እነዚያ እንዲሻገሩ የምንሻቸውን ጉዳዮች እንደ ፍኖተ ካርታ ኣሳይተን ከፍ ሲል የጠቀስናቸውን የለውጥ ኣሻጋሪ ሃይላት ሁሉ ማግባባት ኣብሮ መስራት ይጠቅማል። ሽግግሩ በመግባባት ላይ ሲያተኩር፣ መነሻችን የጋራ ቃል ኪዳን ሲሆን ለውጡ ግቡን ይመታል። ያሉትን ተግዳሮቶች በጣም ያጠባል። ስለዚህ መንግስት የለውጥ ሮድ ማፕ ቀርጾ በዚያ ላይ የማግባባት ስራ ሰርቶ ብዙውን ሃይል ኣሳምኖ ከምርጫው በፊት የሚለወጡትን ለውጦ ለምርጫው ድግስ ማድረስ አለበት:: በሃቀኛ ምርጫ የለውጡን የሽግግር ምእራፍ መዝጋት ይጠበቅበታል።

  1. የጊዜ ሰሌዳ (Time frame)

ሽግግር የጊዜ ሰሌዳ ኣለው። በዓለም ላይ የተለመደውና በብዙ ምሁራን የሚደገፈው የሽግግር ጊዜ ሁለት ዓመት ነው። የሆነ ሆኖ በኢትዮጵያ ሁኔታ ጉዳዮን ኣጥንቶ የሽግግሩን የመጨረሻ ምእራፍ ማለትም የምርጫ ቀኑን ማሳወቅ ተገቢና ኣንዱ የለውጥ ፍኖተ ካርታ ፓኬጅ ነው። የጊዜ ሰሌዳው  የሚይዘው የምርጫውን ቀን ብቻ ሳይሆን የምናሻግራቸውን ነገሮች የስራ እቅድ መያዝ ኣለበት። ሽግግራችን ሁሉን ኣሳታፊ ሆኖ በቅደም ተከተል ለመስራት መንግስት ፍኖተ ካርታውን ሲሰራ የሚሻገሩ ነገሮቻችንን በተቻለ በጊዜ ከፋፍሎ ማሳወቁ ብዙ ጥቅም ኣለው።

 

ማጠቃለያ

ሃገራችን ኢትዮጵያ በክቡር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት የሽግግር ጊዜ ላይ ነች። እኚህ ሰው ለለውጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት ብዙ ጊዜ ገልጸዋል፣ በተግባርም ያየናቸው ለውጦች ምስክሮች ናቸው። ከሳቸው ጎን የተሰለፈው ሃይልም ሌት ከቀን እየሰራ እንደሆነ እናምናለንና ይህንን ማበረታታት ተገቢ ነው። መንግስትን ለለውጥ የምናበረታታው በጭብጨባ ብቻ ሳይሆን በምንችለው ሁሉ ነው። በቅርቡ ዶክተር ኣብይ ሲናገሩ መንግስታቸው  ስድስት ነገሮች ላይ ለመስራት እቅድ መያዙን ገልጸዋል። እነዚህ ስድስት ነገሮች ሰላም፣ ብልጽግና፣ ዴሞክራሲ፣ ብሄራዊ ኩራት፣ ፍትህና ሃገራዊ ኣንድነት ናቸው ብለዋል። እነዚህ ሃሳቦች በሙሉ ቅዱስ ናቸው። እነዚህ ነገሮች የሽግግር ስራ ብቻ ግን ኣይደሉም። ሁል ጊዜም እንደ ህዝብ እንደ ሃገር ስንሰራላቸው የምንኖራቸው ጉዳዮች ናቸው። የለውጡ ሃይል ፍኖተ ካርታ ሳይሆኑ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ፍላጎቶች ናቸው። እንደግፋቸዋልን። ነገር ግን ብሄራዊ ኩራት የብሄር ፖለቲካና የብሄር ፌደራሊዝም ላይ ቁጭ ብለን ኣናመጣውም። ሃገራዊ ኣንድነትን በብሄር ፖለቲካ እርሻ ላይ ኣናገኘውም። ሰላምን ከቋንቋ ፌደራሊዝም መጠበቅ ተላላነት ነው። ዴሞክራሲን ከብሄር ፖለቲካ ሰፈር ኣናገኘውም። ብልጽግናም ቢሆን ከዚህ ስርዓት ኣይመጣም። በመሆኑም ዶክተር ኣብይ ያሏቸውን ቅዱስ ነገሮች ተቀብለን እንደ ረጅም የሁል ጊዜ ግቦቻችን እያየን ለአሁኑ ለሽግግር ጊዚያችን ግን ተግባራዊ የሆነ የሽግግር ጊዜ የመዋቅር ለውጥ ፍኖተ ካርታ ያስፈልገናል። በእኔ እምነት ከፍ ሲል ያነሳሁዋቸው ሰባት ጉዳዮች ለሽግግር ጊዜው እቅድ መነሻ ቢሆኑ የተሻለ ለውጥ እናያለን እላለሁ። አሁን ያለው የዶክተር ኣብይ የለውጥ ሃይል ማተኮር ያለበት ሃገሪቱን ለሃቀኛ ምርጫ ማዘጋጀት ነው። ለሃቀኛ ምርጫ ማዘጋጀት ማለት ደግሞ ከፍ ሲል ያነሳናቸውን የሽግግር ጊዜ ለውጦች ያካትታል። ስለሆነም ብሄራዊ መግባባትን እንደ ሽግግር ዘዴ ይዘን ሃራራዊ ኪዳን ውስጥ ገብተን ሽግግራችንን ማሳመር ተገቢ ነው። አማራጭ የሽግግር መንገድ እንዲሆንልን ብየ የጻፍኩትን መጽሃፍ እንድታነቡት በአክብሮት እጋብዛለሁ።

እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

geletawzeleke@gmail.com

2 Comments

  1. ገለታ ዘለቀ!ጠቃሚና መጋቢ አሳብ ስላስነበቡን እግዚአብሔር ይስጥልን! የእኛ አገር ፖለቲካ ወደፊት የማየት ችግር ስላለበት፣የጀመረውን መንገድ እየሳተም ገደል የመግብት ልምድ ስላለው በየጊዜው የአሳብ መንገዱን የሚጠርጉ ጸሐፍያንና አሳባቸው በእጅጉ ያስፈልጉናል።

  2. There are One of the 304 candidates for the Nobel Peace Prize for 2019 one of the candidates is PM Abiy Ahmed.Out of the 304 candidates 219 are individuals and 85 are organizations. One of the individuals is Abiy Ahmed, Prime Minister of Ethiopia.
    As one of his first major actions after taking office in April 2018, Ethiopian Prime Minister Abiy Ahmed took steps to formally end the conflict with Eritrea, handing over the disputed border city of Badme and signing a “Joint Declaration of Peace and Friendship” on 9 July 2018 with his Eritrean counterpart Isaias Afwerki. In a similarly bold move, Abiy has engaged in dialogue with the many armed, regional Ethiopian opposition groups, succeeding in persuading the Oromo Liberation Front to commit to peaceful participation in the political process.
    Progressive reforms following his rise to power include constitutional and security sector reforms, lifting the state of emergency, pardoning political prisoners, and establishing a ministry for peace. Himself of mixed Oromo and Amhara heritage, his mother being an Orthodox Christian and his father a Muslim, Abiy appointed a cabinet demonstrating a rare sensitivity to political inclusion. The president and half of the ministers are women, including a female minister of defense, and all major ethnic and religious groups are represented.

    Ethiopia is amongst the countries ranked near the bottom of the Human Development Index, and Abiy’s ambitious program for economic and social reform arguably represents a broader, long-term conflict prevention agenda. Similarly, his initiatives to boost economic collaboration and trade in the region, including agreements securing Ethiopian access to ports in neighboring Djibouti, Sudan, Somaliland, and Kenya, bring hope for a more stable and prosperous development for the whole of the Horn of Africa.PM Abiy reading a book, “War on Peace”
    Despite having initiated democratic reforms, Abiy Ahmed has yet to bring about free and fair elections in Ethiopia. In what is still effectively a one-party state, the country ranks below 150 on the V-Dem Liberal Democracy index. While there is precedent for the award of Nobel prizes for contributions to peace processes still underway, the absence of a committed and concrete plan for free and fair elections remains the most serious hurdle to a 2019 peace prize for Abiy.
    A possible co-winner could be Eritrea’s president Isaias Afwerki, in acknowledgement of the peace agreement finally resolving the Eritrean-Ethiopian War.

Comments are closed.

Previous Story

የኢትዮጵያ መሬት ችብቸባ፤ በታሪክ እይታአጼ ዮሐንስና አጼ ካሌብ ቢኖሩ አንዴት ያዝኑ!

Next Story

ጉልበት ዓልባ መሆን ብዙ ርቀት አያሥጉዝም ” – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop