የኢህአዴግ “አሸባሪነት”በ2007 ምርጫ ማንን ያስር ይሆን?

ሳሙኤል ተወልደ በርሔ/ሃርስታድ ኖርዌይ/
ሳሙኤል ተወልደ በርሔ/ሃርስታድ ኖርዌይ
ሰው በላው የኢህአዴግ “አሸባሪነት” ለ2007 ምርጫ ምን እየቆመረ ይሆን?…ኢህአዴግ  ስልጣኑን ከተቃውሞም ሆነ ከነፃው ፕሬስ ወቀሳ የሚያረጋጋበት በርካታ ኢ-ፖለቲካዊ (ኢ-ዴሞክራሲያዊ) አካሔዶች አሉት፡፡ ኢህአዴግ እንደቀደምቶቹ የኢትዮጵያ መንግስታት ሁሉ የተቃውሙትን ፖለቲከኞች አስሯል፤ በዩኒቨርስቲ ውስጥ የአካዳሚ ነፃነታቸውን የጠየቁ ተማሪዎችን በፖሊስ አስደብድቧል፤ ከፍ ሲልም በእስር አሰቃይቷል፡፡ ብዙዎችንም በፖለቲካ አመለካከታቸው (በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ) ከገዛ ሀገራቸው እንዲሰደዱ አድርጓል፡፡ ንቁ  የፖለቲካ ተሳትፎ በሚያደርግ አባወራ ምክንያት የቤተሰቡ አባላት ከፍተኛ ወከባ እና እንግልት እንዲደርስባቸው አስደርጓል፡፡

የ1997 ዓ.ም ምርጫ ውጤት ፍፁም ወደተቃዋሚዎች ማጋደሉን የተመለከተው እና ስልጣኑ አደጋ ላይ መውደቁን የተገነዘበው ኢህአዴግ ከ97 ዓ.ም በኋላ እስከአሁን ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ እጅግ አስጨናቂ ማድረጉ የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡ ከአስጨናቂ እና ከኢ-ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ርምጃው መካከል በዋነኝነት ሊጠቀስ የሚችለው ደግሞ “አሸባሪነት” የሚለው ታፔላው ነው፡፡

በዚህ ሰው በላ ሐሳዊ ፍረጃውም ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ተቃዋሚዎችን፣ ሞጋች የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞችን፣ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞችን…ባጠቃላይ ስልጣኔን በዓይነ ቁራኛ ይመለከቱብኛል ብሎ ቀይ መስመር ያሰመረባቸውን ሰዎች አስሮ አስቀምጧቸዋል፡፡

በዚህ ስጋቱ የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ በ2007 ዓ.ም በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ንቁ ተሳታፊ ይሆናሉ ብሎ የሚገምታቸውን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም የነፃው ፕሬስ  ሞጋች ጋዜጠኞችን በ“አሸባሪነት” ሰበብ እየቀፈደደ ወህኒ ሊያወርዳቸው እንደሚችል የማይጠረጥር የኢህአዴግን አስከፊ የፖለቲካ ስነ-ባህሪ የማያውቅ ብቻ ነው፡፡

ይህን ያልኩት ያለ በቂ ምክንያት አይደለም፡፡ በ1997 ዓ.ም የምሁራን ስብስብ በነበረው ቅንጅት የደረሰበት ወደር አልባ ሽንፈት ዳግም እንዲደገምበት ስለማይፈልግ ለስልጣኑ የሚያሰጉ ፓርቲዎችን (አመራሮቻቸውን) አነፍንፎ ከመያዝ ወደ ኋላ አይልም፡፡

በዚህም የተነሳ የ2007ቱን ብሔራዊ ምርጫ ተቃዋሚዎች እንደፈለጉ እንዲሆኑበት እና የነፃው  ፕሬስ አባላት በነፃነት እንዲዘግቡት ሁኔታዎችን ያመቻቻል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ እናም በ97  ዓ.ም ምርጫ ለወህኒ ቤት እንደተገበሩት ተቃዋሚዎች እና ጋዜጠኞች ለ2007ቱም ምርጫ እንደ አድባር የሚገበሩ ተቃዋሚዎች እና ጋዜጠኞች አይጠፉም፡፡ ጥያቄው ይገበራሉ ወይስ አይገበሩም? የሚለው ሳይሆን፤ እነማን ይገበራሉ? የሚለው ነው፡፡

ደርግ በዘመነ ስልጣኑ የተቃውሞ ድምፅ ሲያሰሙት የነበሩ ሰዎችን “አድኃሪ፣ አወናባጅ…” ወዘተ እያለ ይፈርጅ ነበር፡፡ ፈርጆ ሲያበቃም “አድኃሪዎች” ምኖች፣ ምናምኖች ያላቸውን ሰዎች  ከማሰርና ከመደብደብ አልፎ እስከ መግደል የደረሰ እርምጃ ይወስድባቸው ነበር፡፡ ደርግ እንዲያ ሲፈርጅ፣ ሲገድል፣ ሲያስር፣ ሲደበድብ የነበረው ለህልውናው ስለሚሰጋ ነበር፡፡

እየፈረጀ ባያስር፣ እያሰረ ባይገድል…የተቃውሞ ድምፅ የሚያሰሙ ወገኖች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ስልጣኑ (ህልውናው) አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ስለሚያምን የስልጣን ትንኮሳ ለሚያደርጉበት ሰዎች እንቅልፍ የለውም ነበር፡፡ ጃንሆይም ተቃውሞ ያሰሙባቸው የነበሩ  የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን “ፀረ ዘውድ፣ ፀረ ንጉስ…” እያሉ በመፈረጅ ለህልውናቸው ማቆያ  ወይም ለስልጣን ማረጋጊያ የሚያግዙ ርምጃዎችን ይተገብሩባቸው ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  “እግዚአብሔር የቀባው” ከቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

እነሆ ኢህአዴግም “ከማን አንሼ” በሚል ስሜት የሰላ ሂስ የሚያቀርቡ ጋዜጠኞችን፣ ለስልጣኔ  (ለወንበሬ) ያሰጉኛል የሚላቸውን ጠንካራ ተቃዋሚዎችን እያደነ በ“አሸባሪነት” ስም ወህኒ ያወርዳቸው  ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ በጋዜጠኞቹ በእነ እስክንድር ነጋ እስር (“የአሸባሪነት ታፔላ”)  ነፃውን ፕሬስ ለማስበርገግ፣ በፖለቲከኞቹ በእነ አንዷለም አራጌ ተመሳሳይ ታፔላ የተቃውሞውን መንደር ለማስደንበር መላ ዘይዶ የተነሳው ገዢው ፓርቲ “አሸባሪ” የሚለውን ሰበብ የህልውናው ማስጠበቂያ “ዘበኛ” ሳያደርገው የቀረ አይመስለኝም፡፡

ጋዜጠኞች በ“አሸባሪነት” ስም ወህኒ በወረዱ ቁጥር መንግስት የሰላ ሂስ ከሚሰነዝሩ የነፃው  ፕሬስ አባላት ሂስ “ነፃ” እየወጣ ይሄዳል፡፡ እንዲሁ ከፍተኛ የህዝብ ቅቡልነት የተቀዳጁ  የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች “አሸባሪ” በሚል ሰረገላ ወህኒ ሲወርዱ ገዥው ፓርቲ የስልጣን ማገሩን ይበልጥ እየተከለው እና እያጠበቀው ይመጣል፡፡ ታዲያ ከ”አሸባሪነት” በላይ  የመንግስትን ህልውና (ስልጣን) እያስጠበቀ ያለ ዘብ ይኖር ይሆን?

ኢህአዴግ “አሸባሪነት”ን ለብቻው የሚረዳበት (የሚተረጉምበት) የተለየ መዝገበ ቃላት እንዳለው የምናውቀው የነ አሜሪካን አቋም በአንክሮ የገመገምን ዕለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው አሜሪካና  ኢትዮጵያ “የጸረ ሽብር” አጋር ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት “አሸባሪ” እያለ የሚያስራቸውን ጋዜጠኞች እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አሜሪካ “አዎ! አሸባሪ ናቸው” ብላ አታምንም፡፡

ይባስ ብላ “በሽብርተኝነት” ስም የታሰሩ ጋዜጠኞችን እና ፖለቲከኞችን በአስቸኳይ ይፈታ ዘንድ የኢትዮጵያን መንግስት ያሳሰበችበት ጊዜ በርካታ ነው፡፡ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትም የኢትዮጵያ መንግስት “ሽብርተኛ” እያለ ወህኒ የወረወራቸውን ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች  “ጀግና” እያሉ ሲሸልሟቸው ነው የምናስተውለው፡፡

ከዚህ እውነታ የምንገነዘበው ኢህአዴግ ራሱ በፈለሰፈው እና የተቀረው አለም በማይስማማበት “ሽብርተኝነት” ስም እየነገደ መሆኑን ነው፡፡ አዎ! ሽብርን እና አሸባሪዎችን የማይጠየፍ ጤነኛ  ሰው የለም፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ “አሸባሪ” የሚለውን ቃል የሚተረጉምበት መዝገበ ቃላቱ  ከሌላው አለም የተለየ በመሆኑ ሰርክ እንደተወገዘበት ነው የሚገኘው፡፡

አንድ የማውቃቸው ባለትዳሮች ነበሩ። ምንም እንኳን ዛሬ ተነጣጥለው ለየብቻ መኖር ቢጀምሩም፤ ሚስትየው ባሏ መጠጥ እንዲያቆም ያልተሳለችው ስለት እና ያላንኳኳችው የቤተክርስቲያን በር የለም። ከዚህም ሌላ ጠዋት ከቤት ሊወጣ (ወደ ስራ ሊሄድ ሲል) እግሩን ከመላስ በማይተናነስ መልኩ ማታ ጠጥቶና ሰክሮ እንዳይመጣ ትወተውተዋለች፣ ትለምነዋለች፣ ታስጠነቅቀዋለች።

ውትወታዋም ሆነ ልመናዋ እንዳልሰመረ የምትረዳው ማታ ወደ ቤት ሲመጣ ሰክሮ እየተንገዳገደ  መሆኑን ስትመለከት ነው። ጠዋት ሲወጣ አስጠንቅቃው ማታ ሲገባ የሚሰክረው ለምንና ምን በድላው እንደሆነ ስትጠይቀው `ሰይጣን አሳስቶኝ ነው` ይላታል በመጠጥ የተላወሰው ምላሱ  እየተደናቀፈበት። እሱ እየሰከረ እሷ እየመከረችና እየለመነች ለአንድ አመት ያህል አብረው ቢኖሩም, መፋታታቸው ግን አልቀረም ነበር። አብረው በኖሩባቸው ወቅቶች ጠጥቶ ሲመጣ `ለምን?` ማለቷን አትተውም ነበር። `ሰይጣን አሳስቶኝ ነው` የሚለው ቃል የዘወትር መልሱና ሰበቡ መሆኑን የተገነዘበችው ሚስት `ምን አለበት ለአንድ ቀን እንኳን ሰበብህን ለወጥ ብታደርገው? ሁልጊዜ ሰይጣን አሳስቶኝ ነው እያልክስ ለምን ታሞኘኛለህ?` ብላ በተናገረች ማግስት እቃዋን ይዛ ላትመለስ ተለየችው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢህአዴግ መንግስት በሚቃወሙትና በሚተቹት ላይ እየወሰደ ያለውን አፈና እና እስር የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲታገለው ጥሪ እናቀርባለን!!!

እውነት ነው! አመቱን ሙሉ ወይም ለአመታት በአንድ በማይለወጥና በማይሻር ሰበብ  አድራጎታችንን (ስህተታችንን) እየሸፋፈንን ለመቀጠል የምናደርገው ሙከራ ሰበባችንን  በሚያደምጠው ሰው ላይ የማይሰረይ መሰላቸት ይፈጥራል። ሁልጊዜ በአንድ ሰበብ ለመጓዝ መሞከር ፋራነታችንን እና አራዳ አለመሆናችንን ያሳብቅብናል።

በማይለወጥ ሰበባቸው (ምክንያታቸው) ልንጠቅሳቸው ከምችላቸው አካላት ደግሞ ገዥያችን ኢህአዴግ አንዱ ነው። ኢህአዴግ መንግስት እንደመሆኑ የአገሪቱን ፀጥታና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት አለበት። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ (አንዳንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በርከት ለሚሉ አንዳንድ ጊዜዎች) ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ሙስሊሙን ወክለው የሚንቀሳቀሱ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ሲከስስ ወይም ሲያስር እንደ ምክንያት (ሰበብ) የሚያስቀምጣቸው መልሶች  እጅግ ተመሳሳይ እና ማሻሻያ የማይደረግባቸው ናቸው። ጋዜጠኛን ሲያስር ‹‹ህገ-መንስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን በሀይል (በሽብር) ለመናድ ሲቀሳቀስ…›› የምትል የተለመደችውን ምክንያት ያስቀምጣል። ይህ ምክንያት ጋዜጠኛውን ለመክሰሻ አገልግሎት ብቻ የሚውል አይደለም። ተቃዋሚዎችን ሲያስርም ‹‹ሽብርተኛ›› የምትለውን ቃል ለመክሰሻ ፍጆታው ያውላታል። በአሁን ሰአት በእስር ላይ የሚገኙ የሙስሊሙን ተወካዮች ሲያስር እንደ ምክንያት የተጠቀመው ጋዜጠኞችንና ተቃዋሚዎችን ለመክሰስ የደረደራቸውን ሰበቦቹን ነው።

ከላይ የባለትዳሮቹን የህይወት ተሞክሮ ያነሳሁት ያለ ምክንያት አይደለም። ከኢህአዴግ ምክንያት ድርደራ ጋር ተቀራራቢ (ተመሳሳይ) ባህሪ ስላለው ነው እንጂ። ሚስት ‹‹ሰይጣን አሳስቶኝ ነው›› በሚለው የባሏ ቋሚ ተሰላፊ ሰበብ ትዳሯን እስከመናድ ያደረሰ መሰላቸት  አሳድሮባታል።

የ1997 ዓ.ም የምርጫ ውጤቱ ወደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካጋደለና ሁኔታዎች ወደአላስፈላጊ አቅጣጫ ከዞሩ በኋላ በርካታ ተቃወሚዎች እንዲሁም ጋዜጠኞች ወህኒ ወርደዋል። የዛን ጊዜ የታሰሩበት ምክንያት ‹‹ህገ-መንግስቱን እንደ ሾላ በድንጋይ ለማውረድ…›› የሚል ነበር። 1997 ዓ.ም ጥሎን ከነጎደ ዛሬ ወደ ስምንት አመት ሆኖታል። በነዚህ ስምንት አመታቶች ውስጥ ፖለቲካው፣ ኢኮኖሚው፣ ኑሮው፣ የሰው አስተሳሰብ… በውድቀትና በእድገት ምህዋር ውስጥ ወይ ወደ ላይ ወጥቷል፤ አሊያም ወደታች ወርዷል። በአጠቃላይ ሁኔታው ተለውጧል፤ ተለዋውጧል። “ህገ-መንግስቱንና ህገ-መግስታዊ ስርዓቱን በሀይል (በሽብር) ለመናድ ሲንቀሳቀሱ…›› በመንግስታችን ቋንቋ፤ የቁመት፣ የወርድ፣ የመጠን ለውጥ ሳይደረግባት ይኸው እስከዛሬ እንዳለች አለች። ኢህአዴግ ወደፊት እስከሚኖርበት ጊዜ ድረስም አብራው ትኖራለች፤ ሰንደቁና አርማው ናትና አትጠፋም። ጋዜጠኞች፣ ተቃዋሚዎች፣ ‹‹እምቢየው›› መብቴን የሚሉ ዜጎች ከኢትዮጵያ ምድር  ሲጠፉ ብቻ ነው ያቺ የኢህአዴግ ምክንያት ‹‹በክብር›› ወደ ማህደሯ የምትመለሰው። እስከዚያው ድረስ ግን፤ እንደ ርዕዮተ አለም የተያዘችው ምክንያት ሳትከለስ፣ ሳትበረዝም ሆነ ተሐድሶ ሳይደረግባት በዶግማ (Doctrine) መልክ ትቀጥላለች።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ክፉ ሞቶም ይገድላል”  ማላጂ

የአዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጆች ‹‹መንግስት በሽብርተኝነት ሊያስረን እንደሆነ ከታማኝ ምንጮቻችን ሰማን›› ብለው አገር ጥለው ከተሰደዱ በኋላ፤ እንዳሉትም በሌሉበት በሽብርተኝነት ተከስሰውና ‹‹ሽብርተኛ›› ተብለው ተፈርዶባቸዋል። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ርእዮት አለሙ ተከስሰው የተፈረደባቸው ‹‹ሽብርተኛ›› በምትለዋና ለአዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረቦች በተለጠፈችው ቦሎ ነው። አንድ ጋዜጠኛ ሲታሰር የክሱ ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ የግድ የሚመለከተው አካል መግለጫ እስኪሰጥ መጠበቅ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። አሁን አሁን እከሌ የሚባል ጋዜጠኛ ታሰረ የሚል ወሬ ሲሰማ፤ ያው ‹‹በሽብርተኝነት›› እንደሚከሰስ አስቀድሞ ማረጋገጥ እየተለመደ መጥቷል። ይህ እንዲሆን በር የከፈተው መንግስታችን በተለይም ከ1997 ምርጫ በኋላ እየተከተለው የመጣው ተሐድሶ አልባ ምክንያቱ (ሰበቡ) ነው።

ለአዲስ ነገር ጋዜጠኞች ክስ የተጠቀመውን ምክንያት ለእስክንድር ነጋ፣ ለእስክንድር ነጋ  የተጠቀመውን ለርዕዮት አለሙ… ለውብሸት ታዬ… ነገ  ደግሞ አንድ ጋዜጠኛ ሲታሰር፤ ለእሱም ፍጆታ ያውለዋል።

በአንድ ተመሳሳይ ምክንያት የተለያዩ ጋዜጠኞችን ማሰር አይሰለችም? የሰው ልጅ አንዴ፣ ሁለቴና ሶስቴ በሰይጣን “ሊሳሳት” ይችል ይሆናል። ግን እንዴት ዘለአለአም በሰይጣን እየተሳሳተ ይኖራል?  እያንዳንዱ ጋዜጠኛስ እንዴት ‹‹ሽብርተኛ›› ሊሆን ይችላል?

በደርግ ጊዜ ነው አሉ፤ ‹‹አንድ ሰው አይደለም በጤናው ሰክሮ እንኳን የመንግስቱ ኃይለማርያምን አስተዳደር መውቀስም ሆነ መተቸት አይችልም ነበር ይባላል። “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” የሚለው አባባል በደርግ ጊዜ አይሰራም ነበር።” ሲሉ አንድ አባት አጫውተውኛል። ደርግ ከተገረሰሰ ከሃያ ሁለት አመታት በኋላ ማለትም ዛሬ፤ ያውም “ዴሞክራሲና ነፃነት ያለገደብ መስፈኑ” በሚነገርበት በዚህ ጊዜ ሳይሰክሩ መንግስትን መተቸት ከባድ እየሆነ መጥቷል። ከባዱን መከራ እጋፈጠዋለሁ ያለ ጋዜጠኛም ‹‹ያቺ ነገር›› ትመዘዝለታለች።

እንግዲህ በደርግና በኢህአዴግ መካከል ያለውን ልዩነት እንመርምር። በደርግ ጊዜ ተሰክሮም ሆነ ሳይሰከር ትችት እሰነዝራለሁ ማለት ከባድ ነበር። በኢህአዴግ ጊዜ ዲሞክራሲው “ያለ ገደብ”  በመንሰራፋቱ፣ በገደብ ሰክረው ያለገደብ የመንግስትን ስህተት መተቸት ይቻላል። ታዲያ  በመጠጥ ስካር እንጂ በኑሮው ንረት፣ በመልካም አስተዳደር ችግር፣ በመኖሪያ ቤት እጥረት ስካር መንግስትን ማማረር፣ ከማማረርም አልፎ ለተቃውሞ መውጣት “ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል ለመናድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች…” ለሚል የክስ ፋይል አሳልፎ ይሰጣል። መቼም አሜሪካና አውሮፓ የሽብርተኞች ደጋፊና አፍቃሪ ስለሆኑ አይደለም-የኢትዮጵያ መንግስት “አሸባሪ” ያላቸውን እነ እስክንድርን እየሸለሙ ያሉት፡፡ እናም ኢህአዴግ ሆይ! የተበላች ዕቁብ የመሰለችውን ምክንያትህን (አሸባሪነትን) ቀየር ብታደርጋትስ?!…

 

 

2 Comments

  1. Dear writer
    Minew weyanen ena dergen sitawedader weyane
    Sew megdelun eresahew yedergen tifat neber yasayehen
    Weyane gedele ymil neger altsafhim Yeweyane tilku tifat maser bicha mehonun new yenegerhen
    Ehain tsihuf lemin be ETV atakerbewm.
    Ezih gin yanten mereja yemifelg yelem::

Comments are closed.

Share