December 16, 2018
63 mins read

አትረፍ ያለውን በሬ ቆዳውን ለከበሮ ይውላል ዘራፊዎችን ለሕግ ማቅረብ ማለት ለትግራይ ህዝብ ነፃነትና እፎይታ እንጂ ማንበርከክ አይደለም

ከበላይ ገሰሰ

የሁሉም ችግሮች ምንጭ የሆነው ህወሓት ራሱን ለማዳን ያልቻለና በመክሰም ላይ የሚገኝ ያረጀ ያፈጀ ስርዓት በፍፁም የትግራይ ህዝብን ነፃ አውጪ፣ ጠበቃና መድህን ሊሆን አይችልም:: ጭንቀት የወለደው የመቀሌው የቀቢፀ ተስፋና የትንኰሳ ሰላማዊ ሰልፍም የህወሓቶችን ሞትና ግብኣተ መሬትን የሚያቀላጥፍ እንጂ ከእነርሱ በላይ የነቃ ፣ የተደረጃ ፣ ጠላቱንና ወዳጁን ጠንቅቆ ያወቀና ለለውጥ ቆርጦ የተነሳ ጀግና የኢትዮ}ያ ህዝብን ዳግም በሐይል አንበርክኮ መግዛት አይቻልም:: አክትሟል:: ለሰላም የተዘረጉትን እጆች አሻፈረኝ በማለት ፣ ሕግን እየጣሱ ሕግን መጠየቅ፣ የሌላውን ህዝብ መብትና ክብር እየደፈሩ የራስህን መብት ማስከበር አይቻልም:: ስለሆነም በሌላው ወገን ላይ ጣት ከመቀሰርህ በፊት በመጀመሪያ ልክህን ማወቅ ፣ ለሕግ መገዛትና ሽንፈትህን በፀጋ አሜን ብለህ በመቀበል ከለውጡ ጋር ተስተካክለህ መጓዝ ብልህነት ነው:: ካልሆነ ግን አደባባይ ወጥቶ ጦርነት ማወጅና መቀስቀስ ማለት የሌላውን ወገን ቁስል መቀስቀስ ስለሚሆን መዘዙ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል:: ስለዚህ ህወሓቶችና አጃቢዎቻቸው ቆም ብለው ሁለት ጊዜ ማሰብ ያለባቸው አንድና አንድ ብቻ ነው:: እሱም ገና የህዝቡን እንባ ሳይደርቅ : በየአስፋልቱ የፈሰሰውን የወጣቱን ንፅህ ደም ሳይደርቅ : በየማጎሪያ ቤቱ አካሉን የጎደለውና አእምሮውን የተጎዳው ወገን ሳይሽር : በጠራራ ፀሃይ በገፍ የተዘረፈውን የሀገራችን አንጡራ ሃብት ሳይመለስ የኢትዮ}ያ ህዝብ ይተኛል ብለው ማሰብ የዋህነት ነው:: “አህያ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ውላ አድራ የጅብ ናት” እንዲሉ በሀገርና በሀዝብ ላይ በደል የፈፀሙ ወንጀለኞች የትም ይግቡ የት ከተጠያቂነት እንደማይድኑ በውል ሊገነዘቡት ይገባል::

 

የተከበራችሁ ወገኖቼ ሆይ

 

የትግራይ ህዝብ ከህወሓት በላይ ሌላ ደመኛ ጠላት እንደሌለው ከራሱ ከህዝቡ በላይ ሌላ ምስክር የሚያስፈልገው አይደለም:: የትግራይ ማህፀን ለሀገራቸው ክብርና ነፃነት ሲሉ አንገታቸውን የሰጡ እንደነ አፄ ዮሐንስና እንደነ አሉላ አባ ነጋ የመሳሰሉትን ብሄራዊ ጀግኖች እንዳልወለድች ሁሉ ዛሬ በምድርዋ እንደ ህወሓት የመሰሉት እሾኽ አሜካላዎች መፈጠር ለትግራይ ህዝብ ውርደት፣ ኪሳራ፣ ሓፍረት፣ ድፍረት ፣ መፈናቀል፣ ሞት ፣ ስደት ፣ ባርነት ፣ ማለቂያ የሌለው ጦርነት፣ የዕልቂትና የመከራ ታሪክ እንጂ ነፃነትና እፎይታ አላገኘም:: ከታሪክ ፣ ከውድቀታቸውና ከነባራዊ እውነታ የማይማሩ ህወሓቶች ላለፉት አርባና ሐምሳ ዓመታት በትግራይ ህዝብ ስምና ደም እየነገዱና እርስ በርስ እያናከሱ ሆን ብለው ትግራይ በጥላቻ የታጠረች ፣ የጥቃትና የግጭት አውድማ ሆና እንድትኖር አደረጓት እንጂ የሰላም የፍቅር የወንድማማችነትና የዴሞክራሲ ተምሳሌት ለመሆን አልታደለችም:: ህወሓቶች ከተፈጠሩባት ቀን ጀምረው እስካሁን ድረስ የለመዱትና የተካኑት ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨት ባሩድ ባሩድ ሲሸታቸውና እንደ ሳዲስቶች የንፁሃንን ደም ሲፈስ ሲያዩ የልብ ልብ ተሰምቷቸው ጀግኖች ነን እያሉ በአደባባይ ቀረርቶና ጉራ ከማሰማት አልፈው ለሀገርና ለወገን የሚበጅ ሙያና እውቀት የሚጠይቅ ስራ የመስራት ልምዱም ጥበቡም ችሎታውም የላቸውም:: ሰላም ፍቅር ሰብኣዊ ርህራሄ ኢትዮ}ያዊነትና አንድነት የሚሉትን ቃላቶች ለነርሱ አባ ጨጓሬ ናቸው:: ከዶር ዓቢይ አህመድ የሚለያቸው ባህሪያትም ይኸው ነው::

 

ዶክተር ዓቢይ በሀገሪቱ ሰላም ለማስፈን ዕረፍት አጥቶ ይሰራል :: ህወሓቶች ደግሞ በመቀሌ ተሸሽገው የጦርነት ነጋሪት ይጎሱማሉ:: ዶክተር ዓቢይ ኑ እንደመርና ተባብረን ለሁላችን የምትሆን ጠንካራ ሀገር እንገንባ ይላል :: ህወሓቶች ደግሞ ይባስ ብለው በአደባባይ የብትናና የግንጠላ መፈክር ያስተጋባሉ :: ዶክተር ዓቢይ ግጭትን ለማብረድ : ህዝብ ለህዝብ ለማስተቃቀፍና ለማስታረቅ ይሰራል:: ህወሓቶች ደግሞ ጥላቻን በአደባባይ ከመስበክ አልፈው ፀረ ሰላም ቡድኖችን እያስታጠቁ ሀገርን ለማፍረስ እንቅልፍ አጥተው ይሰራሉ:: ዶክተር ዓቢይ የሀገር ባለቤት ህዝብ ነውና ሁላችንም ልካችንን አውቀን በእኩልነት ተከባብረን ተሳስበንና ተፋቅረን እንኑር ይላል :: ህወሓቶች ደግሞ የህወሓት የበላይነት የማይረጋገጥባት ኢትዮ}ያ ገደል ትግባ እያሉን ነው:: ዶክተር ዓቢይ ከዘረኝነትና ከጠባብ አመለካከት ወጥተን ሀገራችንና ህዘባችን ብቃትና ሙያ ባላቸው ዜጎች ይመራ ይለናል:: ህወሓቶች ደግሞ ከኛ በላይ ጀግና የለም:: ሌሎቹ ሀገርን መምራት የማይችሉ ትላንት የኛ ምርኮኞችና ተስፈኛ የነበሩት ናቸው እያሉን ነው:: ዶክተር ዓቢይ ሀገርን ለማረጋጋት ይጥራል:: እነርሱ ደግሞ ጨለማ ለብሰው የተሰራውን ሲያፈርሱ ያድራሉ :: ባጠቃላይ ዶክተር ዓቢይ ጥሩ ነገር በተናገረና መልካም በተሰራ ቁጥር ህወሓቶች በኢትዮ}ያ ህዝብ ፊት ከቀን ወደ ቀን እያሽቆለቆሉ በመሄድ የዓይጥን ያህል አንሰው እንዲታዩና እንዲናቁ አድርጓቿል::

