August 1, 2014
3 mins read

ገንዘብ ሲናገር ህግ ዝም ይላል!!!

ከጋሻው መርጊያ

የሰው ልጅ ነጻ ሆኖ እንደተፈጠረ ታላቁ መጽሀፍ እንዲህ በማለት ይገልጻል፡፡‹‹በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፡፡ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤እንደገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ›› ገላትያ 5፤1፡፡ የዚህ ጥቅስ ጭብጥ ሰው ነጻ ሆኖ ይኖር ዘንድ ክርስቶስ ዋጋ ከፍሎለታል የሚል ነው፡፡እውነታው ይህ ቢሆንም ቅሉ እያደገ የመጣው ማህበራዊ ግንኙነቱ አንዱ በሌላው ላይ አለቃ የመሆንን ዝንባሌ አሳዬ፡፡ አለቅየውም በበታቹ ይፈራና ይሰገድለት ዘንድ ህግ የሚሉት መጨቆኛ አወጣ፡፡ ይህ ህግ እንደ ዛሬው ዘመን ህግ ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው የሚል ሳይሆን እንደ ጆርጅ ኦርዌል የእንስሳ እድር(animal farm) ገጸ ባህርያት ‹‹ሰው ሁሉ እኩል ነው አንዳንድ ሰው ግን የበለጠ እኩል ነው›› የሚል አይነት ነው፡፡ በዚህ የአሸናፊና ተሸናፊ መስተጋብር ውስጥ አሸናፊው በተሸናፊው ላይ ቀንበሩን እየጫነ እርሱ እንደሚፈልገው እየነዳ፤ሲያሻው አሽከር አድርጎ እየገዛው ካስፈለገውም ባሪያ አድርጎ ሲሸጠው እና ሲለውጠው እንደኖረ የሰው ልጅን የማህበራዊ እድገት የፈተሸ ሁሉ ያውቀዋል፡፡ ተፈጥሮ እንደ ጎልያድ ግዙፍ እንደምታርግ ሁሉ እንደ ዳዊት ልባምነትንም ታጎናጽፋለች፡፡ እንደ ጥንት ኢትዮጵያዊያን አትንኩኝ ባይነትን እንደምትሸልም ሁሉ እንደ ዘመን ተጋሪዎቸ ፍርሃትንም ታጎናጽፋለች፡፡ በዚህም የተፈጥሮ መሰናሰል ጉልበታሙ ገዥ በደካማው ተገዥ ላይ የግዛት ቀንበሩን ሲጭንበት እዚህ ዘመን ደረስን፡፡ ፈረሱ እስካልደነበረ ድረስ ጋላቢው አለመሰልቸቱን ማን ይዘነጋዋል፡፡ የታዘለ ልጅ የከተማውን ርቀት ሊረዳ አይችልም እንደ ማለት ይሆናል፡፡

በዚሁ የሰው ልጅ የአሽከርና ጌታ ግንኙነት ከላይ ያለው ተንደላቆ ይኖር ዘንድ የታችኛው ትክሻውን አደንድኖ፤ጉልበቱን አበርትቶ መሸከም ግድ ይለዋል፡፡ በነገራን ላይ አንዱ ገዥ ሌላው ተገዥ ለመሆን መስተጋብር መፍጠሩ እራሱ በሰውኛ እሳቤ ግርምትን ያጭራል፡፡ ለነገሩ የሚገዛለት እስካገኘ ድረስ ገዡ ምን ከዳው፡፡ መግዛት አይሰለች፡፡ ማዘዝ አቀበት(ዳገት) የለውም ይላሉ አባቶቻችን፡፡ ተገዥው እንደ እርሱው በአምሳሉ ለተፈጠረ ሰው አሽከር ለመሆን ሲወድ ማየት እና መገዛትንም እንደ ቁም ነገር በመውሰድ <<እኔ የእንትና አሽከር›› ብሎ ብሎ መፎከሩ ገራሚ ነው፡፡ ከራሱ አልፎ ‹‹ልጀ የእንትና አሽከር ነው›› ሲልም ሊኮፈስ ያምረዋል፡፡ በቆየው ዘመናቻን አባቶች ልጆቻቸውን ለነገስታት እሽከርነት ለመስጠት ይሽቀዳደሙ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ለነገሩ አሁን ላይ የእኔ ዘመን ተጋሪዎች ራሳችንን አሽከር ለማድረግ ስንደክም ሲታይ የአባቶቻችን ብዙም ላይደንቅ ይችላል፡፡ የሀገሬ ህዝብ በገዥና ተገዥ መስተጋብር በአለም አንደኛ ነው ብየ ብናገር ውሸታም የምባል አይመስለኝም፡፡ እነዚያ አትንኩኝ ባይ አባቶቻችን ለውጭ ጠላት ረመጥ ሆነው እንዳለበለቡት ሁሉ ለውስጥ መዥገሮች ግን ለስላሳ ነበሩ፡፡ ይህ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህላችን ጠርንፎ ይዞን አለም በስልጣኔ የት በደረሰበት በዚህ ዘመን እንኳን የተፈጥሮ ኡደት እስኪመስለን ድረስ መገዛትን አሜን ብለን እንቀበላለን፡፡ የኢህአዲግ መንግስት ሀገረ ኢትዮጵያን ዘውዱን ጭኖ ኮርቻውን አደላድሎ፤እርካቡን አስተካክሎ፤ይጓሙን ሸብቦ፤በአዞ አለንጋ ሾጥ እያደረገ ካሰገራት ይሄው ድፍን 23 አመታት ተቆጠሩ፡፡ በኢህአዲግ የስልጣን ዘመን የተወለዱት ወጣቶች ሳይቀር የስርዓቱ ቀንደኛ ተቃዋሚዎች እስኪሆኑ ድረስ ጉልበታሙ ስብስብ አሰራሩን ሊያሻሽል ፈቃደኛ አለመሆኑ የተገዥዎቹን ትዕግስት የስርዓቱንም ‹‹ስልጣን ሙጥኝ›› ለትዝብት ይዳርገዋል!!:: ይህን ክፉ ልማድ ዘወር ብሎ ለሚያየው የእኛን ትዕግስት ብቻ ሳይሆን የኢህአዲግን የሩብ ክፍለ ዘመን ስልጣን አለመጥገብም ይታዘብ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ስለ ኢህአዲግ ዘልዛላ የስልጣን እድሜ ከአንድ ወዳጀ ጋር እናወራለን፡፡ ይህ ወዳጀ እንዲህ ሲል በትዝብት መልክ ኢህአዲግን አሽሟጠጠልኝ፡፡ ኢህአዲግ ዲሞክራት ቢሆን እንኳ ለሩብ ክፍለ ዘመን ስልጣን ላይ ሙጥኝ ማለቱ በራሱ ወንጀል ነው፡፡ እስኪ አስበው ይላል ይህ ወዳጀ ኢህአዲግ ምኒልክ ቤተ-መንግስትን ከተፈናጠጠ ታላቋን አሜሪካን ስንት መሪዎች መሯት? የታሪክ ማጠንጠኛችን በኋላ ማርሽ አሽቀንጥረን ከተጓዝን ለዚህን ያክል ጊዜ እንዲህ ተበድለን ኑሯል ያስብላል፡፡ እዚህ ጋር የሚመሳሰል የአንድ ሰውዬ ታሪክ ትዝ አለኝ፡፡ በአዲስ መስመር እንመለስ፡፡ ሰውየው ባልንጀራው በጣም ይበድለዋል፡፡ ተበዳይም በደሉምን መሸከም ያቅተውና በባልንጀራው ላይ ክስ ለመመስረት ይወስናል፡፡ ተበዳይ ራቦል ጸሃፊ (ክስ አቀነባብሮ ጸሀፊ) ዘንድ ይሄድና በደሉን በዝርዝር አንድ በአንድ እየነገረ ያጽፈዋል፡፡ ክስ ጸሀፊውም እያንዳንዷን ጉዳይ በሚያምር ቋንቋ ክሽን አድርጎ ከጻፈለት በኋላ በንባብ እንዲያሰማው ይስማማሉ፡፡ ተበዳይም አንድ በአንድ ራሱ እየነገረ ያጻፈውን የክስ ዝርዝር በንባብ ሲሰማው ሲቅስቅ ብሎ ያለቅሳል፡፡ በሁኔታው የተደናገጠው ክስ ጸሃፊ ምን ሆኖ እንደሚያለቅስ የግል ተበዳይን ይጠይቀዋል፡፡ ከሳሽም(ተበዳይ) ‹‹ለካ ይህን ያክል ተበድዬ ኖሯል›› አለ ይባላል፡፡ ይህ ታሪክ ከኢትዮጵያውያን ጋር በቀጥታ ተመሰሳይነት አለው፡፡ በደላችንን ሳስታውስ ለካ ይህን ያክል ተበድለን ነበር እንድል ያደርገኛል፡፡ ዘመን ዘመነኛ ጨቋኞችን እያስነሳ በግፍ ላይ ግፍ ሲደራረብ እዚህ ደርሰናል፡፡ የግፉ ጽዋ በምድረ ኢትዮጵያ ሞልቶ ቢፈስም ፈውስ ማግኘት ግን አልቻልንም፡፡ የኢትዮጵያ እናቶች እንባ ጸባኦት ደርሶ የአምላክን ቁጣ መቀስቀስ አልቻለም፡፡ ዘመነኛው ጨቋኝ <<ብሶት ወለደኝ›› የሚለው ኢህአዲግ እርሱን ከወለደው በላይ የሆነ ብሶት አስረግዞናል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ለክብራቸው ሲሉ መስዋዕት የሚሆኑ፤ለውዷ ሀገራቸው ሲሉ የግፍ ጽዋውን የሚጎነጩ፤በሰላማዊ ትግል ከሀገሪቱ እምብርት አዲስ አበባ እስከ ኢትዮጵያ ጫፍ የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም ዱሩ ቤቴ ብለው ኢህአዲግ በሚያውቀው ቋንቋ ውረድ እንውረድ ብለን እናነጋግረዋለን የሚሉና ሽፍታው ህወሀት የተከተለውን የስልጣን መፈናጠጫ መንገድ የጀመሩ አልጠፉም፡፡ በአሁኑ እንቅስቃሴያቸው የሁለቱም ትግል ግን የኢህአዲግን መንበር በቀላሉ የሚነቀንቀው አይነት አይደለም፡፡ ዱሩ ቤተ ያሉት ይህን ያክል ዘመን አንድ ወረዳ እንኳን ነጻ ሳያወጡ ለኢህአዲግ የአፈና ስርዓት መጠናከር የራሳቸውን ድርሻ ከመወጣት ያለፈ ፋይዳ ሲኖራቸው አይታይም፡፡ ግንቦት ሰባት ካሰባሰበው ሽምቅ ተዋጊ ይልቅ ኢህአዲግ ግንቦት ሰባት ብሎ ቃሊቲ ያወረዳቸው ሰዎች በቁጥር ይልቃሉ፡፡ አሁን አሁን አመራሩም አልቀረለትም፡፡ ኦነግ ሚኒሶታ ሆኖ በጮኸ ቁጥር እስር ቤቱ ሁሉ በኦሮምኛ ተናጋሪ ይጥለቀለቃል፡፡ የድርጅቱ ጀማሪዎች እንኳን የማያስታውሱትና እስትንፋሱ ህቅ ብላ የጠፋችው አርበኞች ግንባር እንኳን ስንቱን የጎንደር ወጣት ለመግረፍ አገልግሏል፡፡ የሕወሀት የጡት አባት የሆነው ሻዕቢያ እንኳ ሳይቀር ‹‹የሻዕቢያ ተላላኪ ለሚል›› መወንጀያነት ታገለግላለች፡፡ ፈረንጆቹ አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ላለማድረግ ከፈለግክ ሁሉም ነገር ምክንያት ነው እንደሚሉት አይነት፡፡ አካፋውን ለባልንጀራው ላለማዋስ የፈለገ ሰው እንዲህ አይነት ምክንያት ቢሰጥ እንደማለት ነው፡፡ አካፋየን አላውስህም ምክንያቱም ‹‹ነገ የቻይና ነጋዴዎች ከአሜሪካ ነጋዴዎች ጋር የምክክር ጉባኤ ስላላቸው›› አይነት ያልተገናኝቶ ምክንያት፡፡ በሌላ ረድፍ ብሶቱ ያንገሸገሻቸው ኢትዮጵያውያን በየአቅጣጫው የኢህአዲግ ግፍ እየተጋቱ ይገኛሉ፡፡ በየ ማጎሪያው ያለውን የግፉ ዘግናኝነት አይደለም ለመክፈል ለመስማት እንኳ ከባድ ያደርገዋል፡፡ ከፖለቲከኛ እስከ ጋዜጠኛ፤ከሀይማኖት መሪ እስከ ተማሪ ድረስ በየስርቻው የኢህአዲግን ዘግናኝ ጽዋ የሚቀምሱ ኢትዮጵያውያን እስር ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ በጣም የሚያሳዝነውና እንደ ሀገር የሚያሽማቅው ደግሞ ወላጆቻቸውን በእስር ምክንያት ያጡ ህጻናት የሚማሩበት ደብተር እንኳ ሲቸግራቸው ማየት ነው፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ የምወስደው በአንድ ወቅት ከጓኞቸ ጋር በመሆን የተወሰኑ የሕሊና እስረኞችን ቤተሰቦች ለመጎብኘት ሙከራ አድርገን ነበር፡፡ የእነዚህ የህሊና እስረኞች ልጆች በሚያሳዝን አኳሃን ፍዝዝ ብለውና አመድ ውጧቸው ማየት እንዴት ያማል መሰላቹ፡፡ ያለ አባት እንዲያድጉ የተፈረደባቸው ህጻናት ነገ የሀገራችን መልካም ዜጋ የማፍራት ምኞታችንስ ምን ያክል ያሳካል፡፡ በአንድ ወቅት የአቶ አስገደ ልጆችን መታሰር ምክንያት አድርገው ፕሮፌሰር መስፍን በአንድ ጋዜጣ ላይ ከኦሪት ዘመን የባሰ ህግ ብለው ነበር፡፡ በኦሪት ዘመን እንኳን አባት ባጠፋ ልጅና ቤተሰብ አይጎዳም ነበር፡፡ ከኦሪት የባሰው ኢህአዲግ ግን እስክንድርን አስሮ ልጁ ናፍቆትን ማሳደጊያ ያሳጣዋል፡፡ ቤት ንብረቱን በመውረስ ጎዳና ላይ እንዲወድቅ ያደርጋል፡፡ መቸም ይህን መረን የለቀቀ አምባገነንነት አንዳች የሚገታ ታኮ ካልተደረገለት የማያሳየን የግፍ አይነት አይኖርም፡፡ በአንድ ወቅት በእኔ ህግ መተላለፍ ሳይሆን በኢህአዲግ ፍርሀት ምክንያት ለሁለት ሳምንታት ያክል ታስሬ ነበር፡፡ በእነዚህ የእስር ቀናት ውስጥ ያዬሁትን አፈናና ለአቅመ ችሎት የማይደርስ ውሽልሽል ክስ በኮሜዲ ድራማ እንኳን ያጋጥመኛል ብየ አስቤው አላውቅም፡፡ ‹‹የታሸገ ውሃ እናስገባለን ብለው ጠይቀዋል›› የሚል ክስ እስከማቅረብና ዳኛውም እህ ብሎ በመስማት ለማጣሪያ ብሎ የሶስት ቀን ቀጠሮ ሲሰጥ ሳይ በእስር ቤቱ ግድግዳ ላይ ተጽፎ ያየሁትን ‹‹ገንዘብ ሲናገር ህግ ዝም ይላል›› አይነት አባባል እውን ሆነልኝ፡፡ እስከተከፈላቸው ድረስ ህሊና ለሚባለው ነገር ግድ የሌላቸው የጸጥታ አካላት፤ክፍያቸውን እንጅ ቃል የገቡለትን የዳኝነት ስነ-ምግባር የማያስታውሱ ጥቁር ጋዎን አጥላቂ ዳኞች፤ከሀገር ደህንነት ይልቅ የግለሰብን ስብዕና ለመጠበቅ ሲታትሩ የሚስተዋሉ ደህንነቶች ከምድረ ኢትዮጵያ ውጭ ከወዴት ማግኘት ይቻላል፡፡ ተቃዋሚነትን እንደ ጠላትና የሀገር ጠልሰም ፈርጆ የሚለፍፍ ስርዓት፤ከሀገር ልዕልና ይልቅ ስልጣን የሚያሳብደው መሪ፤ከሁለትዮሽ ጥቅም ይልቅ መጎናበስን የተከተለ የውጭ ግንኙነት እና ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍ የሚፈጸምባትን ሀገሬን ለመታደግ ለምን ዝም አልን፡፡ ፈሪዎች ስለሆን ይሆን ወይስ ‹‹ገንዘብ ሲናገር ህግ ዝም ይላል›› የሚለው አባባል እኛንም ስለሚመለከት፡፡ ኢትዮጵያ ትቅደም!!!

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop