April 14, 2014
39 mins read

ስለፍትህ ሲባል ስርዓቱ ይፍረስ! ፪ (ተመስገን ደሳለኝ )

በዚህ ርዕስ ሥር ባለፈው ሳምንት በይደር ካቆየሁት ተከታይ ጽሑፍ በፊት አንድ እርምት የሚያሻው ጉዳይን በአዲስ መስመር ላስቀድም፡፡

ሬዲዮ ፋና እና “አምደኞቹ”

ተመስገን ደሳለኝ
ስለፍትህ ሲባል ስርዓቱ ይፍረስ! ፪ (ተመስገን ደሳለኝ ) 1

በ1988 ዓ.ም በኤፈርት ባለቤትነት ስርጭቱን አሀዱ ያለው “ሬዲዮ ፋና”፣ ከምስረታው አንስቶ ዛሬም ድረስ ልክ እንደ በረሃው ዘመን ሁሉ የሥርዓቱ ቀኝ እጅና የርካሽ ፕሮፓጋንዳው ማስተላለፊያ ቱቦ ሆኖ መዝለቁ ለወዳጅም ለጠላትም የማያከራክር ገሀድ የወጣ ሐቅ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰኑ የግል ሚዲያዎች ላይ የርግማን ዘመቻ የታወጀ ይመስል ለተከታታይ ሳምንታት “ስመ-ጥር” ረጋሚዎችን ጣቢያው ድረስ ጋብዞ ማብጠልጠልና ማውገዙን ቀንደኛ ሥራው አድርጎ ይዞታል፡፡ በርግጥ ይህ ዘመቻ ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የፕሬስ ድርጅት በኩል በ“ጥናት” ስም የወጣው ውንጀላ ቅጥያ ሲሆን፣ በቅርቡ ኢቲቪ ሰርቶ እንዳጠናቀቀው የሚነገርለት ዶክመንተሪ ፊልም ደግሞ “ሳልሳዊ” ዘመቻ ሆኖ ለጥቆ የሚቀርብ መሆኑን የመረጃ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ሰሞነኛውን የፋና ዘመቻ ከተለመደው አቀራረብ የተለየ የሚያደርገው ከህወሓት ከበሮ መቺነት መሻገር የተሳነው ዛሚ ሬዲዮ ጣቢያን ከወከለው አቶ ዘሪሁን ተሾመ በተጨማሪ፣ የኢዴፓው አቶ ሞሼ ሰሙ እና የ‹‹ፎርቹ››ኑ ጋዜጠኛ ታምራት ወልደጊዮርጊስ በውጋ-ንቀል ስልት የርግማኑ ቡራኬ ሰጪ ሆነው መቅረባቸው ነው፡፡ ‹‹አዲስ አማኝ ከጳጳስ በላይ ልሁን ይላል›› እንዲሉ ሩቅ አላሚው የሕዳሴው ግድብ የሕዝብ ተሳትፎ አስተባባሪ ም/ቤት ምክትል ዳይሬክተር የሆነው ዛዲግ አብረሃም ሆነ ሚኒስትር ዴኤታው ሽመልስ ከማል የረከሰውን የአፈና መንፈስ ‹‹ለማቀደስ›› በቁርጠኝነት መሰለፋቸውን ሳንዘነጋ ማለት ነው፡፡ በርግጥ እነዚህ ሰዎች በቀጥታ ከስርዓቱ ህብስት ተቋዳሽ በመሆናቸው በዚህ ደረጃ ‹‹ማሸብሸባቸው›› ብዙም አያስገርምም፤ አስገራሚው ነገር ታምራት ወልደጊዮርጊስ ‹‹እንቁ›› እና ‹‹ፋክት›› መጽሔቶችን በአንድ ሰው የሚዘጋጁ አስመስሎ ከማቅረብም አልፎ፣ ማሕበረ ቅዱሳን የገጠመውን የመበተን አደጋን በተመለከተ የወጣውን ዘገባ እስከማውገዝ የደረሰበት ጽንፍ ነው፡፡

በወቅቱ ዛዲግ አብረሃ ሚዲያዎቹ እንዲደመሰሱ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ፣ ታምራትም የማሕበረ ቅዱሳን አባላት ተቋማቸውን ከመንግስታዊ አፈና መከላከል እንዳለባቸው የምትመክረውን የ‹‹ፋክት›› ዘገባ ቃል በቃል ጠቅሶ ሲያበቃ ‹‹ቋቅ እያለኝም ቢሆን ከዛዲግ አብረሃ ጋር የምስማማበት ጉዳይ ይህ ነው›› በማለት ከፕሬስ አፈናው ጎን መቆሙን አስረግጦ ተናግሯል፡፡ በአናቱም መጽሔቶቹ ‹‹አብዛኛው ህዝብ የሚፈልገውን መርጠው የሚዘግቡ ናቸው›› ያለበት አውድ ነቀፋ ይሁን ምስጋና ግልፅ ባይሆንም፣ ቢያንስ አምባገነኑን በረከት ስምኦን እና ጋሻ-ጃግሬዎቹን ከማስደሰት፤ ብዙሃኑን ግፉአን ማገልገል የተሻለ ብቻ ሳይሆን የተቀደሰ ተግባር ስለመሆኑ በረከትም በልበ-ሙሉነት እሰጥ-እገባ ሙግት የማይሞክርበት ነጭ እውነት እንደሆነ ታምራት ቢያስተውለው የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ግና፣ ሐቁ ይህ ቢሆንም ወንድም ታምራት ራሱ ብቻ ሙያውን አክብሮ የሚሰራ ጋዜጠኛ፤ ሌላውን ደግሞ ኃላፊነት የማይሰማው ከማድረጉም በዘለለ፣ እነዚህን ሚዲያዎች ከአርበኝነት ጋር አዳብሎ ለማውገዝ መሞከሩ የተኮረኮርኩ ያህል ሳልወድ በግድ ያሳቀኝ ጉዳይ ሆኖብኛል፡፡ ምክንያቱም በእኔ እምነት በኢትዮጵያችን ላለፉት ሁለት ዓስርታት ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ለሕግ የማይገዛ እና በሙስና የተጨማለቀ ሥርዓት ከመሆኑ አኳያ በጋዜጠኝነትም ሆነ በየትኛውም ሙያ ለሚንፀባረቅ አርበኝነት የተሻለው ብያኔ፣ ሀገርን ከፍርሰት መታደግ ማለት ነውና፡፡

ደግሞም በዚህች ሀገር ዝግመታዊ-ሞት ፊት ላይ ቆሞ የኮሪደር ሐሜቶችን ከመዘገብ በእጅጉ ለቆና ረቆ በመሻገር የውደቀታችን ምክንያት የሆነውን አገዛዝ በሕዝባዊ እምቢተኝነት ማስወገድ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ብዙ ጊዜ በእንዲህ አይነት ውይይቶች ላይ ሚዛናዊ ለመሆን ይሞክር የነበረው ታምራት (ለዚያኛውም አቋሙ በግሌ አመስግኘው አውቃለሁ)፣ ማሕበረ ቅዱሳንን በተመለከተ የወጡ ዘገባዎችን ባወገዘበት አዛው ሬዲዮ ጣቢያ ስቱዲዮ ውስጥ ተቀምጦ፣ ሽመልስ ከማል አንድ እንኳ የታሰረም የተሰደደም ጋዜጠኛ እንደሌለ ጠቅሶ አይኑን በጨው አጥቦ ሲከራከር ትንፍሽ አለማለቱ የቀራኒዮ መንገድ እና የንግድ ስራ ፍፁም የማይተዋወቁ ሆድና ጀርባ መሆናቸውን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡

በነገራችን ላይ በዚህ ውይይት የአደባባይ ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እና የኢትዮ-ምህዳሩ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ መሳተፋቸው ከሞላ ጎደል ከዘመቻው ጀርባ ያለውን ኢህአዴጋዊ ሴራ አጋልጦታል ብዬ አስባለሁና ባርኔጣዬን ከፍ አድርጌ አክብሮቴን ልገልፅላቸው እወዳለሁ፡፡ በተለይ ጉምቱ የፍልስፍና መምህር ዶ/ር ዳኛቸው፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶችን ብቻ ሳይሆን የሥርዓቱን ሃሳብ አልባነት ለመሞገት ለሚያደርገው አበርክቶ በድጋሚ አመሰግነዋለሁ፡፡…ከዚህ ሁሉ ሰበር ሐተታ በኋላ ወደ ክፍል ሁለቱ ዋናው አጀንዳችን ዘልቀን፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ለፍትሕ መበላሸት የዳኝነት ሥርዓቱ ብቻ ሳይሆን ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግም የአንበሳውን ድርሻ ስለመውሰዳቸው ለማመልከት እሞክራለሁ፡፡
ፖሊስ ሲባል…

…የተወሰኑ የፌደራል ፖሊስ አባላት ዝሆን አድነው እንዲያመጡ በአለቃቸው ይታዘዛሉ፡፡ ከሰዓታት በኋላም ፖሊሶቹ ግዳያቸውን አምጥተው ለአለቃቸው ያስረክባሉ፡፡ ይሁንና አለቅየው ግዳያቸውን ባየ ጊዜ ባለማመን ዓይኖቹ ፈጥጠው ሊወድቁ ደረሱ፤ ለምን ቢሉ፣እሱ ያዘዛቸው ዝሆን፣ እነርሱ ያመጡት ግን ሁለት ጥርሱ የወለቀ፣ አንድ ቀንዱ የተሰበረ፣ አንድ አይኑ የጠፋ፣ ምላሱ የተቆረጠ… ብቻ ምን አለፋችሁ በድብደባ ብዛት ሊሞት የተቃረበ ፍየል ነበርና፡፡ እናም በቁጣ፡-
‹‹ዝሆን አይደል ወይ አምጡ ያልኳችሁ?›› ሲል ያፈጥባቸዋል፤
‹‹ጌታዬ፣ ዝሆን ነኝ ብሎ እኮ አምኗል!›› በማለት ቆፍጣና ፖሊሶቹም በሕብረት መለሱለት፡፡

…ይህችን ቀልድ ለዚህ ንዑስ-ርዕስ መግቢያ ያደረኩት፣ በነባሩ ባሕል እንዲህ ያሉ ጉዳዮች በቀልድ፣ በግጥም፣ በምሳሌዊ አባባል… መገለፃቸው የተለመደ ከመሆኑ አኳያ ስለሀገራችን የፖሊስ አባላት ስንነጋገር ከቀልዷ ጀርባ መራራ እውነት ማድፈጡን አምነን እንድንቀበል ገፊ-ምክንያቶች በመኖራቸው ነው፡፡

እንደሚታወሰው በየትም ሀገር የተፈፀመ ወንጀል ከዐቃቤ ሕግም ሆነ ከፍርድ ቤት በፊት በፖሊስ የምርመራ ሂደት ውስጥ ማለፉ የግድ ነው፡፡ የዘርፉ ምሁራን ‹‹የፖሊስ ምርመራ ሳይንስ ነው›› እንዲሉ ሙያው ክህሎት የሚጠይቅ መሆኑ አይካድም፡፡ ይሁንና ተጨባጩ እውነታ የሚነግረን የ83ቱን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ በዘርፉ እንዲሰማሩ የተደረጉት አብዛኞቹ መርማሪዎች ድርጅቱን ለቡሕተ-ሥልጣን ያበቁ ታጋዮች መሆናቸውን ነው፡፡ በርግጥም በረባውም ባልረባውም ወንጀል ተጠርጥሮ እጃቸው የገባውን ሁሉ አፈር-ድሜ በማስጋጥ የ‹‹ሚመረምሩበት›› መንገድ ኩነቱን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ይህ ሁናቴም ይመስለኛል የፖሊስን ሙያ ከሳይንሳዊ ጥበብ ወደ አሳረ-ፍዳ ማሳያ አውርዶ የተጠላ ያደረገው፡፡ ለዚህም ኩነና በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ የሩቁን ትተን የቅርቡን እንኳ ብንመለከት የህዝበ-ሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ችሎት ላይ ቀርበው በማዕከላዊ ምርመራ እስር ቤት መርማሪ ፖሊሶቹ ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተገርስሶ ሲያበቃ ምን ያህል አካላዊና መንፈሳዊ ስቅየት እንደደረሰባቸው ከተናገሩት መሀል የሚከተሉትን በዋናነት እናገኛለን፡-

‹መርማሪ ፖሊሶቹ እንቅልፍ ከልክለው የተዳከመ አካልን ልብስ አስወልቆ እርቃን በማስቀረት መግረፍ፣ የዘር ፍሬ ብልት ላይ በውሃ የተሞላ ጠርሙስ ማንጠልጠል፣ በኤሌክትሪክ ገመድ የውስጥ እግርን መግረፍ፣ ጢምን በአሰቃቂ ሁኔታ መንጨት፣ እጅና እግርን ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ ለረጅም ሰዓታት ማሰር፣ ጭንቅላትን በቆሸሸ ውሃ ውስጥ መንከር፣ ከ24 ሰዓታት በላይ ቀጥ ብሎ እንዲቆሙ ማስገደድ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ሾክ ማደረግ እና የመሳሰሉት፡፡› በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትም በተደጋጋሚ ጊዜ በተለይም ከደርግ ስርዓት ጀምሮ ዋነኛ ማሰቃያ በሆነው ማዕከላዊ የምርመራ ጣቢያ የሚፈፀመውን ተግባር በሪፖርት መልክ ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡ ከወራት በፊት ሂዩማን ራይትስ ዎች ይህንን የስቃይ ጣቢያ አስመልክቶ ‹‹They want a confession: Torture and Ill-treatment in Ethiopia’s Makelawi Police Station›› በሚል ርዕስ ባሰራጨው ሪፖርት በጣቢያው የሚፈፀመውን ግፍ ከመግለፁም በተጨማሪ፣ ታሳሪዎች እንዴት ባለ ሁኔታ ‹‹የእምነት ቃል››እንደሚሰጡ አመላክቷል፡፡ ለማሳሌም አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ፤ ነገር ግን በጣቢያው ታስሮ የነበረ ሰው ገጠመኝን ከሪፖርቱ እንደሚከተለው ልጥቀሰው፡-

‹‹ወደ ጣቢያው የገባሁ ቀን ኢ-ሜይል አድራሻዬን ከነምስጢር ቁልፉ እንድሰጣቸው ጠየቁኝ፤ ሰጠኋቸው፡፡ በውስጡም ምንም አይነት የፖለቲካ አንድምታ ያለው መልዕክት አልነበረም፡፡ ይሁንና ከሶስት ቀን በኋላ በዛው አድራሻዬ ‹ከኦነግ የተላከ መልዕክት ተግኝቷል› ብለው ጠየቁኝ፡፡ ሆኖም ነገሩን እንደማላውቅ እያወቁ ‹ለእኔ የተላከ መልዕክት ነው› ብለህ ፈርም ሲሉ አዘዙኝ፡፡ እኔም ከታሰርኩ በኋላ የተገኘ በመሆኑ አልፈርምም አልኩ፡፡ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ድብደባ ፈጽመውብኛል፡፡››

በርግጥም የሀገሪቱን የወንጀል ምርመራ ስራን ተነቃፊና ተወጋዥ ያደረገው በእውቀት ማነስ፣ በስቅየት (በቶርቸር) እና በሙስና የተተበተበ መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ በአደረጃጀቱም ነው፤ ለምሳሌ ከፌዴራልና ክልል ፖሊስ በተጨማሪ ግምሩክ የራሱ እስር ቤት፣ የራሱ መርማሪና ዐቃቢ-ሕግያን አሉት፡፡ ፀረ-ሙስናም እንዲሁ የጠረጠረውን ሁሉ አስሮ ይመረምራል፤ ይከስሳልም፡፡ አንዳንድ ምንጮቼ እንዳቀበሉኝ መረጃ ከሆነ ደግሞ በሽብር ጉዳይ የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን (ቡድኖችን) ራሱን ችሎ አስሮ የሚመረምር እና የሚከስ ተቋም በቅርቡ በአዋጅ ሊቋቋም ዝግጅቱ ተጠናቅቋል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ መዋቅራዊ ትስስር በሌለው ሁኔታ በፖሊስ ስራ የመሰማራታቸው ምስጢር፣ አንድም ሳይንስ እንጂ አሳር ዕውቀት ባለመጠየቁ፣ ሁለትም ንፁሀንን ከወንጀለኛ ጋር ደባልቆ ለመውቀጥ ስለሚመች፣ ሶስትም ስርዓቱ ተቀናቃኞቹን ለመደፍጠጥ በ‹‹ሕጋዊ አሠራር›› ሽፋን ተጨማሪ ጡንቻ እንዲኖረው ማስቻሉን በማስላት ይመስለኛል፡፡ በዚህ አይነት ምርመራ የተገኙ መረጃዎችም ፍርድ ቤት ቀርበው እንደሕጋዊ ማስረጃ እየተቆጠሩ እስከ ዕድሜ ልክ የእስር ቅጣት ሲያስበይኑ ደጋግመን ተመልክተናል፡፡

ይህም ሰፊው ሕዝብ በፍርሃት እየተርበደበደ ሰጥ-ለጥ ብሎ እንዲገዛ፤ አሊያም እንደ ጥንቸሊቷ አገር ጥሎ እንዲጠፋ ለማድረግ ያለው ጉልበት በግልፅ ተተግብሮ የታየ የሥርዓቱ የዕለት ተዕለት ምግባር ነውና ከዚህ በላይ ትንታኔ አያሻውም፡፡ ከዚህ ይልቅ የጥንቸሏ አፈ-ታሪክ ተብሎ የሚነገረው ነባራዊ እውነታውን በሚገባ ያንፀባርቃልና እንደወረደ ልጥቀሰው፡-…ከለታት አንድ ቀን አንዲት ጥንቸል ከመጣባት የመዓት ናዳ ማምለጥ የምትችለው ቀዬዋን ጥላ ስትሰደድ እንደሆነ ብቻ በማመኗ ልቧ እስኪፈነዳ ድረስ ጋራ-ሸንተረሩን እያቆራረጠች ስትሮጥ ድንገት ከሀገሪቱ ድንበር አጠገብ ከሚኖር አንድ ግድንግድ ጦጣ ጋር ፊት-ለፊት ተፋጠጠች፣ በድካም ዝላም ቁና ቁና እየተነፈሰች ‹‹ይህ ጦጣ ፖሊስ ይሆን እንዴ?›› ብላ እየተጠራጠረች ማምለጫ ዘዴ ስታውጠነጥን፣አያ ጦጣ፡- ‹‹ወይዘሪት ጥንቸል፣ ለመሆኑ ምን የከበደ ጉዳይ ቢገጥምሽ ነው እንዲህ ልብሽ እስኪፈርስ ድረስ የምትሮጪው?›› ሲል ይጠይቃታል፤‹‹የዝሆን ዘር በሙሉ ከያለበት ተለቅሞ በቁጥጥር ስር እንዲውል አስቸኳይ ትዕዛዝ መውጣቱን እስካሁን አልሰሙም እንዴ?›› ብላ በጥርጣሬ ትክ ብላ እያስተዋለችው ጥያቄውን በጥያቄ ስትመልስለት፣

አያ ጦጣ፣ እጅግ በጣም ከመደነቁም በላይ ግራ ግብት እያለው ‹‹ታዲያ አንቺ ምን አገባሽ፤ ዝሆን አይደለሽ?›› ሲል መልሶ ይጠይቃታል፤ ‹‹ወይ አያ ጦጣ! ዝሆን ባልሆንስ?! አለመሆኔ ተጣርቶ እስክለቀቅ ድረስ ለምን ብዬ ታስሬ ልገረፍ? ደግሞስ በዱላ ብዛት ዝሆን ነኝ ብዬ ያመንኩ እንደሆነ መጨረሻዬ ምን ሊሆን እንደሚችል አስበውታል? ይልቅ እርስዎም አይሞኙ! በጊዜ አብረውኝ ከመዓቱ ዘወር ብለው ቢቆዩ ይሻሎታል፤ ኑ እንሂድ›› ብላ በፍርሃት የተዋጠችው ምስኪኗ ጥንቸል ሩጫዋን ቀጠለች፡፡ …በእኛይቱ የመከራ ምድርም፣ እኛና ኢህአዴግ በዚህ ደረጃ ፍፁም የማንተማመን፣ በጎሪጥ የምንተያይ ሆነን ከቀረን እንደ ዘበት ሃያ ምናምን አመታት ተቆጥረዋል፡፡

ዐቃቢ ሕግ ሲባል….

በዚህ አውድ ሌላው ተጠቃሽ ተቋም፣ ፖሊስ በ‹‹የትም ፍጪው…›› መንገድ ያመጣለትን ‹‹መረጃ›› ሳያላምጥ በመዋጥ ለክስ የሚያበቃው ዐቃቤ ሕግ ሲሆን፣ ለአጠቃላዩ የፍትሕ መዛባትና መጨማለቅም በዕኩል ደረጃ ተጠያቂ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ለአደባባይ ያልበቁ አያሌ የዐቃቢ-ሕግያን ሸፍጦችን ትተን በድህረ ምርጫ 97 የተከሰተውን አለመግባባት ተከትሎ ለእስር ከተዳረጉት የቅንጅት ለአንድነትና ለፍትህ ፓርቲ አመራሮች ጋር የተያያዘውን እንመልከት፡፡ እንደሚታወሰው መጀመሪያ የቀረበባቸው ክስ ‹‹የዘር ማጥፋት›› የሚል የነበረ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን በተመለከተ ለረዥም ዓመታት ጥናት ያደረገው አሜሪካዊ ፕ/ር ዶናልድ ሌቨን፣ አቶ መለስን ‹‹ዘር ማጥፋት እኮ ቀልድ አይደለም›› በማለት አጥብቆ ከወቀሰው በኋላ ክሱ ‹‹ሕገ-መንግስቱን በኃይል የመናድ እና ዘር የማጥፋት ሙከራ›› ወደሚል መቀየሩን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ይናገራሉ፡፡

የሆነው ሆኖ ጉዳዩ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ዐቃቢ-ሕግያኑ በተከሳሾቹ ላይ በ‹‹ማስረጃ››ነት ካቀረቡት ሰነዶች መካከል የአባላዘር በሽታ የህክምና ምርመራ ወረቀትን ጨምሮ፣ ሀሰተኛ (ፎርጅድ) ደብዳቤዎች እና ከክሱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው የቪዲዮ ፊልሞች እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ‹‹የቃሊቲው መንግስት›› በሚለው መጽሐፉ፣ በጥቅምት 25/1998 ከ‹‹አዲስ አበባ ፖሊ ከፍተኛ ክሊኒክ›› ቢኒያም (የአባቱም ስም ተጠቅሷል) ለተባለ ሰው የአባላዘር ምርመራ አድርጎ የተሰጠው የሕክምና ምስክር ወረቀት ‹‹ሕገ-መንግስቱን በኃይል ለመናድ ሞክረዋል›› በተባሉት የቅንጅት መሪዎች ላይ በ‹‹ማስረጃ››ነት መቅረቡን ከመጥቀሱም በላይ ሰነዱን በገጽ 444 ላይ እንዳለ በማተም ለታሪክ ምስክርነት አብቅቶታል፡፡ መቼም ይህ ሁናቴ አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያን የወረረው የአሜሪካንን ተልዕኮ ለማስፈፀም ነው? ተብሎ ለቀረበበት ወቀሳ አከል ጥያቄ፣ አሜሪካ የምትሰጠው ዕርዳታ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን መከላከል ላይ ያተኮረ እንደሆነ ከገለፀ በኋላ ‹‹ሶማሊያ ውስጥ ደግሞ በኮንዶም አንዋጋም!›› ብሎ እንደመለሰው አይነት ቧልት አቅልለን እንዳናልፈው የሚያግደን ጉዳዩ ‹‹አንድ ንፁህ በሀሰት ከሚፈረድበት፣ ሺ ወንጀለኞች በነፃ ቢለቀቁ ይመረጣል›› ከሚባልለት ፍትሕ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ነው፡፡

በጥቅሉ ላለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ለእስር የተዳረጉ ንፁሀንም ሆነ በሙስና የተወነጀሉት ላይ እየቀረበ ያለው ክስና ማስረጃዎችን ሥራዬ ብሎ ለመረመረ ሰው፣ የፍትሕ መዛባቱን ደረጃ ፍንትው አድርገው ያሳዩታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምሳሌም ከወራት በፊት ‹‹በገቢዎችና ግምሩክ ባለሥልጣን የአ/አ ኤርፖርት ቅ/ጽ/ቤት የመንገደኞች ጓዝ የሥራ ሂደት መሪ›› ባለሥልጣን ላይ የተመሰረተውን ክስ ብናየው እንዲህ የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡-

‹‹ከአሜሪካና ከአውሮፓ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መንገደኞች ዕቃዎቻቸውን አስፈትሸው ቀረጥና ታክስ ሊከፈልባቸው የሚገቡት ላይ መክፈል እንዳለባቸው ኮንትሮባንድም ከሆነ እንደሚወረሱ እያወቀ ማንነታቸውና ብዛታቸው ያልተለዩ መንገደኞች ዕቃቸው እንዳይፈተሽ ማድረግ፡፡››

መቼም ይህ አይነቱ ክስ በምድራችን የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ማንነታቸውና ብዛታቸው፣ ቀኑና ወሩ ተለይቶ ባልታወቀበት ጊዜ ከመንገደኞች ጋር በመመሳጠር የተሰራ ወንጀል አለ ብሎ ክስ መመስረት ከጥንቆላ በምንም ሊለይ አይችልምና ነው፡፡ ኧረ ለመሆኑስ! የሰዎቹ ቁጥርና ያስገቡት የዕቃ ዓይነት ካልታወቀ ባለሥልጣኑ ‹‹ፈፀመ›› በተባለው ሙስና ሀገሪቱ ከቀረጥ ማግኘት የነበረባትና ያሳጣት ገቢ ምን ያህል ነው? አንድ ብር? አንድ ሺህ? አንድ ሚሊዮን ወይስ አንድ ቢሊዮን? ይሁንና የተከሳሽ ጠበቆች ክሱ በዚህ መልኩ መቅረቡን በፍርድ ቤት በመቃወማቸው ዐቃቢ ህግ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ይታዘዛል፡፡ ተሻሽሎ የቀረበው ደግሞ ባጭሩ እንዲህ ይጠቀሳል፡-

‹‹ቀኑና ወሩ ተለይቶ ባልታወቀበት በ2002 ዓ.ም ዜግነታቸው አሜሪካዊ የሆነ ሁለት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ሁለት ሻንጣ የመኪና መለዋወጫ ከተያዘባቸው በኋላ አስለቅቋል፡፡ ግንቦት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ሳሙኤል ታፈሰ ከዱባይ ሀገር ያስገቡት የመኪና መለዋወጫ ዕቃ እንዲያልፍ ሲያስደርግ በሌላ ባልደረባው ተይዟል፤ ከሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም እስከ ነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ባለው ጊዜ ከተለያዩ ሀገራት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ መንገደኞች ሠልፍ ይዘው እያለ ከዚህ መለስ ያሉት መንገደኞች ሻንጣቸውን ሳያስፈትሹ፣ ቀረጥና ታክስ ሳይከፍሉ እንዲያልፉ ማድረግ፡፡››

እነሆም እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ሀገሪቱ እንዲህ ባሉ የሕግ ባለሙያዎች ስር ወድቃለችና ‹እግዚኦ በሉ›፡፡ እግዚኦታው ግን የሁለቱ እንስቶች ስም እና ያሳለፉት ዕቃ ተመን ባለመታወቁ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም በጽሁፍ በቀረበ ክስ ላይ ከሠልፈኞቹ መካከል ‹‹ከዚህ መለስ ያሉት መንገደኞች…›› ተብሎ ድፍን ያለ ነገር ‹‹መረጃ›› ሆኖ መቅረቡ ነው፡፡ ግና፣ ይህ ምን የሚሉት መረጃ ነው? ያውም ለፍርድ ቤት! እናም ጥያቄያችን እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡- የትኛው ሠልፍ ጋ ያሉ መንገደኞች ናቸው በሕገ-ወጥ መንገድ ያለፉት? የቀኙ? የመሀለኛው? የግራው? የሠልፉስ ርዝመት ምን ያህል ነው? የሠልፈኞቹስ ብዛት? አምስት? ሀምሳ ወይስ አምስት መቶ? በርግጥ ክሱ ለአንዱም ጥያቄያችን ምንም አይነት ምላሽ አይሰጥም፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ የሚያወሳስበው ደግሞ ይህ ‹ሾላ በድፍን› የሆነ ወንጀል የተፈፀመው ከሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም እስከ ነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም ድረስ በየቀኑ መሆኑ ነው፡፡ መቼም እነዚህ ሁሉ ጉዶች እውነት ከሆኑ በዚህች ሀገር፣ ማፍያ እንጂ መንግስት አለ ብሎ የሚመሰክር ደፋር ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡

በጥቅሉ የፖሊስም ሆነ የዐቃቢ-ሕግያኑና የዳኞቹ እንዲህ ሙያውን እና ተቋሙን የማራከስ አካሄድ ከአንድ ገፊ-ምክንያት የዘለለ ሌላ መነሾ የምናገኝለት አይመስለኝም፡፡ ይኸውም ሥልጣኑን ለማራዘም ምንም ነገር ከማድረግ የማይመለሰው ኢህአዴግ፣ በዋናነት ዋስትና የሚሆኑትን ፖሊስ፣ ዐቃቢ-ሕግ እና ፍርድ ቤቶችን በታጋዮች እና በካድሬዎች በመሙላት፣ በተለየ የፖለቲካ አቋም ከፊቱ የሚቆሙትን እየጨፈለቀ ለማለፍ አስልቶ የቀመረው በመሆኑ ነው፡፡

ኦርዌላዊ ስርዓት

የዚህን ስርዓት ቅጥ ያጣ አምባገነንነት ማብራራት አድካሚ እየሆነ ነው፡፡ የሚፈርሰው ማህበራዊ ዕሴት፣ የሚናደው ሀገራዊ ማንነት፣ እንደ አምባሻ የሚቆራረሰው መሬት፣ አልፎ ተርፎም እየጠፋ ያለው ትውልድ እና መሰል ጉዳዮችን ጠቃቅሶ፣ የነገይቷ ድህረ-ኢህአዴግ ኢትዮጵያ በገዢው ስብስብ ክፉ መዳፍ ሳቢያ ህልውናዋ ከገደሉ ጠርዝ ላይ ስለመቆሙ ማተት መደጋገም ነውና እንለፈው፡፡ ይህም ሆኖ ግን አገዛዙ በፍትሕ ስርዓቱ በኩል የሚያካሂዳቸው ዘግናኝ ድርጊቶች የመዓቱን ጊዜ ቅርብ የሚያደርጉ መሆናቸውን ማስታወስ (የሚሰማ ባይኖርም) የዜግነት ግዴታ ይመስለኛል፡፡ የአሜሪካ መንግስት ስቴት ዲፓርትመንትን ጨምሮ፣ ቁጥራቸው የበዛ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማት በተደጋጋሚ እንደዘገቡት፣ የዚህች አገር ምስኪን ልጆች በማይታወቁ ድብቅ እስር ቤቶች ጭምር መከራ እየወረደባቸው ነው (እኔ ይህንን ጽሑፍ በማዘጋጅበት፣ እናንተም አሁን በምታነቡበት ሰዓትም ቢሆን ለይተን በማናውቃቸው በርካታ የስቃይ እስር ቤቶች፣ በእልፍ አእላፍ ወገኖቻችን ላይ ግፍ እየተፈፀመ መሆኑን መካድ አይቻልም)፡፡

እነዚህ ማሰቃያ ቦታዎች ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከደቡብ እስከ ሰሜን ባሉት የሀገሪቱ አካባቢዎች ተሰበጣጥረው የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በነዚህ ካምፖችም የሚታጎሩት ዜጐች በዋነኝነት ከገዢው ግንባር የተለየ (የሚቃረን) ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው ስለመሆኑ የተቋማቱ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም ብረት አንስተው የሚታገሉ ኃይሎች የተነሱባቸው ክልል ተወላጆችን ማሰቃያ ካምፖቹን የሚያደልቡ ‹የተመረጡ› መከረኞች ሆነዋል፡፡ ኢህአዴግ እንጥፍጣፊ ለሕገ-መንግስቱ አክብሮት ቢኖረው፣ የዜጎቹ ወንጀሎች የቱንም ያህል ቢከፉም እንኳ፣ በግልጽ የፍርድ ሂደት ተገቢ የሆነ ተመጣጣኝ ቅጣት ማግኘት በተገባቸው ነበር፡፡

የዚህ አይነቱን የፍትህ ምኩራቡ አስፀያፊ እርክስናን፣ በግላጭ የሚያሳየን ሌላኛው ጭብጥ በኦጋዴናውያኑ ላይ እየወረደ ላለው ግፍ ተጠያቂ ተቋምም ሆነ ባለሥልጣን እስካሁን ድረስ አለመኖሩ ነው፡፡ የስዊድናውያኑን ሁለት ጋዜጠኞች መታሰርና በይቅርታ መፈታት ተከትሎ፤ በክልሉ ያለው ፍርድ ቤት ስለማያውቀው ዝርፊያ፣ እስርና ግድያ በምስልና በድምፅ የተደገፉ ማስረጃዎች ከጥቂት ወራት ወዲህ ተሰምተዋል፡፡ የአካባቢው የቀድሞ ባለስልጣን ወደስዊድን በተሰደደ ማግስት ያቀረባቸውን እነዚህን ማስረጃዎች ኢህአዴግ እንደለመደው የኦብነግ ከንቱ ውግዘት አድርጎ ማለፍ አይቻለውም፡፡ በዚህ ሰው ማስረጃም ሆነ ክልሉን ባጠኑ ምሁራንና ተቋማት ዘገባዎች መሰረት የጠቀስኳቸው ዘግናኝ ክስተቶች ማህበረሰቡን እየናጡት ነው፡፡

በተለይ ልዩ ሚሊሺያ የሚባለው ሕገ-ወጥ ሀይል፣ በሱማሌ ክልል ጎዳና ላይ ያሻውን እያነቀ እንዲያስር፣ ልጃገረዶችን እንዲደፍር፤ ገፋ ካለም በጥይት አረር እንዲረሽን የተተወበት አግባብ የሚመሰክርልን የፍትሕ ስርዓቱ ድምጥማጡ ስለመጥፋቱ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መልኩ በሌሎቹም የሀገራችን ክፍሎች ካለዘውግ፣ ሐይማኖት እና ዕድሜ ልዩነት፤ ካለፍርድ ቤት እውቅና እየተፈፀመ ያለው ግፍ፣ የፍትህ ተቋሙ የዜጎችን ህልውና ለመጨፍለቅ ከገዢዎች ጋር በጥብቅ የተጋመደ ስለመሆኑ ያስረግጡልናል፡፡ እንግዲህ ፍትሕና ርትዕ የሰማይ ላይ ሩቅ ተስፋዎች እንዲሆኑብን የፈቀደውን ስርዓት እስከ መቼ መታገስ ይቻለናል? ስለርትዕ በኢትዮጵያ ምድር ላይ መስፈን ሲባልስ፤ የኢህአዴግን ቅፅር በህዝባዊ ሰላማዊ አብዮት ብንንደው፣ መስዋዕትነታችን ሀገርን ከመዓት ለማዳን ሲባል በፈቃደኝነት የሚከፈል ትውልዳዊ ግዴታ አይደለምን?! (በቀጣዩ ከአራጣ ማበደር ወንጀል እስከ መንግስታዊ ሙስና ላሉ ጉዳዮች እና ለፍትሕ ሥርዓቱ ሞቶ መቀበር ማሰሪያ አበጅቼ አጀንዳውን ለጊዜው እደመድመዋለሁ)

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

አዲስ አበባ

 

Latest from Blog

ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop