September 1, 2013
16 mins read

ፕላሴቦ

ፕላሴቦ
The placebo Effect
መቼም ሁልጊዜ ጤና መሆን የለምና እክል ገጥሞን የህክምና እርዳታን ፍለጋ ወደ ባለሙያዎች እንሄዳለን፡፡ ተገቢው ምርመራና ምዘና ከተካሄደ በኋላም የጤና ችግሩን የሚያስታግስ፣ የሚያሽል አሊያም ሙሉ ፈውስን የሚሰጥ መድሃኒት እና ህክምናን እናገኛለን፡፡ ሐኪሞች የሚሰጡን መድሃኒቶች እና ህክምናዎችም በቀጥታ የበሽታ ምንጩን የሚያደርቁ ፊዚዮሎጂካል ወይም ባዮሎጂካዊ መሰረት እንዳላቸው ብዙዎቻችን እንቀበላለን፡፡ ባለሙያዎቹ ግን ይህ ሁልጊዜ አይሰራም ይሉናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የበሽተኛው የምርመራ ውጤት ከህመም ነፃ ምልክቶችን እያሳዩ በሽተኛው አይሻለውም፣ ፍቱን የሚባል መድሃኒት በሌለው በሽታ ይታመማል፣ አለዚያም ሐኪሙ የበሽታውን ምንጭ ማወቅ ይቸግረዋል፡፡ በዚህ ወቅት ሐኪሞች ለበሽተኛው የሚሰጡት መድሃኒት እንደሚያድነው በመግለፅ ምንም አይነት ችግር ፈቺነት የሌላቸው እና ሰውነት ውስጥ ገብተው ምንም የማይሰሩ በሽተኛውንም የማይጎዳ ክኒኖችና ሽሮፖች ይሰጣሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም ምንም ስራ የማይሰራበት ‹‹ቀዶ ጥገና›› ያካሂዳሉ፡፡ እነዚህን ህክምናዎች በሽተኞች ያድኑናል ወይም ያሽለናል ብለው ስለሚያስቡ ያለንም ፊዚዮሎጂካዊ ስራ ከበሽታው ይድናሉ፡፡ እነዚህ በመድሃኒት ስም የሚሰጡ ክኒኖች ንፁህ ስኳር ወይም ቫይታሚን ሊሆኑ የሚችሉ ሲሆን ፈሳሽ መድሃኒቶቹም ንፁህ ውሃዎች ናቸው፡፡ ታዲያ የስኳሩንም ሆነ ንፁህ የሆነውን ውሃ የተፈጥሮ ቀለም እና አይነት ለውጥ ለማድረግና እውነተኛ መድሃኒት ለማስመሰል የተለያዩ ቀለሞችና ማሸጊያዎች ይሰራላቸዋል፡፡ ይህን አይነቶቹ ሰውነት ውስጥ ገብተው ምንም ስራ የማይሰሩ መድሃኒቶች፣ ግን ደግሞ ሰዎች ያሽሉናል በሚል አስተሳሰብ እና እምነት የሚወስዷቸው እና በእርግጥም ውጤት የሚያገኙባቸው ‹‹መድሃኒቶች›› በሳይንሱ አጠራር ፕላሴቦ (Placebo) ይባላል፡፡ ይህ በእምነት ብቻ የሽታ ምልክቶችን ከዚያም አልፎ ህመሞች ፈውስ የመስጠት ሂደት እና ውጤት ‹‹ፕላሴቦ ኢፌክት›› ይሰኛል፡፡ ይህ አይነት የህክምና ዘዴ አዕምሮ በሰውነት ፊዚዮሎጂ እና ባዮሎጂካል ስርዓቶች ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ እንደሚደረግና ሳይኮሎጂካዊ ሁኔታዎች ሌሎች የሰውነት ደህንነት ደረጃዎች ላይ በጎም ይሁን መጥፎ ተፅዕኖዎችን የማድረግ ብቃት እንዳላቸው አመላካች መሆኑን ባለሙያዎች ያወሳሉ፡፡
Power of Suggestion
ፕላሴቦ የሚለው ቃል ምንጩ ላቲን ሲሆን ‹‹ደስ አሰኛለሁ›› (I shall Please) የሚል ትርጓሜን ይሰጣል፡፡ በረጅሙ የህክምና ታሪክ ውስጥ ፕላሴቦ ለበርካታ ህመምተኞች መፍትሄ ሆኖ የዘለቀ የህክምና መልክ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በተለይም ታማሚዎቹ ከኬሚካል ይልቅ አዕምሮአዊ ምቾትን የሚፈልጉ ሲሆኑ ኬሚካላዊ ይዘት ያለው የሚመስልና ጥቅምም ሆነ ጉዳት የሌለውን መድሃኒት መስጠት የተለመደ ነበር፡፡ የዚህ አይነት ከበሽታ አምጪ ጀርሞች ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ህክምና በብዙ ባህላዊ እምነቶች ዘንድም ይከናወናል፡፡ ዋናው በሽተኛው ያድነኛል ብሎ የማመኑ ኃይል እንደሆነ ፀሐፍት ያወሳሉ፡፡ ፕላሴቦ በሽታን በማከም ብቻ ሳይሆን በመድሃኒት ቅመማ ውስጥም ሰፊ ታሪክ አለው፡፡ በተለይ የአዕምሮ ህመሞችን ለማከም የሚሰሩ መድሃኒቶችን ውጤታማነት ለመፈተሽ መድሃኒት የማይሰጣቸው ግን እንደተሰጣቸው የሚነገራቸውን ሰዎች በመቆጣጠሪያነት (Control group) በመጠቀም በኢንዱስትሪው ይተገበራል፡፡
