Health: መነሻውን ሳላውቀው እጅ እግሬን የሚደነዝዘኝና የሚያቃጥለኝ ምንድነው?

የማክበር ሰላምታዬን እያቀረብኩ ጥያቄዬን አስከትላለሁ፡፡ ከቅርብ ወራት ወዲህ ሁለቱም እጆቼንና ሁለቱንም እግሮቼን እንደመደንዘዝ ያደርገኛል፣ ያቃጥለኛል፣ ይለበልበኛል፣ ልክ በመርፌ እንደሚወጋ ነገር ጠቅ- ጠቅ ያደርገኛል፣ አንዳንዴም ውስጥ ውስጡን የሆነ ነፍሳት የሚሄድብኝ/የሚርመሰመስብኝ ይመስለኛል፡፡ ሲነሳብኝ ማስታገሻ ወስጄበትም አይተወኝም፡፡ ዕድሜዬ በአርባዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኝና የልጆች አባት ነኝ፡፡ ከዚህ በፊት በግልፅ የታወቀና በሐኪም የተነገረ በሽታም የለብኝም፡፡ ይሁንና ይህ ችግር በተለይም እየደጋገመ ሲመጣብኝ በጣም አሳስቦኛል፡፡ እባክዎትን እንደተለመደው የህመሜ መንስኤ ምን ሊሆን እንደሚችል ከነመፍትሄው ቢያብራሩልኝ!? በ.ተ

የዶ/ር ዓብይ ምላሽ፦ ምንም እንኳን ከሰጡን መረጃ በመነሳት የጠያቂያችን የጤና እክል ይህ ነው ብሎ እቅጩን ማወቅና መናገር ባይቻልም ባለው መረጃ ላይ ተመስርተን በቀዳሚነት ሊሆን ይችላል በምንለው የጤና ችግር ላይ እንደተለመደው ጠቅለል ያለ ማብራሪያ ለመስጠት እንሞክራለን፡፡ ከሁኔታው እንደተረዳነው ችግሩ በእንግሊዝኛው አጠራር ‹‹Peripheral Neuropathy›› በመባል የሚታወቀው በሽታ ነው፡፡ ይህም ማለት በተለያዩ የጤና እክሎች እጆቻችንና እግሮቻችን ላይ የሚገኙት ነርቮች ሲጎዱ የሚከሰት በሽታ ነው፡፡ የጠያቂያችን እጅ እግሮች ላይ የተከሰቱት የህመም ስሜቶችም ከዚሁ በሽታ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ መገለጫ ምልክቶቹ ናቸው፡፡ በተለይም እጅ እግር ላይ ከሚሰሙ ስሜቶች ያለመሰማት፣ በተቃራኒው ተጋኖ ወይም ተዛብቶ መሰማት ጋር ተያይዞ የሚከሰተው ‹‹Sensory Neuropathy›› የተሰኘው የዚሁ በሽታ አንዱ አይነት የሆነው ችግር እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ስለሆነም ስለ ‹‹Peripheral Neuropathy›› ምንነት፣ መንስኤዎች፣ ዋነኛ መገለጫ ምልክቶቹ፣ ምርመራዎቹ እና ህክምናዎቹን በተመለከተ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡ በቅድሚያ ስለ ችግሩ ምንነት በማብራራት እንጀምር፡፡
ውጫዊው የነርቭ ስርዓት Peripheral Neuropathy ማለት ለእጅ እግር ከሚያገለግሉ የነርቭ አይነቶች አንዱ ወይም ከዚያ በላይ በአንዳችን የጤና እክል አማካይነት ሲጎዳ የሚያስከትላቸው የህመም ስሜቶችን ይወክላል፡፡ የህመም ስሜቶቹ መገለጫዎች እንደየነርቭ አይነቶቹ እና ተግባራቸው ይለያያል፡፡

ሴንሰሪይ ኒውሮፓዚይ (Sensory Neuropathy)፡- ይሄኛው አይነት የነርቭ ችግር ዋነኛ መገለጫዎቹ በተለምዶ መሰማት የሚገባቸው ስሜቶች ሳይሰሙን ሲቀሩ አልያም ስሜቶቹ ከተለመደው የተለየ ወይም የተጋነኑ ስሜቶች ሲሆኑና ይህም ያለመመቸትና የህመም ስሜቶችን ሲያስከትሉብን ነው፡፡ ማለትም ሙቀት ቅዝቃዜንና ሌሎች የህመም ስሜቶችን… የመሳሰሉትን መለየት አለመቻል ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም እነዚህ ስሜቶች ተዛብተውና ተጋነው ሲሰሙን ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ የመደንዘዝ፣ የማቃጠል፣ የመጠዝጠዝ፣ የመለብለብና የመሳሰሉት ስሜቶች ሊሰሙን ይችላሉ፡፡ አንዳንዴም ልክ እንደ መርፌ ጠቅ-ጠቅ የማድረግ ስሜት ሊሰማን፣ አሊያም ልክ ነፍሳት ከቆዳ ስር የሚሄዱ የሚመስል አይነት ስሜት የሚያጋጥማቸው ታማሚዎችም አሉ፡፡ የጠያቂያችንም አብዛኞቹ ምልክቶች ከእነዚህ ጋር ስለሚመሳሰሉ ችግራቸው ይሄኛው አይነት የነርቭ ችግር ሊሆንም ይችላል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፕላሴቦ

– ሞተር ኒውሮፓዚ (Motor Neuropathy)፡- ይኼኛ የነርቭ ችግር ደግሞ የሚያጠቃው ለእንቅስቃሴ የሚረዱ በተለይም የእጅና የእግር ጡንቻዎችን በመሆኑ እነርሱን ማንቀሳቀስ አለመቻል ዋነኛ መገለጫው ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ችግር ያለባቸው ሰዎች እንደፈለጉ መንቀሳቀስ አለመቻል፣ በእጅ ጣቶች የሚከወኑ ተግባራትን (ለምሳሌ መጨበጥ፣ ዕቃ ማንሳት፣ መዳፍ… የመሳሰሉትን) መከወን አለመቻል እና የመሳሰሉትን ከእንቅስቃሴ ጋር የተገናኙ ተግባራትን ማከናወን አለመቻልና የእጅ እግር መዛል ዋነኛ ምልክቶቹ ናቸው፡፡

እነዚህ እንግዲህ የ ‹Peripheral Neuropathy› ዋነኛዎቹ አይነቶችና መገለጫዎቻቸው ሲሆኑ በተናጠል ወይም በጋራ ምናልባትም ከሌሎች ማለትም ከማዕከላዊ የነርቭ ስርዓት ችግሮች ጋር አብረው ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ የሚከሰቱበት ሁኔታም ከአጣዳፊ የጤና ችግር ጋር በተያያዘ በአጣዳፊነት (Acute) ወይም ስር ከሰደዱ የጤና እክሎች ጋር በተያያዘ በዘላቂነት (Chronic) ሊሆን ይችላል፡፡ በተመሳሳይም አንድ ነርቭ ብቻ የተጎዳ ከሆነ ሞኖኒውሮፓዚይ (Mononeuropathy) ሲባል ከአንድ በላይ ወይም ብዙ ነርቮች በአንድ ጊዜ የተጎዱ ከሆነ ደግሞ ፖሊኒውሮፓዚ (Polyneuropathy) በመባል ይታወቃሉ፡፡

የውጫዊው የነርቭ ስርዓት መጎዳት (Peripheral Neuropathy) መንስኤዎች ምን ምንድናቸው?

የተለያዩ ነርቮችን በማጥቃት ለተለያዩ የነርቭ ችግሮች የሚዳረጉ በርከታ የጤና እክሎች አሉ፡፡ በጥቅሉ ከዕጢ ጋር፣ ከልዩ ልዩ ኢንፌክሽኖች ጋር፣ ከመርዛማ ነገሮች ጋር፣ ከመድሃኒቶች ጋር እና ከሌሎችም ስር ሰዳጅ በሽታዎች ጋር የተያያዙ መንስኤዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ዋነኞቹ መንስኤዎችም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

– የስኳር በሽታ፡- መንስኤ ከሆኑት ስር ሰዳጅ በሽታዎች ቀዳሚው ነው፡፡ በተለይም ሁለተኛው አይነት የስኳር በሽታ የተለያዩ የነርቭ ችግሮችን የሚያስከትል ሲሆን በዋነኝነት ሴንሰሪ ኒውሮፓዚ (Sensory Neuropathy) የተሰኘውን አይነት በተለይም በእጅና በእግር ላይ በማስከተል ከላይ በተጠቀሱት ምልክቶች ይገለጣል፡፡

– አልማዝ ባለጭራ፡- በተለምዶ አልማዝ ባለጭራ እያልን በተለምዶ የምንጠራውና በህክምናው እርፐስ ዞስተር የምንለው ህመም ይህ ሌላው የተለመደ የችግሩ መንስኤ ሲሆን በመጀመሪያ የሚያወጣው ቁስለት ከዳነ በኋላ የሚከሰተው የነርቭ ህመም (post herpetic neuralgia/shingles) በመባል ይታወቃል፡፡ ህመሙ ሁሌም የአልማዝ ባለጭራን ተከትሎ የሚከሰት ባይሆንም ከተከሰተ ግን ከፍተኛ ስለሆነ ማስታገሻ ያስፈልገዋል፡፡
– የአልኮል መጠጥ፡- በአልኮል መጠጥ ውስጥ የሚገኘው ኬሚካል ከነርቮች ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር የተጠቀሰውን ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ብዙ አልኮል ለብዙ ጊዜ በጠጡ ሰዎች ላይ ነው፡፡
– የቫይታሚን እጥረት፡- ከተለያዩ ምግቦች የሚገኙ ቫይታሚኖች በተለይም ቫይታሚን ቢ12 የተሰኘውና ፎሌት የተሰኘው በሚያስፈልጉን መጠን ካልተወሰዱ የተጠቀሰውን የነርቭ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡
– ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ፡- በሽታው የተባለውን የነርቭ ችግርና ሌሎችንም የነርቭ ችገሮች ከሚያስከትሉ የተለመዱ መንስኤዎች አንዱ ነው፡፡ በራሱ በበሽታው ሂደት ብቻም ሳይሆን በሚያስከትላቸው ሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች፣ ለህመሙ በሚወሰዱት መድሃኒቶች ሳቢያ እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ሊሆን ይችላል፡፡
– ሌሎች ኢንፌክሽኖች፡- ከኤች.አይ.ቪ ኤድስ ባለፈም ሌሎች ልዩ ልዩ ኢንፌክሽኖች የተባለውን ችግር በማስከተል ይታወቃሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ቂጥኝ፣ የስጋ ደዌ በሽታ፣ የተለያዩ ቫይረሶች እና ሌሎች ባክቴሪያዎች ይጠቀሳሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የደ/ሰ/መ/ቤ/ክ ፓሪሽ ፕሮግራም አመታዊ ሄልዝፌር (በሚኒሶታ ለምትኖሩ ወገኖቻችን ነፃ የህክምና ምርመራና ትምህርት ቀን)

– ካንሰርና ህክምናው፡- ከዕጢዎችና ካንሰር መገለጫዎች አንዱ ይኸው የነርቭ ችግር ነው፡፡ ከበሽታውም ባለፈ ለፈውስ ተብለው የሚሰጡ መድሃኒቶቹም ችግሩን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡

– ሌሎች ስር የሰደዱ በሽታዎች፡- እነዚህም የነርቭ ችግር በማስከተል ከሚታወቁት መንስኤዎች ይመደባሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የኩላሊትና የጉበት ድክመት፣ ከሆርሞኖች ጋር የተያያዙ በሽታዎች (ለምሳሌ ሃይፓታይሮዲዝም የተሰኘው በእንቅርት ሆርሞን ማነስ ምክንያት የሚከሰተው በሽታ) እና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

– መድሃኒቶችና መርዛማ ንጥረ ነገሮችን፡- እንደ የተባይ ማጥፊያ፣ (ለምሳሌ ዲዲቲ) ሜርኩሪ፣ እና የመሳሰሉት ማዕድናትና መርዛማነት ያላቸው የፋብሪካ ውጤቶች ወደ ተረፈ ምርቶች፣ እንዲሁም ከላይ የተጠሱትና ሌሎች አንዳንድ መድሃኒቶች የተጠቀሰውን የቫይታሚን እጥረት በማስከተል ለነርቭ ችግር ይዳርጋል፡፡ ይህም ከመድሃኒቶች የበዛ የጎንዮሽ ጉዳት የተነሳ የሚመጣ ነው፡፡

– አካላዊ አደጋ (Physical trauma)፡- ይህም በነርቮች ላይ ወይም በደም አቅርቦታቸው ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ለተባለው ህመም ሊዳርጉ ከሚችሉት መንስኤዎች አንዱ ነው፡፡ በተመሳሳይም ነርቮቹ በሚያልፉባቸው የእጅና የእግር አጥንት ቀዳዳዎችና ክፍልፋይ መሿለኪያዎች በአደጋ ወይም በበሽታ አብጠው ወይም ጠበው ነርቩን የሚጫኑበት ሁኔታ ከተፈጠረ የተባለውን ተመሳሳይ የነርቭ ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡
– ሌሎችም ብዙም ያልተለመዱ ልዩ ልዩ በሽታዎች ችግሩን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡- ይሁንና አንዳንዴ በተለያዩ ምርመራዎች እነዚህም ሆኑ ሌሎች መንስኤዎች ስለመኖራቸው ላይረጋገጥና ትክክለኛው መንስኤ ላይደርስበት ይችላል፡፡ እንዲህ አይነቱ መንስኤ በህክምናው አጠራር ኢዲዮፓቲክ ተብሎ ይታወቃል፡፡ መንስኤው ያልታወቀ እንደማለት ነው፡፡

ምርመራዎቹስ ምን ምን ናቸው?

ምርመራዎቹ እንደየመንስኤው ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ይሁንና በሽታው ከተከሰተ ‹‹Peripheral Neuropathy›› መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚረዱ ምርመራዎች አሉ፡፡ እነርሱም፡-
ኤሌክትሮማዮግራም፡- የጡንቻዎቻችን የመኮማተርና የእንቅስቃሴ ፍጥነትና ምጣኔን የሚያሳይ ምርመራ እና የሚሰሩ ነርቮችን መለየት፡- እነዚህን ጡንቻዎች ለማንቀሳቀስ የሚረዱት ነርቮች በትክክል መስራት አለመስራታቸውን ለማወቅ የሚያስችል ምርመራ ናቸው፡፡
ህክምናውስ ምንድነው?

ተጨማሪ ያንብቡ:  Health: የባህል መድሃኒት (ዶ/ር ቁምላቸው አባተ)

ፐሪፐራል ኒውሮፓዚ (Pheripheral Neuropathy) ሙሉ ለሙሉ ለመፈወስ አደጋች ከሆኑ የጤና ችገሮች አንዱ ነው፡፡ ይሁንና ምንም አይነት መፍት ወይም ህክምና የለውም ማለት አይደለም፡፡ ህክምናውም ሆነ የህክምናው ውጤት በዋነኝነት በመንስኤው ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ዋና ዋናዎቹ መፍትሄዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ – አስቀድሞ መከላከል፡- የመጀመሪያውና አዋጪው መፍትሄ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት አጋላጭ ሁኔታዎችን ለይቶ በማወቅ መከላከል ነው፡፡ ለምሳሌ አልኮልን፣ የምግብ እጥረትን፣ አንዳንድ ከላይ የተጠቀሱት ኢንፌክሽኖችን፣ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን የመሳሰሉትን ቀድሞ ማስወገድና መከላከል ይቻላል፡፡ የስኳር በሽታንም ቢሆን ተገቢውን ህክምናና ክትትል በማድረግ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ቢያንስ ማዘግየት ይቻላል፡፡
– መንስኤውን ማከም፡- መከላከሉ ካልተቻለና መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ በሽታዎች ከተከሰቱና ችግሩን ካስከተሉ ደግሞ መሰረታዊውን መንስኤ ማከም እጅግ ጠቃሚ ህክምና ነው፡፡
– የህመም ማስታገሻዎችን መውሰድ፡- ህመሙን ለማስታገስ የተለያዩ ማስታገሻ መድሃኒቶች ይሰጣሉ፡፡ የማስታገስ ኃይላቸውም እደየመድሃኒቶቹና በሽታው ይለያያል፡፡ በተለምዶ ለማንኛውም ቀለል ያለ ህመም ከሚሰጡት ማስታገሻ መድሃኒቶች ጀምሮ ጠንከር እስካሉ የነርቭ መድሃኒቶች ድረስ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ በተለይም ልክ ስኳርን ተከትሎ እንደሚከሰተው አይነት የነርቭ ህመም ጠንከር ያለ ከሆነ ትራይሳይክሊክ አንቲዲፕረሳንትስ የተባሉ መድሃኒቶችን ለሚጥል በሽታ የሚሰጡት መድሃኒቶች ሊወሰዱ ይገባል፡፡ – ‹‹ፊዚዮቴራፒ›› እና ቀዶ ህክምና፡- ከዚህ ባለፈም ነርቩን ተጭኖ ከላይ የተጠቀሰውን አይነት ችግር ከተከሰተ በቀላል ቀዶ ህክምና ሊድን ይችላል፡፡ አንዳንዴ በመርፌ በሚሰጡ መድሃኒቶች ማከምም ይቻላል፡፡ ከነርቩ መጎዳት ጋር በተያያዘ የእጅግ እግር መዛል ከተከሰተም በማሸት የማቃቃት ‹‹ፊዚዮቴራፒ›› መስጠትም አንዱ የህክምና ዘዴ ነው፡፡
እንግዲህ ውድ ጠያቂያችን እርስዎም ይህንን ካነበቡ በኋላ የችግርዎን መሰረታዊ መንስኤና መፍትሄውን ለማወቅ ወደ ተገቢው ባለሙያ በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራራ ክትትልና ህክምና እንደሚያደርጉ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በተለይም የስኳር በሽታ እንዲህ አይነቱን ችግር በማስከተል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛልና ተመርምሮ ራስን ማወቁ አይከፋም!

1 Comment

  1. Beshitawun bizu sew indeh yisemanyal silu esemalehu.enem koyyet biloal injii amonyi berase yebahel medihanit teftolinyal. Lerejim gize ke sex mekoteb jemro yeteleyaye yebahil medanitochin tetekime titonyal. Yemakatel simetu wusti egre inna medaf wusti new .yene labetem nebreW. Minalbat Hiv yihonal biye bimeremer Negative ne aluny. Merfem altekemenyim gin yebahelu betam redanyi,wageb yemiyamenyem teshaleny. Be shitaw ye Hiv jimaro kistet sayhoon aykerm biyye hemichalehu.

Comments are closed.

Share