የለውጡ ተግዳሮቶች በኔ ዕይታ – ይነጋል በላቸው (ከአዲስ አበባ)

በተለምዶ “የለማ ቡድን (ቲም ለማ)” የሚባለው ደፋርና ጀግና ስብስብ እያኬሄደው ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ እጅግ ግሩም ነው፡፡ “የአህያ ሥጋ አልጋ ላይ ሲሉት ዐፈር ላይ” እንዲሉ ሆኖብን አንዳንዶቻችን በረባ ባልረባ ምክንያት ይህን ለውጥ እንቃወም እንደሆነ እንጂ ለውጡ ያልተጠበቀና ሀገራችንን ከውድመት፣ ዜጎቻችንን ከዕልቂትና ከውርደት የታደገ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ እኛን ብዙዎች ኢትዮጵውያንን ብቻ ሣይሆን መላው ዓለምን ያስደመመ ነው፡፡ እንዲህ ስል “ለውጡ ምሉዕ በኩልሄ ሆኖ ሁሉንም ወገን እኩል ያስደሰተና እያስደሰተ የሚገኝ ነው” ለማለት ፈልጌ እንዳልሆነ ይያዝልኝ፡፡ ፍርድ ከሁሉም አቅጣጫና ለማንም የማያዳላ ሲሆን ደግ ነው፡፡ አንድ የለውጥ እንቅስቃሴ ደግሞ በአንዳንድ ነገሮች መታማቱና መወቀሱ ወይም ተቃውሞን ማስነሳቱ ያለ ነው፡፡ እንኳንስ የኛን  ሀገር በመሰለች ምስቅልቅሉ የወጣ ማኅበረ-ኢኮኖሚዊ ባለበት ሀገር ይቅርና ሶማሊያን በመሰሉ በብዙ ነገሮች የሚመሳሰሉ ኅብረተሰቦች ባሉባቸው ሀገራትም ሁሉንም ሊያስደስት የሚችል የለውጥ ሂደት አይኖርም፡፡ አንድን ነገር መቃወም – ጠቃሚም ይሁን አይሁን – ተፈጥሯዊና ሰብኣዊም ነው፡፡ ሲቃወሙና ለተቃውሞ ብቻ መኖር ግን አጠያያቂ ይመስለኛል፡፡

ሕወሓቶች በዚህ ለውጥ ያጡት ብዙ ነገር በመኖሩ እነሱ ለውጡን ከመቃወም አልፈው አሁን እያደረጉት እንደሚገኙት ለመቀልበስ ቢጥሩ አይገርምም፡፡ የነሱ የታወቀና የለየለትም ነው፡፡ የለውጡ ተጠቃሚ ከሆንነው ወገኖች ውስጥ የሚታየው ምናልባትም “የኔን ወገን በቅጡ አላካተተም፤ እነእገሌን አግልሏል፤ እነገሌን ይበልጥ እያሰባሰበ ነው፣ ለውጡ በሚፈለገው ፍጥነት አልተጓዘም…” ከሚል አንዳንዶቹ አስተሳሰቦች ሰባት ዓመት የታወረውንና “ነገ ትድናለህ” ቢሉት “ዛሬን እንዴት አድሬ?” ያለውን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ “የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል” የምንለውን፣ ምናልባት አንዳንዶቹ ደግሞ የረጋ ወተት ቅቤ እንደሚወጣው መዘንጋታቸውን የሚያስታወሰን ይመስለኛል፡፡ የሆኖ ሆኖ ለውጡ አሁን ባለው ሁኔታ ከተጓዘ የማታ ማታ ባለድል ለመሆኑ በበኩሌ ጥርጥር የለኝም፡፡ መተቻቸታችን ለዕድገታችን አንዳች አስተዋፅዖ የሚኖረውና ከተንኮልና ከመጠላለፍ አዙሪት ነፃ ከሆነ እደግፈዋለሁ፡፡ ባህላችን ዱለኝነትን ስለሚያበረታታ በቶሎ ወደ ኩርፊያና ወዳልተፈለገ ንትርክ እንገባለን እንጂ በመሠረቱ  ትችትና ሂስ ጠቃሚ ነው፡፡ መስትዋትን የሚጠላ ሊኖር አይገባም፡፡ እፊቴ ላይ ያለን የሚያስጠላ ጉድፍ እንዳነሳውና እንዲያምርብኝ ስትነግረኝ ለምን እጠላሃለሁ? ስትነግረኝ ግን በትኅትና ይሁን፤ ስትነግረኝ የምትነግረኝ ነገር እውነትና ያልተጋነነም ይሁን፡፡ ስትነግረኝ አንተ ከኔ መብለጥህን ወይም መሻልህን በሚያሳብቅና ሥነ ልቦናዊ የበላይነትን ለማግኘት በመሻት አይሁን፡፡ በጨዋነትና በወንድምነት የሆነ ሁሉ ማር ነው፡፡ በፍቅር የሆነ ሁሉ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅርን ደግሞ የሚያሸንፈው የለም – ሆድም ቢሆን፡፡ ትልቅ የፍቅር ጠላት ሆድ ነውና፡፡

