June 17, 2014
44 mins read

ኮካ ኮላ የተባለው መጠጥ አጠገቤ አይደርስም! (ፕ/ር አለማየሁ ገብረማርያም)

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

ኮካ ኮላ ትክክለኛ ነገር አይደለም!

የኮካኮላ ኩባንያ በታዋቂው የኢትዮጵያ ኮከብ ድምጻዊ ሙዚቀኛ በሆነው በቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ላይ ያደረገውን ስነምግባርን የጣሰ፣ የዘፈቀደ እና ፍትሀዊ ያልሆነ ድርጊት በማስመልከት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ በማህበራዊ እና በመገናኛ ድረ ገጾች ተቃውሞውን በመግለጽ የኮካ ኮላ ምርት እንዳይጠጣ ጥሪውን በማስተላለፍ ላይ ይገኛል፡፡ የዲያስፖፈራው ማህበረሰብ በማያያዝም የኮካ ኮላ ኩባንያ ተንኮልን ባዘለ መልኩ ቴዲን ነጥሎ በማውጣት የአድልኦ ሰለባ እንዲሆን አድርጓበታል በማለት ላይ ነው፡፡ የኮካ ኮላ ኩባንያ 32 የልዩ ልዩ አገሮች ሙዚቃ የቡድን አቀንቃኞችን ለብራዚል የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽን/FIFA ዋንጫ የመክፈቻ ስነስርዓት ማድመቂያ ሙዚቃ አንድያቀነባበሩ አድርጎ ነበር፡፡ የኮካ ኮላ ኩባንያ በቴዲ አፍሮ ከተቀነባበረው የኢትዮጵያ ሙዚቃ በስተቀር የሁሉንም ዓይነት መሰል ሙዚቃዎች ለቅቋል!

አሁን የኮካ ኮላ ምርት እንዳይጠጣ የሚለውን መርህ እቀላቀላለሁ፡፡ ባለፉት ስምንት ዓመታት ሳቀርባቸው የነበሩትን ትችቶቸን ስትከታተሉ ለቆያችሁ በሚሊዮኖች ለምትቆጠሩ አንባቢዎቸ አሁን የኮካ ኮላ ምርት እንዳይጠጣ የሚለውን ቡድን እንድትቀላቀሉልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

የኮካ ኮላ ኩባንያ እና ተወካዮች በቴዲ ላይ ስህተት የፈጸሙ መሆናቸውን ከጥርጣሬ በላይ ተገንዝቢያለሁ፡፡ ስሙን አጥፍተዋል፣ ስብእናውን ዝቅ አድርገዋል እናም በአደባባይ በህዝብ ፊት አዋርደውታል፡፡ ይዞት የቆየውን ዝና እና ክብር ነፍገዋል፣ ስሙን ጥላሸት ቀብተዋል፣ እናም በስራው እና በጥሩ ስነምግበሩ ተጎናጽፎት የቆየውን ጥሩ ስሙን አጉድፈዋል፡፡ ፍትሀዊ ያልሆነ፣ ጨካኝነት የተሞላበት እና የሞራል ስብዕናን ባልተላበሰ ሁኔታ አስተናግደውታል፡፡

እ.ኤ.አ ጁን 7/2014 የኮካ ኮላ ኩባንያ ተወካይ የሆኑ ባለስልጣን የተናገሩትን ዘገባ በመጥቀስ እንደሚከተለው ቀርቧል፣ “ለፊፋ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ‘ዓለም የእኛ ናት‘ የሚለውን የኢትዮጵያ ልዩ ሙዚቃ ለማቅረብ ዓላማ በማድረግ ዜማውን እንዲያቀርብ እና እንዲቀረጽ እዚህ እኛ የኮካ እስቱዲዮ ድረስ ወደ አፍሪካ እንዲመጣ ተደርጎ ነበር፡፡ ከቴዲ አፍሮ ጋር የተደረገው የኮንትራት ስምምነት ‘ማንዳላ የተወሰነ’ በተባለ መቀመጫውን በናይሮቢ ያደረገ በሌላ ሶስተኛ አምራች ወገን የተፈጸመ ሲሆን ቴዲ አፍሮም ላደረገው ጥረት ሙሉ ክፍያ ተሰጥቶታል፡፡“ የባለስልጣኑ መግለጫ በመቀጠልም እንዲህ ይላል፣ “የድምጽ ቀረጻው ከተጠናቀቀ በኋላ ኮካ ኮላ ሴዋ የተባለ ኩባንያ የሚያዝዝበት የግል መጠቀሚያ ንብረት ነው፣ ሆኖም ግን ሙዚቃው እስከ አሁን ድረስ አልተለቀቀም፣ እናም በአሁኑ ጊዜም እንኳ ሙዚቃው ይለቀቃል የሚል ዕቅድ የለም፡“ በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡

እ.ኤ.አ ጁን 10/2014 በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የቴዲ አፍሮ ተወካይ ባለስልጣን የኮካ ኮላን አስደንጋጭ አዋጅ በማወጅ እና ቴዲ አፍሮ ሙያዊ ያልሆነ ባህሪ አሳይቷል በማለት በኮንትራት ስምምነቱ በግልጽ በተቀመጠው አንቀጽ መሰረት እምነትን የሚያጎድል ድርጊት ሲፈጸም ለህዝብ እንዳይለቀቅ የሚከለክል እንደሆነ አሳውቀዋል፡፡ መግለጫው በማያያዝም የኢትዮጵያን የዓለም ዋንጫ ልዩ ሙዚቃ ላይ ኮካ ኮላ ያልተገደበ ክልከላ ያደረገበትን ምክንያት ለማወቅ እኛ ጉዳዩን በድረ ገጽ ይፋ ከማድረጋችን በፊት ለእነርሱ ብናቀርበውም እስከ አሁን ድረስ ምንም ዓይነት ምላሽ ያለመስጠቱ እንቆቅልሽ ግራ እንዳጋባው ገልጿል፡፡ በዚህም መሰረት የኮካ ኮላ ኩባንያ መጥፎ እምነትን በማራመድ፣ እና “የእራሱን የኮኩባንያ የጽናት፣ የታማዕኒነት፣የህዝብ እምነት እና በእራስ የመተማመን መርሆዎች” በይፋ በመደፍጠጥ “በኩባንያ እብሪት” ተዘፍቆ ይገኛል በማለት ክስ አቅርቦበታል፡፡ የኮካ ኮላ ኩባንያ “የሚያዋርድ፣ የአድናቂዎቻችንን ስሜት እና የኮካ ኮላን ደንበኞች የሚጎዳ መግለጫ በመስጠቱ የተሰማውን ሀዘን ገልጿል፡፡

የቴዲ አፍሮ ተወካይ የኮካ ኮላን ፍረጃ ሙሉ በሙሉ እንዲህ በማለት ውድቅ አድርጎታል፣ “ከቴዲ አፍሮ ጋር የተፈጸመው የኮንትራት ስምምነት ማንዳላ የተወሰነ/Manadala Limited በተባለው በናይሮቢ የሚገኝ የምርት ተቋም ሶስተኛ ወገንተኝነት አማካይነት ነው፡፡“ አቶ ምስክር ሙሉጌታ [የኢትዮጵያ እና የኤርትራ እንዲሁም የማናዳላ ቲቪ ብራንድ ማናጀር] የተባሉ የኮካ ኮላ ተወካይ ባለስልጣን እኛን ከቀረቡን በኋላ ተነሳሽነቱን በመውሰድ የኮካ ፕሮጀክትን ምርጫ እና በቀጣይነትም እኛን ወደ ኮካ ስቱዲዮ በማምጣት የኮካኮላ ማዕከላዊ፣ የምስራቅ እና የምዕራብ አፍሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ከማንዳላ ቲቪ ጋር የኮንትራት ስምምነት እንድንዋዋል አድርገዋል…” አቶ ምስክር እንደ ሰራተኛ እና ማንዳላ ቲቪ ደግሞ እንደ በርካታ የሙዚቃ ንብረት አገልግሎቶች ኃላፊ ለኮካ ኮላ ማዕከላዊ፣ የምስራቅ እና ምዕራብ አፍሪካ ተወካይ በመሆን በአንድ ዓይነት የህግ ማዕቀፍ እና በኮካ ኮላ ኩባንያ ላይ ለሚያስከትለው እንደምታ ዋና መስሪያ ቤቱን በአትላንታ ያደረገውን ተቋም በመወከል የተደረገ የኮንትራት ስምምነት ነው፡፡”

እንደዚሁም ደግሞ በኮካ ኮላ መግለጫ ላይ ጉልህ የሆኑ መጣረሶች የተስተዋሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ የኮካ ኮላ ኩባንያ ከቴዲ አፍሮ ጋር ምንም ዓይነት የኮንትራት ስምምነት ግንኙነት ባይኖረው ኖሮ በእርሱ ላይ ያነጣጠረ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ለምን አስፈለገው? በሌላም በኩል ኮካ ኮላ ቴዲ አፍሮ “ላደረገው ጥረት ሙሉ ክፍያ ተፈጽሞለታል” ብሏል፣ እንዲሁም የኮካ ኮላ ኩባንያ ከቴዲ አፍሮ ጋር የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ማድመቂያ ሙዚቃን ለማሰቀረጽ የኮንትራት ስምምነት ባይኖረው ኖሮ “የተቀረጸው ሙዚቃ የኮካ ኮላ ሴዋ/Coc-Cola CEWA ንብረት ነው ማለት ለምን አስፈለገው?”

ኮካኮላን የዓለም እግር ኳስ የዋንጫ ጨዋታ ማድመቂያ የሆነውን ልዩ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በይፋ እንዳይለቅቀው ያስገደደው ተቃውሞ ምንድን ነው?

ለዓለም የእግር ኳስ የዋንጫ ጨዋታ ማድመቂያ በወጣው የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ግጥም እና ቅላጼ ላይ ምንም ዓይነት የፖለቲካም ወይም ሌላ አወዛጋቢ ጉዳይ የለበትም፡፡ በእርግጥ ቴዲ ኮካ ኮላ ዴቪድ ኮሬይ አንዲገጥም ባደረገው ግጥሞች ውስጥ ቃላትን በቀጥታ ወስዶ “ዓለም የእኛ ናት” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተርጉሞ ነበር ያቀርበው፡፡ ሌላ የጨመረውም ሆነ የቀነሰው ነገር የለም፡፡

ቴዲ አፍሮ ከ32 የዓለም የሙዚቃ ጥበብ ባለሙያዎች ለምንድን ነው እንዲነጠል የተደረገው እና የኮካ ኮላ የማዋረድ እና የዘለፋ ኢላማ እንዲሆን የተዳረገው? ኮካ ኮላ ለምንድን ነው የኢትዮጵያን ልዩ የቴዲ ሙዚቃ በአደባባይ ለመልቀቅ ያገደበትን ምክንያት? ለቴዲ ለግሉ ለመገለጽ ፈቃደኛ ያልሆነውስ? ኮካ ኮላ ለምንድን ነው ጉዳዩን ግልጽ በማድረግ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩት የቴዲ አድናቂዎች የኢትዮጵያ ልዩ ሙዚቃ እንዳይወጣ የተደረገበትን ምክንያት ለመናገር ያልፈለገው?

ኮካኮላን ለምን እደምማስወግደው፣

የኮካ ኮላ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ የኢትዮጵያን ልዩ ሙዚቃ ላለመልቀቅ ያወጣው ይፋ የተቃውሞ መግለጫ ለቴዲ አፍሮ ጠላቶች የደስታ እና የደረት ድለቃ ምንጭ ሆኗል፡፡ በድል አድራጊነት እንዲህ በማለት ድሰታቸውን ገልጸዋል፣ “ኮካ ኮላ ቴዲን አሽቀንጥሮ ጣለው!“

ኢንዱስትሪዎች መርዛማ ኬሚካሎችን ወደ ቆሻሻ መጣያ ቦታ እደሚጥሉ ሁሉ እኔም እንደዚሁ ኮካ ኮላን ወደ መርዛማ የኬሚካሎች ቆሻሻ መጣያ ቦታ ጥየዋለሁ፡፡ ይህንን ተመሳስሎ አነጋገር በቀላሉ የምጠቀምበት አይደለም፡፡ “የኮካ ኮላ ኩባንያ ካንሰር አምጭ በሆኑት ፋንታ ፒንአፕል እና ቫውልት ዜሮ ቤንዚን (በሁለት ምርቶቹ ላይ) ያለውን መጠጦች በህግ ተከሶ በስምምነት ጉዳይዩን እልባት ሰጥቷል፡፡“ ኮካ ኮላ 114 የምርት ዓይነቶችን በእንግሊዝኛ ቋንቋ አኳፑሬ ከሚለው ጀምሮ ዚኮ እስከሚለው ድረስ ድረ ገጹ ላይ ይፋ አድርጓል፡፡

አሁን 114 ምርቶቹን ላለመጠቀም የማይለወጥ ዉሳኔ አድርጌአለሁ፡፡ አኳፑሬን፣ ባርቅን፣ ኮካ ኮላን፣ ዳሳኒን፣ ኢቪያንን፣ ፉዝን፣ ጋላሴኡን፣ ቪታሚን ዋተርን፣ ሐይ-ሲንን፣ ኢንካኮላን፣ ጀሪኮንን፣ ኪንሌይንን፣ ሊፍትን፣ ሚኑት ሜይድን፣ ኖርዘርን ኔክን፣ ኦዱዋላን፣ ፓዎሬድን፣ ሬድ ፍላሽን፣ ስፕራይትን፣ ታብን፣ ቫውልትን፣ ወርክስ ኢነርጅን፣ ዚኮን… አነዚህን መጠጦች በምንም ዓይነት ሁኔታ አልገዛም ወይም በምንም ዓይነት መንገድ አልጠቀምም፡፡ ማንም ቢሆን እነዚህን ምርቶች እንዲገዛ ወይም እንዲጠቀም አላደፋፍርም ወይም ደግሞ ሀሳብ አላቀርብም፡፡ በዚህም እውነታ መሰረት በዓለም ላይ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አንባቢዎቼ እነዚህን ምርቶች እንዳይገዙ ወይም ደግሞ እንዳይጠቀሙ በአክብሮት እጠይቃለሁ!

ሁላችንም አንድ በመሆን እንተባበር እና ኮካ ኮላን እና 114 የሚሆኑ ምርቶቹን ባለመጠቀም ከገበያ ውጭ እናድርጋቸው፡፡

ለአስርት ዓመታት የኮ ካላ ኩባንያ ምርቶቹን በደስታ እና የደስታ ስሜት በተቀላቀለበት ዓይነት ሁኔታ እና መፈክሮችን ሊረሱ በማይችሉ ቃላት በማሽሞንሞን የኮርፖሬት ንግዱን ሲካሄድ ቆይቷል፣ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት እና አጠቃላይ የንግድ እሴቶቹን ሲያስተዋውቅ ቆይቷል፡፡ ባለም የተሰራጩት መፈክሮቹ እንዲህ ይላሉ፣ “ኮካ፡ እውነተኛ ነገር ነው“፣ “ከኮካ ጋር ነገሮቸ ሁሉ የተሻሉ ይሆናሉ“፣ “በአሁኑ ጊዜ ዓለም የሚፈልገው ኮካን ነው”፣ “ኮካ ይህ ነው“፡፡ ኮካ ኮላ እንዲህ ብሎ የሚጀምር የቴሌቪዥን የንግድ ሙዚቃ አለው፣ “የተሟላ ደስታ ባለበት ሁኔታ በመዘመር ዓለምን ለማስተማር እወዳለሁ“፣

ኮካ እንደ እስፕራይት እውነት ሳይሆን ዉሸት
በኢትዮጵያ ነገሮች ኮካ መራራ ያደርጋል፣
ኮካ ኮላ በኢትዮጵያ ጥላቻ እንጅ በኢትዮጵያ ፍቅርን የሚያመጣ አይደለም፣
ኮካ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እድሜ ሳይሆን ጥላቻ ነው የጨመረው፣
ኮካ ኢትዮጵያውያንን ፈገግ የሚያደርግ ሳይሆን በጥላቻ እንዲሞሉ ያደረገ ነው፣
ብዙ የስኳርነት ባህሪው ስለሚያፍነኝ ኮካን አልጠጣም፣
የዓለም ህዝብ ኮካን ወይም ደግሞ ማንኛውንም 113ቱን የኮካ ምርቶች እንዳይገዛ እፈልጋለሁ፣
በአሁኑ ጊዜ የመጨረሻው እና የዓለም ህዝብ የማይፈልገው ነገር ቢኖር ኮካ ነው፣
ኮካ ዘበት ነው!

የኢትዮጵያ ታዋቂ ሙዚቃ በኩሩው የኢትዮጵያ ወፍ ሲዘመር እንዳይሰማ የተደረገበት ምክንያት ለምን እንደሆነ አውቃለሁ፣

ቴዲ አፍሮ የእራሱን ህዝብ እና አገር ይወዳል፣ ለዚህ ዓላማው አየተቀጣ ይገኛል፡፡

ውርደት ቀለቡ የሆነው እና የትንሽ ጭንቅላት ባለቤት የሆነው በኢትዮጵያ ህዝቦች ጫንቃ ላይ ከፍላጎታቸው ውጭ ተቆናጥጦ የሚገኘው ገዥው አካል ኮካ ኮላ የቴዲን ሙዚቃ እንዳይለቅቀው ተጽዕኖ ያደረገበት ለመሆኑ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ እነዚህ በበቀል እና በጥላቻ የተሞሉት ገዥ ጽንፈኛ የወሮበላ ስብስብ ቡድን የቴዲ አፍሮ ትክክለኛ ጌታው ማን እንደሆነ ለማሳየት ያደረጉት ከንቱ ምግባር ነው፡፡ እነዚህ የበቀል እና የጥላቻ ቋቶች እንዴት ባለ የማታል ዘዴ እና የተለሳለሰ በሚመስል ማደናገሪያ እየተጠቀሙ በቴዲ እና በደጋፊዎቹ ላይ እየወሰዷቸው ያሏቸውን ዕኩይ ተግባራት ለማሳየት ነው፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከኮካ ኮላ ጋር የተደረገውን አጠቃላይ ስምምነት ብልግና በተቀላቀለበት መልኩ እየሳቁ ሲመለከቱት ቆይተዋል፡፡ እንዲቀጥልም ፈቅደዋል፡፡ እንዲህም ብለው ነበር፣ “ቴዲ ከልቡ ጥረት ያድርግ እና ቆንጆ የሙዚቃ ስራ ይዞ ይቅረብ“፣ መዳፎቻቸውን በማፋተግ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ጥሩ አድርገን በመበቀል ሊረሳው በማይችል መልኩ አርአያ የሚሆን ትምህርት እንሰጠዋለን“፡፡ በእነዚህ የእኩይ ምግባር አራማጆች የደም ስሮች ውስጥ ጥላቻ እና በቀልተኝነት ተዋህደዋል፡፡

በመጨረሻዋ ደቂቃ በኮካ ኮላ በኩል የበቀል እርምጃቸውን ወስደዋል፡፡ (ኮካ ኮላ እ.ኤ.አ በ2013 ሶስተኛውን የጠርሙስ ፋብሪካ በድሬ ዳዋ ከተማ ያጠናቀቀ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡) ኮካ ኮላ ገበያውን በኢትዮጵያ ለማስፋት ከፈለገ የቴዲ አፍሮን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ማድመቂያ ሙዚቃ መልቀቅ የለበትም፡፡ ምስኪኑ ኮካ ኮላ በሰይጣኖች እና በቴዲ አፍሮ መካከል በተያዘው ጉዳይ ላይ መሳሪያ በመሆን የይስሙላ መወዛወዝን ይዞ ቀትረ ቀላል ሆኖ ይገኛል፡፡

በእርግጥ ያ ሁሉ በገዥው አካል እየተደረገ ያለው በሸፍጥ የተሞላ እርባና የለሽ ድርጊት በቴዲ አፍሮ ስብዕና ላይ የሚያመጣው ነገር አይኖርም፡፡ ቴዲ በሚመስጠው ቅላጼው “ፍቅር ሁሉን ያሸንፋል” የሚል ሙዚቃውን ማሰማቱን ይቀጥላል፡፡ “ሙሉ ይቅርታን ከማድረግ በላይ በቀል የለም” የሚለውን መርህ ነው የሚከተለው፡፡ እሱን ጥፋተኛ ያደረጉትን ይቅርታ ያደርግላቸዋል (ጃህ ያስተሰርያል!)

በኢትዮጵያ ላለው ወሮበላ ዘራፊ ቡድን ማንኛውም ተመልካች የቴዲ አፍሮን ስም ጥላሸት ለመቀባት፣ ለማበሳጨት እና የአገሪቱ ብሄራዊ የአንድነት እና የክብር መገለጫ ምልክት የሆነውን ጀግና ታዋቂ የኢትዮጵያ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ስሜት ለመጉዳት በሚያደርጉት እርባና የለሽ የስነ ልቦና ጦርነት ላይ እንግዳ ሊሆንበት አይችልም፡፡ ለበርካታ ዓመታት እነዚህን ቆሻሻ የማታለል ድርጊቶቻቸውን በተቀናቃኞቻቸው ላይ ሲፈጽሙ ቆይተዋል፣ አሁንም ይህንን እኩይ ምግባራቸውን በተጠናከረ መልኩ ይቀጥሉበታል፡፡

እውነታው ግን የቴዲ አፍሮ የኪነ ጥበብ ሙያ ለኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት የማይሞተውን ጠንካራ ፍቅር አሳይቷል፡፡ በሁሉም ሙዚቃዎቹ እና ግጥሞቹ ቴዲ የኢትዮጵያን ክብር ከፍ አድርጎ አሳይቷል፣ እንዲሁም ለወሮበላ ዘራፊዎች እና ለከሀዲዎች እውነታውን ነግሯቸዋል፡፡ የእርሱ ሙዚቃ፣ መዝሙሮች እና ግጥሞች የአውዳሚነት ጥረቶችን በማዳከም በኩል የኢትዮጵያን ህዝብ እምነት እና ሞራል ከፍ በማድረግ ውጤታማ ክስተቶችን ፈጥረዋል፡፡ ቴዲ በግጥሞቹ እንዲህ በማለት አውጇል፣ “ያዙት፣ ጠበቅ አድርጋችሁ ያዙት! እርስ በእርሳችን ይቅርታ ካደረግን እና ከተፋቀርን የኢትዮጵያ ትንሳኤ ቅርብ ነው፡፡“

ቴዲ ተያስተሰርያል በሚለው አልበሙ በቡድን የወሮበላ ስብስብ ወንጀለኞች የተያዘውን ዙፋን አጋልጧል፡፡ መዝሙሩን በመጠቀም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ሁሉም የጎሳ መሰረት ያላቸው ህዝቦች በስምምነት፣ በሰላም እና በፍቅር በአንድ ኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር በህብረት እንዲኖሩ አዚሟል፡፡ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን የሙዚቃ ክህሎት በመጠቀም የክርስቲያን እና የእስልምና እምነት ተከታዮች እጆቻቸውን በማጣመር በአንድነት በሰላም እና በፍቅር እንዲኖሩ አስተምሯል፡፡ ቴዲ የታደለውን የዓላማ ጽናት ለእኩይ ምግባር እንዲሸጥ ለማድረግ ለመቁጠር ከሚያዳግተው በላይ በርካታ ሀብት እና ሽልማት ቀርቦለት ነበር፡፡ ሆኖም ግን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ነብሱን ለወሮበላ ዘራፊዎች ለመሸጥ እንደማያስብ ጽኑ ተቃውሞ አሳይቷል፡፡

ቴዲ አፍሮ በእርሱ የትውልድ ዘመን ካሉ የጥበብ ባለሙያዎች ሁሉ የበለጠ እና የላቀ ተነሳሽነት ያለው ወጣት ከያኒ ነው፡፡ ቴዲ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን/ት ወጣቶችን ቀልብ በመሳብ ዴሞክራሲ፣ ነጻነት እና ሰብአዊ መብቶች በአንዲት ኢትዮጵያ እንዲጠበቁ እና እንዲከበሩ አነቃንቋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የእኩይ ምግባር አራማጆቹ በሙዚቃው ያሳየውን አርበኝነት ለመበቀል አሁን ያዘጋጀው ሙዚቃ እንዳይለቀቅ በመከልከል “ዋጋ” እንዲከፍል እያደረጉ ነው፡፡ የእውነትን መዝሙርን በምንም ዓይነት መልኩ ማገድ እና ጸጥ ማድረግ አይቻልም፡፡

ቴዲ የሚሸጥ ዕቃ አይደለም! ቴዲ በኮካ ኮላ ወይም በወሮበላ ዘራፊ ቡድን ባለብዙ ቢሊዮን ገንዘብ ባለቤት ቱጃሮች የሚገዛ ሸቀጥ አይደለም፡፡ እርሱን ለማዋረድ እና ለመዘለፍ መሞከር ይችላሉ፡፡ ቀላሉ እውነታ ግን ቴዲ በእራሱ እና በሀገሩ ላይ የራስ ደጀን ተራራን የሚያህል ኩራት እና ክብር ያለው ትንታግ ወጣት መሆኑን ያለመገንዘባቸው ነው፡፡ ወሮበላ ዘራፊዎች ከህዝብ በሰረቁት እና በዘረፉት ኃብት ምንም ያህል ኃብት ቢያከማቹ ማጅራት መችዎች ለዘላለም የሚኖሩ ወሮበላ ዘራፊዎች፣ በጥባጮች እና ማጅራት መችዎች ሆነው ይቀራሉ፡፡ ይህም የሚያዋርድ የቋንቋ ቃላትን መደርደር አይደለም፡፡ ይህ እንደ ቀትር ጸሐይ የበራ ኃቅ ነው!

