አምቦ
በደምሽ የተገነባ
በሕልምሽ ላይ የታለመ
ከቅባት ከ ማር ከቡናሽ
ያተርፍሽው ይሄን ሆነ ።
ምነው አምቦ የላቀች የገብረ ምድህን ሀገር
ምነው አንቺ የጸጋዬ የአዴ አርገጡ ሰፈር
አምቦ የቀዊሳ አድባር
አንቺ የ ቦራ ጨፌ
ምነው ምድርሽ በደም እና በንባ ጎርፍ ረጠበ
ምነው የልጆችሽ ደም የሰሜን እግር አጠበ።
አንቦ አንቺም አልፎልሽ ብሎልሽ ደምሽ ፈሰሰ
ይሄው ደስ ይበልሽ ዛሬ የተመኘሽው ደረሰ።
ህጣናቶችሽ ተደፍተው
እናት አንጀቱዋን አስራ
ዋይታ እንደ እልልታ ባገሩ ፣ በየመንደሩ ተጠራ
ጩኸት ፈለገሽ ሆነ ፣ አንድ መሆን ይኸው ተፈራ።
የሃዘን ድንኩዋን እንደ ንግሥ ቤቀየሽ ላይ ተሰየመ
ወጣትነትሽ አረጀ፣ ክብርሽ ተገሶ ፈረሽ
ሳምራዊነትሽ ቀለመ።
አምቦ የእትብቴ አፈር
ወተቱን ከቦራዬ ግት
ማር አልያም ደሞ አጉዋት
ግትሽን ግቼ እንደ ጊደር
ከሳር ፣ ካዛባ ፣ ከፍጉ
ከከብቶች ትንፋሽ ጋ ሳድር
በህጻን ከንፈሬ አቅፌ
በህጻን ልቤ አፍቅሬሽ
በህጻን ልቤ ኑሬሽ
ጉልበቴን ያጠነከርሽው
ዛሬ
በደም ሆነ እናትነትሽ
ያን ደግነት ረሳሽው።
አምቦ ወና አትሁኝ ቀና በይ
ጉልበትሽን አሳያቸው
ዛሬም አርበኞች በምድርሽ
ላንድነት ይሰየሙልሽ
ዛሬም ጸጋዬን ውለጂ ፣ አንድነት ጉልበት ይሁንሽ።
አምቦ ተነሽ አትነሺ
ድሮም ትልቅነት እንጂ ማነስ አያምርብሽም
አምቦ ለቅሶዬን አድምጭ
አምቦ እጅሽን ለባንዳ ለሰሜን ተኩላ አትስጪ።
አምቦ የጎጃም በሩዋ
አምቦ የኩሽ ምድሩዋ
አንቦ የቀዊሳ ሀገር
አንቦ የሃብተግዮርጊስ የድናግዴ ምድረ ምውጫ
አምቦ እሉ አባ ቦራ የነ ዋቆ ፈረስ መጠጫ
የኔ አያና ጦር ሰፈር
አምቦ ምድረ ኢትዮጵያ
ይብቃሽ ብቻሽን ማልቀሱ
ይብቃሽ ብቻሽን ደም መርጨት ፣ ይብቃሽ ጥቁር ደም ማፍሰሱ።
አምቦ ልጆችሽን ጥሪ
አምቦ አንድ ላይ ጩሂ
አምቦ ደምሽ ይመልስ
አምቦ የዋቃ ዝናር የጠፋው ክብሩ ይመለስ
ባክሽ ተባብረሽ ጩሂ።
ሄኖክ የሺጥላ