ግልፅ ደብዳቤ ለአንድነት ብሄራዊ ምክር ቤት አባላት (አሰፋ ዘለቀ)

ከአሰፋ ዘለቀ

አስቸኳይ ጥሪ

 

በቅድሚያ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ። የአንድነት ፓርቲ ደጋፊ ነኝ። በተለይም ላለፉት አንድ አመት የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት በሚል መርህ፣  በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች አንድነት  ሲያደርጋቸው የነበሩት ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች፣  እንዲሁም ከሌላው አንጋፋ ድርጅት መኢአድ ጋር ያቀደው ዉህደት በእጁጉ የኢትዮጵያን ህዝብ ያስደሰቱና ቀልብ የሳቡ መሆናቸዉን መቼም እናንተዉ ሳታወቁት አይቀርም።

በአመራሮች መካከል፣ ዉይይቶች ተደርጎ፣ ቅድመ ዉህደት ስምምነት የተፈረመ ሲሆን፣ የውህደት አመቻች ኮሚቴም ተቋቁሞ ሥራዉን በተሳካ ሁኔታ እየከናወነ ይገኛል። የተቃዋሚዎችን  መሰባሰብ የማይወደው ወያኔ/ኢሕአዴግ ፣ ምርጫ ቦርድን ተጠቅሞ፣ «ያልተሟላ ነገር አለ» በማለት፣  የዉህደት ሂደቱን ለጊዜው ለማጨናገፍ ሞከሯል።

ምርጫ ቦርድ በእጁ ያለው ወረቀት ነው። የዘነጋው ነገር ቢኖር ግን፣ አገዛዙ እውቅና ሰጠም አልሰጠም፣ መኢአዶች እና አንድነቶች በተግባር መዋሃዳቸዉን ነው። የመኢአድ እና የአንድነት አባላት በዞን እና ወረዳ ደረጃ ተዋህደው አብረው መስራት ከጀመሩ ቆይተዋል። አብረው ነው ድምጻቸውን የሚያሰሙት። አብረው ነው የሚታሰሩትና የሚደበደቡት። በመካከላቸው ልዩለት የለም። የዉህደት እንቅስቃሴ በቅንጅት ጊዜ ሊደረግ እንደነበረው፣  ከላይ ወደ ታች ሳይሆን፣  ከታች ወደ ላይ  ነው።  ለዚህም ነው ቅንጅትን ማፍረስ እንደተቻለው፣  በመኢአድ እና በአንድነት መካከል ያለውን ግንኙነት ማፍረስ በቀላሉ የማይቻለው።

ሁኔታው ይህ ሆኖ እያለ፣ የአንድነት ፓርቲ ምክር ቤት፣  አሳፋሪዉ የምርጫ ቦርድ ዉሳኔ በተሰማ በቀናት ዉስጥ፣ ከመኢአድ ጋር በመሆን ምርጫ ቦርድ ላይ ጫና ማሳደር ሲገባው፣ የዉህደት አመቻች ኮሚቴን አፍርሷል። ይሀ በጣም ትልቅ ስህተት ነው ብዬ አምናለሁ።

የዉህደት አመቻች ኮሚቴ ጥሩ ሥራ ከሰሩ ኮሚቴዎች መካከል አንዱ ነው። በመኢአድ እና በምርጫ ቦርድ በኩል ያለውን  ችግር መፍታት የሚቻልበትን አማራጭ ሐሳቦችን በማውጣትና በማውረድ ላይ ይገኝ ነበር። ይህ ኮሚቴ እንዲፈርስ ዉሳኔ ሲወሰን፣ ከመኢአዶች ጋር ምክክር አልተደረገም። በመኢአዶች ዘንድ ሊያስከትል የሚችለውን ቅሬታ ከግምት አላስገባም። ዉሳኔው፣ ሊዋሃዱ በተዘጋጁ ወገኖች መካከል ቀዳዳ የሚከፍት ጠቃሚ ያልሆነ ዉሳኔ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ማሩኝ! - በላይነህ አባተ

 

መኢአድ ከወያኔ ጋር እየተፋጠጠ ባለበት ወቅት፣ የዉህደት አመቻች ኮሚቴዉን ማፍረስ፣ በተግባር ምርጫ ቦርድ የጀመረውን ይዞ እንደመሮጥና፣ አገዛዙን እንደማስደስት ተደርጎ በአንዳንዶች ቢወሰድ፣  ተሳስተዋል ብሎ መከራከር  ያዳግታል። የምክር ቤቱን፣  በተለይም ደግሞ የሊቀመንበሩን ተቀባይነት በእጁጉ የሚሸረሽር ነው።

