እልህ ያረገዘው – ያለወለደው። (ሥርጉተ ሥላሴ)

ሥርጉተ ሥላሴ 13.06.2014 (ሲዊዘርላንድ ዙሪክ)

ከዬት መጀመር እንዳለብኝ ሳላውቅ እንሆ ጀመርኩት። ለሁለተኛ ጊዜ እርእስ ሰጥቼ ለመጻፍ ተሰናደሁ። ግን ይቻለኝ ይሆን? አላውቀውም። ጉዴ ይታይ።

በጓጉሎ ቀናት መታሸት – እንደ ተልባ። በወለምታ በወላላቁ ፍላጎቶች መሾክሾክ – እንደ አጃ። ባለተደላደለ አለሎ መዳጥ – እንደ ጥጥ። በላተገራ መቀንጠቢያ መነን – እንደ ባዘቶ። ለቅሞ ማፍስስ አፍሶ መልቀም። እልህ ያረገዘው ግን ያልወለደው ትዕይንት የእኛ ሃብታችን መሆኑ። እም!

„ኢትዮጵያ“ „ኢትዮጵያ“ „ኢትዮጵያ“ „ኢትዮጵያ“ „ኢትዮጵያ“ „ኢትዮጵያ“ „ኢትዮጵያ“ „ኢትዮጵያ“ „ኢትዮጵያ“  በምላስ መጋዘን ስትደገም – ስተሰለስ። ስትሞሸር – ዘውድ ስትጭን። ስትሽሞነሞን መንበር ላይ ከፍ ብላ ስትታይ ፍላጎት- ምኞት ህልም። መመኘት መልካም። ደስ ይላል። ይህን ቀን  ምኞት ማግኘት የሚቻለው ግን ማሸነፍ እራስን መርታት ሲቻል ብቻ ነው። ለማሸነፍ እልህን አግብቶ እልህን ማርገዝ። ማርገዙ ብቻውን ደግሞ ሸክም ነው። እልህ ያረገዘውን መገላገል ነው ብልሃቱ። በስተቀር ብልሃት የሌለው ቅላት።

ሰለ ወያኔ አስከፊነት ቀን እራሱ ከአመት አስከ አመት ታዳሚ ነውና ይናገራል;። ነገም ይናገራል ቢሄድም ተከታዩ ነገ መምጣቱን ስለሚያውቅ። ደንበሩም ወሰኑም ይናገራል – በቁሙ ታርዷልና። ዱሩ ጫካው ይናገራል – እርቃኑን ነውና። ካቴናው ይናጋራል ከእልፍ ጋር አብሮነቱ አና ብሏልና። ባሩዱም ይናገራል ሰፊ የሥራ መስክ ተክፍቶለታልና። መገፋቱም ይናገራል ከዳር እስከ ደንበር ተካልሏልና። ራህቡ ይናገራል ሁሉም ዓይነት ራህብ ድንኳን ጥለው ሃዘን ላይ ቁጭ ብለዋልና። መጠቃቱም ይናገራል ማህጸን ተቀጥቅጧል – አብራክም ተመትሯልና። መዋረዱም ይናገራል ክብር ተጥሷልና። ታሪክም ይናገራል – ምድማዱ ጠፍቷልና። እንዲያውም ብራና ላይ ያሉት ባህርማዶ የተሻገሩት ሳይቀሩ ሳንከሰል ድረሱልን እያሉ መልእክት እዬላኩ ነው።

ማንነታቸውን የተገፈፉት ትውፊት ገብ ቦታውች ትናንሽ መንዶሮች ሳይቀሩ ስማቸውን ተልጧል፤ እነሱም እራሳቸው አቤት ባዮች ናቸው ለሰማዩ ዳኛ። ቋንቋ የለም ጠፍቷል። ቋንቋው ጎሳ ሆኗል። ቅርሱ ተጥሷል ስለሆነም ይጮኃል ሰሚ ቢያገኝ። ይህ ሁሉ ሆኖ ግን እልሁ መጋኛ መሆን አልቻለም። እልሁ በሽታ መሆን አልቻለም። እልሁ በሽታ ከሆነ ለመዳን ትታገላለህ። ለመዳን የምትታገለው በሃኪም የተሰጠህን መዳህኒት ሳታቅማማ ተከታትለህ ከወሰድከው ብቻ ይሆናል። በስተቀር እንዲያውም ሌላ ጠንቅ ይዞ ከች።

ወይ መዳህኒተአለም አባቴ አሁን ደግሞ አንድ ነገር ነሰተኝ – መንፈሴ። ግን እሺ ንገረኝ አልኩት። „ዋናውን መሳሪያ አትዝለይ“ እያለኝ ነው። አስከትሎም እንዲህ አለኝ። …. „እልሁ እራሱ ከቦታው ስለመኖሩ አረጋግጪ“ እለኝ። እውነቱን።“ ግን ግን ጥቃቱን እንደ ክኒኗ ዋጥ ሰልቀጥ ሲደርግ የጤና ነውን? ይህም ሌላው ጉዳይ ነው። አፋቸውን ሞልተው ወያኔ ይሻላል። ይሄኛው በደል በዚህ ይካካሳል ይሉናል የጎጥ ጠበብቶች። ወያኔ „ኦሮምዬ“ የምትባል ክልል ፈጥሮልናል ቢያንስ በቋቋችን እዬተናገርን ነው በማለት በፍቅር ድብን ሲሉ አስተውላለሁ። ተጠቂሚ ነን ባዮች አልገባቸውም እንጂ እራሱ „የኦሮምያ ክልል“ የሚለው ስያሜ እኮ አንባገነን ነው። „የአማራ ክልል“ የሚለውም እንደዚሁ። „የደቡብ ህዝቦች ክልልም“ የሚለውም እንደዚሁ ወዘተ። ስለምን? በስውር ደባ፤ በረቂቅ ቋሳ የዋጣቸው ማንነቶች አሉና። የደፈጠጣቸው ማንነቶች አሉና። በእርህራሄ አልቦሽ የዳጣቸው ማንነቶች አሉና። ወለጋ እኮ የለም ወይንም አዋሳ፤ ወይንም ወሎ። እንደገና በቁጥራቸው አናሳም ቢሆኑ በአንድ ብሄረሰብ ልዩ ሥም በተከለሉ ቦታዎች ቁጥራቸው ያነሱ ኢትዮጵያዊ  ብሄረሰቦች አሉ። አሁን ወሎ አገው፣ ኦሮሞ አለ። ጎንደር ቅማንት ሽናሻ ወይጦ አለ። እኔ እንደማስበው እልሁ የሴራውን ሥር አላገኘውም። እልህ የለሾችም ቢሆኑ በወያኔ ቀለብ የሚሰፈርላቸው ከዘመንተኛው ጋር የመደቡት እራሳቸውን እዬፋቁ ስለመሆኑ አልተገለጠላቸውም። በነጠፈ ህልም ላይ እዬዳከሩ ነው ያሉት። ግርዶሽ ነገር አለባቸው። ወይንም እንደ አባት አደሩ ዓይነ ጥላ ነገር። እራሳቸው እኮ የለም። በሌለ ውስጥነት አለመኖርን እንደ መኖር አድርጎ መቀበል። የመንፈስ ድህነት ወይንም የተፈጥሮ ስጦታን ዝለት …. ዝግተም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለተስፋዬ ገ/አብና ለግንቦት ሰባት እንዲሁም ለኢሳት የሚያስጨንቀኝን ልጠይቅ

ክልል የሚለው ቃል እራሱ የሚከፍል የሚተረትር የሚሰነጥቅ ዲዲቲ ነው። አዲስ አበባ ክፈለ ከተማ በዚህ ስያሜ መንፈስ እንደ አወጣ ተሸኝሽኗል። ወረራው መጠነ ሰፊ፤ ወረደ ሰፊና ቁመተ ረጅም ነው።

በዚህ ስሌት በቦታ ስያሜ እንኳን ሳይቀር መብቱ የተጠበቀለት „የትግራይ ክልል“ ብቻ ይሆናል። ይህ ባለ ጊዜነትን የሚያውጅ ይመስለኛል። „ትግሬነት’ ቀን አልከዳውም እንደ ‚ኢትዮጵያዊነት“ የዚህ ሁሉ ደባ ፍሰት መነሻ መሠረታችን ያፈልሰዋል። ምድረበዳ ያደርገዋል። ይህን በትክክል ተረድትን ስንመረምረው መዳኛችን አንድ ብቻ ነው። ቀረመቱ ሳይሆን መሠረቱ ይሆናል – የፍላጎታችን አውራ ድልዳል። የመንፈሳችን ዓይነ ልቦና ሆነ እዝነ ህሊና መንሹ መሰረቱን ያውጃል። ፍሬ ዘር፤

ሥር ያለው የጥቃት ዓላማ እልህን ጠንስሶ ስለምን መገላገል አላስቸለንም? ምን አልባት በደሉ ግጥግጥ ሆኖልን? ወይንም ቅልቅል? ለዛውም በግንቦት ኢትዮጵያ ሠርግ አልተለመደም። ካልቸገረ በስተቀር … መሰረቱ መርዝ – ጣሪያው መርዝ -ግድግዳው መርዝ – ማገሩ መርዝ – መግቢያ መውጫ በሩ መርዝ።  በመርዝ ላይ ቁጭ ያለ ሰብእና እልህ ሰውነቱ እንዲፈጥር በማደረግና ባላማደረግ መሃከል ያለው ልዩነት እንደ ሰው መሆን ወይንም ይህን ጸጋና መክሊት ከመተላለፍ ይመነጫል።

ከዚህስ በኋላ ለእንጉልቻ የተፈጠረ ወይንም ቀንናና ሌሊት የእንቅልፍ ክኒኑን ወስዶ ለሽ፤ ወይንም የእልህን ትልሞች መቆጣጠር ተስኖት የዛለ አካል ተሸክሞ መኖር ዕጣው ይሄ ነው፤ እንደ እኔ እንደ ሥርጉተ ይህ አርበኝነትን ቅንቅን እዲበላው በሙሉ ድምጽ መፍቀድ ነው። አርበኝነት የግድ ነፍጥ ማንሳት ብቻ አይደለም። በሸር ላይ በመንፈስ መሸፈት። ልብን ቅርቅር አድርጎ በዳይን ፊት በመንሳት አርበኝነት አንቱ ይሆናል። መንፈስን አሸፍቶ በልብ ውስጥ ጫካን ማደራጀት፤ በተገኘው አጋጣሚ ፍቅርን ነፍጎ በቃህንን እያንቦለቦሉ ሰንጎ ማጉረስ። ለጠላትም ለግል ኢጎም። ልምምጥ ጎንበስ ቀና አያስፈልግም የዚህን ጊዜ እልህ ተፈጥሯል – የተፈጠረውም እልህ ተገላግሏል ማለት ያስቻላል። በስተቀር ኤሉሄ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የምንጠብቀው ሌላ፥ የሚሆነው ሌላ - ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

እልህ የግል ሃብት ነው። የግል ንብረት ነው። እልህ እራስ ለራስ ችሎ የሚሰጠው ነፃነትም ነው። እልህ የድል መንበርም ነው። እልህ የራዕይ ጉልላትም ነው። በተለይ ተበደልኩ ለሚል ዜጋ እልህ የበሽታው ሁሉ መፈወሻ ነው። እልህ የቋሳ ሃጢያት የፈጠራቸውን ስንክሳሮች ሁሉ ይፍታህ ይላል እንደ አባቱ እንደ ጴጥሮስ። ስለሆነም የጡሑፉ ወጋግራ በሽታውን ለመፈወስ መጀመሪያ ከራሱ ይነሳ ነው አብዩ ዓምድ። በዙሪያው ያለውን ይቃኝ። እልሁን የሚመሳሳሉትን ደስ ብሎት ማቄን ጨርቄን ሳይል ይቀላቀል። ሲቀላቀል ግን ለማጥመድ ወይንም ለመጠመድ መሆን አይኖርበትም። እልሁን ለማድመጥ የእልህ ዘብ አደር ለመሆን እንጂ።

ይህም ማለት እልሁን ለመገላገል የእልሁን ሥነ ምግባር መፈጸም ግድ ስለሚለው፤ ቅንነነት – እውነት – ንጹህ ልብ – ግልጽነት – ቀጥተኝነት – ታማኝነት – አክብሮተ – ዕሴት – ውል – ለኪዳን ማደር – መሆን – ፈርኃ እግዚአብሄር –  ሁሉንም የመንፈስ ሃብቶች ሳይለግሙ ለማህበርተኞች ፈቅዶና ወዶ ግዙት – ንዱት በማለት መፍቀድ ይኖርበታል። ተጻራሪ ዕኩይነትን በመጸዬፍ መገፍተር —-

ይህን ጊዜ በደል ይረታል። መበደል ያሸንፋል። ግን ችለናል? ወይንስ ገና ታቱ ነው? የተሻለ ወያኔ ነው የሚሉ ጹሑፎችን አነባለሁ እንዲሁም አንደበቶችን አደምጥ ነበር አሁንስ? ቀንበጥ ከትምህርት ቤት ወጥቶ ሲቀር ይመቻልን? የጫጉላ ሽርሽር ነውን? እልሁ የት ላይ ይቀመጥ? የት ነው ያለው ባላንባራስ እልህ? ዳጥ። በኢትዮጵያዊነት ማእቀፍ ግን ጎጤን። „ስንት ጊዜ በንግግሩ ላይ „ኢትዮጵያን“ አነሳ“ ይህ ለአንድ በጎጡ ለሚያምን ታላቅ የተከበረ ሰው እንደ ብርቅና ድንቅ ይነገርለታል። ለእኔ ግን ስለጎጥ የሚያስብ  – የሚደክምም መንፈስ „ኢትዮጵያዊነትን“ ባያነሳ – ሳይፈጠር ቢቀርም ይሻለዋል። ውሃ መልኩ ምን ይመስላል?!!!! የእኔ ክብሮች? መልስ –  ውሃማ። ኢትዮጵያዊነትም እንደዛ ነው።

 

ክወና – ትናንትና 12.06.2014 ብራዚል ላይ አለምአቀፍ ድርጊት ተከወነ – ከተለመደው ውጪ። ነፃነቱን የተቀማ ህዝብ ባላበት ቦታ አንተ ባላህ ጉልበትና አቅም እንኳን አንደበትህን ማዘዝ እንደሚሳነህ ሃቅ እራሱን አስከበረ – አስረከበ። ገድል ነው። የፊፋው ፕሬዜዳንት ሆነ የሀገሪቱ መሪ ወሮ እዬቻሉ ግን ልሳናቸውን ማን ዘጋው? ነፃነት የሚገዛ ሸቀጥ አይደለም። ወይንም የምተሸጠው ሸቀጥ ወይንም በችርቻሮ የመትሸቅጠው – የምትሸቅጥበትም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጭራቅ አሕመድ፤ ያማራን ሥጋ፣ የኦሮሞን ነፍስ የበላ ኦነጋዊ አውሬ

የእግር ኳስ እስፖርት አፍቃሪን በምልአት በመሩበት በድንቆቹ በነፔሌ በሀገረ – በብራዚል አንደበት ተከርችሞ የአሻንጉሊት ትርዒት ብቻ ቀረበ። ዳመናማ ነበር። ይህንን ዘመናችን ያበረከተልንን ትልቅ አጋጣሚ ሳናከባልለው ወይንም በኢጎ መርዝ ሳንበክለው ከራሳችን ጀመርን ይህን እናንብበው  – እንተርጉመው – እናመሳጠረው። ጩኸቱ ሌላው ላይ ሲሆን ወይንስ ከእኔም ላይ ባላው!?! ….. እንለካው።

የሬግኑ የ2012ቱ የክብር ጉባኤ አባልና የመንበር ተናጋሪ አፈሩ ይከብዳቸውና ሄሮድስ መለስ ዜናው ነበሩ። ግን ከታች የተቀመጠው ከብላቴናው ጋዜጠኛ አበበ ገላው ንግግር በኋላ ያ – ክብር ልብን ነፍቶ መንቀሳቀስ፤ ያ ካለቦታ ተኮፍሱ እዩዩኝ ማለት-  ኩምሽሽ ብሎ ተኮመታተረ። የሚገርመው መሰንበት አልችል በሎ ጠንዝሎ ትንሽ ቀናት በደመንፈስ ዕብኑን ሞካከረ። ይህም አልሆነም ሰኔልና ቹቻን አዳብሉኝ ብሎ አለፈ …. ። የዚህ ዓመት የአቤዋ ድምጹም የዓለሙን መሪ ፕ/ ባራክ ኦባማን የቀጣይ የመሪነት ክብርና ዝና በምን ይዋጀዋል? መጠበቅ።

ይህ ሁሉም ሰው ባለው መድረክ፤ ባለው ዕድል፤ በእጁ በገባ ሥልጣን፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሊያስተውለው ዬሚገባ ዘመን ያፈራው ትልቅ አመክኖዊ – ክስታታዊ – ተቋም ነው። ለዛውም የዶግማ። በእጅህ ያለውን ነገር የምታከብረው ስታጠው መሆን አይገባውም። ይልቁንም ልብህ ከአንተ ጋር መሆኑን ካረጋጋጥክ ከማጣትህ በፊት ለሥነ ምግባሩ ፈቅደህ – ወደህ – ደስ ብሎህም መገዛት አለበህ። አፈና …. ለፈርዖን ለሄሮድስ – ለጋዳፊ – ለሙጋቤ – ለናዚ – ለሂትለር ለማንም አይሆንም ….። ማበጥ ——- መተርተርን – መፈንዳትን ያልማል። ጌጦቼ የእኔ ውቦች ይሄው ነው ዛሬ እኔና ብራናዬ የምናወጋችሁ።

መልካም የልደት በዓልን በፍቅር – በአክብሮት – በትህትና – ተመኘሁ ነፃነትን ለዛውም ለሴት ሳልጠብቀው ግን በተባረከች ቀን አገናኝቶ ላጎናጸፈኝ ለዘሃበሻ ድህረ ገጽ ዝግጅት ክፍል እና ታዳሚዎች።  እንኳን ለ6ኛ ዓመት ምስረታ ልደታችሁ አደረሳችሁ – አደረሰን። አዝመራማ አመትም ተመኙሁ  ከልብ – ለልቤዎቹ።

በተረፈ Radio Tsegaye Aktuell Sendungn ወይንምwww.tsegaye.ethio.info ጎራእያላችሁጊዜስታገኙበድምጽደግሞእንገናኝናፍቆትንእናወጋጋ።ኑሩልን – የኔዎቹ።

 

እልህን የምወደው የቆሰለውን ውስጤን ለመፈወስ አቅም እንዲኖራው አድርጌ መምራቴን ሳረጋግጥ ብቻ ነው!

 

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

Share