የመፅሃፉ ደራሲ፤ ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ
አስተያየትና ማስተካከያ ሃሳብ አቅራቢ፤ ላቀው አለሙ (ዶ/ር)
አጠቃላይ አስተያየት፣
ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ መፅሃፍ ማሳተማቸውን እንደሰማሁ መፅሃፋቸውን አግኝቼ ለማንበብ በጉጉት እጠባበቅ ነበር። ዘግይቶም ቢሆን በአንድ ወዳጄ አማካኝነት መፅሃፉ እጄ ገብቶ አነበብኩት። ደራሲው በዚያ የአብዮት ዘመን ስለተከናወኑ ተግባሮች አጠር ባለና በጥሩ አቀራረብ ፅፈዋል። በሂደቱ ውስጥ ላለፍነውም ሆነ ለአዲሱ ትውልድ ጠቃሚ መረ
ጃዎችን መፅሃፉ አካቶ ይዞዋል። የሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ አስተዋፅኦ የሚደነቅ እና እርሳቸውም ላደረጉት ጥረት ሊመሰገኑ ይገባል።
አነሳሴ በሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ መፅሓፍ ላይ ሁለንተናዊ ግምገማና ትችት ለማቅረብ አይደለም። መፅሃፉን ካነበብኩ በሁዋላ በአዕምሮዬ ውስጥ ሲጉላሉ ለነበሩ ጥቂት ጉዳዬች አጭር አስተያየት እና ማስተካከያ ለማቅረብ ነው። በቅድሚያ በወቅቱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች በተለይም መኢሶንና ኢህአፓ ስለኢትዮጵያ ህብረተሰብ ከነበራቸው የተለያየ ግምገማ በመነሳት ያከናወኑዋቸው ተግባሮቶች እና በዚያም ሳቢያ ስለደረሱ ጥፋቶች ከመፅሓፉ ያገኘሁትን ግንዛቤ አሰፍራለሁ። በሁለተኛ ደረጃ ታላቅ ወንድሜ ሻምበል አለማየሁ ሃይሌን በተመለከተ ደራሲው ከፃፉት ሃሳቦች አንዳንዶቹ የተሳሳቱ በመሆናቸው እውነተኛውን ነገር ካለኝ መረጃ በመነሳት ላብራራ እሞክራለው ።
በቅድመ አብዮት ኢትዮጵያ ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት አልነበራም። በድርጅታዊ አቅም እና በልምድ የዳበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችም በህብረተሰቡ መካከል አልነበሩም። የንጉሳዊ አገዛዙ እያቆጠቆጠ ከነበረው ማህበራዊ ንቃተ ህሊና ወደሁዋላ ቀርቶ ስለነበር የህብረተሰቡን የለውጥ ፍላጎት እና ጥያቄዎች ለማስተናገድ አቅም አልነበረውም። ስለሆነም ሀገር አቀፍ ህዝባዊ ብሶት ወደ ብሄራዊ የአመፅ እንቅስቃሴ ወይም አብዮት ተሸጋገረ። በአብዮታዊ እንቅስቃሴው ውስጥ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ የነበሩ ቢሆንም የተሻለ የድርጅት አቅም የነበረው የወታደሩ ክፍል የህዝቡን ብሶት እየተከተለ ፀረ መንግስት እርምጃዎችን መውሰድ ጀመረ። በሂደትም ንጉሳዊ ስርአቱን አስወግዶ ስልጣኑን ተቆጣጠረ ። ይህ የወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ የፈጠረውና የህብረተሰቡ ግፊት የታከለበት አስገዳጅ ክስተት እንደነበር ከመፅሃፉ ይዘት መረዳት ይቻላል።