ይልቁንስ የለውጡ ኃይል ከፖለቲካው እልህ አስጨራሽ ተግባራት በተጓዳኝ የሕዝቡን የኢኮኖሚ ሕይወት በማሻሻሉ ረገድ አንዳንድ መሠረታዊ እርምጃዎችን ለመውሰድና ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ፊቱን ወደዚያም ያዙር፡፡ “የነብር ዐይን ወደ ፍየል፣ የፍየል ዐይን ወደ ቅጠል” እንዲሉ እየሆነ ነው፡፡ ሕዝቡ አሁንም በኑሮ ውድነቱ ክፉኛ እየተንገበገበ ነው፡፡ አሻጥረኞችም እንበላቸው ሆዳሞች ንግዱንና አገልግሎቱን በብቸኝነት ተቆጣጥረው አሳራችንን እያበሉን ነው(ልብ አድርጉ! የአንድ ሽህ ብር ደሞዝተኛ በሚኖርባት አዲስ አበባ አንድ ኪሎ ቅቤ በአማካይ 300 ብር፣ አንድ ኪሎ ሥጋ 400 ብር፣ የአንዲት መናኛ ክፍል ኪራይ 2500 ብር … በሆነበት ሁኔታ ሰው እንዴት፣ የትና በምን ይኑር? ከነቤተሰቡ ዛሬን ነገ ለማድረግ ሙስና ውስጥስ እንዴት አይዘፈቅ? ከተቻለው ሀገሩንስ ለመሸጥ እንዴት አይደራደር?)፡፡ በደመወዙ የማይኖርና ሲቻለውና ቢቻለው በስርቆትና በሙስና ኑሮውን ከመግፋት የማይመለስ ግዴለሽና ተስፋ የቆረጠ ዜጋ ተይዞ የትም አይደረስም፡፡ ኑሮው እጅግ ከመሰቀሉ የተነሣ በመያዶችና በጥቂት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ከሚሠሩ ከፍተኛ ደሞዝ ተከፋዮች በስተቀር (ገንዘብ አይጠገብምና እነሱም ለበለጠ ኑሮ መሞሰናቸው እንዳለ ሆኖ) ሚኒስትሮችንና ከፍተኛ ባለሥልጣችን ጨምሮ ማንም ደሞዝተኛ በደሞዙ ብቻ ይህን ወር ከቀጣዩ ወር በምንም ተዓምር አይገጥማትም፡፡ የዐዋጁን በጆሮ እየተናገርኩ ነው፡፡ ሁላችንም ሙሰኞች ነን ማለቱ ከጨዋነት አኳያ ጥሩ አይደለም እንጂ ከሙስና የፀዳ ስብዕና በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን ፈልጎ ለማግኘት የዲዮጋንን ፋኖስ መዋስ ያስፈልጋል፡፡ አፍና ተግባር ለየቅል ናቸው፡፡ በአንደበታችን ንጹሕ እምንጹሓን ለመምሰል ብንሞክርም ኑሯችን የሚናገረው ሌላ ነው፡፡ ወደዚያ ብንገባ አውሎ ያሳድረናልና እንተወው፡፡ እኔ መምህሩ እንኳን ሙሰኛ ነኝ – የሚሰረቅ ቢጠፋ ጊዜ እሰርቃለሁ፡፡ ለምን ይዋሻል? “ለዚህ ደሞዝ፣ ለዚህ ኑሮ…” እየተባለ መሥራት የሚገባንን የጊዜ ርዝማኔ የማንሠራና በወጉ የማንዘጋጅ፣ በቅጡ የማናስተምር መምህራን አለን፡፡ ይሄውላችሁ – የኑሮ መመሰቃቀል ትውልድን በዚህ መልክ እስከመግደል ይደርሳል፡፡ ኑሮው – ተጨባጩ የዛሬው ኑሮ – ይታሰብበት ለማለት ነው ጓዳየን እስከመፈተሽ በድፍረት የተጓዝኩት፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Video: ኢትዮጵያን ዛሬም ያለቅሳሉ

የለውጡ አንዱ ተግዳሮት እንግዲህ ይሄው ነው – ሙስና፡፡ ከቀበሌና ከወረዳ ጀምረህ ከፍተኛንና የልማትም በላቸው የአገልግሎት መሥሪያ ቤቶችን አቆራርጠህ ወደ ላይ ወደ ሚኒስትር መ/ቤቶች ብታመራ የሚታየውና የሚሰማው የሙስና ትስስርና የብላ ተባላ ዘመቻ ያሳብዳል፡፡ “የት ነው ያለነው? ወዴትስ ነው እየሄድን ያለነው? “ በሚል ልታብድም ትችላለህ፡፡ እኔ ወንድማችሁ በዚህና በሌላው ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳይ የተነሣ ደሜ ክፉኛ ፈልቶ ዛሬ ጧት ለምሣሌ 160/110 ሆኖ ነበር፡፡ እውነቴን ነው፡፡ “እንዴት ቆመህ ሄድክ?” ልትሉ ትችላላችሁ፤ የኔም ጥያቄ ነው፤ ግን የማምነው የማይቻለው የለምና ከመቆምም ባለፈ ይህችን ማስታወሻ እየከተብኩ ነው፡፡ እርግጥ ነው ምልክቶቹን ሁሉ በሰውነቴ እያየሁ ነው፡፡ የሀገራችን ጉዳይ ቁጭ ብላችሁ ስታስቡት ከዚህም በላይ ያጦዛችኋል፡፡ የኔ ጉዳይ ቀላል ነው – ችግሩ ያውም ለተወሰነ ጊዜ ለጥቂት የቤተሰብ አባሎቼ ነው፡፡ የኔን የግል ጉዳይ እዚህ መጥቀሴም የሀገራችን ችግር ምን ያህል በየቤቱ ጎልቶ እንደሚታይ በምሣሌ ለማስረዳት እንጂ ከንፈር እንዲመጠጥልኝ ፈልጌ አይደለም፡፡ የሀገራችን ጉዳይ ሁሉም ባለመጻፉ ወይም ተጽፎም ከሆነ ባለመነበቡ እንጂ ብዙ ኪሣራ እያስከተለ ነው፡፡ በየቤቱ ልክ እንደኔ የሚያር የሚተክነውንና በበሽታዎች ከመለከፍ ባለፈ ራሱን የሚያጠፉውን ዜጋ አንድዬ ይቁጠረው፡፡ ይህ የወያኔ የፍዳ ዘመን በቀላሉ የማይሽር ብዙ ጠባሳ አሳርፎብናል፡፡

