June 14, 2014
14 mins read

ወጣቶቹና – ቅዳሜ (ጽዮን ግርማ)

አንዷን ቅዳሜ በፍርድ ቤት

በዛሬው ችሎት ፖሊስ የሃያ ስምንት ቀን የምርምራ ጊዜ ቀጠሮ ተፈቀደለት

ጽዮን ግርማ

ጽዮን ግርማ
[email protected]
ወጣቶቹና - ቅዳሜ (ጽዮን ግርማ) 1

 

ለአብዛኛው ወጣት አዲስ አበባ ላይ ”ቅዳሜ” ትርጉም አላት። የሣምንቱን የሥራ ቀናት በየፈርጁ ያሳለፈው ኹሉም ወጣት ”ቅዳሜ”ን ደግሞ እንደየምድቡ ይውልባታል። እንደሰማኹት ከኾነ ለዞን ዘጠኝ አባላትና ጓደኞቻቸውም ቅዳሜ ልዩ ቀን ናት። ለወጣቶቹ አብሮነት የጡመራ መድረኩ ቢያግዛቸውም ከዛ በላይ ግን ጓደኝነታቸው ቤተሰባዊነትን ፈጥሮላቸው አብዛኛውን ቅዳሜ እንደየቅርበታቸው አብረው ያሳልፋሉ።

አብረው እስረኛ ይጠይቃሉ፣ የታመመን ያጽናናሉ፣ በጋራ ምሳ ይቋደሳሉ፣ የተለየ ዝግጅት ካለም አብረው ይሳተፋሉ። ከዚህ የተረፈ ጊዜ ካላቸው ደግሞ ፈጣንንና ነጻ የገመድ አልባ ኢንተርኔት አገልግሎት በሚገኝበት ሆቴል ገብተው ዓለም በምን ኹኔታ ላይ እንዳለች ለመከታተል ይሞክራሉ። አገሪቷ ውስጥ ባለው ከፍተኛ የኢንተርኔት ኮኔክሽን ችግር ምክንያት አብዛኛው ጋዜጠኛና ጥቂት ወጣቶች የእነዚህ ትልልቅ ሆቴሎች ገመድ አልባ ኢንተርኔት ተጠቃሚ ነው። በቅዳሜ ወደእነዚህ ሆቴሎች ጎራ ያለ ከጦማሪያኑ ወይም ከጋዜጠኛ አንድ ሰው ሊያገኝ ይችላል። በቃ ሲገናኙ ሰላም ተባብለው መቀላቀል ነው። እናም በአንድ ጉዳይ ጨዋታ ጀመራል። አብዛኛው ጨዋታ በአገር ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሊኾን ይችላል። ኮምፒዩተሮቻቸውን እየነካኩ ስለ አገራቸው ግድ ያላቸውን ይነጋገራሉ፣ ይከራከራሉ አሊያም ይጨቃጨቃሉ። መሄጃው ሰዓት የደረሰበት ደግሞ ተሰናብቶ ይሄዳል። በእነዚህ ሆቴሎች በቀጠሮ የሚገናኝ ሰው የለም። ”የት ነህ? የት ነሽ?” የሚለው የስልክ ጥያቄም ለመገናኘት በቂ ነው።

የተስፋዓለም ቅዳሜ ደግሞ ሌላ ነበረች። ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አብዛኛውን አርቦች ከእነ ለሊታቸው በሥራ ያጠፋቸዋል። ቅዳሜንም ረፈድ አድርጎ ይነሳል። እናም የመጀመሪያ ሥራው ለሕትመት የበቁ ጋዜጣና መጽሔቶችን አበጥሮ ማንበብ ነው። በማንበብ ብቻም አያቆምም፤ ከዘገባዎቹ አብዛኖቹ የተሠሩት በጓደኞቹ አሊያም በሚያውቃቸው ጋዜጠኞች ስለሚኾን ስልክ ይደውላል። ከዘገባዎች ውስጥ ተስፋዓለምን የሚያስደስቱት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ሊኾኑ ስለሚችሉ የስልክ ልውውጦቹ ”እንዲህ ብታደርግ/ብታደርጊ ኖሮ፣ እንትናን ብታናግረው በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ ይሰጥህ ነበር፣ እዚህ ቦታ እኮ እንዲህ ዓይነት መረጃ ነበር፣ ይሄ እኮ ከዚህ በፊት እንዲህ ያለ ሕትመት ላይ ወጥቷል፣ እውነቱን ለመናገር ይሄ ለሕትመት የሚበቃ ዘገባ ነው ብዬ አላምንም” በሚሉ አስተያየቶች የተሞሉ ነበሩ። በዚያው ልክ ደግሞ የሚያስደስተውን ዘገባ ሲያነብ ወይም ፕሮግራም ሲሰማ አዘጋጁን አወቀው አላወቀው ስልክ አፈላልጎ በመደወል ያበረታታል። የተስፋዓለም ግማሽ ቅዳሜ የምታልቀው ይህን ሲያደርግ ነው።

አኹን እነዚህ ወጣቶች ቅዳሜያቸውን በፌደራል ወንጀል ምርመራ መምሪያ (ማዕከላዊ) ፖሊስ ተነጥቀዋል። ሃምሳ ቀናት ታስረው ዘጠኝ ቅዳሜን አጥተዋል። እንዳሻቸው የሚያደርጓትን ቅዳሜ አኹን እነርሱ አያዙባትም። ከጠዋቱ ዐስራ ሁለት ሰዓት ሲል ከእንቅልፋቸው ይቀሰቀሳሉ። ለቁርስ ዳቦ በሻይ ይሰጣቸዋል። (ቤተሰብ የሚያወስድላቸው ምግብ ቁርስ ከበሉ በኋላ ነው የሚደርሳቸው) እናም ተመልሰው ገብተው ይዘጋባቸዋል። አብዛኞቹ ለየብቻ ከሌሎች እስረኛ ጋር የታሰሩ ሲኾን ሁለት፣ ሁለት ተደርገው የታሰሩም አሉ። እናም ከምርመራ የተረፈ ቀናቸውን በዝጉና በጨለምተኛው ክፍል ያሳልፋሉ። በአንዷ ቅዳሜ ደግሞ እንደዛሬው ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።

አንዷን ቅዳሜ – በፍርድ ቤት

ዛሬ ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2006 ዓ.ም.፤ ሦስቱ ወጣቶቹ እነርሱ በማያዙባት ቅዳሜ እጆቻቸውን በካቴና ታስረው ፒያሳ በሚገኘው የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ግቢ ውስጥ ሲደርሱ ከሌላው ጊዜ የበለጠ ቁጥር ያለው በዐይን ግምት ሦስት መቶ የሚደርስ ችሎት ተከታታይ በግቢ ውስጥ ተገኝቶ ነበር። የዛሬዎቹ ጠባቂ የፌደራል ፖሊሶች ባለፈው ጊዜ ከነበሩት ሻል ያሉ ስለነበሩ ቤተሰቦች ችሎት ውስጥ ገብተው እንዲታደሙ ባይፈቀድላቸውም ግቢ ውስጥ ከመቆም የከለከላቸው ወይም ያመናጨቃቸው አልነበረም።

ከጠዋቱ አራት ሰዓት ከሃያ ደቂቃ አካባቢ ሲኾን ችሎቱ በሴት ዳኛ በመሰየሙ፤ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎቹ ናትናኤል ፈለቀ እና አጥናፉ ብርሃነ እጃቸውን በሰንሰለት እንደታሰሩ ወደ ግቢው ገቡ። ዛሬ ወጣቶቹ በስስ ፈገግታ ”አይዞአችሁ ደህና ነን” የሚል የተስፋ ምልክት ለቤሰተቦቻቸውና ለጓደኞቻቸው አሳይተዋል። ከእነርሱ ቀጥለው በፖሊስ ታጅበው የገቡት ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስና የሕግ መምሕርና የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ዘለዓለም ክብረት እጆቻቸው በካቴና እንደታሰረ ለቤተሰቦቻቸው ሰላምታን ሰጥተዋል። የእነርሱ ፈገግተኛ መኾን ለቤተሰቦቻቸው፣ ለጓደኞቻቸውና ለወዳጆቻቸው ጥቂትም ቢኾን እፎይታን ሰጥቷል።

ተጠርጣሪዎቹ ችሎት የቀረቡት እንደወትሮው ኹሉ በሁለት መዝገብ ተከፍለው ቢኾንም ፖሊስ ያቀረበው ምክንያትና መከራከሪያ አንድ ዓይነት ነበር። ችሎቱ ከተሰየመ በኋላ ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ ቀጠሮ በርካታ ጉዳዮችን ሲመረምር መቆየቱንና አሁንም ያልተጠናቀቀ ምርመራ ስለሚቀረው ተጨማሪ ሃያ ስምንት ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል።

ጠበቃው አቶ አመሐ፤ ”ፖሊስ ከዚህ ቀደም በወሰደው ጊዜ ቀጠሮ ሰነድ ለማስተርጎም፣ የምስክሮችን ቃል ለመቀበል፣ ኢሜሎቻቸውን ለመፈተሽ እንዲሁም ያልተያዙ ግብረአበሮቻቸውን ለመያዝ ብሎ እንደነበርና አሁን ዝም ብሎ በጥቅሉ በርካታ ሥራዎችን ሠርቼያለሁ እንደገና ይጨመርልኝ ማለቱ አግባብ አይደለም” ሲሉ አመልክተው ነበር። ዳኛዋ ፖሊስ የሠራውን ሥራና የሚቀረውን ምርምራ እንዲያስረዳ በማዘዛቸው፣ ”ከሠራናቸው በርካታ የምርመራ ሥራዎች መካከል የተባባሪዎቻቸውን ቤት ፈትሸናል፣ ለተለያዩ ባንኮች የተጠርጣሪዎቹን ዝርዝር መረጃ እንዲሰጡን ጠይቀን ከተወሰኑት ምላሽ አግኝተናል፣ የተወሱ ምስክሮችን ቃል ተቀብለናል፣ ከትርጉም ሥራውም የተወሰነውን ሠርተናል። ግብረአበሮቻቸው ወደ ክፍለ ሃገርና ወደ ተለያዩ አገራት እየሸሹ መያዝ ስለተቸገርን የፖሊስ ኃይል አሰማርተን እያፈለግናቸው ነው እነርሱንም መያዝ ይቀረናል።” በማለት ተናግሯል።

አቶ አመሐ በበኩላቸው፤ ”ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ካዋለ ሃምሳ ቀናት ሞልቶታል። እነዚህ የሚላቸውን ነገሮች አጠናቆ ለመጨረስ የነበረው ጊዜ ከበቂ በላይ ነው። አሁንም ቢኾን እነዚህን ምርመራዎች ለማድረግ ደንበኞቼን አስሮ ማስቀመጥ አስፈላጊ አይደለም፤ ስለዚህም ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቻውን ሊያከብርላቸው ይገባል። ይህን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ባይቀበለው እንኳን ከዚህ በኋላ ፖሊስ በሚሰጠው ሃያ ስምንት ቀናት ጊዜ ውስጥ ምርመራውን አጠናቆ እንዲመጣ፤ አጠናቆ ባይመጣ ደግሞ ጥያቄው ተቀባይነት እንደማይኖረው ተደርጎ ይመዝገብልን” በማለት ጠይቀዋል።

ዳኛዋ አቤቱታውን ካደመጡ በኋላ፤ ፖሊስ ከዚህ በኋላ ሲቀርብ ለተጨማሪ የምርመራ ቀነ ቀጠሮ መጠየቂያ አሁን የጠቀሳቸውን ምክንያቶች በምክንያትነት ይዞ እንዳይቀርብ በማሳሰብ የጠየቀውን የሃያ ስምንት ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ፈቅደዋል።

በዛሬው ዕለት ችሎት ከቀረቡት መካከል ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፤ ከፍተኛ የኾነ የጀርባ ሕመም ስላለበት ወንበር እንዲገባለት መጠየቁንና እስካኹን ሊገባለት እንዳልቻለ ጠቅሶ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት አመልክቷል። ዳኛዋ ከምንም ነገር በላይ የጤና ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ በማሳሰብ የጠየቀው ወንበር እንዲገባለት ሲሉ ተናግረዋል። በችሎት የተገኘው መርማሪ ፖሊስ፤ ”በአጋጣሚ የእርሱ መርማሪ እኔ ነኝ የጀርባ ሕመም እንዳለበት ነግሮኛል። ወንበር እንዲገባለት ግን አልጠየቀኝም። አሁንም ቢኾን ይህ በጣም ቀላልና እዛው እኛው ጋር ሊያልቅ የሚችል ነገር ነው። ችግር የለም እናስገባለታለን” ሲል ቃሉን ሰጥቷል።

እስረኞቹ ከችሎት ሲወጡ እንደ አገባባቸው በፈገግታ ሰላምታ እየሰጡ ሲኾን፤ ችሎቱን ለመከታተል መጥቶ ፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ የቆመው ሰውም እጁን በማውለብለብ ተሰናብቷቸዋል።

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop