ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
“ይድረስ ለእገሌ” ማለቱ ሰለቸኝና ተውኩት እንጂ ዛሬም መጻፍ የፈለግሁት የአማራን ዕልቂት ለመታደግና የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለማብሰር እየተዋደቁ ላሉት ወገኖቼ ነው – በፋኖም ይሁን በሌላ ስም፡፡ ኢትዮጵያን ወደቀደመ ክብሯ ለመመለስ የነገድና የጎሣ ልዩነት ሊኖር አይገባም፡፡ ሀገራችን ክፉኛ ተዋርዳለች፡፡ (የአሜሪካን መሪዎች የአፄ ኃይለ ሥላሤን እጅ ለመጨበጥ እንዳልተሯሯጡ ዛሬ “በሥርዓተ ሲመታችሁ እንድገኝ እባካችሁ ጋብዙኝ” ብሎ የሚለምንና ያልተሳካለት አብዶ የሚያሳብድ ወፈፌ ሰው ገጥሞን ሀገራችን ተዋረደች፡፡)
መግቢያየ እንዲህ ቢሆን እመርጣለሁ፡- አማራም ሆነ ኢትዮጵያ አይጠፉም፡፡ እንዲያውም ከቀድሞው ባማረባቸው ሁኔታ እንደእባብ አሮጌ ቆዳቸውን ገሽልጠው ጥለው በአዲስ መልክ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይከሰታሉ፡፡ ይሄ አስመሳይና አጭበርባሪ በአማራና በኢትዮጵያ ስም የሚነግድ አጋሰስ ሁሉ ዋጋውን የሚያገኝበት ጊዜ በፍጥነት እየመጣ ነው፡፡ አማራ ሆኖ አማራን በመሸጥ የማይበላውን ሀብትና የማያዝበት የማይናዝዝበትን ጥሪት በፎቅና በፋብሪካ ስም የሚያከማች ሁሉ ከየት መጣ ሳይባል ልክ እንደሎስ አንጀለሱ ሰደድ እሳት ድንገት በሚነሣ በላ ወይም መለኮታዊ ውርጅብኝ ከነሀብት ንብረቱ የዶግ ዐመድ ይሆናል፡፡ አማራን ባወጣ ሸጦ ከብአዴንና ከብልጽግና የአንድ ሰው ፓርቲ የተጠጋ ኅሊናቢስ ከርሣም ሁሉ ይገባበትን የሚያጣበት ዘመን እየመጣ ነው፡፡ የፋኖ መሪ ሆኖ፣ የፋኖ አዋጊ ሆኖ፣ የፋኖን ጦር በመመሥረት ትልቅ ድርሻ ኖሮት ነገር ግን ሀብትና ንብረት፣ ሥልጣንና ሥጋዊ ድሎት አማልሎት ትግሉን የከዳና በባንዳነት ኦሮሙማን እያገለገለ ያለ ወራዳ ባንዳ ሁሉ ማንም ይሁን ማን የነአንሻ ደም፣ የነውባንተ ደም፣ የነአምባቸው ደም፣ የነአሣምነው ደም፣ በነፃነት ትግሉ ሲዋደቁ የተሰውት የእልፍ አእላፋት አማራውያንና ሌሎችም ዜጎች ደም በመጨረሻው ይፋረደዋል፡፡ አምላክን ለብቀላ የሚያማው የለም፤ ራሱም “በቀልን ለኔ ተውልኝ” ብሏልና፡፡ በዚያ ላይ የደርግን መጨረሻ አስብ፣ የወያኔን መጨረሻ አስታውስ፣ የነሂትለርንና ሙሶሊኒንም አትዘንጋ፡፡ የውሻን ደም በከንቱ የማያስቀረው አምላክ፣ የሁሉም ፈጣሪና ሁሉንም እንደየሥራው የሚከፍለው አምላከ ሰማይ ወምድር የፖለቲካ ጠ/ሚኒስትርና የሃይማኖት ፓትርያርክ ብሎ ሳይለይ ለሁሉም እንደዬሥራው ይከፍለዋል – “ለለአሃዱ በበምግባሩ” እንዲል መጽሐፉ፡፡ አበቃ፡፡ ከዚህ ነባራዊ እውነት የሚወጣ ምንም ነገር የለምና በዚህ እንጽናናለን፡፡ ችግሩ የሰማዩ አምላክና የኛ የምድራውያን የጊዜ ሥሌት መለያየቱ ነው፡፡ ለዚህም ነው በ“አይነጋ መስሏት…” እነኦሮሙማ ይሠሩትን ያጡት፡፡
ወደዋናው ነጥብ ገባሁ፡፡ በፋኖ አካባቢ የሚሰማው ነገር ደስ አይልም፤ እነሱን በጉጉት ለሚጠብቅ ክፉኛ ያስከፋል፡፡ የሚወራውን ሁሉ ከሰማንና ካመንን ደግሞ ተስፋ የምንቆርጠውና ለዕብደትም የምንዳረገው ዜጎች ጥቂት አንሆንም፡፡ ነገር ግን “ዋ ብሎ ጉርስ አይቀርም” እንደሚባለው በምንሰማው ነገር አእምሯችንን ልናጣ የተቃረብን ሁሉ ከሰው ጋር ስንገናኝ ጭንቀታችንን እንደምንም እየረሳን ደህና ሰው ለመሆን እንሞክራለን፡፡ እንጂ እንደምንሰማውማ ቢሆን …
በጣም የምታምኑት አታጋይ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰችን ሕጻን ደፍሮ የፊስቱላ ችግር ሲፈጥርባት፣ አንቱ የተባለ የትግል አመራር አባል በሴት ደፈራና በልቅ ወሲብ እንዲሁም በሀብት ክምችት ሲታማ፣ የት ያደርሰናል የተባለ አታጋይ የምስኪን አማሮችን ሀብት ንብረት እየቀማና እየዘረፈ አስተሳሰቡ ድፍን ቅል ሲሆን፣ ሰዎችን እያገተና እያሳገተ በሚሰበስበው ገንዘብ በከተሞችና በገጠር ቀመስ ቀበሌዎች ሕንጻና ኢንዱስትሪ ሲገነባ፣ የተዋጊ ፋኖዎችን ችግር ማዳመጥና መፍታት የሚያቅተውና እንዲበተኑም ምክንያት የሚሆነው አመራር እየበዛና ፋኖዎች የትሚናቸውን እየተበተኑ፣ ሀገርና ሥልጣን በሌለበት ሁኔታ ገና ከአሁኑ – “ከብቱ ሳይገዛ ሌባው በረት ሞላ” – እንዲሉ ገና በዋዜማው የሥልጣን ቅርምቱና በሥልጣን ሳቢያ እርኩቻውና መገዳደሉ በዝቶ እየታዬ፣ አንድም ዞን ነፃ ሳይወጣና አንድም የረባ ከተማ ከብአዴንና ጌታው “ብልጽግና” ተፅዕኖ ሳይላቀቅ ባልተጨበጠ ድል ቡራ ከረዩውና ሰበር ዜናው በየቀኑ “እየተበሰረ”፣ … ሁለት ዓመት መዝለቃችን በርግጥም የሚወራውን አሉታዊ ወሬ ላለማመን እንቸገራለን – የዛየር ተቃዋሚ ኃይል እኮ በጥቂት ወራት ነው ከሀገሪቱ ጫፍ ገስግሶ ዋና ከተማዋን ኪንሣሳን የተቆጣጠረው፤ ከጫጫ አዲስ አበባ ታዲያ ስንት አሠርት ዓመታትን ሊፈጅ ነው? “ባልዘፈንሽ፣ ከዘፈንሽ ባላፈርሽ” ይባላል፡፡ ከሺህ ቃላት የሚበልጥ ቆንጆ ሥነ ቃል ነው፡፡ አዎ፣ ታጋይ ደምመላሽ ከጓደኞቹ ጋር ለአማራ ነጻነት በረሃ በመውረዱና ያን ተከትሎ በርካታ የድልና የምርኮ ዜናዎች በየጊዜው በመናፈሳቸው ሕዝብ ተደስቷል፤ የአጋንንቱን ዓለም ወካዩ መንግሥትም በተቃራኒው ፋኖዎች እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ – በአዲስ አበባ፣ በወለጋ፣ በባሌ፣ በሻሸመኔ፣ በአርሲ፣ በሸዋ፣ በኢሉባር፣ ወዘተ. ሕጻን ሽማግሌ ወንድ ሴት ሳይል ባገኘው መሣሪያ አማራን በመግደልና ከቤት ንብረቱ የማፈናቀል ሥራ ላይ ተጠምዷል – በተለይ ላለፉት 7 የመከራና የግዞት ዓመታት፡፡ ይህን መከረኛ ሕዝብ ነፃ ለማውጣት የገቡትን ቃል እውን እንደማድረግ የምንሰማውን የመሰለ እርስ በርስ የመከፋፈልና ትግልን ለአደጋ የማጋለጥ አሳዛኝ መርዶ በታጋዮች መካከል ፈጥሮ በሰነቅነው ተስፋ ላይ ቀዝቃዛ ውኃ መቸለስ የኩነኔዎች ሁሉ ቁንጮ ነው፡፡
የምንሰማው ሁሉ እውነትም ሀሰትም የተጋነነም ሊሆን ይችላል – የከፋፋዮች ሀሰተኛ ወሬ ቢሆን ዕዳው ገብስ ነበር፡፡ የሆነው ቢሆን ግን በመግቢያየ የተናገርኩት እውነት፣ እውነት ነው፡፡ እርግጥ ነው – አሁን ጀልባዋ ክፉኛ እየተናወጠች ነው – ከመስመጥ የምትተርፍ በማትመስል ሁኔታ፡፡ መርከቢቷም እንደዚሁ እየተናጠች ነው፡፡ በጀልባዋ ላይ የተኛው የክርስቶስ ባረርያ ገና አልተነሳም፡፡ አልታዘዘም፡፡ ሲታዘዝና ሲነሳ ግን የሚችለው ማዕበል አይኖርም፡፡ እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ የገባነው መጥራት ያለበት እንዲጠራ ነው፡፡ በል በል የሚለኝ መንፈስ የሚያናግረኝ ይህንን ነው፡፡ የኔ አይደለም፡፡ እኔን በግል ብትሰሙኝ ሌላ ነኝ፡፡ ስለሆነም እንዲጠራ የተፈለገው ሲጠራ፣ በፈተና እንዲፈተንና ማለፉን በተግባር እንዲያረጋግጥ የተፈለገው ሲያረጋግጥ ያኔ የትንቢቱ ሁሉ ፍጻሜ ይሆንና ስደት ወደ ኢትዮጵያ ይሆናል፡፡ እንጂ አሁን ጳጳስ ሆኖ ልጆችን ከየሥፍራው እየወለደ፣ ጳጳስ ለመሆን ከ3 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ገንዘብ እየተከፈለ፣ የንስሃ አባት ብለህ ይዘኸው ሚስትህንና ልጆችህን በዲኤንኤ እየተካፈለ፣ በዋናው ካቴድራል ወለል ላይ ሥዕለ መስቀል አስቀምጦ እንድትረግጠው የ666ን ተልእኮ የያዘ የሀገረ ስብከት አመራር ሀገር ምድሩን ሞልቶት፣ በዚህ ሁሉ መከራና ስቃይ አንድም ምህላ ሊያዝዝ ያልቻለ አጭበርባሪ ሚሊዮነር፣ ሟርተኛና ሴሰኛ የሃይማኖት አባት ካቴድራሎችንና አድባራትን አጨናንቆ ይዞ ከሰማይ መናም ሆነ ምሕረት አትጠብቅ፡፡ ገና አሣራችንን እንበላለን ወንድሜ፡፡ እረኛ የሌላቸው በጎች ለተኩላና ለቀበሮ መጋለጣቸው አሁን አልተጀመረም፡፡ ዱሮም ነበር፡፡ ሃይማኖቱና ፖለቲካው በማን እጅ እንደሆነ ካልገባን ሞኞች ነን፡
በጫካ ላላችሁ ወንድም እህቶቼ! የነጻነት ታጋይ ከሥጋዊ አምሮትና ፍላጎት በተወሰነ ደረጃ ካልራቀና የእውነተኛ ባሕታዊን ጠባይ ካልወረሰ ቢወቅጡ እምቦጭ ነው – አይሆንም፤ የነፃነት ትግል የደምና የአካል ብቻ ሳይሆን የባሕርይ መስዋዕትነትንም ይሻል፡፡ አንዳንድ ፍላቶችን ቀን እስኪወጣ ማፈን ተገቢ ነው – አለበለዚያ ከንቱ ልፋት ነው፡፡ ያ ሁሉ የሰው ኃይልና የመሣሪያ ምርኮ እያለ ትግሉ የተንቀራፈፈው ታጋዮችና አታጋዮች ልክ እንደካህናቱና ደባትሩ ሁሉ እነሱም በዓለም የሥጋ ፍላጎት ተማርከው ስለጠፉ ነው፡፡ እንደሱ ከሆኑ ደግሞ አምላክ ረድኤቱን ይነፍጋል፡፡ ከሁለት ሰይጣናት ለማን ሊያዳላ ይችላል? አዎ፣ ፍርድ ለራስ ነው፤ ፍርድ እንደራስ ነው፡፡ የአምላክን ትኩረት ለመሳብ መደረግ ያለበት አለ – ንጽሕና፡፡ የሣጥናኤልን ትኩረትና ቁሣዊ እገዛ ለመሳብ መደረግ ያለበት ነገር አለ – ርኩሰትና ፀረ-ክርስቶሳዊነት፡፡ ሁለት ወዶ አይሆንም፡፡ ለሁለት ጌቶች መገዛትም አይቻልም፡፡ እንዲያ የሚቻል ቢሆን እኔ አራት ኪሎ አካባቢ ባይሆንልኝ የብዙ ሕንጻዎች ባለቤት ከመሆን የሚያግደኝ ባልነበረ – ለጭዳነቱ ደግሞ እንስሳት እስከ ሰው ሕጻናት በሽ ነው፡፡ ይህን ስል ታዲያ የማንንም ወዝና ጉልበት ሳይበዘብዝ ወይም ኅሊናዊ የፍትኅ ሚዛኑን በጠበቀ ሁኔታ ተገቢውን ዋጋ እየከፈለ ለራሱ በራሱ ጥረትና ድካም ያለፈለትን ሰው ማለቴ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡
ጨው ለራስህ ስል ጣፍጥ፡፡ ከበረኸኞቹ አንዳች የብሥራት ዜና እንጠብቃለን፡፡ ብዙ ጊዜ አይደለም የቀረን፡፡ ዲያስፖራም ሀብታምም ዛሬ በገንዘብህ አርቲፊሺል ደስታን ስላገኘህ እንደዚሁ እንዳለህ የምትኖር አይምሰልህ፡፡ የፈጣሪን ጉብኝት በሁሉም አቅጣጫ እናውቀዋለን፡፡ እናታችን ማሕጸን ብንገባ መለኮታዊ ቅጣትን አናመልጥም፡፡ የምናመልጠው ህግጋቱንና ትዕዛዛቱን በማክበርና ሳት ብሎን ብንተላለፍ ደግሞ በልባዊ ንስሃ ነው፡፡ የኃጢኣት ባርያ አለመሆን ቀዳሚ ምርጫችን ቢሆን የመጀመሪያ ተጠቃሚዎች እኛው ነን፡፡ እግዚአብሔር ለዚያ ፀጋው ያድለን፡፡ አሜን፡፡
አምላክ ሆይ! በቶሎ ናልን፡፡ ኃጢኣተኛ ፍጡራንህ በክፋታችን ምክንያት በተላከብን የኃጢኣተኛ አጋንንት መንጋ እያለቅን ሀገራችንም እየወደመችና እየጠፋች ነውና ፈጥነህ ድረስልን፡፡
——————-
የፋኖ ክንፍ ናችሁ በሚል ጉራጌ ዞን የታሰሩት የአማራ ተወላጆች
የሳፋሪኮም የጥሪ ማዕከል ሠራተኞች አድማ መቱ
ለቸኮለ⬇️⬇️⬇️ pic.twitter.com/a6XjYnaw5X— Wazema Radio | ዋዜማ ሬዲዮ (@Wazemaradio) January 21, 2025