የውህደት አመቻች ኮሚቴ መፍረሱ በተጨማሪ፣ ከዚሁ ከአንድነት ጋር በተገናኘ፣  ሌላ ያሳዘነኝ ነገር አለ። ከአንድነት የሥራ አስፈጻሚ አባላት አምስቱ ፣ ምክትል ሊቀመንበር ተክሌ በቀለ፣ ምክትል ሊቀመንበር በላይ ፍቃዱ፣ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ ዳንኤል ተፈራ፣ ኢኮኖሚ ጉዳይ ሃላፊ ዳዊት አስራደ፣ የፖለቲካ ጉዳይ ሃላፊው ሰለሞን ስዩም፣ እንዲሁም ገንዘብ ያዡና የዉህደት ኮሚቴው ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ጸጋዬ አላምረው «ከሊቀመንበሩ ጋር መስራት ስለማንችል፣ ሊቀመንበሩ አብረውት ሊሰሩ የሚችሉ አመራሮች መርጦ ስራዉን ይቀጥል። እኛም በምክር ቤቱ አባልነታችን ስራችንን እንቀጥላለን »  በማለት ራሳቸውን ከሥራ አስፈጻሚ  ኮሚቴ አግለዋል።

እነዚህ አንጋፋ ወጣት የአንድነት አመራሮች ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከወጡ፣  ድርጅቱ ምን አይነት መልእክት ነው የሚያስተላልፈው ?  ሊቀመንበሩስ  ኢንጂነር  ግዛቸው ፣ «የተቃዋሚ ድርጅቶች አሰባስባለሁ። ወጣቶችን ወደ አመራሩ አመጣለሁ» ሲሉ አንዳልነበረ፣  ወጣት አመራሮች «ከርሳቸው ጋር መስራት አንችልም» ብለው ሲለቁ፣ የርሳቸው ተአማኒነት ጥያቄ ምልክት ዉስጥ ሊገባ አይችልምን ? ከርሳቸው ጋር የሚሰሩትን ማቀፍና ማሰባሰብ ካልቻሉ እንዴት መኢአድን ፣ ሰማያዊን የመሳሰሉትን በዉጭ ያሉትን ሊያሰባስቡ ይችላሉ?

ዉድ የአንድነት ምክር ቤት አባላት፣ ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኋላ በቅንጅት ዉስጥ ተፍጠሮ የነበረዉን መከፍፈል ታስታወሳላችሁ ብዬ አስባለሁ።  በወቅቱ ለቅንጅት መፍረስ ምክንያት ከሆኑ ወገኖች መካከል ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው አንዱ ነበሩ። በ2000 ዓ.ም የወዳደቀዉን የቅንጅት ፍርስራሽ በማሰባሰብ፣ በወ/ት ብርቱክን ሚደቃሳ የሚመራ ጠንካራ የፖለቲክ እንቅስቃሴ ተጀመረ። በአጭር ጊዜ ዉስጥ አንድነት በሚል ፓርቲ ስም ፣ እንቅስቃሴዉ ሕዝባዊ ድጋፍ አገኘ። ተቃዋሚዎች ሲጠናከሩ የማይወደው ወያኔ/ኢሕአዴግ ብርቱካን ሚደቅሳን አሰረ። ያኔ ኢንጂነር ግዛቸው ድርጅቱን መምራት ጀመሩ። በዚያን ጊዜ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን እና፣ አቶ አመሃ ደስታን  ጨምሮ፣ አሁን ሰማያዊ ፓርቲን ከመሰረቱ በርካታ የቀድሞ አንድነት አመራር አባላት ጋር ኢንጂነር ግዛቸው መስማማት አልቻሉም። የሚቋወሟቸውን በዉስጣዊ አሰራር ከድርጅቱ እንዲታገዱ በማድረግ በአንድነት ፓርቲ ዉስጥ ትልቅ መከፋፈል እንዲፈጠር አደረጉ። ይህ ደግፊዎችን የሚያደማ ፣ ወያኔዎችን ጮቤ የሚያስረገጥ ክስተት ሲፈጸም እንግዲህ ሁለተኛ መሆኑ ነው። በሁለቱም ጊዜ ኢንጂነር ግዛቸው ዋና ተዋናይ ነበሩ።

ተጨማሪ ያንብቡ:   “መደብ ሳይኖር ወደብ ”

አሁን ደግሞ ይኸው ፖለቲካ በቃኝ ብለው ከሶስት አመታት በላይ ከተቀመጡበት ግዞት ወጥተው «ተለውጫለሁ፣ ካለፉት ስህተቶቼ ተምሪያለሁ፣ ከወጣቶች ጋር አብሬ እሰራለሁ። ብቃት ያላቸው ወጣት አመራሮች ከመጡ ደግሞ ሃላፊነቴ እለቃለሁ። ሌሎች ድርጅቶችን አሰባስቤ ጠንካራ ተቃዋሚ ስብስብ እንዲኖር አደርጋለሁ» ብለው ለሊቀመንበርነት ተወዳደሩ። አብዛኛዉ የአንድነት አባል ድጋፉን ሰጣቸው።

ስድስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ እራሳቸው ከመረጧቸው የሥራ አስፈጻሚ ጋር አብረው መስራት አልቻሉም። በድርጅቱ ዉስጥ እንደ ከዚህ በፊቱ የተካኑበትን ዉስጣዊን የሴራ ፖለቲካ ጀመሩ። ቡድን በፍጠር፣ አንዱን ከሌላው በመለየትና በማጋጨት፣ አብረው በጋራ ሲታገሉ የነበሩ ወገኖችን፣ ከሶስት አመታት በላይ ዶር ነጋሶ መሪ የነበሩ ጊዜ ሰላም የነበሩትን፣ ለስልጣናቸው ሲሉ መከፋፈል ጀመሩ።

እንግዲህ ክቡራን የአንድነት ምክር ቤት አባላት፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ዉስጥ በማስገባት፣ በኢንጂነር ግዛቸው እየተደረገ ያለዉን ጎጂ እንቅስቅሴ መገደብ አያስፈልግም ብላችሁ ታምናላችሁን ? ለሁለት ጊዜ ኢንጂነር ግዛቸው የታጋዮችን ልብ አቁስለዋል። ለሶስተኛ ጊዜ ተመሳሳይና ከፋፋይ ሥራ እንዲሰሩ ስለምንም ይፈቀድላቸዋል? የአንድነት ፓርቲ ላለፉት አንድ አመት ተኩል እጅግ በጣም ጉም ስራዎችን እየሰራ ነበር። ይኸው ኢንጂነር ሽፈራው ወለድ በሆኑ ችግሮች ነገሮች ቆመዋል። ሰኔ መጨረሻ ላይ ይገባደዳል የተባለው የሚሊዮኖች ንቅናቄ ተረስቷል።

እንግዲህ ምክር ቤት ቆም ብሎ ራሱን እና ድርጅቱ ያለበትን እንዲመረምር እጠይቃለሁ። የመኢአድ እና አንድነት ዉህደት አመቻች ኮሚቴ እንዲፈርስ የተደረገው ዉሳኔ እንዲቀለብሱና ከሥራ አስፈጻሚ የለቀቁ አንጋፋ ወጣት የአመራር አባላት ያቀረቡትን፣ መልቀቂያ ዉድቅ በማድረግ፣ ሊቀመንበሩ ኢንጂነር ግዛቸው ቡድናዊ የሴራ ፖለቲካቸው ትተው፣  በቅንነት ከነርሱ ጋር እንዲሰሩ መመሪያ እንዲሰጥ፣ ወይንም ሊቀመንበሩን ከሃላፊነታቸው እንዲያነሳ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ድምጻዊያን አምና በዳላስ ዘንድሮ በሜሪላንድ

አንድነት የአንድ ሰው ተክለ ሰዉነት የሚገነባበት ሳይሆን ተቋማዊ ጥንካሬ እንዳለው መታየት አለበት። ከ4፣ 5 አመታት በፊት ወጣት አመራሮች እንደተገለሉት፣ አሁን ወጣት አመራሮችን በማግለል፣ የስድሳዎቹ ፖለቲከኞች የትግሉን ግለት ወደ ታች እንዲያወርዱት ሊፈቀድላቸው አይገባም። ምክር ቤቱ፣ በታሪክ እና በትዉልድ የሚያስጠይቀው ትልቅ ሃላፊነት ስላለበት፣ ለግለሰቦች ታማኝነቱን ለማሳየት ይልቅ፣  የአገርን እና የሕዝብ ጥቅም እንዲያስቀድም እመክራለሁ።

አንድነት የዉህደት ኮሚቴዉን አፍርሶ፣ ሲሰሩ የነበሩ ወጣት አመራሮች ገፍቶ ፣ በሕዝብ ተቀባይነት ያለው ድርጅት ሆኖ ሊቀጥል አይችልም። ያለ ምንም ማገነን የነኢዴፓ እጣ ፋንታ ይደርሰዋል። ትልቅ ትኩረት ይሰጠበት እያልኩ፣ መልካም ዜናን እንደምታሰሙን ተስፋ አደርጋለሁ።

 

 

 

 

 

Share