እባካችሁ ቴዲ አፍሮ በእራሱ እና በእናት ሀገሩ ላይ ኩራት እና ፍቅር ያለው ትንታግ ወጣት በመሆኑ ምክንያት ብቻ አትጥሉት! እርሱን አትጥሉት፣ ምክንያቱም የሀገር ምልክት ነው፡፡ እርሱን አትጥሉት፣ ምክንያቱም የሀገር አርበኛ ነው፡፡ ምንም ማድረግ አይችልም፡፡ እንደዚያ ሆኖ ነው የተወለደው!

በኢትዮጵያ ያለው እውነተኛው ቴዲ አፍሮ እንጂ የኮካ ሸቀጥ አይደለም!

ዓለም እና አብዛኛው የዓለም ህብረተሰብ እንዲሁም የዓለም የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ቴዲ አፍሮን ይፈልገዋል፡፡ ቴዲ የአፍሪካ የሙዚቃ ሊቅ ነው፡፡ የእርሱ የሙዚቃ ግጥም “ፍቅር ሁሉን ያሸንፋል” በሚል መርህ ላይ የተዋቀረ ነው! አፍሪካውያን/ት ግጥሞቻቸውን እና የሙዚቃ ፍቅሮቻቸውን ወደ አንድነት መድረክ እንዲያመጡ እያደረገ ነው፡፡

ቴዲ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ታዋቂው የጥበብ ባለሙያ ነው ምክንያቱም የእርሱ ሙዚቃ ህዝቡን ወደ አንድነት እያመጣ ነው፡፡ ቴዲ አፍሮ በኢትዮጵያውያን/ት እና አፍሪካውያን/ት ፍቅርን፣ ሰላምን፣ አብሮነትን እና መልካም ነገርን ሁሉ ይዘምራል፡፡ የእምቢተኝነት መዝሙሮችን ይዘምራል፡፡ ስለእርቅ አስፈላጊነት፣ መግባባት እና ይቅርባይነት ይዘምራል፡፡ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት አጠንክረው ለሚሰሩ ሀገር ወዳዶች ሁሉ የስራ መዝሙሮችን ይዘምራል፡፡ ስለኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ማራኪነት እና ስለህዝቧ ደግነት ይዘምራል፡፡ ቴዲ አፍሮ በአፍሪካ ላይ ስላለው ፍቅር ይዘምራል፡፡

የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ህይወትን የበለጠ አስደሳች አድርጎታል፡፡ የዓለም ህዝብ ቴዲ አፍሮ ሰለፍቅር ሲዘምር እንዲያዳምጠው ማየት እፈልጋሁ፡፡ በማያቋርጥ አምባገነንነት መዳፍ ስር ወድቃ ህይወት አልባ እና ደስታ ከራቃት አገር ይልቅ የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ህይወትን እና ደስታን ይጨምራል
ቴዲ አፍሮ እውነተኛ ነገር ነው! ቴዲ አፍሮ እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ነው!

ቴዲ አፍሮ በቅርብ ጊዜ ያሳተመው “ጥቁር ሰው” የተባለው አልበሙ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1896 በኢጣሊያ ቅኝ ገዥ ወራሪ ኃይል ላይ የተቀዳጀችውን ድል የሚዘክር ነው፡፡ ያ አንጸባራቂ ድል በአፍሪካ እና በዓለም ታሪክ ላይ ጉልህ ምዕራፍን ይዞ ይገኛል፡፡ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን እንደ ቅርጫ ስጋ ለመከፋፈል እና የአፍሪካን ህዝቦች በባርነት በመያዝ ጥሬ ሀብቷን ለመዝረፍ በማቀድ በበርሊን ከተማ ከተደረገው ጉባኤ ሁለት ዓመታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በኢጣሊያን እና በኢትዮጵያ መካከል በተደረገው የመጀመሪያው ጦርነት የኢትዮጵያው ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የኢጣሊያንን ወራሪ ወታደሮች በአድዋ ጦርነት ላይ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት የሞቱት ሞተው የተረፉት እግሬ አውጭኝ በማለት ወደመጡበት እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡ የአድዋ ጦርነት የአውሮፓ ኃያል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ወታደሮች ጉልበት ስር እንዲንበረከክ የተገደደበት ጊዜን ያስታውሳል፡፡ ፋሽስት ኢጣሊያ እንደገና እ.ኤ.አ በ1935 ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛትነት ለመያዝ ሁለተኛውን የኢጣሊያን እና የኢትዮጵያን ጦርነት ለኮሰች፡፡ በዚህም ጦርነት ለዘላለም ሊረሱት የማይችሉት የሽምቅ ውጊያን ሽንፈት ተከናንበው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ (በአፍሪካ ከሌላዋ ላይቤሪያ በስተቀር) ነጻነቷን ጠብቃ የቆየች ከቅኝ ግዛትነት ነጻ የሆነች አገር ሆና እንድትቆይ አድርጓታል፡፡ ቴዲ አፍሮ ስለፍርኃት የለሽ መሪዎቿ እና ነጻነታቸውን እና ሉዓላዊነታቸውን ላለማስደፈር በቀስት እና በደጋን እንዲሁም ኋቀር በሆኑ ጠብመንጃዎች በመታገዝ ብቻ ሳይሆን በነበራቸው ኩራት እና ወኔ በጀግንነት ተዋግተው የሀገራቸውን ነጻነት እና ህልውና ላስከበሩት ተራ ኢትዮጵያውያን ጀግኖችም ዘምሯል፡፡

በቴዲ እና ልዩ በሆኑት የኪነ ጥበብ ስራዎቹ ኮርቻለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ልዩ ባህል እርሱ ላበረከታቸው እጅግ መጠነ ሰፊ በሆኑ አበርክቶዎቹ ሁሉ በጣም ኮርቻለሁ፡፡ በሙዚቃ ስራዎቹ አማካይነት ፍቅር፣ አንድነት እና በህዝቦች መካከል ብሄራዊ ዕርቅ እንዲወርድ ባደረጋቸው እልህ አስጨራሽ ጥረቶች ላይ እጅግ ኮርቻለሁ፡፡ ቴዲ ልዩ የመንፈስ ጽናት ያለው እና የውርደትን ትጥቅ ያስፈታ ትንታግ ከያኒ ወጣት ነው፡፡ የእርሱን ዝና እና ክብር ለማንቋሸሽ በተከታታይነት ዘመቻ ሲያደርጉበት ምንም ዓይነት ምላሽ አይሰጣቸውም፡፡ በእርግጠኝነት እንዲህ ብቻ ይላል፣ “ፍቅር ሁሉንም ያሸንፋል፡፡“ በጥላቻ የተሞሉ የእኩይ ምግባር አራማጆች ፍቅር ሁሉንም ያሸንፋል ብሎ የተነሳን ሰው በምንም ዓይነት መልኩ ሊያሸንፉ አይችሉም፡፡

አሁን በህይወት የሌለው መለስ እ.ኤ.አ በ2008 በሰው ላይ የመኪና አደጋ አድርሶ አምልጧል በሚል በውሸት የተቀነባበረ የሸፍጥ ክስ ሳቢያ ቴዲ አፍሮን ወደ እስር ቤት በወረወረው ጊዜ በቴዲ ጎን ቆሜ በዓለም ህዝብ የሕሊና ፍርድ ቤት ስከራከር ነበር፡፡ እንደዚሁም ቴዲ አፍሮ ፈጽሟቸዋል በሚል የፍብረካ ወንጀሎች በቁጥጥር ስር ውሎ ክስ እንዲመሰረትበት መለስ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ የተቀነባበሩ 10 አገር ከመውደድ ጋር ተያይዞ የሰራዉን የ “ወንጀል ክሶች” ዝርዝር መዝግቤ ይዣለሁ፡፡ የመለስ እኩይ የሙት መንፈስ በቴዲ ግጥሞች በተገለጹ እውነቶች እና እምነቶች ሲወጋ እና ሲባንን ይኖራል፡፡

ቴዲ እ.ኤ.አ በ2010 ወደ ሎስ አንጀለስ በመጣበት ወቅት የእርሱን የሙዚቃ ትርኢት ተመልክቸ ነበር፡፡ የሙዚቃ ትርኢቱ አስደናቂ ነበር፡፡ የቴዲ የሙዚቃ ትርኢት ወጣት በነበርኩበት ጊዜ እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በመጀመሪያው እረድፍ ላይ ቆሜ ያየሁትን የታላቁን ቦብ ማርሌይን ካያ እና የህይወት ግብግብ ጎዞ/Kaya and Survival tour በሚል ርዕስ የቀረበውን ሙዚቃዊ ትርኢት እንዳስታውስ አደረገኝ፡፡ ቦብ ማርሌይ በአፍሪካ ነጻነት እና በፓን አፍሪካኒዝም ላይ እንደነበረው ፍቅር ሁሉ ቴዲ አፍሮም በተመሳሳሳይ መልኩ በነጻነት፣ በአንድነት፣ ዕርቀ ሰላም በማውረድ እና በአትዮጵያ ህዝቦች ላይ ፍቅር እንዲሰፍን ይፈልጋል፡፡ እንደ ማርሌይ ሁሉ የቴዲ ሙዚቃም ቀስቃሽ፣ አስደማሚ እና ልብ አንጠልጣይም ነው፡፡ እንደ ማርሌይ ሁሉ ቴዲም ስለፍቅር፣ ሰላም፣ ተስፋ፣ እምነት፣ ለጋሽነት፣ ፍትህ፣ ዕርቅ፣ መግባባት እና ይቅርታ አድራጊነት ይዘምራል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ነገሮች ናቸው የቴዲ አፍሮን የሙዚቃ የቅላጼ ኃይል በኢትዮጵያውያን/ት ልብ እና ልቦና ውስጥ ዘልቀው በመግባት የተስፋ ማጣት ቁስልን፣ ማለቂያ የሌለውን ጭቆና እና ኢትዮጵያን ከአምባገነንነት መቃብር ለማዳን ለቀዶ ጥገናው ስራ በመስፊያ ክርነት እያገለገሉ ያሉት፡፡ ቴዲን በኢትዮጵያ ውስጥ ስለፍቅር፣ ሰላም እና ፍትህ ከመስበክ እና ከመዘመር የሚያግደው ምንም ምድራዊ ኃይል የለም፡፡

ቴዲን የኢትዮጵያ ጅግና የስነ ጥበብ ባለሙያ እና የእራሴም ግላዊ ጀግና አድርጌ እቆጥረዋለሁ!