 

አትረፍ ያለውን በሬ ቆዳውን ለከበሮ ይውላል እንደተባለው ሁሉ ህወሓቶች ትናንት ራሳቸው በለኮሱት እሳት የተለበለበውን የትግራይ ህዝብ ገና ቁስሉን ሳይሽር ዛሬም እንደገና ጥቂት ሌቦችን ከተጠያቂነት ለማዳን ሲባል የትግራይ ህዝብን የጦርነት ማገዶ ለማድረግ አደባባይ ወጥተው የውጊያ ቀረርቶን በማሰማት አካኪ ዘራፍ  ሲሉ ስናይ የጨነቀው እርጉዝ ያገባል ነውና የሚገርመን አይሆንም:: ነገር ግን የሚገርመውና የሚያሳዝነው የኢትዮ}ያ ህዝብን ፣ የመንግስትንና የታጋይ ሐይሎችን ትዕግስት እንደ እንደፍርሃትና ሞኝነት በመቁጠር ቀይ መስመሩን አልፈው የህዝብን ክብር የሚዳፈር ስራ ሲሰሩ መገኘታቸውን ነው:: ይሁን እንጂ በወንደማማች ህዝቦች መካከል ጦርነት ለመለኮስ ሲባል እየተካሄደ ያለው ትንኮሳ ከማንም በላይ የሚጎዳው በጉዳዩ የሌለበት ጭቁኑ የትግራይ ህዝብ መሆኑን እሙን ነው::

 

ትግራዋይ ማለት ለመከራና ለጦርነት የተፈጠረ ህዝብ ይመስል ላለፉት አርባና ሓምሳ ዓመታት በህወሓት ባርነታዊና አረሜናዊ አገዛዝ ስር ወድቆ የከፈለውን መስዋእትነትና ያሳለፈውን የሰቆቃና የመከራ ዘመን እንዳይበቃው ዛሬም በተመሳሳይ የመለስ ዜናዊ ቅሪቶችና በስብሓት ነጋ የጎበዝ አለቃነት ዙሪያ የተሰባሰቡት ጥቂት የፓለቲካ አዛውንቶች ህዝቡን እንደ ሆስቴጅ (ጅሆ) ይዘው የቀቢፀ ተስፋ ጦርነት ሲያውጁና ሀገርን የሚያፈርስ ስራ ሲሰሩ በአደባባይ እያየን ነው:: እነዚህ በጋብቻ በጥቅምና በሙሱና የተሳሰሩት መሪዎች የትግራይ ክልልን የጦርነት አውደ ሙኮራ ማሳያ አድርገው ለመጠቀም ሲባል እየፈፀሙ ያሉት እኩይ ተግባር የኢትዮ}ያ ህዝብ በአግራሞት እየተከታተለው ይገኛል:: የዛሬው ፅሑፌ መነሻም ሰሞኑን በተለይም የስርዓቱን ሕገ ወጥ ተግባር መገለጫ የሆነውን በመቀሌ ከተማ የተካሄደው አሳፋሪ ሰላማዊ ሰልፍ መንደርደሪያ በማድረግ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን አጭር ዘገባ እንመልከት::

 

የሰላማዊ ሰልፉን አላማና እንድምታው ምንድን ነው?

  1. ዋናውና ትልቁ የሰላማዊ ሰልፉን አላማ ለውጡን ለመቀልበስ ተብሎ የተደራጀና የተቀናጀ ዘመቻ ነው:: ህወሓቶች በንግስና ዘመናቸው በሀገርና በህዝብ ላይ ምን እንደሰሩ ጠንቅቀው ያውቃሉ:: በመሆኑም ከተጠያቂነት ለማዳን ሲሉ ብዙ የህይወት መስዋእትነት ተከፍሎበት የተገኘውና በህዝባዊ ማዕበል ታጅቦ በማኮብኮብ ላይ ያለው የለውጡን ሂደቱ ስር እንዳይሰድና መሬት ላይ ወርዶ ተግባራዊ እንዳይሆን: ህዝቡ በለውጡ ላይ አሜኔታና ተስፋ እንዳይኖረው ገና በለጋነቱ ለመቅጨት አፍራሽ ተግባር መፈፀም ግድ ይላቿል:: በዚህ መሰረት አላማቸውን እውን ለማድረግ የትኩረት ማዕከል አድርገው የወሰዱት ፅናትን : ብስሌትን : ጥበብን : ትግስት የተሞላበትና ከአህጉራችን አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናና አድናቆት ያገኘውን የዶክተር ዓቢይ ሳይንሳዊ አመራር መልክ እንዳይዝና ወደ ተግባር እንዳይሸጋገር ለማሰናከል ለማንቋሸሽና ለማፍረስ ሲባል ብዙ የገንዘብና የማተሪያል ወጪ ተደርጎበት የተካሄደ አፍራሽ ተልእኮ ነው::

 

  1. የሰልፉን አላማ ህወሓቶች እንደ ባቢሎን ግንብ ከላይ ወደ ታች ወድቀው በመፈረካከሳቸው ምክንያት ለደረሰባቸው ውርደት ሐፍረትና ውድቀት ማካካሻና የሞራል ማሳጅ አድርገው በመጠቀም በህይወት አለን አልሞትንም ገና የሚል የጡንቻ ማሳያና ማስፈራሪያ መልእክት ለማስተላለፍ ሲሆን በተለይም ለትግራይ ተወላጆችና እንዲሁም በሌሎች ክፍላተ ሀገራት በሕቡዕ እያደራጁ በፀረ ሰላምና በፀረ ህዝብ ተግባር ላይ የሚያሰማሯቸውን ታጣቂ ቡድኖች አይዛችሁ ቀጥሉ የሚል የሞራል ድጋፍ ለማስተላለፍ ነው::

 

  1. የሰልፉን አላማ የትግራይ ህዝብ ሌላ አማራጭ መንገድ እንዳያስብ፣ ስለለውጡ በቂ ግንዛቤ እንዳይኖረው : ስለመፃኢ ዕድሉ ሰከን ብሎ ለመወያየት ዕድል እንዳያገኝ : ጠላቱንና ወዳጁን ለይቶ እንዳያውቅ : የችግሮቹን መንሲኤ በነፃ መድረክ በግልፅ ተወያይቶ ሐቁን በማወቅ የመፍትሄ አካል እንዳይሆን : ከሌላው ወንድም ህዝብ ጋር የትግል አንድነትን በመፍጠር የለውጡን አጋርና ተጠቃሚ እንዳይሆን፣ በተለይም በህወሓት መሪዎች ላይ ተቃውሞ እንዳያስነሳና እንዳያምፅ በመፍራት ነጋ ጠባ በስብሰባና በሰልፍ እንዲጠመድ በማድረግ ዕረፍት ለማሳጣትና ቀልቡን ለመቀየር ነው:: ይህንን አላማቸው ተግባራዊ ለማድረግም ካሁን በፊት ያደርጉት እንደነበረ ሁሉ ዛሬም የተለያዩ አደናጋሪና አሳሳች አጀንዳዎችን በመቅረፅና በመቀስቀስ የትግራይ ህዝብ ፀረ ጥቅሙ እንዲሰለፍና የገዛ ቤቱን መልሶ ራሱ እንዲያፈርስ ለማድረግ በሬ ወለደ ብለው ማውራትና ማሸበር መደበኛ ስራችን ብለው ተያይዘውት ይገኛሉ::

 

  1. የሰላማዊ ሰልፉን አላማ ህወሓቶች የህዝብ ድጋፍ ያላቸው በማስመሰል የትግራይ ህዝብ ከወንጀለኞችና ከዘራፊዎች ጋር አብሯል ተብሎ በሌሎች ወንድም ህዝቦች ዘንድ በጥላቻ ዓይን እንዲታይና የጥቃት ዒላማ እንዲሆን ለማድረግ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሴራ ነው:: ካሁን በፊትም ያደርጉት እንደነበር ሁሉ ዛሬም ህዝቡ ዙሪያውን በጥላቻ አጥረው ወደደም ጠላም የሌላ ጅብ ከሚበላኝ የወንዜ ጅብ ይብላኝ ብሎ እንዲወስን በመገፋፋት ዕድሜ ልኩን የጥቂት ዘራፊ መሪዎች አገልጋይና ከለላ ሰጪ ሆኖ እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን እሙን ነው::

 

  1. ሌላው የሰልፉን አላማ ለጠቅላላ የኢትዮ}ያ ህዝብ የተላለፈ የማስፈራሪያ መልእክት ሲሆን በተለይም በዶክተር ዓቢይ አህመድ አስተዳደር ላይ ጫና በመፍጠርና በማሸማቀቅ እሽሩሩ እንዲባሉና መንግስትም ተገዶ ፓሊሲውን እንዲቀይር አሊያም ተደራድረው ለሰሩት ወንጀል በይቅርታ እንዲታለፍላቸው ለማድረግ የትግራይ ህዝብን እንደ መደራደሪያ መሳሪያ አድርገው ለመጠቀም ነው:: በዚሁ መልኩ ከቀናቸው ደግሞ የገንዘብ ዓቅምም ስላላቸው አዘናግተው ለውጡን ገና ከእንጭጩ ለመቅጨት ዕድል ይኖራቿል ማለት ነው::

የሰላማዊ ሰልፉን ተዋናዮችና ባለቤቶችስ እነማን ናቸው?

አብዛኛውን ጊዜ በትግራይ ክልል ሰላማዊ ሰልፍ ተደረገ : ስብሰባ ተካሄደ : ጉባኤ ተጠራ : ወዘተ ሲባል በቀጥታ ፊት ለፊት የምናያቸው ሰዎች የሰፊው የትግራይ ህዝብ  ነፃ ተሳትፎና ድጋፍ ያለበት መስሎ ነው የሚታየን:: ነገር ግን ጉዳዩን በቅርብ ሆኖ ለሚከታተለውና ሰከን ብሎ ለሚያየው ሰው ሁሉ ከሰልፉ በስተጀርባ ያለውን እውነታ ምን እንደሆነ በቀላሉ ለመረዳት ይችላል:: የድራማው ደራሲዎች ቀስቃሾችና ተዋናዮች በሙሉ ከ6 ሚሊዮኑ የትግራይ ህዝብ ውስጥ ከ60 – 80 ሽሕ የማይበልጡ ካድሬዎችና የድርጅቱ አባላት ናቸው::  እነዚህ ካድሬዎች በህዝቡ መሀል ከላይ እስከታች ተሰግስገው እንደ ጅግር የህዝቡን ደም የሚመጡ : እንደ ምስጥ የህዝቡን ሀብት የሚያቆረቁዙ : እንደ ካንሰር የህዝቡን ባህል ታሪክ እሴት አንድነትና ፍቅር በመበከልና በማፍረስ በሬ ወለደ ብለው የጥላቻና የሐሶት ፕሮፓጋንዳ የሚያሰራጩ ናቸው:: ህዝብ መስለው ህዝብ ለህዝብ የማናቁርና የሽብር ስራ የሚሰሩ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ውጤት የሆኑት ካድሬዎችና አባላት ናቸው እንጂ በቀን ሶስት ጊዜ እንኳን መብላት የማይችለውና ሁለት ሶስተኛውን በምግብ ለስራ የእርዳታ ሶፍት ኔት እህል እየተሰፈረ የሚኖረው ሰፊው የትግራይ ህዝብ አይደለም::

የሰልፉን አካሄድ ፣ በሰልፉ ላይ የተስተጋቡ መፈክሮችና ዘፈኖች ፣ የተደረጉ ንግግሮችና የቀረቡ ውግዘቶች ደምረን ስናያቸው ዘራፊን የሚያወግዙ ሳይሆን የሚያወድሱ ናቸው:: የነበረው ሽርጉም ትግራይ በጦርነት ዋዜማ ላይ ያለች አስመስለው ነው ያቀረቡት:: ከሁሉም በላይ በሰላማዊ ሰልፉም ሆነ ቀደም ብሎ በተለያዩ ቦታዎች  ከተደረጉት ንግግሮች ውስጥ የክልሉ ምክትል አስተዳዳሪ ተቢዮው የደብረፅዮን ንግግር ነው:: አዎ!! ንግግሩን ላዳመጠው ሰው ይቅርና ከአርባ ዓመት በላይ በትግል ቆይተናል ከሚሉት መሪዎች ቀርቶ ከተራ የመንደር ዱሩዬም ቢሆን የማንጠብቀው የወረደ አቀራረብ ነው:: ደብረፅዮን ቢያንሰ የተማረ ዶክተር ነውና የተሻለ ስራ ይሰራ ይሆናል ብለን ስንጠብቅ የባሰ ጉልቻና አቋም የሌለው ዋላዋይ ሆኖ መገኘቱ ያልታደለች ትግራይ የሚያሰብል ነው:: ለንጉሥ ያጨኹትን ሰው ጥጃ ሆኖ አገኘሁት እንደተባለው ሁሉ ደብረፅዮን ተደናግሮ አዳናጋሪ እንጂ መሪ ሆኖ አልተገኘም:: ለምሳሌ በቅርቡ በተለያዩ ከተሞች ባካሄዳቸው የህዝብና የምሁራን ስብሰባዎች ላይ ካደረጋቸው ንግግሮች ውስጥ ለመጥቀስ ያህል “አሁን በስልጣን ላይ ሆነው በኛ ላይ የሚዝቱ እኮ በህወሓት የትጥቁ ትግል ዘመን ከሶስት ጊዜ በላይ የማረክናቸው ሰዎች ናቸው:: ስለዚህ እኛን ለመውጋት ከመጡም ያው ትላንት የምናውቃቸው ሰዎች ስለሆኑ የሚያሰጋን ነገር የለንም:: ይቅርና ተከዜን ተሻግረው እኛን ሊያጠቁ ቀርቶ አንድ ስንዝርም ቢሞኩሩ ማን መሆናችንን ጠንቅቀው ያውቁናል:: እኛ ታግለን መስዋእትነት ከፍለን የተከልነውን ስርዓት ማንም ከመንደር ተነስቶ ሊነቅለውና ሊያፈርሰው በፍፁም አንፈቅድም ::” በማለት ዝቷል::

የደብረፅዮን ፌዝ በዚህ ብቻ አላበቃም:: ለስልጣን ያሰጉኛል ለሚላቸው የተለየ አመለካከት ላላቸው ለትግራይ ተወላጆችም ጭምር እንዲህ ሲል የማስፈራሪያ ንግግር አድርጓል:: “በደርጊ ገዜ ከመንግስት ጋር ሆነው የሚሰሩና እኛን የሚቃወሙ ባንዳ የትግራይ ተወላጆች እንደነበሩ እናውቃለን:: ዛሬም ከመንግስት ጋር የሚጠጉ ባንዳ ተጋሩ መኖራቸው እሙን ነው:: ስለዚህ እነዚህ ባንዳዎች ተከታትለን ከውስጣችን ማፅዳትና መቆጣጠር አለብን ” በማለት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል:: ደብረፅዮን ጥዋት የተናገረውን ማታ የማይደግም ፣ የተደናበረ : በያዘው አጀንዳ ፅናት የሌለው ፈሪና አስመሳይ የምሁር መሃይም ብቻ ሳይሆን በሁለት ባላ የረገጠና የጠራ አቋም የሌለው ባዶ ቆፎ ነው በማለት ብዙዎች ይስማማሉ:: ደብረፅዮን ይቅርና የሀገርና የህዝብ ጉዳይ በብስለት ለመምራት ቀርቶ ራሱን በአግባቡ መግለፅ የማይችል አሰልቺና ካሪስማ የሌለው ሰው ነው::

ደብረፅዮን አዲስ አበባ ሲሄድ የለውጥ ሰውና ትልቅ መሪ ለመምሰል ከዶክተር ዓቢይ አጠገብ ቁጭ እያለ ፎቶ ይነሳል:: ትግራይ ሲሄድ ደግሞ አዛውንቶቹ ሲያስፈራሩት ወደ ቀድሞ የአውሬነት ባህሪው ይለወጣል:: ደብረፅዮን የተለየ አመለካከት ያላቸውን ተጋሩ ባንዳዎች ብሎ ሲናገር ምን እያለ እንደሆነ ለራሱ የሚረዳው አይመስለኝም:: ህወሓት ራሱ የመንግስት አካል ሆኖ እየሰራ ባለበት ሁኔታ የዶክተር ዓቢይን መንግስት የደገፈ ትግራዋይ ሁሉ ባንዳ ነው ብሎ ሲናገር የተረዳው አይመስለኝም:: ስለዚህ ባንዳ የሚለው ቃል የፓርላማ አባላትና በየመንግስት መስሪያ ቤቶች ተቀጥረው ለሚሰሩ የትግራይ ተወላጆች ማለቱ ነው ወይስ ለራሱ ነው:: ደብረፅዮን ባንዳ ማለት ቃሉ ምን እንደሆነ እንኳን በቅጡ ሳያውቁ እንዴት ዶክትሬት አገኘ::? ለነገሩ የህወሓት መሪዎች ዶክትሬት ማስትሬት የሚባሉትን ነገሮች ዕድሜ ለዘረፉት ሃብት እንደሸሚዝ በቀላሉ የሚቀያዩሩት ዕቃ ነው:: ደብረፅዮን አልገባውም እንጂ ባንዳ ማለት እኮ እንደ ህወሓት እናት ሀገሩንና ብሄራዊ ጥቅምን ለባዕድ አሳልፎ የሚሰጥ እንጂ ለራሱ መንግስትና ህዝብ የሚያገለግል ዜጋ ባንዳ አይባልም ፀያፍና ወንጀል ነው:: ደብረፅዮን እኮ አልተነገረለትም እንጂ መለስ ዜናዊ ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ከቤተ መንግስት የተባረረበት ዋናው ምክንያት የፓለቲካ አቋም ስለነበረው ሳይሆን ለውጭ ሀገር የስለላ ተቋም የሚሰራ ሰላይ ነው ተብሎ በመገምገሙ ምክንያት እንደሆነ ከሰማን ዓመታት አልፎበታል:: ስለዚህ ከደብረፅዮን በላይ ባንዳና ዋላዋይ የሆነ ትግራዋይ አለ ቢባል ውሸት ነው:: ደብረፅዮን ከጥቂት ቀናት በፊት እኛን ሳያማክሩ የሰረቁትን ሌቦች አሳልፈን እንሰጣለን ብሎ እነ ጀነራል ክንፈ ዳኘውን አሳልፎ እንደ ሰጠ በህዝበ ፊት ሲናገር ከቆየ በሗላ በነስብሓት ነጋ ጆሮውን ሲቆነጠጥ ሃሳቡን ቀይሮ ዘራፊዎችን አሳልፈን አይንሰጥም ብሎ ካንገት በላይ ቢፎክር ማን ያምነዋል:: እርግጥ ነው ጌታቸው አሰፋ ስለነ ደብረፅዮን ገመና የሚያውቀው ነገር ሊኖር እንደሚችል መገመቱ አያዳግትም::

የደብረፅዮን መደነጋገር በይበልጥ ጋሃድ የወጣው በተለይም ሰሞኑን በመቀሌ ስታዲዮም በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ነው:: የሰልፉን ፊተውራሪ በመሆን ፊት ለፊት በመቆም ትዕቢትንና ድንቁርናን በተቀላቀለበት አንደበቱ በይፋ ሲናገር “ በለውጥ ስም ስልጣን ላይ የወጡ ሰዎች ሀገርን ማስተዳደር የማይችሉ ናቸው “ ሲል ተደምጧል:: ነገር ግን ደብረፅዮን ያልተገነዘበው ነገር አንድ ሐቅ አለ::  ህወሓቶች ከዶክተር ዓቢይ የተሻለ ሀገርን የመምራትና የማስተዳደር ችሎታ ቢኖራቸው ኖሮ ከአርባ ዓመት ተመኩሮ በሗላ ጓዛቸውን ጠቅልለው ለምን ወደ መቀሌ ፈረጠጡ?  የሚለውን ጥያቄ ግን አይመልስም:: የመመለስ አቅሙም ሞራሉም ይኖሯል ብዬም አላምንም:: ስለዚህ ሰላማዊ ሰልፉ ዘራፊዎችን የሚያወግዝ ሳይሆን ላለፉት አርባና ሐምሳ ዓመታት በሀገርና በህዝብ ላይ ሲቀልዱ የነበሩትን መሪዎች በሕግ እንዳይጠየቁ ከለላ የሚሰጥና የሚደግፍ ነው:: የሰላማዊ ሰልፉን ሽፋኝ አድርጎ የተነሳው ደግሞ ሕገ መንግስት ይከበር የሚል ቢሆንም በተግባር ሲታይ በትግራይ እየተደረጉ ያሉት የተቃውሞ ሰልፎች ግን በባህሪያቸው ፀረ ሕገ መንግስትና ፀረ ህዘብ ናቸው :: ህወሓት የኢሕአዴግና የፓርላማ አባል ነው:: የፌዴራል መንግስትም አካል ነው:: ነገር ግን የፌደራል መንግስትንና የፓርላማን ውሳኔ በመጣስ ነው ወንጀለኞችን አሳልፌ አልሰጥም እያለ የሽብርና ሕገ ወጥ ስራ እየሰራ ያለው ራሱ የህወሓት መንግስት ነው::

ህወሓቶች የትግራይ ህዝብን ለማደናገር ከሚጠቀሙበት የማጥላላት ዘመቻ አንዱ የዶክተር ዓቢይ አህመድ አሰተዳደርን ከፋሽዝም ከደርግ ስርዓት ከግራኝ መሐመድና ከሽብርተኝነት ጋር አመሳስለው በመቅረፅ የትግራይ ህዝብን ለማጥፋትና ለማንበርከክ የመጣ ወራሪ እያሉ የፕሮፓጋንዳ መርዛቸውን ሲረጩ ይታያሉ:: ሐቁ ግን ዶክተር ዓቢይ የትግራይ ህዝብ ጠላት ሳይሆን ለራሳቸው ለህወሓቶችም ጭምር ከጥፋት ያዳነ መሪ ነው:: ዶክተር ዓቢይ ወደ ስልጣን ባይመጣ ኖሮ በተለይም በትግራዋይ ላይ ተጠንስሶ የነበረውን አደጋ ምን ሊሆን እንደነበር የኢትዮ}ያ ህዝብ ይሰቷል ብዬ አላምን:: ዶክተር ዓቢይ ለትግራይ ህዝብ እውቅናና ክብር የሰጠና ከልቡ የሚወድ ርህሩህ ብቻ ሳይሆን በባድመ ጦርነት ከትግራይ አፈር ጋር የተቀላቀለ ወንድም እንደነበረው ተናግሯል:: ዶክተር ዓቢይ አህመድ ለትግራይ ህዝብ ክብር ሲል ስልጣን ከያዘ ማግስት መቀሌ ድረስ ሂዶ የተናገረውን መልካም ምኞት የትግራይ ህዝብ አንገት የሚያስደፋ ሳይሆን ተስፋ የሚሰጥና ትግራይን ከፍ ከፍ የሚያደርግ እንደነበር በዓይናችን ያየነውና የሰማነው ሓቅ ነው:: ለምሳሌ ዶክተር ዓቢይ በመቀሌ በጠራው ስብሰባ ከተገኙት የትግራይ እናቶች አድንዋ ከነበራቸው አድናቆትና ክብር የተነሳ ነብዩ የሚል የተቀደሰ ስም የተሰጠው በዚያው በትግራይ ክልል ነው:: የዶክተር ዓቢይ የመቀሌ ንግግር የሰሙና የተመለከቱ በሀገር ውስጥና በውጭ ዓለም የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችም የተሰማቸው ኩራትና አድናቆት መግለፃቸው የሚታወስ ነው:: የዶክተር ዓቢይ የመቀሌ ጉብኝት በስብስባ ብቻ የተወሰነ አልነበረም:: ለታጋዮች ያለውን ክብር ለመግለፅ ሲል በከተማው በዓዲ ሐቂ የሚገኘው የሰማእታት ሓወልት ላይ የአበባ ጉንጉን አስቀምጧል:: ይህ ሁሉ ደምረን ስናይ ዶክተር ዓቢይ የትግራይ ህዝብ መድህንና ባለውለታ እንጂ ጠላት አለመሆኑን እንረዳለን:: ከላይ እንደተጠቀሰው ለትግራይ ህዝብ ለሁሉም ችግሮች የዳረገው ማን እድሆነ በገጠር የሚኖር ተራ እረኛም ሳይቀር ያውቃል::

ታዲያ!! ሐቁ ይህ ከሆነ ህወሓቶች ዶክተር ዓቢይን በትግራይ ህዝብ ላይ የመጣ ጠላት አድርገው ለምን ተረባረቡበት? መልሱም አጭርና ግልፅ ነው:: ከአዲስ አበባ ፈርጥጠው በመቀሌ የተሸሸጉትን የህወሓት መሪዎች የዶክተር ዓቢይን የመቀሌ ጉብኝትና ንግግር ከጠበቁት በላይ አስደንግጧቿል:: ለህልውናቸውም እንደ ትልቅ ስጋት አድርገው ነው ያዩት:: ለምን ቢባል የመጨረሻ መሸሸጊያ ምሽግ ይሆነናል ብለው ያሰቡትን ህዝብ ከእጃቸው እንዳያመልጥና የለውጡ አጋር ሆኖ በዘራፊዎቹ ላይ እንዳይነሳ ካላቸው ስጋት የሚነሳ ነው:: በዚህ መሰረት የዶክተር ዓቢይን ለትግራይ ህዝብ ያለውን መልካም አሳቢነትና ያደረገውን አስተዋፆዖ በመካድ ያላንዳች ይሉኝታ ገልብጠው ወደ ጥላቻና ጠላትነት በመቀየር ከመንግስቱ ሀይለማሪያም ፈቶ ጋር እየቀላቀሉ ጠላት መጣብህ እያሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስምና ክብር ሲያጠፉና ሲያጎድፉ ይታያሉ:: “በለውጥ ሰም ስልጣን የያዙ ሰዎች ሀገርን ማሰተዳደር አይችሉም ” የሚል የደብረፅዮን ዘለፋም የዘመቻቸው አንዱ አካል መሆኑን ያሳየናል:: ይሁን እንጂ እውነትና ጢስ መውጫ አያጣም እንዲሉ ጌዜ ዳኛ ታሪክ ምስክሩ ነውና ሁሉም በለውጡ ሂደት ላይ ጊዜውን ጠብቆ ጋሃድ ይሆናል::

የመቀሌው የክተት የጦርነት ነጋሪት የት ይደርሳል?

በመቀሌ ስለተደረገው የክተት ሰላማዊ ሰልፍ ስመለከት በአእምሮዬ ውስጥ ድቅን ብሎ ያስታወሰኝ በትግራይ አካባቢ ለዓመታት ሲነገር የቆየ አንድ አስቂኝ ተረት ነው:: እሱም እንዲህ ይላል:: ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጉረኛ ሰውዬ ነበረና ምሳውን ቋጥሮ ገራዴውን ይዞ ወደ አደን ይሄዳል:: ጫካ ገብቶ ሲዞር ሲዞር ምንም የሚታደን እንስሳ ሊያገኝ አልቻለም :: ከዚያም በሗላ ተስፋ ቆጦ ባዶ እጁ ወደ ቤቱ ሲመለስ አንድ ወንዝ ዳር ደረሰና ጠባቂ የሌላቸው ጥቂት ፍየሎች አገኘ:: ግራና ቀኙን ሲመለከት ሰው እንደሌለ አረጋጠና አንዱን ወጠጤ አርዶ ሚዳቋ አገኝቼ ገደልኩ ብሎ ለሚስቱ ለመስጠት ወሰነ:: ከዚያም ወጠጤውን ያዘና ተሸክሞ ወደ አንድ ዋሻ ገብቶ ተደብቆ ለማረድ ሲንደረደር ገበያ የዋሉ ሰዎች አገኙትና ለካስ ፍየሎቹን የጎረቤቶቻቸው መሆናቸውን ያውቁ ኖሯል ሰውዬውን ደብድበው የያዘውን ወጠጤ አስጥለው ጎራዴውንና ስንቁንም ጭምር ማርከው ለቀቁት:: ሌባው ሰውዬ ሲያዘግም ውሎ ወደ ማታ አካባቢ ሲጨልም ሰው ሳያየው ቤቱ ገባ::  አድኖ ለዓውዳ ዓመት የሚሆን ስጋ ይዞ ይመጣል ብላ ድልህና አዋዜ አዘጋጅታ በጉጉት ስትጠብቅ የነበረችው ሚስቱም ደንግጣ ምን ሆኑ ምን ሆኑ ብላ በጭኾት ስትጠይቀው “ ሚዳቆ ገድየ ተሸክሜ ስመለስ አስር ሰዎች በመንገድ ላይ ዘረፉኝ “ ብሎ መለሰላት:: ጎራደውስ የት አለ? ብላ ጠየቀቺው:: ጎራዴውንም ጭምር እንደወሰዱት ነገራት :: ከዚያም በነገሩ ሁሉ ተበሳጭታ በትካዜ ስትመለከት ለካስ ትዃን አለው ብለው ንቀው የተውለትን የጎራዴው ሰፈር (አፎት) አየችና ለምን ታዲያ አፎትን አልወሰዱትም? ብላ ስትጠይቀው ከተቀመጠበት ብድግ ብሎ ዘራፍ ዘራፍ አለና ሞኝ ነሽ እንዴ ጎራዴው ቢወስዱትም አፎቱንማ ክንዴን ሳልተራስ በፍፁም አልሰጥም ሲል ተናገረ:: ሚስቲቱም የባልዋን አነጋገር ገርሟት ፈገግ አለችና “ወይ አንተ ሰውዬ ጉራ እንጂ በሽታ አይገድልህም:: በል አሁን ስለገራዴውና ስለስጋው ነገር እንርሳውና የባሰ አታምጣ ብለን አርፈን እንኑር:: ይልቁንስ ጉዳችን ጎረቤት እንዳይሰማው በኔና ባንተ ይቅር ስትል ተናገረቺው ይባላል::

ህወሓቶች ጊዜ ከድቷቸው በህዝብ የተባበረ ክንድ ተደቁሰው ጥርሱ ያለቀበት አሮጌ አንበሳ መስለው ከአዲስ አበባ ፈርጥጠው በመቀሌ መደበቅ ከጀመሩ እኖሆ ወራት አሳልፏል:: በዚሁ ቆይታቸው እየቆዘሙ ድሮ ያሳለፉትን የደደቢት ታሪክ በዓይነ ህሊናቸው እየቃኙ እንዋጋለን ብለው ቢፎኩሩ ከላይ የተጠቀሰውን ተረት ተረት ከመሆን አልፎ ትርጉም ያለው ጉዳይ ሆኖ አልተገኘም:: ህወሓቶች ይቅርና ጦርነት መርተው ለድል ሊያበቁ ቀርቶ ራሳቸውን እንኳን ማዳንና መመራት ወደ ማይችሉበትና ተመልሰው ወደ ማይጠገኑበት ደረጃ የደረሱ መሆናቸውን ዛሬ በሀገራችን የለውጥ ሂደቱን ተከትሎ የመጣ በመሬት ላይ እየታየ ያለው እውነታ ራሱ ተናጋሪ ነው:: ህወሓት ላለፉት በርካታ ዓመታት ሾላ በድፍን እየተመራ ከቆየ በሗላ ውስጡ ውስጡን በስብሶ በመጨረሻ በምስጥ እንደተበላ ትልቅ ዛፍ ከስረ መሰረቱ የተገረሰሰና የተፈረካከሰ ስርዓት ነው:: ስለዚህ ከስሩ በስብሶና ደርቆ የወደቀ ዛፍ እሱን አስወግዶ መሬቱን አመቻችቶ በሌላ አዲስ ችግኝ ዛፍ ካልተተካ በስተቀር ደርቆ የተጣለውን እንጨት መልሰን ብንተክለው ህይወት ሊዘራ አይችልም:: ዓሳ ሲገማ ከጭንቅላቱ ይጀምራል እንዲሉ ህወሓት የታመመውን አካሉ እንደ ጋንግሪን ቆርጦ በመጣል በአዲስ ራዕይና በአዲስ ትውልድ ካልተተካ በስተቀር ህወሓትን እናድን በሚል መፈክር እየተካሄደ ያለው ጀምላዊ እንቅስቃሴ ራስህን ከማሞኘትና ከመላላጥ አልፎ ውጤት ሊኖረው አይችልም::

  1. ህወሓት ጦርነትን ለመምራት የሚያስችለው የጠራ ራዕይና የመሪነት ቁመና የለውም:: ህወሓት እንደ ድርጅትም ሆነ እንደመንግስት ራዕይ የሰነቀና በሙያ የተካነ አመራር አጥቶ ምርኩሱን ጥሎ እንደሚደነባበር ዓይነ ስውር ሽማግሌ ሆኖ ከቆየ ዓመታት አልፎታል:: ዛሬ ህወሓት ይመካበት የነበረ ነገር ግን በተግባር ተፈትኖ የወደቀ ዲሪቶ አብዮታዊ ዴሞክራሲም ተጠራርጎ ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት ተጥሏል:: መሪዎቹም ውስጣቸው በተለያዩ የጎበዝ አለቆች የተከፋፈሉና ለየቅሉ የሆነ አላማና ጥቅም ያላቸው እርስ በራሳቸው የማይተማመኑ ናቸው:: ህወሓት የጠራ ራዕይና አላማ የለውም ብቻ ሳይሆን የአመራር ኢንተግሪቲ ዲሲፐሊንና ጥምረት የሌለው : ከየት ተነስቶ የት እንደሚደርስ የማያውቅ: መላ ቅጡ የጠፋበትና የፓለቲካ ካፒታሉን በልቶ የጨረሰ ድርጅት ነው:: አብዛኞቹ የአመራር አባላቱም በዕድሜ የገፉና በአስተሳሰብ የደከሙ ከመሆናቸውም በላይ የውጊያ ልምድ የነበራቸው ጀነራሎችና መኰነኖችም ብዙዎቹ በተለያየ ምክንያት ጡረታ በመውጣት ወይም ተቋሙን በገዛ ፍቃዳቸው በመተው ወደ ግል ንሮኣቸው ገብቷል:: ሃብት አፍርቷል:: ቤተሰብ መስርቷል:: ዳግም ወደ ጦርነት ለመሄድ አይፈልጉም:: ስለዚህ ህወሓት የጠራ ራዕይና ብቃት ያለው አመራር የለውም ስንል ተዋግቶ አሸናፊ ለመሆን በመጀመሪያ ህዝቡን ለማሳመንና ከጎነህ ለማሰለፍ የሚያስችል ምክንያታዊነት ያለው ለጦርነት የሚያበቃ አጀንዳ ይዞ መቅረብ ያስፈልጋል:: ይሁን እንጂ ህወሓቶች በተጨባጭ ጦርነት ለመክፈት የሚያስችል አሳማኝ አጀንዳና መነሻ የላቸውም:: አጀንዳቸው የፍትሕ : የሕግ የበላይነት :  የመብትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ሳይሆን በሀገር ደረጃ የአንበሳ ድርሻ ይዘው ለመኖር ሌላውን ህዝብ በሐይል ማንበርከክ : የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ መቀልበስና ፌዴራል መንግስቱን ማፍረስ ነው:: ይህ ካልሆነላቸው ደግሞ የመገንጠል አጀንዳ ማራመድ ነው:: ይህ ደግሞ የማይሆን ነገር ነው:: ስለሆነም ህወሓት በንቀት በትዕቢትና ከሕግ በማፈንገጥ ጦርነት አካሂዳለሁ ብሎ ቢነሳ ራሱን በራሱ የመግደል (ሱሳይዳል) ሙኮራ ካልሆነ በስተቀር የትም የሚደርስ አይደለም:: የድሮ የዘመነ መሳፍንት ዓይነት አሰላለፍና አስተሳሰብ ተይዞ ከዘመናዊ ሀገራዊ ሰራዊት ጋር የሚደረግ ጦርነት የዓይጥና የድመት ጫዋታ ዓይነት ነው የሚሆነው::

 

  1. የህወሓት መሪዎች የጦርነት ስሌት መነሻው የተዛባና የተሳሳተ ነው:: ህወሓቶች ደርግን ማሸነፍ ማለት የኢትዮ}ያ ህዝብን ማሸነፍ ማለት ነው ብለው ስለሚያስቡ መልሰው መላልሰው እንደማስፈራሪያ የሚጠቀሙበት ፊልምም ያው ያረጀ ያፈጀው የዘመነ ደደቢት ትርክት ነው:: ነገር ግን አሁን ያለው እውነታ በድሮ በሬ ማረስ እንደማይቻል ያሳየናል:: ጊዜው ተለውጧል፣ ትውልድ ተቀያይሯል፣ የሐይል አሰላለፉ ሚዛን ተቀይሯል ፣ የውጊያ ዓይነትና ስርዓትም ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አብሮ ተለውጧል ፣ የአህጉራችንም ሆነ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲና የፓለቲካ ሁኔታም ከግሎባላይዘሽን ጋር ተያይዞ ተቀያይሯል:: ነገር ግን ራሱን ያልለወጠ ህወሓት ብቻ ነው:: በሀገራችን ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው:: ዛሬ ህወሓት የበላይ የመሆን ቀርቶ እንደ ድርጅት የራሱን ህልውና ጠብቆ ለመኖር እንኳን ወደ ማይችልበት ደረጃ ደርሷል:: ህወሓቶች ከኛ ጎን ይሰለፋሉ ብው ይመኩባቸው የነበሩትን አጋር ድርጅቶችም ህወሓት የከሰረ ድርጅት መሆኑን እየተረዱ ቀስ በቀስ ከለውጡ ጋር እየተደመሩ ናቸው:: ይጠቀሙበት የነበረ የስለላ መረባቸውም ከጥቂት ቦታዎች በስተቀር በሀገር ደረጃ ተበጣጥሷል:: ይመካበት ከነበረው መከላኪያና ድህንነት ተቋማትም በወሳኝ መልኩ ተጠራጎ ወጥቷል:: በኢሕአዴግና በመንግስታዊ መዋቅር ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር ዓቅማቸውም ተመናምኗል:: በኢኮነሚም ቀደም ብሎ ካሸሸውና ከዘረፈው ሃብት በስተቀር በአሁኑ ገዜ እንደፈለገ የሚፈተፍትበት ዕድል የላቸውም:: በፓለቲካም ህወሓት የብሄር ብሄረሰብ ጠበቃና ነፃ አውጪ መስሎ ለአርባ ዓመታት ያህል ወንድም ከወንድሙ ጋር ለማጋጨት ይጠቀምበት የነበረው የለያይተህ ግዛ ካርድም ተነጥቋል:: ባጠቃላይ ህወሓት በአሁኑ ገዜ በኢትዮ}ያ ህዝብ ዘንድ ድጋፍ የለውም ብቻ ሳይሆን የተጠላና እንደ ጨካኝ አውሬ የሚታይ ድርጅት ሆኗል:: ስለዚህ ህወሓት ራሱ በሰራው ጥፋት እርቃኑ የወጣ ድርጅት ጦርነት ማካሄድ ቀርቶ ራሱን መከላከል የማይችል ሽባ ሆኖ ቀርቷል::

 

  1. ህወሓት ጦርነት ቢያስነሳ ውጊያው በአማራና በትግራይ ድንበር ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይሆንም:: ትግራዋይ ባለበት ቦታ ሁሉ ሊቀጣጠል ይችላል:: ቢያንስ ከግማሽ በላይ ትግርኛ ተናጋሪ በመላ ሀገሪቱ እንደሚኖር ይታመናል:: ጦርነቱ ከተጀመረም የፍትሕ ጥያቄ መሆኑን ቀርቶ የዘር መልክ ሊይዝ ይችላል:: በሌላ በኩል ደግሞ አይበለው እንጂ ጦርነት ቢነሳ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የሚሆነው ያው የድሃው ህዝብ ልጆች እንጂ የባለስልጣናቱን ማለት የነ ስብሓት ነጋና አባይ ፀሃየ ልጆች አይደሉም:: የባለስልጣናቱና የጀነራሎቹ ልጆችማ በአውሮፓ እሽያና አመሪካ ዕድሜ ለተዘረፈው ሃብት በተንደላቀቀ ንሮና ዓለም የሚኖሩና በምርጥ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ናቸው:: ስለዚህ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት የሚስችል ብቃት ያለው ህዝብና መንግስት እያለ ጠመንጃ ስለያዘ ብቻ ልምድ አለኝ ብሎ ጦርነት መቀስቀስ በታሪክም ሆነ በወንጀል የሚያስጠይቅ ሕገ ወጥ ተግባር ነው:: ድርጊቱም ህወሓት ራሱን ከመንግስትነት ወደ አልሸባብነት፣ ከፓለቲካዊ ድርጅነት ወደ ተራ ሽፍትነት እየተቀረ መሄዱን ያሳየናል:: ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ደግሞ የዶክተር ዓቢይ አስተዳደር ሃላፊነት ብቻ አይደለም:: የአህጉራችን ብሎም የመላ ቀጠናችን ሀገራት ሃላፊነትም ጭምር ስለሆነ ህወሓቶች የሚሸሸጉበት ጫካና ሀገር ሊኖራቸው እንደማይችል ሊገነዘቡት ይገባል:: ስለዚህ የህወሓቶች የጦርነት ነጋሪት ከማንም በላይ የራሳቸውን የመጨረሻ ግብኣተ መሬቱን የሚያቀላጥፍ እንጂ በሀገር ደረጃ የሚያመጣው የፓለቲካና የስትራተጂ መነጋት አይኖርም:: ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ሽንፈቱን የተረጋገጠ ነው::

 

  1. አያርገው እንጂ ህወሓት ጦርነት ቢያስነሳ ከማንም በላይ ተጎጂ የሚሆነው የትግራይ ህዝብ ነው:: ሌላ ቀርቶ ህዝቡ ራሱን ለማዳን ሲል የሚሰደድበትን ቦታ እንኳን እንዳይኖረው ዙሪያውን ሁሉ በጥላቻ አጥረውታል:: የህወሓት የልማት ድርጅቶችም ሆነ የግለ ሰቦች ድርጅቶች ገበያቸውና የገንዘብ ምንጫቸው ኢትዮ}ያ ስለሆነ ጦርነት ቢነሳ ከማንም በላይ የሚጎዱት እነርሱ ናቸው:: ህወሓት አደብ ካልገዛና ልኩን አውቆ ካልኖረ የኢትዮ}ያ ህዝብ ቁጣ ሲገነፍል ምን ሊያስከትል እንደሚችል ሩቅ ሳንሄድ ባለፉት ሶስት ዓመታት በየቦታው የተከሰቱትን ሁኔታዎች በባሰ መልኩ ዳግም ሊከሰቱ ይችላሉ:: ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ ወደ ትግራይ የሚወስዱትን መንገዶች አልፎ አልፎ በመዘጋታቸው ምክንያት በክልሉ ያስከተለው የንሮ ውድነትና የገበያ መናጋት ተፅዕነው ቀላል አይደለም:: ከዚህም አልፎ ከክልሉ ጋር የገንዘብ የንግድ የትራንስፓርትና የኮሚኒከሽን ግንኙነት ከተዘጋና ከተቋረጠ ደግሞ በሕብረተሰቡ ዕለታዊ ንሮ ላይ ሊኖረው የሚችል ቀጥተኛ ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም:: ስለዚህ መፍትሄው ጨው ለራስህ ብለህ ጣፍጥ አሊያም ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል እንደተባለው ነው::

በመጨረሻም በዚሁ አጋጣሚ ለትግራይ ህዝብ በጠቅላላ በተለይም ለወጣቱ ለምሁሩና ለስርዓቱ ደጋፊዎችም ጭምር ለማስተላለፍ የምፈልገው አጭር መልእክት ሀገርና ህዝብ ነባሪ ነው ግለ መሪዎች ፓለቲከኞችና መንግስት ግን ሃላፊዎች ናቸው::  የትግራይ ህዝብ መድህን ዋስትናና ሞሶሶ መቶ ሚሊዮን የኢትዮ}ያ ህዝብ እንጂ በግለ ሰቦች መልካም ፈቃደኝነት ላይ የተንጠለጠለ አለመሆኑን ለፓለቲካ ፍጆታ ወይም ለፕሮፓጋንዳ ተብሎ የሚነገር ስንፈልግ የምንቀበለው ሳንፈልግ ደግሞ የምንጥለው ሳይሆን የአጥንታችን ፍላጭና በደማችን ውስጥ ያለ የማይነጣጠል ባህሪያዊ ትስስር ያለው ነው:: የትግራይ ህዝብ ከሌላው ወንድም ህዝብ የተለየ ፍላጎት የተለየ ጥቅም እምነትና አላማ የለውም:: በጭቁን ህዝቦች መካከልም መሰረታዊ ቅራኔ የሚባል ነገር አልነበረም አሁንም የለም ለወደፊትም አይኖርም:: ነገር ግን ሁሉ ጊዜ ለግጭት ላለመተማመንና ለጥላቻ መንሲኤ ሆነው የቆዩት ግለ መሪዎችና ፓለቲከኞች ከሕግ ከህዝብና ከሀገር በላይ በመሆን የራሳቸውን ጥቅም ለመጠበቅ ሲባል ህዝብን የጭቆና መሳሪያ ለማድረግ በሚከተሉት ፓሊሲና በሚቀርፁት የዓፈና ስርዓት የሚመነጩ ችግሮች ናቸው:: ለምሳሌ በህወሓት ካድሬዎች ተዋናይነት ሰሞኑን በመቀሌ ከተማ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ስንመለከት ከትግራይ ህዝብ ህልውና ይልቅ የግለ መሪዎች ህልውና ይቅደም:: ከትግራይ ህዝብ ድህንነት ይልቅ የጥቂት ዘራፊዎች ድህንነት ይጠበቅ :: ከትግራይ ህዝብ መብትና ክብር ይልቅ የግለ ሰዎች መብትና ክብር ይቅደም:: ከትግራይ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ይልቅ ቡድናዊ ፍላጎትና ጥቅም ይጠበቅ:: በሕግ የሚፈልጉ ጥቂት መሪዎችን አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ የትግራይ ህዝብ በጦርነት ይለቅ በማለት በአደባባይ ሰልፍ የሚወጣ ትውልድ መፈጠሩ የህወሓት ለያይተህና አደንቁረህ ግዛ የሚል ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ የተቀዳ ፓለሲ ምን ያህል ስር የሰደደ ክሮኒክ በሽታ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው:: ለጥቂት ዘራዎች ድህንንት ለመጠበቅ ሲባል የትግራይን ህዝብ መብትና ሉዓላዊ ክብር ለድርድር ማቅረብና መደበቂያ ዋሻና አድርጎ መጠቀም ለህዝቡ ድፍረት ሐፍረትና ውርደት ነው:: በመሆኑም በህዝቡ ደም የሚነግዱ መሪዎችና በስሙ የፓለቲካ ቁማር የሚጫወቱ ግለሰቦችን ዋል እደር ሳይባል ልናጋልጣቸውና ልንቃወማቸው ይገባል::

ለመላ የኢትዮ}ያ ህዝብ ታጋይ ሐይሎች ወጣቶችና ምሁራን የማስተላልፈው መልእክትም ተመሳሳይ ነው:: በአንድ ክልል የሚፈጠር ችግር ወደኔ አይምጣ እንጂ ምን አገባኝ ራሳቸው ይወጡት ብሎ የየክልሉን ህዝቦች ጉዳይ ብቻ አድርጎ መመልከትና ችላ ማለት የተለመደ ሆኖ ቆይቷል:: ይህ በመሆኑም ስርዓቱ ህዝቡን ሆድና ጀርባ አድርጎ በተናጠል በያለበት እየቀጠቀጠ እንዲገዛ በገዛ ፍቃዳችን ዕድል ሰጥተነው ኖረናል:: በየክልሉ የተፈጠሩት ብሄር ተኮር የፓለቲካ ድርጅቶችም የየክልላቸው ትናንሽ መንግስታት (ኢምፓየር) በመፍጠር ፈላጭ ቆራጭና ንኡሳን ነገስታት በመሆን የየክልላቸውን ህዝብ ይግባኝ በማይባልበትና አቤት የሚሉበት ሕግ በሌለበት ሁኔታ በደል ሲያደርሱባቸው ቆይቷል:: ዛሬ በትግራይ ያለው ሁኔታ ስንመለከትም በኢትዮ}ያ ሁለት መንግስታት ያሉ ነው የሚመስለው:: ህወሓት በማዕከላይ መንግስት አልገዛም ብሎ ካፈነገጠ ወራት አስቆጥሯል:: የትግራይ ህዝብ መብት ነፃነትና ዜግነት ባለቤት አጥቶ በህወሓት እንደምርኮኛ ተይዞ በቁም እስረኛነት ይገኛል:: አሁን በትግራይ እየታየ ያለው የተገላቢጦሽ እንቅስቃሴ ስንመለከት በህዝብ ላይ በደል የፈፀመ የህወሓት ቡድን ከተበደለው ህዝብ በላይ ተበዳይ በመምሰል በገንዘብ ሀይል ሚዲያ ተቆጣጥሮ እንደፈለ ሲፈነጭና በህዝብ ላይ ጦርነት ሲውጅ እያየን ነው:: በአንፃሩ በደል የደረሰበትን ህዝብ ግን አንገቱ ሲደፋና ለሰላም ሲባል ትዕግስቱን እንደሞኝነት እየተቆጠረ ዳግም በደል ሲደርስበት እያየን ነው:: በዚሁ ዓይነት ከቀጠለ ደግሞ ዋጋ ተከፍሎበት የተገኘው ለውጥም ዋስትና ሊኖረው አይችልም:: ለውጡ ከተቀለበሰ ደግሞ እንደ ሀገር ቀርቶ እንደሰው ለመኖርም ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነገር ነው:: ስለሆነም ይህቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም እንደተባለው ፀረ ለውጥ ሐይሎች በየትም ይብቀሉ የትም በላይ ላያችን  ላይ እንደፈለጉ እንዲፈነጩብን ዕድል ሊሰጣቸው አይገባም:: በአንዳንድ ክልሎች ሰብኣዊና ሕገ መንግሰታዊ መብታቸውን በመጣስ በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው በደልም በስተጀርባው ማን እንዳለ ያዳባባይ ሚስጢር ነው:: ስለሆኑም አባሪ ተባባሪ በመሆን በሰላማዊ ወገኖቻችን ላይ እተፈፀመ ያለው በደል በመቶ ሚሊዮን ህዝብ ላይ እንደተፈፀመ ቆጥረን አደብ እንዲገዙና ለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድረግ ሁሉም ተባብሮ እንደ አንድ ሰው ጥብቅና በመቆም የወገን ደራሽነቱንና አትንኩኝ ባይነቱን አደባባይ ወጥቶ ማሰማት ይጠበቅበታል::

 

 

 

ኢትዮ}ያ እናት ሀገራችን በልጆችዋ ትግል ትለምልም

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop