ሐራ ተዋሕዶ የተባለው ድረ ገጽ “አቡነ ማቴዎስ አቡነ ሳሙኤልና አቡነ አብርሃምን ከአቡነ ማቲያስ ጋር ለማስማማት ቤታቸው ውስጥ እያነጋገሯቸው ነው የሚል ዜና አስነበቦ ነበር። አባ ሰላማ የተባለው የኦርቶዶክሳውያን ድረ ገጽ ደግሞ በሰበር ዜናው “አባ ሳሙኤል እና አባ አብርሃም ብፁዕ አቡነ ማትያስ እግር ላይ ወድቀው ይቅርታ ጠየቁ” ይላል። ዜናው እንደወረደ የሚከተለውን ይመስላል
አባ ሳሙኤል እና የጉድ ሙዳዩ አባ አብርሃም አቡነ ማትያስን ይቅርታ መጠየቃቸው ተሰማ፡፡ ይቅርታ እንዲጠይቁ ያደረጉት በ6ኛው የፓትርያርክ ምርጫ ሁለት መለያ አጥልቀው ሲሻቸው ለማቅ ዞረው ደግሞ በሽምግልና ስም እየተጫወቱ የቆዩት የመንደሩ ቀኛዝማች ሀይሉ ቃለወልድ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የመንደሩ ቀኛዝማች በሐዘን ድባብ የተዋጠውን የማቅን መንደር ባለበት ትተው “ኧረ ጉድ እንዳንሆን እነአባ ሳሙኤልን ከአቡነ ማትያስ ጋር እናስታርቃቸው” ብለው የማቅ እጩ ወደነበሩት (“ነበር እንዲህ ቅርብ ነው ለካ?” አሉ እቴጌ ጣይቱ) ወደአባ ማቴዎስ በመደወል ከአቡነ ማትያስ ጋር እንዲያስታርቋቸው ይጠይቃሉ፡፡ አባ ማቴዎስም ሌሎች ጳጳሳትን ይዘው ወደአቡነ ማትያስ እንደገቡና ይቅርታ እንዲጠይቁ እንዳደረጓቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚያም አባ አብርሓም እግራቸው ላይ ወድቀው ስቅስቅ ብለው በማልቀስ “ይቅርታ አድርጉልኝ አባቴ፣ እኔ እኮ በሽተኛ ነኝ የምለውንም አላውቅም” በማለት ይቅርታ ጠይቀዋል ተብሏል፡፡ አባ ሳሙኤልም በተመሳሳይ መንገድ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ግን “እኔን ምን አደረጋችሁኝ? ይቅርታ መጠየቅ ያለባችሁ እኔን ሳይሆን የደፈራችሁትን ሲኖዱሱን ነው፡፡ አልሰማ ያላችኋቸውን ሰብሳቢውን ነው ይቅርታ መጠየቅ ያለባችሁ፡፡” ማለታቸውን ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡
አባ ሳሙኤል እንኳን ለውድድር ለዕጩነትም ብቁ ባለመሆናቸው ተናደውና አኩርፈው በምርጫው ዕለት አለመገኘታቸውን የገለጹት ምንጮች ከእርሳቸው ጋርም የጉድ ሙዳዩ አባ አብርሃምና የማቅ አንደኛ ዕጩ አባ ማቴዎስ አድመው እንዳልተገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የጉድ ሙዳዮቹ አድራጎት ከአንድ ጳጳስ ፈጽሞ የማይጠበቅና በቀጣይም ከብፁዕ አቡነ ማትያስ ጋር ሊያጋጫቸው እንደሚችል ስለተሰጋ ነው ይቅርታ እንዲጠይቁ የተደረገው ተብሏል፡፡ ወላዋዩ አባ ገብርኤልም በግል ወደ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ገብተው በተመሳሳይ “ደብዳቤው እውነት መሆኑን አረጋገጥኩ አባቴ ይቅርታ ያድርጉልኝ ሰዎች አሳስተውኝ ነው” ማለታቸው ታሰምቷል፡፡ አሳሳቱኝ ያሏቸው ምናልባትም በአዋሳ ምእመናን ጉዳይ ወዳጆች የሆኗቸው የማቅ ሰዎች ሳይሆኑ እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡
በምርጫው ሕግ ውስጥ አቡነ ማትያስን ከጫወታው ለማስወጣት የእድሜ ገደብ በማድረግና የዜግነት ጥያቄን በማቅረብ የተንቀሳቀሱትና በቆፈሩት ጉድጓድ የገቡበት አባ ሳሙኤል፣ ከምርጫው አስቀድሞ 500 ሺህ ብር መድበው የምረጡኝ ቅስቀሳ በማድረግ ግርግር ለመፍጠር መሞከራቸውና ሕዝብ መርጦኛል በሚል በአስመራጭ ኮሚቴው ላይ ጫና ለማሳደር በከፍተኛ ሁኔታ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡ በተለይም የሥላሴ ኮሌጅ ተማሪዎችን በደካማ ጎናቸው ማለትም ከኮሌጁ ዲን ከአባ ጢሞቴዎስ ጋር ያላቸውን አለመግባባት እንደጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም መብታቸው እንዲከበርላቸው አባ ጢሞቴዎስን “ለምንድነው ተማሪዎቹ የሚጠይቁትን መብታቸውን የማያከብሩላቸው?” በማለት በተደጋጋሚ በመጠየቃቸው በዚህ ደስ ያልተሰኙት አባ ጢሞቴዎስ ፊት ነስተዋቸዋል፡፡ አባ ሳሙኤልም ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እርሳቸው ፓትርያርክ ከሆኑ ችግሮቻቸውን ሁሉ እንደሚፈቱላቸው ቃል በመግባት በተላላኪዎቻቸው በኩል ተማሪዎቹን አሳምነው ነበር ተብሏል፡፡
በዚህ ያልተወሰኑትና የፓትርያርክነት ሥልጣን ያሳወራቸው አባ ሳሙኤል ያኔ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ተጋጭተው ለዓመት ያህል ያለስራ ተቀምጠው በነበረ ጊዜ መሸሻ የሆኗቸውን ብፁዕ አቡነ ማትያስን ለመቀናቀን መሞከራቸውና በዕጩነት እንዳይቀርቡ በርካታ ክፉ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተው ሁሉም ከከሸፈባቸው በኋላ በመጨረሻው ይቅርታ የጠየቁት ጥፋታቸው ስለተሰማቸው እንዳልሆነና በቀጣይ ሊወሰድባቸው የሚችለውን እርምጃ ፈርተው እንደሆነ የአባ ሳሙኤልን ማንነት ጠንቅቀው የሚያውቁ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ የምርጫው ግርግር በትኩሱ እየተቃኘ ባለበት በአሁኑ ወቅት የአባ ሳሙኤል በጊዜ ከጨዋታ ውጪ መሆንን በማሰብ ሌላው የጉድ ሙዳይ አባ ሉቃስ “ለመሆኑ የእጅጋየሁ አማች አባ ሳሙኤል ቢመረጥ ኖሮ እርሱን እጅ ልንነሳ ነበር ወይ?” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ምንች፡ አባ ሰላማ ድረ ገጽ