April 21, 2014
16 mins read

[የፋሲካ ወግ] ቴሌፎኑ ‘ለግዜው’ ጥሪ አይቀበልም – ክንፉ አሰፋ (ጋዜጠኛ)

ክንፉ አሰፋ

“የደወሉላቸው ደምበኛ ለግዜው ጥሪ አይቀበሉም።…” የምትለዋ አሰልቺ የቴሌ መልእክት ያላጋጠመው ቢኖር ወደ ኢትዮጵያ ስልክ ደውሎ የማያውቅ ሰው ብቻ መሆን አለበት። ኮ/ል መንግስቱ ሃይለማርያም ወደ ቀድሞ ወዳጆቻቸው መደዋወል ጀመሩና በመሃል ተስፋ ቆረጡ አሉ። አስር ለሚያህሉ አርሶአደሮች እና የሰራዊቱ አባላት ዘንድ ደውለው አልተሳካለቸውም። ለሁሉም ጥሪ ያገኙት ምላሽ “የደወሉላቸው ደምበኛ ለግዜው ጥሪ አይቀበሉም።” የሚል ሲሆንባቸው ራሳቸውን ነቀነቁ። ሰው ሁሉ የጨከነባቸው መሰላቸው። እንዲህም አሉ። “የሃገሬ ሰው እንኳን የስልክ ጥሪ፤ የእናት ሃገር ጥሪስ መች ተቀበለ።”

ለአመታት በተከታታይ በሁለት ድጅት እያደገች ያለች ሃገር የስልክ መስመር ችግር ይገጥማታል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ችግሩን በደንብ ላልተረዳው፣ ሰው የሞባይል ስልክ የሚገዛው እንዲሁ ይዞ ለመታየት ነው ያስብል ይሆናል። ይህ አባባል በከፊል ትክክል ነው። ዘመናዊ ስልክ በመያዝ ለላንቲካነት ብቻ የሚጠቀሙበት ሰዎች አይጠፉም። የቻይናው ቀፎ ከሞዴል አርሶ አደሮች አልፎ ተራው አርሶ-አደር እጅ ላይም ገብቷል። አብዛኞቹ ግን ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን አይጠቀሙበትም። ለዚህም ይመስላል በርካታ ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚይዙ ሰዎች እንዲሁ ለእይታ እና ለላንቲካ ብቻ የሚመስላቸው። አገልግሎቱን በተመለከተ ግን 99 በመቶ የሚሆነው ችግር የመዋቅር ችግር ነው።

ለዓውዳመቱ ወደ ኢትዮጵያ ስልክ የደወላችሁ ካላችሁ፤ ይህ ነገር እንደገጠማችሁ እርግጥ ነው። ዘንድሮ ደግሞ ቴሌ ከፍቷል። የሞባይሉ መስመርማ እንደ አይን እልም ብሎ ነው የጠፋው። ከበርካታ ሙከራ በኋላ መስመር ያገኘ ሰው ካለ በደስታ ይዘልላል። የተቀባዩም ስልክ ካቃጨለ ተዓምር ነው የሚባለው። ከርማ ብቅ እንደምትለው የአዲስ አበባ መብራት… ልክ እንደ ቧንቧ ውሃ፤ ስልኳም “መጣች – መጣች!” ብሎ መጨፈሩ አይቀርም።

(በመከራ መስመር ሲገኝ እንዲህ ያስደስታል)
[የፋሲካ ወግ] ቴሌፎኑ 'ለግዜው' ጥሪ አይቀበልም - ክንፉ አሰፋ (ጋዜጠኛ) 1

“እንኳን አደረሳችሁ!” ለማለት እኔም ወደ ሃገር ቤት ስልክ መታሁ።

“የደወሉላቸው ደምበኛ ለግዜው ጥሪ አይቀበሉም።” የሚል መልስ ነበር ያገኘሁት። ለሁለተኛ ግዜ ስሞክር ደግሞ “የደወሉት ስልክ ለግዜው ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ነው።” የሚል ምላሽ አገኘሁ። ደቂቃ ባልሞላ ግዜ ውስጥ ጥሪ ያማይቀበለው ስልክ ከአገልግሎት መስጫ ክልል መውጣቱ አስገረመኝ። ተስፋ ሳልቆርጥ ደገግሜ ሞከርኩ። ቢያንስ ከአስር ግዜ ሙከራ በኋላ፤ መስመር አገኘሁና ሎተሪ የወጣልኝ ያህል ተሰማኝ።

ደስታዬ ግን ብዙም አልዘለቀም። በመሃል እንግዳ ነገር ተፈጠረ። ስልኩን የተቀበለኝ የደወልኩለት ሰው አልነበረም። የተፈጠረው ክስተት – ባለንበት የመረጃ ዘመን እንደ 17ኛው ክፍለዘመን “ቴሌ በኦፐሬተር መስራት ጀመረ እንዴ?” ያሰኛል። ነገሩ ግን ሌላ ነው። ስልኩን ያነሳው የተለመደው የስልክ ጠላፊ ስለመሆኑ አንዳች ጥርጥር አልነበረኝም። ሶማሌያውያን መርከብ ሲጠልፉ ጸሃዩ መንግስታችን ደግሞ የስልክ ፓይረት መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ዎች በዚያን ሰሞን ነግሮን ነበርና።

ውጭ ሃገር ያለ ኢትዮጵያዊ ዘመድ ለመጠየቅ መደወሉ አይቀርም። ተስፋ የማይቆርጥ፤ ደጋግሞ ይሞክራል። እንደ እድል የስልኩን መስመር ካገኘ ደግሞ ሌላ ችግር ይገጥመዋል። ዘው ብለው የሚገቡ የስልክ ጠላፊዎች መስመሩን ያውኩታል። ሌላው አማራጭ ደግሞ አጭር የጽሁፍ መልእክት ነው። በኢትዮጵያ ቴሌኮም አጭር መልእክት ከመላክ ይልቅ ደብዳቤ ጽፎ በፖስታ መላኩ እየፈጠነ መጥቷል። አጭር መልእክት የሚደርሰው ከቀናት ብኋላ ነው። ከላኪው ዘንድ መልዕክቱ መድረሱ ቢረጋገጥም ተቀባዩ ጋ ጨርሶ ላይደርስም ይችላል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በሰጡት ጋዤጣዊ መግለጫ “የኢትዮጵያ ቴሌኮም ቴክኖሎጂ ከዴንማርክ፣ ከኖርዌይ እና በከፊል ከእንግሊዝ ቴክኖሎጂ ጋር አንድ ነው” ብለው ነበር። በዚህ መግለጫቸው አቶ ሃይለማርያም የኢትዮጵያን የኢንተርኔት አገልግሎት፣ እንዲሁም የስልክ መስመሩ ጥራት እና አስተማማኝነት በደንብ አድርገው ነበር “ለጋዜጠኞቹ” የገለጹላቸው። ይህን ተናግረው እንዳበቁ ግን የራሳቸውም ስልክ መጠለፉን ሰማን። ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው እንዲሉ አልሰሙት ይሆናል እንጂ፤ “እኛ ሲም ካርድ፤ አንተ ደግሞ ቀፎ ነህ!” ይሏቸዋል – ከላይና ከታች ያሉ አለቆቻቸው።

የኢትዮጵያን ስልክ አገልግሎት ከዴንማርክ፣ ኖርዌይ እና እንግሊዝ ጋር አወዳድረው ማወደሳቸው ግን ራሳቸው ካዴሬዎቹንም ሳይቀር ሳያሰፍራቸው አልቀረም። ሰውየው የኢትዮጵያን ቴሌኮም እያወዳደሩ ያሉት 99.9 በመቶ ሳያቋርጥ አገልግሎት ከሚሰጠው አራተኛው ጀንሬሽን የምእራቡ ቴክኖሎጂ ጋር ነው። መቼም ሁሉም ይዋሻሉ። ነብሳቸውን ይመርና አቶ መለስ ዜናዊም ይዋሹ ነበር። ለዛ ያለው ውሸት አለ። እጅ፣ እግርና አይን የሌለው ውሸትም አለ። እንዲህ አይነት ያፈጠጠ ውሸት ግን እመራዋለሁ የሚሉትንም ሕዝብ እንደመናቅ ይቆጠራል። እኚህ ሰው የሞራል እሴታቸውን ሁሉ አሽቀንጥረው ሊጥሉት ይችሉ ይሆናል። ምሁራዊ ግብአታቸውንም ለተራ ፖለቲካ ጥቅም ሊያስወግዱት ይችላሉ። እምነታቸውስ እንዲህ አይነቱን ቅጥፈት ይፈቅድላቸው ይሆን?
የቴሌ የኢንተርኔት አገልግሎት የመንግስት አልባዋ ሶማልያን አንድ መቶኛም። ኮሜዲያን ክበበው ገዳ እንደቀልድ የነገረኝ ቁም-ነገር የኢትዮጵያን ኢንተርኔት ፍጥነት በደንብ ይገልጸዋል። ክበበው ሰሜን አሜሪካ የስራ ጉብኝቱ ወቅት ፎቶ ተነስቶ ለቤተሰቡ በኢሜይል ይልካል። የላከው ፎቶ መድረሱን ለማረጋገጥ በነጋታው ወደ አዲስ አበባ ደወለ።
“ፎቶ ደረሰ?”
“አልደረሰም!”
ሌላ ቀን እንደገና ደውሎ የላከው ፎቶ እንዳልደረሰ ተነገረው። ለሶስተኛ ግዜ ደውሎ ኢሜይሉ እንደደረሰ ጠየቀ። አሁንም አልደረሰም ተባለ። እንዲህ እያለ ሳምንት ሞላው።
“በሳምንቱ እኔ ቀድሜ ደረስኩ።” ነበር ያለው ክበበው።
የኢሜይል መልእክቱ መድረሱ ከተረጋገጠ በኋላ – ሌላ ችግር ገጠመው። ኢሜይሉ ሲከፈት ግማሽ አካሉን ነበር የሚያሳየው። ፎቶው እስኪያወርድ (ዳውንሎድ እስኪያደርግ) ደግሞ ግማሽ ቀን መፍጀቱ ግድ ነበር።

ይህንን አገልግሎት ነው አቶ ሃይለማርያም ከምእራቡ አለም አገልግሎት ጥራትና ፍጥነት ጋር እያወዳደሩ የሚነገሩን። በአስር ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ በስልክ መገኛኘት ህልም በሆነበት ሃገር፤ ስለ ስልክ ጥራት መናገር ቅጥፈት ብቻ ሳይሆን የሰውየውንም የሞራል ውድቀት ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ቴሌኮም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀጥሎ ትልቅና ግዙፍ የሃገሪቱ ተቋም ነው። እድገቱ ግን ያሳዝናል። በአስር አመት ግዜ ውስጥ ብቻ እንኳን እድገቱ በ75 በመቶ ቁልቁል ወርዷል። ለዚህ ዋናው ምክንያት ተቋሙ አገልግሎት መስጠቱን አቁሞ ወደ ስለላ ተቋም መቀየሩ ነው። ባለፈው ወር ይፋ የሆነው ባለ 100 ገጹ የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ ይህንን መንግስታዊ የስልክ እና የኢንተርኔት ጠለፋ አረጋግጧል።

“የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የነበረን አንድ ዜጋ አፍነው ካሰሩት በኋላ ውጭ የተደዋወለበትን የስልክ ቁጥር ዝርዝር አሳዩት።” ይላል ጠቀማጭነቱ ዩናይትድ ስቴትስ የሆነው አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም። ሰውየው የታሰረው ያልተከፈለ የስልክ ሂሳብ ኖሮበት አልነበረም። ባለስልጣናቱንም አላማም፣ ወይንም መንግስትን በሃይል ለመገልበጥ አላሴረም። ወንጀሉ፤ ከውጭ ሃገር ስልክ ስለተደወለለትና ከወዳጅ ዘመዶቹ ስለተወያየ ብቻ ነበር። ይህ ደግሞ ፍጹም እንግዳ ነገር ነው። ከተለምዶ ልማታዊ መንግስት አስተሳሰብም እጅግ የከፋ!

የዜጎች ሁሉ ስልክ በቴሌ በኩል ይጠለፋል። እንደ ስካይፕ እና ቫይበር ያሉ የቮይስ ኦቨር ስልኮች ደግሞ ፊን ፊሸር በተባለ የኮምፒዩተር ቫይረስ አማካኝነት ይጠለፋሉ። በዚህ አይነት በዜጎች የግል ህይወት ሳይቀር እየገቡ ቴሌን ሙሉ በሙሉ የስለላ ተቋም አደረጉት።

ሞባይል ስልክ እና ኢንተርኔት በአፍሪካ አህጉር በእጅጉ እየተስፋፋ ይገኛል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ 30 በመቶ የሚሆነው የአፍሪካ ህዝብ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጠጠቃሚ እየሆነ መጥቷል። በኢትዮጵያ ግን የስልክ እና የኢንተርኔት ተጠቃሚው ከ2.5 በመቶ አልዘለቀም።

ጎረቤት የሆነችው የኬንያ ህዝብ 40 በመቶ የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ነው። መንግስት አልባዋ ሶማልያ እንኳን፣ ስድስት የቴሌፎንና ስልክ አቅራቢ ኩባንያዎች አሏት። የሶማልያ ህዝብ ጥራት ያለው የስልክ መስመር እና ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል። በኡጋንዳም የዚህ አገልግሎት ሰጪ በመንግስት ሞኖፖሊ ስር አይደለም። ከሰባት በላይ የግል ኩባንያዎች እየተፎካከሩ ፈጣን አገልግሎት እየሰጡ ጠተቃሚውን ህዝብ ወደ 50 በመቶ አድርሰውታል።

ያለነው በመረጃ ዘመን ነውና ያለመረጃ እና ያለ መረጃ ቴክኖሎጂ እድገት አመጣለሁ ማለት ዘበት ነው የሚሆነው። የኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ሃገሪቱን ወደ መረጃ ሳይሆን ወደ ጨለማ ዘመን ነው እየመራት ያለው። እንድምናነበው ከሆነ የኢትዮጵያን ቴሌኮም ለማስፋፋት ከሶስት ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ ሆኗል። ይህ ገንዘብ በትክክል ስራ ላይ ቢውል አባይንም ይገድባል። ለዚህ የእድገት ሳይሆን ይልቁንም የጥፋት ጎዳና ተባባሪ የሆነቸው ቻይናም በውጭ ምንዛሪ እየተከፈላት ቴሌን ብቁ የስለላ ተቋም አድርጋዋለች። የኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ሚኒስትሩም ከተለያዩ የኢንዱስትሪ ሃሮች ጋር በመተባበር የቴሌ ጥራት ላይ ሳይሆን የሚሰራው የስለላ ሃርድዌር እና ሶፍትዌር ማስገባቱ ላይ ነው።

የሃገሪቱ ግብር ከፋዮች ገንዘብ መልሶ ራሳቸውን እንዲያፍን መደረጉ እጅግ ያሳዝናል።

የቴሌ መልስ መስጫ ላይ ያለው መልዕክት ግን መሻሻል አለበት። “ለግዜው” የሚለው ቢቀየር ድርጅቱን ከሃሜት ያድነዋል። እናም መልእክቱ እንዲህ ነው መሆን ያለበት፣
“የደወሉላቸው ደምበኛ ‘ለሁልግዜ’ ጥሪ አይቀበሉም። ..”
ከዚያ በኋላ ደዋዩም ተስፋ ቆርጦ መደወል ያቆማል።

Latest from Blog

ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop