የሚታደስ ቃል ኪዳን (ከጸጋዬ ገብረ መድኅን አርአያ)

“ መኳንንቶቼ፣ ልጆቼና ሕዝቦቼ ሆይ! እኔ ስለ እናቴ ኢትዮጵያ ሕይወቴን ልሰዋላት ሙሉ ፈቃድ አለኝ። በእኔ ልብ ያለው አሳብ በትክክል በእናንተም ልብ በመታሰቡ በጣም ደስ ብሎኛል።
“ እንግዲህ አሳባችን አንድ ከሆነ ጠንክሩ እንጂ አትፍሩ። ለዘመቻውም አዋጅ አናግራለሁና አይዞአችሁ አትፍሩ!
“ አገሬ ሆይ ስሚ! መኳንንቶቼ፣ ወታደሮቼ፣ ሕዝቦቼ ስሙ…..ወደፊት ገስግሱ እንጂ ወደኋላ አትቅሩ!
“ የኢትዮጵያ ልጅ ሆይ! ልብ አድርገህ ተመልከት ኢትዮጵያ የተባለችው አንደኛ እናትህ ናት! ሁለተኛ ዘውድህ ናት! ሦስተኛ ሚስትህ ናት! አራተኛ ልጅህ ናት! አምስተኛ መቃብርህ ናት! እንግዲህ የእናት ፍቅር፣ የዘውድ ክብር፣ የሚስት ደግነት፣ የልጅ ደስታ፣ የመቃብር ከባቲነት እንደዚህ መሆኑን አውቀኸው ተነሳ!”
አንበሳው አጼ ዮሐንስ- ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
ለእናታቸው፣ ለሚስታቸው፣ ለልጃቸው፣ ለዘውዳቸውና ለመቃብራቸው የተሰውትና በሕይወት ዘመናቸው “አንበሳው አጤ ዮሐንስ” እየተባሉ ይጠሩ የነበሩት ሰማዕት ከሞቱ 125 ዓመት ሆናቸው። አንድ አሜሪካዊ ታጋይ በ1775 በአንድ የፊላደልፊያ ፍርድ ቤት ቀርቦ የታላቁን የእንግሊዝ መንግሥት አመራር በመቃወም በፈፀመው ወንጀል እንዲሰቀል ሲፈረድበት የተናገረው ተጠቃሽ ቃል ነበር። “አዝናለሁ እግዚአብሔር አንድ ነፍስ ብቻ ስለሰጠኝ” ነበር ያለው። አጤ ዮሐንስን በዚያ ታሪካዊ ብጽአት የምለካቸው፣ በዚያው ራሳቸው በመደቡት የወርቅ ሚዛን የምመዝናቸውና ለኢትዮጵያ ተከታታይ ትውልዶች ሁሉ ዘላለማዊ ብሔራዊ ቃል ኪዳን ቀርጸው ያለፉ ታላቅ መሪ ስለሆኑ ነው። በዚህ መስፈርት የኖሩም ናቸው። ደርቡሽ ጀግናውን መሪ ገድያለሁ፣ አንገቱንም ቆርጨ ወስጄ ተጫውቸበታለሁ ሊል ይችላል። ዮሐንስ ተገድሎ የኢትዮጵያ መሬት በደርቡሽ ተወስዶ ቢሆን ቁጭቱ ባነደደን ነበር። እስከማዕዜኑ። ቢያንስ 125 ዓመት የዚያ አካባቢ ኢትዮጵያዊ መሬትነት ተጠብቆ ቆይቶአል። ደርቡሽ የደፈረንስ አሁን ነው። አገር ሲያረጅ እሾህና አሜከላ ያበቅላልና!
አጤ ዮሐንስ – ራሳቸው ባሰፈሩት መዳልው መሠረት ለእናታቸው፣ ለሚስታቸው፣ ለልጃቸው፣ ለዘውዳቸውና ለመቃብራቸው ሕይወታቸውን “ለመሰዋት ሙሉ ፈቃድ አለኝ” እንዳሉት ጽዋውን ተጐንጭተው አለፉ። ልቅሶ መቀመጥ የሚገባቸው “እናታቸው፣ ልጃቸው፣ ሚስታቸው፣ ዘውዳቸውና መቃብራቸው” ደግሞ እንደ ዘመኑ ባህል ቅቤ መቀባት የነበረባቸው ይመስለኛል። በደስታ የሚሞትላቸው መሪ መታደል እንደ ቀላል ነገር የሚታይ አይደለማ። እኔስ በእኔው ደረጃና አጋጣሚውን አውቀዋለሁ። ከጉራና ከአጉል መንጠራራት ጋር ካላያችሁብኝ።
አንድ ጊዜ በጦቢያ ላይ በወጣ ጽሑፍ ምክንያት ከከፍተኛው ፍርድ ቤት እመላለስ ነበር። እንዳጋጣሚ ታላቅ እህቴ ማን እንደነገራት ሳላውቅ በመጨረሻው የፍርድ ዕለት ችሎቱ ሲከፈት ከሕዝቡ መሐል ጉብ ብላለች። እህቴን ሳያት “አርፈህ ብትቀመጥስ? አንተ ታማሚ ነህና ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርገህ ተቀመጥ- እኛንም በስጋት ጨረስኸን” ብላ ትጨቀጭቀኛለች ብዬ ጥርሶቼን ሳፉዋጭ ቆየሁ። ወዲያው ተጠራሁና ፍርደ ገምድሉን የእነ ሽመልስ ከማል ውሳኔ ተቀብዬ የተጣለብኝን አሥር ሺህ ብር መቀጮ ጓደኞቼ ከፍለው ወጣሁ። ከመኪናችን ውስጥ ሁለቱ የጦቢያ አርበኞች ደርበውና ጐሹ ነበሩ። እህቴ ዘርትሁን ከእኛው ጋር ትዳበላለች። አሁን ካሁን ጭቅጭቅዋን ትጀምራለች ስል “በሉ ከሰዓት በኋላ ሁለት ላሞች ሸጨ አሥሩን ሺ ብር እሰጣችኋለሁ። በእኔ በኩል ዛሬ የፌስታዬ ቀን ነው። የጀግና እህት ሆኛለሁ። እግዚአብሔር እኔን ጀግና አድርጐ አልፈጠረኝም። ወንድሜ ከወያኔ ጋር ተቋቁሞ…እንዲህ ሲያስከብረኝ ምነዋ አልደሰት! ሁላችንም በዕድሜና በበሽታ ተቀፍድደን ነው እንጂ ኑሮአችን በዱር በሆነ ነበር። አዎን እንደ ደሀ ጨርቅ በመርፌ እየተጠቀጠቅን.. ሽባ ሆነን ጠበቅናቸው” ስትል ሆደ ቡቡ ነኝና እንባዬን ስለቅቀው ሁለቱ ጓደኞቼ ለብዙ ጊዜ የእህቴን ንግግር የመጽናናት መልእክትና የሕዝባችንን ባሮሜትር መለኪያ ያደረጉት ይመስለኛል።( ዛሬ እህቴ ከዘመናት ክስለት በኋላ አርፋለች)
ጌቶቼና እመቤቶቼ፣ ወንድሞቼና እህቶቼ- ልጆቼም! አንድ ውለታ ዋሉልኝ። የአጤ ዮሐንስን አዋጅና ኢትዮጵያን በምን እንደመሰሉአት መላልሳችሁ አንብቡልኝ። መለስ ዜናዊና እሱን ለመሆን የሚፈልጉ ፍጡራን ለመሆኑ ይህን መሆን ሳይሆን ለማንበብ እንኳ እንደሚደነግጡ አይሰማችሁም? ኢትዮጵያ እናት፣ ልጅ፣ ሚስት፣ ዘውድ፣ መቃብር..ሁሉንም ናት። አጤ ዮሐንስን ሠራዊታቸው- የጦር አበጋዞቻቸውና ጭፍራው በሙሉ ያደነቃቸው ፊት ለፊት ፈረሳቸውን እየጋለቡና እንደ አንበሳ እየተጐማለሉ የሚመሩ ጀግና በመሆናቸው ነው። በአዋጁ ላይ እንደተመለከተው ሠራዊታቸውን በማሳሳት መልክ እንኳ ከኋላ አልተከተሉም። በመሐል ሆነው አልተደበቁም። ምሽግ አሠርተው፣ እርድ አስቆፍረው ከዚያ መምራትን አልፈለጉም። እንደ ንጉሥ ዳዊትና እንደ ትልቁ እስክንድር – እንደ አቲላና እንደ ጄንጂስካን ሠራዊታቸውን ከፊት ለፊት የመሩ ልዩ ፍጥረት ነበሩ። The Leadership Secrets of the Rogue Warrior የሚለውን ሪቻርድ ማርኪንጐን አሥርቱ ትእዛዛት ሳነብብ ነበር፤ የመጀመርያውን ትእዛዝ- በእንግሊዝኛው ላስቀምጠው – I am the war lord and the wrathful God of combat and I will always lead you from the front, not the rear በአማርኛው እኔ የጦር መሪና የትግል አምላክ መቅሰፍት ነኝ። ከፊት ለፊት እንጂ ከኋላ ሆኜ አልመራችሁም። እንደማለት ሲሆን በሦስተኛው ትእዛዙ ደግሞ “ እኔ አስቀድሜ የማላደርገውን እንድታደርጉ አልሻም። በዚህም መሠረት እንደኔ ያላችሁ የጦር መኰንኖች ሆናችሁ ትቀረጻላችሁ” ይላል። (የሪቻርድ ማርኪንኮን ሌሎች ትእዛዞችና ለአገር ገድሎ የመሞትን ብፅአት ዛሬ ዘርግፌ ለማለፍ አልሻም። ብቻ ዕድሜውን ይስጠን)
በዚህ ጽሑፍ የመጀመርያው አንቀጽ ላይ የአጤ ዮሐንስ አዋጅና የአገር ምንነት ትርጉም ውብ ሆኖ ቀርቦአል ባይ ነኝ። የንጉሠ ነገሥቱ ቆራጥ ውሳኔ፣ በመሪዎቹና በሕዝቡ መካከል ሊኖር የሚገባው ቁርኝት በግልጽ ታይቶአል። በእኔ እምነት አጤ ዮሐንስ በዚያ ሰዓት የተናገሩት “ቃል ኪዳን” ከኢትዮጵያ ጋር ኢትዮጵያውያን ያካሄዱት ቃለ መሐላ ነበር። ትውልዶች እስከ ምጽአት ድረስ የሚቀባበሉትም መሐላ ነው። በእኔ እምነት ዜግነታቸውን ወደ እንግሊዛዊነት፣ ወደ ጀርመንነት፣ ወደ አሜሪካዊነት የለወጡ እንኳ ሳይቀሩ ኢትዮጵያን በተመለከተ በዚህ ቃል ኪዳን ታስረዋል። እንዲያውም በሚቀጥሉት ወራት ይህንን ቃለ ብፅአት (የአጤ ዮሐንስ የአገር ትርጉም) ቢቻል በየቤታችን በመስተዋት ሰቅለን እንደውዳሴ ማርያም የምናነበንበው መሆን አለበት። የምንኮራበት ቃል- ከአገራችን ጋር ያለንን ኪዳን የምናሳውቅበት ሊሆን ይገባዋል።
የታሪክ ጸሐፊዎች በ19ኛውና በሃያኛው ክፍለ ዘመን የነበሩትን ነገሥታት የሚገመግሙባቸው ሁኔታዎች ሞልተዋል። ወደ ታሪክ ፈጠራና ድርሳነ ደናቁርት የሚያዘነብሉ ደግሞ አየር ዘግነው የሚያወሩት አላቸው፤ የሆነው ሁሉ ሆኖአል። ማናቸውም መሪዎች የኢትዮጵያ መሪዎች ነበሩ። ወደ ውድቀት የወሰዱን ካሉ ታሪክና የአገሪቱ አምላክ ፍትሕ ይሰጣቸዋል። ወደ አኩሪ ድል የመሩንና ያኰሩንን ደግሞ ዛሬ የተፈጠረው ጫጫታና የደንባሮች ሁካታ ሳይሆን ታሪክ ነፃ ያወጣቸዋል። እውነት አርነት ያወጣልና! (የኩባው አብዮታዊ መሪ መፈክርና የትዝታ መጽሐፉ ርእስ History Absolves Me- ታሪክ ይፈርድልኛል የሚል ነው።) በዛሬ ሚዛን- በዛሬው ነፃ ያልወጣና ገና ነፃ መውጣት ባለበት ፍርድ ቤት ሳይሆን በፍትሕ አማልእክት ፍርድ ቤት።
እንደ ማናቸውም የ18ኛና 19ኛ ምዕት ዓመት ነገሥታችን አጤ ዮሐንስ በሩቅ ብዕሲነት (በሰውነታቸው) የሚወቀሱበትና የሚከሰሱበት ውሳኔና አቋም አላቸው። ጄኔራል ናፒየር በአጤ ቴዎድሮስ ላይ ዘመቻ ሲከፍት ከወራሪው ጋር በመቆም፣ የኢትዮጵያን ሙስሊሞች በግድ ክርስትና እንዲነሡ፣ አለዚያ እንዲደመሰሱ አቋም በመውሰድ፣ ከንጉሥ ተክለ ሐይማኖት ጋር በመጋጨታቸው ብቻ ጐጃምን “በማቃጠል”ና የብዙሃኑን ሕዝብ ዓይን በጋለ ብረት በማቃጠል፣ ከአድሚራል ሒወት ጋር በተደረገው ውል ፀረ ኢምፔሪያሊስት አቋም ይዘው ይታገሉ የነበሩትን ደርቡሾች በማስቀየምና በማነሣሣት…..ይወቀሳሉ። አላውቅም የእኔንም አንዱን ቅም አያት ገድለው ይሆናል። ይህን ሁሉ ለአጤ ዮሐንስ ወንጀለኛነት አላነሣም። ላምንም አልፈልግም። ዮሐንስ ለኢትዮጵያ ትርጉም የሰጠ “የኢትዮጵያ ልጅ– የኢትዮጵያ ባል…የኢትዮጵያ ዘውድ ነበር!”
“አጤ ቴዎድሮስ ብዙ ገደለ፣ ጐንደር ተኝታ ያደረችው ቴዎድሮስ የሞተ ዕለት ነው። ወይም እንደ አንዱ እንግሊዛዊ አላን ሙርሔድ አገላለጥ “ A mad dog let loose in Abyssinia” ነበር። “ይኸ ሁሉ ጥራዝ ነጠቆች አዋቂ ለመባል የሚያራግፉት ተራና ተርታ ኦለቲካ ነው። እንዲያውም ጠላቶቻችንና ጥራዝ ነጠቅ ሒሰኞች ቴዎድሮስን ከዚህ በከፋ ሁኔታ ገልጠውታል። እንደ ገና ምኒልክን ጡት ቆራጭ፣ አምስት ሚሊዮን ኦሮሞ የጨፈጨፈ ግፈኛ ተስፋፊ የሚያደርጉ አሉ። በአየሩ ውስጥ ያለው ቁጥር አለማለቁ! በዚህ ደግሞ ወያኔ ከቁጥር በሽታ አለመዳኑ…! ( አንድ ጊዜ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የጻፍኋት መጠነኛ ሽሙጥ ነበረች። ተሳካልኝና። ነገሩ እንዲህ ነበር። የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆነች አንዲት የቀይ መስቀል ሠራተኛ በደርግ ጊዜ ወያኔ ገደልሁ ያለውን ሠራዊት ቁጥር ደመረችና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ጋር እኩል ይሆንባታል። ከዚህ በመነሳት ነበር እኔ “ከሚመጡት ትውልዶች በመዋስ ነው የገደሉት” ያልሁት። አሁን ሳስበው ደግሞ በሽፍትነት ጊዜያቸው ያልቻሉትን አሁን ተሳክቶላቸዋል። እየገደሉ ናቸው። “ኦሮሞዎች ነን” የሚሉትና መለስ እንደሚለው ግን ፋቅ ፋቅ ሲያደርጉአቸው ወይም ጭንብላቸው ሲወልቅ ወያኔዎች የሆኑ ወገኖች ምኒልክ በዚህ መልክ ከትውልዶች ተበድሮ መግደሉን ይነግሩናል። ጌታ በወንጌሉ እነዚህን ቅዱሳንን ለመግደል፣ ለመስቀልና ለመውገር የተነሡ ኅይሎችን “የሚያደርጉትን አያውቁምና..ማራቸው” ይላል። ከምሕረቱ ተጠቃሚዎች ሊሆኑ ከቻሉ! አለዚያ ግን እነዚህ ነገሥታት ሁሉም እንደ ዘመናቸውና እንደ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች- ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግና ጠላቶችዋን በመመከት ረገድ ከአገሪቱና ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን የነበራቸው መሪዎች ናቸው። ጣባቦቹ የአድዋ መኳንንት አጤ ዮሐንስ የተወለዱት በተምቤን በመሆኑ ምን እያደረጉ እንደሆነ እየታዘብን ነው።
ባለፉት ሃያ ሦስት ዓመታት ከዚህ ልክፍትና በሽታ ያልተላቀቁት የሽብር ሪፐብሊክ ካድሬዎች የአድዋን ጦርነት ድል ያለ ምኒልክና ያለ ጣይቱ ለማክበር ሲሩዋሩዋጡ ነበር። ስሙን ለመጥቀስ ያልፈቀደልኝ አንድ የታሪክ ምሁር ይህንን “Hamlet Minus the prince” ብሎኛል። ከመተማ ጦርነት ዮሐንስን ማስቀረት ማለት ነው። ነገሥታቱ የሚገባቸውን ክብር መነፈግ፣ ለአገር ያበረከቱትን መስዋዕትነት መቀማት እንደሌለባቸው ጠንካራ እምነት የነበራቸው ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ነበሩ። በፖለቲካል ኢኮኖሚ መጽሐፋቸውና በአስተዳደር እውቀታቸው ተደናቂ የነበሩት ገብረሕይወት ባይከዳኝ በአንድ ወቅት በፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ “አጤ ምኒልክ” መጽሐፍ ክፉኛ ተከፍተው የጻፉትን አሳብ ማንሳት ደግና አስፈላጊ ይመስለኛል። አጭር ናት። “ምኒልክን ለማሞገስ ዮሐንስን ማንኳሰስ ያስፈልጋል?” ነበር ያሉት። እውነታቸውን ነው። ነጋድራስ አፈወርቅ በእቴጌ ጣይቱ ውሳኔ ከአዲስ አበባ ርቀው ከቶውንም በኤርትራ መኖር ይዘው ነበርና ያንን መጽሐፍ የጻፉት (ብዙ ቁም ነገርና ታሪክ ቢኖርበትም) እቴጌይቱን መታረቂያ አድርገው ነው እየተባለ ይነገር ነበር። ለእኛ ዘመን ትምህርት ሊሆነን የሚገባው- በዘመነ ግሉባላይዜሽንና- ስለ ግሥጋሴና ነገ ከዛሬ መሻል አለበት – ብርሃንም ከሩቁ አድማስ ባሻገር መታየት አለበት- ለሚለው ትውልድ ፋይዳ ሊኖረው የሚገባው ነገር አለ። እነዚያ የወቅቱን ፈተና በወቅቱ ስልትና ብልሃት ተወጥተውታል። የዚያን ዘመን ፈተና ለመረዳት ደግሞ ሕሊናን ከወቅቱ ጋር ማዛመድን ይጠይቃል። ይህን ካልሁ በኋላ ከአንባቢው ጋር እንዲቀርልኝ የምሻው አንድ ጉዳይ አለ። አጤ ዮሐንስ በደሙ፣ በአጥንቱና በነፍሱ ኢትዮጵያን የቀደሰ መሪ ነው። አጤ ምኒልክ በአንድ አጭር የታሪክ ዘመን ግዙፉን ተግባሮችን የፈጸመ፣ የአገሩን አንድነት የመሠረተ፣ ዓለምን ያስደነቀ- የጥቁርን ሕዝብ መንፈስ ከፍ ከፍ ያደረገ – በሺህ ዓመት ጊዜ ውስጥ ምትክ የማይገኝለት መሪ ነበር። ኢትዮጵያን ባረከ- ኢትዮጵያውያንን አኮራ- ጥቁር ሕዝቦችን ሰው አሰኘ። በዚህ መልክ ነበር በኢትዮጵያ ሰማያት ላይ የታየው ኮከብ ያለፈው። አጤ ዮሐንስ ደግሞ ኢትዮጵያን ለመውረርና የዓባይን ምንጭ ለመቆጣጠር ተደፋፍረው የመጡትን ግብፆች በጉንደት፣ በጉዳጉዲ፣ በጉራዕ ድባቅ የመታ ታላቅ መሪ ነበር።
ዮሐንስ በወደቀበት ሥፍራ ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ኖረውበታል። ይኖሩበታል። በጉበኝነት መልክ እየሄዱ ሳያውቁት ተሳልመውታል። አንድ ሰሞን (በቀዳማዊ ኅይለ ሥላሴ ዘመን) የሱዳን መንግሥት የባለቤትነት ጥያቄ አቀረበ ሲባል ከተወሰኑ የፓርላማ አባላት ጋር ወደዚያ አምርቼ ነበር። በሑመራም፣ በመተማም ወዘተ ከወልቃይት ጠገዴ..እስከ ጸለምት..ድረስ በመኪና ሄደናል። እግር እስከ ወሰደ ድረስ ኳትነናል። የሰው ውበት፣ የመሬት ውበት፣ የተራራ ውበት…ሊገለጥ አይችልም። የንጉሠ ነገሥቱ መኰንኖች፣ ሚኒስትሮች ወዘተ የተቀራመቱትን ጋሻ መሬት መግለጫ ሁሉ ሰምተናል።
ጓንዴና ሰነኔ፣ ከዚያም ወዲህ የሰው ነፍስ የመሰለ ጠመንጃ ከጐናቸው የለጠፉ፣ በአንዱ ጐናቸው ደግሞ ስንቃቸውን የጣፉ የአሥርና የአሥራ አንድ ዓመት ጉብሎች ታገኛላችሁ። እነዚህ ገና ጡጦ ጥለው ወደ አገር ጠባቂነት የተላለፉ ልጆች ስለ መሣሪያ አጠቃቀም ሳይቀር ሲተነትኑላችሁ ይቺ አገር በየትውልዱ የጠላትን ጉሮሮ እያነቀ የሚጥል ጀግና ረሃብ እንደሌላት ትረዳላችሁ። አንዱን ልጅ “ሱዳን ጦር ይዛ ብትመጣብህ ልትወጋት ትችላለህ?” ብዬ ሰነፍ ጥያቄ አቀረብሁለት። “ይህን መሣሪያ ለለበጣ የያዝን ይመስላችኋል? ጌታው ይስሙኝ! እዚህ ከብት የምናቆም ልጆች እንበቃለታለን። ብቻ የመንግሥት ጦር አይምጣብን። ነገር ይበላሽብናል። ሱዳንን እናውቃታለን። ታውቀናለችም” አለኝ። በውቅቱ ..የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጠኛ የነበረው ወንድም-አከል ጓደኛዬ መርስዔ ኅዘን አበበ ይህን አሳብ ለብዙ ጊዜ ለብዙ ሰው አጫውቶአል።
በትውልድ ከተመካህ በዚያ ዓይነቱ አገር የትውልዶች ሃላፊነት ምን እንደ ሆነ እየተረዱ ያደጉ..በትውልድ መመካት ምን ማለት እንደሆነ ይህ መሬት ከእኛ በፊት የሚያስከብሩት ሰዎች እንደነበሩና ጥለው የወደቁትም ምንኛ እንደቀደሱት የሚረዳ ትውልድ ዝግጅት ስትረዳ ነው። ወጣቶቹ ገና ከሕፃንነታቸው ጀምረው በዚያ አካባቢ ሲገጥመን የኖረውን ችግር ከአባቶቻቸው እግር ሥር ተቀምጠው ሰምተውታል። ለምሳሌ አጤ ዮሐንስ የገጠማቸውን ችግር ሁሉ… የጦርነቱን ሁኔታ ..ወዘተ ለተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ የዮሐንስ ዘመን የታሪክ ምሁር ለነበረው ለዓለሜ እሸቴ፣ የዮሐንስን ዘመን ታሪክ ባይጽፉትም ሲያጫውቱአችሁ ለሚያፈዝዙአችሁ ለጄኔራል አሳይያስ ገብረሥላሴ…የሚያስተምሩ ናቸው። ከእንግዲህ ወዲያ የዚህ ዓይነት ታጋይ ትውልድ ልናፈራ እንችላለን? እጆቻችንን ወደ ሰማይ እንርጭ!
ከዚህ ወግ ለመውጣት እፈልጋለሁ። ከመርስዔ ኀዘን (ነፍሱን ይባርካትና) ጋር ስንነጋገር እንደጋጣሚ ሁለታችንም መሬቱ ልዩ ስሜት ቀሰቀሰብንና “ይህ አካባቢ ታጥሮ የዮሐንስንና አብረውት የቆሙትን- የተሰየፉትንና ሰማዕትነታቸው የተረጋገጠው ያልታወቁ ጀግኖች- መዘከር እንዲሆን አሳቦች ብናቀርብስ?” ተባባልን። ሌላው አሳብ ደግሞ በትላላቅ ሆሄያት “ይኽ ሥፍራ የተቀደሰና የተከበረ ሥፍራ ነው። የምትረግጡት መሬት ወደ አፈርነት የተሸጋገሩ ንጉሣችንና ሠራዊታችን ነው።” የሚል አሳብም ተለዋወጥን። ብቻዬን ቀረሁ እንዴ? በኤርትራና በኦጋዴን ያገኘኋቸው ዛሬም በሕይወት የሚገኙ መኰንኖችና ስማቸውን ያልያዝሁላቸው ኢትዮጵያውያን አሉ። አሉ፣ አሉ። ሃሌ ሉያ! ምን ያደርጋል የትዝታን ጓዝ ተሸክሞ መኖር?
አንዲት ነጥብ ላክልበት መሰለኝ። የሱዳኖቹ የመሬት ጥያቄ የመጣው በ1963 አካባቢ ይመስለኛል። ያን ጊዜም የፓርላማ አባላት ( በተለይ የጐንደር ክፍለ ሀገር ተወካዮች) ሱዳኖች ንጉሠ ነገሥቱን ሊያሳስቱ ነው ተብሎ ሲወራ በግልጽ ተፋለሙአቸው ተብሎ ተወራ። በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ የሱዳን መንግሥት የኤርትራን ወንበዴዎች (ዛሬም ያው ናቸው) መርዳቱ ጣልቃ ገብነትና የጉርብትናን መንፈስ የሚያደፈርስ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትንና የአፍሪካ አንድነትን ቻርተሮች የሚጻረር ነው የሚል አቋም ነበር። በጉርብትና የሚኖሩ አገሮች በየድንበሩ ላይ ካሉ ብሔረሰቦች ጋር የፖለቲካ ጨዋታ ቢጫወቱ- ወይም ለወደፊት ችግር ማስተንፈሻ ቢያደርጉ ክፉ አይደለም። የሞራል ጣጣም የለበትም። ታዲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን – ቀልጣፋውና ወሳኙ ከተማ ይፍሩ “በመስተዋት ቤት የሚኖሩ ወደ ሌሎች ደንጊያ በመወርወር የመጀመርያዎቹ መሆን የለባቸውም” የሚል መግለጫ ሰጡ። Those who live in glass houses should not be the first to throw stones to others ነበር የተባለው።
አዎን ወዲያው በዮሴፍ ላጐ የሚመራ የደቡብ ሱዳን ንቅናቄ (አናንያ ሁለት) ሲመሠረት ( በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድጋፍ) በወቅቱ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ሰዲቅ ማኅዲ (ከላይ የጠቀስነው ማኀዲ የልጅ ልጅ) ሮጦ መጥቶ ከጃንሆይ እግር ሥር ወደቀ የሚባል ወሬ ተወራ። “እርስዎ የአፍሪካ አባትና ሱዳንም አገርዎ አይደለችም ወይ?” በማለት ሲማጸናቸው የአናንያ ሁለት መሪ ጆሴፍ ላጐንና ሱዳንን አስታራቂ ሆኑ። በነገራችን ላይ ብዙም ሳይቆይ ነበር ጄኔራል ጃፋር ኒመሪ በመፈንቅለ መንግስት አማካይነት ሥልጣን የያዙት።
ሱዳን ከዚያ በኋላ የመሬት ጥያቄ ያቀረበችበትን ጊዜ ሁኔታ አላስታውስም። ታሪክ በዕዳና በቅጣት መልክ ከጣለብን ከእነ ኅይለማርያም- አንደበት የምንሰማው ካልሆነ በቀር! በዚያ ሰሞን የቀድሞ መሪያችን ኮሎኦኔል መንግሥቱ በኢሳት ቴሌቪዥንና ራዲዮ ተጠይቀው መልስ ሰጥተውበታል። ምን ሲደረግ? በሌላ ሌላ (በአብዛኛው በፈጣን ውሳኔያቸው) መንግሥቱን ከሌሎች ሰዎች ጋር ላማቸው እችላለሁ። የኢትዮጵያን መሬት የሚጠይቅ አሳብን በማስተናገድ ረገድ መጽሐፉ አይጠቅሳቸውም። በነገራችን ላይ በ17ቱ ዓመት የደርግ አመራር እኔም እንዳቅሜ ኢትዮጵያ ከጐረቤት አገሮች ጋር ያላትን ፖለቲካ፣ የድንበር ጥያቄና ሌሎች አለኝታዎች በሚመለከተው ኮሚሽን በአባልነት ሠርቻለሁ። ከሱዳን ጋር በርከት ላሉ ዓመታት በፖለቲካ ባላንጣነት መቆየታችን ይታወሳል። ያንን መጋረጃ ለመቅደድ በተደረገው ሙከራ ካርቱም ላይ ይኸው ኮሚሽን ከሱዳን አቻው ጋር በፍቅር ተመርቶ ባስገኘው ውጤት መሠረት ሁለቱ መሪዎቻችንን ለማቀራረብ ተችሎአል። እንዲያውም የኮሚሽኑ አባላት በዶክተር ፈለቀ ገድለ ጊዮርጊስ- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በሱዳን አቻቸው አማካይነት ከፕሬዚዳንት ኑሜሪ ጋር ስንገናኝ ስለ ግንኙነቱ መታደስ ከእኛ የበለጠ ሱዳኖቹ መደሰታቸውን ተረድተነዋል። ኑሜሪ እንደ ቀልድ አድርገው “ምሥጢር ልንገራችሁ። ከእናንተ ጋር ሆነን ሻዕቢያዎችን እንደምወጋቸው ቃል እገባለሁ” ማለታቸውን አስታውሳለሁ። (በፕሬዝዳንት ኑመሪ ላይ ከ16 የሚበልጡ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ተደርገው ነበር። ከ12 በማያንሱት የሻዕቢያ ተሳትፎ ነበረበት)
ፕሬዚዳንት ኑሜሪ በፈንታቸው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ (አሁንም የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባል ሆኘ) ከመሪያችን ጋር በሰፊው ተነጋግረዋል። እንዲያውም የሁለቱ አገሮች ልዑካን በተገኙበት ጓድ መንግሥቱ “ወንድሜ ፕሬዚዳንት ኑሜሪ ምንም እንኳ ሕመም የሚሰማቸው ቢሆንም ያለ ማቋረጥ አሥራ ሰባት ሰዓት ብቻችንን ተነጋግረናል” ማለታቸውን አልዘነጋውም። ከሱዳን ጋር የመሬት ጥያቄ ቢኖር ባለቤት የሌለው አገር ባገኙበትና ሱዳንን ተገን አድርገው ሲወጉን ለነበረው ውለታው መሬት ከሆነ ያ ሌላ ጉዳይ ነው። የመሬት ጥያቄ ከተነሣ ኢትዮጵያ የተወሰደባትን ( በእንግሊዞች፣ በግብፆች፣ በራስ ደበብና በደጃች ገብረሥላሴ ተዋናይነት) ከሰላን፣ ገዳሪፍንና ከኤርትራም የተሰነይን ባለቤትነት ልታነሣ ትችላለች። የሚያሳዝነው ኢትዮጵያ ልጅ አላወጣችም- በመንግሥት ሰፈር።
ለእኛ ለዛሬዋ የኢትዮጵያ ትውልድ እንደ ሐውልት የጐላ ቅርስ የሚሆነን የንጉሠ ነገሥቱ ከአገሩ ድንበር ላይ ከአያሌ መኳንንቱ ጋር መውደቁ ነው። ለእኛ ለዛሬ የኢትዮጵያ ልጆች ውርሳችንና ቅርሳችን ሆኖ አላስተኛ ሊለን የሚገባው ያንን ዳርድንበር በማስከበር ሒደት ሺህ በሺህ ወገኖቻችን የጠላትን ጉርንቦ እየያዙ፣ እየጣሉ መውደቅ ነው። ጃንሆይ አጤ ዮሐንስ በጠላት ጥይት ከወደቁ በኋላ እንኳ “አስከሬናቸውን” አናስነካም በማለት የተሰውት (ከመኳንንቱ) ትልቁ ራስ አርአያ፣ ቢተወደድ ገብረ መስቀል፣ ደጃች ተድላ፣ ብላታ ገብረማርያም፣ መምህር ወልደ አረጋዊ፣ መምህር ክንፈ ኪሩብ፣ ቄስ ገበዝ ሰላማ…ይገኙበታል። ሌሎች ደግሞ- አትጠራጠሩ- መለከት ያልተነፋላቸው፣ ምንም ያልተዘመረላቸው የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ናቸው። The Unknown Ethiopian Soldiers የሚባሉቱ
አዎን የትናንቱ ለዛሬ፣ የዛሬው ለነገ የሚያወርሰው ይህን መሳዩ የታሪክ ሰንሰለት በምንም ምክንያትና አጋጣሚ መቋረጥ የለበትም። ይህ የታሪክ ሰንሰለት የተበጠሰ ዕለት ሕልውና ዋስትና ያጣል። ይህ ሒደት ለብዙ ምዕት ዓመታት በኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ባሕርይ ላይ ሲታይና ሲያንፀባርቅ ኖሮአል። እንዲህ ያለ ብሔራዊ ፋይዳ ደግሞ ተመልካችን ሳይቀር “የማን ልጅ ነህ? የየትኛው አገር ልጅ ነህ?” የሚያሰኝ መሆኑን ከአሜሪካ ሕገ መንግሥት አርቃቂ ምሁራን ዋነኛው ቤንጃሚን ፍራንክሊን ያብራራል- በአጭሩ። ከተወሰኑ ሰዎች ጋር ሆኖ በፓሪስ ከተማ ሲወያይ አገርን፣ ብሔራዊ ግዴታን፣ ትግልንና የትውልድ ኅላፊነትን በተመለከተ መግለጫ ሲሰጥ አንዱ፥ “እናት አገርህ ማናት?” ሲለው ፍራንክሊን “እናቴ አሜሪካ ናት” ይለዋል። ሰውዬው ሲመልስ “ለአዲሲቱ አገርህ የሺህ ዓመታት ዕድሜ ሰጥተሃታል” እንዳለው አንብቤአለሁ። ጥንታዊት ኢትዮጵያ አዲስ አገር መሆን እንዳለባት አምናለሁ። የሺህ ዓመታት ታሪክዋ እንዳይዘነጋ የምናደርገው – በቃልም በተግባርም ነው።
አገር ተደፈረ፣ አንድነታችን ተፈታ- በቁም ተሸጥን እያልን…በጫማ ተይዞ የሚሄድ አፈር ሥስት እንዳልነበረን ሁሉ… በእጅ አዙር ቅኝ ገዥነት የተከሰቱትን የወደፊት የኢትዮጵያ ገዢዎች ይኸው ክመሐላችን እያየናቸው ነው። እያቀበጥንና እያፋፋናቸውም ነው። የመሬት ቅርምቱን ጉዳይ በአኅዝ አስደግፈው፣ ከፖለቲካል ኢኮኖሚ ጋር አያይዘው- በሰፊው ሲያብራሩልን የቆዩትን እነ ዶክተር ዓለማየሁ ገብረማርያምን፣ ዶክተር ጌታቸው በጋሻውን፣ ፈቃደ ሸዋቀናን እንደገና እንድታነብቡአቸው ወደነሱ እመራችኋለሁ። በእኔ በኩል ግን እንዲያው የአገሬ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ ኢንቬስተር ከውድድር ውጭ የመሆኑን ምሥጢር ደኅና አድርጐ የሚያጫውተን ምሁር እየፈለግሁ ነው። የማያልቅ ቂል ጥያቄ ሞልቶኛል።
ኢትዮጵያን ቆራርጠን …አንዱን በአዋሽ፣ ሌላውን በአፋር ክልል ሦስተኛውን በጋምቤላ…የምሸጥላቸው ነጋዴዎች- ፈረንጁ- አረቡ- ሕንዱ- ፓኪስታኑ…ከመቶ ዓመት በኋላ “ኢትዮጵያን መጀመሪያ የገዛኋት እኔ ነኝ..እኔ ነኝ” በመባባል ርስበርሳቸው ጦርነት እንዳያበቅሉ የሻጩ (ወያኔ) ሚና ምን ሊሆን ይችል ይሆን? አይ ቴዎድሮስ አንድ ፈረንጅ በመጫሚያው ላይ ይዞት ለሚሄደው አፈር እንዲያ መጨነቅ። አይ ዮሐንስ ሱዳን እንዲህ አንዲት ቀለህ ሳይተኩስ ለሚወርሰው መሬት “ቅዱስ ደምህን” ማፍሰስህ! (ከዚህ ላይ ባቋርጥ የሚከበኝ ባለቅኔ አለ? )
ከ1972 እ.አ.አ ጀምሮ እስከ ደራሲ መንግሥቱ ኀይለማርያም ስደት ድረስ በዓመት አንዴም ሁለቴም በመመላለስና ወራትም በመጨማመር ሕንድን አውቃታለሁ። 1972 ሃያ አምስተኛው የነፃነት በዓላቸው መታሰቢያ ነበር። በዚያ በር ገባሁና የ Institute of Mass Communications የማያቋርጥ ጐብኝ ሆንሁ። Hindustan Times እና All India Radio, Times of India ባልደረባ መሰልሁ። በየዓመቱ ወይም በየስድስት ወሩ የሚጠራው Financial Writers አባልም እየተባልሁ እጋበዝ ነበር። ለነገሩ ስለ ፋይናንስ ስለመጻፍ ችሎታውም ዝንባሌውም አልነበረኝም። ብቻ ሕንድን ከዳር እስከዳር ለማወቅ ቻልሁ።
በመጀመሪያ ሕንድን ስጐበኝ የነበረው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥዕሉ አስደንጋጭ ነበር። ከትልልቆቹ እንደ ሒንዱስታን አቶሚክ ሪሰርች ጣቢያ በር ላይ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ቤት አልባ ደሆች ታያላችሁ። በአግራ በሚገኘው ዝነኛው ታጅ መሐል ግቢ ሌሎች ሺህ በሺህ ደሆች ተረፍርፈው ታያላችሁ። ወደ ካልካታ ስትሄዱ ጐህ ሲቀድድ ጀምሮ ለዓይን ድንብዝብዝ እስኪል ድረስ በፈረስ ምትክ ጋሪ የሚጐትት ሰው ነው። (ሪክሾ ይባላል) በእግራችሁ ስትሄዱ ያም ሩዝ መግዣ ይለምናችኋል። ይኸም አንዲት ቂጣ (ፑሪ) መግዣ አንድ ሩፒ ጣል አድርጉልኝ ይላል። ሕንድ ይህን ሁሉ ችግር ተቋቁማና ድል አድርጋ ትናንት ተራ ሸርፓ (ኩሊ) የነበሩ ሰዎች ቢሊየነሮች መሆናቸው ያስደስታል። ምሳሌነታቸውም ግሩም ነው። ሌላ የሚደንቅ ነገር ደግሞ አለ። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ነፃነትዋ ከ67 ዓመት የማይበልጠው ሕንድ ከኢትዮጵያ የኅብረት ቅኝ ገዥዎች መሐል አንድዋ መሆንዋ ነው። አንድ ጓደኛችን እንደሚለው የአሰብ ወደብ የኢጣልያ ቅኝ ግዛት የሆነው በዚሁ አዝጋሚ ርምጃ ነው። ጁሴፔ ሳፒቶ ትንሽ መሬት ከራሒቶ ባላባቶች ይገዛል። ሩባቲኖ ለተባለ የመርከብ ኩባንያ ያዛውረዋል። ያ በፈንታው ለኢጣልያ መንግሥት ባለቤትነት ያስተላልፈዋል። ባለቤትዋ ኢትዮጵያ እያለች ለኤርትራ ይሰጣል። አባ መስጠት ወያኔ!
ዝነኛው የኢትዮጵያ ማዕድናት ባለቤትና የአዲስ አበባን “ዓይን የሆኑ ቦታዎች” ከልሎ የያዘው የሳዑዲ ነጋዴስ? ሌላው ግለሰብ (ለጊዜው) የኢትዮጵያ ቅኝ ገዥና- እንደ ጁሴፔ ሳፔቶ ቀስ ብሎ ለሳዑዲዎች የሚያስረክባት ነው። የታሪክ መቅድም አድርጋችሁ እዩልኝ። አንዳንድ የአሜሪካ ጋዜጦችና ከመስከረም አንዱ የአሜሪካ ትዊን ታወርስ አደጋ በኋላ በታተሙ መጻሕፍት ጭምር ስሙ የተነሳው ግለሰብ (በአሸባሪዎች ገንዘብ አቀባባይነት) ከእኛው ባንኮች እየተበደረ በመግዛት ያጠራቸው ብዙ ብጥስጣሽ መሬቶች አሉ። በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በእስራኤልና በሳዑዲ፣ በግብፅና በኢትዮጵያ ፖለቲካ የበሰለ ትንተና የሚሰጥና መልካም እይታ አለው የሚባለው ምሁር ሐጋይ ኤርሊሽ ነው። ይህ የታሪክና የፖለቲካ ሊቅ የተመለከተውና የደመደመው ጉዳይ አለ። Islam, Chrstianity and Politics entwined በሚለው መጽሐፉ አንደኛው ምዕራፍ ላይ ከአንድ ግለሰብ ጋር ይወያያል። ስለ ሸራተን ሆቴል ፋይዳ፣ ግለሰቡ ምንም ላይሰራባቸው አጥሮ ስለያዛቸው ቦታዎች ይጠይቀዋል። ፕሮፌሰር ሐጋይ እንደሚነግረን እነዚህ ሥፍራዎች የተያዙትና የሚጠብቁት ሦስተኛውን ሒጂራ ነው፤ የመጀመርያው ሒጂራ ሰማንያ አራት የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች ወደ አክሱም የተሰደዱበት ነው። ሁለተኛው ሒጂራ እንዲሁ የነቢዩ ተከታዮች የሜካ ስደት (ሒጂራ) ነው። ሦስተኛው ሒጂራ ደግሞ የዋሐቢ መሪዎች የሆኑት የሳዑዲ መሳፍንትና መኳንንት አንዳች አደጋ ሲያንዣብብባቸው የሚጠጉበት ሥፍራ ነው። ኢትዮጵያ ለሦስተኛው ሒጂራ ዝግጁ ነች። ( የነቢዩ ተከታዮች በአሁኑ ዘመን ስደት ይጠብቃቸዋል ማለት ሳይሆን፣ የነገሥታቱና የመሳፍንቱ የግንባር ሰው የሆነውና በሞራል ድቀት፣ በኢትዮጵያ ዘረፋ- የወያኔ መሳፍንት የንቅዘት መምህር በመሆን ስሙ የሚጠቀሰው ግለሰብ ነው። ይህን ተልእኮ በተመለከተ የሐጋይ መጽሐፍ ጥሩ ብርሃን ይፈነጥቃል። በቅርብ ጊዜ በሰፊው በተግባር በሚረጋገጠው የወያኔ ፕሮጄክት መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሦስትና አራት ፎቅ ቤት ለመሥራት የማይችሉ ሁሉ ከከተማው እንዲወጡ ይደረጋል። ድህነታቸው እንደ ሙሴ ለምፃሞች ከከተማ ያባርራቸዋል። ከተማይቱ ለአላሙዲ እንግዶች አትበቃምኮ! በቁማችሁ የረገጣችሁት መሬት ሲሸጥ ተመልካች ስትሆኑ፣ ልጆቻችሁ የሚማሩበትና የሚያድጉበት ሥፍራ አጥተው ሲንቀዋለሉ፣ ለእናንተ የሚሆን ከተማ የለንም ተብላችሁ አውጥተው ሲጥሉአችሁ- ሠርታችሁ ለመብላትና ሞትንም በወጉ ለመጠበቅ በማትችሉበት አዙሪት ውስጥ ስትወድቁ..
በወረቀትና በስክሪፕቶ አማካይነት ብዙ ሮሮ አውጥታችሁ በመጻፍ ትንሽ መገላገል ትችሉ ይሆናል። ለሰው ያካፈሉት አሳብ በአየር ላይ እንዳልቀረ በመገመት ግማሽ ጭንቀታችሁን በመገላገል ብቻ ልትደሰቱ ትችሉ ይሆናል። በቁም መሸጠን የመሰለ ውርደት ግን የማይሽር ጠባሳ፣ አንድዶና አክስሎ የሚጨርስ ካንሰር ነው። በእኔማ በኩል ባናነሳው ይሻላል። ምክንያቱም- ጥቂቶች ብዙሃንን አስተኝተው የሚገርፉበት፣ ንዑሳን እልፍ አእላፍ የሆኑ ዜጐችን ለባርነት የሚዳርጉበት፣ አንድ ግለሰብ ሃያና ሠላሳ ሚሊዮን ሕዝብ የሚነዳበት ተአምር አልታይህ ይለኛል። በባሕላችን አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው እያለቀሱ ወደ ቤት ሲመለሱ ራሳቸው የተደፈሩ እየመሰላቸው የሚወስዱትን ርምጃ ሁሉ አሰላስላለሁ። እናንተም ምን ይሁን? በሚል ጥያቄ እንደምታጣድፉኝ እገምታለሁ። የድሮ መሪያችን “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!” በማለት የጀመሩት ዘመቻ ያን ጊዜ አልሠራም። በምንም ስም ይጠራ የኢትዮጵያ ሕዝብ በገዥዎቹ አማካይነት የታወጀበትን ጦርነት መጀመሪያ መገንዘብ አለበት። ሁለተኛ ለጦርነት በጦርነት መዘጋጀት ያስፈልገዋል። ሦስተኛ ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር የሚለው ቋንቋ ነጃሳ ከሆነ ሌላ እናምጣ። በቁምህ ተሸጠሃል። በቁምህ ትነዳለህ፣ በቁምህ ትሰየፋለህና ነፍስህንና የእናት አገርህን ሕይወት ለመታደግ ዮሐንስን ተከተል። የባለሙያው ሙያ ለትግሉ ይዋል። የብዕረኛው ቃላት ይህን አገር መገለባበጥ ካልቻሉ ከነፍሱ የተቆረጡ አይደሉም። ሠዓሊው ይህን ትግል በሸራው ላይ ሲስል ይቺ መሬት ካልተናወጠች ሥዕሉን ይተወው። የኪነቱ ሰው የትግሉን ዐውድ እንደ እሳተ ጐመራ ካላደበላለቀው በአፍንጫዬ ይውጣ! ከማይክራፎን ጀርባ የሚቀመጠው፣ ለማታ ዜና የሚሯሯጠው ጋዜጠኛ የኢትዮጵያን ሰማያትና ምድር ካልገለባበጠ ሙያነቱ ይቅርብን! በአንድ ማብራሪያ እንሰነባበት።
ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ የጦር ኀይሎች ኤታማጆር ሹም በነበሩበት ጊዜ በተደጋጋሚ አሥመራ ላይ እንገናኝ ነበር። ከዚህ ቀደም አንሥቼው ከሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ለማያስታውሱት ይጠቅም እንደሆነ ነው የምደግመው። በቃኘው ሰፈር ግቢ ቆመን ስንጨዋወት “ጸጋዬ ለመሆኑ ይኸን ጦርነት ለማሸነፍ ስንት ጊዜ የሚፈጅ ይመስልሃል?” ይሉኛል። የቪየትናምን፣ የደቡብ አፍሪካን፣ የቻይናን..ጦርነቶች በማንሳት መልስ ለመስጠት ተንደረደርሁ። “እሱን ተወው! ይኸ ማርክሳዊ ምናምን አንተንም ያበላሸህ ይመስለኛል። በእኔ እምነት እዚህ የተመደበው እያንዳንዱ ወታደር ለአንድ ቀን – ለሃያ አራት ሰዓት- ቆሞ ቢዋጋ አንድ ጠላት አይኖርም” አሉኝ። በወያኔ ተቃጠልሁ፣ ከሰልሁ- በገንሁ የሚል አሥር ሺህ ሰው ቆሞ ቢዋጋ ኢትዮጵያ የማትድንበት ምክንያት የለም! ዳግመኛ በጦርነት አልምጣባችሁ? ደኅና ሁኑ!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ውድ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች "እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በዓል አደረሳችሁ!" ጌታቸው ወልዩ (ከሜክሲኮ ባህረ-ሰላጤ)

1 Comment

  1. What an interesting and brilliant man please keep writting we the young people have a lot from you and your likes and please make sure to send your article to different websites so that lots of readers will learn about their country please do not only send your articles to ethiomedia, you should even send your articles to Ethiopa thanks a lot and I would rather be happy if you use your real name vis vis your pen name
    Many thanks and I also expect you to write about the ongoing hate campaign against the poor Amharas by OLFi cadres and hate writer OLF historians claiming Menilik killed 5 million Oromos for their grand plan of Genocide

    You should also write about the infamous Arteran Hate Writter TESFAYE GEbre EBAB who took your respected position as the head of Ethiopian Printing Agency btw sir I don’t know if you realized this TESFAYE intentionally praises people who have good writting skills and powerful BIer so that they will not attack and write about him so far he managed it and every Writter he praised including you about this evil man who is working hard to encite hate among AMHARA and OROMOS so that ARTERA will be fine with a weak and divided Ethiopia

    This evil guy(tesfaye) has been successful in making the good writers not to say anything about him except the exceptionally courageous Temesgen Dessalegne who understood why he is doing that

Comments are closed.

Share