Health: የአልኮል መጠጦችና እፆችና ወሲብ [Let’s Talk About Sex…& Alcohol]

የዘ-ሐበሻ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ እንዳጠናቀረው

በአንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ‹‹የወሲብ ፍላጎትን ያነሳሳሉ›› በሚል እምነት ተዘውትረው ጥቅም ላይ የሚውሉ አልኮል መጠጦችና ሌሎች ሱስ አስያዥ እፆች ሰዎች ከወሲብ ማግኘት የሚገባቸውን እርካታ እንዲያጡ የሚያደርጓቸው ከመሆኑም በላይ በአጠቃላይ የጤና ሁኔታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያስከትሉ በቅርቡ ይፋ የሆኑ ጥናቶችና ባለሙያዎች ገለፁ፡፡
ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 20 በሆኑ 7,441 ሰዎች ላይ በአሜሪካ በቅርቡ የተደረገው ጥናት ይፋ እንዳደረገው ከሆነ ከወሲብ በፊትም ሆነ በኋላ አልኮልን ጨምሮ ሌሎች አቅልን በቀላሉ ሊያስቱ የሚችሉ እፆችን መጠቀም ከስንፈተ ወሲብ ባሻገር ጥንቃቄ ከጎደለው የወሲብ ህይወት ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ የአባላዘር በሽታዎች እንደሚያጋልጥ ነው የጠቆመው፡፡
እንደ ጥናቱ ዘገባ በአሜሪካ ከ12 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች ተጋላጭ እንደሆነ የሚገመት ሲሆን፤ በቀዳሚ ምክንያትነት የተቀመጡት ደግሞ የአልኮል መጠጦችና በቅፅበት አቅልን የሚያስቱ እፆች ናቸው፡፡ በተለምዶ የወሲብ ፍላጎትን በማነሳሳትም ሆነ የተሳካ ወሲብን ለመፈፀም አልኮል መጠጦችን አብዝቶ መጠቀም ተመራጭ መፍትሄ አድርጎ የማሰብ ሁኔታ በአንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በስፋት የሚስተዋል ቢሆንም ከወሲብ ሊገኝ በሚችለው ደስታም ሆነ እርካታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ጥናቱን መሰረት አድርገው የወጡ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ በተለይም ከመጠን በላይ አልኮል ተጠቅመው ወሲብ ከሚፈፅሙ ወንዶች 54 በመቶ የሚሆኑት የመጨረሻው የእርካታ ደረጃ ለመድረስ ወይም ፈሳሽ ለማውጣት የሚቸገሩ ከመሆኑም በላይ ለመሀንነት የመጋለጥ ዕድላቸውም ሰፊ እንደሆነ ጥናቱ አብራርቷል፡፡
አልኮልና ጫት ከጤናማ የወሲብ ህይወት ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን እንደሆነ ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ለመቃኘት በመፈለግ የዘ-ሃበሻ ዘጋቢ በአዲስ አበባ ከተማ በመዘዋወር የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችንና የዘርፉን ባለሞያዎች አነጋግሯል፡፡ በቅድሚያ ከግለሰቦች ያገኘነውን አስተያየት በማስቀደም የሙያተኞችን ትንታኔ ሰፋ ባለ መልኩ ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡

የ45 ዓመቱ አቶ አለሙ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪና ባለትዳር ናቸው፡፡ ቢያንስ በሳምንት ሶስት ቀን የአልኮል መጠጦችን የመጠቀም ልምድ ያላቸው መሆኑን የሚናገሩት እኚህ ግለሰብ ከትዳር አጋራቸው ጋር የወሲብ ግንኙነት ሲፈፅሙ ‹‹የመጨረሻው እርካታ ላይ ለመድረስ ብዙ ጊዜ እቸገራለሁ›› ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪ የሆነው ወጣት ቢኒያም በጥናት በሚል ሰበብ አልፎ አልፎ ጫት የሚቅም ቢሆንም፤ ከፍቅረኛው ጋር በሚፈፅመው የወሲብ ህይወት ውስጥ ይሄ ነው ተብሎ የሚገለፅ ጥቅምም ይሁን ጉዳት አለው ብሎ እንደማያምን ተናግሯል፡፡
ከላይ በስም ከገለፅናቸው በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች አስተያየት ከሰጡት መካከል ይበልጡን ቁጥር ያላቸው ‹‹ወሲብ የመፈፀም አቅማቸውን ከፍ ለማድረግ›› በሚል ሰበብ አልኮልም ሆነ ጫትና ሌሎች ሱስ አስያዥ እፆችን የመጠቀም ልምድ እንዳላቸው አልደበቁም፡፡
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ከላይ በቀረበው መልክ አልኮል እና ጫት ከወሲብ ህይወት ጋር ያላቸውን ትስስር አስመልክተው ‹‹በጎ ውጤት አለው›› ቢሉም ጥናቶችም ሆኑ ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች በግለሰቦቹ አስተያየት እንደማይስማሙ በመግለፅ ሙያዊ ትንታኔያቸውን ሰጥተዋል፡፡
አንድ የስነ ልቦና ባለሙያ በሰጡት ቃለ ምልልስ አልኮልና ሌሎች ሱስ አስያዥ ነገሮች ከጤናማ የወሲብ ህይወት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከመነጋገራችን አስቀድሞ በስንፈተ ወሲብ ችግሮች ምንነት፣ በአይነታቸው፣ በመንስኤቸውና በመፍትሄዎቻቸው ዙሪያ አሉ በሚባሉ ሳይንሳዊ እውነታዎች ላይ መግባባት ከተቻለ ወሲብ ከአልኮልና ከጫት ጋር ያለውን ግንኙነት በቀላሉ መገንዘብ አይገድም፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት የስንፈተ ወሲብ ችግር በውስጡ በርካታ ማህበራዊ ጉዳዮችን የያዘ በመሆኑ በቀላሉ እንዲህ ነው ብሎ ለመተርጎም አስቸጋሪ ነው፡፡ ሀሳባቸውን በምሳሌ ሲያብራሩ በአብዛኛው ባህላዊ በሚባለው ማህበረሰብ ውስጥ ወንዱም ሆነ ሴቷ ለወሲብ ዝግጁ ሆነው የወንዱ ብልት ወደ ሴቷ ከገባበት ጀምሮ እርካታ ላይ እስከሚደርስበት ድረስ ያለው ጊዜ ከአንድ ደቂቃ የሚበልጥ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ሰሜን አሜሪካ ሲኬድ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ወሲብ የመፈፀም ሂደት ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከ5 እስከ 10 ደቂቃ እንደሚፈጅ ሲያስረዱ፤ በአንፃሩ በኤስያ አገሮች ከ20 እስከ 30 ደቂቃ እንደሚወስድ ነው የሚናገሩት፡፡ ከዚህ በመነሳት ወሲብን ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ መጨረስ በራሱ ችግር እንዳልሆነ ባለሙያው አብራርተዋል፡፡ የስነ ልቦና ባለሙያው ‹‹የስንፈተ ወሲብ ችግሮች በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ተፈርጀው የሚታዩ ናቸው›› ካሉ በኋላ የስንፈተ ወሲብ ችግር አይነቶችን እንደሚከተለው ዘርዝረዋል፡፡
የፍላጎት መዛባት (ማጣት) አንደኛው አይነት የስንፈተ ወሲብ ችግር ሲሆን ይሄም ስለ ወሲብ የማሰብ፣ የመመኘትና የመፈለግ ስሜት ግለሰቡ ላይ መጥፋት ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለ ችግር ያለባቸው ሰዎች የቱንም ያህል በአካልና በስነ ልቦና ወሲብ ለመፈፀም ዝግጁ ቢሆኑም ወሲብን ለመፈፀምም ሆነ ለመደሰት የሚያስችል ፍላጎት ግን የላቸውም፡፡ የችግሩ መንስኤ በአብዛኛው ህብረተሰብ ለወሲብ የሚሰጠው የተጋነነ ግምት በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት በግለሰቦች ላይ የስነ ልቦናዊ ውጥረትን ይፈጥራል፡፡ በዚህም ሳቢያ የወሲብ ፍላጎት ስሜታቸውን ይጣሉ፡፡ ሌላኛው የስንፈተ ወሲብ ችግር አይነት መነቃቃትን ማጣት ነው፡፡ የፍላጎትና የስሜት ችግር ባይኖርም በአካልም ሆነ በስነ ልቦና ዝግጁ ለመሆን ግን አይችሉም ነው፡፡
ለወሲብ አካላዊና ስነ ልቦናዊ መነቃቃትን ማጣት ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከል መጠጥ አዘውትሮ መጠቀም፣ በራስ መተማመን ማጣትና በጥንዶች መካከል ግጭት መፈጠር በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ በሶስተኛነት የሚታየው የስንፈተ ወሲብ ችግር የእርካታ ጣሪያ ላይ ለመድረስ መቸገር እንደሆነ የሚናገሩት ባለሙያው ይህ አይነቱ ችግር በአብዛኛው ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ አዘውትሮ የሚከሰት ሲሆን የችግሩ መንስኤም ሴቶች ሳይረኩ (ሳይደሰቱ) ወንዶች ፈጥነው መጨረሻቸው፣ ስለ ወሲብ አሉታዊ አስተሳሰብ መኖር፣ ስለወሲባዊ ጉዳዮች በግልፅነት አለመነጋገርና ስለ ወሲብ ሲወራም ሆነ ሲፈፀም በተለያዩ ምክንያቶች የጥፋተኝነት ስሜት የሚንፀባረቅ ከሆነ ከወሲብ ደስታን ማግኘትም ሆነ የመጨረሻው የእርካታ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚቻል አይሆንም፡፡
በአብዛኛው ከወንዶች ጋር ተያይዞ የሚነሳው የስንፈተ ወሲብ ችግር ወሲብ በሚፈፀም ወቅት የመጨረሻው እርካታ ላይ ሲደርስ ፈሳሹ ወደ ሴቷ ብልት መግባት ሲገባው ወደኋላ የመመለስ ችግር ያጋጥማል፡፡ በዚህም ሳቢያ ወንዶች የእርካታ ጣሪያ ላይ ላይደርሱ ይችላሉ፡፡ ሌላውና አራተኛው የስንፈተ ወሲብ ችግር ወንዶች አስቀድሞው ከገመቱት እጅግ በአነሰ ጊዜ ወይም ከሴቶች ፈጥነው የዘር ፍሬን የመርጨት ችግር ነው፡፡ ለአቅመ አዳም ከደረሱ ወንዶች 28.5 በመቶ ፈጥኖ የመርካት ችግር እንዳለባቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ይሁን እንጂ በወንዱ ወይንም በጥንዶች መካከል ያለመርካትና የጥፋተኝነት ስሜትን ጨምሮ ያልተፈለገ ውጥረትን፣ ጭንቀትንና ፍርሃትን አልያም ደስታን ያለማግኘትን ችግር እስካልፈጠረ ድረስ ቀድሞ መጨረስ በራሱ እንደስንፈተ ወሲብ ችግር ላይቆጠር ይችላል፡፡
ከስንፈተ ወሲብ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ችግር ወሲብ በሚፈፀምበት ወቅት የህመም ስሜት መኖር ነው፡፡ ህመሙ ከቀላል እስከ ከባድ የሚደርስ ሲሆን መንስኤው ፍርሀት፣ የጥፋተኝነት ስሜት፣ በልጅነት የተፈፀመ የወሲብ ጥቃት ካለ፣ አካላዊ ህመሞችና የሆርሞን መዛባት ሁኔታ ካለ ለወሲብ ዝግጁ ያለመሆን ሁኔታን በተለይም በሴቷ ላይ ይፈጥራል፡፡ ዝግጁ ባልሆነ ሴት ብልት ላይ ወሲብ ሲፈፀም በሴቷም ሆነ በወንዱ ላይ ህመምን መፍጠሩ እንደማይቀር የስነ ልቦና ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡
እንደ ማብራሪያቸው የስንፈተ ወሲብ ችግሮች መንስኤ ተጠቃለው ሲታዩ ስነ ልቦና፣ አካላዊ ጤና ችግሮችና ከሆርሞን መዛባት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የማህበረሰብ ጤና ባለሙያ የሆኑ አንድ ዶ/ር ደግሞ ‹‹አልኮልና ጫትን ጨምሮ ሌሎች ሱስ አስያዥ እፆች ሰዎች ጤናማ የወሲብ ህይወት እንዳይኖራቸው ያደርጋሉ›› ካሉ በኋላ በተለይም አልኮል በአዕምሮና በአካል መካከል የሚኖረውን ትክክለኛ መስተጋብር (መጣመር) በማወክ በቂ የደም ዝውውር እንዳይኖርና የወንዶች ብልት ለወሲብ ዝግጁ በሚሆንበት አግባብ እንዳይቆም (እንዳይጠነክር) ያደርገዋል ብለዋል፡፡
እንደ ባለሙያው ትንታኔ አልኮል በተፈጥሮ በሰዎች ሁለንተናዊ ማንነት ላይ ድባቴን ከሚያመጡ ነገሮች አንዱ ሲሆን፤ የወሲብ ፍላጎትን እንደሚጨምር ቢታወቅም ትክክለኛና አስደሳች ወሲብን ለመፈፀም የተፈጠረውን ውስጣዊ ፍላጎት የምናሳካበትን በቂ አቅም እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ‹‹በዚህ ሳቢያ አልኮል ከወሲብ ደስታንና እርካታን እንዳናገኝ ምክንያት ይሆናል ብለዋል›› ዶ/ሩ፡፡
የስነ ልቦና ባለሙያው በበኩላቸው በአገራችን የሚዘወተረው ጫት ከወንዶች ይልቅ ሴቶችን ለወሲብ የማነሳሳት አቅም እንዳለው ጥናቶች ያረጋገጡ ቢሆንም ‹‹ጫት ከመጠን በላይ አብዝቶ መጠቀም በሴቶችም ሆነ በወንዶች ላይ ወሲብን በብቃት የመፈፀም አቅምን ያሳጣል›› ይላሉ፡፡ ባለሙያው አያይዘውም ጫት የወንዶች ብልት እንዳይቆምና የዘር ፈሳሻቸው መጠን እንዲቀንስ ከማድረጉም በላይ ጫት ከሚቅሙ ወንዶች ከ65 በመቶ በላይ የሚሆኑት የዘር ፈሳሽ ሴላቸው ቅርፅ የተዛባ እንዲሆን ያደርጋል፡፡
ተፈጥሮአዊ ቅርፁና ባህሪው የተዛባ እንዲሁም በቂ መጠን የሌለው የዘር ፍሬ ደግሞ ልጅ ለመውለድ የሚቻልበት እድል ጠባብ መሆኑን የሚናገሩት የስነ ልቦና ባለሙያው፤ ከአልኮልና ከሌሎች ሱስ አስያ ነገሮች በራቀ መልኩ የስንፈተ ወሲብ ችግርን ለማስወገድ እንዲሁም የጤናማ የወሲብ ህይወትን ለማዳበር የሚያግዙ መፍትሄዎችን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ በጥንዶች መካከል የግልፅነት፣ የመተማመን፣ የመነጋገርንና የመግባባት ባህልን ማሳደግ እንደዚህም ፍርሐትን፣ ውጥረትን፣ ጭንቀትን እና ስለወሲብ ያለንን አሉታዊ አመለካከትን ከማስወገድ ባሻገር ስለጤናማ ወሲብ ህይወት የተፃፉ መፅሐፍትን ማንበብንና እርዳታ መጠየቅን መልመድ ጠቃሚ ነው ይላሉ ሙያተኛው፡፡
የወሲብ አፈፃፀምን ሁልጊዜ በተለመደው መንገድ ብቻ ማካሄድ መሰልቸትን የሚያስከትል በመሆኑ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀሙ ጠቃሚ እንደሆነ የሚናገሩት ባለሙያው የስንፈተ ወሲብ ችግርን ለመከላከል የአመጋገብ ስርዓትን ማስተካከል፣ አካላዊ እንቅስቃሴን ቢያንስ በሳምንት ሶስት ቀን መስራትና ወንዶች በወሲብ ወቅት የሚከሰትባቸውን ፈጥኖ የመጨረስ ችግር ብልታቸውን በእጃቸው በመጭመቅና ለወሲብ የተነሳሳውን ብልት እያበረዱ መልሶ እንደገና የማነቃቃት ዘዴን በመጠቀም አስደሳች የወሲብ ህይወት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚችሉ ሙያተኛው ይመክራሉ፡፡
እንደ ሙያተኞች ማብራሪያ ከሆነ ማንኛውም ሰው ጤናማ የወሲብ ህይወት እንዲኖረው አካላዊ ጤናውን መጠበቅና የሆርሞን ችግሮችን በማስወገድ እንዲሁም ስነ ልቦናዊ ጤንነታችን ማስተካከል እና ከፍላጎት ውጭ የሚፈፀምን ወሲብ ማስወገድ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ መፍትሄ የተጣለባቸው የስንፈተ ወሲብ ችግር ካጋጠመ አግባብ ያላቸውን ሙያተኞች በማነጋገር ፈጥኖ መፍትሄ መፈለግ ተገቢ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የነጭ ሽንኩርት የጤና ጥቅሞች

1 Comment

Comments are closed.

Share