በ ጋዜጣው ሪፖርተር
ሰንደቅ
ሰሞኑን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ከመረጃ እጥረት ጋር ተያይዞ ተከስቶ የነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የተረጋጋ ሁኔታ ይታይበታል። ሆኖም ግን በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከተሞች ውስጥ ብልጭ ድርግም የሚሉ ተያያዥ ተቃውሞዎቹ መቀጠላቸው እየተሰማ ነው። በርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ተቃውሞ ተደርጎባቸዋል በተባሉ የክልሉ ከተሞች ውስጥ የተለያዩ ምንጮች የሰው ህይወት መጥፋቱም ዘግበዋል።
በማንኛውም መመዘኛ ቢወሰድ የሰው ህይወት የሚቀጥፍ የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴ የፖለቲካ ዋጋው ከፍተኛ ነው። በዚህ የተቃውሞ ሂደት ውስጥ ለጠፋው የሰዎች ህይወት በአንድም በሌላ መልኩ ባለቤት ሊበጅለት እና ተጠያቂ ወገኖችን ለፍርድ ማቅረብ የግድ ይላል። ከሕዝብ ጋር በውይይት በሚደረግ የጋራ መግባባት ብቻ ሊታለፍ የሚገባው ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። በተለይ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚደረጉ አብዛኞቹ የተቃውሞ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መነሻቸው “በከሃዲ” ወይም “በተንበርካኪ” የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት የተፈጸመ ስህተት ነው እየተባለ የሚፈረጅበት የፖለቲካ ትግል ስልት ከመሰረቱ መንግሎ ማውጣት ካልተቻለ ወደፊትም የሚያስከፍለው ዋጋ ምትክ አልባ መሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል።
ይህም ሲባል በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ወይም ፊንፊኔ ዙሪያ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ለመዘርጋት የተሄደበትን ሂደት መሰረታዊ ችግር ምድንነው በሚለው ጉዳይ ላይ ሁለት የተለያዩ አተያየቶች ተቀንቅነዋል። በአንድ በኩል ያለውና ወደ ተቃውሞ አደባባይ የወጣውን ኃይል ያደረጁ ወገኖች እንደሚሉት፣ የተቀናጀውን ማስተር ፕላን ለመዘርጋት በተሄደበትን ሂደት ውስጥ በመሰረታዊ ችግርነት የሚያነሱት ተንበርካኪ የኦህዴድ አመራሮች የኦሮሚያን ክልላዊ መንግስት ግዛት ለአዲስ አበባ አስተዳደር አሳልፈው ለመስጠት መወሰናቸው ነው። ይህም በመሆኑ ለሰዎች ህይወት መጥፋት ተንበርካኪ የኦህዴድ አመራር ምክንያት ሆኗል ሲሉ ይከሳሉ።
በሌላ መልኩ ደግሞ የፖለቲካ አመራሩ የሚያነሳው መሰረታዊ ችግር በተለየ መልኩ ነው። የተዘጋጀው ማስተር ፕላን ተመጋጋቢ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ በኦሮሚያ ልዩ ዞኖች እና በአዲስ አበባ አስተዳደር መካከል የሚፈጥር መሆኑ ያስታውሳል። ይህም ሆኖ ረቂቅ ማስተር ፕላኑ በሁለቱ አስተዳደሮች ገና ውይይት የሚደረግበት በመሆኑ ሰነዱ ሲዘጋጅ ችግሮች ተፈጥረው ቢሆን እንኳን ለማረም የሚያስችሉ ብዙ እድሎች አሉ። ችግሮችን ለማረም የተዘጋ የውይይት መድረክ የለም። ስለዚህም የሂደቱ መሰረታዊ ችግር፣ በኦህዴድ ድርጅታዊ መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ እና በሌላ የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ ውስጥ የሚገኙ ጠባብ ብሔርተኞችና ኪራይ ሰብሳቢዎች በድርጅቱ ውስጥ የትምክትና የጥገኝነት ዝቅጠት በመፍጠራቸው እንዲሁም በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ በመዘፈቃቸው ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆነዋል ሲሉ ይከሳሉ።
በተፈጠረው ችግር ዙሪያ የሚንፀባረቁት እነዚህ ሁለት የተለያዩ አተያየቶች፣ አንዱ ሌላውን አሸንፎ መውጣት እስካልቻሉ ድረስ የሚከፈለው ፖለቲካዊ ዋጋ እዚህ ላይ ያበቃል ብሎ መደምደም የዋህነት ነው። ምንአልባትም የተራዘመ ትግል ይጠይቅ ይሆናል። እነዚህ ሁለት አተያየቶች በተቀናጀው ማስተር ፕላን ጥያቄ ላይ ብቻ የተንፀባረቁ ሳይሆን፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተደረጉ የተለያየ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በስፋት የሚቀርቡ “የታማኝ” እና “የካሃዲ” ወይም የአፈንጋጭ ፖለቲከኞች የፖለቲካ መታገያ ስልቶች ናቸው።
በተለይ ለፌዴራል መንግስቱ “ተንበርካኪ የኦህዴድ አመራሮች” ተብሎ ያልተከሰሰ ከፍተኛ የኦህዴድ አመራር የለም። አመራሮቹ በምን መመዘኛ እና አመለካከት የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም ለሌሎች አሳልፈው እንደሚሰጡ የቀረቡ የተለያዩ የአመክኒዮ መከራከሪያዎች ውሃ የሚያነሱ አይደሉም። እነዚህን አመራሮች ከሚከሱት መካከል በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከኦህዴድ የፖለቲካ ሜዳ የተገለሉ የቀድሞ ጓዶቻቸው ይበዛሉ። ትችት የሚሰነዝሩት የቀድሞ የኦህዴድ ካድሬዎችም ቢሆኑ በተመሳሳይ ሁኔታ ስልጣን ላይ በነበሩ ወቅት ተመሳሳይ የፖለቲካ ትችት ይቀርብባቸው ነበር። ዛሬ ላይ እንዴት የተለየ የኦሮሞ ሕዝብ የመብት ታጋይ ሆነው መቅረባቸው ግን እንቆቅልሽ ነው።
ሌላው አስፈሪው አስተሳሰብ ለ“ሌሎች” ወገኖች የሚለው ቅጽል መነሻው “ተንበርካኪ የኦህዴድ አመራሮች” የሚለውን ለመሰየም ወይም ለመፈብረክ ስለተፈለገ የሚመስል ነው። እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ቁምነገር፤ ማነው የኦሮሚያን ሕዝብ ለማንበርከክ የሚሰራው? የኦሮሚያን ሕዝብ ጥቅም ተንበርክኮ የሚሰጠው ማነው? የኦሮሚያን ሕዝብ ጥቅም ለመውሰድ ሌት ተቀን የሚተጋው ማነው? የኦሮሚያን ሕዝብ ከሌሎች ክልሎች የእኩል ተጠቃሚነትን መብትን ለመግፈፍ የሚሰራው ማነው? የኦሮሚያን ሕዝብ መብት ወስዶ በዚህች ሀገር ውስጥ ሰላም ዴሞክራሲ ልማት ማረጋገጥ የሚችለውስ ማነው? የኦሮሚያን ክልላዊ መንግስት ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት የሚሰራ የሚሻ የኦሮሞ ተወላጅ፤ የየትኛው ብሔር ተወላጅስ ነው? የኦሮሚያን መብቶች ለመቀራመት መሰረታዊ አስተሳሰብ አድርጎ የሚሰራው ማንስ ነው? በኢትዮጵያ ውስጥስ “ሌሎች ወገኖች” ተብለው የሚጠሩትስ እነማን ናቸው?
ከላይ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች እንደአንድ ተራ ዜጋ ምላሽ ለመስጠት ከባድ ነው።ምላሽ ለመስጠት ቢፈለገም ብዙ ርቀት መሄድ ያስፈልጋል። ለተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች ግን በጣም ቀላልና ፈጣን መልስ ለመስጠት ብዙም አይከብዳቸውም። ምክንያቱም የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማንኛውም ዋጋ የመንግስት ስልጣን ለመቆናጠጥ የሚፈልጉ ሃይሎች በመሆናቸው ስልጣን የጨበጠን ማንኛውንም አካልን በእነዚህ ጉዳዮች ተጠያቂ ያደርጋሉ። ሌላው፣ የፖለቲካ ስልጣን በያዘ አካል እና የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ በሚፈልግ የፖለቲካ ኃይል መካከል ሊኖር የሚችል ተፈጥሮያዊ መነሻ ነው ብሎም አቅልሎ እነዚህን መሰል አተያየቶች መረዳት እጅግ ወደ ተሳሳተ መደምደሚያ ሊያደርስ ይችላል። ስለዚህም በደንብ መፈተሽ ያለበት አቅጣጫ ነው። ይህን መሰል “የከሃዲ” እና “ተንበርካኪ” የፖለቲካ አተያየት ነፋስ ወዴት ሊያደርሰን እንደሚችል መገመት ከባድ ነው።
በአንድ ወቅት ኤድዋርድ ሎሬንዞ የተባለ የሒሳብና የሜትሮሎጂ ልሂቅ አንድ ጥናት ለዓለም አበርክቶ ነበር። ጥናቱ “butterfly effect” ተብሎ የሚጠራ ነው። ይህ ሰው ቢራቢሮ በአየር እየተንሳፈፈች የምትቀዝፈው አየር ምን ዓይነት ለውጥ በዩኒቨርስ ላይ ሊኖራት ይችላል ሲል ያስባል። ቢራቢሮ በዩንቨርስ ውስጥ ያለውን አየር እየቀዘፈች በመሄዷ ምን ሊፈጠር ይችል ይሆን ብሎ ያልታደለ ሰው፣ እንዴት ሊያስብ ይችላል። በጣም ትንሽ እንቅስቃሴ ዓለምን ሊያውክ ይችላል ተብሎ ማሰብ ከባድ ነው። የጂኦግራፊ ልሂቃንን ትንተና ብንመለከተው በአንዱ የምድር አቅጣጫ ቢራቢሮ በክንፎቿ አየሩን ብትዘፍቀው በሌላ የምድር አቅጣጫ ሃሪኬን ሊፈጠር ይችላል። (In Geography, it is belief that a butterfly flaps its wings in one end of the world; it can cause a hurricane in another.)
እ.ኤ.አ. 1963 ኤድዋርድ ሎሬንዞ ለንድፈ ሃሳብ ምርምሩ ይህን ሲል ጠይቆ ነበር፤ “The stoke of a butterfly- wing in the forest of Amazonas could affect an orcan in Europe” (cpr. www.chaostheorie.de). ከዚህም መነሻ ትንሽ እንቅስቃሴም ብትሆነ ትልቅ ያልተጠበቀ ነገር ሊያስከትል እንደሚችል አመላካች ነው። ፖለቲከኞችም በፖለቲካ ሂደት ውስጥ ወደፊት ሊፈጠር የሚችለውን ሁኔታ ማወቅ ስለማይቻላቸው የተለየ ነገር ለመፈጸም ቃል መግባት አይጠበቅባቸውም።
ሌላው ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚነሳው በሕብረተሰብ ውስጥ ያለውን የተወሳሰበ እድገትን መሰረት ያደረገው ከፖለቲካ ተግባሮች ጋር በተሳሰረ መልኩ የሚተነትነው “Murphy’s Law” ተብሎ የሚጠራው ነው። መርፊ የአሜሪካ አየር ሃይል ባልደረባ የነበረ ሰው ነው። በጣም የሚታወቅበት ““If there is more than one outcome of a job or task, and one of this outcomes will result in disaster or an undesirable consequence, then somebody will do it that way” (www.wikipedia.org).” መርፊ እንደሚለው ማንኛውም የፖለቲካ ተግባር ከአንድ በላይ ውጤት አለው። የሚኖረው ውጤትም ምንአልባትም ያልተፈለገው ሊሆን ይችላል። ይህ ሲሆን ቢዚያው መልኩ ነው ሊሰራው የሚገባው። ይህም ሲባል ሕብረተሰብ የተወሳሰበ በመሆኑ ብዙውን ግዜ የተጠበቀው ሳይሆን ያልተጠበቀው ውጤት ሲከሰት ይታያል። ፖለቲከኞችም በፖለቲካ ሂደት ውስጥ የሚከሰቱ ብዙ ነገሮች ከመኖራቸው አንፃር የተለየ ነገር ሊያመጡ እንደሚችሉ ቃል መግባት የለባቸውም። ተጨባጭ እውነታው በራሱ የሚሰጠው መልስ መኖሩን ሊዘነጉትም አይገባም።
በመጨረሻም ከሰሞኑ ብጥብጥ ጋር መነሳት ያለበት የካዖስ ቲየሪ ነው:: ይሄውም የካዖስ ቲየሪ እንደሚለው፣ ማንኛውም ዳታ በግብታዊነት የተዳረጀም ቢሆን ወሰን አልባ የሆነ ተዛምዶ አለው። አንድነገር እዚህም እዚያም ተበታትኖ ሊከሰት ቢችልም ተዛምዶና ትስስሮች እንዳለው ግንዛቤ መውሰድን ይጠቁማል። (“Chaos theory is a rule involving anything in nature. In essence, it considers all data to be infinite correlation, no matter how random the data may seem.”)
ከላይ ከተቀመጡት “butterfly effect”፣ “Murphy’s Law”፣ “Chaos theory”፣ አንፃር የሰሞኑን በመረጃ ክፍተት የተነሳው የፖለቲካ ተቃውሞ መፈተሽ አለበት። የዚህ የፖለቲካ ቀውስ አዲስ በተዘጋጀው የተቀናጀ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ እድገት ማስተር ፕላን ብቻ የተከሰተ ተደርጎ መውሰድ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ያደርሳል። ክስተቱም ትንሽ ነው ብሎ መቀበልም፣ በጣም ከባድ ነው። የክስተቶቹ በተለያየ ቦታዎች መከሰታቸው ብቻ ሳይሆን መናበባቸው ግብታዊ እንቅስቃሴ አለመሆኑንም መረዳት፣ ተገቢ ነው የሚሆነው።