ንጉሳዊ ስርአቱ እንደተወገደ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች በህብረተሰቡ መካከል እንቅስቃሴ ማካሄድ ጀመሩ። ሆኖም በመካከላቸው በነበረው የአላማና የአካሄድ ልዩነቶች እንዲሁም ስልጣን በያዘው ወታደራዊ ደርግ ላይ በያዙት አቋም እርስ በርስ በመጠላለፍ ተግባር እና የፖለቲካ ሽኩቻ ውስጥ ገቡ። በዚህም ተግባራቸው የትውልድ ጥፋትና ክስተት እንዲደርስ አድርገዋል። ለጋ እድሜ የነበራቸው እነዚህ የፖለቲካ ድርግቶች ከሌሎች ሃገሮች የቃረሙትን ንድፈ ሃሳብ በድፍኑ በማንበልበል ከእገሪቱ እውነታና ከህዝቡ የግንዛቤ ደረጃ በመራቅና በስሜት እየተገፉ የስልጣን ፍላጎት ላይ ብቻ በማተኮራቸው በወቅቱ ለደረሱት ጥፋቶች የበኩላቸውን አስተዋፆ አድርገዋል።
ወታደራዊ ደርግ በጊዜው ህዝቡ ላነሳቸው መሰረታዊ የኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ተገቢና ስር ነቀል እርምጃዎችን ወስዷል። የኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ (reforms) ላአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ጠቀሜታ የነበራቸውና ለተከታታይ እድገትም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ነበሩ። ይሁን እንጂ ለሁለንተናዊና ቀጣይነት ላለው የኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት ወሳኝ የሆነው የፖለቲካ ጥያቄ ተገቢውን መፍትሄ ሳያገኝ በመቆየቱ ችግሮች ይበልጥ ተወሳሰቡ፤ ያልተፈለገ ጥፋትም በሃገሪቷ ላይ ደረሰ። ተራማጅ ነኝ ይል የነበረው የምሁሩ ክፍል ብስለት ማጣትና ለስልጣን መስገብገብ እንዲሁም ለደርግ ከነበራቸው ንቀት የተነሳ ለፖቲካዊ ችግሮች መወሳሰብ አስተዋፆ ማድረጋቸውን የሻ/ል ፍቅሬን መፅሃፍ በጥንቃቄ ላነበበ ሁሉ በግልፅ ይታያል። ከነዚህም በተጨማሪ የቅርብና የሩቅ ሃገሮች ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነትና ግፊት ሌላው የችግሩ ምንጭ እንደነበር የግል ግንዛቤና አስተያየት አለኝ።
የደርግ አባላት በተለይም ሊ/መንበር መንግስቱ ኃ/ማሪያም ብልሃት በጎደለው የኢትዮጵያዊነትና የሃገር ፍቅር ስሜት በመገፋፋት የፖለቲካውን ውስብስብ ችግሮች በሃይል ብቻ ለመፍታት በመሞከራቸው በትውልዱ ላይ ከፍተኛ መከራና ጥፋት እንዲደርስ አድርገዋል። አልፎ ተርፎም ሃገራችን ዛሬ ለምትገኝበት የችግር ማጥ ዳርገዋት ሄደዋል።
ሻምበል ፍቅረስላሴ ከላይ ያነሳኋቸውንና ሌሎች የወቅቱን አበይት ክስተቶች በመፅሃፋቸው ውስጥ ለመዳሰስ ሞክረዋል። አያሌ ቁምነገሮችና ጠቃሚ መርጃዎች በመፅሃፉ ውስጥ ተካተው ስለቀረቡ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ብዬ አምናለው። ሻምበል ፍቅረስላሴ በቅርበት የሚያውቋቸው ሌሎች ቀሪ ጉዳዬች ቢኖሩም በመፅሃፉ ውስጥ የቀረቡ ማብራሪያዎች በአብዛኛው ሚዛናዊ ናቸው ብዬ እገምታለው።
ሻምበል አለማየሁ ኃይሌን በተመለከተ፣
ሻምበል አለማየሁ ከኦሮሞና ከከፋ ብሄረሰቦች እንደሚወለዱ ሻምበል ፍቅረስላሴ በመፅሓፋቸው ጠቅሰዋል። ይህ ፈፅሞ ትክክል ያልሆነ መረጃ ነው። ምንም እንኳ የወላጆቻችን የትውልድ ሃረግ ከኦሮሞ፤ ከጉራጌና ከአማራ ብሄረሰቦች የሚመዘዝ ቢሆንም የወላጆቻችንና የእኛ ስብዕና በአብዛኛው ኦሮሞነትን መነሻ አድርጎ በኢትዮጵአዊነት ስነልቦና የተገነባ ነው። ስለዚህ ሻምበል አለማየሁ ብሄረሰቡ ኦሮሞ እንጂ ከከፋ ብሄረሰብ ጋር በቀጥታ የሚያገኛኘው ነገር የለም። ይሁን እንጂ እንደአብዛኛው ኢትይጵያዊ በጋብቻ የተነሳ በከፊል ከከፋ፤ ከሲዳማና ከሃዲያ ብሄረሰቦች የሚወለዱ የሩቅ ዘመዶች እንዳሉን መካድ አይቻልም።
ሻምበል ፍቅረስላሴ በደርግ ውስጥ በእነ አለማየሁ ወገንና በሊ/መንበር መንግስቱ ደጋፊዎች መካከል ስለነበረው ቅራኔና በመጨረሻም ስለተወሰደው እርምጃ (የመንግስት ግልበጣ) ባብራሩት የመፅሃፋቸው ክፍል ውስጥ፣ ሻምበል አለማየሁ የኢህአፓ አባል እንደነበር፤ የታገለውም ኢህአፓን ስልጣን ላይ ለማውጣት እንደነበር ፅፈዋል (ገፅ 310)። እውነቱ ግን በፍፁም ከዚህ የተለየ እንደነበር እኔ በቅርብ የማውቀው ጉዳይ ነው። በመጀመሪያ ነገር አለማየሁ የኢህአፓ አባል አልነበረም። ይህንኑ ሃቅም የኢህአፓ አንዱ መሪ የነበሩት አቶ ክፍሉ ታደሰ በመፅሃፋቸው ውስጥ ገልፀዋል (ያ ትውልድ)። የአለማየሁ እምነትና ፍላጎት ደርግ ለኢትዮጵያ ህዝብ በይፋ ቃል ገብቶ ስልጣንን በጊዚያዊነት የያዘ ኃይል እንደመሆኑ፤ የአብዮቱ ወገን የሆኑና ኃላፊነት የሚሰማቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ተባብረውና የጋራ ግንባር ፈጥረው በህዝብ ይሁንታ ስልጣኑን እንዲረከቡ ይፈልግ ነበር። የደርግ አባላትን በተመለከተ ምርጫ በማድረግ ወደ ፈለጉት ድርጅት ውስጥ ተጠቃለው ትግሉን መቀጠል ይችላሉ ወይም ሌሎች የግል ምርጫዎችን መውሰድ ይችላሉ ብሎ ያምን ነበር። ደርግ በመንግስትነት ሚናው ለሁሉም ፓርቲዎች መድረኩን በእኩልት ማመቻቸት አለበት እንጂ አንዱን ድርጅት አገልግሎ፣ ሌላውን ማቅረብ የለበትም የሚል አቋም ነበረው። ለአብዮቱ የቆሙትን ኃይሎች ሁሉ በእኩል አይን በማየት፤ በማዕከልነት ማስተባበርና እኩል ድጋፍ መስጠት የደርግ ኃላፊነት መሆን አለበት ይል ነበር።
ለዚህም ሲባል እያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት በተለይም መኢሶንና ኢህአፓ አቋማቸውን አስተካክለው የአብዮቱን አላማ፤ የሀገሪቱን ጥቅምና የህዝቡን ፍላጎት እንዲከተሉ አለማየሁ በግሉ ይወተውታቸው እንደነበር በቅርብ አውቃለሁ። የመኢሶን መሪዎችን “እኛን ብቻ ማለትን መተው አለባችሁ።” ኢህአፓዎችን ደግሞ “የግለሰቦችን ግድያና ንብረት ማውደምን አቁሙ።” በማለት ሁለቱን ወገኖች በግልፅ እየወቀሰ እንዲቀራረቡ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ መኢሶንና ኢህአፓ እንዲሁም ሌሎች ህቡዕ የፖለቲካ ድርጅቶች በማሌ እርዮተ አለም ዙርያ ተሰባስበው በመሰረታዊ የፖለቲካና ሃገራዊ አጀንዳዎች ላይ ተግባብተው በጋራ ግንባር ስር እንዲሰባሰቡና እንዲሰሩ አለማየሁ ብርቱ ፍላጎት ነበረው፡ መኢሶንና ኢህአፓ በብቸኝነት ስልጣን ላይ ለመውጣት ሲሉ እርስ በርስ ለመጠላለፍ ያደርጉ የነበረውን እሩጫና በሴራ የታጀበ የትግል ሥልታቸውን አለማየሁ ፈፅሞ አይደግፍም ነበር። የእርስ በርስ ሽኩቻና የመጠላለፍ አካሄድ በአገሪቷ ላይ የግለሰብ አባገነንነትን ያስከትላል፣ በዘላቂነት ደግሞ አገራችንንና ህዝቡን ይጎዳል ብሎ ያምን ነበር። ከዚህ ውጪ አለማየሁ በግሉ የስልጣን ፍላጎት ወይም ኢህአፓን በብቸኝነት ለስልጣን ለማብቃት አቅዶ አልተቀሳቀሰም። የእርሱ ጥረት እያሰጋ በመምጣት ላይ የነበረውን የግለሰብ አባገነንነት ወይም ብቸኛ የስልጣን ማዕከልነት ለማስወገድ ብሄራዊ እርቅና የፖለቲካ ትብብር ተፈጥሮ ለኢትዮጵያና ለህዝቡ ጥቅም በጋራ የሚሰራበት ሁኔታ መፍጠር ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል የፖለቲካ ድርጅቶች ያነገቡት ድብቅ ፍላጎትና ይህንኑ ለማሳካት የቀየሱት የሴራ መንገድ ሻምበል አለማየሁን እና ሌሎች አያሌ ሀቀኛ ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆችን ላልተጠበቀ መስዋዕትነት ዳርጓል፡፡
ሻምበል አለማየሁ አላማውን ለደርግ ከማቅረቡ አስቀድሞ እርሱና ጓደኞቹ ስለ ህቡዕ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቋምና አሰራር ጥናትና ግምገማ አድርገዋል፡፡ ሻምበል ፍቅረስላሴ ቢያንስ የዝያን ታሪካዊ ፅሁፍ ይዘትና ዓላማ ለምን በመጽሓፋቸው ውስጥ ለመጥቀስ እንዳልፈለጉ አስገርሞኛል፡፡ ጥናታዊ ፅሁፉ በደርግ አባላት መካከል ለተፈጠረው የሐሳብ መለያየትና ደርግ በአዲስ መልክ ተዋቅሮ የስልጣን ክፍፍል እንዲደረግ የረዳ በ45 ገፅ የተጠናከረ መሰረታዊ ሰነድ ነበር፡፡ ሻምበል ፍቅረስላሴ እንደፃፉት (ገፅ 305)፣ ሰነዱ በኢሕአፓ ተዘጋጅቶ ለነአለማየሁ የተሰጠ ሳይሆን ለዚሁ ተብሎ በተቋቋሙ ኮሚቴዎች የተጠና እና ረቂቁ በአለማየሁ ተስተካክሎ በደርግ ስብሰባ ላይ ለወይይት እንዲቀርብ የተደረገ ነበር፡፡ በተቋቋሙት የጥናት ኮሚቴዎች ውስጥ በህቡዕ የሚሰሩ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት በአባልነት ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል::
እስከማቀው ድረስ ወንድሜ ሻምበል አለማየሁ በባህሪው ግልፅ፣ ነገሮችን በቀና መንገድ የሚመለከት፣ ለግል ጥቅም የማይጓጓ፤ ወዳጆቹን ከልብ የሚወድና የሚያምን፣ ላገሩ ከፍተኛ ፍቅር የነበረው ወጣት መኰንን ነበር፡፡ የነገሮችን አመጣጥ ፈጥኖና አስቀድሞ የመረዳት ችሎታ የነበረው ቢሆንም የፖለቲካ ብልጠት፣ አሻጥር እና ሴራ ግን በፍፁም አያውቅም፡፡ አለማየሁ ሁሉ ነገሩ ፊት ለፊትና በቀጥታ ነበር፡፡ በኔ ግምት ይህ የግልፅነት እና የየዋህነት ባህሪው እንዲሁም በወቅቱ በደርግ ውስጥ ለጊዜው ታይቶ የነበረው የዲሞክራሲ ጭላንጭል አለማየሁን እምነት ስላሳደረበት በፍርሃትና በአድር ባይነት ከመጓዝ ለአመነበት ዓላማ መስዋእትነትን ከፍሎ ማለፉን እንዲመርጥ አድርጎታል፡፡ ይህንን ሁኔታ እኔና ወንድሞቼ እንዲሁም ሌሎች የአለማየሁ የቅርብ ወዳጆች እስከዛሬ በታላቅ ቁጭት የምናስታውሰው ጉዳይ ነው።
ጥር 26 ቀን 1969 የደርግ አባላት ስብሰባ ላይ እያሉ መፈንቅለ መንግስት ተደርጎ አለማየሁንና ሌሎችን ለሞት ያበቃው እርምጃ ታስቦበትና በከፍተኛ ሚስጥር በጥንቃቄ እንደተዘጋጀ የሚታወቅ ነው፡፡ ለዚህ ዝግጅት መጀመር ፋና ወጊ የነበሩት ሻምበል ፍረስላሴ ወግደረስ እንደነበሩ፣ የሰውና የጽሁፍ ማስረጃዎች አሉ። የደርግ አባል የነበረው ወታደር እሸቱ አለሙ የፃፈው መፅሓፍ የሚጠቀስ ነው። እነ አለማየሁ በበኩላቸው ከሊቀመንበር መንግስቱ ሊደርስባቸው የሚችለው አደጋ እውን ከመሆኑ በፊት ቀድመው እርምጃ ለመውሰድ ሻምበል ፍቅረስላሴ እንደፃፉት (ገፅ 316)፣ በእርግጥ ዝግጅት ነበራቸው። በዚህ መሰረት ሊቀመንበር መንግስቱ ጥር 28 ቀን 1969 በቁጥጥር ስር ውለው፣ አድርሰዋል ለተባሉት ጥፋቶች ሁሉ በህግ እንዲጠየቁ ቀደም ሲል ወስነው ነበር፡፡ ይህ የተወሰነው በብርጋዴር ጄኔራል ተፈሪ በንቲ ሰብሳቢነት የተወሰኑ የደርግ አባላት በተገኙበት ስብሰባ ሲሆን፣ ሻምበል ፍቅረስላሴም የዚህ ስብሰባ ተሳታፊና የውሳኔው ተካፋይ ነበሩ፡፡ ታድያ ጥር 28 ቀን ሊታሰሩ የነበሩት ሊቀመንበር መንግስቱ እንዴት ጥቂት ቀናት አስቀድሞ ጥር 26 ቀን 1969 መፈንቅለ መንግስት ለማካሄድ እድሉን አገኙ? እርሶን በቀጥታ የሚመለከተው የዘማቾች በጀት ጉዳይ ከመደበኛ የቅዳሜ ስብሰባ በፊት ሀሙስ እለት በአስቸኳይ አጀንዳ ተይዞ ለውይይት እንዲቀርብ አለማየሁ በዋና ፀሀፊነቱ እንዴት አምኖ ሊቀበል ቻለ? ማንስ አነጋግሮ አሳመነው? ይህ ጉዳይ በቀጥታ እርሶን የሚመለከት ስለሆነ እባክዎትን ሻምበል ፍቅረስላሴ ሃቁን አፍረጥርጠው ይንገሩን፡፡ ከንግዲህ በኋላ ያለው ነገር ሁሉ ፋይዳው ለትውልድና ለታሪክ ስለሆነ የተደበቁ እውነታዎች በሙሉ ይፋ መሆን አለባቸው የሚል ብርቱ እምነት አለኝ፡፡
ሻምበል አለማየሁ ከፖለቲካ ልዩነት ባሻገር በሊቀመንበር መንግስቱ ላይ የግል ጥላቻና ቂም አልነበረውም፡፡ በህይወታቸውም ላይ ጥፋት ለማድረስ አላማና ሃሳብም አልነበረውም፡፡ ሊቀመንበር መንግስቱ ሊያጠፉት እንዳሰቡ ካወቀ በኋላ እንኳን “መንግስቱን እንምታው” እያሉ ለሚጎተጉቱት ወገኖች እንኳን “ይህ ትክክል አይደለም፣ እኔ በነፍስ ማጥፋት አላምንም፣ ጥፋት ካለ ታይቶ በህግ መጠየቅ አለበት እንጂ ለምን ይገደላል?” እያለ ይመልስላቸው ነበር፡፡ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነና “ለምሳ ሲያስቡን ለቁርስ አደረግናቸው” ተብሎ በአደባባይ የተፎከረው በሃቅ ላይ ያልተመሰረተ የሴረኝነት እና የጭካኔ መግለጫ ከመሆን ውጪ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡
ሻምበል አለማየሁ ሊቀመንበር መንግስቱ ላይ የነበረው ቅሬታ ስልጣን በብቸኝነት ጠቅልሎ ለመያዝ የነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎትና ጭካኔ የተሞላው ተግባራቸው ብቻ ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ ሊቀመንበሩ በነበራቸው የማስተባበር ችሎታ ዘወትር አድናቆቱን ይገልፅ እንደ ነበር አውቃለሁ፡፡
በመጨረሻ ሻምበል ፍቅረስላሴ ሻምበል አለማየሁ ታታሪና ጎበዝ ሰራተኛ እንደነበር አያሌ ስራዎችን በብቃት በማከናወን ደርግ ስርአትን ተከትሎ እንዲሰራ ከፍተኛ ጥረትና አስተዋፅኦ ማድረጉን በመፅሐፋቸው ውስጥ ጠቃቅሰዋል፡፡ በቅንነት ላቀረቡት የምስክርነት ቃልም በበኩሌ ላመሰግን እፈልጋለሁ፡፡
መልካም ጊዜ ለሁላችን !
ላቀው አለሙ (ዶ/ር)
Email ፡ [email protected]
Mobile፡ 202 492 0674
የሻምበል አለማየሁን የግል የህይወት ታሪክ በዝርዝር ለማጀጋጀት ስለታሰበ በተለያየ መልኩ ለመተባበር የምትፈልጉ ሁሉ በአድራሻዬ ልታገኙኝ ትችላላችሁ፡፡