“ሁለቱም ባዶዎች ነበሩ!”/ለዘመኑ የሀገራችን “ቦለቲከኞች”/ – ከፊሊጶስ (ግጥም)

/

እ’ስራና  ቅል ……..

አፈጣጠራቸው፣  ቢሆንም  ለየቅል፤

እንደ  አቅማቸው፣  ሠርተው

በሀሳብ – ተግባር፣ ተግባብተው፤

ሰላም አግኝተው፣ አንድነት

ይኖሩ ነበር፣ በአንድ ቤት።

 

በፍቅራቸው፣ የሚቀናው

ዱባ ግን፣ ጉረቤታቸው፤

ያሴር ነበር ሴራ፣ የሚያሥር

ይሸርብ ነበር ነገር፣ የሚያደናግር፤

ያጠምድ ነበር፣ ወጥመድ

ባረፉበት ቤት፣ ሳይቀር በመንገድ።

 

እ’ሰራን ሲያገኘው፣ ብሎ  ጎንበስ – ቀና

የሰላምታ አይነት፣ ያዥጎደጉድና፤

በማር የተቀባ፣ የመርዝ ቃላት

ይነግረው ነበረ፣ መስሎ ተቆርቅሪ፣ ለሱ ያዘነለት።

 

ቅልንም ሲያገኘው ወይም ቤቱ ሄዶ

ከአስረደው በኋላ፣ እንደሚፈልግው በፍቅሩ ተገዶ፤

ምክር ነው እያለ፣ ነገር ይነግረዋል

በማያውቀው ጉዳይ፣ ደሙን ያፈለዋል።

 

ከለ’ታት አንድ ቀን፣ ሥራ በፈቱበት

በነገር ተይዘው፣ ”በተሰለቡበት”፤

እ’ስራ ተክዞ፣ ወደ ቤት ሲሄድ

ቅልም በበኩሉ፣ ሲያስብ በምንገድ፤

ዓይን – ለዓይን ተጋጩ፣ እጅግ ተፋጠጡ

በሰላምታ ፋንታ፣ ንትርክ መረጡ።

 

ቅል ኮራ ብሎ፣ ምላሱና ሳለና

ዱባ ከነገረው፣ ብዙ አስታወሰና፤

”እኔ ከ’ንተ አላንስም፣ እንዲያው ባልበልጥህ ”

በማለት ጀመረ፣ “አንተ እ’ስራ ሆድ ነህ!”።

“ለሰው ልጅ አገልጋይ፣ ወሃ ለመያዝ፣ ተመራጭ እኔ ነኝ

እንደ አስፈለጋቸው፣ የሚሽከረክሩኝ።”

”እኔ ቅል ብቻ ነኝ፣ ቶሎ ውሃ በመሙላት የሚመርጠኝ ሰው

ይዘውኝ ቢዞሩ፣ የማልከብዳቸው፣ የምመቻቸው።”

 

ነገሩ ተካሮ፣ ዱላ መረጡና

ይጣለዙ ጀመር፣ በሰፊው ጎዳና።

ገላጋይ መስለው፣ የቀረቡት ሁሉ

ዘወር ብለው ሄዱ፣ ዱላ እያቀበሉ።

እነሱም ቀጠሉ፣ ቀጠሉ….  ቀጠሉ

እስቲ  እናስብበት፣ ለነገም አላሉ

ጎዳናውን አልፈው፣ ሜዳውንም  ሞሉ።

የመደባደቡ፣ ኃይል ቢያጥራቸው

ተያይዘው ወደቁ፣ ‘ርስ – በ’ርሳቸው

ብትንትንም አሉ፣ መሬት ብትነካቸው።

 

 

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  አሁን ተረጋግጧል። ባንዳው የኦህዴድ ብልፅግና “የኢትዮጵያ መንግሥት” አይደለም። ሊሆንም አይችልም

የእ’ስራና ቅል፣ ዱባ ጉረቤት

ጠቡን ሲከታተል፣ ቁጭ ብሎ በ’ርቀት፤

”ከቶ ማን ያሸንፍ፣ ፈሪ ማን ይሆን”

እያለ ሲደሰት፣ በማየት ፍልሚያውን፤

ወድቀው፣ ተበታትነው፣ ተፈረካክሰው

ሜዳውን ሞልተውት፣ ሲያስታውላቸው

”ለካስ ሁለቱም ባዶዎች ነበሩ!” በማለት ሳቀና

ቤታቸውን ሊወርስ፣ ሄደ እየተዝናና።

—–//——-

ፊልጶስ / 2006  / E-mail: philiposmw@gmail.com

*”ለካስ ሁለቱም ባዶዎች ነበሩ!” የሚለውን የወሰድኩት ከኮንፊሽዬስ አባባል ነው::

 

 

 

2 Comments

  1. This poem applies for those ethnic based “politicians” who always cry about past grievances forgetting the present and imminent danger, who grew up listening only the negative aspects of our history like “Menilik the cruel king” etc.
    Weyane laughs sitting aside when they stll cry on Menelik statue instead of coming to terms with other oppositions, forgetting the abuse on their brothers and sisters by Weyanes.
    Also apllies equally to other ethnic based groups who only think about their means of climbing to power at the cost of other opposition forces. They are busy denouncing other means of struggles instead of finding their own way to topple this brutal govt.
    Wey nedo!

  2. ይህ ግጥም በጣም ድንቅ ግጥም ነው፣የወቅቱን የኛን ሁኔታ በምሳሌ ይናገራል።

Comments are closed.

Share