የኢትዮጵያ መሬት ችብቸባ፤ በታሪክ እይታአጼ ዮሐንስና አጼ ካሌብ ቢኖሩ አንዴት ያዝኑ!

ሕብረት ሰላሙ

ከጥንቶቹ ጀግኖቻችን

 

እንደሚታውቀው፤ አጼ ዮሓንስን እጅግ በጣም ከሚያስደንቃቸውና ከሚያስከብራቸው ታሪካቸው ዋነኛው፤ ለውድ ሐገራቸው፤ ለኢትዮጵያ፤ ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር መከበር በቆራጥነት ይከላከሉ የነበረውና ሕይወታቸውንም የሰዉለት መሆኑ ነው። የጀግናው የአጼ ዮሐንስ ራስ ተቆርጦ ሱዳን ከተወሰደ ልክ 120 ዓመት ሆኖታል። እስካሁን አልተመለሰም!

 

አጼ ካሌብማ ይገዙ የነበረው፤ የዛሬውን አያድርገውና፤ ኢትዮጵያ ከኃያላን መንግሥቶች አንዷ በነበረችበት ዘመን በመሆኑ፤ እነየመንንና የዛሬዋን ሳውዲ ዓረቢያን አብዛኛውን ክፍል በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው ይገዙ ነበር።

 

ዛሬስ?!!!

 

ዛሬማ፤ በኢትዮጵያ ላይ የተንሰራፋው በሙስና የተዘፈቀው የውስጥ ጠንቀኛ ጠላት መንግሥት በብዙ አርበኞች ደም ለዘመናት ተጠብቆ የቆየውን አንጡራ የሐገር መሬታችንን፤ እንደ አልባሌ እቃ፤ ለሌሎች ሐገሮች እየቸበቸበው ነው። ኤርትራን ከእናት ሐገርዋ አስገንጥሎ ኢትዮጵያን ለጅቡቲና ለሶማሊላንድ ተንበርካኪ አደረጋት። በሱዳን ወሰን በኩል ያለው ሰፊ ለም መሬት ለሱዳን፤ እንዲሁም ሌሎች ሰፊ ለም መሬቶች፤ “ለኢንቨስትሜንት”rእየተባለ፤ ለሕንድ፤ ለግብጽ፤ ለሳውዲ ዓረቢያ፤ ለጅቡቲ፤ ወዘተ. ድርጅቶች ለግል ጥቅም እየተሸጡላቸው ናቸው። ይህ ሁሉ በግልጽ የሚያረጋግጠው፤ አሁን በሐገራችን ላይ ተጋርጦ የሚገኘው መንግሥት የኢትዮጵያ ጠላት እንጂ ወገን አለመሆኑን ነው። ይህ ሁሉ እኩይ ተግባር አሳዛኝ ቢሆንም፤ በተለይ፤ እጅግ በጣም የሚያስገርመውና የሚያስቆጨው ደግሞ፤ በአባይ ወንዝ አማካኝነት ውሀችንንና አፈራችንን በነጻ በገፍ መለገሳችን ካልቀጠለ ወደ ጦርነት የሚያመሩ መሆኑን ለዛቱት፤ ለግብጾች የኢትዮጵያ መሬት መሰጠቱ ነው። በሱማሌና በኬንያ ወሰኖች በኩል ያሉትም መሬቶች ተመሳሳይ የመሸጥ ተራቸውን እየጠበቁ ይሆን?!!!! ሕዝቡን በዘረኛነት ስልት ከፋፍሎት እርስ በርሱ እንዲተናነቅ እያደረገው ነው። ይህ ሁሉ እኩይ ተግባር እየተከናወነ ሳለ፤ ብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በረሐብ አለንጋ እየተቀጡ ፍዳቸውን እያዩ ነው። ኢትዮጵያ፤ የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው የሰው ልጅ ልማት መስፈርት፤ ከመቶ ሰባ ሰባት ሐገሮች መቶ ሰባኛ ናት!

 

የኤርትራ መገንጠል ሰላምና ልማት በማስገኘት ፈንታ ያስከተለው ውጤት እልቂት፤ የባሰ ድሕነትና አጅግ የከፋ ጭቆና ብቻ ነው። ጎረቤት ከሆነችው፤ ክሱማሌያ ጋርም የተከናወነው የደም መቃባት ጠባሳ ብቻ ነው።

 

አጼ ዮሐንስና አጼ ካሌብ የዛሬዎቹን ጉደኞች የኢትዮጵያ መሪዎች ድርጊት ማየት ቢችሉ ኖሮ የደም እንባ ያለቅሱ እንደ ነበረ አይጠረጠርም!!

 

እኛስ በሕይወት ያለነው፤ ኢትዮጵያውያን፤ ምን እያደረግን ይሆን?!

 

ሰፊ ለም መሬትና ለሌሎች ሐገሮች የተትረፈረፈ ውሀ (ለግብጽ ከሚጎርፈው ውሀ ሰማኒያ ስድስት በመቶው ከኢትዮጵያ ነው) በሐገራችን እያለ፤ በስንኩል አገዛዝ ምክንያት፤ በድህነትና በገዳይ ደዌዎች ስለምንሰቃይ አብዛኞቻችን ለእለት ኑሮአችን ከማሰብ ሌላ ለሐገራችን ሉዓላዊነት መቁዋቁዋም ተስኖን ይሆን? ጥቂቶቻችንስ፤ ለሐገራችን ሉዓላዊነት እየታገልን አንዳንዶቻችንም በወያኔ የጭቆና አንግልት እየተሰቃየን፤ ሕብረት ተስኖን የምንገኝ አይደለን? ሌሎቻችንስ የሐገራችንን ጉዳይ አንደ ባእድ በሩቁ እያየን እጃችንን አጣምረን የምናይ አይደለን?

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሚፈርስ አገርና የሚበተን ሕዝብ እንዳይኖር እንትጋ (መላኩ አያለው)

 

የነአጼ ዮሐንስ ጀብድ

 

በአጼ ዮሐንስ፤ በነራስ አሉላና ሌሎች ጀግኖች የተመራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኢጣልያኖች፤ ከግብጾችና ከደርቡሾች የተቃጣበትን ጥቃት መመለስ እንደቻለ፤ እነተክለጻድቅ መኩሪያ፤ ስቬን ሩበንሰን፤ ባሕሩ ዘውዴና ሌሎችም ብዙ የታሪክ ጸሐፊዎች በሰፊው ዘግበውታል። ግብጾችን በጉንደትና በጉርዓ፤ ኢጣሊያኖችን በዶጋሊ ጦርነቶች ድባቅ እንደመቱዋቸው የታወቀ ነው።

 

 

“የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአድዋ ድል”rበተሰኘው የብላቴን ጌታ ሕሩይ ወልደሥላሴ መጽሐፍ (ገጽ 184-187)፤ ስለ አጼ ዮሐንስ የመጨረሻ ጀብድ እንደሚከተለው ተጽፉዋል፤

 

“አጼ ዮሐንስም ……….rደርቡሽ ወደ ኢትዮጵያ ወሰን ሊመጣ ይሰናዳል ማለትን ሰምተው ነበርና እርሱ

ሳይወጣ እርሳቸው ወደ መተማ ወርደው ለመዋጋት ሲሉ ፊታቸውን ወደ መተማ አዞሩ። ………………..

 

ከዚህም በ(ሁዋ)ላ አጼ ዮሐንስ ከጎጃም ተነሥተው በአገው ምድር አልፈው ወደ ደምቢያ ወርደው ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትና ደርቡሾች ወደ ተዋጉበት ሣር ውሀ ወደሚባለው ሥፍራ ሲደርሱ በጦርነት ውስጥ የሞቱትን የሕዝበ ክርስቲያን አጥንት ብዛቱን አይተው አጅግ አዘኑ። ልባቸውም እንደ እሳት ተቃጠለ።

 

………….. ከዚያም ወደ መተማ ገሠገሡ። አሳባቸውም በፊት መተማን አጥፍተው ቢመቻቸው ወደ ትልቁ

ከተማ ወደ ኡምዱርማን ለመሄድ ነበር። ከአጼ ዮሐንስም ጋራ የዘመቱ መኩዋንንቶች ትልቁ ራስ አርአያ ቢትወደድ ገብረ መስቀል፤ ራስ ሚካኤል፤ ራስ ሐይለ ማርያም፤ ራስ አሉላ፤ ራስ መንገሻ፤ ራስ ሀጎስ ነበሩ። የዘመተውም ሠራዊት ሁሉ ቁጥሩ 150 ሺ ነበር።

 

ከዚሁም ከ150 ሺ ሀያው ሺ ፈረስኛ ነው። ………………………………………….. ከዚያም አጼ ዮሐንስ

የየካቲት ወር ሲያልቅ መተማ ደረሱ። ለጦሩ አበጋዝ ለዘኬም “መጣሁብህ ተዘጋጅተህ ቆየኝ። አንደ ሌባ በድንገት መጣብኝ አንዳትለኝ መምጣቴም የክርስቲያንን ደም ለመበቀል ነው”rብለው ላኩበት።

 

በመጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም ቅዳሜ ጦርነት ተጋጠሙ። ……….. በብርቱ

ጦርነት ከተዋጉ በሁዋላ ግን የከተማውን ቅጥር ባንድ ወገን ጥሰውት ገቡ። በከተማው ውስጥ ያለ ስው ሁሉ እየሸሸ እንዲወጣ ብለው ቤቱንና ቅጥሩን አቃጠሉት። ባንድ ወገንም ዘልቀው ግምጃ ቤቱን ያዙት። የአቡ አንጋንም አጽም ለማቃጠል ቤቱን ሁሉ ይቀሰቅሱ ጀመር። ይህንንም ያሰቡበት ምክንያት አቡ አንጋ ጎንደርን አጥፍቶ ሊቃውንቱን ሁሉ በእሳት አቃጥሉዋቸው ነበርና የዚያን ብድር ለመመለስ ነበር። ነገር ግን አጼ ዮሐንስ ምንም አጠንክረው ቢዋጉ ድል ማድረጋቸው ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ አይሆንምና ድል ለማድረግ ጥቂት ሲቀራቸው አጼ ዮሐንስም በጠመንጃ ቆሰሉና ወሬው ያንጊዜውን በየሠልፉ ውስጥ ተሰማ። መኩዋንንቱም ወታደሩም ከቅጥሩ ውስጥ እየወጡ መሸሽ ጀመሩ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በዓሉ ግርማን ለመግደል ሴራ ያስፈልግ ነበር ወይ?

 

  • ቀጥለውም……ለርሱ (ለራስ መንገሻ) ተገዙ ብለው የኑዛዜ ቃል ተናገሩና በማግሥቱ አረፉ። ያጼ ዮሐንስን ሬሳ በሣጥን ውስጥ አግብተው ይዘው ወደ አትባራ ወንዝ ፊታቸውን መልሰው ሸሹ።

………ደርቡሾችም በጦርነት ውስጥ የሞቱትን የኢትዮጵያ መኩዋንንት ሁሉ ራሳቸውን እየቆረጡ

ኦምዱርማን ድረስ ለከሊፋ አብደላ ላኩለት። ………..

 

በመጋቢት ሶስት ቀን የአጼ ዮሐንስን ሬሳ ይዘው የሚጉዋዙትም መኩዋንንቶች በአትባራ ወንዝ ዳር ሠፍረው ደረሰባቸውና አደጋ ጥሎ ተዋጋቸው። …………

 

ከዚህ በሁዋላ ደርቡሾቹ በድንኩዋን ውስጥ አንድ ትልቅ ሣጥን አገኙ። ሣጥኑም በሰም ተመርጎ ነበር። በመጀመሪያ ገንዘብ ያለበት መስሉዋቸው ነበር። ቢከፍቱት ግን የሰው ሬሳ ሆኖ አገኙት ወዲያው ከምርኮኞቹ አንዱን ሰው አቅርበው ቢጠይቁት የአጼ ዮሐንስ ሬሳ ነው አ(ላ)ቸው። ………….. ደርቡሾችም

 

የአጼ ዮሐንስ ሬሳ መሆኑን ከተረዱ በሁዋላ ራሳቸውን ቆርጠው ለከሊፋ አብዱላሂ ወደ ኡምዱርማን ሰደዱለት። ከሊፋ አብዱላሂም ያንን ባየ ጊዜ የደስታ ነጋሪት እንዲመታ መለከት እንዲነፋ አድርጎ የከተማው ሰው ሁሉ ይህንን በመስማት ደስ አለው። ከሶስት ቀን በሁዋላ የአጼ ዮሐንስን ራስ በእንጨት ላይ ሰክቶ በግመል ጀርባ ላይ አድርጎ ገበያ ለገበያ መንደር ለመንደር እያዞረ ለትልቅ ለትንሹ ለሴት ለወንዱ ሲያሳያቸው ዋለ ይባላል።”

 

የጀግናው የአጼ ዮሐንስ ራስ ተቆርጦ ሱዳን ከተወሰደ ልክ 120 ዓመት ሆኖታል። አሁንም ተወርውሮ ያለው ካርቱም ከተማ በሚገኝ የሱዳን ሚዩዚየም ውስጥ ነው ይባላል።ለሐገር የመቆርቆር ስሜት ያለው መንግሥት ቢኖር፤ የአጼ ዮሐንስን ራስ አስመልሶ ከሌላው ስውነታቸው ጋር በክብር እንዲቀበር ማድረግ አይገባውም ነበር?!!!