ፕላሴቦ በጥናት ሲፈተሽ
የፕላሴቦን ተፅዕኖ በርካታ ተመራማሪዎች ትኩረት ሰጥተው ሲያጠኑ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ በቀደመው ዘመን ከተሰሩ ጥናቶች መካከል ኤች.ኬ ቢቸር በ1955 እ.ኤ.አ ‹‹The power of placedo›› በሚል ርዕስ ያሳተመው ወረቀት መሰረታዊ ግንዛቤን ያስጨበጠ እንደነበር ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ቢቸር ትንታኔ በሰጠባቸው እና ባጠናቸው 26 ምልክታዎች ከተካተቱ በሽተኞች ውስጥ 32 ከመቶ የሚሆኑት በፕላሴቦ ተሽሏቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በርካታ ጥናቶች የተካሄዱ ቢሆኑም ዛሬም ድረስ ሳይኮሎጂካዊ ተፅዕኖዎች አካላዊ ህመሞችን በማባባስም ይሁን በማሻል ያላቸው ሚና ላይ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ‹‹በብዙዎቹ ጥናቶች የተረጋገጠው እውነታ ሁለቱም በቅንጅት እንደሚሰሩና ብዙዎቹም የህመም ስሜቶች መፈጠሪያቸው አዕምሮ በመሆኑ አዕምሮን ‹‹በውሸት መድሃኒት›› (ፕላሴቦ) በመሸወድ ማሻል እንደሚቻል ነው›› ይላሉ የፕላሴቦን ውጤት ለ20 ዓመታት ያጠኑት የካሊፎርኒያ ፕሮፌሽናል ሳይኮሎጂ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር ማይክል ጆሴፍ፡፡
ፕላሴቦ ከተሰጣቸው ታማሚዎች መካከል ቢያንስ 30 በመቶው የሚሻላቸው መሆኑን ኒውሳይንቲስት መጽሔት ላይ የሰፈረ የቅርብ ጊዜ ዘገባ ያትታል፡፡ በተለይ ሐኪም በእርሱ ደረጃ ሊረዳቸው ለማይችላቸው ታማሚዎች የሚሉትን ከማዳመጥ እና እነዚህን መሰል መድሃኒቶች ከመስጠት የዘለለ አማራጭ አይኖረውም፡፡ የመድሃኒት ዋጋ የሌላቸው ክኒን እና መርፌዎች እንዴት ከበሽታ ሊያሽሉ ይችላሉ? ይህን ለማድረግ የሚያስችለው የአዕምሮ ክፍል እና ሁኔታስ ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጥረት ያደረጉ ተመራማሪዎች አንዳንድ ውጤቶችን ይፋ አድርገዋል፡፡
ኢንዶርፊንና ሴሮቶኒን የፕላሴቦ መልዕክተኞች
ሰፊ ጥናት ፕላሴቦን ውጤታማ የሚያደርጉትን በመዝናናት ወቅት ከአዕምሮ የሚመነጩት የተፈጥሮ ህመም አስታጋሽ የሆኑት አዶርፊንስ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
የጥናቱ ባለቤቶች እንደሚሉት መድሃኒቶች ያድኑኛል የሚል ቀዳሚ እምነት ካለ አዕምሮአችን እፎይታና መዝናናት ስሜትን ያገኛል፡፡ ይህን የሚሰሩት ደግሞ በአዕምሯችን መዝናናትና መነቃቃትን የሚሰጡት ኢንዶርፊን የተባሉት ኬሚካሎች ናቸው፡፡ ‹‹የደስታ፣ መዝናናት እና ጤና መልዕክተኞች›› ይሏቸዋል ተመራማሪዎቹ፡፡ ታህሳስ 2008 ላይ በስዊድን አፕሳላ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደ ጥናት ደግሞ ሰዎች ጥቅም ብለው መድሃኒት የሚድኑት መሰረት ይህን የሚያስተናግድ ጂን (ዘረ መል) ስላላቸው ነው ብሏል፡፡ የአዕምሮ ስሜትና አጠቃላይ ሁኔታን የማስተካከል ሚና ያለው ሴሮቶኒን የተባለው ኬሚካል ወሳኝ ግብአት ነው ያሉት የስዊድን ተመራማሪዎች ይህን የሚቆጣጠረው ደግሞ ትሪፕቶፋን ሃይድሮሌዝ (trypotophan hydrolase-2) የተሰኘ ጂን መሆኑን ጆርናል ኦፍ ኒውሮሳይንስ በተባለው የምርምር መፅሔት አስፍረዋል፡፡ በበሽታ መጠቃቱ ያስከትልብኛል ከሚለው ቀውስ የሚነሳ ፍራቻ ከፕላሴቦው በኋላ በእጅጉ መውረዱንም አሚግዳላ በተሰኘው የአዕምሮ ክፍል የተመዘገበውን እንቅስቃሴ በመለካት ደርስበታል፡፡ በተገኘው ውጤት ብዙ ድምዳሜ መስጠት አይቻልም ያሉት ባለሙየዎቹ ተጨማሪ ጥናቶች መካሄድ እንዳለባቸው ያሳስባሉ፡፡ ሐኪሞች ፕላሴን እንደ አማራጭ ማከሚያ መጠቀማቸውን በሽተኛውን ማታለልና የበሽተኛ ሐኪም ግንኙነትን በእምነት ላይ ያልተመሰረተ ማድረግን ያስከትላል የሚል ሌሎች ባለሙያዎች ጥናቶቹን በጥርጣሬ ይመለከታሉ፡፡ ለዚህም የቀደሙ ሌሎች ጥናቶችን በአብነት ይጠቅሳሉ፡፡
ሐኪሞች ሁልጊዜ በኬሚካል አያድኑም
ከ600 የሚበልጡ የቁርጥማትና መሰል ችግሮች ስፔሻሊስቶችን እና የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቶችን ያማከለው ጥናት እንዳለው ከግማሽ በላይ ሚሆኑት ሐኪሞች በሽተኞች እንዲሻላቸው ሲሉ ብቻ የመድሃኒት ጥቅም ያላቸውን ‹‹የውሸት መድሃኒቶች›› ያሽላችኋል ብለው ሰጥተዋቸዋል፡፡ ከበሽተኞቹ መካከልም ከ20-30% የሚሆኑት ከበሽታቸው አገግመው ተገኝተዋል፡፡ በዚህ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ባለሙያዎች አንዳንድ የጤና ችግሮች በራሳቸው ጊዜ የሚድኑ በመሆናቸው ውጤቱ የተገኘው በዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልና የግድ የፕላሴቦ ውጤት እንደማይሆን እያነሱ ይከራከራሉ፡፡
ከዚህ የከረረ ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው የሚሰጡ መድሃኒቶች ጀርሞችን ከመላመድ (Drug resistance) ጋር የሚነሳው ነው፡፡ አንዳንድ ሐኪሞች ለምሳሌ የድብርት ማስለቀቂያ እና ፀረ ባክቴሪያዎችን ለሌሎች ህመሞች በፕላሴቦ ስም ይሰጣሉ፡፡ በጉንፋን ወቅት የተለመደ እየሆነ የመጣው ፀረ ባክቴሪያዎችን የመተቀም ልምድ አንዱ ነው፡፡ ጉንፋን በመሰረቱ በቫይረስ እንጂ በባክቴሪያ አይመጣም፡፡ ከጉሮሮ ቁስለት ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችል ኢንፌክሽንን እንደሚከላከል ባለሙያዎቹ ምክንያት ቢያቀርቡበትም ይህ የመድሃኒትን መላመድ ከመቀነስ አንፃር ተቀባይነቱ ዝቅተኛ መሆኑ ይወሳል፡፡
ፕላሴቦ በህፃናትና እንስሳት
ህፃናት፣ ውሻ፣ ድመት እና ሌሎች እንስሳት ላይ የፕላሴቦ ውጤት ይታይ እንደሆነ ያጠኑ ባለሙያዎች ውጤቱ የሚታየው መድሃኒቱን በሚሰጠው ሰው ላይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ፍጥረታት መድሃኒት ስለመውሰዳቸው ስለሚያስተውሉ በእነርሱ ላይ ፕላሴቦ አይሰራም፡፡ መድሃኒቱን የሚሰጠው ሰው ግን መድሃኒት ሰጥቻቸዋለሁና ይሻላቸዋል ብሎ ስለሚያስብ ባይሻላቸውም ተሽሏቸዋል ሲሉ ይወስዳሉ፡፡
የመድሃኒት ቅመማን በፕላሴቦ መፈተን
በመድሃኒት ቅመማ ሂደት መድሃኒቶቹ የሚሞከርባቸው ሰዎችም ሆኑ መድሃኒቱን የሚሰጡት ባለሙያዎች እውነተኛ መድሃኒትና ፕላሴቦው የትኛው እንደሆነ ሳያውቁ ሙከራው ይደረጋል፣ መድሃኒቱ ይሰጣቸዋል ይህም Double blind trial ይባላል፡፡ እውነተኛ መድሃኒት የወሰዱት ሰዎች ፕላሴቦ (ማስመሰያውን መድሃኒት) ከወሰዱት የተሻለ የመሻሻል ውጤት ካሳዩ መድሃኒቱ ስኬታማ ይልና ለገበያ ይቀርባል፡፡ እውነተኛ መድሃኒቱን ካልወሰዱት መቆጣጠሪያ ቡድኖች የተለየ ውጤት ካላመጣ መድሃኒቱ ውጤታማ አይደለምና ተጨማሪ ምርምሮች ይቀጥሉበታ፡፡ እርግጥ ሌሎች የደረጃና ቀመር መመዘኛዎችም ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ እድናለሁ ብለህ እመን ትድናለህ ነው ጭብጡ! ሰላም፡፡

Previous Story

ርዕስ በምርቃት፤ የማን ሙት አመት? (ስለ ሙስሊም ጉዳይ፤ ስለ አገር ጉዳይ)

6946
Next Story

የአባይ ቦንድ ሽያጭ በጉተምበርግ ከሸፈ፤ ድብድብ ተነሳ (Video)

Latest from Blog

“መነሻችን እዚህ መዳረሻችን እዚያ” የሚለው የዲያስፖራ ከንቱ አታካራ! – ክፍል ሁለት

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) በአንዳንድ ስብሰባዎችና የሕዝብ መገናኛ መድረኮች የሚታየው የአንዳንድ ዲያስፖራዎች  “መነሻችን እዚህ መዳረሻችን እዚያ” የበከተ ከንቱ አታካራ በልጅነታችን ወላጆቻችን ትምህርት እንዲሆነን ይተርኩልን የነበረውን ከጫጉላ ወጥተው ጎጆ ለመመስረት የታከቱ ሁለት ያልበሰሉ ባልና ሚስትን ታሪክ

መነሻችን አማራ መድረሻችን አማራ እና ወያኔያዊ መሠረቱ

የማይወጣ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል። የዛሬን አያድርገውና የትግሬ ልሂቆች “ትግራይ የጦቢያ መሠረት ናት ።  ጦቢያ ያለ ትግራይ፣ ትግራይ ያለ ጦቢያ ሊታሰቡ አይችሉም” በማለት ጦቢያዊ ከኛ ወዲያ ላሳር እያሉ አለቅጥ ይመጻደቁ፣ ይኩራሩ፣ ይታበዩ ነበር። ወያኔ

አቶ ታዲዮስ ታንቱ በተከሰሱባቸው ወንጀሎች ጥፋተኛ ተባሉ

ለአመታት በእረስር ላይ የሚገኙት  አቶ ታዲዮስ ታንቱ በተከሰሱባቸው የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት እና የዕርስ በዕርስ ግጭት መቀስቀስ ወንጀሎች ጥፋተኛ መባላቸው ታውቋል፡፡ አቶ ታዲዮስ ታንቱ በተከሰሱበት ክሶች በዛሬ ቀጠሮ የጥፋተኝነት ፍርድ የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ

ከ”ችርቻሮ” ድል አልፎ ለመሄድ የአንድነት አስፈላጊነት – ግርማ ካሳ

በአሁኑ ጊዜ ሁለት የፋኖ አሰላለፎች አሉ:: መኖር ያልነበረበት:: አንከር ሜዲያ ከሁለቱም አሰላለፎች፣ ሁለት ፋኖ መሪዎች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ ሁለቱን አደመጥኩ፡፡ በሰማሁት ነገር ተደስቻለሁ:: ትልቅ ተስፋ እንድሰንቅም አድርጎኛል:: የአማራ ህዝባዊ ድርጅት የፖለቲካ
Go toTop