ዛሬም የኢትዮጵያ ሙስሊም ድምጹ ከፍ ብሎ ተሰማ፤ ‹‹313 ሚሊዮን ብሩን ለልማት!›› ሲል ዋለ

April 26, 2013

ከ ድምፃችን ይሰማ

በእርግጥ ጥያቄው ትላንትም ዛሬም አንድ ነው፡፡

የሃይማኖት ነጻነትና እኩልነት መሰረታዊ ከሚባሉ የሰው ልጅ መብቶች ይመደባል፡፡ ‹‹መንግስት እምነታችን ላይ በጀመረው ኢፍትሀዊ ዘመቻ ነጻነታችንን ነፈገን! ሃይማኖታቸንን በግድ ሊያስለውጠን እየሞከረ ነው! ድምጻችን ይሰማ!›› በሚል ለመብቱ ሲታገል የነበረው የኢትዮጵያ ሙስሊም አደባባይ መዋል ከጀመረ ብዙ ጊዜ ሆነው፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ በርካታ መስዋእትነቶች እና ዘርፈ ብዙ የመብት ጥሰቶች ከትግሉ ሊያስቆሙት አልቻሉም፡፡ አሁንም ጠንክሮ እግሮቹን አደላድሎ ‹‹ለመብቴ በሰላማዊነት እታገላለሁ›› የሚል ቁርጠኝነቱ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም፡፡ ከትግሉ መጀመር አንስቶ እለተ አርብ ለሙስሊሞች ብዙ አደጋን ያዘለች፣ በርካቶች የሚደበደቡባት፣ በርካቶች የሚታሰሩባት፣ በርካቶች በግፍ የሚጉላሉባት ብትሆንም ህዝበ ሙስሊሙ ግን በጉጉት ይጠብቃታል፡፡ ለምን? ለመብቱ የሚታገልባት፣ ድምጹን የሚያሰማባት፣ ህመሙን የሚተነፍስባት እለት ስለሆነች ነው! በማንነቱ ተከብሮ የመኖር መብቱን የሚጠይቅባት ቀን ስለሆነች ነው፡፡ ለዚያም አይደል በየጁሙአዎቹ የህዝቡ ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ሲሄድ የምናየው?

እንደወትሮው ሁሉ የዛሬዋም ጁምአ በሙስሊሞች ተቃውሞ ደምቃ፣ በፍትህ ጥሪ ተንቆጥቁጣ ነው የዋለችው፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ደማቅ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል፡፡ እጆች ለዱአ ተዘርግተዋል፡፡ ወንድማማችነት እና አንድነት፣ የአላማ ጽናት እና ቁርጠኝነት ገኖ የወጣባት ከብዙ ያማሩ ጁምአዎች መካከል ደምቃ የወጣች ጁምአ ነበረች፡፡ በዚህች ቀን መንግስት በማን አለብኝነት የአህባሽን ስልጠና እንደአዲስ ለማስቀጠል 313 ሚሊየን ብር በጀት መድቦ ከመጅሊስ ጋር ስምምነት ማድረጉ ያስቆጣቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች በአገሪቱ የተለያዩ አቅጣጫዎች ‹‹313 ሚሊዮን ብሩን ለልማት›› እያሉ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ውለዋል፡፡ የተወሰኑት አብረን እንያቸው፡፡

የህዝበ ሙስሊሙ ተቃውሞ መነሻ እና መዳበሪያ ሆና የቆየችው፣ የትግሉ ጽንስ የተወለደባትን አወሊያን በያዘችው አዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጊድ ሰው በጠዋቱ መትመም ጀምሮ ነበር፡፡ አንዋር በአራቱም አቅጣጫ በሰው ተሞላ፡፡ በርካታ ፖሊሶች በጠዋቱ ቢስ መብራት በሚገኘው ጅንአድ ግቢ ውስጥ ተጠቅጥቀው የነበረ መሆኑን ያየ የህዝበ ሙስሊሙን ጨዋነት መንግስት የማያውቀው ይመስላል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ግን ሁሉም ሰላምን ትጥቁ አድርጎ ነበር የተገኘው፡፡

