የቅ/ጊዮርጊስ አካሄድ አስፈሪ ሆኗል

የዘንድሮው የውጭ ተጨዋቾች ግዢ ስኬታማ ተብሎለታል
ሊጉ ሲጀመር ፈፅሞ ባልጠበቁት ሁኔታ ከደረጃው ግርጌ ስር የተቀመጡት ጊዮርጊሶች ሻምፒዮናነት በለመደው ቤታቸው የተከሰተ ዱብ ዕዳ ስለነበር ሁሉም ተደናግጠዋል፡፡ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ብቻ ሳይሆን በሜዳው ላይም ተደጋጋሚ ሽንፈትን ማስተናገዱና የቡድኑም ጥንካሬ በእጅጉ በመውረዱ በብዙሃኑ የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊዎች ስሜት ሀዘን ለመቀመጥ ተገዷል፡፡ በአንፃራዊነት ዘንድሮ ለሻምዮናነት የተሻለ ግምት የተሰጣቸው ክለቦች በነጥብ ርቀው መሄድ ልዩነቱን የበለጠ እንዲሰፋ አድርጎታል፡፡ በሂሳብ ስሌትም ጊዮርጊስ እያስመዘገበ የሚገኘው ውጤት ማነስና የሌሎች ፈጥኖ መሄድ ክፍተቱን ስላጎላው የተወሰኑ ደጋፊዎች ከስታዲየም ለመራቅ የተገደዱበት ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ በተደጋጋሚ የሻምፒዮናነት ክብር ያሳያቸው ቡድናቸው በዚህ ሁኔታ ሲዳከም ማየትን ስለማይመርጡ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የብዙሃኖች ጥያቄ ቢሆንም ለተወሰነ ጊዜ ምላሽ ያላገኘው ጊዮርጊስ ምን ነክቶት ነው? የሚል አንገብጋቢ ጥያቄ በወቅቱ በእጅጉ አነጋጋሪ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ ሁሉም የየራሳቸውን መላ ምት ሰንዝረዋል፡፡ ከውጤቱ ጋር በተያያዘም ዘንድሮ ኃላፊነቱን በተረከቡት ጣሊያናዊ አሰልጣኝ ዶሴና ላይ ጣታቸውን የቀሰሩም አልታጡም፡፡ ከግንዛቤ አኳያም በዘንድሮው ስኳድ ከቡድኑ በጉዳትና በቅጣት የተለዩ ተጨዋቾች ጉዳይም ለቡድኑ ውጤት ማሽቆልቆል እንደምክንያትነት ተነስቷል፡፡ ምንም እንኳን በክለቡ ላይ የተፈጠረው የውጤት ቀውስ የደጋፊውን ያክል የክለቡን አመራሮችም የሚያሳስብ ጉዳይ ቢሆንም የተነሱትን ችግሮች ተንተርሶ የክለቡ አመራር እርምጃ ለመውሰድ አልተጣደፈም፡፡ ከዚህ ይልቅ ያሉትን የውስጥም ሆነ የውጭ ችግሮችን ከማጥናቱ ጎን ለጎን ቡድኑ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ክፍተት በሚታይባቸው ቦታዎች ላይ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾችን ከውጭ ሀገር አስሶ ማምጣት በለውጡ አጀንዳ ስር የተያዘ ጉዳይ እንደነበር አመራሮች ይናገራሉ፡፡
ምንም እንኳን ከጊዜያዊ ውጤት መያያዘ ጋር የአሰልጣኙ ብቃትን የሚጠራጠሩ አንዳንድ ወገኖች የነበሩ ቢሆንም ከፍተኛ የሆነ የስልጠና ሲቪና በአፍሪካ ደረጃ እነ ጋናን የመሳሰሉ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድኖችን እንዲያሰለጥኑ ኃላፊነት በተሰጣቸው ጣሊያናዊው ዶሴና ላይ የክለቡ ኃላፊዎች እምነት ነበራቸው፡፡ ከዚህ አንፃር በግብታዊነት ከመወሰን ይልቅ የተፈጠሩትን ችግሮች በሂደት በማስተካከል ለአሰልጣኙ በቂ ጊዜ በመስጠት አቅማቸውን የመፈተሽ ሁኔታን በተሻለ አማራጭነት እንደተቀበሉት ነው የሚነገረው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ተጨዋቾቹ ለውጤቱ መታጣት ጣሊያናዊው ሙያተኛ የሚሰጧቸው ታክቲካል ዲሲፕሊን ከእነርሱ አጨዋወት ጋር አለመጣጣሙን እንደ ምክንያት ሲያቀርቡ ተደምጧል፡፡ ከዚህም አንፃር የቡድኑ ተሰላፊዎች የሚያነሱት የተባለውን ያክል ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል ወይ? የሚለው አጀንዳም በአግባቡ እንደተፈተሸ ነው የሚነገረው፡፡ ክለቡ ሃያል ከመሆኑ አንፃር በሂደት እያጣ የሚገኘው ውጤት ደጋፊዎቹን ማረጋጋት ያልቻለ ቢሆንም ለመሰረታዊ ለውጡ ትግበራ ደጋፊው ትዕግስት ማድረግ አለበት የሚለው መሰረታዊ እምነት በክለቡ አመራሮች ላይ አድሮ እንደነበር ተገልጿል፡፡ አሰልጣኝ ዶሴናም የክለቡን የቀድሞ ውጤታማነት ጠንቅቀው ስለሚያውቁት በወቅቱ የተፈጠረውን ችግር መስመር ለማስያዝ ጠንክረው ለመስራት ቃል ከመግባታቸውም በላይ ለክለቡ ኃላፊዎች ከጊዜ በኋላ የቅ/ጊዮርጊስ ውጤታማነት ተመልሶ ደጋፊውና የክለቡ ኃላፊዎች የሚናፍቁትን ለውጥ ለማሳየት ቃል መግባታቸው አይዘነጋም፡፡ በተለይ ደጋፊው ክለባቸው በደረጃ ሰንጠረዥ በ16ኛ ላይ ይገኛል የሚለው ዜና ለጆሮአቸው በእጅጉ የሚዘገንን ወሬ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ በመሆኑም የጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤቶቹ የክለቡ አመራር፣ ተጨዋቾችና አሰልጣኞቹ ለለውጥ የጋራ ምክክር ከማድረግም ባሻገር እንደ ችግር የተነሱ ድክመቶችን ለማረም በስፋት መንቀሳቀሳቸው ተነግሯል፡፡
ከዚህ በኋላ የቅ/ጊዮርጊስ ቡድን ከጊዜ ወደ ጊዜ የፈጠነ ባይሆንም በወቅቱ ለተፈጠረው የውጤት ቀውስ የመፍትሄ መንገድ የሚያመላክት ውጤቶችን ማስመዝገብ ጀመረ፡፡ ቡድኑ ክፍት በሚታይበት ቦታ ላይም ተገቢውን ሚና ይጫወታሉ የሚል እምነት የተጣለባቸው አራት የኡጋንዳና አንድ የጋና ተጨዋቾች ክለቡን እንዲቀላቀሉ ተደርጓል፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ ተጨዋቾች የመጡት የአንደኛው ዙር የሊጉ ውድድር ሊገባደድ ሲል ቢሆንም በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ያልመተዘገበ ተጨዋች ህጋዊነትን ማግኘት ስለማይችል ተጨዋቾቹ በጊዮርጊስ ማሊያ ወደ ሜዳ ለመግባት የግዴታ ሁለተኛው ዙር እስኪጀመር መጠበቅ ነበረባቸው፡፡
በሁለተኛው ዙር እነዚህን ተጨዋቾች በቡድኑ ውስጥ ያካተተውና በመፍትሄ አካሄዱ ላይ ተጨባጭ ለውጥ መያዝ የቻለው የቅ/ጊዮርጊስ ቡድን በሂደት እያሳየ የመጣው ለውጥ የደጋፊዎቹን ፍርሃት ያንዣበበትን ስጋት እየቀረፈ ለመሄድ ችሏል፡፡ በዚህ መሰረትም በሁለተኛው ዙር ያደረጋቸውን አራት ጨዋታዎች በአጠቃላይ በማሸነፍ 12 ነጥብ ማሰባሰብ በመቻሉ ከ16ኛ ደረጃ በመውጣት የአራተኛ ስፍራ ላይ ከመቀመጡም ባሻገር ዘንድሮ ለሻምፒዮናነት ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው መከላከያ፣ ኢትዮጵያ ቡናና ደደቢት የነጥብ ጎራ ውስጥ መቀላቀል ችሏል፡፡ ከዚህም በላይ ቡድኑ አሁን ባሰባሰበው ነጥብ አራተኛ ስፍራ ላይ የተቀመጠው ሶስተኛ ደረጃ ከሚገኘው የደደቢት ክለብ እኩል ነጥብ አሰባስቦ ብዙ ባገባ በሚለው መለያ ነው አንድ ደረጃ የተንሸራተተው፡፡ በፊት የነበረውን ሁኔታና አሁን እየታየ ያለውን ለውጥ የተመለከቱ የክለቡ ደጋፊዎች የቡድኑ የፈጠነ አካሄድን ከግምት በማስገባት ዛሬ ዛሬ ሻምፒዮናነታቸውን ማለም ጀምረዋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከምስረታ አንጋፋነቱ በተለየ ሁኔታ ለበርካታ የውድድር ዓመታት የሻምፒዮናነትን አክሊል የደፋ ሲሆን አሁን አሁን በስፋት ሌሎች ክለቦችም እየተጋሩ ያሉትን የውጭ ተጨዋቾችን ግዢ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገ ክለብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጊዮርጊስ በተለያየ ጊዜ የውጭ ሀገር ተጨዋቾችን ወደ ሀገር ቤት ቢያስመጣም በአንዳንድ የቡድኑ ተሰላፊዎች ብቃት ላይ ጥያቄ የሚነሳበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር፡፡ ነገር ግን ዘንድሮ ክለቡን የተቀላቀሉት ተጨዋቾች ከጀምሩ እያሳዩ የሚገኘው ብቃት የብዙሃን ስፖርት ቤተሰቦች ይሁንታ ማግኘት የቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ተጨዋቾቹ ካላቸው ተክለ ሰውነት ጀምሮ በትንፋሽ ረገድ ያላቸው ብቃትና የተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮችን በማስጨነቅ ረገድ ያላቸው ተሰጥኦ ከጊዮርጊስ ደጋፊዎች ባሻገር የሌሎች ክለብ ደጋፊዎችን ሳይቀር አድናቆት በጊዜ ያገኙ ይመስላል፡፡ በተለይ በተመላላሽ ቦታ የሚጫወተው ሱላ ማዳቪ፣ ተከላካዩ አይዛክ ኤሴንዴና ግዙፉ ግብ ጠባቂ ሮበርት አቦን ማካራ የጊዮርጊስን ስኳድ በማጠናከሩ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በሁለተኛው ዙር ቡድናቸውን በየአቅጣጫው ለማጠናከር ቆርጠው የተነሱት ጊዮርጊሶች በተለይ የተከላካይና የአጥቂ ክፍላቸው ላቀዱት የሻምፒዮናነት ጉዞ ተስፋ ሰጪ ቢመስልም የቡድኑ የመሀል ክፍል ግን አሁንም የተጠበቀውን ያክል አለመሆኑ አንዳንዶች ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ይሄን ክፍተት ለመድፈን ከሚኬሌ ከቅጣት መመለስ በተጨማሪ ከወጣት ቡድን ያደገውና አሁን ከጉዳቱ ያገገመው የኤልያስ ወደ ቡድኑ መመለስ ተስፋ እንደሚሰጣቸው ጊዮርጊሶች በፅኑ ያምና፡፡ ደጋፊዎቹም በሁለተኛው ዙር ቡድናቸው ያሳየው ከፍተኛ መሻሻል በአንደኛው ዙር ገጥሟቸው ከነበረው ሀዘን መሻሪያ እንደሆነላቸው ይናገራሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከጊዜ ወደ ጊዜ የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ እየገዛ የሚገኘው የ2003 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳትፎና ፉክክር አጓጊነቱ የበለጠ ጨምሯል፡፡ በተለይ የሻምፒዮናነት ቅድሚያ ግምትን የወሰዱት መከላከያ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢትና ቅ/ጊዮርጊስ አሁን ያላቸው የተሳሰረ የነጥብ ልዩነት የዘንድሮውን የሻምፒዮናነት ምዕራፍ የስፖርት ቤተሰቡ በጉጉት እንዲጠብቀው አድርጎታል፡፡ ከዚህ በኋላ ሁሉም ቡድኖች ከፊታቸው 12 የሊጉ ጨዋታ የሚቀራቸው ሲሆን ግምቱ በከፍተኛ ደረጃ ያጋደለላቸው የአራቱ ክለብ ተሰላፊዎች ‹ዋንጫውን እኛ እንወስደዋለን›› በማለት ይናገራሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቫን ኒስቴልሮይ ማላጋ ገባ
Share