«የቅማንት ኮሚቴ» ነን የሚሉ የወያኔን ባለ አምባሻ ባንዲራ እያውለበለቡ በፋሽስት ወያኔ ዘመን ሕግና ስርዓት እንዳለ አድርገው በመቁጠር «በሕገመንግሥቱ መሰረት» እያሉ «ራስ በራስ የማስተዳደር ጥያቄ» ያሉትን የሕወሓት አጀንዳ ይዘው አብረዋቸው ከኖሩት፤ አባትና ልጅ፤ እናትና ልጅ እንዲሁም ቤተሰብ ከሆኑት ከአማራ ወገናቸው ጋር ግጭት ውስጥ ሲገቡ ስመለከት ግርም ይለኛል። ያለፉት ሀያ ሰባት የፋሽስት ወያኔ የአፓርታይድ አገዛዝ ዓመታት በባህላቸን የነበረው ሕግና ስርዓት እንኳ ከነአካቴው ጠፍቶ፤ ሕገ-ጉልበት፣ ሕገ- ኃይልና ሕገ አራዊት ሰፍኖ በጎሳ አጥር ተለያይተን አቤልና ቃኤል ሆነን የኖርንበት የጨለማ ዘመን ነው።
«የብሔር ብሔረሰቦች መብት» ምናምን የሚባል ነገር ሁሉ የፋሽስት ወያኔና የርዕዮተ ዓለም አጋሮቹ የውሸት ማታለያ ነው። ወደድንም ጠላንም ላለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት የነበረን ሕገ መንግሥት ተብዮው የሰጠን «መብት» ሳይሆን ከትግራይ የወጣው የወያኔ መደብ አሽከር በመሆን፤ ይህንን ተገን አድርገን ከኛ ጎሳ ውጭ ነው የምንለውን በመቀማት፣ በመግደል፣ በማሰር፣ በመዝረፍና በማሳደድ የወያኔን ፈቃድ የፈጸምንበት የሎሌነት ዘመን ነበር። የዚህ የሎሌነት ስርዓት አገልጋይ አልሆንም ያለ እንደ ጎሳም፣ እንደ ኢትዮጵያዊና እንደሰው ምንም መብት ኖሮት አያውቅም። ባለፉት ሀያ ሰባት የመከራ አመታት መብት ነበረን የምትሉ የነበራችሁ መብት ከእንስሣም ያነሰ መብት ነበር። የነበረህ መብት የኔ ጎሳ አይደለም የምትለውን ሰው የወያኔን ፍቃድ ለመፈጸም ስትል የመግደል፣ የመደብደብና የማፈናቀል መብት ብቻ ነው። ሕግ ስለሌለ ለነዚህ ሁሉ ማንም ከልካይና ተጠያቂ አልነበረም። ከዚህ በላይ መብት አለመኖር ምንም የለም። ባለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት እያንዳንድህ እንኳን «መሬቴ፣ አገሬ» በምትለው ላይ ይቅርና የገዛ አካልህም ባለቤት አልነበርክም። አካልህ የፋሽስት ወያኔ መጫወቻ ነበር። ይህ ፋሽስታዊ ስርዓት የሚቆየው ተጠቂው በቃኝ እስኪል ድረስ ብቻ ነበር።
በቃኝ የሚለው ድፍረት ከዚህም ከዚያም በማፈትለኩ ለጊዜውም ቢሆን ያ የጨለማ ግርማ ባለቤት ከተሰየመበር ሰው የማጥቂያ ወንበር ወደተከላካይነት ዝቅ ብሏል። እግዚአብሔርንና ፍትሕን መሰረት ባደረገ የሰው ሕግ ኢትዮጵያ የሁሉም ነች። ምክንያቱም ዛሬ ግብኗ የቆመው ኢትዮጵያ ሁሉም ዋጋ የከፈለባት ምድር ናትና። የትኛውንም የኢትዮጵያ አካል ማንም ተነስቶ «ይህ የኔ ብቻ ምድር ነው» የማለት መብት የሌለባት አገር ነች። «ቅማንቶች ይህ መሬት የኔ ነው ሲሉ»፣ እውነታው አማራን ብቻ ሳይሆን ሌላውን መቶ ሚሊዮኑን ኢትዮጵያዊም መብት እየነጠቁ ነው። ትግሬውም እንዲሁ፣ አደሬውም እንዲሁ። ስልጢውም እንዲሁ። ኦሮሞውም እንዲሁ። አማራውም አዲስ አበባ የኔ ብቻ ነች ካለ የሌላውን ሁሉ ሕዝብ መብት መንጠቁ ነው። በፍትህ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ ቤቱና ንብረቱ ነች። ማንም መጨቆን፣ መፈናቀል፣ መከልከል፣ መገደል፣ መገለል የለበትም። አባቶቻችን በነጻነት እንድንኖር የደምና የአጥንት በከፈሉባት አገር ሁሉም በኩልነት ሊኖርባት ይገባል።
ይህ ሳይሆን ይቀርና «ከዚህ ወዲህ የኔ ነው» ካልሕ ግን ሕግ የለም ማለት ነው ያንን ያሰመርኸውን መሬት የምትይዘው ጉልበት እስካለህ ድረስ ብቻ ነው። ያንን ማድረግ የምትችለው የፍትህ ስርዓትን ገድለህ ነው። ያንን ካደረግህ በኋላ ሌላው ተነስቶ ያንተኑ ተግባር ሲደግም «በሕግ አምላክ» ማለት አትችልም፤ አንተ ራሱ አፈር ድሜ ያበላኸውንና የሌለውን ሕግ ከየትም አታመጣም። አንተ በመረጥኸው መንገድ ሕገ አራዊት ስላነገስህ አንተም በዚያው ትዳኛለህ። እንኳን ቅማንት፣ እንኳን ትግራይ፣ ኤርትራም ቢሆን እንደዚሁ ነው። ዛሬ ፋሽስት ወያኔዎችና ደርጎች ስለሕግ ሲያወሩ፣ በእስር ሲውሉ ስለተጣሰው መብታቸው አብዝተው አቤቱታ ሲያሰሙ ይገርመኛል።
ታሪክ የሚያስታውሰን፤ ፍትሕና ሕግ የሚደርሰን «ባለጊዜ» በነበርንበት ወቅት ለሌሎች የሰጠነውን ያክል ነው! ለዚያኮ ነው «በሰፈሩት ቁና ተመልሶ የሰፈርሎታል» የሚለው ያገሬ ሰው! የወያኔ ዘመን እሳ የሌላቸው የትግራይ ዘራፊዎች፣ ገፋፊዎችና ገዳዮች በመንግሥትነት የተሰየሙበት የንጥቂያ ዘመን ነበር። የንጥቂያው አገዛዝ ለመግደልና ለመዝረፍ ሕዝብና ሕዝብን ማፋጀቱ የግድ ነበር። አውሮፕላኖች፣ መርከቦች፣ ሆቴሎች፣ ቢሊዮን ረብጣ ዶላሮች፣ ወዘተ በመዝረፍ ከአገር በላይ የከበሩት «ብሔር፣ ብሔረሰቦች» የሚሏቸውን እያጋጩ ነው። ይህ ሁናታ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተዘረጋ ሩብ ክፍለ ዘመን አልፎታል። ይህ ሩብ ክፍለ ዘመን የቆመው የፋሽስት ወያኔ የዘረፋ፣ የቅሚያና የግድያ አገዛዝ ጎንደር ላይ አማራ «የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው ሲል» ጅብ ሲጮህ እንደሚፈርስ ከአህያ ቆዳ እንደተሠራ ቤት መናድ ጀመረ።
አማራው በቃኝ ካለ ራሱን የመከላከል ታሪካዊም፣ ስነልቦናዊም ቁሳዊም ክህሎት አለው። እስካሁንም ይህንን ክህሎቱን አለመጠቀሙ «በአንድነት መኖር ይሻላል» የሚለው ስነልቦናዊ ምክሩ አለቅ ብሎትና ገና ጥንት አብርሀም ሊንከን « በአንድ ቤት ሆኖ ለመፈጸም ያልተቻለውን ውል ከተለያዩ በኋላም ያስቸግራል» እንዳለው የወደፊቱን ከፍተኛ ግጭትም እያሰበ ኖሯል። አብሮ መኖር ግን ጉዳት ብቻ የሚያመጣበት ከሆነ እሱም ይቅርብኝ ብሎ ወደ «ንጥቂያው» መግባቱ አይቀርም። ያን ጊዜ እሱም ሕገ አራዊትን ሕግ ቢያደርግ አይፈረድበትም። አውርቶ ያልጠገበውን ያባቶቹን ታሪኩ እየጠቀሰ የአባቶቹን አገር claim በማድረግ ጉልበቱ የቻለለትን ያህልም ይነጥቃል። እየሄድንበት ያለው መንገድ እዚህ አያደርሰንም የሚል ካለ ያስብበት። ይህንን የሚጠራጠር ካለ እስካዚያው ብርታቱን ይስጠው እንጅ ወደሜዳው እየዘለቅን ስለሆነ ስንደርስበት ያየዋል። ከዚህ ውጪ ግን ሕገ አራዊት ሰፍኖ የሌለ ሕግ በማጣቀስ «ይገባኛል» ማለቱ ራስን ከማታለል ውጭ ፋይዳ የለውም።