April 8, 2014
32 mins read

ስለፍትሕ ሲባል፤ ሥርዓቱ ይፍረስ! (ተመስገን ደሳለኝ)

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ (አዲስ አበባ)

ባለፉት አራት አስርታት ሀገሪቱ አያሌ ተግዳሮቶችን መጋፈጧ ባይዘነጋም፤ በተለያየ ጊዜ ሚሊዮኖችን ካረገፈው አሰቃቂው ረሃብ በማይተናነስ መልኩ ሕዝቦቿን ዋጋ ያስከፈለ ጉዳይ ቢኖር የፍትሕ አለመከበር ያስከተለው ሁለንተናዊ ምስቅልቅሎሽ ነው ብሎ ለመናገር የሚያስደፍሩ በርካታ ማሳያዎች አሉ።

የየካቲቱን አብዮት ጠልፎ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊው ደርግ፣ የፍርድ ቤት ደጆችን በጓጉንቸር ቆልፎ ሲያበቃ፣ የራሱ አባላት እጃቸውን እያወጡ ድምፅ በመስጠት በአፄው ባለስልጣናትንም ሆነ ግብረ-አበሮቹ በነበሩ መኮንኖች ላይ የሞት ቅጣትን ያህል የመጨረሻ ከባድ ውሳኔ የማሳለፍን አስደንጋጭ ክስተት ጨምሮ፤ ከከተማ እስከ ገጠር ያደራጃቸው የአብዮት ጠባቂዎችና የገበሬ ማሕበራት ከየቤቱ አንቀው እያወጡ “ነፃ እርምጃ” እንዲወስዱ፣ ከየእስር ቤቱ እየለቃቀሙ በጅምላ እንዲረሽኑ በአዋጅ የፈቀደበት ጊዜ የፍትሕ ምኩራቡ ፈርሶ በግላጭ የተቀበረበት ዕለት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በርግጥ ይህ የማን-አለብኝነት አረመኔያዊ አገዛዝ የታቃውሞውን ጎራ በማጠናከር ታሪካዊ ውድቀቱ እንዲፋጠን ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ እንደነበር ለመረዳት 17 ዓመታትን መውሰዱ አይዘነጋም።

“ፍትሕ አልባው አምባ-ገነናዊ የደርግ ስርዓት አማርሮ በርሃ ያስወጣንና ብሶት የወለደን የለውጥ ሃዋርያት ነን፤ በመቃብሩም ላይ ፍትሕ-ርትዕ የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት አገር እንመሰርታለ” በማለት ከበሮ ይደስቁ የነበሩት የያኔው “ነፃ አውጪዎች”ም፣ ደርግ አፍርሶ የቀበረውን የፍትሕ ምኩራብ አመዱን አራግፈው ቢያነሱትም፤ ባነበሩት አስመሳይ ሥርዓት በኩል በዘውግ ማንነት፣ በሙስናና በሙያ አልባ ዜጎች በክለው ክብር የለሽ ሲያደርጉት በጣት የሚቆጠሩ ወራት እንኳ አልፈጀባቸውም። ‹‹አዲስ ንጉስ አንጂ ለውጥ መቼ መጣ!›› እንዲል ከያኒው፤ ካስወገዱት የደርግ መንግስት ጋር ልዩነታቸው-ደርጉ ያልቻለበትን የተቃውሞ ድምፆች በአዋጅ እንዲንቀሳቀሱ በአንድ በኩል ፈቅደው፣ በሌላ በኩል መልሶ ለመጨፍለቅ የፍርድ ቤቶችን ባረኮት የመጠቀም ባለ ሁለት ገፅ ብልጠታቸው ብቻ ነው።

 

ይህ አይነቱ አገዛዝም ሥልጣን በያዘ ማግስት ሀገሪቱን እንዳሻው ለመርገጥ ሲቪል ቢሮክራሲውን ብቻ ሳይሆን የፍትሕ ስርዓቱንም በአምሳሉ አፍርሶ መስራት ነበረበት። ይሁንና ተቋሙን በዚህ መልኩ ለማዋቀር ጊዜ እንደሚያስፈልግ በመረዳቱ አሁን ድረስ በቂ መከራከሪያ ሊቀርብላቸው የማይችሉ ጉዳዮችን ከፍትሕ ሥርዓቱ ነጥቆ ሕገ-መንግስቱ ውስጥ በመዶል ለሌሎች ሰጥቷል። ለዚህ ደግሞ በቂ ማሳያ የሚሆነው፤ ሕገ-መንግስታዊነትን አስመልክቶ የሚነሱ የማጣራት ኃላፊነቶችን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መስጠቱ ነው። በርግጥ አንዳንድ የወቅቱ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ሕገ-መንግስቱ በተረቀቀበት ሰሞን፣ ከሕገ-መንግስቱ የሚጣረሱ አዋጆች፣ ክሶች አሊያም ኩነቶች ሲፈጠሩ፣ የማጣራቱ ኃላፊነት የፍርድ ቤት መሆን አለበት ሲሉ የተከራከሩ ድምፆች ነበሩ። ዳሩ ውሎ-አድሮ ምን እንደሚሰሩ አስቀደመው የሚያውቁት ታጋዮች፣ በዛ ካድሬ-ዳኞች ባላፈሩበት ወቅት እንዳሻቸው ሕገ-መንግስቱን እየናዱ ቢያስሩ፣ አዋጅ ቢያወጡና ቢያስፈርዱ ድጋፉን የሚሰጣቸው ተቋም፣ በኢሠፓውያን እንደተሞላ የሚጠረጥሩት ፍርድ ቤት ሳይሆን፣ እንደ ልብ ሊቆጣጠሩት የሚችሉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑን በመረዳታቸው፣ በፓርላሜንታዊ ሥርዓት ትመራለች በተባለች ሀገር ብዙም ባልተለመደ አኳኋን ሕገ-መንግስታዊ ትርጉም የሚሻቸውን ጉዳዮች የማጣራት ስራን ለዚሁ ምክር ቤት ሰጡት፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም በጥቂት ዓመታት ውስጥ የፍትሕ ተቋሙን በፓርቲ ፖለቲካ የተተበተበ፣ ለጉልበተኛ የሚገብር፣ ገንዘብ ሊገዛው የሚችል፣ ተቀናቃኝ ድምፆችን የማፈኛ መሳሪያ… አድርጎ የመቅረፅ ዓላማቸውን ማሳካት ችለዋል፡፡ በውጤቱም ተቋሙ የህግ የበላይነት የተደፈጠጠበት አድሎአዊና በየጊዜው ደካሞችን የሚያጠቃ ከሆነ እነሆ ከሁለት አስርት በላይ አስቆጥሯል።

 

የሆነው ሆኖ የሥርዓቱን ፍትሕ ረጋጭነት በተጨባጭ ፍፃሜዎች አስደግፎ ለማቅረብ ሁለት አብነቶችን እጠቅሳለሁ፡፡ ቀዳሚው የበርካታ ግፉአንን እሪታ ሲወክል፤ ተከታዩ ደግሞ የገዥዎቹን የሙስና እና የጓዳ ፖለቲካ ትስስሮች ይጠቁመናል ብዬ አምናለሁ።

 

የሞገስ ወልዱ-ጩኸት

ሰማይ ከመፍገጓ በፊት፣ ሁሌ ንጋት ላይ ኮተቤ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ተነስቶ፣ በእግሩ ሰከም ሰከም እያለ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ግድም ልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይደርስና ዋናው በር ፊት ለፊት ቆሞ ከአንድ ሰዓት ላላነሰ ጊዜ ‹‹ሌባ ዳኛ!›› እያለ ይጮኻል፡፡ ያፏጫል፡፡ ‹‹እናንተ ገላችሁኛል፤ ቀብራችሁኛል፤ አምላክ ፍርዱን ይሰጣል!›› በማለትም ተስፋው በሰማያዊው መንግስት ላይ ብቻ እንደሆነ ያውጃል፡፡ …ይህ ሰው እንደምን ያለ ከባድ በደል ቢደርስበት ይሆን ምሬቱ እንዲህ ጣራ የነካው?

 

አሳዛኙ የሞገስ ታሪክ እንዲህ ይጀምራል፡- በ1997 ዓ.ም የወላጅ እናቱን ወ/ሮ አስካለ ቢፋ ህልፈት ተከትሎ፣ ወንድሙ ኃይሉ ወልደአማኑኤል የወራሽነት ድርሻውን እንዲያካፍለው ክስ መስርቶ ሲያበቃ፤ ሶስት ጥያቄዎችን ለፍርድ ቤቱ ያቀርባል፡-

 

‹‹ንብረትነቱ የእናታችን የሆነ ቀበሌ 14/15 ውስጥ የሚገኝ 250 ካሬ ሜ. ላይ ያረፈ መኖሪያ ቤት፣ ሁለት ማሳ የእርሻ መሬት እና በንግድ ባንክ አራት ኪሎ ስላሴና መገናኛ ቅርንጫፍ የተቀመጠ መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብን ያካፍለኝ፡፡››

 

የከሳሽ ወንድም የሆነው ኃይሉም ፍርድ ቤት ቀርቦ ‹‹ቤትም ሆነ የእርሻ መሬት የሚባል ነገር የለም፤ በባንክ አለ ስለሚባለው ገንዘብም አላውቅም፤ እናታችን በሞተችበት ወቅት ስሟን ለማስጠራት ስል የእርሷ የነበረውን መሬት በ30 ሺህ ብር ሸጬ፤ ለአርባ፣ ለመንፈቅ፣ ለተስካር 10 ሺህ ብር ያወጣሁ ሲሆን፤ ቀሪውን 20 ሺህ ደግሞ ለወንድሜ ማረፊያ የሚሆን ቤት ሰርቼበታለሁ›› ሲል ምላሽ ይሰጣል፡፡ ችሎቱም ‹ቤቱንና የእርሻ መሬቱን በተመለከተ የቀረበ ማስረጃ አለመኖሩን› ገልፆ ‹የ30 ሺህው ጉዳይ ግን ያለይግባኝ ባይ ፍቃድ ወጪ የተደረገ ስለሆነ፤ የገንዘቡ ግማሽ 15 ሺህ ብር ድርሻው ስለሆነ እንዲሰጠው› በማለት ወስኖ መዝገቡን ይዘጋል፡፡

 

በውሳኔው እጅግ በጣም የተበሳጨው ሞገስ፣ ጉዳዩን በይግባኝ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይወስደዋል፤ ይግባኝ ሰሚውም ‹‹ቤቱ ይገኝበታል›› የተባለው ቀበሌ የእናታቸውን ማህደር እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ግና፣ ሀገሪቷ ኢትዮጵያ ናትና፤ ቀበሌው ማህደሩ መጥፋቱን፣ ሟችም በተከሳሽ ቤት ይኖሩ እንደነበረ በደብዳቤ ያሳውቃል፡፡ ሆኖም ቀበሌው ይህንን ምላሽ ከሰጠ ከ14 ቀን በኋላ ‹የቀድሞውን አስተዳደር ጠይቄ ያገኘሁት መረጃ ነው› በማለት ለፍርድ ቤቱ እንዲህ የሚል ሌላ ደብዳቤ ይልካል፡- ‹ወ/ሮ አስካለ የግል መኖሪያ ቤት የነበራቸው ሲሆን፣ ቤቱ ያረፈበት መሬት ለ‹‹ሪል እስቴት›› በመሰጠቱ፤ ምትክ ቦታና ስድስት ሺህ ብር ወስደዋል›። የሰው ምስክሮችም ቀርበው ሟች እናት ቤት ሰርተው እንደነበረ ያረጋግጣሉ፡፡ ይህም ሆኖ የወ/ሮ አስካለ ማህደር ከቀበሌው ‹‹ጠፍቷል›› በመባሉ ምንም አይነት ማስረጃ ስላልቀረበ የቀድሞው ውሳኔ በይግባኝ ሰሚው ችሎትም ሊለወጥ አልቻለም፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛው ፍርድ ቤት በር ላይ ቆሞ መጮኽን ስራዬ ብሎ ይዞታል፡፡ በርግጥ ከቀን ቀን አካላዊ መዳከም እየበረታበት መሄዱ በግልፅ ቢታይም የ40 ዓመቱ ጎልማሳ ሞገስ ወልዱ ዛሬም ከፍርድ ቤት ደጅ ቆሞ መጮኹና ማፏጨቱ የበርካታ ግፉአንን ድምፅ የሚወክል ይመስለኛል።

 

ይህ ጉዳይ የሚያሳየው፣ የመንግስት ደመወዝ እየተከፈላቸው በዜጎች ሕይወት ላይ ሊወስን የሚችል እንዲህ አይነቱን ማስረጃ ያለአንዳች ጭንቀት ‹‹ጠፋ›› ብሎ ለመናገር የሚደፍሩ፣ ስለሕዝብ ብሶትና ችግር ምንም ግድ የሌላቸው ካድሬዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም እንደ ሞገስ ያሉ የፍትሕ እጦት ረመጥ ሆኖ ያንገበገባቸው ምስኪኖች በአደባባይ ሲጮኹ ውለው፤ ሲጮኹ ቢያድሩ ‹‹ምን ይሆን ችግራቸው?›› ብሎ ለማድመጥ የሚሞክር አንድ እንኳን ባለሥልጣን መታጣቱንም ጭምር ነው። ‹‹ሳይሰሙ ቀርተው ይሆናል!›› ማለቱን ከባድ የሚያደርገው ደግሞ፣ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አካባቢ የሚተላለፉ መንገደኞችም ሆኑ ወደ ተቋሙ የሚመጡ ባለጉዳዮች ክስተቱን የማወቃቸው እውነታ ነው፡፡ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ሰዎችን የችሎት ውሎ ለመሰለል ከተከሳሾች ቀድመው የሚደርሱ የደህንነት ሰራተኞችም ሞገስን ለማወቃቸው እኔው ራሴ ምስክር ነኝ። በአናቱም ከዚህ ቀደም በሸገር ራዲዮ ‹‹ኧረ በሕግ›› የሚል ፕሮግራም ያዘጋጅ የነበረውና በአሁኑ ወቅት በ97.1 ኤፍ.ኤም ‹‹የእኔ መንገድ›› የተሰኘ በተመሳሳይ ጭብጥ ዙሪያ የሚያተኩር ፕሮግራም የሚያዘጋጀው በሳሉ የሕግ ባለሙያ ሰለሞን ጓንጉል፣ ይህንን ታሪክ ከአንዴም ሁለቴ ለአድማጭ አድርሶታል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ነው ከቀበሌ አንስቶ ላይ ድረስ ያሉ መንግስታዊ መዋቅሮችን የዘረጋውና የሚቆጣጠረው የኢህአዴግ አመራር አባላት፣ የሞገስን ጩኸት ‹‹አልሰሙም›› ማለቱን ከባድ ያደረገው (በነገራችን ላይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ግቢ ለአስር አመት ያህል በየቀኑ እየተመላለሱ የሚቆሙ አንዲት አዛውንት እና በፍትሕ ሚኒስቴር በር ላይ ቆማ መዋል ከጀመረች ስድስት ዓመት ያለፋት ራሄል የተባለች አቤት ባይ እንስት… መኖራቸውን አልዘነጋሁም)

 

ሙስና እና የጓዳ ፖለቲካ ትስስሮሽ

አገሪቷ በዚህ ሁሉ መፍትሔ እጦትና በፍትሕ መዛባት እየተመሰቃቀለችና በሕዝቦቿም ዋይታ እየተናወፀች ቢሆንም፤ መጽሐፉ ‹‹ዓይን አላቸው አያዩም፤ ጆሮ አላቸው አይሰሙም›› እንዲል፤ ገዥዎቻችን ይህን መሰሉን የድሆችና የአቅመ ደካሞች ብሶት መስማትን ፍፁም አይሹም። እነርሱ የታጋሉትም ሆነ የሚሰሙት አለቆቻቸውንና ባለፀጋዎችን ብቻ እንደሆነ ከሚያሳዩን በርካታ ማስረጃዎች መሃል ለአብነት አንድ ምሳሌ ላቅርብ፡-

 

ጉዳዩ በሙስና ተጠርጥሮ በእስር ላይ ከሚገኘው የቀድሞ ገቢዎችና ጉምሩክ ዳይሬክተር መላኩ ፈንቴ ጋር ይያያዛል፡፡ ከዚህ ሰው ሃያ አንድ ገፅ ከፈጀ የእምነት ክህደት ቃል ውስጥ ኮነ ምህረቱ የተባለ ግለሰብ በአራጣ ማበደር ተጠርጥሮ ከተያዘ በኋላ ‹‹እነአየለ ደበላ ለዳኛ ጉቦ ሰጥተው በዋስ ከእስር ተፈትተው፣ ከሀገር ለመውጣት ያስባሉ›› የሚል ‹‹መረጃ›› በመስጠት መተባበሩን ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ እንደነገረው ገልፆ፣ ከእስር እንዲለቀቅ መደረጉን እናገኛለን፡፡ መቼም በሙስና ወንጀል ከተጠያቂነት የሚድን ተከሳሽ የሚሰጠው መረጃ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ለመጠየቅ የሚጠቅም ሲሆን እንጂ፤ እንዲህ ባለ ከዋናው ክስ ጋር በማይዛመድ ተራና የአሉ-ባልታ ወሬ አለመሆኑን እነገብረዋህድና እነመላኩ ቀርቶ ማንኛውም መንገደኛ እንኳ ሊጠፋው አይችልም፡፡ አውቆ የተኛ… እንደሚባለው ካልሆነ በቀር።

 

የሆነው ሆኖ ከመላኩ ፈንቴ የእምነት-ክህደት ቃል ትኩረት የሚስበው፣ ግለሰቡ በዚህ መልኩ ከሱ ተነስቶለት ከእስር ከተፈታ በኋላ ንብረቱና የባንክ ሒሳቡ መታገዱን አስመልክቶ የተፈጠረው ኩነት ነው፡፡ አቶ መላኩ ጉዳዩን ለመርማሪዎቹ ሲያብራራ ቃል-በቃል እንዲህ ነበር ያለው፡-

 

‹‹አቶ አባይ ፀሀዬ እና አቶ ደመቀ መኮንን ደውለው ‹ግለሰቡ አቤቱታ እያቀረበ ነው፡፡ ለምን አታዳምጡትም? ሲሉኝ፤ እኔም ከዚህ በኋላ ነው ግለሰቡን እቢሮዬ አግኝቼ ከላይ በገለፅኩት ሁኔታ እንዲስተናገድ ያደረኩት።››

 

እነዚህ ሰዎች ‹‹ነፃ አወጣነው›› የሚሉትን ሕዝብ ለስቃይ ዳርገው፣ ጥቂት ባለፀጎችን ብቻ ለማገልገል የቆሙ መሆናቸውን ለማስረገጥ ከዚሁ የእምነት-ክህደት ቃል አንድ ማሳያ ልጨምር፡- ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የተባለ የአዲስ ልብ ህክምና ክሊኒክ ባለቤት ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የሕክምና መሳሪያዎች (የልብ ፒስ ሜከር ተብሎ ተጠቅሷል) በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያስገባ በቦሌ ኤርፖርት ጉምሩክ ሠራተኞች እጅ ከፍንጅ ከተያዘ በኋላ መለቀቁን በተመለከተ የህወሓት ከፍተኛ አመራር አባል የሆነው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድህኖም ስልክ ደውሎ ‹‹ክሱን ብታነሱላቸውና በአስተዳደራዊ መፍትሔ ብትሰጧቸው›› ብሎ ከመንገሩም በላይ የግለሰቡ ክስ እንዲቋረጥ የሚጠይቅ ደብዳቤ እንደፃፈላቸው መላኩ ፈንቴ ለመርማሪዎቹ መናገሩ በመዝገቡ ላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ይህንን ሁናቴም ከወቅቱ የፖለቲካ አሰላለፍ አኳያ ስንተነትነው አቶ መላኩ ‹ዶ/ር ቴዎድሮስን መስማት፤ ህወሓትን እንደመታዘዝ ነው› የሚል እምነት አድሮበት የተባለውን ፈፀመ ብለን ብንደመድም ተምኔታውያን አያሰኘንም፡፡

 

እነዚህ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያውም ሀገር በሚጎዳ ወንጀል የተከሰሰ ተጠርጣሪን በተመለከተ ከሥልጣን ገደባቸው አልፈው ‹‹አድምጥ!›› እያሉ የማዘዛቸው ምስጢር ሥርዓቱ ለፍትሕ ያለውን ግድየለሽነት እና በዚህ ሥርዓት የሕግ የበላይነት ብሎ ነገር እንጦሮጦስ መውረዱን ፍንትው አድርጎ ያሳያል ብዬ አምናለሁ፡፡ በርግጥ ይህንን ጉዳይ ለጥጠን ከተመለከትነው ‹‹…ለምን አታዳምጡትም?›› የምትለዋን ቃል ሰምና ወርቅ የለበሰች ቅኔ አድርገን በመውሰድ ልንፈታት እንችላለን፤ በተለይም መላኩ ፈንቴ ከዚህች ጥያቄ መሰል ትዕዛዝ በኋላ ግለሰቡን ቢሮ ጠርቶ ማስተናገዱን ስናስተውል፡፡ ምንም እንኳን አባይ ፀሀዬ በጊዜው በጉዳዩ ላይ መላኩን ሊያዝበት የሚያስችል መንግስታዊ ሥልጣን /የዕዝ ተዋረድ/ ባይኖረውም፤ አንጋፋ የህወሓት አመራር አባልና የበለጠ የፖለቲካ ጉልበት ያለው መሆኑ፤ ደመቀ መኮንን ደግሞ በብአዴን በኩል የአለቃነቱ ነገር ሲታሰብ፣ አሁንም መላኩ ፈንቴ የተጠየቀውን ‹‹ጥያቄ›› ከማስተናገድ ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖረውም ወደሚል ጠርዝ ይገፋናል፡፡ በርግጥ እውነታው ይህ ቢሆንም፣ መላኩ ዛሬም እስር ቤት ውስጥ ሆኖ የቀድሞ አለቆቹንም ሆነ ራሱን ተጠያቂ ለማድረግ አልደፈረም፡፡ በግልባጩ ለቀረቡበት ክሶች በሙሉ ተጠያቂው ገብረዋህድ እንደሆነ ከመናገሩም በላይ እንዲህ በማለት ወንጅሎታል፡-

 

‹‹የአያት ባለቤት በግብር ማጭበርበር ተከሶ በነበረበት ወቅት የተከሳሹ ቤተሰብ የሆነ ሰው እቢሮዬ መጥቶ ‹ገብረዋህድ ምንም ጥፋት ሳያጠፋ ነው የአያት አክሲዮን ማሕበር ባለቤትን ያሳሰረው፤ አሁንም አንድ ሚሊዮን ብር ካመጣችሁ ከእስር ይፈታል ብሎናል› የሚል ጥቆማ አመጣልኝ፡፡ …ገብረዋህድ እና ነጋ ገ/እግዚአብሔር (የነፃ ትሬዲንግ ባለቤት ነው) ጓደኛሞች ናቸው፡፡ ነጋ ዕቃ ሲያስመጣ አያስፈትሽም፤ የነጋም ጓደኞች እነ አልሳም፣ ጌት አስ የመሳሰሉት ድርጅቶች ዕቃ በቀላል ቀረጥና ታክስ እንዲሁም አልፎ አልፎ ሳይፈተሹ ያልፋሉ፤ …ባለቤቱ ሃይማኖትም፣ በነጋ ድርጅት ውስጥ ትሰራለች…››

 

መላኩ ፈንቴ ይህንን ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መናገሩንና ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ፀጋዬ በርሄን ‹‹ተከታተል›› ብሎት እንደነበረ ከአስረዳ በኋላ እንደሚከተለው ይቀጥላል፡-

 

‹‹ገብረዋህድ በኋላ እንደነገረኝ ባለቤቱን ከነጋ ድርጅት አስወጥቶ በአዜብ ትዕዛዝ መሰረት ኤፈርት ውስጥ ያስቀጠራት መሆኑን ገልፆልኝ ‹አንተም ላይ የሚወራው ስለምትታገል ነው ብላኛለች አዜብ› ሲለኝ እኔም ተከታትዬ ፀጋዬ በርሄ ከምን እንዳደረሱት አልጠየኩም፡፡ መጠየቅ ነበረብኝ፤ ጥፋት ነው፡፡ በአጠቃላይ ገብረዋህድ ላይ ብዙ ነገር ይባል ነበር፡፡››

 

መቼም ይህ ምላሽ በ1981 ዓ.ም ከአስመራ ዩንቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ዲግሪውን፣ ከአውስትራሊያ በገቢ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪውን፤ ከለንደንም በቢዝነስ አስተዳደር በተመሳሳይ መልኩ ትምህርቱን ካጠናቀቀና የረዥም ዓመታት የስራና የፖለቲካ ተሞክሮ ካለው ሰው የተሰጠ መሆኑን ስናስተውል፤ ሀገሪቱ የአምባገነን ባለሥልጣናት መቀለጃ ብቻ ሳትሆን፤ የሰዎቹንም የአቅም ማነስ ያመላክታል፡፡ እንዲሁም እነሞገስ ሰሚ ያላገኙበትን ምክንያትም ሆነ በዚህች ሀገር ገንዘብ ያለው የፈቀደውን መፈፀም የመቻሉን ምስጢር ይገለፅልናል።

 

ኢህአዴጋዊ ዕድሜ ማራዘሚያ…

ገዥው ስብስብ የፍትሕ ስርዓቱን ተቋማዊነት ሳይነካ፣ ለጨቋኝነቱ መጠቀሚያ የሚያደርግበት አንዱ መንገድ ከጠቅላይ እስከ ታች በተዋረድ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ድረስ ያሉ ዳኞችን የሚመድብበት አካሄድ ነው፡፡ በርግጥ እንዲህ አይነቱ ሀገርና ሕዝብ አልያም ሞራላዊ ልዕልና እና የሕግ-የበላይነት የማያስጨንቀው አገዛዝ፣ የፍትሕ ስርዓቱ ቅጥ የለሽ ተባባሪነት ሳይታከልበት የሥልጣን ዕድሜውን ማራዘም እንደማይችል መረዳት አይሳነውም፡፡ ይህን ለማድረግም ያለው ብቸኛ ምርጫ ዳኞቹን ከስሩ መሰብሰብ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢህአዴግ መሩ-መንግስት ሁለት አካሄዶችን ለመተግበሩ ያሳለፋቸው ሁለት አስርታት በሚገባ ያሳያሉ።

 

የመጀመሪያው የሚሾሙት ዳኞች፣ የግንባሩ ከፍተኛ የካድሬ ማሰልጠኛ እንደሆነ ከሚነገርለት ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ተማሪዎች መካከል ማድረጉ ነው፡፡ ከዚህ ‹‹የትምህርት›› ተቋም ውስጥ የሚወጡ የሕግ ምሩቃን ደግሞ ስለጥልቅ ዘመናዊ የሕግ ፅንሰ-ሃሳብ ለማወቅ ከመትጋት ይልቅ፤ የኢህአዴግ ፖሊሲዎች እና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሕግን እንዴት ‹‹ለመደብ ጠላት›› መጠቀም እንደሚያስችሉ በሚሰብኩ መምህራን ስር እንዲያልፉ ይገደዳሉ (ስለመምህሮቹ ምሁራዊ ልሽቀት ለመረዳት የሕዝብ ሙስሊሙን ጥያቄ በሽብር ተግባር ለመፈረጅ እና ማሕበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት ለመወንጀል በ‹‹ጥናታዊ ጽሑፍ›› ስም የተጓዙበትን ርቀት ማየቱ ብቻ በቂ ይመስለኛል)፡፡ ተማሪዎቹም በዚህን መሰሉ የካድሬ ተቋም ስልጠና ስር ሰንብተው ሲወጡ፤ በፍፅምና ሊታመኑላቸው ይገቡ የነበሩትን ፍትሓዊ ዳኝነትና ህሊና የሚባሉ ጉዳዮችን ጨፍልቀው፣ በተለይም ፖለቲካዊ ነክ በሆኑ አይረቤ ክሶች ፊታቸው በሚቆሙ ንፁሀን ዜጎች ላይ መከራን የሚያዘንቡ አሽከሮች ይሆናሉ፡፡ ይህንን አስነዋሪነት ካለመታከት የሚፈፅሙትም፣ ሥልጣንን እና ተያያዥ ጥቅማ-ጥቅሞችን እያጋበሱ ወደ ከፍታ ሲወጡ ተመልክተናል።

 

ሁለተኛው የግንባሩ አካሄድ ከካድሬ ማሰልጠኛውም ሆነ የተሻለ ነው ከሚባለው የአ.አ.ዩ. የሕግ ፋካሊቲ የሚመረቁትን፣ በተከታታይ ርዕዮተ-ዓለማዊ ጠመቃ የሥርዓቱ ጋሻ-ጃግሬ ማድረግ ላይ ያተኮረው ነው፡፡ በሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ሲያገለግሉ ቆይተው ስደትን የመረጡ ዳኞችና ዐቃቢ-ህግያት በተለያየ ጊዜ እንደ መሰከሩትም አሰልቺ የርዕዮተ-ዓለም ጠመቃ የፍትሕ ሥርዓቱን ነፃነት ጽልመት ካላበሱት ሂደቶች በዋነኛነት ተጠቃሽ ነው፡፡ በአንድ ወቅትም ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ የሀገሪቱን ዳኞች ሰብስቦ ስለሕገ-መንግስት እና ሕገ አተረጓጎም መርህ ሲያስተምር ለማየት የተገደድነው የዚሁ የጠመቃው አንድ አካል በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ ዳሩስ፣ ይህማ ባይሆን ኖሮ እስክንድር ነጋ ላይ 18 ዓመት መፍረድ ሕሊና እንዴት ይፈቅድ ነበር? ኦልባና ሌሊሳንስ ለ11 ዓመታት ወህኒ ያስወረወረው ጥፋት ምን ተብሎ በአሳማኝ መልኩ ሊጠቀስ ይችል ይሆን?

…ቀሪው ለሳምንት ይቆየን!

Latest from Blog

ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop