የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበረው እና አሁን ላይ በአማራ ፋኖ በጎጃም የሁለተኛ (ተፈራ ) ክፍለጦር ሰብሳቢ የነበረው ፋኖ ዮሐንስ አለማየሁ በክብር ተሰዋ።
የአማራ ህዝብ የተጋረጠበትን የህሎና አደጋ ለመቀልበስ ያለ እረፍት ከአባልነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት ግንባር ቀደም ትግል ሲያደርግ የነበረው ጀግናው ፋኖ ዮሐንስ አለማየሁ ጥር 12 ቀን ሌሊት ለጥር 13 አጥቢያ ዋሸራ በተባለ ቦታ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት ተናንቆ የክብር መስዕዋትነትን ተቀብሏል ።
ፋኖ ዮሐንስ አለማየሁ በጎንጅ ቆለላ ወረዳ ጎንጅ ወ እንዘግድም በተባለ ቦታ የተወለደ ሲሆን የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ከማጠናቀቁ በፊት “በአማራ ተማሪዎች ማህበር አተማ ” ከፍተኛ አመራር በመሆን ወቅቱ የጠየቀውን ትግል አድርጓል ።
ከዚያም አብይ አህመድ አማራን መውረሩን ተከትሎ ወደ ትውልድ ቀዬው እንዘግድም በመሔድ ቀደም ሲል የነበረውን ” ጎንጅ ወ እንዘግድም ብርጌድን” የአሁኑን “ንስር ብርጌድን” ከሌሎች ጓዶቹ ጋር በመመስረት አይተኬ የትግል አሻራ ያሳረፈ ጀግና ነበር።
ፋኖ ዮሐንስ አለማየሁ በሞጣ : በአዴት : በምላጭበር : በፈረስ ቤት በቋሪት ከትግል ጓዶቹ ጋር በመሆን ከባድ ውጊያ ያደረገ ልበ ቆራጥ አርዓያ ፋኖ ነበር።
የአማራ ፋኖ በጎጃም ከተመሰረተ ዕለት ጀምሮ በአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል የህዝብ ግንኘነት ሀላፊ በመሆን ሰለቸኝ ታከተኝ ሳይል ያገለገለ ሲሆን ከቅንነት የመነጨ ልበ ቆራጥነትን ያስመሰከረ እና ታታሪነትን እና ለህዝብ ዋጋ መክፈልን መርህ ያደረገ ጀግና የፋኖ አመራር ነበር።
የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ በነበረበት ጊዜ ያለፈውን ፈታኝ ጊዜ በመረዳት የመምራት እና ችግርን የመፍታት ትልቅ አቅሙ ታምኖበት የሁለተኛ ( ተፈራ) ክፍለጦር ሰብሳቢ በመሆን ትልቅ የመንፈስ መነቃቃትን የፈጠረ ታጋያችን ነበር።
ፋኖ ዮሐንስ አለማየሁ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ሌሊት ለጥር 13 አጥቢያ ጠላት ወደ ዋሸራ ከተማ ለመግባት በመገስገስ ላይ እያለ ባደረገው የፊት ለፊት ውጊያ አብሪ የጠላት ሐይሎችን በመደምሰስ የክብር መስዕዋትነትን ተቀብሏል ።
ፋኖ ዮሐንስ አለማየሁ ፅናትን : መታመንን : ቁርጠኝነትን እና መስዕዋትነትን ከታላላቅ ሰማዕታት ፋኖዎች በመውረስ ለቀሪው የአማራ ትውልድ ዕውነትን አስተምሮ ያለፈ ጀግና ነው።
ድርጅታችን የአማራ ፋኖ በጎጃም የፋኖ ዮሐንስ አለማየሁን ክብር የሚመጥን ዝግጅት እንደሚያደርግ እየገለፀ ለትግል ጓዶቹ እና ለቤተሰቦቹ መፅናናትን ይመኛል ።