Health: የሚያሳፍሩ 6 ታላላቅ የጤና ችግሮች እና ቀላል መፍትሄዎቻቸው

ከሰዎች ጋር ትልቅ ስብሰባ ሊጀምሩ ተዘጋጅተዋል፡፡ ክብ ሰርታችሁም ለመወያየት ተዘጋጅታችኋል፡፡ መናገር ሲጀምሩ አጠገብዎ ያሉ ሰዎች ፊታቸውን አዙረው ነው የሚያዳምጡዎት፣ በቅርብ ያሉትም ራቅ ብለው ነው የሚሰሙዎት፡፡ ትንሽ ግራ ቢገባዎትም ቀጥለዋል፡፡ በስብሰባው እረፍት ሰዓት በጣም የቅርብ የሚሉት ወዳጅዎ ጠጋ ብሎ መጥፎ የአፍ ጠረንዎ ሰዎችን እንዳራቃቸው ነገረዎት፡፡ ይህ አይነት ነገር ገጥሞዎት ያውቃል? ከገጠመዎት ብቻዎትን አይደሉም፡፡ የእርስዎን አይነት መጥፎ የአፍ ጠረን፣ መጥፎ የእግር ሽታ፣ ላብ፣ የወሲብ ድክመት አሊያም ፍላጎት ማጣት፣ ሽንት ማምለጥ እና ሌሎችም ለተመልካቹ የሚያሳፍሩ የጤና እክሎች በርካቶች ይገጥማቸዋል፡፡ ለማውራትና ምክርን ለመጠየቅ ሰዎች ቢያፍሩባቸውም፡፡ ጥቂቶቹን ብቻ መርጠን ለዛሬ ልናወጋችሁ ተዘጋጅተናል፡፡
ይህን ጽሁፍ ከዘ-ሐበሻ ድረገጽ ሰርቀን ነው ያመጣነው

6. ሽንት ሲያመልጥ
አንዳንድ ጊዜ በጣም የሚያስቅ ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ ሽንትዎ አምልጦዎት ይሆናል፡፡ ይህ ከስንት አንዴ የሚፈጠር እና ለክፉም የማይሰጥ ነውና አያሳስብዎ፡፡ ነገር ግን መቆጣጠር የማይችሉት እና ተደጋጋሚ የሽንት ማምለጥ ለሰሚው ግራ ይሆናል እርስዎንም ያሳፍርዎታል፡፡
በሽንት ማምለጥ ምክንያቶች መካከል ከሽንት ቧንቧ መቆጣት እስከ ስኳር ህመም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከልክ ያለፈ ካፌይን በሻይና ቡና መጠጣት እንዲሁም ብዙ አልኮል መጠጣትም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሊያስቀምጥዎት ይችላል፡፡ በተለይ በቅርቡ የወለዱ ሴቶች ላይ ይህ ሊከሰት ይችላልና የወር አበባውን እንደሚቀበሉ ሁሉ ይህንንም ለተወሰነ ጊዜ በዚህ ይቆጣጠሩት፣ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ችግሩ ይፈታል፡፡
ባለሞያዎች ይህ ሁኔታ ተደጋግሞ ከገጠመዎት ሙሉ ምርመራ አድርገው የጤና ችግሮችን መፍታትን ቀዳሚ መፍትሄ ያደርጋሉ፡፡ የጤና እክል ከሌለ ደግሞ የፈሳሽ አወሳሰድ መጠንና የሚያጠነክሩ ኤክሰርሳይሶችን ማድረግ ይመከራል፡፡

5. መጥፎ የአፍ ጠረን
በዕለት ተዕለት ህይወታችን ከበርካታ ሰዎች ጋር እንገናኛለን፣ እናወራለን፡፡ ታዲያ ሰዎች ቀረብ ሲሉን ከአፋችን የሚወጣው ጠረን ክፉ ከሆነ ሰዎች እኛን በሩቁ ማለታቸው አይቀርም፡፡ በተለይ እኛ ዘንድ የሰዎችን ህፀፅ በግልፅ መናገርና እርምት እንዲወሰድበት ከማድረግ ይልቅ ለሶስተኛ ሰው ማስተላለፍ በበርካቶች ዘንድ የሚታይ በመሆኑ ሳናውቀው በሰዎች ወደ መጠላት ልንሄድ እንችላለን፡፡

