Health: ለራስ ምታት ህመም ፍቱን የሆኑ 4 የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች

የውጪ ሀገራትን ያህል ባይሆንም በርካቶች ለትንሹም ለትልቁም ህመም ክኒን ወደ አፋቸው ወርወር ማድረግን ከለመዱ ቆይተዋል፡፡ መድሃኒቶች በአግባቡ ሲወሰዱ የመርዳት አቅማቸው ከፍተኛ የመሆኑን ያህል ከበሽታ አምጪዎች ጋር ሲላመዱ ደግሞ ጣጣቸው ብዙ ነው፡፡ የጎንዮሽ ጉዳቶችንም ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ለህመሞቻችን ሁሉ ሁልጊዜ ክኒኖችን እንድንወስድም አይመከርም፡፡ ቀለል ያሉትን በአካባቢያዊ፣ አመጋገብ እና አጠቃላይ ጤናማ አኗኗር ብቻ ማስታገስ እና ማዳን እንደምንችል ባለሞያዎቹ ይጠቁማሉ፡፡ ለዛሬ ትኩረት ያደረግነው አንዴ ወይም ሌላ ጊዜ አብዛኞቻችን ገጥሞን በሚያውቀው ራስ ምታት ላይ ነው፡፡ መደበኛው ቀላል ራስ ምታት ወይም ጠንካራው ማይግሬይን ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ቀላል መፍትሄ አድርገው ሰዎች የሚወስዱት የራስ ምታት ክኒን ውጠው እንዲሻላቸው መጠበቅ ነው፡፡ ነገር ግን ከክኒኖች በተሻለ ያለጎንዮሽ ጉዳት በምግብና መጠጦች ራስምታቱን በፍጥነት ማስታገስና ማስቀረት እንደሚቻል በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሞያዎች እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ለመደበኛው ራስምታትና ማይግሬይን ፍቱን የተባሉት ምግቦችና መጠጦች የትኞቹ ይሆኑ?
ራስ ምታት የሚደጋግማት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ ማህሌት ግርማ ራስ ምታት ሲጀምራት ሰው ማት ራሱ ያስጠላታል፡፡ የለመደችውን ክኒን ካልዋጠች ፍፁም እረፍት አታገኝም፡፡ ክኒኑ ግን ሁልጊዜ በቅርብ ላይገኝ፣ የተፈገለውን ፈጣን ፈውስም ላይሰጣት ይችላል፡፡ ‹‹አንዳንዴ እናቴ ቡና ታፈላልኝና አንድ ስኒ ስወስድበት ቀለል ይላል፡፡ ምናልባትም ከክኒኑ ቡናው ፍቱን ሳይሆን አይቀርም›› ትላለች ማህሌት፡፡ የማህሌትን ሀሳብ አሁን አሁን የሚደረጉ ጥናቶችም ሳይንሳዊ ድጋፍ እየሰጡት ይገኛሉ፡፡ ቡና ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ተፈጥሯዊ ምግብና መጠጦች ከራስ ምታት ክኒኖች በተሻለ ለቀላሉ ራስ ምታትም ሆነ ከበድ ላለው ማይግሬይን ጥሩ የጎንዮሽ ጉዳት የሌላቸው መፍትሄዎች መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ምስጋና የመጣላቸው ቡና እና የተለያዩ ፍራፍሬዎች በውስጣቸው የያዟቸው ንጥረ ነገሮች ለዚህ አብቅተዋቸዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Health: ዲ.ኤን.ኤ - DNA ለምን ጉዳይ? እንዴት? መቼ?

1ኛ. ቡና
ቡና በሳይንሱ ከፍተኛ ጥናትና ምርምር ከሚካሄድባቸው አነቃቂ መጠጦች አንዱ ነው፡፡ ለአንዳንዶች ቡና ፍቱን የራስ ምታት መድሃኒት ሲሆን ማይግሬይን ላለባቸው አንዳንድ ሰዎች ላይ በብዛት ሲወሰድ ማይግሬይኑን የሚቀሰቅስበት አጋጣሚ አለ፡፡ ሳይንሱ ሁሉንም የቡና ምስጢር ፈትቶ ባይጨርስም እስካሁን ባሉት ትናቶች መሰረት ግን ቡናን ፍቱን የራስ ምታት መድሃኒት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ መጠኑን በልክ ማድረግ አብሮ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ለከባዱ የራስ ምታት ማይግሬይን የሚታዘዙ ክኒኖች ውስጥ የቡና ዋና ንጥረ ነገር ካፌይን ይገኛል፡፡ ስለሆነም ቡና ለራስ ምታት በመፍትሄነት መቅረቡ አስደናቂ ነገር አይሆንም፡፡ ይሁንና መጠኑ በበዛ ቁጥር ራስ ምታትን ከማስታገስ ይልቅ ጭራሽ ሊቀሰቅሰው ይችላል፡፡ ማህሌት ‹‹ብዙ ጊዜ ይህን ሞክሬ ተሳክቶልኛል፡፡ ቡና መድሃኒቴ ነው›› ትላለች፡፡ ሳይንሱም ለዚህ ድጋፉን እየሰጠ ይገኛል፡፡ እጅግም ወፍራም ያልሆነ አንድ ወይም ሁለት ስኒ ቡና ከሁለት ክኒን የተሻለ ተፈጥሯዊ መድሃኒት ሆኖ ተገኝቷል፡፡

2ኛ. ሃብሃብ
ሃብሃብ ወይም በእንግሊዝኛው ወተርሜለን በውስጡ እጅግ ብዙ ፈሳሽ እና ማዕድናትን የያዘ ከፍራፍሬዎችም በትልቅነቱ የሚታወቅ ነው፡፡ በተለይ ከአዲስ አበባ ወደ ናዝሬትና ሐዋሳ መስመር ሲሄዱ በመንገድ ዳር ተሸክመው ሲሸጡት እንመለከታለን፡፡ ሞክረውት እንደሆነ ባላውቅም በጉዞው ወቅት ለሚኖረው ሙቀት እና የውሃ ጥም ሁነኛ መፍትሄ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጥቅሙም ባሻገር ለራስ ምታት ፍቱን መድሃኒት መሆኑ በባለሙያዎች ተጠንቶ ተቀምጧል፡፡ የሪደርስ ዳይጀስት መጽሔት በቅርቡ ባሰፈረው ጽሑፍ ሃብሃብ ለራስምታት ፍቱን ያስባለው ከፍተኛ የውሃ እና ማዕድናት በተለይም ከፍተኛ የማግኒዚየም ማዕድን መጠኑ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ለራስምታት ከሚያጋልጡ ምክንያቶች አንዱ ድርቀት ወይም በሰውነት ውስጥ በቂ ፈሳሽ ያለመኖሩ ነው፡፡ ይህ ፍራፍሬ ደግሞ ይህን ችግር በደንብ ይፈታል፡፡ ከራስ ምታት ክኒን ይልቅ በቅርብ ሃብሃብ ከተገኘ በደቂቃዎች ውስጥ ከራስምታቱ እረፍትን ይሰጣል ብለው ባለሞያዎቹ ይናገራሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኦቦ ዓለማየሁ አቶምሳ እንዴት በምግብ መመረዝ ሊሞቱ ይችላሉ? - በምግብ መመረዝ የሚከሰቱ 4ቱ ገዳይ በሽታዎች

3ኛ. ዝንጅብል
ዝንጅብል ላይ የሚደረጉ ምርምሮች ገና በቅርቡ የተጀመሩ ቢሆንም በውስጡ የደም ቧንቧዎችን መቆጣት እና ህመም የሚቀንሱ መድሃኒቶች ውስጥ ካሉ ኬሚካሎች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ተመራማሪዎች ማግኘት ችለዋል፡፡ በተለይ በከባድ የራስ ምታት ወቅት የደም ቧንቧዎችን መቆጣት በማስከተል ራስምታቱ እንዲቀሰቀስ የማድረግ ተግባር ያላቸውን ፕሮስታግላንዲን የሚሰኙ ንጥረ ቅመሞች መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ራስ መታቱን እንደሚያስታግስ የሪደርስ ዳይጀስት መጽሔት ይገልጣል፡፡ ራስ ምታቱን ሙሉ በሙሉ ባያቆመው እንኳ ከራስ ምታት ጋር የሚመጡ ደስ የማይሉ እንደ ማቅለሽለሽ አይነት ስሜቶችን በቶሎ ይቀንሳል፡፡ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ኢትዮጵያውያን ያለጥናቶቹ ውጤትም ቀድመው ለሆድ ህመም እና ማቅለሽለሽ ዝንጅብል አኝክበት ሲሉ የኖሩት!

4ኛ. ስፒናች
ትኩስ ስፒናች ጎመን ቅጠል በውስጡ የያዛቸው ቅመሞች ራስ ምታትን በማስታገስ ብቻ ሳይሆን የደም ግፊት መጠንን በመቀነስም በቀደመው ጊዜ ጥቅም እንደነበራቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አትክልትና ፍራፍሬ በርካሽ ለሚገኝባቸው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ይህ ጥሩ ዜና ይመስላል፡፡ በውጪው ዓለም ስፒናችን አብስሎ ወይም በትኩሱ ከቲማቲም ጋር ከትፎ በመብላት ብቻ ሳይሆን ጨምቆ ከመጠጣትም ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ የቅርብ ጊዜ ጥናቶች ደግሞ ይህ ፍቱን አትክልት ለራስ ምታትም ፈጣን መፍትሄ ይሰጣል ብለዋል፡፡ ቢፈልጉ ጨምቀው ከሻይ ጋር አለዚም ባዶውን ወይም ትኩሱን ቅጠል ሰላጣ እንደሚያዘጋጁት አዘጋጅተው ቢመገቡት ከራስ መታቱ ፋታ እንዲያገኙ እንደሚረዳዎት የተደረጉ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናቶች አመልክተዋል፡፡

ነገር ግን…
ለራስ ምታት ፍቱን ተብለው በጥናት ስር ያሉ በርካታ ተፈጥሯዊ ምግቦችና ፈሳሾች የሚገኙ ሲሆን በአንፃራዊነት ጥሩ ውጤት ካስገኙት መካከል ጥቂቶቹን አነሳሳን እንጂ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ በዋነኛነት ባለሞያዎች የሚመክሩት ራስ ምታቱን ከማስታገስ ባለፈ ዋናውን የራስ ምታት ምንጭ ፈልጎ መፍትሄ መስጠቱ ላይ ነው፡፡ እንደ ድርቀት፣ ውጥረት፣ ከፍተኛ ድካም መሰል ከስራ እና ማህበራዊ ምክንያቶች መነሻነት የሚመጣውን ራስ ምታት ከክኒን ይልቅ በተፈጥሮ መፍትሄዎች ማስታገስ ቢመከርም ከሰውነት የውስጥ በሽታዎች ምክንያት የሚነሳን ራስ ምታት ግን ምንጩን ካልታከሙት ማስታገስ ይከብዳል፡፡ አልፎ አልፎ ለሚከሰት ራስ ምታት ያነሳሳናቸው አይነት የቤት ውስጥ ቀላል መፍትሄዎች ጥሩ ናቸው፡፡ ተደጋጋሚ ራስ ምታት ግን የባለሞያ እርዳታን ይሻልና ቸል አይበሉት ይላሉ ባለሞያዎቹ፡፡ ራስ ምታት ይደጋግመኛል ስትል ሃሳቧን በመግቢያችን ያጫወተችኝ ማህሌት ከዚህ ምክር ሳትመደብ ትቀራለች ሰላም!

ተጨማሪ ያንብቡ:  Ask Your Doctor: በወሲብ ጊዜ የሚያመኝ ለምንድን ነው?

ከዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ላይ የተወሰደ

1 Comment

Comments are closed.

Share