Health: የገጠመኝ ደም መፍሰስ ለምን አይቆምም?

ይድረስ ሰላምታዬ ለእናንተ፡፡ ከዛሬ 5 ወር በፊት አካባቢ በምስጢር ማንም ሳያውቅ ውርጃ ፈፅሜ ነበር፡፡ እስካሁን ድረስ ሞዴስ በመጠቀም ላይ እገኛለሁ፡፡ እናም እኔና ጓደኛዬ በጣም ጨንቆን ያላችሁን ተስፋ እናንተ ስለሆናችሁ ወደ እናንተ ብዕራችንን ልናነሳ ተገደናል፡፡ እናንተም ይህንን ጭንቀታችንን እንደምትገላገሉን ባለ ሙሉ ተስፈኞች ነን፡፡ መልሳችሁን በጉጉት ነው የምንጠብቀው አደራ አደራ!! C.G
ይድረስ ሰላምታዬ ለእናንተ፡፡ ለአንድ አዳም አንዲት ሔዋን ያስፈልጋታል ብሎ እግዚአብሔር ከግራ ጎኑ አውጥቶ አጋር እንድትሆነው ሰጥቷታል፡፡ ዛሬ እኔም የራሴን የሆነ አጋር ስለሚያስፈልገኝ ከ‹‹መ›› ህጎች መወሰን በምለው ላይ ተስማምተን ከፍቅረኛዬ ጋር ለዓመታት በፍቅር አብረን አሳልፈናል፡፡ በመሀል ያልተፈለገ እርግዝና አጋጠመኝ፡፡ በዚህ መሀል እኔ ለጊዜው ልጅ መውለድ አልገለግኩም ነበር፡፡ ተስማምተን ወደ ግል ክሊኒክ ሄጄ የተወሰነ ብር ከፍዬ ፅንሱን አስጠረግኩት፡፡ ሆኖም ለሶስት ሳምንታት በትንሹ ደም ይወጣኝ ነበር፡፡ ከሶስቱ ሳምንታት በመጨረሻው ለሁለት ቀን በጣም ብዙ ደም ፈሰሰኝ፡፡ ከዛ ጊዜ ጀምሮ አሁን በሁለት ወር ውስጥ ነው ያለሁት፡፡ ነገር ግን የወር አበባዬ አልመጣም፡፡ ስለዚህ በጣም ፈራሁ፡፡ ተጨነቅኩኝ ከዕለት ዕለት እንቅልፍ አጥቼ እጨነቃለሁ፡፡ ምን ትሉኛላችሁ? አደራ ምላሻችሁ ፈጣን ይሁን ተስፋ ቆርጫለሁ፡፡ እና አንድ በሉኝ ምንም ሆነ ምን ምላሻችሁን በተስፋ እጠብቃለሁ፡፡ ከሰላማዊት

መልስ፡- ዛሬ በዚህ አምዳችን በአጋጣሚ ከኢትዮጵያ (ጋዜጣችንን ከድረገጻችን amharic.zehabesha.com ከሚያነቡ) ለደረሱን ሁለት ተመሳሳይ ችግር የያዙ ጠያቂዎችን ለማስተናገድ እንሞክራለን፡፡ ሁለቱም ውርጃ ፈጽመዋል፡፡ ውርጃውን ካደረጉ በኋላም ሁለቱም የተለያዩ ችግሮች ተከስቶባቸዋል፡፡
ውድ ጠያቂዎቻችን ለህይወታችሁ ጥንቃቄ እንድታደርጉ የባለሙያ እገዛ መጠየቃችሁ ያስመሰግናችኋል፡፡ ሆኖም ግን ሁሉም ነገር ከመሆኑ በፊት ቢሆን በጣም ተመራጭ ስለሆነ አንድ ነገር ከማድረጋችን በፊት ተገቢው እውቀት ሊኖረን ይገባል፡፡
ውድ ጠያቂዎቻችን፡- ውርጃ ምን እንደሆነ የምታጡት ጉዳይ አይመስለንም፣ የት እንደሚደረግም፡፡ ሆኖም ግን ከሁሉም በፊት መቅደም ያለበት አለማርገዝ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ቀላሉ ዘዴ ኮንዶም መጠቀም ሲሆን ከዚህ የተሻለው ደግሞ ምንም አይነት የግብረ ስጋ ግንኙነት ከትዳር በፊት አለማድረጉ በጣም በጣም ተመራጭ ነው፡፡
ከዚህ አልፎ ያልተፈለገ እርግዝና በሚከሰትበት ጊዜ ግን ወደ ባለሙያ (በክሊኒክ ወይም ሆስፒታል) በመሄድ ብቻ አስፈላጊውን ህክምና ማድረግ ተገቢም ወሳኝም ነው፡፡
ውርጃው ከተፈፀመ በኋላ ከዚህ በፊት ያልነበሩ ነገሮች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ሰውነታችሁን ንቁ አድርጎ መከታተል ከዛም የተፈጠረ ወይም የተከሰተ ነገር ካለ ወደዛው ባለሙያ በመሄድ ማስረዳትና ተገቢውን መፍትሄ ማግኘት አስፈላጊ ነው፡፡
ከዚህ D&C የተባለ የማህፀን ጠረጋ ህክምና ወይም የምርመራ ሂደት የሚካሄደው በክሊኒክ ወይም በሆስፒታል ውስጥ ለዚሁ ሙያ በሰለጠነ ሐኪም መሆን አለበት፡፡ ይህም ከ15-30 ደቂቃ ሊፈጅ ይችላል፡፡
ውርጃ የምትፈፅም ሴት በቅድሚያም የአዕምሮ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባታል፡፡ ቢቻል አብሯት የሚመጣ ሰው ያስፈልጋል፡፡ ይህ የማህፀን ጥረጋ (D&C) ከተካሄደ በኋላ እንደ በሽተኛዋ ሁኔታ የሚከሰቱ ችግሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡
– የማህፀንን ግድግዳ መቀደድ፡- የአንዲት እርጉዝ ሴት የማህፀን ግድግዳ በእርግዝናው ምክንያት መሳሳት ያጋጥመዋል፡፡ ስለሆነም ከባለሙያ ውጭ በሚደረግ የውርጃ ሂደት አንዳንድ ጊዜም በባለሙያ ስህተት የማህፀን ግድግዳ ሊቀደድና ደም ሊፈስ አልፎም የውስጥ ሰውነት ሊጎዳ ይችላል፡፡ ስለዚህ ከተደረገም በባለሙያ እርዳታ መጠቀም ይሻላል፡፡ ይህንን የተቀደደ ግድገዳ በቀዶ ጥገና ማስተካከል ይቻላል፤ ማንኛውም ህክምናውን ያደረገች ሴት የማያቋርጥ የሆድ ህመም ከተከሰተባት ወደ ባለሙያ መሄድ ይኖርባታል፡፡
– የማህፀን በር መጎዳት፡- የማህፀን በርን የሚይዘው መሳሪያ ወይም በሩን ለማስፋት የምንጠቀምበት ብረት የማህፀንን በር ሊጎዳና መድማት ሊያስከትል ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ የተቀደደውን በመጫን ወይም በመስፋት ማስተካከል ይቻላል፡፡
– የማህፀን ግድግዳ ላይ የሚፈጠር መያያዝ ወይም ጠባሳ መፈጠር በዚህም ምክንያት የወር አበባ መቅረት፣ የወር አበባ መዛባት፣ የወር አበባ በሚመጣበት ጊዜ ያልነበረ ወይም የባሰ የሆድ ህመም ማስከተል፣ ተከታዩ እርግዝና እንዲጨናገፍ ማጋለጥ፣ መካንነትን ማምጣት ናቸው፡፡ ይህንን በአልትራሳውንድ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ለዚህ ችግር የማህፀን ሐኪም ማማከር ያስፈልጋል፡፡
– ፅንሱ ሙሉ ለሙሉ ካልተጠረገ ቀጣይ ደም መፍሰስን ያስከትላል፡፡ ለዚህም እንደገና መጠረግ ያስፈልጋል፡፡ የቀረውን ፅንስ ወይም የፅንስ ክፍል ለማውጣት፡፡
– የማህፀን ኢንፌክሽን ሊፈጠር ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ማህፀን ውስጥ የቀረውን የፅንስ ክፍል ለማውጣት መጀመሪያ በሽተኛዋ ተኝታ በክንዷ የአንቲባዮቲክ መድሃኒት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ከሰዓታት በኋላም ማህጸኗን በመጥረግ ከህመሟ ማዳን ይቻላል፡፡
የማህጸን በር ብረት መሰል በሆኑ የተለያዩ መጠን ያላቸው መሳሪያዎችን በመጠቀም በማህፀን ውስጥ ያለውን ፅንስ ወይም የማህፀን ግድግዳ በመጥረግ የሚከናወን ድርጊት በህክምናው D&C በመባል ይታወቃል፡፡ የ D&C ጥቅሞች ሁለት ሲሆኑ አንደኛው በማህፀን ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ለማወቅ የሚደረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ማህፀንን በመጥረግ ለህክምና የምንጠቀምበት ሂደት ነው፡፡
ከማህፀን ግድግዳ በትንሹ ናሙና በመውሰድ ለምርመራ በመጠቀም የበሽተኛውን ችግር ለማወቅ የምንጠቀመው ሂደት ለምርመራ የሚደረግ D&C በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ጊዜ የማህፀን በር ቀስ እያለ በማስፋት የማህፀንን ውስጥ ለማግኘት እንጠቀምበታለን፡፡ የማህፀንን ግድግዳ በሚያሳይ መሳሪያ በመጠቀም የት ቦታ ችግር እንዳለ እናያለን፡፡ ካስፈለገም ከተጠርጣሪው ቦታ ላይ ትንሽ ሳምፕል በመውሰድ ለምርመራ እንልካለን፡፡ ከዚህ ውጤትም በመነሳት የበሽታውን ችግር ለመረዳት እንችላለን፡፡ ከነዚህ ችግሮች መካከል የማህፀን ካንሰር፣ ካንሰር ሊሆን የቀረበን የማህፀን ግድግዳ እና በማህፀን ግድግዳ ላይ ማደግ የጀመረን ጣት መሰል ዕጢ መለየት እንችላለን፡፡
በህክምና የሚደረግ D&C ከዚህ በታች ለተጠቀሱት ችግሮች ይጠቅማል፡፡
– ለውርጃ፡- ያልተፈለገ እርግዝናን ለማስወገድ ይህንን D&C ህክምና የማህፀንን በር በማስፋት የማህፀንን ግድግዳ መጥረግ በመጠቀም እርግዝናውን እናቆማለን ወይም እናቋርጠዋለን፡፡
– ለተጨናገፈ እርግዝና፡- ሳይታሰብ የእርግዝና ሂደት በሚሰናከልበት ጊዜ ይህንን D&C የተባለ የህክምና አይነት በመጠቀም በሽተኛዋን ከብዙ ደም መፍሰስ እና ወደ ፊት ከሚመጣ የማህፀን ኢንፌክሽን እንከላከላለን፡፡
– ለረጅም ጊዜ የቆየና ብዙ ደም ለሚፈሳት ሴት እንጠቀመዋለን፡፡
– ከእርግዝና በኋላ ወይም ከወሊድ በኋላ ለሚከሰት የማያቋርጥ እና ብዙ ደም መፍሰስ እንጠቀማዋለን፡፡
ውድ ሰላማዊት፡- እስከዛሬ ህክምና ካለድረግሽ የዚህ የአንቺ ደም መፍሰስ ያመጣው የቀረ ማህፀን ውስጥ ያለ የፅንሱ ክፍል ሊኖር ስለሚችል መጀመሪያ ህክምናውን ወዳደረገልሽ ባለሙያ በመሄድ ማህፀንሽን ድጋሚ መጠረግ ይኖርብሻል፡፡ ይህ የሚደረገው መጀመሪያ የአልትራ ሳውንድ ምርመራ ተደርጎ ቢሆን ይመረጣል፡፡
እንግዲህ C.Gም የአልትራሳውንድ ምርመራ ማድረግ ያስፈልግሻል፡፡ ከዚያም የማህፀን ሐኪም ማነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ለሁለታችሁም መልካሙን ሁሉ እንመኛለን፡፡ ሰላም!
{በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 52 ታትሞ የወጣ}

ተጨማሪ ያንብቡ:  Health: የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን በዶሮ ሾርባ
Share