የተበጣጠሱ የሞራል ክሮቻችን እንዴት ይጠገኑ? የተበጣጠሱት ሃይማኖታዊ ክሮቻችን እንዴት ይጠገኑ? የምንታወቅባቸው የመተዛዘንና የመረዳዳት ወግ ልማዶቻችን እንዴት ወደቦታቸው ይመለሱ? ስርቆትንና ዋልጌነትን የሚጠየፍ ትውልድ እንዴት እናፍራ? ቃለ እግዚአብሔርን ከማነብነብ ባለፈ ወደ ተግባር የሚለውጥና ሕዝቡን በአርአያነት የሚመራ የሃይማኖት አባት እንዴት እናግኝ? በየሙያ ዘርፉ ምሣሌ የሚሆነን አንጋፋ ትውልድ ከወዴት ይምጣልን? ሀገራችን ከወደቀችበት እንዴት ትነሣ? … ይጨንቃል እኮ፡፡ “ያልተነካ ግልግል ያውቃል”፡፡ ምነው እግዜሩ ወዷቸው እንደጠራቸውና በየቤተ ክርስቲያኑ ጓሮ እንደተኙት ባደረገኝ!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ተሰቀለ? (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም)

የሚገርማችሁ ሌላው ነገር የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ከፍቅር ይልቅ ለጠብ የቀረብን ነን፡፡ መቻቻል ጠፍቷል – በትንሹም በትልቁም ቱግ ነው፡፡ አምስት ቃላትን ከመነጋገራችን የሚቀድመን ሸሚዝ መሰብሰብና መቧከስ ነው፡፡ አንደበት የተፈጠረው ግን ተነጋግሮ ለመግባባት ነበር፡፡ ባትግባባም በተለመደው አገላለጽ  ባለመግባባትህ ተስማምተህ ለመለያየት ቋንቋ ወሳኝ መሣሪያ ነው፡፡ የመደማመጥ ችሎታችን፣ የመግባባት ችሎታችን፣ የመተዛዘንና የመረዳዳት ባህላችን አፈር ድሜ ግጦት ሰው መሳይ በሸንጎዎች ሆነናል – ብዙዎቻችን፡፡ ከዚህ የጨለማ አዘቅት እንዴት እንውጣ? ያንዳችን ቁስል ሌላኛችንን እንዲጠዘጥዘን፣ ባንድኛችን ደስታ ሌላኛችን እንድንቦርቅ ምን እናድርግ? በዚህ አሁን ባለንበት ሁኔታ ከተጓዝን እኮ ውኃና ዘይት እንደሆን ዓለም ማለፏ ነው፡፡

እነዶ/ር ዐቢይ ብቻቸውን ምንም አያመጡም፡፡ ዛሬ ብርቱካን ብትሾም፣ ነገ ብርሃኑ ቢሾም፣ ከነገወዲያ አንዷለም ቢሾም፣ የዛሬ ሣምንት ይሄኔ አንዳርጋቸው ቢሾም፣…… ከታች ያለነው ዜጎች የነሱን አመራር ተከትለን ራሳችንን የማናስተካክል ከሆነ ትርፉ ልፋትና ድካም ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ለውጡ በእያንዳንዱ ዜጋ አእምሮ ውስጥ ገብቶ መቃጨል አለበት፡፡ ለውጥ ከታችም ሲሆን እንጂ ከላይ ብቻ የትም አይደርስም፡፡ ከሚያለያዩን ይልቅ የሚያቀራርቡን ምክንያቶች እጅግ ብዙ ናቸውና በነሱ ላይ ብቻ እናተኩር፡፡

ሁላችንም እንዲህ እናድርግ፡፡ በቃኝን እንወቅ፡፡ በዚህ’ች ምድር የምንኖረው ለተወሰነች ቅጽበት ነው፡፡ ያቺን ደግሞ በፍቅርና በስምምነት እንኑራት፡፡ ብዙ ሀብትና ሥልጣን ብናግበሰብስ፣ ለመቶና ሁለት መቶ ዓመታት የሚሆን ሀብትና ንበረት እንዲሁም ገንዘብ ብናካብት ከትዝብት በስተቀር ምንም አይጠቅመንም – ታዛቢ ደግሞ ከሩቅ አይመጣም፤ ከቅርባችን የገዛ ኅሊናችን ሳይቀር እየጠዘጠዘ የሌት ዕንቅልፍና የቀን ዕረፍት ይነሳናል፡፡ “ለልጆቼና ለልጅ ልጆቼ ይሆናል” የሚባለው ፈሊጥም እንደማምለጫና ራስን ማታለያ ምክንያት የሚጠቀስ እንጂ ሚዛን አይደፋም፡፡  የልጅ ልጆች ቢመጡ እንኳን ከነዕድላቸው ይወለዳሉ እንጂ ከኛ የሚጠብቁ ሰነፎች ሊሆኑ አይጠበቅባቸውም፡፡ አሁን ላለው እንጨነቅ፡፡ ገና ለሚወለደው ስናስብ አሁን ያለውን ምስኪን ድሃ በቁሙ መቀመቅ እየከተትነው መሆናችንን እንረዳ፡፡ ፈጣሪንም እናስብ፡፡ እርሱ ይታዘበናል ብቻ ሳይሆን በኛ ስግብግብነት ምክንያት ያዝንብናል፡፡ አንዱ በሚሊዮኖችና በቢሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ በባንክና በቤቱ አቁሮ ይዞ ሌላው ምስኪን ደግሞ ጥርኝ ቆሎ አጥቶ በርሀብ ጠኔ ሲሞት ማየት እንደውነቱ ሰው ሆኖ መፈጠርን ሳይቀር ያስጠላል፡፡ እየሆነ ያለው ደግሞ ይሄው ነው – መስገብገብና ለማይኖሩበት ሕይወት በሌሎች ስቃይ ሀብት ማካበት፡፡ ነገን ስለማየታችን እርግጠኞች ሳንሆን፣ ዛሬን ስለማደራችን ዋስነትና ሳይኖረን ይህን መሰል ኢኮኖሚያዊ ወንጀል በወገናችን ላይ መሥራት ትልቅ በደል ነው፡፡ ካረጀን በኋላ የዕርዳታ ድርጅት ማቋቋም፣ ልብስና ምግብ ገዝቶ ለድሃ ማደል… ዋጋ የለውም፤ አሁን ነው ጊዜው! አሁን ነው ተያይቶና ተሳስቦ ለማደግ መጣር፡፡ በመቶ ብር የገዛኸውን ዕቃ እስኪወደድ ጠብቀህ ሁለትና ሦስት ሽህ ብር ብትሸጥና በቶሎ ብትከብር – እውነቱን ተረዳው – ደኸየህ እንጂ አልከበርክም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን አንብብ፡፡ በሸፋፋ ሚዛን የሚነግዱና ዕቃን እስኪወደድላቸው የሚያስቀምጡ ነጋዴዎችና ሻጮች ትልቅ የኃጢኣት ዕዳ አለባቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰላማዊ ትግል፤ የኤርምያስና የልደቱ የወቅቱ ማጭበርበሪያ

ቅጥር ሠራተኞች በተቻለን መጠን በደሞዛችን ብቻ ለመኖር እንሞክር፡፡ በጠማማና ኢ-ህጋዊ መንገድ ከሚገኝ የጎን ገቢ እንታቀብ፡፡ በተለይ በሰዎች መጎዳት የሚገኝ ገንዘብ ባፍንጫችን ይውጣ፡፡ በሥራችን ሰበብ ጉቦ የምንቀበል ሰዎች ከዚህ አእምሮን ከሚያላሽቅና ስብዕናን ከሚያጎድፍ አጸያፊ ተግባር በአፋጣኝ እንውጣ፡፡ ሙስናን እንጠየፈው፡፡ ለተወሰነ ጊዜ እንቸገር ይሆናል፡፡ ግን እንችላለን – ደግሞም ጎመን በጤና፡፡ ኑሯችንን በገቢያችን መጠን አስተካክለን መኖር ብንጀምር ችግራችን እስክንለምደው ብቻ ነው፡፡ ሁሉም እንዲህ እየሆነ ሲሄድ ደግሞ ብዙ ርቀት አንቸገርም፡፡ ሁሉም ሲቸገር መፍትሔው ቅርብ ነው፤ ችግሩ ወልጋዳ አካሄድ ነው፡፡

ነጋዴው ማሰብ ይጀምር፡፡ መስዋዕትነትም ይክፈል፡፡ የመኪና ፋሽን ውድድሩን፣ የሽርሽር ቦታዎች መረጣ ውድድሩን፣ የልብስና የጫማ ፋሽን ውድድሩን፣ የመኖሪያ ቤት ግንባታና የቤት ውስጥ ዕቃ ግዥ ውድድሩን ቆም ብሎ ይመርምር –  እነዚህ ችግሮች ይበልጡን ካለመማርና አንጎልን በአግባቡ ካለመጠቀም የሚመነጩ ናቸው (የሀገራችን ነጋዴዎች ደግሞ ባለመማር አይታሙም!)፡፡ ለማንኛውም ነጋዴው ማኅበረሰብ አላግባብ በሚያግበሰብሰው ትርፍ፣ አላግባብ ዝቅተኛ ደሞዝ እየከፈለ በሚመዘብረው የሰው ደምና ላብ ምክንያት እንደዚያ ያለ የዘቀጠ የብልጭልጭ ዓለም ውስጥ መግባቱን ያስታውስና በርሀብ ለሚሰቃየው ወገኑ ማሰብ ይጀምር፡፡ ሀገር የጋራ ናት፡፡ ዜግነት እኩልና የጋራ ነው፡፡ እናም አንዱ በርሀብ እየሞተ ሌላው በቁንጣን እየተሰቃዬ መኖር ማብቃት አለበት፡፡ ከተማችንን ስናይ የአንድ ሀገር ዜጎች መሆናችንን ማመን ይከብዳል፡፡ ሀገርን ወራሪ ሲያጠቃት ግን ሄዶ የሚሞተው ድሃው ነው፡፡ ይገርማል፡፡ ባጭሩ ሰው እንሁን ነው መልእክቴ፡፡ ትንሽ ማሰብ ነው፤ ጥቂት ጊዜ ወስዶ ማሰላሰል፡፡ ከሁሉም ደግሞ የሞትን መኖር አለመርሳት፡፡

መንግሥትም እስከታች እየወረደ የዜጎችን ኑሮ ይመልከት፡፡ ዜጎችን ይጠይቅ፤ ነጋዴዎችንና አገልግሎት ሰጪዎችን ይመርምር፡፡ የባለሥልጣናትን ኑሮ እስከጓዳቸው ድረስ በመሄድ ይፈትሽ፡፡ ሁላችንም እንደተወርዋሪ ኮከብ ለተወሰነ ቅጽበት ታይተን ለምንጠፋባት ለዚህች አጭር ዕድሜ ስንል እጅግ ብዙ የሚያስተዛዝቡ ሁኔታዎች ውስጥ ገብተን እንታያለንና ብዙም ሳይረፍድብን ተያይተን እንተራረም፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ሳንሞክር ለውጥ ለውጥ ብንል ጉንጭን ማልፋት ነው፡፡ ሰብኣዊነት የሚሰማቸው እንደማህተመ ጋንዲና እንደማዘር ቴሬሳ ያሉ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ በፖለቲካው ረገድም እንደማንዴላና እንደ ጁሊየስ ኒሬሬ ያሉ ፣ እንደ ፓራጉዩ መሪ እንደ ጆሴ ሙጂካ ያሉ ከራሳቸው ብልጽናና ክብረት ይልቅ ለሀገራቸው የሚያስቡ ዜጎች ያስፈልጉናል፡፡ የተቸገርነው ራስ ወዳድና ሥልጣን ወዳድ አሰለጦች በአቋራጭ ቤተ መንግሥት እየገቡ የራሳቸውን ሀብትና ሥልጣን ሲያደላድሉ እኛ መረሳታችን ነው፡፡ አንዳንዱ ገልቱ በልቶ ለማይጨርሰው አምስት ቢሊዮን ዶላር አራት ኪሎን ይዞ ሲሟሟት አጅሬ ሞት ላፍ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ እንኳን መማር አንችልም፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮ አንዳንዴ ምናልባትም ብዙውን ጊዜ ይገርማል፡፡ ለማንኛውም እስኪ ልብ ይስጠን፡፡

yinegal3@gmail.com

Share