ትንሽ ስለነ ገብሩ አሥራት

(ይህን ፅሑፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ የበዮ ተ ‘የእነ ገብሩ አሥራት ዓላማ ትግራይን ለመጥቀም ነበር’ የሚል መልእክት ያለው ሐሳብ ነው። በዮም ሐሳቡ የሰጠው የቀድሞ የህወሓት ታጋዮች የጡረታ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል ለሚለው ፅሑፌ ለመተቸት ነው)

እነ ገብሩ አሥራት (ከፍተኛ የህወሓት አመራር አባላት የነበሩና አንጃ ተብለው የተፈረጁ የሚመለከት ነው) ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር በመሆን ትጥቅ ትግል ጀመሩ። ህወሓት በሁለት እከፍለዋለሁ፤ ስልጣን ፈላጊ መሪዎችና ነፃነት ፈላጊ ታጋዮች። ስልጣን ፈላጊ መሪዎች በግዜው የነበረውን የኢትዮጵያ ጨቋኝ ስርዓት ለመጣል ጫካ ገቡ። ትጥቅ ትግል ጀመሩ።

እነዚህ የህወሓት መሪዎች ስልጣን ፈላጊ ናቸው (ፍላጎታቸው ስልጣን እንደነበር ከጅምሩ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የምናየው የስልጣን ጥማተኞች መሆናቸውን ነው፤ ለዚህም ነው ስልጣን መልቀቅ የሞትን ያህል የሚፈሩት)። ስልጣን መፈለግ በራሱ ግን ችግር አይደለም። ማንም ሰው ስልጣን የመፈለግ፣ ለለውጥ የመታገል፣ ጨቋኝ ስርዓትን የመጣል መብት አለው። ስለዚህ የህወሓት መሪዎች ስልጣን ፈላጊዎች በመሆናቸው አልወቅሳቸውም። ስልጣን እንደ ግብ ወስደው ህዝብ ለነፃነት እንዲታገል ቀስቀሰው በፈጠሩት ዓቅም ለህዝብና ሀገር የሚጎዳ ተግባር መፈፀማቸው ግን ያስወቅሳቸዋል። ስልጣን ይዘው ስልጣኑ ፍትሕ ለማስፈን፣ ዴሞክራሲ ለማምጣት፣ ነፃነት ለመስጠት ከመጠቀም ይልቅ ህዝብን ለማፈንና ሀገርን ለማበታተን ተጠቀሙበት። በዚሁ ሊወቀሱ ይገባል።

ነፃነት ፈላጊ የህወሓት ታጋዮች ግን የከፈሉት መስዋእት እንጂ ያጠፉት ነገር አይታየኝም። የህወሓት መሪዎች የትጥቅ ትግሉ ከጀመሩ በኋላ የመንግስት (የደርግ) ወታደሮች ትግራይ ዉስጥ ማንዣበብ ጀመሩ። በአንድ በኩል የህወሓት መሪዎች የትግራይ ወጣቶች በሙዚቃ እያታለሉ አንዳንዴም እያፈኑ ካልተሳካም ንብረት እየወረሱና ወላጆች እየረሸኑ ወደ ትጥቅ ትግሉ እንዲቀላቀሉ ያስገድዳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የደርግ ወታደሮች ወጣቶችን ይገድላሉ፣ አዛውንቶችን ይረሽናሉ፣ እናቶችን ይደፍራሉ። የትግራይ ህዝብ በሁለቱም (በደርግና ህወሓት) ተሰቃየ። የደርግ በደል የከፋ ስለነበረ አብዛኞቹ የትግራይ ወጣቶች ወደ ህወሓት ተቀላቀሉ። ነፃነት ፈላጊ የህወሓት ታጋዮች ሆኑ።

የህወሓት ታጋዮች ዓላማ ታድያ ደርግ ከሚፈፅመው ግፍ ለማምለጥና ደርግን ከትግራይ ማባረር ነበር። ወጣቶቹ ወደ ህወሓት ሲቀላቀሉ በደርግ ወታደሮች ከሚሰነዘር ጥቃት ለማምለጥም ጭምር ነበር። ትግራይ አልተረጋጋም ነበር። ሰው በየመንገዱ ይታረዳል። ህዝብ ነፃ አልነበረም። እነዚህ ወጣቶች ታድያ ነፃነት ፈልገው ከህወሓት ጎን ተሰልፈው ለመዋጋት መረጡ። ዉሳኔያቸው ትክክል ነው።