 

አጼ ዮሐንስና ሌሎችም ስፍር ቁጥር የሌላቸው ኢትዮጵያውያን የተሰዉለትን የሐገራችንን መሬት ክሕደት በተጠናወጠው ስልት ለሱዳን ከማስረከብ ይልቅ!

 

አጼ ካሌብና ታላቂቱ ኢትዮጵያ

 

በአክሱሞች ዘመን፤ በተለይም በአጼ ካሌብ ዘመነ መንግሥት (485-515)፤ ኢትዮጵያ የማትደፈር ታላቅ ሐገር ነበረች። ግዛትዋም በአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን የመንንና አብዛኛውን ዛሬ ሳውዲ ዓሬቢያ የሚሰኘውን ሐገር ትቆጣጠር ነበር። ስርግው ሐብለሥላሴ በጻፈው “Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270” በተሰኘው መጽሐፉ፤ ገጽ 128-137፤ አጼ ካሌብ በ230 መርከቦች በመጠቀም፤ ከ70,000-120,000 የሚገመት ጦር ዛእፈርና ናግራን በተሰኙ (ዛሬ ሳውዲ ዓሬቢያ ውስጥ የሚገኙ) ከተሞች ሁለት ጊዜ አዝምተው በኢትዮጵያውያንና በሌሎች ዜጎች ላይ ጥቃት ፈጽሞ የነበረውን ተቀናቃኝ አሸንፈው ወኪላቸውን አብርሃ የተሰኘውን (በሁዋላ በዝሆን ታጅቦ መካን የወረረው) ሰንዓ፤ የመን አመቻችተው ወደ አክሱም ተመልሰዋል። ይህንንም ዘመቻ ለማከናወን ሲነሳሱ እርዳታቸውን በጽሑፍ አድርገው የጠየቁዋቸው፤ በጊዜው የሮማ የቄሣር ገዢ የነበሩት ቀዳማዊ ጀስቲን የተሰኙት ነበሩ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰላማዊ ሰልፉ ቢታገትም ፣ የተሳካ ሕዝባዊ ንቅናቄ ነበር! -ከአንድነት ፓርቲና ከ 33ቱ ፓርቲዎች የተሰጠ መግለጫ

 

ዛሬስ?!

 

ዛሬማ፤ የኢትዮጵያ የውስጥ ጠላት፤ የሐገሪቱን መሬት ለዓረቦችና ለሌሎች ዜጎች እያስረከበ ነው። የኑሮ ፍዳ እያስገደዳቸው፤ ኢትዮጵያውያን፤ ሥራና ጥቅም ፍለጋ፤ ወደ ዓረብ ሐገሮች እየፈለሱ ነው። ወደ የመን ለመሸሽ በጥቃቅን መርከቦች ሲጉዋዙ እየሰመጡ ሕይወታቸው ያለፈው ብዙዎች ናቸው።

 

መፍትሔው ምን ይሆን?!

 

አማራጭ ያልሆን አንድ ነገር ቢኖር፤ የሐገራችን ሉዓላዊነት መደፈሩን እያየን ዝም ማለት ነው። ጭቆናና ድሕነት ቢያዳክመንም፤ ወኔያችንን አላኮላሸውም። ስለዚህ፤

 

  • የሐገርህ ሉዓላዊነት የተደፈረብህ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በቃኝ ብለህ ተነስተህ ለመብትህ መታገል አለብህ።

 

  • የኢትዮጵያ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊቶች አባሎች ሁሉ፤ የራሳችሁ ሐገርና ሕዝብ ሲጠቃ ማየት ለሕሊናችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ ጥቅም እጅግ ጠንቀኛ መሆኑን በመገንዘብ ታሪካዊ ጀግንነታችሁን ለውድ ሐገራችሁ ለኢትዮጵያ ለዘለቄታው በሚጠቅም ሁኔታ አሁኑኑ ማሳየት አለባችሁ። በሙስና የተዘፈቀ፤ ለሐገር ሉዓላዊነት ደንታ በሌለው መንግሥት የጭቆና መሣሪያ መጠቀሚያ መሆናችሁ

 

እናንተንም ሊያስነውራችሁ ይገባል።

  • ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት በመታገል ላይ ያላችሁ የፖለቲካና የሰብአዊ መብት ተፋላሚዎች የሚጎድላችሁ አንድ ከባድ ጉዳይ ቢኖር ሕብረት ማጣታችሁ በመሆኑ፤ “ድር ቢያብር” ስለሆነ ሐገራችንን እያሽመደመደ ያለውን አውሬ መንግሥት በአንድነት እንድንታንብረክኩት

 

ያስፈልጋል።

  • የአፍሪካ ቀንድ ሐገሮች ሰላምና ልማት ማግኘት የሚችሉት፤ ዲሞክራሲ ሥርዓት የሰፈነበት የተቀናጀ ሕብረት ሲኖራቸው ብቻ ነው።

 

(ሠ) ኢትዮጵያ ከዓረብ ሐገሮች ጋር ሊኖራት የሚገባው ግንኙነት ሚዛናዊነት ባለው ጥቅም የተመሠረተ ሲሆን ብቻ ነው። ኢትዮጵያ የሰው ሐይል፤ እንዲሁም የውሀና የእርሻ ሐብት ልትሸጥላቸው ስትችል በዓረቦቹ በኩል ደግሞ ነዳጅ ማቅረብ ይችላሉ። በተጨማሪም፤ በሳውዲ ዓሬቢያ በኩል የሚፈለገው ሚዛናዊነት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ መስጊዶች ማቁዋቁውም እንደ ተፈቀደላት ሁሉ ኢትዮጵያም ሳውዲ ዓሬቢያ ውስጥ ቤተክርስቲያን እንድትሠራ መፍቀድ አለባት።

 

  • መንፈሳዊም ሆነ ማሕበራዊ፤ ባሕላዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ፤ ሰላምም ቢሆን እርቅ፤ ሌላም፤ ሌላም ተልእኮ ቢኖረን ሊሳካ የሚችለው የሐገር ሉዓላዊነት ሲኖር በመሆኑ እንደ የጥንት አባቶቻችንና እናቶቻችን ተባብረን በርትተን ስንታገል ነው።

 

ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ ሐገራችንን እንድንጠብቅ ያበርታን!!!

 

 

 

 

 

2 Comments

  1. ግን ለምን ታሪክ ታዛባላችሁ፡፡ ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር ናት፡፡ በጋራ ብንገነባት ለሁላችንም የምትጠቅም አገር መመስረት እንችላለን፡፡ እኛ ሙስሊሞች አጼ ዮሃንስን በጸረ፟ኢትዮጵያዊነቱ ነው የምናውቀው፡፡ ቦሩ ሜዳ ላይ የተጨፈጨፉት 35፣000 ሙስሊሞች ኢትዮጵያውያን አይደሉምን፡፡ ኢትዮጵያን የሚወድ የአጼ ዮሃንስን ስም አይጠራም፡፡

  2. ይቅርታ አባባልሽን ዘግየት ብዬ በማየቴ፣ ግን እንዲሁም ሆኖ፣በኢትዮጵያ ላይ ከዖንድሩማን እስከ ወሎ ድረስ የመሽሎክሎኩን ጉዳይንስ የኢትዮጵያዊነት “ሃወርያዊ” ተግባር ነው ብለሽ ትመሰክርያለሽን……!?የጎንደር 44 አድባራት መውደምን ሲከላከሉ የመሰዋታቸው ጉዳይም እንደሆነ ኢትዮጵያ,” A Christian Island in a Muslim Sea” ተብላ በምትታወቅበት ስዓታት ላይ መሆኑን ደግሞ ማስታወሱም ይጠቅማል! ከሁሉ በፊት ንጥረ ሃብታችንን ሊዝቁ ለሚፈልጉ ኮሎኒያሊስቶችና እንዲሁም የራሳቸውን አባባልና እምነት ሊጭኑብን ለሚፈልጉ ሃይሎች ተላላኪነትን ማቆም ያስፈልጋል!

Comments are closed.

Share