ዓለም የእኛ ናት የኮካ አይደለችም፡፡ አንድ ኮካ ኮላን በአንድ ሰው ማስወገድ፣ አንድ ኮካ ጠርሙስ በአንድ ጊዜ ማስወገድ አለብን!

የእኔን ሳምንታዊ ትችቶች ለበርካታ ዓመታት በመከታተል ላይ ለሚገኙት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አንባቢዎቼ እኔን እዲቀላቀሉኝ እና “ኮካን ከመጠቀም እንዲያስወግዱ” የአክብሮት ጥሪየን አቀርባለሁ!

ኮካ ኮላ በጨለማ እንደሚካሄድ የኃይማኖት ክብረ በዓል የሻማ ብርሀን ይዘን ለተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ብንወጣ ጉዳዩ አይደለም፡፡ ኮካ ኮላ ስለእኛ ሞራል ዝቅጠት ጉዳይ ደንታ የለውም፡፡ የኮካ ኮላ ዋና ጉዳይ ከሁሉም በላይ ስለትርፍ እና ኪሳራ ማሰላሰል ብቻ ነው፡፡ ኮካ ኮላ ከ200 በላይ በሚሆኑ አገሮች ከ30 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ሽያጮችን ያካሂዳል፡፡ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ለገበያ ማስተዋወቂያ ዘመቻ ወጭ ያደርጋል፡፡ ኮካ ኮላ በውል ሊገነዘበው የሚችለው ብቸኛው ቋንቋ የትርፍ እና ኪሳራ ቋንቋ ነው፡፡

በአንድ ጊዜ አንድ ሰው ኮካ ኮላን መግዛት እና መጠቀምን ቢያቆም እና የ114 የኮካ ኮላ ምርት ውጤቶችን መግዛት እና መጠቀምን ብናቆም ዓለማችንን ከኮካ ኮላ መዳፍ ስር በ114 ቀናት ውስጥ ማላቀቅ እንችላለን፡፡

በኢትዮጵያ ያሉ አንባቢዎቼ ኮካ ኮላ መጠጣትን እንዲያቆሙ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ የእራሳቸው “የኮካ መጠቀም ማስወገጃ ቀን” እንዲኖራቸው እጠይቃለሁ፡፡ ሁልጊዜ ኮካ ሲቀርብ አሻፈረኝ አልፈለግም አንዲሉ !!!

ይህ የማስወገድ ስልት በኮካ ኮላ ላይ ብቻ የተወሰነ መሆን የለበትም፡፡ ስለኢትዮጵያ ብሄራዊ ኩራት ጭምር ነው፡፡ አገራችንን ከሶዳ ቸርቻሪ እና ከወሮበላ ዘራፊዎች ማላቀቅ አስፈላጊ ነው፡፡

አንድ የካካ ኮላ ጠርሙስን ባንድ ሰው እንዋጋ እላለሁ፣ አንድ ሰው ኮካ ኮላ በአንድ ጊዜ ማስወገድ ይቻላል! እምቢ ኮካ አልፈልግም

ኮካ ኮላ እንዲህ በማለት ጉራዉን ይነዛል ፣ “ዓለም የእኛ ናት!“ አኛ ደግሞ ለ ኮካ ኮላ ኢትዮጵያ የእኛ መሆኗን ማሳየት አለብን!

በመጨረሻም የእኔ ኮካ ኮላን መጠጣት የማስወገድ ዓላማ ቴዲን ነጻ እንዲያደርገው በኮካ ኮላ ላይ ውጥረት ለመፍጠር አይደለም፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ከጀርባ መጋረጃ ሆኖ የኮካ ኮላን እጅ ለሚጠመዝዘው ለአንደበተ ድሁሩ የገዥ አካል እውነተኛውን ነገር እስከ አፍንጫው ለመንገርም አይደለም፡፡ ይህንን የማደርገው ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ስለሚሰማኝ ክብርና ሞገስ ስለማስብ ብቻ ነው፡፡

ተባበሩኝ እባካቸሁ ለክብራችሁ
ተባበሩኝ ለክብራችን
ውርደት እስከመቼ ተሸክምን እንችላለን?
ባንደበታችን መናገር ባንችል
ባንደበታችን የሚገባዉን ማስቆም አንችላለን ::

ተባበሩኝ ወገኖች ጀግኖች ለክብራችን !
ኮካ ኮላ ነው በሉ የሚያስጠላ፥ የሚያጣላ::

በግሌ የምለው አንዲህ ነው፥

ኮካ ኮላ ለዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ ካዘዛቸው 32 አገራዊ ልዩ ሙዚቃዎች መካከል 31ዱን ከለቀቀ እና የታላቂቱ የኢትዮጵያን ልዩ ሙዚቃ አሽቀንጠሮ ከጣለ በበኩሌ ኮካ ኮላን የምለው “ተምዘግዝጋችሁ ገሀነም ግቡ” ነው!!!”

ኮካ ኮላ፥ የሚያስጠላ የሚያጣላ!!!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሰኔ 10 ቀን 2006 ዓ.ም

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop