ወደ ህሊናችን እንመለስ (አንተነህ መርዕድ)

 

የመሬት ጥያቄ ብዙ መስዋዕት የተከፈለበት ቢሆንም አሁን በባሰ ሁኔታ ወያኔ ከሁሉም ዜጋ ነጥቆ በግሉ አድርጎታል። ማንም ኢትዮጵያዊ የሃገሩ፣ የመሬቱ ባለቤት አይደለም። ከዚህ የባሰ ዜጎችን የማዋረድ ተግባር የለም። አባቶቻችን መሬታቸውን ለባዕድ አንሰጥም በማለት ህይወታቸውን ከፍለው አቆይተውናል። ዛሬ እኛ የራሳችን መሬት ባለቤት እንዳንሆን ሁላችንንም መሬት አልባ ያደረገን ስርዓት ዜጎችን አፈናቅሎ ካድሬዎቹን በመሬት ችብቸባ አሰማርቷል። ለባዕዳን ከመሸጥ አልፎ “እኛም የመሬት ባለቤት ልንሆን ይገባናል” ያሉትንና ይህንኑ የዜጎችን ህጋዊ መብት የጠየቁትን ሁሉ በጠራራ ፀሃይ ባደባባይ ይገድላል።

ጋምቤላዎች፣ አፋሮች፣ ሲዳማዎች፣ ጉጂዎች፣ ሶማሌዎች ዛሬ ደግሞ አምቦዎችና ጎንደሮች የተገደሉት መሰረታዊ የሆነውን የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በማንሳታቸው ነው። በየቦታው እያናጠለ ዜጎችን የሚገድለው የወያኔ ስርዓት በቀነበበልን ጠባብ መንደር ተከልለን ጥቃቱ ወደየቤታችን እስኪመጣ የምንጠብቅ ገልቱዎች መሆናችንን ከብዙ የህይወት መስዋዕት በኋላ እንኳ የተማርን አይመስልም። ትናንት አገራዊ አጀንዳ ይዘው የመታገልና መስዋዕት የመክፈል ታሪክ ያላቸውን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች “የትግራይ፣ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የሶማሌ…” እያለ ከፋፍሎ በወንድሞቻቸው ላይ የሚደረገውን ጥቃት በጋራ  እንዳይከላከሉ እስከ ማድረግ ደርሷል። አያቶቻችን ከሰሜን ከደቡብ፣ ከምስራቅ ከምዕራብ ተጠራርተው ጠላታቸውን በመከላከል ተደራርበው የወደቁባት ይህች አገር የማን ናት? ኦጋዴን፣ ኤርትራ፣ መተማ ወዘተ. የወደቁ አባቶቻችንን አጥንት የየትኛ ጎሳ አባል እንደሆኑ መለየት እንችላለን?

ከመቶ ዓመት በፊት ተገደሉ የተባሉ ዜጎቻችንን ካረፉበት መቃብር እየተቆፈረ ለፖለቲካ ፍጆታ፣ ለከፋፋይ ዓላማ የሚያናፍሰው ስርዓት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ዜጎች መሰረታዊ መብታቸውን በሰላማዊ መንግድ ስለገለጹ ብቻ እየገደለ ነው። ሰሞኑን ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንዲሁም የኦሮሞ ፌዴራሊስት አመራር አባላት እንደገለጹት ያለፈ ታሪክ ስህተትን ስንቆፍር አዲስ ኢትዮጵያን በጋራ ለማለም አልቻልንም። ተባብረን አሁን በተከሰተ ችግር ዙርያ እንታገል ሲሉ ያቀረቡት ጥያቄ ተገቢ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለምንገኝበት እጅግ መሪርና አስከፊ እውነታ ተገቢውን ትኩረት እየሰጠን ካልተራመድን ...

ከሁለቱም ወገን ያሉ ጽንፈኞች የሚያካሂዱትን የጥላቻ ዘመቻ ችላ ብለን አሁን ባለ የጋራ ችግር ዙርያ ትግልን በማቀናበር የምንመኛትን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ ለመገንባት መተባበር የወቅቱ አብይ ቁም ነገር ነው።

የሁሉም ኢትዮጵያውያን ህይወት ክቡር ነው። ለንጹህ ዜጎች መሞትና መታሰር ሃላፊ የሆኑትን ሁሉ ኢትዮጵያዊ ሰብአዊ መብት ተቋማት፣አክቲቢስቶች፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች እየመዘገቡ መያዝ ያስፈልጋቸዋል። ሁሉም በሰራው ነገ ተጠያቂ መሆኑ አይቀርምና።

የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ከደርግ አወዳደቅ ለመማር ጊዜው ሩቅ አይደለም። መንግስቱ ኃይለማርያምና ከጥቂት ባልደረቦቹ በቀር አብዛኞቹ ላለፈ ተባባሪነታቸው ዋጋ ከፍለውበታል። ከሁሉም በላይ ግን የህሊና ጠባሳቸው ቀላል አይደለም። አቅፋችሁና ደግፋችሁ የያዛችሁት ስርዓት ተጠቃሚዎችና ወንጀለኞች ጥቂትና በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ለማምለጫቸው ቦታ፣ ለኑሮአቸው ከፍተኛ ንብረት አሽሽተው የመጨረሻውን ቀን እየተጠባበቁ ነው። እነሱ ሲሄዱ በጠራራ ፀሃይ ልጆቻቸው የተገደሉባቸውን፣ መሬታቸውንና ንብረታቸውን ተነጥቀው የተፈናቀሉን፣ በየእስር ቤቱ በግፍ ሲማቅቁ የነበሩትን፣ ባጠቃላዩም ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ግፍ ሲፈጽምባቸው የነበሩ ኢትዮጵያንን ቀና ብላችሁ ማየት የማትችሉበትና ለድርጊታችሁ ተጠያቂ የምትሆኑበት ጊዜ ይመጣል። ወደ ህዝባችሁ መመለስ ካለባችሁ ጊዜው አሁን ነው።

ሁላችንም ወደ ህሊናችን እንመለስ። እየጠፋ ያለው ነገ አገሪቱን የሚረከቡ ወጣቶች ህይወት ነው። በደርግ ወቅት በእርስ በርስ መጨራረስ ከተሞች ወስጥ ያለቀው፣ በኦጋዴን በረሃ፣ በኤርትራና በትግራይ ጋራዎች የረገፉ ወጣቶቻችን፤ ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮ-ኤርትራ ትርጉም አልባ ጦርነት እንዲሁም በየቦታው የተገደሉ ዜጎች ቁጥር የባከነውም ንብረት አገራችንን አሁን ላለችበት የዓለም ጭራነት ዳርጓታል። ከዚህ በኋላ ሌላ ውድ ህይወትና የአገር ሃብት ማጥፋት የማንኛውም ቅን ኢትዮጵያዊ አላማ አይሆንም። ችግራችን የጋራ ነው። አገሪቱም የጋራችን ናት። የገራ የሆነ አገርና ህዝብ ደህንነት የሚጠበቀው በጋራ ተሳትፎ ነው። ድብቅ አጥፊ ዓላማ ካላቸው በቀር ሁላችንም ለጋራ ቤታችንና ህዝባችን ባንድ እንቁም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ስለሥርዓታዊ ለውጥ ዕድሎችና ሁኔታዎች ስናስብ - በተስፋዬ ደምመላሽ

ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርክ

አንተነህ መርዕድ  amerid2000@gmail.com

ሜይ 2014

 

 

 