መጥፎ የአፍ ጠረን ከበላነው ምግብ፣ በጥርሶቻችን መካከል ከተጠራቀመው የምግብ ቅሪቶች አሊያም እንደ ጨጓራ ህመምን ከመሰሉ መነሻዎች ሊከሰት የሚችል ሲሆን በቂ ኦክስጅን አፍ አለማግኘቱ እና ንፅህናው አለመጠበቁ ናቸው አስረጅ ምክንያቶች፡፡ አፍ በተፈጥሮው በርካታ ባክቴሪያዎች አሉት፡፡ እነዚህ ባክቴሪያዎች ጥቅማቸው ሌሎች በሽታን አምጪ ባክቴሪያዎች በአፍ ውስጥ እንዳይራቡና በሽታም እንዳያመጡበትን መከላከል ነው፡፡ ባክቴሪያዎቹ የሚኖሩትም በጉሮሮ እና ምላሳችን እንጂ ጥርሳችን ላይ አይደለም፡፡ በመሆኑም ጥርስን መቦረሽና መታጠብ፣ ጥርስ እንዳይበሰብስ ከማድረግ እና መጥፎውን ሽታ ለጊዜው ከመሸፈን ያለፈ ጥቅም አያስገኝም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Health: HPV ክትባት አብዛኛውን የአባለዘር እከክ (Genital Warts) እና አብዛኛውን የማኅጸን ነቀርሳ (Cervical Cancer) ለመከላከል ያስችላል

ዋናው መጥፎ የአፍ ጠረን መነሻ ከሌሎች ጎጂ ባክቴሪያዎች ሊከላከሉልን አፍ ውስጥ የሚቀመጡት ባክቴሪያዎች ኦክስጅን በሚያጡበት ወቅት የሚያመነጩአቸው ሰልፈር የተባለውን ኬሚካል የያዙ ንጥረ ነገሮች ናቸው፡፡ ሽታውም የሰልፈሩ ነው፡፡ ባክቴሪያዎቹ ኦክስጅን እንዳያገኙ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ለረጅም ጊዜ አፍን ዘግቶ መቀመጥ፣ የአልኮል ስሪት የሆኑ አፍ መጉመጥመጫ ፈሳሾችን መጠቀም እንዲሁም አንዳንድ መድሃኒቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ነጭ ሽንኩርት በተፈጥሮው ሰልፈር ኬሚካሎችን በብዛት የሚይዝ በመሆኑ ነጭ ሽንኩርት እና ተመሳሳይ ቅመም የበዛባቸውን ምግቦች ስንወስድ አፋችን መጥፎ ጠረን ማምጣቱ አይቀርም፡፡

በመሆኑም ቀዳሚ መፍትሄው አፋችን በቂ ኦክስጅን እንዲያገኝ መፍቀድ፣ ውሃ በብዛት መጠጣት በዚህ ካልተመለሰም የተፈጠረውን ሰልፈር የሚያረክስ ክሎሪን ዳይ ኦክሳይድ የያዘ የአፍ መጉመጥመጫ መጠቀምን ባለሞያዎች ይመክራሉ፡፡ በኦክስጅን የበለፀጉ አትክልቶችም መልካም መፍትሄዎች ናቸው፡፡ የመጨረሻው ወደ ጥርስ ሐኪም ሄዶ ምክር መጠየቅ ይሆናል፡፡

4. መጥፎ የእግር ሽታ

እንደ በርካታ የሰውነት ክፍሎቻችን ሁሉ እግርም በርካታ መደበኛ ባክቴሪያዎች አሉት፡፡ እነዚህ ባክቴሪያዎች የሚያመነጩአቸው ፈሳሾች ከካልሲ እና ጫማ ውስጥ ከሚፈጠር እርጥበት ጋር ሲገናኙ መጥፎ ጠረን ያመጣሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እግር ንፁህ በማይሆንበት ወቅት እና ላብ ከእነዚህ የባክቴሪያዎቹ ኬሚካል ጋር ሲገናኝ መጥፎው ጠረን ይፈጠራል፡፡ ፈንገሶችም የራሳቸው አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ መጥፎ የእግር ጠረን ችግር መሆኑን ተቀብለው መፍትሄ የሚፈልጉ እንዳሉ ሁሉ አፍነውት በመቀመጥ ለሰውም ለራሳቸውም ጤና ጠንቅ የሚሆኑ፣ ሰው በተሰበሰበበት ጫማ ማውለቅ የሚያሳቅቃቸውም በርካታ ናቸው፡፡
ችግሩ በቀላል የንፅህና እርምጃዎች ሊፈታ የሚችል በመሆኑ እግርን በየቀኑ መታጠብ፣ ካልሲዎችን በየዕለቱ መቀየር፣ እግር ከታጠቡ በኋላም በንፁህ ፎጣ ሙሉ በሙሉ ሳያደርቁ ካልሲና ጫማ አለማድረግ ይመከራል፡፡ ከዚህ የበረታ ከሆነ የባለሞያ ምክር ያስፈልግዎታል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Health: ጽንስ ያለጊዜው እንዲወለድ የሚያስገድደው ደም ግፊት ለእናቶች ሞትም 14 በመቶ ድርሻ አለው ተባለ

3. ጋዝ ማስወጣት፣ ‹‹መፍሳት››

ማንም ይህ ችግር አለብኝ ብሎ ሊናገር የማይፈቅደው ችግር ነው ብዙ ጋዝ ማስወጣት (መፍሳት)፡፡ አሳፋሪ የሚባል እና የሰዎች መሳለቂያ ስለሚያደርግም ድንገት በሰው መሀል ያመለጠው ሰው የሚገባበት ቀዳዳ ያጣል፡፡ አብዛኞቻችን በተለያየ ጊዜ ይህን ጋዝ የምናስወጣ ቢሆንም አንዳንዶች ላይ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ማህበራዊ ህይወታቸው ላይም ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡
ለፈስ ምክንያት ከሚባሉት መካከል የምንወስዳቸው የምግብ አይነቶች ቀዳሚው ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ ባቄላ፣ ጎመን እና መሰል ምግቦች ብዙዎቻችን የምናውቃቸው ውጤታቸውንም የምንረዳቸው ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ጋዝ የበዛባቸው ለስላሳ መጠጦች እና ማስቲካም እንዲሁ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ መጠጦችን በስትሮው መጠጣት እና ምግብን ሳያላምጡ በፍጥነት ወደ ሆድ መላክ ተጨማሪ ሰበቦች ናቸው ሲሉ ባለሞያዎች ያስቀምጧቸዋል፡፡ መነሻዎቹ ከታወቁ እነዚህኑ ማስወገድ ላይ በርትቶ መስራትን የሚጠቁሙት ባለሞያዎች በስርዓት አላምጦና ተረጋግቶ መብላት፣ ፈስ የሚያበዙ ጥራጥሬዎችን እና መጠጦችን በልክ ማድረግን ይመክራሉ፡፡ ከዚህ ያለፈ ችግር ከሆነና በተለይ የጨጓራ ህመም ጋር የሚያያዝ ችግርን ከሐኪም ምክር ጋር መፍትሄ በማድረግ ከችግሩ ነፃ መሆን ይቻላል፡፡

2. በወሲብ ወቅት የወንዶች ቶሎ ዘርን ማፍሰስ

ከወሲብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በግልፅ መወያየት ብዙም ባልዳበረበት አገራችን ርዕሰ ጉዳዩ ሲነሳ ብዙዎች ከየራሳቸው ችግር ጋር በማያያዝ ሲወያዩበት ይደመጣል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይ ወንዶች እንዳሉባቸው በግልፅ የማያምኑባቸው እና ለመወያየት ከማይፈቅዱት ርዕስ አንዱ በወሲብ ግንኙነት ወቅት የዘርፈሳሽን በቶሎ መርጨት ነው፡፡ ችግሩ የሴቷን ስሜት አለመጠበቅንና የጋራ እርካታን ስለሚያሳጣ የወንዱን በራስ መተማመን ሲሸረሽር የሴቷን እርካታ ይነጥቃል፡፡
የዘር ፈሳሽን ከሚፈልጉት ባነሰ ጊዜ ቶሎ የመርጨት ችግር አንዳንድ ባዮሎጂካዊ መነሻዎች አሉት ቢባልም በአብዛኛው ከጭንቀት፣ ፍርሃት እና የወሲብ ልምድ ማነስ የሚነሳ መሆኑን ባለሞያዎች ይጠቁማሉ፡፡
የዘር ፈሳሽን በቶሎ መርጨት የሚለው አባባል አንፃራዊነትን የሚያሳይ በመሆኑ ፈጥኗል ወይም ዘግይቷል ለማለት መነሻ እንደሚያስፈልግ አንዳንድ ባለሞያዎች ይጠቅሳሉ፡፡ ግንኙነቱ በተጀመረ በአማካይ አብዛኛው ወንድ ከ4-10 ደቂቃ ጊዜ ውስጥ ይረጫል፡፡ ከዚያ ያነሰ ሲሆን ቶሎ ዘሩን አፍስሷል ሊባል ይችላል፡፡ ይሁንና ከዚህ ይልቅ ስምምነት ያገኘ የሚመስለው ሀሳብ ሴቷን እርካታ ጫፍ እስካደረሰ ድረስ የሚቆይበት ጊዜ አነሰም በዛም ፋይዳው ብዙ አይደለም የሚለው ነው፡፡
የሆነው ሆኖ የዘር ፈሳሽን ቶሎ መርጨት በእርግጥ ችግር የሆነባቸው እና ግንኙነቱም ላይ ተፅዕኖ እያደረገ ከሆነ፣ ከውስጥ በሽታ በተለይ ፕሮስቴት ችግር ጋር ዝምድና ካለው ይህን በምርመራ መለየት እና መታከም ይመክራል፡፡ ውስጣዊ ህመሞች ከሌሉት አዕምሮአዊ ሁኔታዎችን በማስተካከልና እራስ የማዘግየት ቴክኒክን በመተግበር ችግሩን ማሸነፍ ይቻላል፡፡
አዕምሮዎትን ነፃ ያድርጉ፣ ወሲብ የሚፈፅሙት በጣም ምቾት በሚሰማዎ ጊዜ እና ቦታ እንዲሁም ጓደኛ ጋር መሆኑን ያረጋግጡ፣ መነጋገርን ይልመዱ፡፡ ይህን ከተገበሩ በኋላ ደግሞ በወሲብ ወቅት ወደ መርጨት እና እርካታ የቀረቡ ሲመስልዎት ያቁሙ እና እንደገና ይጀምሩ፡፡ ‹‹Coping with premature Ejaculation›› የሚለው መፅሐፍ ላይ እነዚህ ሀሳቦች ያሰፈሩት ዶ/ር ባሪ ማካተርቲ የዚህ ቴክኒክ ውጤት 95 በመቶ ስኬታማ ያደርጋል ይላሉ፡፡ ስፖርት መስራትና ጡንቻዎችን ማዳበር እንዲሁም ዮጋ ለዚህ ተመካሪ ሆነው ቀርበዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Health: ስለ ኩላሊት ጠጠር ሊያውቁ የሚገባዎት 5 ነገሮች

1. የወሲብ ፍላጎት መቀዝቀዝ፣ ማጣት
የወሲብ ፍላጎት እና መነሳሳትን ማጣት የበርካታ ጥንዶች መለያየት ምክንያት የሚሆን ለውይይትም የሚከፈት እክል ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ ሳይኮሎጂያዊ እና ከስሜት ጋር የተያያዙ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ከተጠማጅዎ ጋር ወሲብ የመፈፀም ፍላጎትዎ ከቀነሰ ወይም ከሞተ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ወደ ሐኪም ከመሄድ በፊት በግንኙነቱ ውስጥ ችግር ይኖር እንደሆነ ይፈትሹ፡፡ ሁለታችሁም ጋር የተጣላችሁበትም ሆነ የተከፋችሁበት ጉዳይ ከሌለ የጤና ችግሮች ከእናንተ በተቃራኒ እየሰሩ፣ ችግርም እየሆኑአችሁ ስለሚሆን ይህን እንዲፈትሹ ባለሞያዎች ይመክራሉ፡፡ ቀዳሚ ችግር ፈጣሪ ሊሆን የሚችለው ድብርት እና የአዕምሮ መረጋጋትን ማጣት ነው፡፡ ድብርት ከጥቂት ሰዓታት አልፎ ለወሲብ መነሳሳት ሲያሳጣ የአዕምሮ ህመም ሊሆን ስለሚችል ከወሲብ አጋር ጋር የስነ አዕምሮ ባለሞያን ማማከር ይገባል፡፡ ውስጣዊ ህመሞች ከሆኑም የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ያማክሩ፡፡ ሁሉም መፍትሄ ሲፈለግ በጋራ ሊሆን ይገባል፡፡ አለዚያ ብቻዎን መብሰልሰልዎት ለግንኙነቱ መቋረጥ መነሻ የመሆን እድል ይኖረዋል፡፡
ችግሩን የተናገረ መፍትሄ አያጣም፡፡ አንዳንዶቹ ችግሮች ሲያነሷቸው የሚያሳፍሩ ቢመስሉም ሊያፍሩባቸው አይገባም ብለን ይኸው አንስተናቸዋል፡፡ እኛ በጣም ጥቂቶቹን አንስተናል፣ መፍትሄም ጠቁመናል፡፡ ይሞክሩአቸው ባለሙያም ያማክሩባቸው፡፡ ጤና ሰንብቱ!

1 Comment

Comments are closed.

Share