ይድረስ…
መቼም ለአርቲስት ‹‹አድናቂህ ነኝ›› ከሚለው ቃል በላይ የልቡን የሚያደርስለት ሌላ ቃል አይኖርምና ከመቶ ሃያ ክፍሎች በላይ ለተሻገረው ድራማችሁ ያለንን ልባዊ አድናቆት በማስቀደም እንጀምራለን፡፡ እንኳን በርካታ ተመልካቾች የወደዱትን ረጅም ድራማ መፃፍ ቀርቶ አንዲት ገፅ ደብዳቤ አሣክቶ መፃፍም ራሱን የቻለ ጥበብ ይጠይቃል፡፡ ድራማችሁ ይህን ያህል ርቀት ሲጓዝ ጠንካራዎቹን እያደነቅን፤ ደካማዎቹን ተዋንያን ደግሞ በልባችን እየተቸን ዕድሜ ሠጥቶን እዚህ ደርሠናል፡፡ ታዲያ ከሠሞኑ ገብታችሁበታል የተባለው ውዝግብ እኛም በልባችን ይዘነው የተቀመጥነውን ቅሬታ እናወጣ ዘንድ ምክንያት ሆነን፡፡
ሰው ለሰዎች ሆይ!
ድራማችሁን የሚያስተላልፈው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና የሰው ለሰው ባለቤት ስፓርክስ የፊልም አምራች አልተግባቡም የተባለው እውነት ይሆን? የንትርካችሁ መነሻ ደግሞ ድራማውን ቶሎ ጨርሱት የሚል ነው አሉ፡፡ እናንተም’ኮ አበዛችሁት፤ ቅዳሴ እንኳን ረዘመ ብሎ የሚያጉረመርም ህዝብ ባለበት ሀገር ድራማን ማንዛዛት ምን የሚሉት እርፍና ነው? ከሶስት ሺህ ዘመን ታሪካችን በቀር በዚህች ሀገር ምን ረጅም ነገር አለ? ዕድሜያችን አጭር፣ ደስታችን አጭር፣ የእግር ኳስ ስኬታችን አጭር…… ታዲያ ምን ታይቷችሁ ነው የድራማውን ዕድሜ የማቱሳላ ለማድረግ የቆረጣችሁት? ኢቴቪም’ኮ እውነቱን ነው የቴሌቪዥን ጣቢያና ስፖንሰር ተገኘ ብላችሁ ታሪኩ ቀድሞ ያለቀ ነገር እንደመስቲካ ስታላምጡ ሌላ ዓመት መጨመር ነበረበት? ቀድሞም ያደነቅናችሁ እኮ ለድራማው ጥሩነት እንጂ ለተንዘላዘለ እድሜው አልነበረም፡፡ ‹‹ታዲያ ታሪኩን ሰብሰብ አድርጋችሁ ጨርሱት›› የሚል ደብዳቤ እስኪረደርሳችሁ ድረስ ተመልካች ተገኘ ብሎ ድራማን ማንዛዛት ምን ይጠቅማል? ደግሞ ይህ ተመልካች ቤቱ ድረስ የመጣለትን ድራማ ማየቱ ሥራችሁን ለመውደዱ እንዴት ዋስትና ይሆናል? እንኳን ድራማ የኢቴቪ ዜናና ዶክመንተሪዎችንም ልባችን እያዘነ እንኳ እንመለከት የለ? ታዲያ የታየ ሁሉ ይወደዳል እንዴ?
ሠሞኑን የድራማችሁን መንዛዛት አስመልክቶ በአንድ የፌስ ቡክ ገፅ ላይ የተለጠፈ ፅሑፍ ተመልክተን ነበር፡፡ ምነው ድራማውን አንዛዙት፡፡ ይህንንም ቶሎ እንዲጨርሱልን ለቻይናውያን አሳልፈን እንስጣቸው እንዴ? ለዚህም ቻይናውያን ይምጡልን? የሚል ሃሳብ የያዘ ፅሁፍ ነበር፡፡ እንግዲህ ስንት የኑሮ ጥያቄዎች አናታችን ላይ የሚጨፍሩብን አንሶ ከጥበቡ ይልቅ ቢዝነሱ የበዛ የሚመስል አንድ ድራማ ለምን ተንዛዛ ብለን መቼም ሰልፍ አንወጣም፡፡ እናንተ ግን ምነው የአየር ሠዓቱን የስልጣን ወንበር ይመስል ሙጭጭ አላችሁበት?
ሰው ለሰዎች ሆይ!
ድራማችሁ የተበላ እቁብ ሆኗል እየተባለ ነው፡፡ ህዝቡ ታሪኩን ቀድሞ ጨርሶታል፡፡ ከሐዋሳ እስከ ዱባይ የተንሸራሸራችሁባቸው የተለያዩ መቸቶችም ሆን ተብሎ ስፖንሰር ለማብዛትና ቢዝነሳችሁን ለማሳደግ እንጂ የግድ ሆነው የተደረጉ አይመስለንም፡፡ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ተዋናዮችን እየለዋወጣችሁ የምታሣዩን ድራማ ይሁን እግር ኳስ እጅግ ግራ አጋብታችሁን ነበር፡፡ ተቀያሪ ተዋናዮቹን እንደምንም እየለመድን ስንመጣ ደግሞ በፕሮዲውሰሮች መካከል አለመግባባት ተፈጠረ ተባለ፡፡ ‹‹ደራስያኑ ሥነ-ምግባራቸው ብልሹ ነው፤ ከእነርሡ የማይጠበቅ ነገር ሊያደርጉ ሞክረዋል›› የሚል አይነት ክስ ከአንዷ የቀድሞ የድራማው ተዋናይ ተነገረ፡፡ በዚህም አዘንን፡፡
ሰው ለሰዎች ሆይ!
የእናንተ ጉዳይ በዚያ ብቻ ሳያበቃ ከሰሞኑ ደግሞ ድራማችሁን እንድትጨርሱት ብቻ ሳይሆን እንዴት መጨረስ እንዳለባችሁም ትዕዛዝ ተሰጥቷችኋል አሉ፡፡ ምናልባት ድራማን በትዕዛዝ ለመጨረስ በዓለም የመጀመርያዎቹ ደራስያን በመሆን በጊነስ የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ሳትመዘገቡ አትቀሩም፡፡ እናንተስ ‹‹ታሪኩን ሰብስበን መጨረስ አልቻልንም›› ማለታችሁ አሳፋሪ አይደል? ሰው እንዴት የበተነውን ታሪክ መሰብሰብ ያቅተዋል? ለነገሩ አስናቀን የሚያህል ትልቅ ገፀ ባህሪ ፈጥራችሁ ከከፍታው ለማውረድ ሳትቸገሩ የቀራችሁ አይመስለንም፡፡ ቀድሞስ ሳይቸግራችሁ ራሳችሁ ላይ ማን አንግሡት አላችሁ? ወይ ለምን መላው ከጠፋችሁ የአስናቀን ነገር እንደ ዩክሬኗ ክሬሚያ ‹‹በህዝበ ውሳኔ›› አትዳኙትም?
ሰው ለሰዎች ሆይ!
መቼም አስናቀ-መር የሆነ ድራማችሁ መቋጫው እንደ ምፅዓት ዘመን ከሚርቅ የህዝቡን ውሳኔ ሰምታችሁ አስናቀን ወይ በቁጥጥር ስር ታውሉት አልያም የአሸናፊነት ቁልፉን ሰጥታችሁን፡፡ ታሪኩን ታጠናቅቁልን ይሆናል፡፡ የረዘመ ነገር ሁሉ መች ይወደዳል? ፍቅር እስከመቃብር የተወደደው’ኮ በስነ-ፅሑፋዊ ውበቱና ከዘመኑ ቀድሞ የተገኘ በመሆኑ እንጂ እንዲሁ በመዘርዘሙ ብቻ አልነበረም፡፡ ስለዚህ እባካችሁ እድሜው ላይ ብቻ ሳይሆን ውበቱ ላይ ተጨንቃችሁ ለድራማችሁ የደራሲነት መላ ስጡት፡፡
ሰው ለሰዎች ሆይ!
በእርግጥ እናውቃለን የድርሠት ፍዳ እልህ አስጨራሽ ነው፡፡ ያንን ሁሉ ባለሙያ በአግባቡ እየመሩ ተወዳጅ የሆነ የቴሌቪዥን ድራማ ማቅረብ ትልቅ የሙያ ክህሎትና ሀላፊነት ይጠይቃል፡፡ ቢሆንም ግን በየጊዜው የምትገቡበት እሠጥ አገባ ለስማችሁ ጥሩ አይደለም፡፡ እኛም በድራማችሁ ላይ ባሳያችሁን ብቃት እንጂ በፍርድ ቤት ባደረጋችሁት የመካሠስ ታሪክ ልናስታውሳችሁ አንሻም፡፡ የድራማውን ግማሽ ሰዓት የሚወስድ የስፖንሰር ሽፋን እንዳላችሁ እየታወቀ በባንካችሁ የተቀመጠው ገንዘብ ሠባ ዘጠኝ ብር ብቻ እንደነበር መስማታችን ደግሞ ሌላው አነጋጋሪ ነገር ነው፡፡ መቼም ድራማውን ለፅድቅ እንደማትሠሩት እናንተም፤ እኛም አሳምረን እናውቃለን፡፡ ዱባይ ድረስ እየሄዳችሁ የምትሠሩት ድራማ ያስገኘላችሁ ትርፍ ‹‹የህዝብ ፍቅር›› ብቻ ከሆነ ይኸው የህዝቡን ፍቅር አግኝታችኋልና ድራማችሁን መላ በሉት፡፡ እባካችሁ!
ምንጭ፡ ይህ ጽሁፍ የተገኘው ከቁም ነገር መፅሔት 13ኛ ዓመት ቅፅ 13 ቁጥር 177 ይድረስ… ዓምድ ነው፡፡