May 22, 2014
43 mins read

የአሜሪካ የሸፍጥ ዲፕሎማሲ “አስቂኝ የመድረክ ትወና”

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

የኦባማ አስተዳደር የሰብአዊ መብት አያያዝ ፖሊሲ “አስቂኝ የመድረክ ትወና ነውን”?  

የዩናይትድ ስቴትስ የመንግስት መምሪያ ጸሐፊ የሆኑት ጆን ኬሪ ባለፈው ሳምንት የሶሪያን ፕሬዚዳንት ባሽር አላሳድን “አሸባሪ” ወንጀለኛ ናቸው ብለው ከፈረጁ በኋላ የአላሳድ የቀጣዩ ዓመት የምርጫ ዕቅድም “አስቂኝ የመድረክ ትወና” ነው ብለው ተችተው ነበር፡፡ ኬሪ በመቀጠልም እንዲህ በማለት ሀሳባቸውን አጠናክረው ነበር፣ “አሳድ ከአሸባሪ ኃይሎች ጋር ህብረትን ፈጥረዋል፣ አሸባሪዎችንም እያቀረቡ እና እየረዱ ነው፣ እናም በእራሳቸው ህዝብ ላይ አሸባሪነትን በመፈጸም ዕኩይ ተግባራት ላይ ተዘፍቀው ይገኛሉ፡፡“ እንዲሁም ኬሪ የሚከተለውን ነገር አጽንኦ በመስጠት ተናግረዋል፣ “የአሳድ ፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ዕቅዶች ለታዕይታ የተዘጋጁ አስቂኝ የመድረክ ትወናዎች ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ ለመተግበር የሚደረጉ ምርጫዎችም በህዝብ ላይ የሚካሄዱ ዘለፋዎች ናቸው፣ እንደዚህ ዓይነቶቹ ዕኩይ የምርጫ ዕቅዶች በሶሪያ እና በዓለም ህዝቦች ዴሞክራሲ ላይ የሚቃጡ ሸፍጦች ናቸው፣“ ብለው ነበር፡፡

አሳድ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሶሪያን ህዝብ አሳር ፍዳውን በማሳየት ላይ የሚገኙ እና በዘመኑ የሰውን ልጅ ከሚያሰቃዩ አምስት የመጀመሪያዎቹ ወሮበላ ወንጀለኞች ምድብ ውስጥ እንደሚካተቱ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ እ.ኤ.አ ሜይ 2007 በተደረገው ምርጫ ባሽር 97.6 በመቶ ድምጽ በማግኘት ለሰባት ዓመታት ለሁለተኛ ጊዜ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ፡፡ በዚያን ጊዜ የአሜሪካን የዉጭ  ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የነበሩት ማኮርማክ እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላልፈው ነበር፣ “በሶሪያ ያለው ገዥ አካል ዕጩ ተወዳዳሪዎች እንደልብ በህዝቡ ውስጥ ተንቀሳቅሰው ሀሳባቸውን በመግለጽ መመረጥ እንዳይችሉ ለማድረግ በህዝቡ ላይ እየፈጸመ ባለው ማስፈራራት እና በሰላማዊ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው ላይ የሚያራምዱት ግፍ የተሞላበት ጭቆና ላይ የቀረበው ዘገባ ዩናይትድ ስቴትስን ያሳስባታል፡፡ የሶሪያ ህዝብ ተማዕኒነት ያለው ግልጽ እና በህዝቡ ሙሉ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ድባብን በመፍጠር ፍትሀዊ ምርጫ የማድረግ እና የሚወክሉትን ዕጩዎች መምረጥ እንዳይችል ባሽር አላሳድ መብቱን ቀምተውታል“ በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡ ስለአሳድ “አስቂኝ የምርጫዎች ትወና መድረክ” ማውሳት አዲስ ነገር አይደለም፡፡

እ.ኤ.አ ማርች 2011 የቀድሞ የየአሜሪካን የዉጭ  ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሂላሪ ክሊንተን ደም ለተጠሙት ባሽር አላሳድ (በሺዎች የሚቆጠሩ የሶሪያ ሰላማዊ ህዝቦችን ካለፈው ኦክቶበር ጀምሮ ቢያንስ 14 ጊዜ በኬሚካላዊ መሳሪያ ለጨፈጨፉት) መልካም ስብዕና ጥብቅና ቆመው ተስተውለዋል፡፡ እንዲህ በማለትም ሀሳባቸውን አጠናክረው ነበር፣ “በአሁኑ ጊዜ በሶሪያ ለየት ያለ መሪ አለ፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት ወደ ሶሪያ በመሄድ ጉብኝት አድርገው የተመለሱት በርካታ የሁለቱም ፓርቲዎች (ዴሞክራቶች እና ሬፐብሊካኖች) የኮንግረስ አባላት አላሳድ የለውጥ አራማጅ ሀዋርያ በመሆናቸው ላይ እምነት እንዳላቸው ገልጸው ነበር “ ብለዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በአንድ ጊዜ ተቀይሮ ከሶስት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አሳድ “የለውጥ አራማጅ ሀዋርያ” መሆናቸው ቀርቶ ወደለየለት “አሸባሪነት” እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ተዋናይነት ተቀይረው ተገኙ፡፡ እንደ ሂላሪ አባባል የት ይደርስ የተባለ ወይፈን አጎንብሶ ሲጠባ ተገኘ መሆኑ ነውን?

በእኔ የአዕምሮ ዕይታ ኬሪ በአላሳድ ላይ እያሰሟቸው ያሏቸው የውግዘት ቃላት ተመሳሳይ ጥያቄዎችን እንዳነሳ ያስገድዱኛል፡፡ የኦባማ አስተዳደር የሰብአዊ መብት አያያዝ ፖሊሲ “ለአስቂኝ የመድረክ ትወና” የዲፕሎማሲ አካሄድ ነው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላልን? በዓለም ላይ “ሸፍጥ” ለመስራት የተቀነባበረ ተንኮል ነውን? ይህ ሁኔታ ሆን ተብሎ ህዝብን እና የሰብአዊ መብት ጥበቃን ለመዘለፍ እና ለማዋረድ የሚደረግ ደባ ነውን? የኦባማ አስተዳደር የሰብአዊ መብት አያያዝ ዲፕሎማሲን በአስመሳይነት ወይም ደግሞ “በዲፕሎክራሲ” (የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት አያያዝ ፖሊሲውን አስመሳይነት ለመግለጽ የተጠቀምኩበት ትርጉም ነው) ሰበብ ተጨባጭነት በሌለው መልኩ ለይስሙላ እየተጠቀመበት ነውን? ማንም ቢሆን አመልካች ጣቱን በሌሎች ሰዎች ላይ ሲቀስር ሶስቱ ጣቶቹ ተቀስረው ወደ እራሱ እንደሚያመለክቱ በጥንቃቄ መገንዘብ ይኖርበታል፡፡

እ.ኤ.አ ኤፕሪል 2013 የመንግስት መምሪያ ቃል አቀባይ የነበሩት ኬሪ ኒኮላስ ማዱሮ በቤንዙዌላ በምርጫ አሸንፈው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መሆናቸውን እውቅና እንደማይሰጡ እና እንደማይቀበሉ አሳወቁ፡፡ ማዱሮ ያንን ምርጫ በጣም በጠበበ ሁኔታ 50.66 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸንፈው ነበር፡፡ የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ የነበሩት ሄንሪክ ካፕሪልስ ስለምርጫው ነጻ እና ፍትሀዊ አለመሆን ጉዳይ አስመልክቶ ዝርዝር ታሪኩን ከተናገሩ በኋላ ኬሪም የእርሳቸውን ሀሳብ በመቀበል የሀሳባቸው ተጋሪ በመሆን እንዲህ ብለው ነበር፣ “ስለምርጫው ዝርዝር ማብራሪያ መሰጠት የነበረበት መሆኑን እናምናለን…በግልጽ ለመናገር ከፍተኛ የሆኑ የምርጫ ግድፈቶች ተከስተው ከሆነ ስለሚመሰረተው የማዱሮ መንግስት ቅቡልነት በርካታ ጠንካራ ጥያቄዎችን የምናነሳ ይሆናል“ ብለው ነበር፡፡ በተጨማሪም የኋይት ሀውስ ቤተ መንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት ጃይ ካርኔይ በተመሳሳይ መልኩ ስለምርጫው አፈጻጸም ዝርዝር ማብራሪያ መቅረብ እንዳለበት በመግለጽ መግለጫ አወጡ፡፡

ዚምባብዌ እ.ኤ.አ ኦገስት 2013 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ባካሄደችበት ወቅት ኬሪ እንዲህ ብለው ነበር፣ “በግልጥ በማያሳስት መልክ እንየው፣ በአገር ውስጥ እና በአህጉራዊ የምርጫ ታዛቢዎች በቀረበው ዘገባ መሰረት በርካታ ግድፈቶች የተንጸባረቁበት ምርጫ  መሆኑን የገለጹ ቢሆንም ዩናይትድ ስቴትስ በዛሬው ዕለት ይፋ የሆነው የምርጫ ውጤት የዚምባብዌን ህዝብ ፍላጎት የሚያሟላ ነው የሚል እምነት የላትም…የቀረበው ማስረጃ እንደሚያረጋግጠው የዛሬው የምርጫ ውጤት የረቀቀ እና ጥልቅ የሆነ የምርጫ ማጭበርበር ሂደት ማክተሙን ያረጋገጠ ነው “ ብለው ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ሙጋቤ በዚያን ጊዜ በተካሄደው  ምርጫ 61 በመቶ ድምጽ በማግኘት ነገር ያሸነፉት፡፡

እ.ኤ.አ ሜይ 2010 በኢትዮጵያ በተካሄደው ፓርላሜንታዊ ምርጫ በቅርቡ ያረፉት አቶ መለስ ዜናዊ 99.6 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸንፊያለሁ ብለው ሲያውጁ ዩናይትድ ስቴትስ ሁኔታው “የሚያሳስበን እና በጉዳዩም ላይ ያለንን ጥልቅ ስጋት እንገልጻለን” በማለት የተለመዱ እና አሰልች የግዴታ አይነት የቃላት መግለጫዎችን ከመስጠት በዘለለ ስለምርጫ ዘረፋው ህገወጥነት በተጨባጭ በመሬት ላይ የሚታይ  ያደረጉት አንድም ድርጊት አልነበረም፡፡ የኋይት ሀውስ ብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ የሆኑት ሚክ ሀመር እንዲህ ብለው ነበር፣ “ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን የምርጫ ሂደቱን ከታዘበ በኋላ ባወጣው መግለጫ መሰረት ምርጫው ዓለም አቀፍ የምርጫ መስፈርትን አያሟላም፣ ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ላይ ያለንን ስጋት እንገልጻለን፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ባለስልጣኖች በምርጫው ዕለት ከአገሪቱ ርዕሰ መዲና ወጣ በማለት በየአቅጣጫው ተዘዋውረው የምርጫውን ሂደት ለመታዘብ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ያልተሰጠው በመሆኑ የተሰማንን ቅሬታ እንገልጻለን፡፡ ነጻ የሆነ የምርጫ ታዛቢ ያለማግኘት እና ባሉት የነጻ ሜዲያ ተወካይ ታዛቢዎች ላይ የሚደረገው የማሸማቀቅ ስራ ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በጣም የተወሳሰበ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ከምርጫው ዕለት በፊት እንኳ ነጻ እና ፍትሀዊ የምርጫ ከባቢ አልነበረም… ለነገሩ እ.ኤ.አ በ2010 በኢትዮጵያ የተካሄደው “ፓርላሜንታዊ ምርጫ” አስቂኝ የምርጫ ትወና መድረክ ነበርን? የዚህ ዓይነት መሰሪ እና ዕኩይ ተግባራት በኢትዮጵያ ህዝብ እና በዓለም ላይ የሚካሄድ ዘለፋ እና በዴሞክራሲ ላይ የሚደረግ ሸፍጥ ነውን?“

በዝንጀሮ ቆንጆዎች መካከል የቀንጅና ውድድር አይካሄድም ሆኖም ግን ዩናይትድ ስቴትስ ባሽር አላሳድ 97.6 በመቶ ድምጽ በማምጣት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን አሸንፈዋል በማለት ስታወግዝ በኢትዮጵያ በተደረገው ፓርላሜንታዊ “የብዙሀን ፓርቲ” ተብዬ ምርጫ አቶ መለስ ዜናዊ 99.6 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸነፍኩ ብለው ድንፋታ ሲያሰሙ ዩናይትድ ስቴትስ አልሰማሁም፣ አላየሁም በማለት ጆሮ ዳባ ልበስ ብላለች፡፡

የኦባማን የሰብአዊ መብት መርህ መገንዘብ፣

የኦባማ የሰብአዊ መብት አያያዝ መርህ ግልጽ እና ቀጥተኛ ይመስላል፡፡ የሰብአዊ መብት አያያዝ ፖሊሲ የማውጣት ስራ በዋናነት ከሁለት ሰይጣኖች መካከል የትኛው የተሻለ ምርጫ ሊሆን ይችላል እንደማለት ነው፡፡ ዓለም እንደ እነ አሳድ፣ ሙጋቤ እና ማዱሮ ባሉ በሰው ልጆች ላይ ወንጀልን የሚፈጽሙ የተጠሉ “ሰው በላ ጭራቆች” የተሞላች ናት፡፡ እንዲሁም እንደ የግብጹ ኢል ሲሲ ፣ የኡጋንዳው ሙሴቤኒ፣ የሩዋንዳው ካጋሜ እና በቅርቡ በህይወት የተለዩት የኢትዮጵያው አቶ መለስ ዜናዊ በሰው ልጆች ላይ ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊቶችን የፈጸሙ እና አሁንም በመፈጸም ላይ ያሉ የተሻሉ ““ሰው በላ  ጭራቆች” ናቸው፡፡ በሁለቱ ጭራቆች መካከል ያለው ልዩነት የኋለኞቹ የእኛው “ሰው በላ ጭራቆች” መሆናቸው ነው፡፡ የእራሳችንን ስራ ይሰሩልናል፡፡ ትዛዛችን ይቀበላሉ:: ለዚህ ውለታቸው ደግሞ ነጻ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ይፈቀድላቸዋል፡፡ በየዓመቱ በምጽዋት ስም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ዶላሮች እንሰጣቸዋለን፡፡” በማለት ዩናይትድ ስቴትስ ሀሳቧን አጠቃላለች፡፡

እ.ኤ.አ በ2008 ዕጩ ተመራጭ ኦባማ በማያቋርጥ ሁኔታ በየጊዜው በዋሽንግተን በሚወጡት “እምነት የማይጣልባቸው” “የውጭ ፖሊሲ መርሆዎች” ላይ የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸው ነበር፡፡ ይህንን ጉዳይ በማስመልከት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ልንታገላቸው ከሚገቡን ጠላቶች መካከል በእርግጠኝነት አንዱ አሸባሪነት ብቻ አይደለም… ይልቁንም እምነት የለሽ መሆንም አንዱ እና ዋናው ነው፡፡ “በስድስት ዓመታት የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የኦባማ የሰብአዊ መብት ጥበቃ አያያዝ ፖሊሲ ደጋፊዎቻቸው ኦባማን ወደ ታማኝ የለሽነት አውቶብስ ጎማ ስር ውስጥ ወርዉረዋቸዋል፡፡ የሂዩማን ራይትስ ዎች ዋና ዳይሬክተር የሆኑት  ኬን ሮዝ በቅርቡ የሚከተለውን ምልከታ አድርገው ነበር፣ “ፕሬዚዳንት ኦባማ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን ቀዳሚ የትኩረት አጀንዳ አድርገው ባለመያዛቸው ምክንያት በርካቶችን አሳዝነዋል፡፡“ ወሳኝ በሆኑ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ለመደራደር የሚያሳዩት ዝግጁነት ለሰብአዊ መብት ጥበቃ መርሆዎች ያላቸውን ቁርጠኝነት አናሳ መሆን የሚያመላክት አስተሳሰብን ይፈጥራል፡፡ “በዓለም ላይ ያሉ ህዝቦች ሁሉ ለነጻነታቸው እና ለመብቶቻቸው መጠበቅ የጋራ የሆነ ፍላጎት ያላቸው መሆናቸውን“  ኦባማ የረሱት ይመስላል፡፡

እ.ኤ.አ በ2008 ፕሬዚዳንት ኦባማ በጋና አክራን ሲጎበኙ ለአፍሪካ ወጣቶች ባደረጉት ንግግር ላይ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈው ነበር፣ “ታሪክ ከጀግኖቹ አፍሪካውያን/ት ጎን ነው“ በማለት ማረጋገጫ ከሰጡ በኋላ እንዲህ ብለው ነበር፣ “መሪዎቻችሁ ለሚሰሯቸው ማናቸውም ስራዎች ሁሉ በህዝቡ ዘንድ ተጠያቂዎች እንዲሆኑ የማድረግ ስልጣኑ አላችሁ፣ እናም ህዝቡን ሊያገለግሉ የሚችሉ ተቋማትን መገንባት እና ማጠናከር አለባችሁ፡፡“ በቅርቡ ኦባማ ከእነዚያ ወጣት እና ጀግና ኢትዮጵያዊውያን/ት አፍሪካውያን/ት ወጣቶች እርሳቸው “እምነት ማጣት” እያሉ በሚጠሩት ከፍተኛ ዋጋ ሰጥተውት በነበረው ጉዳይ ላይ በድንገት ትልቅ ፈተና ገጥሟቸው ተስተውለዋል፡፡ በካሊፎርኒያ ግዛት በሳን ጆሴ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነው ጋዜጠኛ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አበበ ገላው በኋይት ሀውስ ድረገጽ ላይ እንደተለቀቀው ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር የሚከተሉትን የሃሳብ ልውውጦች አድርጓል፣

አበበ ገላው (የስብሰባው ታዳሚ አባል)፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ! ለኢትዮጵያ ነጻነት! ነጻነት! ነጻነት ለኢትዮጵያ ጌታዬ!

ፕሬዚዳንት፡ ለትንሽ ጊዜ ቆይ፡፡ በምትለው ጉዳይ ላይ እስማማለሁ ሆኖም ግን ስጨርስ ኋላ ለምን አላነጋግርህም፣ ምክንያቱም ለመጨረስ እየተቃረብኩ ነው

(የመሳቅ ዓይነት አዝማሚያ እያሳዩ)፡፡ እኔ እና አንተ ስለጉዳዩ እንነጋገራለን፡፡ ወደዚያው አካባቢ እየመጣሁ ነው፡፡

አበበ ገላው (የስብሰባው ታዳሚ አባል)፡ (አይሰማም)–

ፕሬዚዳንት፡ እዚያ ሂድ

አበበ ገላው (የስብሰባው ታዳሚ አባል)፡ (አይሰማም)–

ፕሬዚዳንት፡ በምትለው ጉዳይ ላይ አስማማለሁ፡፡

አበበ ገላው (የስብሰባው ታዳሚ አባል)፡ (አይሰማም፡፡)

ፕሬዚዳንት፡ ከአንተ ለመስማት እፈልጋለሁ፡፡

አበበ ገላው (የስብሰባው ታዳሚ አባል)፡ እንወድዎታለን!

ፕሬዚዳንት፡ እኔም እወዳችኋለሁ፡፡ ብቻ የንግግሬን መጨረሻ አበላሸህብኝ፡፡ ቢሆንም ምንም አይደለም፡፡ (ሳቅ እና የድጋፍ ጭብጨባ ከታዳሚው አስተጋባ፡፡) እሺ፡፡ ይህች አገር የመናገር ነጻነት የተከበረባት ናት– (የድጋፍ ጭብጨባ እንደገና አስተጋባ)– ይህም ታላቅ ነገር ነው፡፡

ለአምላክ/አላህ ምስጋና ይግባውና በአሜሪካ የመናገር ነጻነት አለን፡፡ አንድ ተራ ጋዜጠኛ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ግለሰብ በቁጥጥር ስር እውላለሁ ብሎ ሳይፈራ፣ እታሰራለሁ ብሎ ሳይሰጋ፣ ድብደባ ወይም ደግሞ ስቃይ ይደርስብኛል ብሎ ሳያስብ  ለዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ቀጥ ብሎ ቆሞ በነጻነት መናገር ይችላል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ እና አበበ በአንድ ዓይነት ስሜት ሆነው ነው የተነጋገሩት፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ጋዜጠኛ አበበ የንግግራቸውን መጨረሻ እንዳበላሸባቸው በቀልድ መልክ ተናግረዋል፡፡ አበበ ግን የኦባማ የሰብአዊ መብት አያያዝ ፖሊሲ የትውልድ ሀገሩን እያበላሻት እንደሆነ በቁም ነገር ተናግሯል፡፡

ከዚህ ክስተት ልንማረው የምንችለው ታላቅ ቁም ነገር በዓለም ላይ ታላቅ ስልጣን እና ኃይል ያለው ሰው እና አንድ ተራ ዜጋ በዓለም መድረክ በአንድ ላይ መቆማቸው ነው፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም በነጻነት ላይ በተለይም በመናገር ነጻነት ላይ እምነት አላቸው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አበበ ገላው በሳን ጆሴ ከተማ በመገኘት ድምጻቸውን ያሰማላቸው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን/ት የመናገር ነጻነት ወይም እምነትን በነጻ የማራመድ ነጻነት ወይም ደግሞ የመሰብሰብ ወይም ለሚፈጸሙባቸው በደሎች ቅሬታ የማቅረብ ነጻነት የላቸውም፡፡ ለዚህም ነው አበበ ገላው ድምጹን ከፍ አድርጎ ለኢትዮጵያውያን/ት ወገኖቹ ነጻነት ሲል “ፕሬዚዳነት ኦባማ! ነጻነት ለኢትዮጵያ!“ እያለ የጮኸው፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ በኢትዮጵያ እና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የመናገር ነጻነት እና ሌሎች ነጻነቶች እንዲኖሩ እምነት ያላቸው በመሆኑ ጉዳይ ላይ ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ጥያቄው ተያያዥነት በሌላቸው ባዶ የተስፋ ቃላትን በማነብነብ የተግባር ኮስማና እና ድሁር የመሆናቸው እና የአፍሪካን ወሮበላ አምባገነኖች በጽናት የመደገፋቸው ጉዳይ ነው፡፡ ኦባማ በኢትዮጵያ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ በእርግጠኝነት እምነት ያላቸው ከሆነ ለምንድን ነው እርሳቸው ወይም (የእርሳቸው የመንግስት መምሪያ ጸሐፊ፣ አምባሳደሮች እና ተወካዮቻቸው) የእርሳቸውን የመናገር ነጻነት እና በኢትዮጵያ በእስር ቤት የሚማቅቁትን ጋዜጠኞች እና ጦማሪስቶች እንደ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ውብሸት ታዬ፣ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ፣ ተስፋለም ወልደየስ፣ ኤዶም ካሳዬ፣ አቤል ዋቤላ፣ አጥናፍ ብርሀኔ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ዘላለም ክብረት እና በፈቃዱ ኃይሉ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል እንዲፈቱ ጥረት ሲያደርጉ የማይታዩት፡፡

ነጻነት በነጻ የማይገኝ መሆኑን ፕሬዚዳንት ኦባማ በእርግጠኝነት ማወቅ አለባቸው፡፡ ተግባርን አግልሎ በረዥሙ ምላሳቸው ስለይስሙላ ነጻነት ብቻ ማውራት ርካሽ ንግግር ነው፡፡ በተደጋጋሚ እየተደረጉ ያሉት በጣም በርካታ ሆኖም ግን እርባናየለሽ ንግግሮች ናቸው፡፡ እናም በኢትዮጵያ ነጻነት እጅግ ውድ የሆነ ዋጋ ተከፍሎበት የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ውብሸት ታዬ እና ሌሎቸም የእራሳቸውን ድሎት ሰውተው ለነጻነት የሚከፈለውን ክቡር ዋጋ በመክፈል ላያ ናቸው፡፡ ለሰው ልጆች የነጻነት ክብር ሲሉ በእስር ቤት ውስጥ በመማቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ትንታንግ የነጻነት ታጋዮች የመኖር ሚስጥሩ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙትን ወንጀሎች ለመታገል ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ2005 ወደ 200 አካባቢ የሚጠጉ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ ሰላማዊ የነጻነት ታጋዮች ለነጻነት ሲሉ ክቡር ህይወታቸውን መስዋዕት አድርገዋል፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች ሩብ ምዕተ ዓመታትን ባስቆጠረው የአምባገነኖች የአገዛዝ ስርዓት ለነጻነት ሲሉ ውድ ህይወታቸውን ገብረዋል፡፡ የእነዚህ ንጹሀን ዜጎች ገዳዮች በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ በከፍተኛው የስልጣን ወንበር ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው እና ያለምንም ተጠያቂነት ደረታቸውን ነፍተው በአውራ መንገዶች እንደ ነጻ ሰው ሁሉ ሰው መስለው በወንጀል ባህር ውስጥ ሲዋኙ እንዳልቆዩ እና አሁንም እየዋኙ እያሉ መሆናቸው እየታወቀ ነጻ እና ከወንጀል የጸዱ በመምሰል ደረታቸውን ገልብጠው ሲንገዋለሉ እና ሲኮፈሱ ይታያሉ፣ የቁርጥ ቀን የማይመጣ መስሏቸው፡፡ ኦባማ አነዚህን ወሮበላ አምባገነኖች በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ዶላሮች በመለገስ በስልጣኖቻቸው ላይ ተጣብቀው ህዝብን ሲያሰቃዩ እንዲኖሩ ያደርጓቸዋል ብሎ መናገር ማጋነን አይሆንም፡፡ ተዋቂዋ የአፍሪካ የኢኮኖሚክስ ምሁር የሆኑት እና “የበከተ እርዳታ/Dead Aid” የሚለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ዳምቢሳ ሞዮ እንደዘገቡት “በኢትዮጵያ በጣም ግዙፍ የሆነው በጀት 97 በመቶ የሚሆነው የመንግስት በጀት የሚመጣው ከውጭ እርዳታ ነው፡፡“ ብለዋል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በኢትዮጵያ ያለዜጎች ይሁንታ በጉልበት በስልጣን ላይ ተፈናጥጦ ለሚገኘው ወሮበላ ገዥ አካል ሽማግሌ አናትም አባትም ናት! በአሁኑ ጊዜ 90 ሚሊዮን የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ክብሩን እያጣ እየተሰቃየ፣ ኢፍትሀዊነት ድርጊት እየተፈጸመበት እና መብቱ በወሮበላዎች እና በሙስና በበከቱ ደንቆሮ መሪዎች ነን ባዮች መዳፍ ስር ወድቆ አሳር ፍዳውን በመቀበል ላይ ይገኛል፡፡

የኦባማን የሰብአዊ መብት አያያዝ ፖሊሲዎች እና መርሆዎች ከሚናገሯቸው ባዶ የሰብአዊ መብት ንግግሮች ለመለየት አይቻልም፡፡ ለአሳድ በምናባቸው “ቀይ መስመር” በማስመር የሶሪያን ህዝብ ሊጭርስ የሚችል ኬሚካላዊ መሳሪያ መጠቀም እንዳይችሉ የተሰመረውን ቀዩን መስመር እንዳያልፉ ያስጠነቅቋቸዋል፡፡ ባለፉት በርካታ ወራት አሳድ ይህንን ኬሚካላዊ መሳሪያ በመጠቀም ቢያንስ 14 ጊዜ ተግብረውታል፡፡ ለአፍሪካ ወሮበላ አምባገነኖች ኦባማ ቀጥሉ የሚል አረንጓዴ መብራት በማሳየት በቀዩ መብራት የሰብአዊ መብት ወንጀሎች እንዲፈጸሙ  ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

የአቦማ አስተዳደር የሰብአዊ መብት መርሆዎች እንዲከበሩ ከልብ ተነሳሽነቱን የማያሳይ ከሆነ በተስፋ የሚያስሞሉ እና የዜጎችን ቀልቦች የሚገዙ ታላላቅ መግለጫዎችን እና ንግግሮችን በሚሊዮኞች ለሚቆጠሩ ለዓለም ዓቀፉ የማህበረሰብ አባላት በተደጋጋሚ ማሰማቱ ፋይዳው ምንድን ነው? የኦባማ አስተዳደር ይህን አሰልች እና አደንቋሪ የውሸት የሰብአዊ መብት አጠባበቅ መዝሙር ሲያሰማ ህዝቡ በሚደሰኮረው ዲስኩር እና በተጨባጭ ምንም የተደረገ ነገር ያለመኖሩን ሊያገናዝብ የሚችል አዕምሮ የሌለው ደደብ እና ደንቆሮ አድርገው ሊቆጥሩት ይሞክራሉን? ለምንድን ነው አቦማ በተደጋጋሚ በተግባር ሲያውሏቸው የማይታዩ የአስመሳይነት እና እምነተቢስነት ንግግሮችን እንደበቀቀን እየደጋገሙ ሲናገሩ የሚደመጡት? ፕሬዚዳንት ኦባማ! እስቲ ቆም ብለው ያስተውሉ፣ የአፍሪካ ወሮበላ አምባገነኖች በጊዜ ሂደት የሰብአዊ መብት ጥበቃን የሚያራምዱ እና መርሆዎቻቸው አድርገው ለመተግበር እንደገና ሊበራል ዴሞክራቶች ሆነው ይወለዳሉ ብለው ያስባሉን? የአረም አበባዎች አድገው ጽጌረዳ ይሆናሉን?

ላሜሪካ የሰብአዊ መብት የሚተካ ኢሰብአዊ ፖሊሲ የቀረበ ሀሳብ፣

ኦባማ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የሰብአዊ መብትን በኢሰብአዊ ፖሊሲ መቀየሩ ይበጃል፡፡ የእርሳቸው ስልታዊ የሆኑ ብሄራዊ የሀገር ጥቅሞችን ብቻ በሚያስገኙ ተግባራዊ የፖለቲካ ተግባራት ላይ ብቻ ማተኮራቸው የሞራል ሰብዕናን እና ትክክል ያልሆኑ የፖለቲካ እሴቶችን እንዲያሽቆለቁሉ አድርጓቸዋል፡፡ በሌላ አባባል ስለሰብአዊ መብት ጥሩ እና ጥሩ ያልሆኑ ንግግሮችን ይናገራሉ፡፡ አምባገነናዊ ስርዓት ስለሚያከትምበት እና ዴሞክራሲ በዓለም ላይ ስለሚያብበት ሁኔታ ይናገራሉ ሆኖም ግን የአሜሪካንን የአጭር ጊዜም እንኳ ቢሆን ብሄራዊ ጥቅሟን ከሚነካ አካሄድ ጋር ለሰከንድ እንኳ በፍጹም የሚታሰብ ጉዳይ አይደለም፡፡

እንደ ትክክለኛው አካሄድ ኦባማ የዩናይትድ ስቴትስን “የተሳሳተ የኢሰብአዊ ፖሊሲ” ቢያንስ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ በመርህ ደረጃ በመመስረት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በአፍሪካ ሲፈጸሙ ዩናይትድ ስቴትስ ተመልክታ ጆሮ አልባ መሆኗን ማሳወቅ አለባት፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ የኢሰብአዊ ፖሊሲ መብት መርሆዎች በሚከተሉት ቀላል ሀሳቦች ላይ የተመሰረቱ ይሆናሉ፡አፍሪካ በምዕራቡ ዓለም እንደሚታሰበው ወይም ደግሞ በተግባር እንደሚስተዋለው የሰብአዊ መብት ጥበቃ አስፈላጊዋ አይደለም፡፡ “ሰላም እና መረጋጋት” ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪካ ላይ የምታራምደው ትልቁ እና ጠቃሚዋ የፖሊሲ አካሄድ መሳሪዋ ነው፡፡ በአፍሪካ አምባገነን መሪዎች የሚፈጸሙ ሰብአዊ ወንጀሎች ሌሎች አለመረጋጋቶችን እና ግጭቶችን ይወልዳሉ ከሚል የተሳሳተ እምነት አንጻር ዩናይትድ ስቴትስ አይታ እንዳላየ፣ ሰምታ እንዳልሰማ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ታልፈዋለች፡፡ (ለምሳሌ ያህል በደቡብ ሱዳን ሳልቫኪር እና ሬክ ማቻር በሚያደርጉት ሰይጣናዊ ድርጊት ሰበብ ለፈጸሙት ግድያ፣ እልቂት፣ ዘር ማጥፋት፣ ህዝብን በኃይል ከሚኖርበት ቀየ ማፈናቀል፣ እስራት፣ ስቃይ አስገድዶ መድፈር እና የጎሳ ዘር ማጥፋት ወንጀሎች ከተጣያቂነት ነጻ ነው የሚሆኑት፡፡)

የዩናይትድ ስቴትስን ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ጥቅሞች እስካከበሩ እና ዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪነት ላይ የከፈተችውን ጦርነት እስካልተቃወሙ ድረስ የአፍሪካ ወሮበላ አምባገነኖች በአፍሪካ አህጉር ላይ በጠራራ ጸሐይ ኮሮጆ ገልብጠው ምርጫ ሲዘርፉ እና ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ እየተጠቀሙ በአፍሪካውያን/ት ዜጎች ላይ የቁማር ጨዋታ ሲጫወቱ አሜሪካ ጸጥ በማለት በትዕግስት የምትመለከተው ደንታም የማይሰጣት የዕለት ከዕለት ጉዳዩዋ ሆኗል፡፡

የፍራንክሊን ዲ.ሩዝቬልት “በየትኛውም የዓለም ክፍል” እንዲተገበሩ የሚገባቸው አራቱ አስፈላጊ የሰው ልጆች ነጻነቶች በአፍሪካ ላይ ግን ተግባራዊ አይሆኑም፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ጨለማ የተንሰራፋበትን የአምባገነኖች አገዛዝ በማንኮታኮት እራሷን ከጀግና የነጻ የዓለም ህዝቦች ጋር ለማስተሳሰር የሩዝቬልትን ራዕይ አትከተልም፡፡ “አራት አስፈላጊ የሆኑ የሰው ልጅ ነጻነቶች የሚገለጹባት ዓለምን ዕውን ሆና ማየት እንፈልጋለን፡፡” በማለት ሩዝቬልት የተናገሩትን ወደ ተግባር ለአፍሪቃ አያስፈለግም፡፡የመጀመሪያው የመናገር እና ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት – (ከአፍሪካ አህጉር በስተቀር በዓለም ላይ ሁሉ)፡፡ ሁለተኛው ማንም ሰው በራሱ መንገድ አምላኩን የማምለክ እና የፈለገውን እምነት በመያዝ የእራሱን እምነት የማራመድ መብት – (ከአፍሪካ አህጉር በስተቀር)፡፡ ሶስተኛው የፍላጎት ነጻነት መብት – ከዓለም አቀፍ ሁኔታ አንጻር ሲተረጎም ይህ ማለት የእያንዳንዱን አገር ጤናማ የሰላም ጊዜ የማስፈን እና የእያንዳንዱን ዜጋ ፍላጎት – በየትኛውም የዓለም ክፍል ማሟላት (ከአፍሪካ በስተቀር)፡፡ አራተኛው ከፍርሀት ነጻ የመሆን መብት… ከዚህ አንጻር ማንም ጠብ አጫሪ አገር ተነስቶ በጎረቤቱ ላይ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ጥቃት አይፈጽምም፡፡ እንደዚሁም በዓለም ላይ ጥቃት ለመፈጸም አይቻለውም (ከአፍሪካ በስተቀር)፡፡ የሩዝቬልት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ድንጋጌ እና ሌሎችም በድንጋጌው እየተፈተሉ የሚገኙት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች በየትኛውም የዓለም ክፍል ላይ ተግባራዊ ይደረጋሉ (ከአፍሪካ በስተቀር)፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ ትክክለኛ እና “በተግባር ተኮር ፖለቲካ” ፖሊሲ ላይ እራሱን ብቁ ያደረገ በሚከተሉት የዩናይትድ ስቴትስ ፖሊሲ የሰብአዊ መብት ፖሊሲ ግድፈቶችን ግልጽ በሆነ መልኩ ያካትታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና የሰብአዊ መብት ደፍጣጮች በአፍሪካ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ ስላሏት እሴቶች፣ መርሆዎች እና ፖሊሲዎች ግልጽ የሆነ ግንዛቤ ይኖራቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪካ ላይ ስላሏት ዝንባሌዎች እና ዓላማዎች እንዲሁም አለመግባባቶች እና ግንዛቤ ያለመኖር ችግሮች አይኖሩም፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዩናይትድ ስቴትስ ስለሚኖራት የሰብአዊ መብት ስህተቶች የሚናገሩት በጣም ጥቂት ነገር ብቻ ይሆናል፡፡ ከንፈሮቻቸውን ይነክሳሉ፡፡ አብዛኞቹ የአፍሪካ አምባገነኖች ለሰሩት ታማኘነት ላለው እና መልካም ስራ ትክክለኛ ምስጋና ያገኛሉ፡፡ ዩናይትድ ሰቴትስ ወዲያውኑ እነዚህን አምባገነኖች እንዳላየች አድርጋ የመሄድ አስመሳይነቷን ታቆማለች፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ግንቦት 12 ቀን 2006 ዓ.ም

Latest from Blog

ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop