April 20, 2014
23 mins read

“ሆድ ይፍጀው” እንዳለ ያረፈው የሙዚቃው ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ ካለፈ 5 ዓመት ሞላው


ከቅድስት አባተ

ይህ ጽሁፍ በዘ-ሐበሻ ድረገጽና ሚኒሶታ ውስጥ በሚታተመው መዲና ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ነበር። የጥላሁንን 5ኛ ዓመት ሕልፈት ለማስታወስ እንደገና አቅርበነዋል።

ጥላሁን ገሠሠ በህይወት ዘመኑ ከልጅነት እስከ እውቀት የኢትዮጵያ ህዝብ ልጅ ሆኖ በህዝብ አንቀልባ ላይ ያደገ ነው፡፡ ምክንያቱም ገና በ12 እና 13 ዓመት ዕድሜው ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ስለተቀጠረ እንደ ወላጅ ሆኖ ያሳደገው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ ግን ህዝቡ እንደ ወላጅነቱ ስለ ጥላሁን ገሠሠ ሁኔታ በተለይም እጅግ የከፋ አደጋ ሲደርስበት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሳያውቅ ዘመናት እንደ ዋዛ እየከነፉ ነው፡፡

ተወዳጁ ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ከአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ እስከ ኢህአዴግ ድረስ ማለትም በሶስት ስርዓቶች ውስጥ ልዩ ልዩ አደጋዎች ቢደርሱበትም በየትኛውም ዘመን ግን ይፋ የሆነ መረጃ ለህዝቡ አልተሰጠም፡፡ ከህግ አንፃርም የጥላሁን ገሠሠ አደጋዎች ፍትህ አላገኙም፡፡ ህግና ስርዓት ባለበት ሀገር ውስጥ የዚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ አደጋዎች እንዴት እንቆቅልሽ ይሆናሉ? ብለው የሚጠይቁ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ሌሎች አድናቂዎቹም አሉ፡፡

ለምሳሌ በዘመነ አፄ ኃይለስላሴ ስርዓት ወቅት የጥላሁን ገሠሠ ወላጅ እናት በሰው እጅ በሽጉጥ ተገድለዋል፡፡ ይህን ወንጀለኛ ለማግኘት ጥላሁን ገሠሠ ብዙ ዋተተ፡፡ የናቱ ገዳይ ይገኝበታል ተብሎ የሚታሰብበት ስፍራ ሁሉ አሰሰ፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ጥላሁንም የህይወት ታሪኩን በሚገልፀው መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ይላል፡-

‹‹እናቴ የተቀበረችው ቀጨኔ መድኃኒዓለም ቤተ-ክርስቲያን ነው፡፡ በእውነቱ የእናቴ በሰው እጅ መገደል እንደ እብድ አደረገኝ፡፡ የእናቴን ገዳይ ለማግኘት ሶስት አራት ዓመታትን ወስዶብኛል፡፡ እዚህ ቦታ (እዚህ ሰፈር) ታየ ሲባል እዚያ ሄጄ ሳደፍጥ፣ ከዚህ ተነስቶ ሄዷል ስባል ወደተባለበት ቦታ በመሄድ ስንከራተት ጠላቴን በጭራሽ ላገኘው አልቻልኩም›› (ገጽ 75)

ጥላሁን ገሠሠ የናቱን ገዳይ በመፈለግ ብዙ መከራ ደርሶበታል፡፡ ለፖሊሶቹ እንዲያፈላልጉት ገንዘቡን አውጥቷል፡፡ ገዳዩን በመፈለግ ሲባዝን በትዳሩ ውስጥ ክፍተት በመፈጠሩ የመጀመሪያ ባለቤቱ የሆነችዋንና በጣም ከሚወዳት ከወ/ሮ አስራት አለሙ ጋር የነበረው ትዳር እንዲፈርስ ምክንያት ሆኗል፡፡ የናቱን ገዳይ ይዞ ህግ ፊት የሚያቀርብለት አካል አጥቶ ጥላሁን ገሠሠ እንደ ተቆጨ አልፏል፡፡

የሚገርመው ነገር የጥላሁን ገሠሠን እናት የገደለው ሰው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መኖሩን አንዳንድ ምንጮች ይገልፃሉ፡፡ በ1980ዎቹ ውስጥ ይታተሙ የነበሩት ጋዜጦችና መጽሔቶች እንደገለፁት ከሆነ ደግሞ፤ የጥላሁን ገሠሠን እናት ገድሏል ተብሎ የተጠረጠረ ሰው በንጉሱ ዘመን ተይዞ መታሰሩን ይገልፁና ደርግ ድንገት ወደ ስልጣን ሲመጣ ለእስረኞች ሙሉ ምህረት ሲያደርግ ይህም ተጠርጣሪ ከእስር ቤት መውጣቱን ፅፈዋል፡፡

ይህ ተጠርጣሪ በእርጅና ውስጥ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ መኖሩም ይነገራል፡፡ ግን በወቅቱ አስፈላጊውን ምርመራ ባለመደረጉ የጥላሁን ገሠሠን እናት የገደለው ማን እንደሆነ ሳይታወቅ ዓመታት አለፉ፡፡
ከዚህ በኋላ ደግሞ ጥላሁን ገሠሠ ላይ ከመጡት አደጋዎች በዋናነት የሚጠቀሰው የ1985 ዓ.ም አንገቱን በስለት ቆርጦ ለመግደል የተደረገው እጅግ ዘግናኝ ክስተት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የወንጀል ታሪክ ውስጥ እንቆቅልሽ ሆኖ እስከ ዛሬ ድረስ ተሸፋፍኖ የኖረ አደጋ ነው፡፡ ጥላሁን ገሠሠን ማነው አንገቱ ላይ በስለት የቆረጠው?

እንቆቅልሹ ይሄ ነው፡፡ ጥላሁን ገሠሠ ራሱ መናገር አልፈለገም፡፡ ‹ሆድ ይፍጀው› ብሎት ለምን?

አንዳንድ ሰዎች በዚህ ላይ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ ለምሳሌ ጥላሁን ገሠሠ በህይወት እያለ አንገቱ ላይ በስለት ስለደረሰበት አደጋ እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ቢወጣ ደስ አይለውም፤ በዚህም ሳቢያ በጭንቀት እና በብሽቀት ይጎዳል፤ ስለዚህ ጉዳዩ ሆድ ይፍጀው ተብሎ ቢታለፍ ይቀላል፡፡ ምክንያቱም ጥላሁን እንዲገለፅበት ካልፈለገ ብንተባበረውስ የሚሉ አሉ፡፡
ይህን ከላይ የሰፈረውን ሀሳብ በቅንነት ካየነው ከጥሩ መንፈስ የመነጨ ስለሆነ ልንቀበለው እንችላለን፡፡ ግን እኮ የተፈፀመው ወንጀል ነፍስ የማጥፋት ሙከራ ነው፡፡ በየትኛው የህግ አግባብ እንዲህ አይነት ሙከራ ወንጀል ነው! ስለዚህ ይሄ ጉዳይ እስከ መቼ ነው ምስጢር ሆኖ የሚኖረው? የፖሊስ ሃይል ባለበት ሀገር እንዲህ አይነት ፍጥጥ ግጥጥ ያለ ድርጊት ላለፉት 19 ዓመታት በምን ምክንያት ነው ምስጢር ሆኖ የኖረው?

ይህ በጥላሁን ገሠሠ አንገት ላይ የደረሰው አደጋ ይፋ ባለመሆኑ ጉዳዩ ለብዙ ሃሜታዎች ክፍት ሆኖ ኖረ፡፡ ለምሳሌ አደጋውን የፈፀመው ራሱ ጥላሁን ገሠሠ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ሌሎች መረጃዎች ደግሞ አንድ ሰው በራሱ ላይ እንዲህ አይነት ድርጊት ሊፈፅም ፈጽሞ አይችልም በማለት ይገልፃሉ፡፡ ለምሳሌ የጥላሁን ገሠሠን የህይወት ታሪክ የሚያወሳው መጽሐፍ ‹መሰናዘሪያ› ጋዜጣን ጠቅሶ በተለይም አደጋው እንደደረሰ ጥላሁንን ሲያክሙት ከነበሩት ባለሙያዎች መካከል ዶ/ር ባዘዘው ባይለየኝ የተናገሩትን በሚከተለው መልኩ አቅርቧል፡፡
‹‹ጥላሁንን ከምሽቱ 12፡30 ላይ ሰዎች በአንቡላንስ ሆስፒታላችን ድረስ ይዘውት መጡ፡፡ በጆሮው አካባቢ ደም ይፈሰው ነበር፡፡ በተጨማሪም በአየር ቧንቧው ማለትም ማንቁርቱ ላይ ተቆርጦ ደም ይፈሰው ስለነበር ባደረግንለት የመጀመሪያ እርዳታ ደሙን አቆምን፡፡ በጎን በኩል በስለቱ የደረሰው ጉዳት ጉበቱን አግኝቶታል፡፡ ግራ እጁ ላይ ያለው የደም ስር ከባድ ጉዳት ደርሶበት የነበረና በጠቅላላውም ሁለት ሰዓት የፈጀ የቀዶ ጥገና ህክምና ተደርጎለታል፡፡ በመተንፈሻ አካሉ በደሰበት ጉዳት ምክንያት ቁስሉ እስኪድን ድረስ ጊዜያዊ የመተንፈሻ መሳሪያ ተደርጎለት የሚተነፍሰው በዚያው ነበር፡፡ እንደ ማንኛውም ሰው መተንፈስ አይችልም፡፡ አንድ ሰው ራሱን አንድ ቦታ ላይ ሊወጋ ይችላል፡፡ ሶስት ቦታ ላይ ራሱን አቆሰለ ማለት ይከብዳል፡፡ ድፍረቱም አቅሙም አይኖረውም›› (ገጽ 105) በማለት ሀኪሙ ገልፀዋል፡፡
የህክምና ባለሙያው የሰጡት አስተያየትም አሳማኝ መንፈስ አለው፡፡ ስለዚህ አደጋውን ያደረሰው ሌላ አካል ነው ብለን እንድንጠረጥር ያደርገናል፡፡

ጥላሁን ገሠሠ አደጋው በደረሰበት ወቅት የታተሙ የነበሩት ጋዜጦችና መጽሔቶች ስለ ሁኔታው ያቀረቧቸውን መጣጥፎች በሙሉ መልሼ አይቻቸው ነበር፡፡ ነገር ግን እነርሱም ቢሆኑ እጃቸው ላይ ትክክለኛው መረጃ ስለሌለ ከመላ ምትና ከተጠየቅ (Logic) በስተቀር የተደራጀ ማስረጃ አላቀረቡም፡፡ ዛሬ በህይወት የሌለው ታዋቂው የመድረክ አስተዋዋቂውና የጥላሁን ገሠሠ ጓደኛ የነበረው ስዩም ባሩዳ ተጠይቆ ሲመልስ፣ ‹‹እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ ጥላሁን ገሠሠ በቢላዋ አንገቱን ሊቆርጥ ቀርቶ፣ ጥፍሩን እንኳን በምላጭ ለመቁረጥ የሚፈራ ነው›› በማለት ገልፆታል፡፡ በወቅቱ የተጠየቁት የጥላሁን ገሠሠ ጓደኞች ሲናገሩ፣ ጥላሁን በራሱ ላይ እንዲህ አይነት እርምጃ እንደማይወስድ ጠቁመዋል፡፡ ታዲያ ማን ነው አደጋ ያደረሰበት?

ዛሬ ጥላሁን በህይወት የለም፡፡ አንገቱ ላይ የደረሰበት አደጋ ‹‹በሆድ ይፍጀው›› ሰበብ ለዘመናት ምስጢር ሆኖ መኖር ያለበት አይመስለኝም፡፡ በወቅቱ ፖሊስ የተደራጀ ምርመራ ማድረጉ ይነገራል፡፡ ነገር ግን ያ የምርመራ ውጤት ለፍርድ ቤት ይቅረብ ወይስ አይቅረብ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ጉዳዩንም በሐገሪቱ ውስጥ የተከሰተ አንድ ትልቅ ወንጀል አድርጎ የመመልከት አዝማሚያም አልተስተዋለም፡፡ ስለዚህ እኛ እንደ ጥላሁን ገሠሠ ‹‹ሆድ ይፍጀው›› ብለን ማለፍ ያለብን አይመስለኝም፡፡ እውነታውን ካላወቅን ሆዳችንን ይቆርጠናል፡፡ ከቶስ የማይክል ጃክሰንን አሟሟት በተመለከተ የነበረውን የፍርድ ቤት ሂደት ያየ፣ ጥላሁን ገሠሠን ሲያስታውስ ምን እንደሚል አላውቅም፡፡ የጥላሁን ገሠሠን እናት የገደለው አልታወቀ፡፡ ጥላሁን ገሠሠን አንገቱን በስለት የቆረጠው አልታወቀ፡፡ ምንድን ነው ጉዱ?
ሌላው አሰገራሚውና አሳዛኙ ጉዳይ የጥላሁን ገሠሠ ሞት ነው፡፡ ያንን የሚያክል የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉስ እንደ ዋዛ ሞተ ሲባል በእጅጉ ያስደነግጣል፣ ይቆጫል፣ ያሳስባል፡፡

ሃሳብ አንድ
ድንገት ከአሜሪካን ሀገር ወደ ሐገሩ ኢትዮጵያ የመጣው ጥላሁን ገሠሠ ማታ በቤቱ ውስጥ ታመመ፡፡ ባለቤቱ እና ቤተሰባቸው በድንጋጤ ይዘውት ወደ አንድ የግል ሆስፒታል ሄዱ፡፡ እዚያም እንደደረሱ የኢትዮጵያው የሙዚቃ ንጉስ ተገቢውን ህክምና አለማግኘቱን ባለቤቱ ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ በጥላሁን ገሠሠ የህይወት ታሪክ ውስጥ የሚከተለው ተጽፏል፡፡

‹‹ሰው ታሞብናል! እባካችሁ ዶክተር ጥሩልን›› አለቻቸው፣ እጅግ በተጣደፈ ሁኔታ፡፡ ድምፅ ሰምተው ከመጡት ሰዎች መካከል አንዱ ‹‹መጀመሪያ ካርድ አውጡና ነርሷ ትየው›› አለ በተረጋጋ ስሜት፡፡
‹‹እባካችሁ ጥላሁን ገሠሠ ነው፡፡ በጣም አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልገዋል›› አለች ቶሎ እንዲረዱላት እተንሰፈሰፈች፡፡ ደንገጥ ብሎ ከልቡ የሚሰማት አጣች፡፡

‹‹ወ/ሮ ሮማን መላ ቅጡ ጠፍቶባት አይኖቿ ከወዲያ ወዲህ ሲዋትቱ ከወደ ጥግ በኩል የቆመ አንድ ዊልቸር አይታ ሄደች፡፡ እየገፋች ስታመጣው ያዩዋት ጥበቃ አብረው ወደ መኪናው አጋፏት››
‹‹ጥላሁንን ከመኪናው አውርደው ተሽከርካሪው ወንበር ላይ አስቀመጡት፡፡ ጥላሁንም ቁርጥ ቁርጥ ባለ ትንፋሽ፤ ‹‹እባክህ ዶክተርዬ ተንፍሼ ልሙት፣ የምተነፍስበት ነገር አድርግልኝ›› በማለት የመማፀኛ ቃል ወርወር ያደርጋል፡፡ ሐኪሙ በዝግታ መጥቶ አጠገባቸው ቆም አለና ጥላሁን የተቀመጠበትን ዊልቸር ከወ/ሮ ሮማን በመውሰድ እዚያው በዚያው በክሊኒኩ ኮሪደር ላይ ወደ ፊትና ወደኋላ እየገፋ በዝምታ ተመለከተው፡፡

‹‹ወ/ሮ ሮማን ስለ ህመሙ ስትነግረው በቀዘቀዘ ደንታቢስ ስሜት ያያታል፡፡ ያ ጎልቶ የሚታይ ድንጋጤዋ ስሜት፣ ፊት ለፊቱ ያለው የህመምተኛው ቅዝታ ቅንጣት ያህል ርህራሄ ያሳደረበት በማይመስል ስሜት፡፡
‹‹ስንት አይነት ልበ ደንዳና በየቦታው አለ!›› አለች ወ/ሮ ሮማን በውስጧ፡፡ ስለ ህክምና ስነ-ምግባር በአደባባይ የተገባው የሄፓክራተስ የቃል ኪዳን መሀላ እንደ ጤዛ ተኗል፡፡
‹‹ኧረ ባካችሁ አንድ ነገር አድርጉለት!! ምነው ዝም አላችሁ?›› አለች፡፡ ‹‹ኧረ እባካችሁ እርዱልኝ?›› አለችው፣ አጠገቧ የቆመውን ሐኪም፡፡

‹‹ዶክተርዬ መተንፈስ አቃተኝ፤ ትንሽ የምተነፍስበት ኦክስጂን አድርግልኝ? ተንፍሼ ልሙት›› እያለ ሲማፀን ሌላ ሐኪም ደርሶ ‹‹አስም አለበት እንዴ?›› አለ፡፡ ኋለኛውም እንደ ፊተኛው ሐኪም ርህራሄ ባጣ ስሜት፡፡ ከራሱ ከጥላሁን ይልቅ ስለ እሱ ልዩ ልዩ የህመም አይነቶችና ባሕሪይ በይበልጥ የምታውቀው ባለቤቱ ነች ማለት ይቻላል፡፡ ‹‹ባለሙያ ነኝ ማለት ባልችልም ስለ በሽታው በየጊዜው ከዶክተሮች ጋር የምነጋገረው እኔ በመሆኔ ብዙ ልምዶችና መረጃዎች አሉኝ›› ትላለች ወ/ሮ ሮማን፣ የአያሌ ዓመታት ግንዛቤዋን እያነፃፀረች፡፡
‹‹አስም ሳይሆን የልብ ህመም አለበት›› አለች ወ/ሮ ሮማን ፈጠን ብላ፡፡

‹‹እንግዲያው ጎተራ አካባቢ የልብ ህክምና የሚሰጥበት ኢንተርናሽናል ሆስፒታል ስላለ ወደዚያ ይዘሽው ሂጂ›› ብለዋት መልሷን ሳይጠብቁ ትተዋቸው ወደ ጉዳያቸው ተመለሱ፡፡ (ከገፅ 116-170 በከፊል የተወሰደ)
ይህ ከላይ የተፃፈው ታሪክ እውነት ከሆነ ለጥላሁን ገሠሠ ሞት አንዱ ምክንያት ሊሆን ነው፡፡ ሆስፒታል ደርሶ ህክምና አላገኘም፡፡ በስርዓት ተቀበለውም የህክምና ባለሙያ የለም ማለት ነው፡፡ እናም ይሄን የሚያክል ስህተትን በምንድን ነው የምናርመው? ስለ ጉዳዩስ የቤተዛታ ሆስፒታል አስተዳደር ምነው ዝም ይላል? መልስ የለውም? የሀኪሞች ማህበርስ በዚህ ጉዳይ ላይ እንደ አጀንዳ አይነጋገርም? ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርስ? የህክምና ህጉስ የሄፓክራተስን የቃል ኪዳን መሐላ አላከበሩም ተብለው በሚተቹ ሀኪሞችና ተቋማት ላይ ምን ይላል? ይሄ የማይክል ጃክሰንን የአሟሟት ምስጢር የፈተሸ ችሎት የተወዳጁን የሙዚቃ ንጉስ የጥላሁንን ገሠሠን ህልፈት ክፉኛ አስታወሰኝ፡፡

ሐሳብ ሁለት
የጥላሁን ገሠሠ ባለቤትና ቤተሰቦች፣ የልብ ህክምና የሚሰጥበትን ሆስፒታል ቢፈልጉ ያጡታል፡፡ ከዚያም ጎተራ አካባቢ ወዳለው ሰናይ ክሊኒክ ይደርሳሉ፡፡ እዚያም እንደ አንድ የህክምና ተቋም ተገቢውን እርዳታ እንዳላገኙ ተገልጿል፡፡ ጥላሁን ገሠሠ ኦክስጅን እያለ የፈለገውን ኦክስጅን ሳያገን ማለፉን በፅሑፍ ተገልጿል፡፡ እንደ ባለቤቱ ገለፃ በሁለተኛውም ሐኪም ቤት ውስጥ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ጥላሁን ገሠሠ አላገኘም፡፡ የባለቤቱ የወ/ሮ ሮማን በዙ በተደጋጋሚ ሐኪም ቤቶቹን እና የህክምና ባለሙያዎቹን እየጠቀሱ የሰሯቸውን ስህተቶች ገልፀዋል፡፡ ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ ተገቢው ማጣሪያ ሳይደረግ የጥላሁን ገሠሠ ሞት ብቻ ይነገራል፡፡

አሁን ‹‹ሆድ ይፍጀው›› የሚል ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ሐኪሞቹም ሆኑ የህክምና ተቋማቱ ሆድ ይፍጀው ብለው ተቀምጠው ከሆነ እኔ ሆዴን ቆርጦኛል፡፡ ጥላሁን ገሠሠ ኦክስጂን አጥቶ ከሞተ እና ዝም ከተባለ ጥፋተኛው ራሱ ጥላሁን ነው ማለት ነው? ጊዜው የሆድ ይፍጀው አይመስለኝም፡፡
በአጠቃላይ ጥላሁን ገሠሠ የእናቱን ገዳይ አላወቀም፡፡ ህግም የናቱን ገዳይ አግኝቶ ተገቢውን ውሳኔ አልሰጠለትም፡፡ ከዚህ ሌላም አንገቱ ላይ በስለት የደረሰበት አደጋ እስከ ዛሬ ድረስ ምስጢር ሆኖ ኖሯል፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ ‹‹ዶክተርዬ! መተንፈስ አቃተኝ፤ ትንሽ የምተነፍስበት ኦክስጂን አድርግልኝ? ተንፍሼ ልሙት›› እያለ እጅግ በአሳዛኝ ተማፅኖ፣ እርዳታ ሳይደረግለት እንዳለፈ ይነገራል፡፡ በዚህም ጉዳይ ተጠያቂው ማን እንደሆነ የሚነገር ጉዳይ የለም፡፡ ሁሉም ነገር ዝም ነው፡፡ ውስብስብ የሆነው የማይክልጃክሰን አሟሟት ግን በግልፅ ችሎት ፍትህ አግኝቷል፡፡ የጥላሁን ገሠሠ አደጋዎችና ሞቱ ግን እንቆቅልሽ ሆኖ ይኖራል፡፡ እንቆቅልሹስ ሳይፈታ ለትውልድ እናስተላልፍ?S

ይህ ጽሁፍ በሚኒሶታ እየታተመ በሚወጣው መዲና ጋዜጣ ላይ ታትሞ የወጣ ነው።

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

ትላንት አንድ ወዳጀ ደውሎ “አሳየ ደርቤን” ታውቀዋለህ ወይ” አለኝ፡፡ እኔም አላውቀውም አልኩት፡፡ ኢንጅኔር “ኡሉፍ” የተባለ ሰው የዛሬ ሰባት ዓመት ያሰራረውን ጥልቀትና ስፋት ያለውን ዘገብ አቅርቦታልና አዳምጠው አለኝ፡፡ እኔም “ጉድሺን ስሚ ኢትዮጵያ–ከባድ አደጋ

ተቆርቋሪ የሌላት ኢትዮጵያ – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ወገኖቸ፤ ለጊዜው ትችቱን እናቁምና ለወገኖቻችን እንድረስላቸው፡፡፡ በቤተ አማራ ወሎ ቡግና የተከሰተው ርሃብ ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ለወገን ደራXኡ ወገን ስለሆነ እባካችሁ ህሻናትን እናድን፤ ለግሱ፡፡ ጦርነት ያመክናል፤ ተከታታይ ጦርነት አረመኒያዊነት ነው፡፡ ጦርነት ካልቆመ የረሃቡ

እግዚኣብሔር ግን ወዴት አለ?

Go toTop