2 Comments

  1. ውድ አንተነህ መርዕድ!
    እግዚአብሄር ይባርክህ! እግዚአብሄር ያንተን አይነት በኢትዮጵያ ያብዛልን፡፡ አንጀቴን ነው ያራስከው!….አሁን እንግዲህ ግልፁን እንነጋገር፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እኔ ከኦሮሞ ቤተሰብ ነው በአርሲ ውስጥ የተወለድኩት ….ግን አማራን እጠላለሁ ወይ?? ከጠላሁስ መቼ ነው እንዲህ ዓይነት የተዛባ ስሜት ውስጥ መውደቅ የቻልኩት? ምክንያቱስ ምን ነበር? ………. እንግዲህ አሁን ፍርጥርጡ ይውጣ ….ከላይ እንዳልኩት የተወለድኩት አርሲ ውስጥ ነው…12ኛ ክፍል እስካጠናቅቅ ድረስ ኦሮሞ ወይም አማራ ስለመሆኔም ትዝ ብሎኝ አያውቅም፡፡ ትኩረትም አልሰጠሁት….ምክንያቱም …እንደዚያ ነውና ወላጆቻችን ያሳደጉን!……እርግጠኛ ነኝ…የሌላውን ባላውቅም አርሲ ተወልዶ ያደገ … ስለ ዘር ተጨንቆ አያውቅም፡፡ አርሲ ውስጥ ኦሮሞ…አማራ …ሁሉም አብሮ ይኖራል፡፡ ማንም ስለዘር አስቦ አንዱን የሚጠላበት ሌላውን የሚያቀርብበት ሁኔታ የለም…በአርሲ! ሌላውም የኦሮሞ ክልል እንዲህ ዐዓይነት ስነልቦና እና አስተሳሰብ የሚኖር አይመስለኝም፡፡
    ስለዚህ…….ለመጀመሪያ ግዜ ስለ ዘር ማሰብ የተጀመረው በ1996 ዓ.ም. ዩኒቨርሲቲ ስንገባ ነው …..እንዴት? እንዴት ማለት ጥሩ ነው፡፡….. ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያሉ የጋራ ሽንት-ቤት ስትገቡ የሚያጋጥማችሁ ነገር….በጣም የሚያሳዝናችሁ ነው፡፡ ኦሮሞዎች ምን እንዳደረግናቸው አናውቅም….በዓለም ላይ ያለ ስድብ ሁሉ አይቀርም….ሽንት ቤት ግድግዳ ላይ የሚጽፉት፤…እኛን ኦሮሞዎችን ለመስደብ!፤ እንዴ ምን አረግናቸው… ይሄ ሁሉ ውርጅብኝ…በማለት ማሰብ ጀመርኩ/ን፡፡ አንዳንዴ ደግሞ…አንዳንዱ ከአፉ ያመልጠውና ዶርም ውስጥ “ጋላ” ይላል…በተለይ ከጎንደር አከባቢ የሚመጡ እንዲህ ዓይነት ችግር ነበረባቸው … በዚህ ግዜ ታድያ …እኛ እንነሳና…እቺን ይወዳል!….. ሽንትቤት ጭለማን ተገን አድርገህ የምትለቀልቀው ስድብ አንሶህ….ጭራሽ በግላጭ?….. እንካ ቅመስ! ….. የዶርም ድብድብ ወደ ብሎክ …የብሎክ ወደ ገቢው ያድግና … ከአንዴም ሁለቴ ትምህርት በዚህ ዓይነት ችግር ለሳምንታት በአርባምንጭ መቋረጡ ትዝ ይለኛል፡፡ ሌላ ግዜ ደግሞ… ያኔ ትምህርት ጨርሼ እዚያው ግራጅዌት አሲስታንት ነበርኩ …. አንዱ የጎንደር ተወላጅ የሆነ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል ባለደረባ (…እኔ ውኃ ቴክኖሎጂ ውስጥ ስለነበርኩ ብዙም አላውቀውም)…. ክላስ ይገባና…ተማሪዎችን ዲቤት እንዲያደርጉ… የመከራከሪያ ታይትሎች ይሰጣቸዋል …. ታድያ ካልጠፋ ታይትል … ኦሮሞ ከዬት መጣ ብላችሁ ተከራከሩ ይልና በማስከተል … ከመደወላቡ…ከማዳጋሰካር… ከፈለጋችሁ ከዛፍም ነው የመጣው ብላችሁ መከራከር ትችላላችሁ ይላል፡፡ በዚህ ግዜ ሀገር ቀውጢ ሆነ!….ትምህርት ለሳምንታት ተዘጋ….በመጨረሻ በስንት ጭቅጭቅ … ዩኒቨርሲቲው ከኦሮሚያ ድረስ ሽማግሌ አስመጥቶ… ያ ልጅ ከስራ ታግዶ…ከአርባምንጭ ብቻ ሳይሆን ሌላ ዩኒቨርሲቲም ሄዶ እንዳይቀጠር ደብዳቤ ተበትኖ…አመፁ በርዶ ልጆቹ ወደ ክላስ ሊመለሱልን ቻሉ፡፡
    ሌላወ….ብዙ ግዜ አይደለም…ግን አንዳንዴ ከኛም ልጆች … ለመበሻሸቅ ብለው ይሁን ከምራቸው … ለመጠነኛ ውዝግብ የዳረገንን ቃላት የወረወሩ ልጆች ነበሩ….ለምሳሌ አንድ ግዜ ዶርም ውስጥ ቀደዳ እየተከተፈ …. አንዱ …. ገበያ ውስጥ ዕቃ ከሸመትክ በኋላ ተሸካሚ ለመጥራት ምንድነው የምትሉት ይላል? ከአዲስ አበባ የመጣው….ሠራተኛ! … ሠራተኛ! ብለን ነው የምንጠራው አለ፡፡….ሌላው ደግሞ…ኩሊ!…ኩሊ! ብለን ነው የምንጠራው ምናምን አለ፡፡…..ከወለጋ(ነቀምት) የመጣው ሌላ ተማሪ ደግሞ….ጎጃሜ!…ጎጃሜ! … ብለን ነው የምንጠራው …እነርሱም… እትዬ እኔ ልሸከም!.. እትዬ እኔ ልሸከም!….እያሉ…እየተሽቀዳደሙ ነው ለመጠግረር የሚመጡት አለ፡፡ በዚህ ግዜ ዶርሙ በሳቅ ተናጋ……በዚህ የተበሳጩ ጎጃሜዎች …. አንዲህ ተብለን ተሰደብን ብለው ለተማሪዎች ዲን ለመክሰስ ፒቲሽን ሲፈራረሙ አይቻለሁ፡፡
    እንዲህ…እንዲህ እያለ ግዜው አለፈ፡፡ ሆኖም …. ይህን ዓይነቱ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ አልፈንበት የነበረው አንዳንድ ገጠመኝ …ይሄን ያህል ቦታ ሰጥቸው አንቲ አማራ ኣቋም አላስያዘኝም፡፡ ኸረ ጨርሶም ትዝ ብሎኝ አያውቅም!…እስከዚህ ዓመት ድረስ!…. ለመጀመሪያ ግዜ … በርግጥ አማራ ጠላታችን ነውን?? በማለት ለመጠራጠር የተገደድኩት በዚህ አመት ነው፡፡ ለምን? ….. ለምን ማለት ጥሩ ነው፡፡ አንድ ቀን ጀዋር የሚባል ወገናችን…እኔ ኦሮሞ ፈርስት ነኝ! አለ …. ከዚያ ኦሮሞ ፈርስት ነኝ አለ ተብሎ…. ጠባብ! ዘረኛ! የአማራ ጠላት!… በቃ የእርግማን ዓይነት ይዥጎደጎድ ጀመር፡፡ እንዴ! ምን ማለታቸው ነው?! እኔ ኦሮሞ ነኝ ማለት እንደምን ተተርጉሞ ነው የአማራ ጠላት …ወይም …. አንቲ ኢትዮጵያ የሚያስብለው??… በኦሮሞነትም በኢትዮጵያዊነትም መኩራት አይቻልም ወይ …. ኦሮሞ ነኝ ብለህ በራስህ ማንነት መኩራት ለምን እንዲ አበሳጫቸው ? ምን ዓይነት የተዛባ ፍረጃ ነው እያልን ገርሞን ሳይበቃ….ወድያው ቴዲ አፍሮ የሚባለው ሰው ….ተነስቶ የአጼ ምንሊክ ጦርነት…(የአኖሌው ፍጅት የተካሄደበት ማለት ነው)ቅዱስ ነው አለ ተባለ … ከዚያ ሰማያዊ ፓርቲ….ተክሌ የሻው …በፌስ ቡክ …. በጋዜጣ ….በቃ ፀረ-ኦሮሞ ዘመቻ ይቀጣጠል ገባ፡፡ በዚህ ግዜ በቃ ተስፋ ቆረጥኩ….ብዙ..ብዙ ጓደኞቼም ሆኑ ሌሎች ኦሮሞዎች ይኽው ነው የተሰማቸው፡፡… ስለሆነም ሳናስበው….ሳንፈልግ ..ወደማንፈልገው ጠረዝ እንድናፈገፍግና ወደ ዘረኝነት ካምፕ እንድንገባ ተገደድን፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ያናድድ የነበረው ደግሞ….ስንት ምጡቅ ምሁር…ስንት ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያኮሩ ልጆችን ለኢትዮጵያ ማበርከታችን ተዘንግቶ ….ወይም…..ተክዶ…ኦሮሞ ታሪኩን አያውቅም! ታሪካቸውን የፃፈላቸው ተስፋዬ ገ/አብ ነው! አኖሌ የሚሉት ተረት-ተረት ነው! ወዘተ እየተባለ የተነዛው የንቀት ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የሚገርመውና … በእጅጉም እንድንታዘባቸው ያደረገን ደግሞ…. ኦሮሞ ወራሪ ነው … ኢትዮጵያ ሀገሩ አይደለችም….ወዘተ እያሉ ከመታዘብ አልፈን በሳቅ እስክንፈርስ ድረስ የጋቱን ተረት ነው፡፡ በተጨማሪም….አንዳንድ አባቶቻችንን…ለምሳሌ ጋሽ ቡልቻን ባንዳንድ ድህረ ገጾች ላይ ለማዋረድ(በነሱ ቤት) ያደረጉት ጥረት…በእጅጉ ያሳዝን..ያሰተዛዝብም ነበር፡፡
    በዚህ ምክንያት…. በመበሳጨት ልበል ተስፋ በመቁረጥ…..እና ለካ እንደዚህ ነው የምንታየው…..አብረን እየሳቅን…አብረን እየበላን እየጠጣን ለኛ ያላቸው ድብቅ አቋም ይሄ ነው በማልት……እኔ በበኩሌ ካሁን በኋላ በቃኝ ብዬ ነበር ….እስከዛሬ ድረስ! ግን ሰህተት ነው! ከስሜታዊነት መውጣት መቻል አለብን፡፡ ላለፉት ጥቂት ወራት ካጋጠመን ንትርክም ሚዛናዊ ፍርድ ሰጥተን…. ትምህርት መውሰድ ይገባናል፡፡ የኦሮሞና የአማራ ህዝብ … እንደ ህዝብ እርስ በርሱ… በታሪክ ተጠላልቶ አያውቅም! ወደፊትም አይጠላላም፡፡ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችም ቢሆኑ….ሀገር ውስጥ ያሉትም…..ብዙዎቻችሁ የምትጠረጥሩት ኦነግም ጭምር … የአማራን ህዝብ በጠላትነት ፈርጆ አስተምሮም አያውቅ…. በፖለቲካ ፕሮግራሙ ላይም እንዲህ የሚባል ነገር አልፃፈም፡፡ እመኑኝ አልፃፈም፡፡ ዌብ ሳይታቸው ላይ ገብታችሁ ማየት ትችላላቸሁ፡፡ እራሳቸው…በግልፅ እንደሚናገሩት…በፓለቲካ ፕሮግራማቸውም ላይ እንዳሰፈሩት… ለዘመናት የተቃወሙት…ወደ ፊትም የማይቀበሉት…. የኦሮሞን ህዝብ …በኢክኖሚ…በማህበራዊ …በባህል ….ታሪኩን በመናቅ በመቅበርና አሲሚሌት በማድረግ ሲጨቁኑ የነበሩትን የነፍጠኛ ስረዓት ነው፡፡ የነፍጠኛ ስርዓት ማለት ደግሞ….የአማራ ህዝብ ማለት አይደለም፡፡ የነፍጠኛ ስረዓት ማለት የታጠቀ ሰራዊት ያልታጠቀ ህዝብ ላይ በማዝመት…. በመጨፍጨፍ… በመዘረፍ …መሬትን በመቀማት… የኢክኖሚና የፖለቲካ የበላይ ሆኖ በመቀመጥ … ኦሮሞዎችን በሃገራቸው… በርስታቸው…በወንዛቸው…ገባርና የበይ-ተመልካች የሚያደርግ ስርዓት ማለት ነው፡፡ የነፍጠኛ ስርዓት…. ስለዚህ በዓፄዎቹም ግዜ ነበር….በአሁኑ…በወያኔ ደግሞ የባሰ ሆኗል፡፡ እስቲ እግዚአብሄር ያሳያችሁ…. አንድ በፊንፊኔ ዙሪያ የሚያርስ ጭቁን የኦሮሞን ገበሬ መሬቱን በካሬ 10 ብር(አስር ብር!) ከፍለው ..ካስነሱት በኋላ….አነሱ መልሰው በካሬ 17000 (አስራ ሰባት ሺህ ) ብር በሊዝ ለባለ ኃብት ሲሸጡ፡፡ ከሁሉም … ከሁሉም የሚያስቆጨው…ብሩ ወደ ኢትዮጵያ ህዝብ ካዝና ያለመግባቱ ነው! ለምንድነው …እንዲህ ያልኩት….ብሩን ወደ ካዝና በቀጥታ ለማስገባት የሚያስገድድ አሰራር ካለ ….. ለምን መሬት የመቸርቸሩን ስራ አከባቢውን ለሚያስተዳድረው ኦህዴድ አይተውም??? ስለዚህ…ጥርጣሬ አይግባችሁ…ሰሞኑን ተማሪዎቻችን …ኦሮሚያ የኦሮሞ ናት…ፊንፊኔም የኦሮሞ ናት ሲሉ….ሌሎች(በተለይ አማራዎችን) ጠልተው አያገባችሁም ለማለት ሳይሆን … ቢበሉ የማይጠረቁት ትግሬዎች …. አሁን በተቀናጀ ማስተር ፕላን ስም ሊያካልሉ የፈለጉትን ዞን…..ማስተር ፕላን የተሰራለት አካባቢ ነው በማለት ፈረንጅንና ዲያስፖራን ካሞኙ በኋላ …. ዋጋውን በማዋደድ…. በሊዝ ቸርችረው ሲያበቁ …. እየዘረፉ ቢያጭቁበት የማይጠግበውን የኢፈርት ካዝናቸውን ሊያደልቡበት ነው፡፡ ከዚህ በፊት በአዲሳበባ አስተዳደር ስር ተከልሎ የነበረውን ቸርችረው ጨርሰዋል … አንዳች ልክፍት የተፀናወታቸው ስለሆኑ ….ጠገብኩን አያውቁም፡፡አሁን የተቀናጀ ማስተር ፕላን…ገለመሌ በሚሉት…ቀልድ አትጃጃሉ፡፡…የኦሮሞ ልጆችም እየከፈሉ ያሉትን መስዋዕትነት ….ልማት የማይፈልጉ ደንቃራዎች እያላቸሁ….አታራክሱት፡፡ የነገሩን አካሄድ ሳትረዱ እነኝህን ልጆች ስትቃወሙ በተዘዋዋሪ …አነሱን (ቅማላሞቹን) እያገዛችሁ ነው ማለት ነው፡፡ እመኑኝ ለጭቁኑ ኦሮሞ ተጨንቀው አይደለም…. ሁሌ ለማይሞላውና በቃኝን ለማያውቀው የኢፈርት ካዝናቸው ነው የተጨነቁት፡፡ በነገራችን ላይ ..ይሄን ትልቅ…የዘረፋ እቅድ ያ የሞተው መሪያቸው ነው (እግዚኣብሄር የስራውን ይስጠው) ከመሞቱ ጥቂት ወራት በፊት በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ …..የመሬት ሊዝ አዋጅ ብሎ ያስፀደቀላቸው (FEDERAL NEGARIT GAZETA, 18th Year No. 4, Addis Ababa, 28th November ,2011)..የዚህ አዋጅ ኮፒ እጄ ገብቷል፡፡
    ሌላው….. ኦነግ በበደኖና..ባርባጉጉ…አማሮችን ፈጅቷል ብለው የነዙትንም ፕሮፓጋንዳ አትመኑ፡፡ እኔ ዲፌንድ ላደርገው ፈልጌ አይደለም…ግን እግዚኣብሄር የሚያውቀው ሃቅ ስለሆነ ነው፡፡ ትዝ ይለኛል…የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ነበርኩ….ለኛ ..በዚያ እድሜ ላለን ሳይቀር ቪዲዮውን በትምህርት ቤት አሳይተውናል….እስቲ አስቡት ያንን ዓይነት አሰቃቂ ነገር … ልክ የህፃናት ፊልም ያሳዩን ይመስል…በዚያ እድሜያችን ሲያሰቅቁን፡፡ ማወቅ ያለባችሁ ነገር…ከደርግ ውድቀት በኋላ…ከሻቢያ ጋር በመተባበር ሃብት ከኢትዮጵያ ለመዝረፍ አስበው ነበር…ዋናው የሃብት ምንጭ ነበረው ደግሞ ቡናና የአዶላ ወርቅ ነው፡፡ ስለዚህ ክልሉ ውስጥ የሚገዳደራቸው ፓርቲ እንዲኖር አልፈለጉም…እናም ድርጅቱን ከህዝብ አጣልተው…በዚያን ወቅት የኦሮሞ ህዘብ የማያውቀውንና ከነሱ ጋር የመጣውን አጋራቸው ኦህዴድን በኦሮሚያ አማራጭ የሌለው ብቸኛ ፓርቲ ሊያረጉ ፈልገው ነው፡፡ ይሄ ጥርጣሬ ሃቅ መሆኑን የምትረዱት…ዶ/ር ዲማ በቅርቡ ስለዚህ ጉዳይ ተጠይቀው….አንደኛ-በዚያን ወቅት…የኦነግ ሰራዊት በአንዱ የወንጀል ቦታ ብቻ እንደነበረ… የነሱ(የትግሬ ) ሰራዊት ግን በሁለቱም የወንጀል ቦታዎች (በበደኖም ባርባጉጉም) የነበሩ ሲሆን…..የወንጀሉ ድርጊት በአዲስ አበባ እንደተሰማና በኦነግ ላይ ማስወራት እንደጀመሩ….ኦነግ…ገለልተኛ አጣሪ ጉዳዩን ይመርምርና…የኛም ሰራዊት ይሁን የናንተ ወንጀሉን የፈፀሙ ለፍርድ ይቅረቡ የሚል ሃሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ሆኖም የትግሬው ወንደዴ መሪ … ገለልተኛ አጣሪ ይቋቋም የሚለውን የኦነግ ሃሳብ አልቀበልም አለ፡፡ ነገሩም በዚያው ተዳፍኖ ቀረ፡፡ ስለዚህ…ካሁን በኋላ ያለምክንያት ባሉባልታና መጠላላት እናቁም፡፡
    ጎበዝ እስቲ ቆም ብለን እናስብ….ባለፈው እርባና ቢስ ሃሳብ ስንነታረክ ዳር ቆመው ሲያጨበጭበ የነበሩ…አሁን ምን እየሰሩ ነው?…ትላንት በኦሮሚያ…ዛሬ በጎንደር!
    እንዴ! እኔ አንድ ጥያቄ እራሴን እየጠየኩ ነው፡፡ ለመሆኑ በማን ነው እየተገዛን ያለነው? በጣልያን ነው…በኢትዮጵያዊ? እንዴት ሰውን የሚያህል ነገር….ለዚያውም ኢትዮጵዊን እንዲህ…እንደ አውሬ በጥይት እንደዋዛ ይገድላሉ? ኸረ…ጣሊያንም እንዲህ የኢትጵያን ህዝብ ያዋረደ አይመስለኝም፡፡ መግደል ካማራቸው… ለምን ከ 20 ዓመት በፊት አስፈራርቷቸው…የአሰብን ወደብ የተቀበላቸው ሻቢያ ላይ አይዘምቱም? ….. ይሄን ቁምነገር ቢያደርጉ እኛም እናከበራቸው ነበር፡፡ በጣም ነውኮ የሚያበሳጨው!
    አሁንስ ….. እያንዳንድህ ግልፅ ይሁንልህ … ስለወደፊትህ እያሰብክ እንደድሮህ መዋደድና መተባበር ትተህ … አማራ….ኦሮሞ … እምዬ ሚኒሊክ…ቅብርጥስ እያልክ …. ባፈጀ ታሪክ ትነታረካለህ … ከዚያ ተራ በተራ በጥይት እንደዚህ ትገለባለህ!
    ስለዚህ….እናስብበት!
    በድጋሜ ወንድሜ አንተነህ መርድ…ይህን የተቀደሰ ወቅታዊ ሃሳብ በማቅረብህ ተባረክ! ጤና ይስጥልኝ!
    ታድያለሁ ጉዲሳ ዳባ

Comments are closed.

Share