የለውጥ-ሀይሉ የጅብ እራት እንዳይሆን!!! – አማኑኤል ታደሰ (ከድሬዳዋ)

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ አቶ ዘይኑ ጀማል ለVOA ጋዜጠኛዋ ፅዮን ታደሰ በገለፁላት አሀዝ መሠረት ወደ 240 የሚጠጉ ቀይ ቦኔት ያደረጉ የመንግስት ወታደሮች በተለምዶ አጋዚ ተብለው የሚጠሩት ደመ-ወዝ እና ሌሎች የጥቅማጥቅም ጥያቄዎችን ለዶ/ር አብይ ለማቅረብ በሚል መነሻ ወደ ብሄራዊ ቤተ-መንግስት መሣሪያ ተሸክመው አምርተዋል፡፡

በመርህ ደረጃ እንደእነዚህ አይነት የአስተዳደር ነክ ጥያቄዎች መቅረብም ካለባቸውም የሚቀርቡት የህግ አግባብን ተከትለው በተዋረድ ስልጣን ላለው አካል ነው፡፡ ከመርህ እና ከወታደራዊ ዲሲፕሊን ባፈነገጠ መልኩ ተሻግረህ ጥያቄን ማቅረብ ያውም ጠመንጃን የሚያህል ትጥቅ ተይዞ በቡድን (mass based) የቤተ መንግስት ደጅ መጥናት በየትኛውም የህግ መመዘኛ ልክ አይደለም፡፡ በእርግጥ ጥያቄያቸው ሊሰማ እንደሚገባ እና መሠረታዊ መሆኑ ላይ ህፀፅ አይታየኝም፡፡ ነገር ግን ጥያቄዎቻቸውን ለማቅረብ የሄዱበት መንገድ ስህተት የተሞላበት ነበረ ማለት ይቻላል፡፡ በህግ አግባብ እና በተለምዶአዊ የቅሬታ አቀራረብ ሂደት ከመዘነው የደመወዝና ተያያዥ ጥያቆዎቻቸውን ማቅረብ የነበረባቸው በቀጥታ ለዶ/ር አብይ አህመድ ሳይሆን በተቋም ደረጃ ለሚሰሩበት መስሪያ ቤት ለሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ነው፡፡ ጥያቄዎቹ እንደሚታወቀው አስተዳደራዊ ነክ ጉዳዮች በመሆናቸው በአግባቡ መቅረብ ያለበት ለሚኒስቴር መ/ቤቱ የሰው ሀይል አስተዳደር ዲፓርትመንት ነው፡፡ ከፍ ሲልም ለኢታማዦር ሹሙ ጄኔራል ሰዓረ እና ለሚኒስቴር መ/ቤቱ የበላይ ጠባቂ ለሆኑት አቶ ሞቱማ መቃሳ ነው፡፡ ምናልባት በእነዚህ የማይፈታ ከሆነ ለጠ/ሚኒስቲሩ በፅ/ቤታቸው በኩል ጥያቄዎቻቸው እንዲደርሳቸው ተደርጎ ነው መፈታት ያለበት እንጂ በመንጋ ጠመንጃ አንግተው ደጀ ቤተ-መንግስት በመጥናት መሆን አልነበረበትም፡፡ ወታደር ነገሮችን ሲከውንና ሲጠይቅ የሀገርን የህዝብና የጠ/ሚኒስቴሩን ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥል አኳኃን መሆን የለበት፡፡ የጥያቄያቸው ተገቢነት ባያጠያይቅም ጥያቄቸውን ያቀረቡበት መንገድ ግን ይህንን ተፈጥሮአዊ ሀላፊነትና ግዴታ በዘነጋ መልኩ ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የህዝቡንና የመሪውን ደህነት አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ የተከወነ እኩይ ተግባር ተደርጎ መወሰድ ያለበት ይመስለኛል፡፡

ከዚህ ሁናቴ (Incident) ጋር ተያይዞ መነሳት ያለባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች አሉ እነሱም፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የመሠረታዊ ነፃነት ቀበኞች! (በሰሎሞን ተሰማ ጂ)

➊ የለውጥ ሀይሉ ማለትም የዶ/ር አብይ መንግስት ከዚህ ህጋዊ ጥያቄ ጀርባ ያለውን መጥፎ እሳቤ (bad-intention) ወይንም ድብቅ አጀንዳ (backdoor deal) በግልፅ ማስረጃ በማስደገፍ መመርመር እና መተንተን ያለበት ይመስለኛል፡፡ በህጋዊ ጥያቄ ሽፋን ሌላ በፀረ ለውጥ አቀንቃኞች መዳፍ ስር የወደቀ አጀንዳ ይዘው ነው የመጡት ወይንስ አይደለም የሚለውን ሁናቴ በጥንቃቄ ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ እነዚህ ሰዎች ጥያቄዎቻቸው በሚፈልጉት መንገድ አልተስተናገደም እንበልና የሚወስዱት ዕርምጃስ ምን ሊሆን ይችል ነበረ የሚለውን ማሰብም በጣም ወሳኝ ይሆናል፡፡ ምክኒያቱም መሳሪያን ያህል ተሸክሞ ቤተ መንግስት ድረስ የመጣ አካል የሀይል አማራጭን እንደመፍትሄ ላይጠቀም ይችላል ብሎ ማሰብ የዋነት ይሆናል፡፡

➋ በተጨማሪም ልናናግረው የምንፈልገውና መልሳችንን ሊመልስልን የሚጭለው ዶ/ር አብይ ብቻ ነው የሚለውን የወታደሮቹን አመክንዮ ስትመለከት በሌሎች ጥርጣሬዎች እንድትሞላ የሚያደርግ Scenario ያለው ይመስለኛል፡፡  በእርግጥ በቅን ልቦና (good faith) ካየነው በዶክተር አብይ አህመድ ላይ አመኔታ እንዳላቸው ለመረዳት የሚያስችልህ ነገር እንዳለ ትገነዘባለህ፡፡ በሌላኛው ገፃቸው ስታየው ደግሞ  በግልፅ ቋንቋ ተፈላጊው ሰው እሳቸው መሆናቸውን ስትመለከት እና ጥያቄያቸው በወቅቱ ባይመለስ ብለን እናስብና ሀይልን አማራጭ ከማድረግ ይቆጠባሉ ወይ የሚለውን ጥያቄ ብንጠይቅ እንደኔ አይመስለኝም፡፡ ምክኒያቱም ትጥቅ ይዘው የሄዱት እንደ ማስፈራሪያ አልያም የሀይል አማራጭን እንደ መደራደሪያ ይዘው የመጡ ይመስለኛል አስፍተን ካየነውም ዶ/ሩን የመፈንቅለ መንግስት ሴራ target ሊያደርጓቸው ያሰቡ የሚመስል ነገር ይታይበታል፡፡ እንደሚታወቀው በተለምዶ በቤተ-መንግስት የፕሮቶኮል አሰራር ወታደር ወደ ቤተ-መንግስት ሊገባ የሚችለው ትጥቅ ተፈቶ ነው፡፡ ታጥቀው የሚገቡትም የቤተ-መንግስት ጠባቂዎች እንጂ ሌሎች አይመስለኝም፡፡ እንኳን እነሱ የመንግስት ባለስልጣናት እንኳ ለስብሰባም ሆነ ለሌሎች ጉዳዮች ሲገቡ የግል መሳሪያቸውን አስቀምጠው ነው የሚገቡት፡፡ ስለሆነም ከዚህ አሰራር ጋር የሚጣረስ ነው፡፡ ሌላው ለስምሪት እና ለሌሎች ግዳጆች ሲወጡ መሳሪያን በተመለከተ የሚቆጣጠራቸው የበላይ አካል ያላቸው ይመስለኛል፡፡ ምክኒያቱም አለ ስምሪት መምሪያው ሀላፊ መሳሪያ ይዘው ለግዳጅ የሚወጡበት አግባብ ያለ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ደረጃ የወታደራዊ ክፍሉ የስምሪት መምሪያ ሀላፊዎች ጋር እና ግዳጅ የሚሰጡ አካላት ጋር ቸልተኝነት ያለ ይመስላል፡፡ ከዚህ የወታደራዊ የትዕዛዝ ሰንሰለት ውስጥ እንዴት ሊወጡ ቻሉ የሚለውንም ጥያቄ መንግስት አብሮ ማየት ያለበት ይመስለኛል፡፡

  • ይህ ድርጊት በነገራቸን ላይ የፀረ-ለውጥ ሀይሉን የማገገሚያ ጊዜ መግዛት የሚያስችለውን እድል የሚያገኝበት አውድ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ እንዲሁም የፀረ-ለውጥ ሀይሉን የመኖር ህልውናንም በተወሰነ ደረጃ ሊያሰፋ የሚችልበት ዕድልን ይፈጥራል፡፡ እንደዚህ አይነት ያልተመዱ incidents ማየት ከጀመርን የፀረ ለውጥ ሀይሉ እነዚህን ልዩነቶች ተጠቅሞ የወታደራዊውን ክፍሉን ተዓማኒነት ለመቀነስ በሚያስቸል መልኩ ሊተጉ ይችላሉ፡፡ በእነዚህ ህጋዊ ጥያቄዎችም ሽፋንም ወታደራዊ ክፍሉን የማናጋት ስራ ሊሰሩ ስለሚችሉ መንግስት ትኩረት ሊያደርግባቸው ይገባል፡፡ በተጨማሪም ከፀረ-ለውጥ ሀይሉ ጋር ግንኙነት ይኖረው ይሁን አይሁን የሚሉትን ሁኔታዎች መንግስት መመርመር ያለበት ይመስለኛል፡፡
ተጨማሪ ያንብቡ:  ተደብቃ ታረግዛለች፣ ሰው ሰብስባ ትወልዳለች - አስቻለው ከበደ አበበ

➌ የለውጥ ሀይሉ አሁንም ድረስ የጸጥታ እና የደህነት መዋቅሩን በተገቢው መንገድ ማለትም የዜጎችን ደህነትና ሰላም ብሎም የለውጥ ሀይሉን ህልውና ሊያስጠብቅ በሚችል መልኩ በእጁ ይዟል ወይንስ አልያዘም የሚለውን የህብረተሰቡን ጥርጣሬ ማፅዳት ያለበት ይመስለኛል፡፡

➍ ሌላው ወታደሩ በዚህ መንገድ የደሞዝ ጥያቄዎችን ማቅረባቸው እና የተወሰነ inconvenience መፍጠር መቻላቸው በእራሱ በሀገሪቷ ውስጥ ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች በእንደዚህ አይነት መንገድ ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ በር የሚከፍት ይሆናል፡፡ ስለሆነም ይህም ለሌሎች የህግ ጥሰቶች በር እንደይከፍት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ ሌሎች ሀገራት በፕሬዝዳንት አልያም በጠ/ሚኒስቴር ቢሮዎች አካባቢ በተመጠነ መልኩ ጥያቄዎች በማህበረሰብ ሲቀርቡ በተለያየ አለማት ለመታዘብ ችለናል፡፡ ነገር ግን እንዲህ መሳሪያ ተሸክሞ ቤተ-መንግስት ድረስ በmass ተኪዶ ጥያቄውን ያቀረበ የህብረተሰብ አካል በእኔ የዘመን ትውልድ ታሪክ አላየሁም፡፡ ነገር ግን የዚያኛው ትውልድ በደሞዝ ጭማሪ ሽፋን አብዮት እንዳፋፋመበት ንጉሱን እንደፈነቀለበት አንብብያለው፡፡ ለፈነቀለው ዓላማ ተገዢ ሆኖ ተጠቃሚ የሆነበትን መልካም የታሪክ ማህደር ማግኘት ግን ይከብዳል፡፡ ይልቅ የማይሆን ስርዓት ገንብተው ብዙዎቹን ለስደት ብዙሀኑን ለሞት ዳርጓል፡፡

  • በለውጡ ሂደት ውስጥ መንገራገጮች የሚጠበቁ ቢሆንም ለእንደዚህ አይነት ሁነቶችን ግን የለውጥ ሀይሉ በጥንቃቄ እና በአንክሮ መመልከት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ጥያቄ ጀርባ ያለውንም hidden agenda መመርመር ያለበት ይመስለኛል እንደው ዝም ተብሎ በ10 Pushup ቀጥተህ የምታለፍው silly incident አይደለም፡፡ በተጠና መንገድ ማስታመም ባይቻል ኖሮ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ማሰብ ቀላል ነው፡፡

 

ከተጠያቂነት ጋር በተያያዘ በነገራችን ላይ በ1996 ዓ.ም በተሻሻለው አዲሱ የኢትዮጵያ የወንጀል ህግ አንቀፅ 299 ንዑስ-አንቀፅ አንድ ወታደራዊ አመፅን በተመለከተ የሚከተለውን የህግ ድንጋጌ ያስቀምጣ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:    " በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው... " መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ 

ማንኛውም የመከላከያ ሠራዊት አባል ከሌሎች ወታደሮች ጋር በመተባበር ህጋዊ ባልሆነ ስብሰባ በመካፈል ወይም በማናቸውም ሌላ ሁኔታ በበላይ አለቃ ወይም ወታደራዊ ባለስልጣን ላይ ወይም የበላይ አለቃን ወይም ወታደራዊ ባለስልጣንን በመቃወም በተፈፀመ ያለመታዘዝ የተቃውሞ የዛቻ የሀይል ድርጊት ወይም የእጅ እልፊት እንቅስቃሴ ውስጥ ተካፋይ እንደሆነ ከአስራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡” 

የትላንትናው በቤተ-መንግስት አካባቢ የታየው ድርጊት ወታደራዊ አመፅ የሚመስል አዝማሚያዎች ነበሩት፡፡ በዚህ የህግ አግባብ መሰረት በተጨባጭ ተጠያቂ ሊያደርግ የሚችል ማስረጃ ከተገኘ ከዚህ ጥያቄ ጀርባ ያሉ Bad-Apples በወታደራዊ ፍርድ-ቤት ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል፡፡

ዜጎች ዋጋ የከፈሉበትን ለውጥ የጅብ እራት ማድረግ አያስፈልግም፡፡ የፀጥታ እና የደህነት መዋቅሩ መስተካከል ካለበትም መንግስት ጊዜ ሳይሰጥ በአፋጣኝ ማሻሻያዎችን ማድረግ አለበት፡፡ የፀጥታ አካላትን የመልካም አስተዳደር እና ሌሎች ጥያቄዎችን በአግባቡ በመመለስ መንግስት እና ህዝብ እምነት የሚጥልበት የፀጥታ መዋቅር ሊገነባ ይገባል፡፡ አለበለዛ ሁሉም ጥያቄ ባለው ቁጥር እየተነሳ ጠመንጃ አንግቶ ቤተ-መኅግስት ደጅ የሚጠና ከሆነ የለውጥ ሀይሉ፤ ህዝብ እና ብሎም ሀገሪቷ አደጋ ላይ የሚወድቁ ይሆናል፡፡

1 Comment

  1. This kind of fooling oneself political drama is an insult to the peoples’ intelligence . It is good for yourself and especially for the country to tell the truth and deal with it accordingly !

Comments are closed.

Share