ሰላቱ ከተሰገደ በኋላ አፍታም ሳይቆይ ደማቁ ተቃውሞ ተጀመረ፡፡ እጆች የያዙትን ወረቀት አውለበለቡ፡፡ በነዚያ ወረቀቶች ላይ የተጻፉ መልእክቶች የህዝቡን የልብ ትርታ መናገር የሚችሉ ናቸው – ከድምጹ ጋር ተደባልቀው ሩቅ ይሰማሉ፡፡ ‹‹313 ሚሊየን ብሩ ለልማት!›› ብዙዎቹ የያዙት ወረቀት ነበር፡፡ በኮምፒውተር ህትመት፣ አንዳንዶቹ በማርከር፣ አንዳንዶቹ በስክሪብቶ የተጻፉ ናቸው፡፡ ትኩር ብሎ ላየው ይህ ራሱ መልእክት ነው፡፡ ‹‹በእጄ ባለው ነገርና በአቅሜ ለመብቴ እታገላለሁ! ለትግሉ የምችለውን አበረክታለሁ!›› ነው መልእክቱ፤ የያዙት ደግሞ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ጎልማሶች፣ አዛውንቶችና ህጻናቶች ናቸው፡፡ ሁሉም ቁርጠኝነታቸወን ታጥቀው፣ መስዋእትነት ሊከፍሉ ተዘጋጅተው ነው የመጡት፡፡ ሁሉም በአንድ ድምጽ፣ በአንድ ጽሁፍ፣ የአገር ሀብት የህዝብ ነውና ህዝብን በሚጠቅም ነገር ላይ እንዲውል፣ ያ ቢቀር እንኳ ህዝብን በሚጎዳ ነገር ላይ እንዳይውል ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹ሰሚው አካል የታለ?›› ይላሉ ከሳምንት ሳምንት!

በአንዋር መስጊድ በሴቶች መስጊድ በኩል የታየው የእህቶቻችን ጠንካራ ተቃውሞ አስደማሚ ነበር፡፡ ሴቶቻችንም ለመብታቸው የሚተኙ አይደሉም፡፡ ለሃይማኖታቸው መከበር ዱላን ተጋፍጠው፣ እስርን ገላምጠው መብታቸውን ጠይቀዋል፡፡ ‹‹እኛም ለመብታችን እንታገላለን!›› ብለዋል፡፡ ‹‹ኢስላም ሰላም! ብራችን ለልማት!›› እያሉ በአንድ ድምጽ አድማሱን ሲሞሉት ያየ በእህቶቻችን ምንኛ ይደሰት?
ይህን በመሰለ ውብ ገጽታ የአንዋሩ ተቃውሞ ያለአንዳች ችግር ተፈጽሟል፡፡ በመሀል ለየት ያሉ መፈክሮችን ለማስረጽ የተደረገው ሙከራም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ በሰላም ተቃውሞውን አሰምቶ ወደየፊናው ተበታትኗል፡፡ ሁሉም ወደቤት ሲመለስ በተስፋ መቁረጥ ሳይሆን በቁርጠኝነትና በታደሰ መንፈስ፣ መብቱ እስኪከበርለት ድረስ በሚያታግለው መጠን ኃይል የተሞላ ነበር – አልሐምዱሊላህ!!!

በተቃውሞ ደምቃ የዋለችው ሌላኛዋ ከተማ ወልቂጤ ናት፡፡ የወልቂጤ ሰላማዊ ሙስሊም ማህበረሰብ በጊዜ ነበር ወደ ጃሚአል ከቢር መስጊድ መትመም የጀመረው፡፡ ትልቁ መስጊድ ሞልቶ በዙሪያው የሚገኘው ገላጣ ቦታ ዲናቸው ላይ የሚደርሰው ጥቃት ባሳሰባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተከቧል፡፡ ሁሉም ቁጡ፣ ግን ፍጹም ሰላማዊ ናቸው፡፡ ኢማሙ ሰላት ሰግደው አሰላምተው ሲጨርሱ መስጊዱ በተቃውሞ ተክቢራ ተሞላ፡፡ የእለቱን ተቃውሞ መሪ መፈክር የያዙ እጆች ወደላይ ከፍ አሉ፡፡ በርካታ መፈክሮች በዚያ አስገምጋሚ ድምጽ ተስተጋቡ… ‹‹ፍትሕ!››፣ ‹‹ድምፃችን ይሰማ!››፣ ‹‹አህባሽ አይጫንብንም!››፣ ‹‹አሽእብ ዩሪድ ኢስቃጠል መጅሊስ!››፣ ‹‹ፍትሕ ናፈቀን!››፣ ‹‹ለኢስላም እንሞታለን!››፣ ‹‹የታሰሩት ይፈቱ!››፣ ‹‹ባገራችን ሰላም አጣን!››፣ ‹‹እኛም አቡበክር ነን!›› እና ሌሎችም መፈክሮች በህዝቡ ተሰምተዋል፡፡ ደማቁ ተቃውሞ ያለምንም እንከን በሰላም ተጠናቆ ህዝቡ ወደየመጣበት ተመልሷል፡፡

በተመሳሳይ ጊዜ በስልጢ ዞን ወራቤ በአቡበክር መስጊድ በርካታ ህዝብ በተገኘበት ደማቅ ተቃውሞ ተደርጎ ውሏል፡፡ ትልቁ መስጊድ በተባበሩ ድምጾች ተንጧል፡፡ የትግሉን መንፈስ የሚያንጸባርቁ በርካታ መፈክሮችም በድምጽ ተስተጋብተዋል፡፡ ተቃውሞው የተበተነው በሰላም ያለ አንዳች እንከን ነበር፤ ዱሮውንስ ከጨዋ ህዝብ ከሰላም ውጭ መች ሌላ ይጠበቃል!

የወሎዋ ደሴ ከተማ በበኩሏ ተቃውሞዋን አሰምታ ውላለች፡፡ ጠዋት በዋለው የደሴ ችሎት ለ 260 ቀናት ያለምንም ክስ የታሰሩት እውቅ የዲን አስተማሪ አባቶች በዋስ እንዲለቀቁ ውሳኔውን ያሳለፈ ሲሆን የጀግኖቹን መፈታት በጉጉት የሚጠብቀው ህዝበ ሙስሊም በጦልሀ መስጊድ ተሰባስቦ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ ሰላቱ ከወትሮው ቀደም ብሎ 6፡42 ላይ መሰገዱ ብዙዎች ሰላቱ እንዲያመልጣቸውና እንዲዘገዩ ያደረገ ቢሆንም ከሰላቱ በኋላ ግን ህዝቡ ተቃውሞውን አሰምቶ በሰላም ተበትኗል፡፡ የትግሉን መንፈስ የሚያንጸባርቁ በርካታ መፈክሮችም ተደርገዋል፡፡

በተደጋጋሚና ተቃውሞዋ የምናውቃት ሻሸመኔ የኦሮሚያ ክልልን ለመብት በሚደረግ ትግል ካደመቁ በርካታ ከተሞች አንዷ ነች፡፡ እንደተለመደው ጀግናው የሻሸመኔ ሙስሊም በአራዳ መስጊድ በጊዜ በመሰብሰብ ሰላቱን በስርአቱ የሰገደ ሲሆን ከሰላቱ መጠናቀቅ በኋላ ከፍተኛና ደማቅ ተቃውሞ አሰምቷል፡፡ ‹‹ድምጻችን ይሰማ!›› እና ‹‹የታሰሩት ይፈቱ!›› የሚሉት መፈክሮች የተስተጋቡ ሲሆን ያለአንዳች የጸጥታ ችግር ህዝቡ ብሶቱን አሰምቶ ወደየመጣበት ተመልሷል፡፡ በተመሳሳይ ሰአት በዚያው በኦሮሚያ ዞን ነጌሌ ቦረና ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ መሰማቱም ተዘግቧል፡፡ የነጌሌውን ለየት የሚያደርገው ረዘም ላለ ጊዜ ሰላማዊው የነጌሌ ህዝብ መፈክር እያሰማ፣ ብሶቱን እየተነፈሰ የቆየ መሆኑ ሲሆን ተቃውሞው የተጠናቀቀውም ያለአንዳች የጸጥታ እንከን ነበር፡፡

ኦሮሚያ ክልል በዚህ ብቻ አልበቃትም፡፡ በኮፈሌ ከተማ ሰላም መስጊድ ውስጥ የተሰባሰቡ ምእመኖቿ ‹‹እኛም ለመብታችን ቆመናል!›› የሚል መልእክታቸውን አስተላልፈውባታል፡፡ ሰጋጆች በሙሉ በከፍተኛ ድምቀት በርካታ መፈክሮችን ሲያሰሙ የነበረ ሲሆን ‹‹አላሁ አክበር!››፣ ‹‹ድምፃችን ይሰማ!››፣ ‹‹ኮሚቴው ይፈታ!››፣ ‹‹ፍትህ ናፈቀን!››፣ ‹‹ህገወጡ መጅሊስ አይወክለንም!›› እና የእለቱ ዋና መፈክር የነበረውን ‹‹313 ሚለዮን ብሩ ለልማት!›› በደማቅ ሁኔታ ሲያስተጋቡ ቆይተዋል፡፡ የኮፈሌ ከተማ አጎራባች በሆኑት ቃጬቀታ እና ቃበቴ ከተሞች ላይም በመስጊዶቻቸው እንዲሁ ከፍተኛ ተቃውሞ ተደርጓል፡፡ ተቃውሞዎቹ ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር ነበር የተጠናቀቁት፡፡
ካሁን ቀደም ፖሊሶች ሰላማዊውን ሙስሊም መስጊድ ደፍረው በደበደቡባት አጋሮ ከተማም እንዲሁ ከፍተኛ ተቃውሞ ተደርጎ ውሏል፡፡ በርካታዎች በተገኙበት የተስተጋባው ይህ ተቃውሞ የአጋሮ ሙስሊሞች ወኔ በፖሊስ ዱላ ሊሰበር እንደማይችል ዳግም አረጋግጦ የዋለ ነበር፡፡ የድምጽ ተቃውሞው ከተደረገ በኋላ የፖሊስ ሰራዊት መስጊዱን እና መተላለፊያውን ዘግቶ ከበባ በማድረግ ጥቃት ለማድረስ አስቦ ነበረ ቢሆንም በአላህ ጸጋ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ መስጊዱን የከበበውን ሰራዊት ገብቶ ህዝቡ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ሲማጸኑ የነበሩት የመስጊዱ ኢማም ድርጊት ብዙዎን አሳዝኖ የነበረ ሲሆን ጥቃት ግን ሳይሰነዘር ቀርቷል፡፡ ሶስት ያህል ሰዎች ከሙስሊሞች መካከል ታስረው ተወስደዋል፡፡ በቦታው የተገኙ የመንግስት አካላትም ተቃዋሚዎችን ለማስፈራራት ፎቶዎችን እያነሱ የነበረ ቢሆንም ጀግናው የአጋሮ ሰላማዊ ህዝብ ግን ያለአንዳች መሸማቀቅ ከበባው ሲበተን ወደየመጣበት ተመልሷል፡፡

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የዱአ ተቃውሞ እንዲካሄድባት ታስባ በነበረችው ኮምቦልቻ ከተማ ላይ በኻሊድ መስጊድ በርካታ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላት በተገኙበት ሰደቃና ዱአ መደረጉም ተዘግቧል፡፡ ገና በጊዜ ወደመስጊድ ሲመጣ ለችግረኞችና ለየቲሞች ሰደቃ በመስጠት የጀመረው የኮምቦልቻ ኻሊድ መስጊድ ሰጋጅ ከሰላቱ መጠናቀቅ በኋላ ቋጥሮ የመጣውን ብስኩት እየተካፈለ በመብላት ድንቅ ወንድማማችነት አሳይቷል፡፡ ከሰደቃው መጠናቀቅ በኋላም በእስር እየተንገላቱ ላሉ ሙስሊሞች አላህ ፈረጃውን እንዲያመጣ ዱአ በማድረግ ሰዉ ወደየመጣበት ተመልሷል፡፡ በዚያው ሰሜን ኢትዮጵያ ባህር ዳር እና ጎንደር ላይ የዱአ ተቃውሞ መደረጉም ተዘግቧል፡፡ በባህር ዳር በሰላም በር መሰጊድ ከወትሮው በተለየ ከፍተኛ ቁጥር የተሰባሰቡ ሙስሊሞች ደማቅ የዱአ ስነስርአት ያካሄዱ ሲሆን ስነስርአቱ ያለአንዳች የጸጥታ ችግር ተጠናቋል፡፡ የባህርዳሮች የዛሬ እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪና ገና ብዙ እንደሚያሰዩን በተግባር ያስመሰከሩበት ቀን ነው፡፡

በሶስተኛው እርከን በአንድ መስጊድ ተሰባስቦ የመስገድና አጋርነትን የማሳየት ተቃውሞው በታሰበላቸው ከተሞች ላይ በድምቀት ተደርጎ መዋሉም ተዘግቧል፡፡ መቀሌና አላማጣን የመሳሰሉ የትግራይ ከተሞችና በሎጊያ፣ ዱብቲ፣ ደወይና አይሳይታ የሚገኙ ሙስሊሞች በየከተሞቻቸው ማእከላዊ መስጊድ በበርካታ ቁጥር በመገኘት አጋርነታቸውን አሳይተዋል፡፡ የአማራ ክልሎቹ መካነሰላም፣ ባቲ እና ጃማ ከተሞችም አጋርነታቸውን ካስመሰከሩ ከተሞች መካከል ነበሩ፡፡ በኦሮሚያ በሚገኙት አወዳይ፣ ጭሮ፣ ሀሮማ፣ ያያቤሎ ቦረና፣ ጎሬ እና ሮቤ ከተሞች ላይም ከፍተኛ አጋርነትን የማሳየት እንቅስቃሴ ተደርጎ ነበር፡፡ በደቡቧ አዋሳ እና በሱማሌዋ ጅጅጋ፣ እንዲሁም በአሶሳና በጋምቤላ ከተሞች የሚገኙ ሙስሊሞችም ድምጻቸው ከቀሪው የኢትዮጵያ ሙስሊም ጋር አንድ መሆኑን በአጋርነታቸው አስመስክረዋል፡፡

ሕዝበ ሙስሊሙ ዛሬም እንደ ትላንቱ በሰከነ ልቦና በማሰብ ፍፁም ሠላማዊ በሆነ ስርዓት ሁለንተናዊ የተቃውሞ ዘዴዎችን በመጠቀም ከጫፍ እስከ ጫፍ ድምፁን ሲያስተጋባ ውሏል፡፡ ይህ እውነታ የታሪክ አካል ሊሆን ግድ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ለዕምነታቸው ባላቸው ጥልቅ ቀናዒነት ብቻ የሌሎችን መብት ፍፁም ሳይነኩ፣ የአገር ደህንነት ቀዳሚ ትኩረታቸው ሆኖ፣ ተደራራቢ በደል እየተፈፀመባቸው፣ ውስጣዊም ውጫዊም ሴራዎች እየተጎነጎኑባቸውም ጭምር እሾሀማውን ዳገት ሽቅብ መጓዙን ተያይዘውታል፡፡ ይህ ጉዳይ የሐይማኖት ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥም የሐይማኖት ጉዳይ በመሆኑ ልጅ አዋቂ፣ ወንድ ሴት፣ ሀብታም ድሀ ሳይል ሁሉም ጉዳዩ አድርጎ ይዞታል፡፡ ከደም ከስጋው ተዋህዷል፡፡ ጉዞው አድካሚ፣ ስጋት የተሞላበትና አሰልቺ የመሆኑ እውነታ የተረታበት ሚስጥርም ይኸው ነው፡፡
ትግላችን በአላህ ሱብሀነሁ ወተዓላ ፈቃድ ሁለንተናዊ የሠላማዊ ትግል ገፅታን ተላብሶ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ዳግም ያረጋገጡት እውነታ ሆኗል፡፡ እንቅስቃሴው ‹‹ሀ›› ብሎ ሲነሳ ያነገበው ዓላማ ሳይበረዝ፣ ሳይከለስና ሳይሸረሸር በቀጥተኛና የጠራ አቅጣጫ ላይ ይገኛል፡፡ ምንም የሚያሻማ፣ የሚያከራክር፣ ብሎም የተደበቀ ነገር የለውም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ህገመንግስታዊ መብታችን ተጥሷል፡፡ የእምነት ተቋማችን የእኛ የእምነት ባለቤቶቹ ንብረት ነው፡፡ የምንመርጠውም፣ የምናስመርጠውም፣ የምንሾመውም፣ የምንሽረውም እኛው ነን፡፡ ይህንን መብት በአደባባ ፀሀይ ተክደናል፡፡ተቋማችንን የተቆጣጠሩት አካላት ሕዝበ ሙስሊሙ እንዳልመረጣቸው ዛሬም አደባባይ ወጥቶ ድምፁን ያሰማው ወገን ማረጋገጫ ካልሆነ ምን ማረጋገጫ ይመጣለት ይሆን? የመጅሊሱ አመራር ነን ብለው የተቀመጡት አካላት የሙስሊሙን ህዝብ አይወክሉትም፡፡ በሕዝበ ሙስሊሙ ስም የሚያደርጉት ማንኛውም እንቅስቃሴ ዛሬም ነገም ከህዝበ ሙስሊሙ እውቅና ውጭ ነው፡፡ ይህንን እስከ መጨረሻው ድረስ በሰላማዊ መንገድ እንቃወማለን፡፡

የአሕባሽ አስተምህሮት የተቋማችን እና የመንግሰት ድጋፍ ተችሮት በሰፊው ሙስሊም ጫንቃ ላይ ለመጫን እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዛሬም ውርደትን ተከናንቦ ይቀለበሳል፡፡ በዚህ ስም እየባከነ ስላለው የሀገርና የህዝብ ሀብት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለሚኖሩ መላ ሀገር ወዳድ ወገኖች እንዲሁም እርዳታ ሰጪም ሆኑ አበዳሪ ወዳጅ ሀገራት እውነታው ይደርስ ዘንዳ የበኩላችንን ተወጥተናል፡፡ ይህንኑ መልእክታችንን ለማስተላለፍም ተደጋጋሚ ጥረቶችን ማድረጋችንን እንቀጥላለን፡፡

በዜጎች ላይ በሐይማኖት ሰበብ የሚደርሰውን በደል በመቃወም በምድራችን ላይ ሆነን እያደረግነው ያለው በርካታ ወራትን ያስቆጠረው ይህ የትግላችን ሂደት መቋጫው ሩቅ አይደለም፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደታችን ድፍን ዓለም የመሰከረለትን ሠላማዊነታችንንና ጨዋነታችንን፣ እንዲሁም ያነሳናቸውን ጥያቄዎች ዳግም በማጤን በሰከነ ልቦና ምላሽ ለመስጠት ያኮረፈውን ዜጋ ለመጠገን፣ ከቤቱ የወጣውን ወገን ለመመለስ፣ ብሎም ፊቱን ወደ ልማት እንዲዞር ለማድረግ ከበቂ በላይ ነው እንላለን፡፡ መብታችን እስኪከበርልን ድረስም በቁርጠኝነትና በሰላማዊነት ትግላችንን እንቀጥላለን፡፡
ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለም!

አላሁ አክበር!

1 Comment

  1. መንግስት የለም ወይ: የለም ም ብለዋል:: ልብ ካለህ እሱንም መጻፍ ነበረብህ::

Comments are closed.

016
Previous Story

‹‹313 ሚሊዮኑ ለልማት!›› በሚል መሪ ቃል የተደረገው የሚያዚያ 18 አገር አቀፍ ተቃውሞ ቪዲዮዎች

nail 2
Next Story

የጥፍርዎ ቀለም ስለጤናዎ ምን ይናገራል? (ሊያነቡት የሚገባ)

Latest from Blog

ህገ መንግስታዊ ዲዛይን ምርጫዎቻችን የትኞቹ ናቸው?

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com ) እኛ ኢትዮጵያዊያን እራሳችንን ስንገለጽ የረጂም ግዜ ሥልጣኔና ታሪክ ያለን፣በነጭ ያልተገዛን፣ከ2000 አመት በላይ ተከታታይ የመንግስት ሥርዓት ያለን፣የሦስቱ ዘመን ያስቆጠሩ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች አገር ነን እያልን ነው። ነገር ግን ባለፉት ሃምሳ አመታት

የኢካን ዓላማ በኔዘርላንድ የሚኖረውን ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያውያንን ኮምዩኒቲይ የማሰባሰብ ሳይሆን የመከፋፋልና የማዳከም ተልኮን ያነገበ ነው።

አገር ! ለየአንድ ሠው ቋንቋው፣ ልማዱ፣ ባሕሉ፣ እምነቱ፣ አስተሳሰቡ፣ ወጉና በአጠቃላይ እሱነቱና ማንነቱ የሚከበርበት ብቸኛ ሥፍራ ነው። ኢትዮጵያውያንም በስደት በሚኖሩባቸው አገራት ሁሉ እነኝህን በስደት ያጧቸውን የግልና የጋራ ማንነቶቻቸውን በአንድ ላይ ሆነው ለመዘከር

ፋኖ ምሽጉን ደረመሰው ድል ተሰማ | ” ስልጣን እለቃለሁ ” ፕረዚዳንቷ | ህዴድ ድብቅ ስብሰባ በአዲስ አበባ | “ተመስገንን በመዳፌ ስር አስገብቼዋለሁ” አብይ

-966+9-የኦህዴድ ድብቅ ስብሰባ በአዲስ አበባ “ተመስገንን በመዳፌ ስር አስገብቼዋለሁ” አብይ – ስልኩ ተጠለፈ “እኛ የምን’ዘጋጀው ለፋኖ ሳይሆን ለኤር-ትራ ነው” አበባው|”በጊዜ ቦታ አዘጋጁልኝ” አረጋ

አንድ በኢኮኖሚና በሌሎች ነገሮች ወደ ኋላ የቀረች አገር አንድን ኃያል መንግስት በመተማመንና ጥገኛ በመሆን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማምጣትና የተሟላ ነፃነትን መቀዳጀት ትችላለች ወይ?

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) ሰኔ 4፣ 2016 (ሰኔ 11፣ 2024)   በዚህ አርዕስት ላይ እንድጽፍ የገፋፋኝ ዋናው ምክንያት ሰሞኑኑ ዶ/ር ዮናስ ብሩ የቻይንንም ሆነ የቬትናምን በኢኮኖሚ ማደግ አስመልክቶ ሁለቱ አገሮች እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት ከአሜሪካ ጋር

ፋኖ አንድ ሌሊት አያሳድረንም” የአማራ ብልፅግናየኢሳያስ ግዙፍ ጦር ወደ ወልቃይት

ፋኖ አንድ ሌሊት አያሳድረንም” የአማራ ብልፅግናየኢሳያስ ግዙፍ ጦር ወደ ወልቃይት አብይና ዳንኤል ክብረት ጉድ አሰሙ-|ጀነራሉ በቁ*ጣ ተናገሩ-‘ህዝቡ ጉድ ሰራን’-|“ብልፅግናን ራ*ቁቱን አስቀርተነዋል”-|ታዳሚው ባለስልጣናቱን አፋጠጠ
Go toTop