(ሪፖርተር) የኦሮሚያ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የክልሉ የመሬት አስተዳደርና የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ ምክትል ኃላፊን አቶ መሐመድ ኢብራሂም ሙሳን ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ሥር አዋለ፡፡ የኮሚሽኑ አንድ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኃላፊው በቁጥጥር ሥር የዋሉት በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ነው፡፡ አቶ መሐመድ ኢብራሂም በቁጥጥር ሥር የዋሉት ባለፈው ሳምንት ዓርብ በሥራ ገበታቸው ላይ እንደነበሩ መሆኑን፣ የታሠሩትም ቡራዩ ከተማ በሚገኘው እስር ቤት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ መሐመድ ቀደም ሲል ለሦስት ዓመታት ያህል የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር፣ ለአንድ ዓመት ያህል ደግሞ ኮሚሽነር ሆነው ሠርተዋል፡፡ በዚህ ዓመት መጀመርያ ደግሞ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ወደ መሬት አስተዳደር ቢሮ በኃላፊነት ተዛውረው ይሠሩ ነበር፡፡
የኦሮሚያ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከስልሳ በላይ የተለያዩ የክልሉ ኃላፊዎችን ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ይታወሳል፡፡
በቃለየሱስ በቀለ