የአሜሪካን ሲትዝን ያላገኘ ሰው በድራግ ወንጀል ቢገኝ ምን ያጋጥመዋል?

አንዳንድ ወገኖቻችን እየተስፋፋ ባለው፤ መንግስትና ሕብረተሰቡ በጥንካሬ እየተዋጋው ባለው የአደገኛ እጽ (Narcotic drugs) እና የተከለከሉ መድሐኒቶች (controlled substances) መጠቀምና ይዞ መገኘት ወንጀል ውስጥ ተሳትፈው በመገኘታቸው በፖሊስ ተይዘው ምርመራው ተጣርቶ ለተገቢው አቃቢ ሕግ መ/ቤት (District Attorney office) ከተላለፈ በሁዋላ መዝገባቸው ለፍርድ ሸንጐ (Jury) ቀርቦ ክስ ስለተመስረተባቸው ፍርድ ቤት ቀርበው በአጋጣሚ አገኛቸዋለው ። በተለይ ደግሞ በጣም የማዝነው የአሜሪካ ዜግነትን ያልወሰዱ ወገኖቻችን ላይ የሚያስከትለው ጣጣ በጣም የከፋ መሆኑን ስለማውቅ ነው። ይሕንን በተመለከተ በዚሕ ውስጥ ያለውን የወንጀል ሕግ (criminal law) ከስደተኞች ህግ (Immigration Law) ጋር በማገናዘብ ወደ ፊት በሰፊው የማቀርበው ሲሆን ለዛሬው ግን በወንጀሉ ዙሪያ አተኩራለሁ። ይህ ምክር በአደገኛ እጽ መያዝ ወይንም መጠቀም ለተከሰሰ ሰው ላይ ብቻ ሳይሆን በሌላ አይነት ወንጀልም ለተከሰሰ ሰው የሚረዳ ምክር ይሆናል።
በአደገኛ እጽ እና የተከለከሉ መድሐኒቶች ዙሪያ የሚሠራውን ወንጀል በመሉ የሚቆጣጠረው የህግ ክፍል የራሱ አንቀጽ አለው።
የተከለከሉ መድሐኒቶች (controlled substances) የሚለው አጠራር በጣም ብዙ የሆኑ በላቦራቶር የተፈጠሩና የተቀየሩ አደገኛ እጽ እና መድሃኒቶች ሲሆኑ በዋናነት የምንጠቅሳቸው ግን marijuana፣ cocaine (crack cocaine)፣ Methyl amphetamine (Meth) እና Heroine የመሳሰሉት ናቸው ።
አንዳንድ ሰዎች በዚህ ዝርዝር ውስጥ ጫት መታቀፉ ወይንም አለመካተቱ ቢይደናግራቸውም እኔ በግሌ ባደረግሁት ጥናት ግን የሚኒሶታን ባላውቅም በምኖርባት ጆርጅያ ግዛት ውስጥ ያገኘሁት የሕግ ክፍል ወይንም የፍርድ ቤት ውሳኔ የለም። ስለሆነም በጆርጅያ ውስጥ ጫት የተከለከሉ መድሃኒቶቸ ወይንም አደገኛ እጽ ውስጥ አልተጠቀስም ብል መሳሳት አይሆንብኝም። በሚኒሶታስ? የህግ ባለሙያዎችን በቅርብ ያነጋግሩ።
በመጀመሪያ ደረጃ አደገኛ እጽ ወይንም መድሓኒት መጠቀም ለጤናና ሕይወት ጠር ነው ። በዚህ አባባል ላይ ከአብዛኛው አንባቢ አስተሳሰብ ጋር የምገጥም ይመስለኛል። በመቀጠልም እንደ አደገኛ እጹ ወይንም የተከለከለ መድሕኒቱ አይነትና መጠን፡ እንደ አጠቃቀሙ ወይንም ማስተላለፉ አይነትና ይዘው እንደተገኙበት ቦታ ቅጣቱም እየከበደ ይሄዳል ። ለምሳሌም በብዛት የያዘ ሰው፤ ሲሸጥ ወይንም ለሽያጭ ሲያዘጋጅ ከታየዘ ሰው ጋር ሲነጻጸር ወንጀሉና ቅጣቱ ከባድ ይሆናል ማለት ነው። ኰኬይን የያዘ ማሪዋና ከያዘው ወይንም ከተጠቀመው ወንጀሉና ቅጣቱ
ይከብዳል ማለት ነው። በመኖሪያ አካባቢ የያዘው በትምህርት ቤት አካባቢ ይዞ ከተገኘው ወንጀሉና ቅጣቱ ይቀንሳል ማለት ነው። በማንኛውም አይነት ወንጀል አደገኛ እጽና የተከለከለ መድሀኒት ይዞ ወይንም ሲጠቀም የተገኘውንም ሠውን ጨምሮ በፖሊስ በቁጥጥር ሥር በሚውልበት ጊዜ የእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚገባ የማይናገርና የማይገባው ከሆነ አስተርጉዋሚ መጠየቅ፣ በመቀጠልም ምንም አይነት ቃል ለፖሊስ ከመስጠቱ በፊት ጠበቃ እንዲቀርብለት መጠየቅ፣ ጠበቃ ካልቀረበለት ምንም አይነት የእምነትም ሆነ የክህደት ቃል አለመስጠት አለበት። ፖሊስ ምርመራውን አጣርቶ ለተገቢው ዓቃቢ ህግ መ/ቤት (District Attorney) በሚያቀርብበት ጊዜ ተከታትሎ ጉዳዩ የተመራለትን ዓቃቢ ህግ መ/ቤት በማነጋገር ክስ ተመስርቶ ወደ ፍ/ቤት ከመተላለፉ በፊት በዓቃቢ ህግ መ/ቤት ውስጥ ከፍርድ ውጭ ጉዳያቸው በተለያዩ ፕሮግራሞች ውስጥ ተሳትፈው
ለሚያጠናቅቁና እራሳቸውን ለመቀየር ለተዘጋጁ ሠዎች የሚሠጠውን እድል ለመጠቀም ማመልከት አለበት።
እነኚህም መርሀግብሮች (pretrial diversion programs) ተብለው የሚጠሩት ናቸው። በመርሀግብሩ እንዲሳተፉ እድል ከተገኘ በሚገባ ተከታትሎ አጠናቆ የሚያረካ ማስረጃ ከተገኘ በኋላ የዓቃቢ ህግ መ/ቤት የግለስቡን የእሥር ሪፖርት (arrest record) እንዲደመሰሥና ከፋይል ውስጥ እንዲሰረዝ (expunge) ይደረጋል። ይህም የግለስቡን የወንጀል ታሪክ ለማወቅ ለሚፈልጉና ማጣራት ለሚያደርጉ መ/ቤቶችና ግለስቦች ምንም ዓይነት የወንጀል ሪኮርድ እንደሌለበት ያሳያል።ያም ሆነ ይህ ግን ፖሊስ፣ ዓቃቢ ህግና የፌደራል ፖሊስ (FBI) ይሀን የእሥር ሪፖርት የማየት መብቱና ችሎታው አላቸው።
ከላይ የተጠቀስው መንገድ ካልተሣካና ክስ ተመስርቶ ፍርድ ቤት በሚቀርቡ ጊዜ መንግሥት በጀት ይዞ ገቢያቸው
አነስተኛ የሆኑ ሠዎችን እንዲወክሉ ለተዘጋጁት የመንግስት ጠበቆች (Public Defender) ጉዳይዎን እንዲይዙለት ማመልከት ነው። ባለዎት የገቢ መጠን ምክንያት የመንግስት ጠበቆች ጉዳይዎን መያዝ የማይችሉ ከሆነ ግን በግልዎ ጠበቃ ማቅረብ አለብዎት ማለት ነው።
ለመጀመሪያ ጊዜ በአደገኛ እጽ እና የተከለከሉ መድሐኒቶች ወይንም በማንኛውም አይነት ወንጀል ክስ ለቀረበባቸውና መስፈርቱን ለሚያሞሉ ግለሰቦች እንደ ቅደም ተከተላቸው መሠረት የመጀመሪያ ጊዜ ወንጀለኛ (first offender treatment) መብት መጠቀም ይችላል።
በጆርጅያ የወንጀል ሕግ 16-13-2 መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ በአደገኛ ውጽ ወይንም በተከለከሉ መድሀኒቶች ይዞ መገኘት ወንጀል የተከሠሠ ሰው ፍርድ ቤት በሚቀርብበት ጊዜ ጠበቃው ይህንኑ መብቱን መጠቀም እንዲችል እንዲያመለክትለት ማስታወስ ይገባል። ይህንን መብት ለመጠቀም ሌሎች መሟላት ከሚገባቸውና ህጉ በዝርዝር ከሚያስቀምጣቸው መስፈርቶች በተጨማሪ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ወንጀል ተከሦ ይህንን እድል ተጠቅሞ መገኘት የለበትም። ጥያቄው የቀረበለት ፍ/ቤትም ተከሳሹን ከላይ በተጠቀሰው ሕግ የሚያስተናግደው ከሆነ ተከሳሹ ከዚህ በታች የተጠቀሱትን ጥቅሞች ያገኛል ማለት ነው።
ተከሣሹ በፍርድ ቤቱ የጣለበትን የእስር ወይንም በውጭ ሆኖ የተጣለበትን የቅጣት ገደብ እንዲጨርስ እድል ይሰጠዋል፣ የተጣለበትን ገደብ በሚገባ አጠናቆና መክፈል የሚገባውን ቅጣትና ክፍያዎች አጠናቆ ከጨረሰ፣ በማሕደሩ ላይ የተቀጣ ወንጀለኛ የሚል አይኖርም። ለማንኛውም ጉዳይ ቢሆን በፍርድ ቤት ተቀጥተኃል ወይንም ተወስኖብህ ያውቃል ለሚለው መልሱ በአሉታ (የለም) የሚል ይሆናል። የግለሠቡን የፍርድ ቤት ቅጣት (ወንጀል) ሪኮርድ ለማየት የሚፈልጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሚያገኙት የፍርድ ውሳኔ አይኖርም። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንደአግባቡ በአጠቃላይ የወንጀል ታሪክ ከፍርድ ቤት ማሕደር ውስጥ በአካል እንዲጠፋ ወይንም እንዲደመሰስ (expunge) መጠየቅ የሚቻልበት እድል ይከፍታል። ከማንኛውም የሥራ ወይንም የትምሕርት እድል በወንጀል ታሪካቸው ምክንያት እንዳይሰናከሉ ይረዳል።S

ተጨማሪ ያንብቡ:  መረጃ ትኩረት: የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች!
Share