የሎሬት ህመሙ ቢያመኝ …
———–//———
ይሞላ ብዪ ስኳትን ፣
ህልሜ እልም እያለ ቢፈትነኝ
ለህሊናየ አድር ብዪ ስማስን ፣
ድካሙ ቢሸበርክኝ
ተስፋ አልቆርጥም ባልኩ በተጋሁ፣
ህመሙ ቢደቁሰኝ
ብላቴን ጌታ ታወሰኝ ፣
ጸጋየ ህመሙ ዘልቆ ወጋኝ
የጸጋየ ህመሙን ታመምኩ
መላ ቅጡን አስጠፋኝ ።
ውስጤ ቢደማ ቢታወክ ፣
የጸጋየ ሮሮ በአይነ ህሊናየ መጣብኝ
የመጨረሻው እስትንፋስ ቃሉ ፣
ሎሬት ህመሙ አመመኝ
“እኔ ለእኔ ኑሬ አላውቅም ” ብሎ ያለን
የስንብት ጸጸት ቃሉን አዘከረኝ ፣
……. …….. ……. ……… …….. ……
የጸጋየ ጸጸት …
“የማይሰማ ወጨት ጥጄ –
እፍ ስል የከሰመ ፍም፣
ውርዴም ይፈወሳል ብዬ –
የሰው እከክ ስዘመዝም፣
በሰው ቁስል መቁሰል በቀር –
እኔ ለኔ ኖሬ አላውቅም፡፡
የማይነጋ ህልም ሳልም –
የዘመን ደዌ ሳስታምም፣
የማያድግ ችግኝ ሳርም –
የማይድን በሽታ ሳክም፣
የሰው ህይወት ስከረክም –
እኔ ለኔ ኖሬ አላውቅም፡፡ ”
…… …….. ……. …….. …… ….. ……
ባይሰማ ባያየኝ አባት አለም ፣
ተስፋው በኖ የተለየንን
የቅኔው አባት መምህሩን ፣
የጥበብ ሎሬት ፈላስፋውን
ድካም ልፋቱ መና ቀርቶ የታየውን ፣
“ግዴለም በተስፋ እንኑር አልኩት !” ጸጋየን
መላው ጠፍቶ ቢጨንቀኝ ፣
በተስፋ እኖር መስሎኝ ሳታልላት ደካማ ነፍሴን …
* ብላቴን ጌታ ጸጋየ ፣ ነፍስህን አራያ ገነት ያኑራት: (
በተጎዳ ስሜት … ይህችን ታክል ካልኩ ይብቃኝ! :(
ነቢዩ ሲራክ