May 23, 2014
17 mins read

ቀጠሮ ይዣለሁ (አንዱ ዓለም ተፈራ)

 

አንዱ ዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ

አሜሪካ፤ ሐሙስ ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፮ ዓመተ ምህረት

 

እንደማንኛውም ባለቀጠሮ፤ ቀጠሮዬ ደርሶ፤ ከቦታው ተገኝቼ የማደርገውን የግሌን ጉዳይ እንጂ፤ “ሌላው” ጉዳይ አሁን አላስጨነቀኝም። “ሌላው” ያልኩት ትልቁ ጉዳይ፤ የቀጥሮዬ ቀን መቼ እንደሆነ፣ ለቦታው አደራረሴንና በዚያ ስደርስ የሚጠብቀኝን ነው። እነኚህ ለቀጠሮዬ ሕልውና ወሳኝ ቢሆኑም፤ በኔ ቁጥጥር ሥር ስላልሆኑ፤ ለጊዜው ወደ ጎን ገፋ አድርጌያቸዋለሁ። በተጨማሪም እኒህን ጉዳዮች ከናንተ ጋር የምጋራቸው ስለሆነ፤ አብረን እንድናቃናቸው ለሌላ ጊዜ ትቼ፤ በኔ ቁጥጥር ሥር ስላለውና በአእምሮዬ ስለሚዋልለው እንጨዋወት። ቀጠሮዬ ሀገሬ ኢትዮጵያ ለመግባት ነው። ኢትዮጵያ እስከሆነ ድረስ፤ የተወለድኩባትና ያባትና የናቴ አፅም ያረፈባት ጎንደር – አዘዞ ትሁን የተማርኩበትና ብዙ ጊዜ ያሳለፍኩበት አዲስ አበባ፤ ግድ የለኝም። የሀገሬ የኢትዮጵያ ትዝታዬ፤ ብዙ ቦታ ይወሰደኛል። ጓደኞች ያፈራሁባቸው ቦታዎች፣ በአራት ዓመት ውስጥ ስንከራተት፤ ያስተማርኩባቸው ሁለተኛ ደረጃና አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶችና ያሉባቸው ከተማዎች፣ ( ከምባታ – ዋቸሞና ጢምባሮ – ግምቢቹ፣ ይፋትና ጥሙጋ – ደብረሲና፣ መናገሻ – አቃቂ፣ የረርና ከረዩ – ደብረዘይትና ግምቢቹ፣ ተመልሼ መናገሻ – ሰንዳፋ ) እህቴ በዕድገት በሕብረት ዘምታ ሄጄ የጠየቅኋትና ወደኔ ያመጣሁበት ሲዳማ – አለታ ወንዶ፣ በእናቴ የሚዘመዱኝን ልጠይቅ የሄድኩበት እስቴ – ቆማ ፋሲለደስ፣ በአባቴ የሚዘመዱኝን ልጠይቅ የሄድኩበት አዴት – ደብረመይ፣ ሁሉ በትዝታዬ ፊት ይንከራተታሉ። በ፲፱፻፷፮ ዓመት ምህረት ሰላማዊ ሰልፍ የወጣሁባቸው መንገዶች፣ በወቅቱ በትግሉ ዙሪያ ያሳለፍኩባቸው ቦታዎችና ያገኘኋቸው ሰዎች፤ በአእምሮዬ አብረውኝ አሉ። ለስደት ወደ ሱዳን የተንከራተትኩበት የአርማጨሆና የጭልጋ ምድር ሁሉ በአእምሮዬ እየተንከራተተ፤ ምንድን ነው ቀጠሮዬ? ምን አደርጋለሁ? ይኼን ነው እዚህ ላይ ያሰፈርኩ።

በአስተዳደጌ፤ ሀገር ምንነት ነው። እንደደም በሰውነቴ ውስጥ፣ እንደጥላ ከሰውነቴ ውጪ፣ ኢትዮጵያዊነቴ ሁሌም አብሮኝ አለ። እናም ኢትዮጵያን ከኔ አውጥቼ፤ ለኔም ሆነ ለሀገሬ ሕልውና መሥጠት አልችልም። ባደኩበት ኅብረተሰብ የኔን ሕልውና ትርጉም የሠጠሁት፤ የኅብረተሰቡ አካል አድርጌ ስለነበር፤ እኔን ከኅብረተሰቡ ለይቼ ዓይቼ አላውቅም። የኔን ሕልውና ከነበሩት ቀጣይና ለመጭዎቹ መሰላል አድርጌ ነው የማየው። ስለዚህ ምንም እንኳ አሁን ቀንድ ካበቀልኩ በኋላ በመጣሁበት ሀገር፤ ሁሉም “ለራሴ ነው የምኖር” ብሎ አማኝ ቢሆንም፤ እኔ አሁንም በግል መኖር ወይንም የኔን ሕይወት የራሴ የግሌ ብቻ አድርጌ አልወሰድም። እኔን እኔ በማድረግ በኩል፤ ከወላጆቼ ቀጥሎ፤ አካባቢዬና የሀገሬ ሰዎች በሙሉ አስተዋፅዖ አላቸው። ለዚህም ነው በኢትዮጵያዊያን ገንዘብ ሕልውናዬ ተጠብቆ፣ አድጌ፣ ተምሬ፣ በተማሪነቴ ታጋይ ሆኜ፣ ከዩኒቨርሲቲ ተባርሬ፣ ሥራም ይዤ አስተማሪ ሆኜ፣ የኖርኩ። ይህ የምንነቴ አምድ ነው። ከዚህ ውጪ እኔ የለሁም። እናም ማንነቴ ይኼ ነው። ለዚህ ሕይወቴን ታሣሪ አድርጌዋለሁ። እናም ይህ፤ ምን ጊዜም በምኞቴም ሆነ በሕልሜ የምመላለስበት የግል የአእምሮዬ ጓዳ ነው። አብረውኝ በትግል ዓለም ውስጥ ያለፉት አሁንም በኑሮዬ አብረውኝ አሉ። ለምን ይኼን ዓይነት ኑሮ እንደምኖርና ወደፊት ሀገሬን እንደምመኝ ግልፅ ነው።

ቀጠሮዬ ደርሶ ኢትዮጵያ ስገባ ምን አድርጋለሁ። በመጀመሪያ ደረጃ ቀጠሮዬ ደርሶ ኢትዮጵያ እንደምደርስ፤ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም። ዘንድሮ ለግንቦት አስራ አምስት አልደረስኩም። ለመጪው የ፳፻፮ ዓመተ ምህረት እንቁጣጣሽ ላልደርስ እችላለሁ። አዎ ራሱን “የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር” ብሎ ከሚጠራው መንግሥት ጋር ጠብ አለኝ፣ ትግራይን አልፎ ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይት በገባ ጊዜ፤ ያኔ በነበርኩበት የድርጅት ሠራዊት አባል ሆኜ ጦርነት ገጥመን ቆስያለሁ። ይህ ወገንተኛና አምባገነን ቡድን በሥልጣን ላይ እያለ ሀገሬን ማየቴ አይታሰብም። እርግጠኛ ሆኜ የማምነው ግን፤ ውሎ አድሮ ፀሐይ ነገ መውጣቷ እንደማይቀር ሁሉ፤ ይህ ቡድን ይወድቃል፤ እኔም ሀገሬን አያለሁ። ብቻዬን ደግሞ አይደለሁም። የተለያዬ የግል መንገድ ቢኖረንም፤ ከሞላ ጎደል በዚሁ ጥላ ሥር ያለን ብዙዎች ነን።

የምመለስባት ኢትዮጵያ ከነበርኩባት ኢትዮጵያ የተለየች እንደምትሆን ጥርጥር የለኝም። ሕይወቴን በሙሉ የታጋልኩለት የሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብት መከበር ሀቅ የሆነባት ኢትዮጵያ ትሆናለች። የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መብት በሕግና በተግባር የተጠበቀባት ትሆናለች። የሕግ የበላይነት የሠፈነባት ትሆናለች። የሕዝቡ ሉዓላዊነት ያላንዳች ማቅማማት የተረጋገጠባት ትሆናለች። መቼም እንደኔ ከሀገሩ የወጣ ሁሉ፤ የሀገራችን የኢትዮጵያ መሪ አይሆንም። ሁሉም የኢትዮጵያ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ አምባሳደር አይሆንም። ሁሉም የአዲስ አበባ ባለሕንፃ አይሆንም። ሁሉም በዘመናዊ መኪና ተንፈላሳሽ አይሆንም። ሁሉም በለሙ የኢትዮጵያ መሬት ባለሠፊ እርሻ አይሆንም። ሁሉም ነጋዴ አይሆንም። ሁሉም የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ተጫዋች አይሆንም።  እያንዳንዱ የራሱ የሆነ የተማረበት፣ የሠለጠነበትና ልምድ ያካበተበት ሙያ ይዞ እንደሚገባ እርግጠኛ ነኝ። በዚህም ሀገራችንን ኢትዮጵያን ብዙ ወደፊት እንደምናራምዳት ቅንጣት ታክል ጥርጥር የለኝም። እናም ቀጠሮ የያዝኩት ለዚህ ነው።

በቅርቡ እናቴን በቦታው ተገኝቼ ልቀብራት አልቻልኩም። መቃብሯን ሄጄ አያለሁ። ቦታው ባንድ ላይ በሆነው ባባቴ መቃብርም፤ ብዙ ጊዜ እየተመላለስኩ ለማየት ዕቅድ አለኝ። የጠለምትን ውጣ ውረድ እሄድበታለሁ። በደሴ አልፌ አሲምባ – ስንገደን መጎብኘት እወዳለሁ። ወልቃይት ጠገዴን በየመንደሩ እየሄድኩ ሰዎችን ማግኘት፤ ቦታውን መቃኘት እፈልጋለሁ። ኑሮዬን የት እንደማደርግ ቁርጥ ያለ ዕቅድ ባይኖረኝም፤ ሀገራችን ብዙ የተለያየ ሙያ ያላቸው ሰዋች እንደሚያስፈልጋት ስለምረዳ፤ ባንዱ የሙያ ዘርፍ ገብቼ ወገኔን እንደማገለግል ጥርጥር የለኝም። ተማሪ ነበርኩ መምህር ነበርኩ፤ ዋናው ካገሬ ያወጣኝና በውጭ እንድቆይ ያደረገኝ ለሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብት መታገሌ ነውና፤ ይህ ሲተገበር፤ ራሱ በቦታው ሆኖ ማየቱ፤ የመኖሬን ትርጉም ተጨባጭ ያደርገዋል። እናም በጣም እጓጓለሁ። እዚህም ትንሽ ተምሬ ሙያ አካብቻለሁ። ልምድም ሸምቻለሁ።

ሰዎችን ወደፊት እንዲመለከቱ የሚያደርጋቸው ተስፋ ነው። ተስፋ ደግሞ መነሻው ተጨባጭ የሆነ ክስተት አለው። ወደ ሀገሬ ተመልሼ ለመሄዴ ተስፋዬ፤ አሁን በሀገራችን ያለው የዴሞክራሲ ጥማትና የታጋዩ ብዛት ነው። በዞን ዘጠኝ አርበኞች ምን ያህል እንደምኮራና እንደምቀናባቸው የልቤን አውጥቼ ልናገር ብል፤ መግለጫ ቋንቋው አይበቃኝም። በምንም መንገድ ቢተረጎም ሁላችን የምንፈልገው፤ ረሃብን ከሀገራችን አስወግደን፣ በሺታን በቁጥጥር ሥር አውለን፣ እያንዳንዷ ኢትዮጵያዊት በሀገሯ የትም ሠርታ የመኖር መብቷ ገደብ ሳይኖርበት፣ ሀብት ለማፍራትና ትዳሯን ለመመሥረት አዛዥ ሳይጫናት፣ ልማትና ትምህርት የተሥፋፉባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ነው። ይህ ዋናው ዕሴታችን ነው። ይህ በተግባር ላይ ይውላል። ያኔ ዞረን ብዙ ነገሮችን እንቃኛለን። ያኔ የየራሳችንን ፓርቲዎች በሕዝቡ ፊት እያቀረብን እንወዳደራለን። በቃኝ ብዬ የማልተወው ነገ ቢኖር፤ አሁን ፓርቲ ባይኖረኝም ከሚስማማኝ ጋር ተላትሜ፤ በሀገሬ የፖለቲካ ምኅዳር ተካትቼ ዴሞክራሲያዊ መብቴን መጠቀምና፤ ተሳትፎ ማድረግ ነው። ያኔ ያንድ ቡድን አዋቂነትና ብቸኛ ገዥነት በመጽሐፍ የሚነበብ ይሆናል። የሕዝቡን ሉዓላዊነት በተግባር እንረዳለን። ያኔ መምህሮችና ተማሪዎች እንሆናለን። ከዚያች ቀን ጋር ቀጠሮ ይዣለሁ።

ያኔ በየትኛውም የሀገራችን ኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊት ሁሉ፤ አባታቸው ማነው? እናታቸው ማናት? ደማቸው ከየትኛው ወንዝ ይቀዳል? ምን ቋንቋ ይናገራሉ? ሃይማኖታቸው ምንድን ነው? ስንተኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል ሳይባል፤ ሁሉም እኩል ኢትዮያዊና ኢትዮጵያዊት፤ እኩል መብት ያላቸው ይሆናሉ። በሕግ ፊት ሁሉም እኩል ይታያሉ። የሀገሪቱ መሪ እንደኔ እኩል ከፍርድ ፊት ይቀርባል/ትቀርባለች። ያኔ ኢትዮጵያዊነት ይከበራል። ያኔ የሃይማኖት ነፃነት በገሃድ ይታያል። ያኔ የማመንም ሆነ ያለማመን፣ የራሱን ፈጣሪ የመሰየምም ሆነ በተሰየመው ለመካተት፤ ሁሉም መብት ይኖረዋል። ያኔ የግል ማንነትን ራሱ ግለሰቡ እንጂ ማንም ሊተረጉምለት እንደማይችል ሕጉ ይደነግጋል። ያኔ በኢትዮጵያ ምድር እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊና እያንዳንዷ ኢትዮጵያዊት በግለሰብ ኢትዮጵያዊት ብቻ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን፣ የሥራ ተግባራቸውን፣ የንግድ ስምሪታቸውን ያከናውናሉ። በትምህርት መስክም ሆነ በውትድርና፣ በተቀጣሪነትም ሆነ በቀጣሪነት፤ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ይሆናል መለኪያው። ለዚያ ቀን ቀጠሮ ይዣለሁ።

ያ ብቻ አይደለም። ልቤ ትልቅ ነው። በያንዳንዱ የስፖርት ዘርፍ ግንባር ቀደም ከሚሠለፉት ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ ትገኛለች። ያኔ የሚወለዱ ልጆች ረሃብንና በሽታን በታሪክ መጽሐፍት ብቻ ነው የሚያውቋቸው። ያኔ አረንጓዴ ብጫና ቀይ ቀለም ያለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በየቦታው ሲውለበለብ ልባችን በደስታ ይፈነድቃል። በኒው ዮርክ ማራቶን፣ በፊፋ የዋንጫ ሽልማት ጊዜ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትንንሽ አረንጓዴ ብጫና ቀይ ስንደቅ ዓላማውን አንስቶ፤ ሌሊቱ እንዳይጨልም ይሟገታል። የሳይንስ ሊቆች፣ የሕክምና ፈላስፎች፣ የምርምርና ጥናት አዋቂዎች በየመንገዱ ይታያሉ። ለሙ ያገራችን መሬትና ያገራችን ሆድ ዕቃዎች፣ የምርት መዛቂያ ይሆናሉ። ለዚያ ቀን ቀጠሮ ይዣለሁ።

በነገራችን ላይ፤ አብሮ ከኔ ጋር ቀጠሮ ላማድረግ ለሻ ሁሉ፤ ወጪያችንን ለመጋራትና ለመተባበር ዝግጁ ነኝ። [email protected]

Latest from Blog

ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop