ለ – ህወሐት ልዩ ዞን ጽ/ቤት
አዲስ አበባ
.
ላለፉት አመታት በህውሃት ድርጅት ስር ተደራጅቼ እንቅስቃሴ ሳደርግ እንደቆየሁ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም በፖለቲካው መስክ የመሳተፍ ፍላጎቱ ያልነበረኝ ቢሆንም በታሪክ አጋጣሚ የአገራችንን ፖለቲካ የመቀላቀል እድሉን አግኝቻለሁ፡፡ በተፈጠረው አጋጣሚም ስለሃገሬ የፖለቲካ ምንነት እና በፖለቲካ ገበያው ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦችንና ተቋማትን በቅርበት የማውቅና የመሳተፍ እድሉ ገጥሞኛል፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ በህወሀት ውስጥ አደርግ በነበረው ትሳትፎ በር የመዝጋት የመጠራጠርና እንደ ባዳ የመታየት ስሜት ከላይ እስከ ታች ድረስ አጋጥሞኛል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=-in6p8BndRg
ገና ከጅምሩ ትግሉ ድርብ ድርብርብ ነበር ፡፡ በአንድ በኩል የመጣሁበት አካባቢ በክልሉ ፓለቲካ ውስጥ በዳርነት የሚመደብ ነውና አጠቃላይ ጉዞው እጅግ አቸጋሪ ነበር ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅቱ ወጣቶችን የመጠራጠርና ያለማመን ከፍተኛ ችግር የተንሰራፋበት ነውና እኔም እንደማንኛውም ወጣት ጉዞየ በሳንካ የተሞላ እንዲሆን አድርጎብኛል፡፡
.
ነገር ግን ሁሉንም በአንድ ሙቀጫ መውቀጥ ጥሩ አይደለምና በህይወቴ ነገሮችን በተለየ መልኩ እንዳይ ያደረጉኝ እንዲሁም ትምህርት የሰጡኝ ጥቂት ሰዎች ነበሩና በነሱ ድጋፍና ምክር በችግርም ውስጥ ቢሆን እስካሁን ድረስ ለመዝለቅ ችያለሁ፡፡
.
በእርግጥም! በየሃገሬ ፖለቲካ ረጅም ርቀት ተጉዤ አስተቃጽኦ ላደርግበት የምችልና የሚገባ መሆኑን የማታ ማታ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ይሁንና ገና ከማለዳው ጀምሮ በህውሃት ውስጥ የነበረኝ የፖለቲካ ተሳትፎ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ በአጭሩ በሴራና በአሜኬላ የተሞላ ነበር ብሎ መናገር ማጋነን አይሆንም፡፡ ሆኖም ችግር ሲመጣ መሸሽና ማፈግፈግ ሳይሆን ፊት ለፊት ተጋፍጦና ተፋልሞ ማሸነፍ እንደሚገባ ላስተማረኝ ለውድ አያቴ ለሃዋደ ሻረው አቢቱ አበራ እና በአጠቃላይ ለራያ ማህበረሰብ ምስጋና ይግባውና ምርጫዬ “እግሬ አውጭኝ” ብሎ መሸሽ ሳይሆን አሜኬላውን መንቀልና ሴራውን ደግሞ ማፈራረስ ነበር፡፡
.
በአንፃራዊነት ከእድሜየና ከቆይታየ እንፃር ሲታይ በእርግጥ እድገቴ ፈጣን ነበር ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን እድገቱ የመጣው በእኔ የስራ ፍላጎት እምነት ያላቸው የሌሎች ደርጅቶች የግንባሩ አመራሮች እየገፉና እየጠየቁ እንጅ በህወሀት በኩል እንደዛ አይነት ፍላጎት ስለነበረ አይደለም፡፡ እንዲያውም ቅናት ያደረባቸው አንዳንድ የህወሀት አመራሮች እድሉን ለማሰናከል ሲተጉ ተስተውላል፡፡
.
አንዳንድ ግብዝ የዚህው ድርጅት አመራሮች ተመልሰው የማይገኙ በትላልቅ የአሜሪካ ትምህርት ቤቶች የመማር የነፃ የትምህርት እድልን ሳይቀር ትቼ አገሬን ለማገልገል በመወሰኔ በስልጣን ፍላጎት ከሰውኛል፡፡ በየቢሮው እየዞሩ የስልጣን ያለህ እያሉ የሚውሉት እነዚህ ግለሰቦች ከስልጣን ሲነሱ ደግሞ እንደ ልጅ እያለቀሱ የሚማፀኑ ናቸው፡፡
.
ከሁሉም በላይ የሚያስገርመው ነገር ደግሞ እያንዳንዱን እንጥፍጣፊ ስልጣን ለግል ጥቅምና ዝና ያላንዳች ርህራሄ የሚያውሉትና ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የስንቱን ምስኪን ህይወት የቀጠፉት እነዚህ ጨካኞች በግሌ ያገኘሁትን የነፃ የትምህርት እድልን መሰዋእት ያደረኩትን እኔን በስልጣን ፍላጎት ይከሳሉ፡፡
ይህን የመልቀቂያ ደብዳቤ እንዳዘጋጅና ከህወሀት ራሴን በፈቃዴ እንዳሰናብት በርካታ ገፊ ምክንያቶቼን እንደሚከተለው በዝርዝር የገለጽኩ ሲሆን የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ሊረዱት የሚገባ ትልቅ ቁም ነገር ቢኖር ድርጅቱን በይፋ ለቅቄ ከመውጣቴ በፊት እንዲስተካከል የምችለውን ሁሉ ጥረት ማድረጌን ነው።
እስካሁን መልቀቂያ ሳላቀርብ የቆየሁበት ዋና ምክንያት ከዛሬ ነገ ወደ ማስተዋልና ካለፈው ተምረው በስተታቸውም ተጸጽተው ነገሮችን ያስተካክሉ ይሆናል በማለት ለዚህም ጊዜ መስጠቱ መልካም ነው ብዬ በማሰብ ነበር። ነገር ግን ይህንን እንደማያደርጉና ምንም የሚለወጥ ስብዕና እንደሌላቸው የስካሁኑ አካሄዳቸው ግልጽ ስላደረገልኝ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ።
.
በነዚህ ዓመታት በግሌ የምከተለውን አቋም እና የነበረኝን የትግል አካሄድ ትክክለኛነት እና ፍትሃዊነትን ተረድተው “አይዞህ” ብለው የሞራል ብርታት የሰጡኝ ከፍ ሲልም ከጎኔ ቆመው የታገሉ ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ነገር ግን ወደ ላይ በወጣሁ ቅጥር የተበጀልኝ ሴራ ይበልጥ እየተውሰበሰበ መጣ፡፡ በተለይም የጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዴሊቨሪ ሚኒስትር ሆኜ በተሾምኩ ማግስት ጀምሮ ጥቃቱ ተቋማዊ መልክ እየያዘና ትልልቅ ቱባ የህወሃት ባለስልጣናትም ጭምር የሚሳተፉበት ወደመሆን ተሸጋገረ፡፡
.
የፖለቲካ እስረኞችን ሙሉ በሙሉ ለመፍታትና የሰቆቃ ማእከል ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ማእከላዊ ተዘግቶ ወደ ሙዝየምነት እንዲቀየር ተወሰኖ ለመላው ህዝባችን ይፋ እንዲሆን ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ በግለሰብ ደረጃ ይህ ነው የማይባል ጥቃትና ዛቻ እንዲሁም ማስፈራሪያ ደርሶብኛል፡፡
.
የአገሪቱ ቁንጮ የህወሐት ባለስልጣናት የተሳተፉበት ይኸው ጥቃት “ለምን የፖለቲካ እስረኛ አለ ብለህ ይፋ አወጣህ፤ ውሳኔው በቀጥታ twitter እና Facebook ለአለም በማሰራጨት የጠቅላይ ሚንስትርሩን ውሳኔ የማስቀየር እድላችንን ዝግ እንዲሆን አድርጋሀል፤ በአጠቃላይ ከጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ፤ ከምክትል ጠቅላይ ምንስትር ከአቶ ደመቀ መኮንን፤ ከኦህዴድ አመራሮችና ከፈረንጆች ጋር ወግነህ የስርአት ለውጥ ለማምጣት የምትንቀሳቀስ የቀለም አብዮተኛ ነህ፤ ከዚህ በኋላ ከአንተ ጋር የምንነጋገረው በጥይት ነው!” በማለት ውሳኔው ከተላለፈባት ከዚያች ምሽት ጀምሮ ከፍተኛ ዛቻና የስነ-ልቦና ጫና ከትላልቅ የህወሐት ባለስልጣናት በተደጋጋሚ በተለያዩ ወቅቶች ደርሶብኛል፡፡
.
እዚህ ላይ ግልፅ የሆነልኝ ነገር የድርጅቱ አመራሮች ምን ያክል እንደተበላሹና በታሰሩ ዜጎች መፈታት ምን ያክል እደሚያማቸው ነው፡፡ ጫናው ሲያይልና ይፋ የተደረገበት ምክንያት ግቡን ሲመታ በፌስቡክ ገፅ የተፃፈንውን ነገር ትንሽ ቆየት ብለንና በነጋታው ደግሞ በተለይም የውጭ ሚዲያ ወኪሎች የቀድሞውን ዘገባ እንዲያስተካክሉ አድርገናል፡፡ነገር ግን መረጃው አስቀድሞ በበቂ መጠን ስለተሰራጨ ግቡን ሊመታ ችላል፡፡
.
ከዛ በኋላም ቢሆን በነበሩት ተደጋጋሚ የህወሐት ስብሰባዎች ተመሳሳይ ስሞታና ዛቻ ደርሶብኛል፡፡ በእርግጥ አገራችንን ወደ ትልቅ እስር ቤት እየቀየራት የነበረው የጥቂት አምባገነኖች እርምጃ መቆም እንዳለበትና የነሱ ሰለባ የሆኑት የህሊና እስረኞች ከገባባቸው ነጻ መውጣት እንዳለባቸው ካመንኩኝ ውየ አድሬያለሁ፡፡
.
ከሁሉም በላይ ደግሞ የታገልኩት የሰብአዊ መብት ለማክበር ነው፤ እስረኞች በህግ ጥላ ስር ሊመቱ አይገባም እያለ በአደባባይ ላይ ያለአንዳች ሃፍረት የሚለፍፍ ስርአት ራሱን ፉርሽ በሚያደርግ ሁኔታ ደብዳቢ እና ተጋራፊ ሆኖ መገኘቱ አንድ በቅርብ በማውቀው ወዳጄ ላይ ተከስቶ ካገኘሁት ጊዜ ጀምሮ የህሊና እረፍት ሊሰጠኝ ባለመቻሉ ይህ ሁኔታ መለወጥ እንዳለበት ካመንኩኝ ሰናባብቻለሁ፡፡
.
እናም መልካም እድልና ምቹ ሁኔታ ሲፈጠር መጠቀም ይገባ የነበረ በመሆኑ የህሊና እስረኞችን ለመታደግና ማዕከላዊን ወደ ሙዝየም ለመቀየር በተደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ሚና ከተጫወቱ መሪዎች ጋር ሆኜ የድርሻዬን ተወጥቻለሁ፡፡ በዚህ ውሳኔ ሂደት ውስጥ የበኩሌን የጠብታ ታክል ድርሻ ተወጥቼ ከሆነ በህይወቴ የምኮራበት ትልቅ ተግባር እንጂ በምንም መልኩ አላፍርበትም፡፡ ሆኖም የአምባገነንነት እርካቡ እየተናደበት እንደነበር የገባው ህወሐት ውስጥ የመሸገው ቡድን በርግጎና በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ተነሳስቶ ለዚህ ውሳኔ ድርሻ ነበራቸው በሚላቸው ሃይሎች ያነጣጠረ እርምጃ መውሰድ መቼ ይቀርና!!
.
በተለይም ደግሞ አክራሪው ቡድን በህወሐት ውስጥ መሽጎ እንደሚገኝ የውስጥ አርበኛ ወስዶኝ ነበረና አንገቴን እንድደፋና ሸሽቼ እንድጠፋ ለማድረግ የተቀነባበረ የስም ማጥፋትና የጥቃት ውርጅብኝ ተካሂዶብኛል፡፡ ይህ ሁሉ ሁኔታ እየተካሄደ በነበረበት ሁኔታ እንኳን ምርጫየ ትግል እንጅ መፈርጠጥ አልነበረም፡፡
.
“ሳይደግስ አይጣላም!” እንዲሉ አበው . . . ከዛ በኋላ በፍጥነት በተቀያየረው ሃገራዊ ሁኔታ ትኩረታቸውን ስቦት እና አዛብቶት እንጅ የታሰበልኝን እና የተደገሰልኝማ ነገር አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነም ቢሆን ምርጫዬ መሸሽና አንገት መድፋት ሳይሆን አንገትን ቀና አድርጎ መታገል ነበር፡፡ ምክንያቱም ጥቃቱ በእኔ በግለሰብ ደረጃ ላይ ያነጣጠረ የነበረ በመሆኑ ነው፡፡
.
ይህ በእንዲህ እንዳለ የራያ ህዝብ ያለ ምርጫውና ያለውዴታው ገና ከማለዳው “ሆ. . .!” ብሎ የተቃመው አከላለል ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ መግደልና ማሳደድን መቀጠላቸው ህዝቡም በተደራጀ መልኩም ባይሆን ትግሉ አላቆመም ነበር፡፡
.
የራያ ህዝብ ትግል ፍሬ እንዳያፈራ ካደረጉት መሰረታዊ ምክንያቶች/ጉዳዮች አንዱ ትግሉ በተደራጀ መንገድ አለመከናወኑ መሆኑን አውቆ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተደራጀ መንገድ ወደ ትግል ገብቷል፡፡ ወንድሜ ከሆነውና በጠንካራ ማህበረሰባዊና ስነልቦናዊ ገመድ ከተሳሰርኩት የአማራ ህዝብ ጋር አብሬ ልኑር ብሎም እየተዋደቀ ይገኛል፡፡
.
ይህ ሲሆን ታዲያ የኢትዮጵያ የናሽናል ጥያቄ (የብሄረሰቦች ጥያቄ) ብዝሃነትን የማስተናገድ ችሎታ እጦት ነውና “ኢትዮጵያ ብዝሃነትን ልታከብር ይገባታል!” ብሎ በፕሮግራሙ ላይ በነጭና በጥቁር በደማቁ የጻፈው እንዲሁም በዛ ላይ ተመስርቶም ላለፉት 45 አመታት የፖለቲካ ሞብላይዜሽን ያደረገው ህወሐት ምላሽ ጥይት፤ ግድያ፤ ማፈናቀልና እንግልት ሆኗል፡፡
.
ነገሩ “ሆድ ሲያውቅ ደሮ ማታ ነው!” እና ድርጅቱ ለፕሮግራሙና ለዚያም ሲባል መስዋእት ለሆኑት ታጋዮቹ ክብር እንደሌለው በአደባባይ አስመስክሯል፡፡ የማንነት ጥያቄን ያነሱ እምቦቃቅላ ህጻናትን እስከ አፍንጫው በታጠቀው የክልሉ ልዩ ሃይል አናት አናታቸው እየተመቱ በእንጭጩ ተቀጭተዋል፡፡
.
በአጠቃላይ የራያ ህዝብ የተደራጀ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የስንቱ ህይወት እንደተቀጠፈ፤ ለእስር እንደተዳረገና እንደተፈናቀለ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ አካባቢው በዚህ ምክንያት ለከፋ ማህበራዊ መስቅልቅልና ቀውስ እንዲሁም ለጸጥታ ቀውስና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ተዳርጓል፡፡ በራያ ህዝብ ላይ ይህን የመሰለ ግፍና መከራ እየፈጸመ ካለ ድርጅት ጋር አብሬ እንድቀጥል ህሊናዬ አልፈቀደልኝም፡፡
.
በእርግጥ ገና ከገባሁ በጥቂት አመታት ውስጥ ልቤ ሸፍቶ በመንፈስ የራቅኩት ድርጅት ዛሬ ቀኑ ደርሶ በወጉ የአባልነት ግንኝነታችን ያበቃ ዘንድ የራያው ጉዳይ አንዱ ምክንያት ሆኗል፡፡
.
ከሁሉም በላይ ደግሞ በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እና በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ የለውጥ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ በእርግጥ የአገራችን ችግር መሰረታዊ ለውጥ የሚሻና ውስብስብ ቢሆንም ችግሩን የሚመጥን መሰረታዊ የለውጥ ፕሮግራም ተነድፎ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡
.
ህወሐት በጥቂት ጠባብ ጸረ ለውጥ ቡድን ተጠልፎ ከሃገራዊ ለውጥ ጎን መቆም ሳይሆን ፀረ- አቋምን ምርጫው አድርጎ ለውጡ የትግራይን ህዝብ ጨምሮ መላው የአገሪቱ ህዝብ የሚጠቅም ቢሆንም ቅሉ፤ የውስን ሰዎች ጥቅም የሚያስቀር ሆኖ በመገኘቱ ብቻ ድርጅቱ ሊታገልለት የሚገባውን የትግራይ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ሳይሆን የጥቂት የህወሐት ባለስልጣናት ጥቅም ለማስከበር ሲል ለውጡን ተቃርኖ ብቻ ሳይሆን አፍራሽ በሆነ የሰላ ጥግ ላይ ቆሟል፡፡
.
በመሰረቱ ዲሞክራሲም ሆነ እኩልነት የትግራይ ህዝብ ለዘመናት የታገለላቸው እና ውድ ልጆቹን የገበረላቸው የህልውና ጥያቄዎች እንጂ ባለጋራዎቹ አይደሉም፡፡ አዲሱ የለውጥ ፕሮግራምም ተንጋዶ የበቀለውንና የማቃናትና አሜኬላውን የመንቀል እንጅ ከትግራይ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተቃርኖ የመጣ አይደለም፡፡ ህወሐት በዚህ ታሪካዊ ወቅት እየተወሰደ ያለውን ትክክለኛ እርምጃ የመቃወም ግዙፍ ስህተት ከድርጅቱ ጋር አብሬ እንዳልቀጥል ካደረጉኝ መሰረታዊ ምክንያቶች ሁለተኛው ነው፡፡
ከዛሬ ነገ ችግሮች ተቀርፈውና ተሻሽለው ከመስመር የወጡ አካሄዶችም ፈር ይዘው ይራመዳሉ በሚል ትዕግስትና ተስፋ ፤ ብዙ ነገሮችን በራሴ ይዤ እየታገልኩ ቆይቻለሁ:: በግሌም ሆነ በተገኘሁበት ማህበረሰብ ላይ እጅግ መራር ውርጅብኝ እየወረደ፤ ይባስ ብሎም በአገር ደረጃ ነገሮች እየተበለሻሹ እየሄዱ እንኳ ነገሮችን ለማቃናትና ለማሻሻል የበኩሌን እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ አካሂጃለሁ:: የሆነ ሆኖ ከግትር አቋማቸው ፈቀቅ የማይሉ ተቸካዮች በህዝብና በአገር ላይ የሚያደርሱት ግፍ አልበቃ ብሏቸው፤ በተገኘችው ጭላንጭል ዕድል ይህን መከራ ለማስቆም የሞከርኩትን ግለሰብ ስም ለማጥፋት በየመንደሩ ሲባዝኑ ይውላሉ::
.
ከጥንት ጀምሮ ለነፃነት ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር አብሮ የተዋደቀውን የትግራይ ህዝብ፤ ዛሬ እንደሰብዓዊ ምሽግ ተጠቅመው ሊለያዩት ቢሞክሩም ፤ ይህ የአክራሪ ወንጀለኞች የቀን ቅዠት እንደጉም መብነኑ እና መክሸፉም የማይቀር ነው! ኢትዮጵያዊነትን ከትግራይ ህዝብ ልብ ላይ መፋቅ ከቶም የማይቻልና ዛሬም ቢሆን እላዩ ላይ ተጋድመው የተጫኑትን የቀንበር እንጨቶች ሰብሮ ዳግም ለእኩልነትና ነፃነት እንደሚበቃ ቅንጣት ጥርጥር የለኝም!
.
በመጨረሻም ፀረ-ለውጥ እና ፀረ-ዴሞክራሲ ከሆነው ድርጅት ጋር ለመቀጠል ህሊናዬ ባለመፍቀዱ በገዛ ፍቃዴ ከድርጅት አባልነት የለቀቅኩኝ መሆኑን እያሳወቅኩ በቅርቡ ያታግለኛል ከምለው ድርጅት ጋር ተደራጅቼ የራያና መላ የአገሬ ራችን ህዝብ ጥያቄ ይበልጥ መልስ እንዲያገኝና ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተደረገ ያለውን ርብርብ አቅም በፈቀደው ሁሉ ለማገዝና ለመታገል እንደምሰራ ከወዲሁ ለማሳወቅ እወዳለሁ፡፡ የራያ ህዝብ በተድላና በፍቅር ከወሎ አማራና ከመላው የአማራ ህዝብ ጋር ለዘላለሙ ይኖራል ። ምክንያቶቹ በትንሹ እነዚህ ሲሆኑ በማወቅም ይሁን ባለማቅ በስካሁኑ የፓለቲካ ህይወቴ ያስቀየምኳችሁ ካላችሁ ከልብ የመነጨ ይቅርታን እጠይቃቹሃለው።
.
ዛዲግ አብርሀ
ድልና ነፃነት ለራያ ህዝብ !!!!!
ዴሞክራሲና ሰላም ለመላ የአገራችን ህዝብ!!!!!!