ኢህአዴግ በግዳጅ ገንዘብ አምጡ በማለት ነጋዴውን እያናደደ ነው

በአዲስ አበባ የሚገኙ ባለሃብቶች  ኢህአዴግ ለሚያዚያ 2005 ዓ.ም.  ለሚደረገው የአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ  አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫ ብቻውን  እየተወዳደረም ለምርጫ ቅስቀሳ በሚል  በግዳጅ ገንዘብ እየጠየቀ ህገወጥ  ድርጊት እየፈፀመ እንደሆነና ድርጊቱም  እንዳማረራቸው ለፍኖተ ነፃነት ገለፁ፡፡  “እኛ ሳንፈልግ ለኢህአዴግ ምርጫ
ቅስቀሳ የሚሆን ገንዘብ አዋጡ የሚል  እደምታ ያለውና የመንግስት መስሪያ  ቤት ማኀተም ያረፈበት አስገዳጅ  ደብዳቤ በየድርጅቶታችን ስም እየላኩ  የመኖርና የመስራት ነፃነታችንን  እየተጋፉ ነው” ሲሉ ቅሬታ የተሰማቸው  ነጋዴዎች ለፍኖተ ነፃነት ጠቁመዋል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ  ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት መጋቢት 20 ቀን  2005 ዓ.ም. በወረዳው ማዘጋጃ ቤት  አገልግሎት ጽህፈት ቤት ማኀተም  ባረፈበትና የወረዳው ባህልና ቱሪዝም  ቢሮ የስልክ አድራሻን በመጠቀም  የተላከው ደብዳቤ “…ባለድርሻ አካላት”  ላላቸው “የኢህአዴግ አባላት፣ አጋር  ድርጅቶች፣ታዋቂ ካምፓኒዎች፣ ሪል   ስቴቶች፣ ግለሰቦች፣ መንግስታዊ  ያልሆኑ ተቋማት” በሚል ከተላከው  አስገዳጅ ደብዳቤ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡  ከዚህ በተጨማሪ በተላከው ደብዳቤ  ማጠቃለያ ላይ አስገዳጅነቱን በግልፅ  በሚያሳይ ማስፈራሪያ “…የዚህ  ፕሮግራም ማጠቃለያ የሚሆነው  ለሚመለከተው አካል ጊዜውን የጠበቀ  ዘገባ ማድረግ ይሆናል፡፡ ከዚህ በመነሳት  ኢህአዴግን መምረጥ የሀገራችንን ህዳሴ  ወደ ሌላ ምዕራፍ ማሸጋገር ስለሆነ አገረ  ባለሃብቶችና ጥያቄ የቀረበላችሁ አካላት  አስፈላጊውን ታደርጉ ዘንድ ማሳወቅ  ነው::” በሚል ከፈቃደኝነት ይልቅ  አስገዳጅነት ያለው ደብዳቤ በመላክ  ምላሽ እንድንሰጣቸው ይጠይቁናል  ሲሉ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ  ባለሃብቶች ከመረጃ ጋር አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢህአዴግ ብቻውን 

ሆኖ ይህን ህገወጥ ድርጊት መፈፀሙ  የከዚህ በፊቱ ልምዱን ነው የሚያሳየው፣  ይህ አዲስ አይደልም፤ እንደውም ይባስ  ብሎ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት  እንኳ የእሱ አጋር መሆናቸውን መግለፁ  ኢህአዴግ ህገወጥ መሆኑንና ምን ያህል  የዘቀጠ የፖለቲካ ድርጅት መሆኑን ነው  የሚያረጋግጠው ሲሉ ያነጋገርናቸው   የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገልፀውልናል፡፡  ይህንንም በሚመለከት ምርጫ ቦርድ  ምን ይላል የሚለውን ለማረጋገጥ ጥረት  ብናደርግም ለጊዜው አልተሳካም፤ ከዚህ   በተጨማሪ በመንግስት ማኀተምና  አድራሻ የኢህአዴግ ምርጫ ቅስቀሳ  ደብዳቤ በትነዋል ከተባሉት መካከል  በአዲስ አበባ የንፋስ ስልክ ላፍቶ  ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ዋና ስራ  አስፈፃሚ የሆኑት አቶ  ስለሺ ካሳ  መልስ እንዲሰጡን ብንሞክርም  ያልተሳካ ሲሆን በወረዳው የመንግስት  ቢሮ ውስጥ የህዝብ አደረጃጀት ኃላፊ  በህዝብ ደመወዝ የኢህአዴግ ጽህፈት  ቤት ስራን የሚሰሩት አቶ በረከት  ዮሐንስ በበኩላቸው እኛ እንዲህ  አላደረግንም በማለት ምላሽቢሰጡም  በዝግጅት ክፍላችን የሚገኘው ሰነድ  ግን በባለስልጣኑ ስምና ፊርማ  ደብዳቤው መበተኑን ያረጋግጣል፡፡ 

የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ይህ የገዢው ፓርቲ ህገወጥ ድርጊት  በመላው አዲስ አበባ መፈፀሙን  በማረጋገጡ የደብዳቤውን ቅጂ ለምርጫ  ቦርድ ህዝብ ግንኙነት ክፍል ተሰጥቶ የቦርዱን ምላሽ እየጠበቀ ይገኛል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ="ብልፅግና በአስተሳሰብ፣ በቁጥርም ሆነ በአደረጃጀት ብቃት ያለው ግዙፍ ፓርቲ ነው!፦ዐቢይ አሕመድ
Share