እኔም በዛን ግዜ ብኖር ኑሮ ከህወሓት ጋር ተሰልፌ ደርግን እዋጋ ነበር። ነፃነት እፈልግ ነው። ለነፃነቴ መስዋእት እሆን ነበር። ደርግን ለማባረር እዋጋ ነበር። በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ፣ ዓሰብ ጉዳይ፣ የኢትዮጵያውያን አንድነት ጉዳይ፣ የዴሞክራሲ ጉዳይ፣ አይድይሎጂ ወዘተ ግን ከህወሓት መሪዎች ጋር አልስማማም ነበር። በነዚህ ጉዳዮች ላይ ከሌሎች የህወሓት መሪዎች ጋር እወያይ ነበር። በኔ ሐሳብ ካልተስማሙ ወይ ካላሳመኑኝ ግን ከደርግ ውድቀት በኋላ ከህወሓት እለቅ ነበር። አብዛኞቹ የህወሓት ታጋዮችም ይሄን ነው ያደረጉ። እኔም ብሆን አደርገው ነበር። ስለዚህ በኔ እምነት በነፃነት ፈላጊዎቹ የህወሓት ታጋዮች የተፈፀመ ችግር አይታየኝም።

ችግሩ ያለው በመሪዎቹ ነው: ስልጣን መፈለጋቸው ሳይሆን በብዙ የትግራይ ወጣቶች ደም፣ መስዋእት የያዙት ስልጣን ለግል ጥቅማቸው በማዋል ህዝብና ሀገር በመጉዳታቸው። በሰማእታት ስም እየነገዱ ሌሎች ህዝቦችን መጨቆናቸው፣ የህዝብን መብት ከማክበር ይልቅ መብቱ ለሚጠይቅ መጨፍጨፍ፣ መጨቆን፣ ዜጎች ለነፃነት ብለው መስዋእትነት ከፍለው ባመጡት ስልጣን አምባገነናዊ ስርዓት መትከል ወዘተ ። ይህን ሁሉ ለሰማእታቱ ክህደት ነው።

ወደ እነ ገብሩ አሥራት ልመለስ። እነ ገብሩ ከህወሓት መሪዎች የሚመደቡ ናቸው። የህወሓት መሪዎች ሁነው ለመፈፀሙት ስህተት ይሁን በደል ከሌሎች የህወሓት መሪዎች ጋር ተጠያቂ ናቸው። ስልጣን ፈላጊ የህወሓት መሪዎች ስህተት ፈፅመዋል ባይ ነኝ። እነ ገብሩም የዚህ ስህተት አካል ናቸው። ስህተት መፈፀም በራሱ ግን ችግር ላይሆን ይችላል። አንድ ሰው ወይ ድርጅት ስህተት ሊፈፅም ይችላል። ፍፁም የሆነ የለምና። ጥረት ማድረግ ያለብን ስህተት እንዳይሰራ ብቻ ሳይሆን ስህተት ከተሰራ በኋላ ተሎ ማስተካከልም ነው።

ስህተት ላለመስራት ጥንቃቄ ማድረግ፤ ስህተት ከተሰራ ግን ማስተካከል። ስህተት ለማስተካከል መጀምርያ ስህተቱን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። ስህተትን ካልተቀበልን ልናስተካክለው አንችልም። የህወሓት መሪዎች ባጠቃላይ ስህተት ሰርተዋል ባይ ነኝ። የተወሰኑ ስህተታቸው አምነው ተቀብለው ለማስተካከል ቆርጠው የተነሱ ናቸው፣ ሌሎች ደግሞ ስህተታቸው ያልተቀበሉ ናቸው። ስህተታቸው ያመኑ ስህተቱ ለማስተካከል ዝግጁ የሆኑ ናቸው። ስህተታቸው ያላመኑ በተሳሳተው መንገድ የሚቀጥሉ ናቸው። እነ ገብሩ አሥራት ስህተታቸው የተቀበሉና ለማስተካከል የተዘጋጁ ሲሆኑ እነ መለስ (አሁን በስልጣን ያለ ቡድን) ደግሞ ስህተቱን ለማስቀጠል የሚንደፋደፍ ነው።

ምንም እንኳ እነ ገብሩ የህወሓት መሪዎች በነበሩበት ግዜ ከጓዶቻቸው ጋር ጥፋተኞች ቢሆኑም ጥፋታቸው አምነው መቀበላቸው፣ ለማስተካከል መዘጋጀታቸው የሚደነቅ ነው። ዉሳኔያቸው አንድ እርምጃ ወደፊት ነው። ስህተታቸው በማመናቸው ብቻ ከነዚህ እስካሁን በስልጣን ላይ ያሉ ስህተቱን የሚያስቀጥሉ የህወሓት መሪዎች የተሻሉ ያደርጋቸዋል።

አሁን እነ ገብሩ ሌላ አማራጭ ድርጅት መስርተው እየታገሉ ነው። ዓረና መስርተው ሲታገሉ አንዳንዶች “ያው እነሱማ ህወሓት ናቸው። ዓረና ህወሓት በነበሩ ሰዎች ከተመሰረተ እንዴት ከህወሓት ይለያል? አሁን ዓረና ሁነን ለውጥ እናመጣለን የሚሉን ስልጣኑ የራሳቸው እያለ ምን ለውጥ አመጡ? ከህወሓት የወጡ ስልጣን ፈልገው አኩርፈው ነው፣ እነ ገብሩ የትግራይ ኢምፓየር ለመፍጠር ጥረት ያደርጉ ነበር!… ወዘተ” የሚሉ ሐሳቦች ይነሳሉ።

መጀመርያ እነ ገብሩ ከህወሓት ከፍተኛ አመራር አባላት የሚመደቡ ናቸው። ፍላጎታቸውም እንደ ማንኛውም የህወሓት መሪ ስልጣን ነበር እንበል። ህወሓት የደርግን ስርዓት ከገረሰሰ በኋላ የመንግስት በትረስልጣን መጨበጡ ይታወቃል። ከ1983-1993 ዓም በነበረ ግዜ የህወሓት አመራር ቡድናዊ (Group Leadership) ነበር። በዚሁ መሰረት እነ ገብሩ የህወሓት ስራ አስፈፃሚ አባላት ስለነበሩ የቡድን አመራር አባላትም ነበሩ። ስለዚህ እነ ገብሩ ህወሓት በነበሩበት ግዜ ከፍተኛ ባለስልጣናት ነበሩ ማለት ነው። እነ ገብሩ ከፍተኛ የህወሓት ባለስልጣናት ከነበሩና ይህንን ከፍተኛ ስልጣን ጥለው ለቀው ከወጡ እንዴት ስልጣን ፈልገው አኩርፈው ነው ከህወሓት የወጡ ማለት ይቻላል? ከፍተኛ የሚባል ስልጣንኮ ይዘውት ነበር!? ከዛ በላይኮ ስልጣን የለም። ስለዚህ ስልጣን በፍቃዳቸው ለቀው እየወጡ ስልጣን ፈልገው ነው የወጡ ቢባል ምክንያታዊነት ይጎድለዋል። አቶ ገብሩ አሥራት ለምሳሌ ብንወስድ የህወሓት ስራ አስፈፃሚ አባል ነበር። አሁንም የዓረና ስራ አስፈፃሚ አባል ነው። የዓረና (ስልጣን ያልያዘ ድርጅት) ስልጣን ይበልጣል ወይስ የህወሓት (ስልጣን ያለው ፓርቲ)? እነ ገብሩ ከህወሓት የወጡ ስልጣን ፈልገው ነው የሚል እምነት የለኝም። ምናልባት የስልጣን ፈላጊ የህወሓት አመራር አባላት አካል መሆናቸው ፀፅቷቸው ይሆናል እንጂ።

እነ ገብሩ ህወሓት ነበሩ፣ አሁን ግን የዓረና (የሌላ ድርጅት) አባላት ናቸው። የህወሓት የትጥቅ ትግል ከፍተኛ መስዋእትነት ተከፍሎበታል። እንደ መሪዎቹ ተልእኮ የህወሓት ዓላማ ስልጣን ከነበረ ስልጣን እንደ ዓላማ መያዝ ትክክል እንዳልሆነ እነ ገብሩ ተገንዝበው ይሆናል። ስልጣን መያዝ ስትራተጂ እንጂ ግብ እንዳልሆነ ከተረዱ ዴሞክራሲና ነፃነት ለማስፈን አማራጭ ፓርቲ መስርተው እየታገሉ ይሆናል። የተቀደሰ ሐሳብ ነው።

በታጋዮቹ ዓይን የህወሓት ዓላማ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ ልማት፣ ነፃነት፣ እኩልነት ወዘተ ነበረ። ብዙ የትግራይ ወጣቶች መስዋእት የሆኑበት ምስጢር ለዜጎች ነፃነት ለማስፈን ከሆነ እነ ገብሩ አሥራት መስዋእትነት የተከፈለበትን የነፃነት ዓላማ ተጠቅመው ነፃ ሁነው የፈለጉትን ፓርቲ ቢመሰርቱ፣ የፈለጉትን ፓርቲ አባል ቢሆኑ ችግሩ ምንድነው? የፈለጉትን ፓርቲ ሲደግፉ፣ ያልፈለጉትን ሲቃወሙ የፖለቲካ ነፃነታቸውን እየተጠቀሙ አይደለምን? የታገሉትና መስዋእት የከፈሉትኮ ለራሳቸው ነፃነት ነው። ለራሳቸው ነፃነት ታግለው፣ ለመሰዋእትነት ቀርበው ሲያበቁ የፈለጉትን የመሆን መብታቸው ከተነፈጉ የታገሉበትን የነፃነት ዓላማ አቅጣጫውን መሳቱና ለሌላ ዓላማ መዋሉ ማረጋገጫ አይሆንም? የህወሓት ዓላማ ስለመጠለፉ ከዚህ የበለጠ ማስረጃ ከየት ሊመጣ ነው? እነ ገብሩ በነፃነት መኖር ካልቻሉ ለምን ነበር ታድያ የታገሉት? ነፃነት የተባለው የህወሓት አባል ለመሆን ብቻ ነበር እንዴ? የህወሓት አባላትስ ቢሆኑ ነፃነቱ መቼ ተሰጣቸው? እነ ገብሩ የህወሓት ታጋዮች ራሳቸው ባመጡት ስርዓት ነፃነታቸው ሲገፈፍ እያየሁ እኔ (በትጥቅ ትግሉ ያልተሳተፍኩ) የፈለኩትን የመሆን ነፃነቴ ይጠበቅልኛል ብዬ መገመት እችላለሁ? አልችልም። ስለዚህ እነ ገብሩ ሌላ ድርጅት መመስረታቸው ለታገሉለት የዴሞክራሲ ዓላማ አስተዋፅዖ እያደርጉ እንጂ ሌላ አይደለም።

ዓረና በነ ገብሩ (ህወሓት የነበሩ) ስለተመሰረተ ከህወሓት አይለይም ማለት አንችልም። ሲጀመር ዓረና የተመሰረተው በነ ገብሩ ብቻ አይደለም። የዓረና መስራች አባላት ከአንድ ሺ በላይ ነበሩ። ከነዚህ ስድስቱ ብቻ ናቸው የህወሓት ታጋዮች። በዚሁ መሰረት ዓረና በነ ገብሩ የተመሰረተ ነው ማለት አንችልም። ግን ይሁን። ሐሳብ ለመስጠት እንዲመቸን ዓረና በነ ገብሩ እንደተመሰረተ እንውሰደው። ዓረና በነ ገብሩ ቢመሰረትም ከህወሓት ጋር በብዙ ነጥቦች ይለያል (የዓረና ሕገደንብ፣ ስትራተጂ፣ ፕሮግራም፣ አይድዮሎጂ ወዘተ መመልከት ይቻላል)። እነ ገብሩ ህወሓት ከሆኑ ለምን ከህወሓቶች ጋር አልቀጠሉም? ከህወሓት ጋር ቢቀጥሉ (ቢታረቁ)ኮ ሳይደክሙ ስልጣን ይሰጣቸው ነበር። ዓረና በሐሳብ ክርክር ያምናል። ዓረናና ህወሓት አይገናኙም። የህወሓት ገብሩና የዓረና ገብሩ የተለያዩ ናቸው። የአስተሳሰብ ለውጥ አለ፣ የአቋም ለውጥ አለ፣ የአሰራር ለውጥ አለ፣ የአይድዮሎጂ ለውጥ አለ። ለዚህም ነው እነ ገብሩ ህወሓትን ለቀው መውጣት የመረጡት።

ስለነ ገብሩ ጉዳይ ሲነሳ በአንድ በኩል እነ ገብሩ በስልጣን እያሉ ምን ጥሩ ነገር ሰሩ የሚል ጥያቄ ይነሳል። በሌላ በኩል ደግሞ እነ ገብሩ የትግራይ ኢምፓየር ለመፍጠር ጥረት ያደርጉ ነበር የሚል ትችት ይሰነዘራል። አቶ ገብሩ አሥራት ከህወሓት ከመልቀቁ በፊት የትግራይ ክልላዊ መንግስት ፕረዚደንት ነበር። እንዳጋጣሚ ሁኖ በትግራይ ክልል ዉስጥ የተገነቡ የትእምት ፋብሪካዎች በገብሩና ስየ አብርሃ ዘመን የተገነቡ ናቸው። እነ ገብሩና ስየ አብርሃ ከህወሓት ከለቀቁ ወዲህ በትግራይ ክልል አንድም ፋብሪካ አልተገነባም (ወይም የተገንባ ፋብሪካ አላውቅም)። እነ ገብሩ የትግራይ ኢምፓየር ለመፍጠር ጥረት ያደርጉ ነበር የሚለው ትችት ከዚህ የመነጨ ይመስለኛል። ስለዚህ በነ ገብሩ ዘመን ለውጥ አልነበረም ማለት አይቻልም። በትግራይ ለውጥ መጥቷል ከተባለ በነ ገብሩና ስየ የመጣ ነው።

በነ ገብሩና ስየ ዘመን የመጣ ለውጥ ስላለ እነ ገብሩና ስየ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ ማለት ግን አይደለም። ያኔ ለመጣ ለውጥ (የትእምት ፋብሪካዎች መገባት ለውጥ ከተባለ ማለቴ ነው) እነ ገብሩና ስየ ብቃት ወይ ጥሩ ተግባር አያሳይም። ምክንያቱም በህወሓት የፖለቲካ ባህል መሰረት አንድን ነገር የሚሰራው ወይ የማይሰራው በግለሰቦች ሳይሆን በድርጅት ነበር። አንድ ባለስልጣን የሚሰራውን ነገር ይቅርና የሚናገረው ነገርም በፓርቲ ነው የሚሰጠው። ስለዚህ በህወሓት በግለሰብ ሳይሆን በፓርቲ ነው የሚሰራው። ብህወሓት ዘመን ጥሩ ወይ መጥፎ ከተሰራ ሽልማቱ ወይ ትችቱ የሚሄደው ወደ ፓርቲው እንጂ ወደ ግለሰቦች አይደለም። ይህ የየተማዕከለ ዴሞክራሲ (Democratic Centralism) ዉጤት ነው። ስለዚህ በገብሩ ዘመን ጥሩም መጥፎም ተሰርቶ ከሆነ በህወሓት የተሰራ ነው። ምክንያቱም በገብሩ ዘመን በህወሓት የቡድን አመራር ነበር። እነ ገብሩ ከለቀቁ በኋላ ግን መለስ ህወሓትን ተቆጣጠረው። ስለዚህ ከ1993 ዓም በኋላ በትግራይ (በኢትዮጵያም) ለተሰራ ጥሩም መጥፎም ተግባር የመለስ እጅ አለበት።

በነገብሩ የስልጣን ዘመን የትእምት ፋብሪካዎች ስለተተከሉ ትግራይን የሚጠቅም ስራ ተሰርቷል ብዬ አላምንም። በአንድ አከባቢ ፋብሪካ ሲተከል ያከባቢው ህዝብ ተጠቃሚ ነው የሚባለው ፋብሪካው የስራ ዕድል ሲፈጥር፣ ያከባቢው ኗሪዎች ባላቸው ብቃት፣ የትምህርት ደረጃ፣ የስራ ልምድ ወዘተ መሰረት ያለ ምንም አድልዎ ተወዳድረው ተቀጥረው መስራት ሲችሉ እንዲሁም የተተከለው ፋብሪካ ትርፋማ ሁኖ ባገኘው ትርፍ ሌላ ኢንቨስትመንት ሲከፍት ነው። ይህን ዕድል ከሌለ ፋብሪካ ቢገነባ ባይገነባ ዋጋ የለውም። ምክንያቱም ፋብሪካው ህዝብን የሚጠቅም ሳይሆን ባለሃብቱ ብቻ የሚያገለግል ከሆነ፣ ሰራተኞች በብቃት ሳይሆን በዝምድና የሚቆጠሩበት ከሆነ ትርፉ የሚዘረፍ ከሆነ፣ ባከባቢው ለሌላ የግል ኢንቨስትመንት ዕንቅፋት የሚሆን ከሆነ ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው። ስለዚህ የትእምት ፋብሪካዎች በ አማራ ክልል ቢገነቡም ለ አማራ ህዝብ የሚጠቅም ነገር አይኖራቸውም። ስለዚህ በትእምት ፋብሪካዎች የትግራይ ህዝብ ተጠቅሟል የሚል ግምት የለኝም።

እነ ገብሩ የትግራይን ኢምፓየር ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል ለሚለው ወቀሳ አዘል መልእክት መልስ ለመስጠት የህወሓቶች የተማዕከለ ዴሞክራሲ አሰራና በግዜው የነበረ የቡድን አመራር ሂደት ለግዜው እንተወውና እነ ገብሩ ለትግራይ ይሰሩ ነበር በሚለው የትችት መስመር እንጓዝ።

ገብሩ ትግራይ ክልል የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ሞክሯል እንበል። ይሄ ታድያ ያሸልመዋል እንጂ ያስወቅሰዋል እንዴ? አቶ ገብሩ ኮ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ፕረዚደንት ነበር። አንድ የክልል ፕረዚደንት የሚመራውን ክልል ማሳደግ አለበት፣ የኢንዱስትሪ ማዕከል ማድረግ አለበት፣ በሁሉም ዘርፎች ዕድገት እንድታሳይ ጥረት ማድረግ አለበት። አንድ የወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሚያስተዳድረውን ወረዳ ለማሳደግ ሌትለቀን መስራት አለብት። የአፅቢ ወንበርታ ወረዳ አስተዳዳሪ የራሱ ወረዳ ችላ ብሎ የሐውዜንን ወረዳ ለማሳደግ ጥረት ማድረግ የለበትም።

የትግራይ ክልላዊ መንግስት ትግራይን የምታድግበት መንገድ ነው ማመቻቸት ያለበት። የትግራይ ክልል መንግስት የምንወቅሰው ትግራይን ከማሳደግ ይልቅ የማዳከም ስራ ስለሚሰራ ነው። የአማራ ክልላዊ መንግስት አማራ ክልልን የምታድግበት፣ የኢንዱስትሪ ማዕከል የምትሆንበት ስትራተጂ መንደፍ ይኖርበታል። የአምራ ክልል መንግስት የራሱን ክልል ትቶ የኦሮምያን ክልል ለማሳደግ ጥረት ያደርጋል ተብሎ አይጠበቅም። የኦሮምያ ክልል ፕረዚደንት ኦሮምያን ትቶ ትግራይን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ የለበትም። አንድ ሀገር እስከሆንን ድረስ መተባበር ይቻላል። የአንድን ክልል ዕድገት at the expense of others እድገት መሆን እንደሌለብትም እንስማማለን። ስለዚህ ህወሓት ትግራይ ለማሳደግ ጥረት ቢያደርግ፣ ብአዴን አማራን፣ ኦህዴድ ኦሮምያን ለማሳደግ ጥረት ቢያደርጉ ችግር የለም። ችግር የሚሆነው የኢህአዴግ መንግስት (የፌደራል መንግስት) አንድን ክልል ፍትሓዊ ባልሆነ መንገድ መርጦ ለማሳደግ ሲሞክር ነው። ምክንያቱም የፌደራል መንግስት ለሁሉም ክልሎች በእኩል ይመለከታቸዋል። ስለዚህ ገብሩ አሥራት የትግራይ ፕረዚደንት እስከነበረበት ድረስ ትግራይን ለማሳደግ ጥረት ቢያደርግ ለትችት የሚበቃ አይመስለኝም።

በትግራይ ለውጥ ቢመጣ በአንድ የኢትዮጵያ አካል ለውጥ መጣ ማለት ነው። በአማራ ለውጥ ሲመጣ በኢትዮጵያ ለውጥ መጣ ማለት ነው። በአንድ ክልል ለውጥ አልመጣም ማለት ደግሞ በአንድ የኢትዮጵያ አካል ለውጥ አልመጣም ማለት ነው። በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ለውጥ ሲመጣ በኢትዮጵያ ለውጥ መጣ እንላለን። ስለዚህ ሁሉም የክልል መንግስታት በየክልላዊ ግዛታቸው ለውጥ ለማምጣት ጥረት ማድረግ አለባቸው።

ገብሩ የዓረና አባል ነው። ማንኛውም ሰው (የህወሓት ወይ የሌላ ፓርቲ አባል የነበረም ጭምር) በሐሳብ ክርክር እስካመነ ድረስ የዓረና አባል መሆን ይችላል። በፓርቲ ፖለቲካ ሰው የሚመዘነው በአስተሳሰቡ እንጂ ባለፈው ታሪኩ አይደልም። ትናንት ህወሓት የነበረ ዛሬ ዓረና ሊሆን ይችላል። ዛሬ ዓረና የሆነ ነገ የሌላ ፓርቲ አባል ሊሆን ይችላል። ዋናው ነገር አስተሳሰቡ ነው። ዓረና መርህ መሰረት አድርጎ ነው ሰው የሚገመግም።

ማንም ሰው አዲስ ሐሳብ ይዞ ወደ ዓረና መግባት ይቻላል። ሐሳቡ ከዓረና መርህ ጋር አብሮ ከሄደ ጥሩ ነው። አብሮ የማይሄድ ከሆነ ደግሞ አንድም ተከራክሮ ያሳምናል ወይ ያምናል። ዓረና በሐሳብ ክርክር ነው የምናምነው። አሸናፊ (አሳማኝ) ሐሳብ ካለ የማንቀበልበት ምክንያት የለም። እናም የሚያሳስበን ገብሩ ትናንት ማን ነበር ሳይሆን ገብሩ አሁን ማነው? የሚል ነው። አስተሳሰቡ ያስተካከለ፣ ለውጥ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ወደ ዓረና መቀላቀል ይችላል።

የዓረና አባል መሆን ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም (በቁሳዊ ጥቅም ሳይሆን በፖለቲካ መርህ ሲታይ)። ምክንያቱም ዓረና ከተስማማህ የዓረና አባል ሁነህ ለህዝብህና ሀገርና የምታበረክተው አስተዋፅዖ ይኖረሃል። ዓረና ካልተስማማህ ደግሞ ዓረናን በቀላሉ መተው ትችላለህ። ምክንያቱም ዓረና በሐሳብ የሚያምን ሰለማዊ ታጋይ ነው፤ ጠብመንጃ የለውም። የተለየ ሐሳብ ስለያዝክ ወይ ዓረናን መልቀቅ ስለፈለክ ብቻ አይገድልህም። የመግባትና መልቀቅ መብትህ የተጠበቀ ነው። ምክንያቱም ሰለማዊ ነዋ። መሳርያውም ሐሳብ ነው። ሐሳብ አስተሳሰብን ይቀይራል እንጂ አይገድልም። ስለዚህ ወደ ዓረና ለመግባት አትፍራ።

It is so!!!

6 Comments

 1. I am sick of this man so called university lecturer, every single time he writes only about TIGRAY and Tigrians, When he should be thinking about Ethiopia and would have write about Ethiopian and Ethiopians, I can imagine that the out come of the pupil who are studying in his class. Please grow up and think about Ethiopia, then the people you are trying to protect will then get a solution, I think you and others who are growing in that dust filled land have a problem. The Almighty God help you! (MIN YEBALAL LELA) Zeregna

 2. Ato HABREA ANTE NEHI ENGDI TIGRIE WEST TEKAWAMI YEMETEBALEW . KE TPLF MINIM ATELEYEM. ANTEM HONE TPLF ETHIOPWINET SEMET YELACHEWM ATEWASH. DEGEMO TEWAGTEN NEW YASHENFNEW TILALEY YET NEW YETWAGACHEWT. DERGEN BEMETAGEL ADDIS ABEBA KE 200 000 HIZB BELAY MESEWTENT KEFLOAL. HINANTE YE BANDA LEJOCH KEADIWOCH NACHEW. ANTE KE ETHIOPIA YELEK TIGRENET NEW YEMIBELTEBEH.

 3. ከነዚህ ዘረኞች ኣጋመ ድሮስ ምን ትጠብቁ ነበር? ይህ ሰው ስለ ኢትዮጵያ ጽፎ ያውቅ እንደሆነ እኔ እንጃ። ሁሌ እንደለሎች መሰሎቹ ስለ ትግራይና ስለ ዓረና ዋላ ወያነ ብቻ ነው ሲያለቃቅስ የሚኖረው። ደግሞ እነዚ ገብሩ ኣስራት ዋላ ኣስገደ የሚባሉ የዓረና መሪዎች ትናንት የወያነ ኣባላት ኣልነበሩም እንዴ? ስለ ኤርትራ ጥያቄ ከነመለስ የተለየ ሃሳብ ኖራቸው ኣያውቅም። ኣሁን ከስልጣን ተፈንግለው የወያነ ሰለባ ስለ ሆኑ ብቻ ‘ኢትዮጵያውያን ነን’ ማለታቸው ማንንም ማደናገር ኣይችሉም። ትናንት እንደተሳሳቱ እንኳን ኣደባባይ ወጥተው ለኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ ኣልጠየቁም። ይህ ጋዜጠኛ ነኝ ባይ፡ ለምን ስለነሱ እንደሚያልርቃቅስ ኣይገባኝም። ለራሱ የወያነ መልእክተኛ ሳይሆን ኣይቀርም!!

 4. DEAR EDITOR –

  PLEASE STOP RECYCLING!! I AM NOT SURE IF THIS IS A RECENT ARTICLE. IT TALKS ABOUT “MELES” IN THE PRESENT TENSE AND FOR SURE WAS WRITTEN LONG BEFORE THE PRIME EVIL MINSTER WAS DEAD!!

  Nonethless, as usual Abreha raises an issue of critical importance in the Ethiopian political discourse.

 5. If we all believe in one united Ethiopia, the development of Tigrai if it was done lawfully and appropriately should be commended. The Problem is there is no one Ethiopia we should not Forget the evil Agenda of the fascists to create greater TIGRAI and the Transfer of funds from other kilils to Tigrai illegally by saying the other kilils are not capable of using the fund. Dear Abrha do you think Adwa is the right place to have a textile factory is the Cotton growning in Adwa. Even Mengistu had all the companies in regions where raw materials are available but not in his village. The crimes committed by the home grown fascists are very difficult to defend.

 6. I appreciate this guy for speaking against TPLF and he is by far better than most Tigrians and we should not condemn him, he strongly believe he is Ethiopian and he is being attacked for that position from WOYANNES and any good Ethiopian should encourage this guy and advise him on certain issues
  For instance he argued TIGRAY did not benefit from the INDUSTRIES BUILT in Tigray ….. ABRHAM you must be joking on that I know you are defending the people of Tigray not to be labelled us as beneficiaries like TPLFites and please stop such kind of nonsense
  Any Factory or industry will create lots of opportunities for the locals and also creates employment opportunities and business opportunities not only the people who lives in the area but also for the surrounding areas and we all know and have seen even the impact of one single Factory on the lives of the people who are living in the town or the city the factory operates
  you are just defending TIGRAY like TPLFites

Comments are closed.

Previous Story

ሰበር ዜና- እስካሁን ድረስ ሰባት Ethiopian Online Activists and Bloggers በፖሊስ ታድነው ታስረዋል

Next Story

ሰልፍና ሰደፍ፤ ዘመቻ ነቀምትና ዘመቻ ኢትዮጵያ – ከተክለሚካኤል አበበ

Latest from Blog

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ | አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ | አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል | ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ\  አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

ከመጠምጠም መማርን እናስቀድም!

;በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) አብዛኛው አንባቢ ተገንዝቧል ብዬ እንደምገምተው ሕዝብ ለቡና ቲራቲም፣ ለግብዣ፣ ለበዓል፣ ለሰረግ፣ ለሐዘን፣ ለእድር፣ ለእቁብ ለውይይትና ለሌሎችም ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ሲገናኝ የሚበዛው አድማጭ ሳይሆን ተናጋሪ  ወይም ደግሞ ለመናገር  መቀመጫውን ከወንበር ወይም
Go toTop