April 23, 2013
23 mins read

‹‹በዓሉ ግርማ በባህርዳር ››‎ – ሊያነቡት የሚገባ

ከዓለማየሁ ገበየሁ

ሰሞኑን ለስራ ወደ ሰሜን ስጓዝ በውስጤ ግዘፍ ነስቶ የቆየው የበዓሉ ግርማ ጉዳይ ነበር ፡፡ በቂ ግዜ ካገኘሁ ‹ የፌስ ቡክ ሰራዊት › ሲወያይበትና ሲከራከርበት ለከረመው አጀንዳ ቢቻል የተጠጋጋ ካልሆነም እንደነገሩ የቆመ መረጃ አሰባስቤ እመለሳለሁ ስል አሰብኩ ፡፡

የዜናው መነሻ ፤

‹‹ ከወደ ባህር ዳር አካባቢ የተሰማው ወሬ በርካቶችን እያስገረመና እያስደነገጠ ይገኛል … ደራሲ በዓሉ ግርማ በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ውስጥ አለም በቃኝ ብሎ ሞንኩሶ እግዚአብሄርን እያገለገለ መሆኑ ታውቋል … በይስማዕከ ወርቁ ደራሲነት የምናውቃቸው ዴርቶጋዳ ፣ ራማቶሃራ ፣ ዣንዣራ እና ተልሚድ የተሰኙ ስራዎች የደራሲ በዓሉ መሆናቸው ተረጋግጧል … ይህ ወሬ ከተሰማ በኃላ በርካታ የባህር ዳር ነዋሪዎች የዳጋ ደሴትን ያጨናነቁ ሲሆን የአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ነዋሪዎችም በአስገራሚ መልኩ ወደ ስፍራው እየተመሙ ናቸው … ››

ይህን ዜና ያለማመንታት ‹‹ የማይታመን ›› ያሉ የመኖራቸውን ያህል ‹‹ ትክክለኛ ነው ›› እንዲሁም ‹‹ ትክክል ሊሆን ይችላል ›› የሚሉ ግምቶችን ያስቀመጡ ጥቂቶች አልነበሩም ፡፡ እኔም ‹‹ የደራሲዎች እየሱስ ! ›› የምለውን የበዓሉን ብዕር ከአድማስ ባሻገር እስከ ኦሮማይ እንደ ማስቲካ እያላመጥኩ ፣ ድዴ ሲደክም ደግሞ ወሬውን ለስራ ባልደረቦቼ በማካፈል መቋጫ የሌላው ክርክር እንዲነሳ ማድረጌ አልቀረም ፡፡

ከዚህ ቀደም ባለው አነጋገር ለመሞቱ ፣ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ ለመጥፋቱ ምክንያት የሆነው ኦሮማይ የተባለውን መጽሀፍ … የማላቀውን የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም … እንደ አብርሃም ቤት የለኝ እንደ ሙሴ መቃብሬ አይታወቅ የሚለውን የደራሲው ገጸ ባህሪ… ጽሁፍ ህይወት ነው ከዚያ ውጪ ሌላ የህይወት ምኞት የለኝም የሚለውን በዓሉንና በሰበቡ የተነሱትን እነ ዴርቶጋዳ … ወደ ገዳም ለመጓዝ ሁከትና ጉጉት የሚታይበትን የባህርዳር ህዝብ… ተራ በተራ እየሳልኩ ነበር ባህርዳር የደረስኩት ፡፡

የማጣሪያ ወሬ ፤

በበዓሉ ግርማ ዙሪያ የተነሳውን ዜና ወይም ወሬ ለማጣራትና ወደ አንድ አቅጣጫ ለማምጣት በጉዳዩ ዙሪያ የሚወዳደሩ ክፍሎችን ወይም የሊግ አባላትን ማብዛት ያስፈልጋል ፡፡ ጋዜጠኛም ጸሀፊም በመሆኔ ነው መሰል አስቀድሜ የጨዋታውን ንድፍና ህግጋት / sketch / ለመሳል ያልቦዘንኩት ፡፡ በዚህ ፍትጊያ መሃል ነው ለእውነት የተጠጋ መረጃ ሊገኝ የሚችለው ወይም የተሰወረ መንገድን ማወቅ የሚቻለው ፡፡

እናም የባህርዳር ነዋሪዎች ፣ የተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች / ፖሊስ ፣ ባህልና ቱሪዝም ፣ ጋዜጠኞች / ፣ ቀሳውስት ፣ መጽሀፍት ሻጮች ፣ አንባቢዎች ፣ የጀልባ አከራዮችና የዳጋ እስጢፋኖስ አስተዳደሮች በማጣሪያው እንዲሰለፉ አቀድኩ ፡፡ የትኛው ቡድን ወይም የትኛውም መንገድ ለፍጻሜ እንደሚደርስ ለመተንበይ ግን አልሞከርኩም ፡፡

በጉዳዩ በጣም ተጨናንቋል የተባለውን የባህር ዳር ነዋሪ እኔ ያገኘሁት በሁለት መልኩ ነው ፡፡ አንደኛውና በጣም የሚበዛው ጭራሽ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ ያልሰማና ምንም መረጃ የሌለው ነው ፡፡ ሁለተኛው ክፍል ስለ ጉዳዩ የሚያውቅ ነገር ግን የተለያዩ መላምቶችን ደርዝ በሌለው መልኩ ያዘለ ነው ፡፡ አንዳንዶች ‹‹ እስካሁን ይወራል እንጂ የታመነ ዜና አልተገኘም ›› ይላሉ ፡፡ ሌሎች ‹‹ ተጨባጭ መረጃ ባይገኝም በዓሉ ግርማ ገዳሙ ውስጥ ሊኖር እንደሚችል ይሰማናል ›› ብለዋል ፡፡ ወሬው ሀሰት ነው ከሚሉት ውስጥ ዜናው ተቀነባብሮ የተፈጠረው በጀልባ አከራዮች ነው ያሉት ጥቂቶች አይደሉም ፡፡ ለምን ለተባለው ጥያቄ ደግሞ ‹‹ ገበያ ለመፍጠር ›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ደራሲው ገዳም ውስጥ ሊኖር ይችላል የሚሉ ወገኖች ዋነኛ መከራከሪያ ደግሞ በዓሉ በደርግ ተይዞ ተሰወረ ተባለ እንጂ ስለመሞቱ ማረጋገጫ ያለመገኘቱን ጉዳይ ነው ፡፡

በርግጥ የበዓሉ ግርማ ወሬ በፌስ ቡክ ከተለቀቀ በኃላ በባህርዳር የሚገኙ የመንግስት አካላት ጉጉትና ውጥረት ገኖ ቆይቷል ፡፡ አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ የመንግስት ሰራተኛ የተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊዎች ወሬው እውነት ይሁን ሀሰት እንዲጣራ በተለያዩ መንገዶች በገዳሙ ውስጥ ፍለጋ እንዲከናወን አድርገዋል ፡፡ ይህም ጥረት የገዳሙን ነዋሪ ከማጨናነቅ የዘለለ ተጨባጭ ፋይዳ ያስገኘ አልነበረም ፡፡ አንዳንድ የፖሊስ ሰራዊት አባላትም ወሬውን ሊያረጋግጥ የሚችል መረጃ ባለመገኘቱ እውነት ነው የሚል እምነት የለንም ብለዋል ፡፡

ርዕሰ ጉዳዩ ጋዜጠኞችም ሰፈር ደርሷል ፡፡ ጋዜጠኞችም ወሬው ህብረተሰቡ ምርጫውን በአግባቡ እንዳያከናውን ለማደናቀፍ ወይም ለማዘናጋት የሚደረግ ጥረት እንደሆነ ገለጻ ተደርጎላቸዋል ፡፡

በባህርዳር ከተማ ጥቂት የማይባሉ መጽሀፍት መሸጫ መደብሮች ይገኛሉ ፡፡ በዚህ ወሬ ምክንያት የበዓሉ ግርማ መጽሀፍት ከወትሮው በተለየ መልኩ ሊሸጡ እንደሚችሉ ገምቼ ነበር ፡፡ ይህን ግምት ይዤ አራት ከሚደርሱ ነጋዴዎች ጋር ተወያየሁ ፡፡ ሁሉም ስለ ወቅታዊው ወሬ ከበቂ በላይ መረጃ ቢኖራቸውም በዚሁ ሰበብ የበዓሉ ግርማ መጽሀፍት እንዳልተሸጡ ተናግረዋል ፡፡ ሁለቱ ሚያዚያ ውስጥ የተሰማው ወሬ ‹ የአፕሪል ዘ ፉል › ውጤት መሆኑን ሲናገሩ ሁለቱ ደግሞ ማንኛውም ወሬ ውስጥ ጥቂት የእውነት ፍሬ ሊገኝ እንደሚችል ጠቋቁመዋል፡፡ በየግዜው ለገዳሙ በርካታ መጽሀፍት እየተገዙ መግባታቸው የትላልቅ ሰዎች መናኀሪያ መሆኑን ለማስረዳት በመሞከር ፡፡

ሰው በሰው ያገኘኃቸው ቀሳውስት ወሬው ከተማው ውስጥ እንጂ በገዳሙ እንደማይሰማ ተናግረዋል ፡፡ ለብዙ ዓመታት በገዳም ውስጥ ህይወታቸውን ያቆዩ አባቶችን የትናንት ማንነት ለማወቅ ከባድ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ብዙም ጠቃሚ እንዳልሆነም አስረድተዋል ፡፡ አለም በቃኝ ብሎ ከፈጣሪ ጋር ለመገኛኘት የሚተጋ ህብረተሰብ የቀደመውን ማንነት ማስታወስ ምን ይረባዋል በማለትም ጫጫታውን ለማርገብ የሞከሩም ይመስላሉ ፡፡

ይህ የጥቂት ቀናት አሰሳ ከጥሩ አንባቢያን ጋርም አገናኝቶኛል ፡፡ በተለይ አንድ አንባቢ ‹ ጥሩ ቀልድ ናት › ነው ያለኝ ፡፡ ይህ ሰው ወሬው ሆን ተብሎ ተቀነባብሮ የተፈበረከው የመቀበል ጸጋ በተሳናቸው ጠማማ ሰዎች ምክንያት እንደሆነ ነው የሚያምነው ፡፡ እሱ ጠማማ ሰዎች የሚላቸው የይስማዕከ ወርቁን ችሎታ ለመቀበል የተናነቃቸውን ነው ፡፡ ወጣቱ ደራሲ ያልተጠበቁ ስራዎች መስራቱ የቅናትና የመበለጥ ስሜታቸው እንዲቆጣ ምክንያት ፈጥሯል ፡፡ እናም ህያው ውብ እጅን ከማድነቅ ይልቅ ለሰበብነት የሞተ ማንነትን እንደ ምክንያት መጠቀም ተመርጧል ፡፡

ወሬውን መንግስት ራሱ ሆን ብሎ ያሰራጨው መሆኑን በልበ ሙሉነት የሚናገሩም አጋጥመውኛል ፡፡ ይህ ዓይነት አከራካሪና በቀላሉ እልባት ሊያገኝ የማይችል መረጃ የሚለቀቀው ወቅታዊ ጉዳዮችን ወይም ውጥረቶችን ለማርገብ ሲፈለግ ነው ፡፡ መንግስት ከሙስሊሙ ህብረተሰብ ጋር መጋጨቱ ፣ ከተለያዩ ክልሎች የተፈናቀለው የአማራ ብሄረሰብ ጉዳይ መነጋገሪያ መሆኑን እንደ ምክንያት ያነሳሉ ፡፡ በተቃራኒው የበዓሉ ግርማ በዳጋ እስጢፋኖስ የመታየት ጉዳይ ለገዢው ክፍል የሚመች ዜና ያለመሆኑን ያስረዱ አሉ ፡፡ እንዴት ሲባሉ የበዓሉ በህይወት መገኘት የደርግን ገዳይነትና ጨካኝነት እንዲለዝብ ስለሚያደርግ በኢህአዴግ አይን መታየት ያለበት ጉዳይ አያደርገውም ፡፡ በመሆኑም ለገዳሙም ሆነ ለደራሲው ቀጣይ ስጋት እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል ፡፡

መንገዶች ሁሉ ወደ ጣና ይወስዳሉ ፤

ከሰማኃቸው መረጃዎች መካከል ዳጋ እስጢፋኖስ የዶክተሮች ፣ የምሁራኖችና በንባብ የመጠቁ በርካታ ሰዎች ስብስብ ገዳም ነው የሚለው አስተያየት ከፍ ብሎ ይሰማኛል ፡፡ በገዳሙ ለሚገኙ ሰዎች አንዳንድ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት በጎ አድራጊዎች መጽሀፍና ቁሳቁስ የሚረዷቸው ከምን አንጻር ነው ? የሚለውም ጥያቄ የጥርጣሬ ሚዛን ወደታች ዝቅ ብሎ እንዲመዝን የሆነ አስተዎጽኦ ሊያደርግ ይችላል ፡፡ በርግጥ ዳጋ እስጢፋኖስ ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነና ከሌሎቹ ገዳማትም ልዩ ገጽታ እንዳለው ይታወቃል ፡፡ የገዳሙ ህንጻ የጀልባ ቅርጽ ያለው ሲሆን የዚህ ተምሳሌትም የኖህ ጀልባ የሰው ዘርን ከጎርፍ ጥቃት የማዳኑን ምስጢር ይጠቁማል ፡፡

በዓሉ ግርማ በዚህ ደንና ዋሻ ውስጥ ተደብቆ ይሆን ? ‹ ተፈጸመ › ን ለንባብ አበርክቶ የፍጻሜው ማረፊያ ትሆን ዘንድ በኖህ ጀልባ ተሳፍሮ ይሆን ? ሽቅርቅሩና ታጋዩ ደራሲ በርግጥ ጭምተኛና ገዳማዊ መሆንን መርጧል ? ከሆነ እንዴት ከባድ ምርጫ ነው ፡፡ ምክንያቱም አንድ ገዳማዊ ጤዛ ልሶ ፣ ድንጋይ ተንተርሶ ፤ ድምጸ አራዊትን ግርማ ሌሊትን ታግሶ ነው የሚኖረው ፡፡ አንድ ገዳማዊ ከዓለማዊ ኑሮ ርቆ ፣ ራሱን በራሱ እየረዳ ዘወትር በጾምና ጸሎት ፣ በገድልና ትሩፋት ተጠምዶ የሚኖር የእግዚአብሄር ሰው ነውና ፡፡

እንደ ጣና ማዕበል ግራና ቀኝ የሚላተመውን ሀሳብ ይዤ ወደ ጣና ኃይቅ የግል ጀልባ ማህበር አመራሁ ፡፡ እዚህ ወደ ዳጋ እስጢፋኖስ የሚቀዝፉ ጀልባዎች ይገኛሉ ፡፡ እዚህ ወደተለያዩ ገዳማት የሚጓዙ ሰዎችን ሀሳብና ፍላጎት እንዳልሰሙ ሆነው የሚሰሙ የጀልባው ካፕቴኖች ይገኛሉ ፡፡ እዚህ ስለገዳማቱ የቀረበ መረጃ ያላቸው ሰዎች አይጠፉም ፡፡ እዚህ የሀሰት ፈጠራ ሊፈበረኩ ይችላሉ ተብለው የሚታሙ ሰራተኞችም አሉ ፡፡

ሰላምታ ሰጥቼ ወደቢሮው ከዘለቅኩ በኃላ ስለ ስራ ጉዳይ ማውራት ጀመርኩ ፡፡ የማህበሩ ኃላፊ የሞቀ አቀባበል አደረገልኝ ፡፡ ሞተሬን ካሞቅኩ በኃላ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ መጠየቅ ጀመርኩ ፡፡

‹‹ በዓሉ ግርማ በዳጋ እስጢፋኖስ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል ›› በማለት ማጋደል ያቃተው ምላሽ ወረወረልኝ
‹‹ እንዴት ነው ሊኖር የሚችለው ? ››
‹‹ ገዳሙ የምሁራን አምባ ስለሆነ ››
‹‹ እንዴት ነው የማይኖረውስ ? ››
‹‹ ምክንያቱም እስካሁን እኔ አይቸዋለሁ የሚል ሰው ስላልተገኘ ››
‹‹ ወሬው ከተሰማ በኃላ ወደ ዳጋ የሚሄደው ጎብኚ ቁጥር በዝቷል ? ››
‹‹ እንግዶች ይሄዳሉ ፡፡ ግን ደራሲውን ፍለጋ ነው ብለው አይናገሩም ››
‹‹ ይህ ወሬ ታዲያ ከየት መጣ ? ››
‹‹ ከፌስ ቡክ ነው ! ››
‹‹ ከእናንተ ነው የሚሉም አሉ ፡፡ ማለትም ገበያ ለመፍጠር ››
‹‹ ዉሸት ነው ! እኛ ያልተረጋገጠ ወሬ ለደንበኞች አንናገርም ፡፡ ይኀው እንዳንተ በርካታ ሰዎች እየመጡ በዓሉ ካለ ልሄድ ነው መረጃ ንገረኝ ይሉኛል ፡፡ እኔ ገንዘብ ብፈልግ አደርገዋለሁ ፡፡ በግልጽ የምነግራቸው ምንም መረጃ እንደሌለኝ ነው ፡፡ የምመክራቸውም መሄድ ያለባቸው ገዳሙን የመጎብኘት ፍላጎት ካላቸው ብቻ መሆኑን ነው ››
‹‹ እውነት ስለ በዓሉ ምንም አላውቅም ነው የምትለኝ ? ››

ኃላፊው የሚያውቀውን በትክክል እንደገለጸልኝ ደጋግሞ ነገረኝ ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ግን የአንድ ሰው ስም ጠራና የተሻለ መረጃ ሊገኝ እንደሚችል ጠቆመኝ ፡፡ ወጣቱ የሚሰራው በዳጋ እስጢፋኖስ ጀልባ ላይ ነው ፡፡ ጀልባዋ ሁለት ጥቅም ትሰጣለች ፡፡ አንደኛው የገዳሙን አባላት ካሉበት ወደ ከተማ ፣ ከከተማ ወደ ገዳም ማመላለስ ሲሆን ሁለተኛው ጎን ለጎን ወደ ገዳሙ የሚጓዙ ሰዎችን በተለመደው ታሪፍ ታጓጉዛለች ፡፡ የጀልባዋ ካፕቴን አንተሁን ጥበቡ በገዳሙ የሚኖር ሲሆን የማስጎብኘትም አገልግሎት ይሰጣል ፡፡

ቀጠሮ ለመያዝ ስደውልለት ወደ ክብራን ገብርኤል እንግዶችን ይዞ እንደሄደ ገለጸልኝ ፡፡ ሌላ እድል ስላልነበር የስልክ ቃለ መጠይቁን ማድረግ አንደሚገባኝ ወዲያው ወሰንኩ ፡፡ ዳጋ ውስጥ ከመቶ በላይ መነኮሳት እንደሚገኙ የገለጸው አንተሁን ወደ ገዳሙ የገባ ሰው ራሱን ደብቆ የሚኖር በመሆኑ ተፈላጊውን ለይቶ ለማወቅ ያስቸግራል ባይ ነው ፡፡ በዓሉ ግርማን በፎቶ እንኳ እንደማያውቀው ፣ በቦታው ኖሮ ቢያየው እንኳ ትርጉም እንደሌለው አስረድቷል ፡፡ ብዙዎቹ የበሰሉና ምሁራን ሆነውም ራሳቸውን ምንም እንደማያውቅ መሃይም አድርገው ለመኖር የሚያደርጉት ጥረት ምስጢራዊው ህይወት ምን ያህል ከባድ መሆኑን የሚያስረዳ ነው ፡፡ በዚህም ምክንያት እስካሁን ለጠየቁኝ ሰዎች የሰጠሁት ምላሽ አላውቅም የሚል ነው ብሏል ፡፡ ደራሲውን በአካል የሚያውቀው ሰው ለአዳር መጥቶ መፈለግ እንደሚኖርበትም ሃሳብ ሰጥቷል ፡፡

የገዳሙን ሰው አመስግኜ ወደ ጣና ዳር ተጠጋሁ ፡፡ አያሌ ጀልባዎች ወታደራዊ ሰልፍ ይዘው እንግዶቻቸውን ይጠባበቃሉ ፡፡ ጀልባዎቹ ከተደገፉበት ግንብ አናት ላይ ጉዞን የተመለከተ መረጃ የሚሰጥ ታፔላ ቆሟል ፡፡ የአጭርና ረጅም ጉዞ ታሪፍ ነው ፡፡ ዳጋ እስጢፋኖስ የአጭር ጉዞ ዝርዝር ውስጥ የለም ፡፡ በረጅሙ ጉዞ ውስጥ በሁለተኛ ረድፍ ላይ ግን ጎልቶ ይታያል ፡፡ በብረት ጀልባ ለመሄድ 1700 ብር ፣ በፋይበር ጀልባ ከሆነ ደግሞ 2200 ብር ያስጠይቃል ይላል መልዕክቱ ፡፡

ካፒቴኑ እንደነገረኝ ዳጋ ለመድረስ አራት ሰዓት ይፈጃል ፡፡ ማደር ካለ ደግሞ ክፍያው ከፍ ይላል ፡፡ የቀረኝ እንጥፍጣፊ መረጃ ቢኖር ገዳሙ ራሱ የሚነግረኝ ነው ፡፡ በሁለት ምክንያት ግን ወደ ምሁራኑ አምባ ለማቅናት አልችልም ፡፡ የመጀመሪያው ወደ ደባርቅና ሁመራ ቀሪ መንገድ ስለሚጠብቀኝ የሚያወላዳ ግዜ የሌለኝ መሆኑ ነው ፡፡ ሁለተኛው ገንዘብ ነው ፡፡ ግዜን ከመንግስት ስራ ቀነጫጭቤ ማትረፍ ብችል እንኳ ገንዘብን ከራሴ ኪስ ለመስረቅ አልቸልም – ከባዶ ኪስ ፡፡

ባዶነት ተሰማኝ ፡፡ ውጤቱ ምንም ሆነ ምን ገዳም ላይ የሚደረገውን የመጨረሻ ፍለጋዊ ውድድር መመልከት ነበረብኝ ፡፡ እንደ ሀገሬ ብሄራዊ ቡድን እያለቃቀስኩም ሆነ እየዘፋፈንኩ ስፖንሰር ለመጠየቅ ዕድል አልነበረኝም ፡፡ ለብሄር ብሄረሰቦች በዓል የተገዛችውን ህብር የተባለች የክት መሳይ ጀልባ እየቃኘሁ ሀይቅ ላይ ወደቆመው ጣይቱ መዝናኛ በዝግታ አመራሁ ፡፡ የኔ አሰሳ በዚሁ ተፈጸመ ፡፡ ‹ ተፈጸመ › የሚባለው የበዓሉ ግርማ ጀግና ወይም ‹ ጦሰኛ › መጽሀፍ ግን እንዲህ ይላል ‹‹ ህይወት አንድ ቦታ ላይ አትቆምም … ትቀጥላለች ያንዱን ህይወት ከሌላው ጋር ድርና ማግ እያደረገች … ››

ኦሮማይ !!!

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop